Monday, January 3, 2011

ባለ ራእይዋ ደሴት

ከአቴና ወደ ፒራዎስ ወደብ በባቡር ነው ያመራነው፡፡ ወደ አርባ ደቂቃ ያህል ይወስዳል፡፡ መርከቡ ከላይ ተሳፋሪዎችን ከሥር ደግሞ የቤት እና የጭነት መኪኖችን እያስገባ ጠበቀን፡፡ ወቅቱ የፈረንጆቹ የበጋ ወቅት በመ ሆኑ ሁሉም አካባቢውን ለቅቆ ወደ መዝናኛ ቦታዎች የሚጓዝበት ነው፡፡ የመርከቡ መግቢያ በሰው ተጨንቋል፡፡
ለአሥራ አምስት ደቂቃዎች ያህል መሥመራችንን ይዘን ከተጓዝን በኋላ መርከቡ ውስጥ ገባን፡፡ ውስጡ የጊዮርጊስ እና የቡናን ጨዋታ የሚያስተና ግደውን የአዲስ አበባ ስታድዮም መስሏል፡፡ በግራም በቀኝም ከሰው ውጭ ሌላ ነገር አይታይም፡፡
እንደምንም ብለን መቀመጫ ካገኘን በኋላ ወደ መርከቡ ውጨኛው ክፍል ወጣን፡፡ ቀዘቀዝ ያለ ነፋስ ስላለው እጅግ ደስ ይላል፡፡ በጥንቱ የዓለም ታሪክ ግሪኮች፣ ሮማያን፣ ፋርሶች እና ባቢሎናውያን ሲራወጡበት የኖሩት የኤጅያን ባሕር ፊት ለፊታችን ተዘርግቷል፡፡ በውስጡ ከል የተበጠበጠ ይመ ስል መልኩ ጥቁር ነው፡፡ ውኃው በነፋሱ ሲነቃነቅ ነው ባሕሩ የውኃ መልክ የሚይዘው፡፡ «እስመ ነፋሳት ሕይወቶሙ ለማያት» ሲል ሊቁ የተናገውን ባሕሩ ራሱ ይተረጉምለታል፡፡
መርከቡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ተነቃነቀ፡፡ እንደ ተነገረን ወደ ፍጥሞ ደሴት ለመድረስ 163ቱን ማይልስ ለሰባት ሰዓት ያህል መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ መርከቡ ውኃውን ሲሰነጥቀው ባሕሩ የሳሙና አረፋ መልክ ይይዝ ጀመር፡፡ ግሪክ አያሌ ደሴቶችን ያቀፈች ሀገር በመሆኗ በኤጅያን ባሕር ላይ እዚህም እዚያም በመብት የደመቁ ደሴቶቿ የጨለማውን ግርማ ገሥሠውት ይታያሉ፡፡ መርከቦቿም በሠገነታቸው ላይ ችቦ የመሰለ መብራት አብርተው በባሕሩ ላይ ላይ ይተራ መሳሉ፡፡
አንድ አንድ ጊዜ 41 እስከ 44 ዲግሪ የሚደርሰውን የግሪክ ሙቀት ለመቋቋም ጉዞውን በሌሊት ማድረቸው ተገቢ ነው፡፡ ይሄ ሙቀት ሳይሆን አይቀርም የግሪኮችን የሥራ እና የዕረፈት ባሕል ከሌሎቹ የአውሮፓ ሀገሮች ባሕል የቀየረው፡፡ በግሪኮች ዘንድ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በኦፊሴል የታወቀ የዕንቅልፍ ሰዓት ነው፡፡ የትኛውም ቢሮ ሰው አያስተናገድም፡፡ በተላይ ደግሞ ማክሰኛ እና ኀሙስ ከሰዓት በኋላ ሥራ የለም ዕረፍት ነው፡፡ ዓርብ ደግሞ ከሰዓት በኋላ ሰው በከተማ አይገኝም፡፡ እኔን የገረመኝ መቼ ሠርተው እንደሚኖሩ ነው፡፡ ምናልባትም የአውሮፓውያንን በሙሉ ዕረፍት ግሪኮች ሳያርፉት አይቀሩም፡፡
ወደ መርከቡ የበረንዳ አጥር ተጠግተን አካባቢውን ስንቃኝ ግሪኮቹ ቀረብ ይሉና አንዳንድ መግለጫ ይሰጡ ል፡፡ ይሄ ሰውን ለመርዳት ያላቸውን ፍላጎት ወድጄላቸው ነበር፡፡ ችግሩ ግን አናውቅም ማለትን ስለማያውቁ አንዳንድ ጊዜ የማያ ውቁትን ሁሉ ይነግሯችኋል፡፡ በተለይም አንድ ቦታ ጠፍቷችሁ አራት ግሪኮችን ብትጠይቁ አንዱ ወደ ሰሜን፣ ሌላው ወደ ደቡብ ሌላው ደግሞ ወደ ምሥራቅ፣ የቀረውን ወደ ምዕራብ ነው የሚያሳዩዋችሁ፡፡ ይህንን ጠባይ ያወቁት ኢትዮ ጵያውያን አንዱን ግሪክ «ኦዶስ ማሞ» የት ነው ብለው ይጠይቁታል፡፡ «የማሞ መንገድ የት ነው» ማለት ነው፡፡ አናውቅም የማያውቀው ጀግና በዚህ እና በዚያ አድርጋችሁ ታገኙታላችሁ ብሎ መራቸው ይባላል፡፡
አሁን ሙሉ በሙሉ ጨልሞ አካባውን ጨለማ ወርሶታል፡፡ ቅዝቃዜውም እየጨመረ ነው፡፡ ሁላችንም ቀስ በቀስ እየገባን ተኛን፡፡
ከመሬት ለመነሣት የእጆቹ መደገፊያ የነበረ ከዐለት የተፈለፈለ መያዥያ በብረት ምልክት ተደርጎበት ይታያል፡፡
ፍጥሞ ደሴት መድረሳችን በመርከቡ ጡሩንባ ተበሰረ፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ሆኗል፡፡ እኛም ዕቃችንን ሸክፈን ወረ ድን፡፡ የደሴቲቱ ሰዎች በሩ ላይ ተሰብስበው ቆመው ለአልጋ ፈላጊዎች ማስታወቂያ ይናገራሉ፡፡ እነዚህኞቹ በወረቀት ጽፈው መቆማቸው ነው እንጂ አዲስ አበባ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ ተራ በምሽት የደረስኩ ነው የመሰለኝ፡፡ እንደ አጋ ጣሚ ሆኖ ከእኛው ጋር ወደ ፍጥሞ ለሥራ የሄደች አንዲት እኅት ከአሠሪዋ ጋር አገናኘችን፡፡ እርሷ እዚህ የመጣችው በጋውን ለአንድ ሆቴል በመሥራት ለማሳለፍ ነው፡፡
ለአሠሪዋ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው የሆነለት፡፡ ልጅቱን እና እኛን በአንድ ሌሊት አገኘ፡፡ ለአንድ ክፍል 35 ዩሮ እየከፈልን አልጋውን ተከራየን፡፡ እነሆ ሌሊቱ በጸጥታ አለፈ፡፡
ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ ተነሣን፡፡ ከዚያም መጀመርያ ስካላ ወደ ተባለው የደሴቲቱ ዋና የሰዎች መናኸርያ አመራን፡፡ እዚያ ጥቂት ቆየንና በታክሲ ከባሕር ጠለል በላይ 190 ሜትር ከፍ ወደሚለው የተራራው አናት ላይ ወጣን፡፡ ተራራው ላይ ስትወጡ ደሴቲቱን በሚገባ ታዩዋታላችሁ፡፡ ደሴቲቱ የተዘለዘለ ሥጋ ትመስላለች፡፡ በሽንጧ በኩል አል ፋችሁ ርዝመቷን ስትለኩት ወደ 15 ኪሎሜትር ይሆናል፡፡
ራእዩን እያየ ሲነግረው ደቀ መዝሙሩ አብሮኮሮስ ራእዩን የጻፈበት አትሮንስ የመሰለ ዐለት 
 ደሴቲቱ በጠቅላላው 34 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ሲኖራት በውስጧ 3000 ያህል ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ ደሴቲቱ በሠንሠለታማ ዐለታማ ተራሮች የተሞላች ናት፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረው የመርከቡ ወደብ ባለበት በስካላ አካባቢ ነው፡፡ የተራራውን ግርጌ ይዘው የተነጠፉት የመዝናኛ ቢቾቿ ናቸው ከሃይማኖታዊው ቱሪስት ቀጥሎ ፍጥሞ እንድ ትወደድ ያደረጓት፡፡
በጥንቱ የግሪክ የአማልክት አፈ ታሪክ መሠረት ዜውስ የተባለው የአማልክት ንጉሥ ፍጥሞን ፈጥሮ ለልጁ ለአርጤምስ ሰጣት፡፡ በአካባቢው የተገኘው የአርጤምስ ምስል ዛሬ በቅዱስ ዮሐንስ ገዳም የአርኬዎሎጂካል ሙዝየም ውስጥ ይገኛል፡፡
የታክሲ ትራንስፖርት በምድረ ግሪክ ከሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች በተሻለ ርካሽ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አውቶ ቡስ ይወደዳል፡፡ እኛም ወደ ተራራው ለወሰደን ታክሲ ለአራት ሰው አምስት ዩሮ ብቻ ነበር የከፈልነው፡፡ መጀመርያ የተጓዝነው ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ታሪካዊ ገዳም ነበር፡፡
በፍጥሞ ደሴት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ስም አንድ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ነበር፡፡ ከአምስተኛው መክዘ በኋላ ግን ደሴቲቱ ምን እንደሆነች ሳይታወቅ ነዋሪዎቿ ተተዋት ሄደዋል፡፡ በአፈ ታሪክ እንደሚ ባለው የባሕር ዘራፊዎች ነዋሪዎቹን በማስቸገራቸው የተነሣ ነው ሕዝቡ አካባቢውን ጥሎ የተሰደደው፡፡
1088 ዓም አባ ክሪስቶዶሉስ የተባሉ አባት ወደ አካባቢው መጥተው ዛሬ ድረስ የሚታየውን እና በተራራው አናት ዙርያውን በተመሸገ አጥር የተከበበውን ገዳም መሠረቱ፡፡ ገዳሙ አንድ ዓመታትን ያስቆጠረ ቤተ ክርስቲያን ፣ የመነ ኮሳት መኖርያ እና ሙዝየም አለው፡፡ እኔን ያስቀናኝ በሚገባ የተደራጀው ሙዝየም ነው፡፡
የአርኬዎሎጂ መረጃዎችን፣ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳትን እና የወግ ዕቃዎችን፣ የብራና መጻሕፍትን እና ልዩ ልዩ መዛግ ብትን፣ ሥዕሎችን እና መስቀሎችን፣ በድንጋይ ላይ ተሠርተው የነበሩ የዘመኑ የሥነ ጥበብ ውጤቶችን እና የሐውልት ፍርስራሾችን በሚገባ ሠድረውና በግሪክ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ መረጃዎችን ጽፈው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ ሙዝየሙን ለመጎብኘት ስድስት ዩሮ ያስከፍላሉ፡፡ አቀማመጡን እና የያዛቸውን መረጃዎች ለተመለከተ ክፍያው ያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይሆንም፡፡
ከዋሻው መግቢያ ከላይ ያለው ዐለት ለሦስት ተሰንጥቋል፡፡ በቦታው የሚገኙ መዛግብት እንደሚሉት ዮሐንስ ራእዩን የገለጠለትን ድምፅ ሲሰማ ዘወር ባለ ጊዜ የተሰነጠቀ ነው፡፡ ይህንንም ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር ያገናኙታል፡፡
 ምናለ እነ አኩስም እና ላሊበላ፣ እነ ጣና ገዳማት እና እነ ጎንደር ይህንን ባዩ፡፡ ያንን ሁሉ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርስ ይዘው፤ በአንዲት ጠባብ ዕቃ ቤት ከምረው፣ የብል እና የምስጥ መጫዎቻ ከሚያደርጉት እና ታሪክ ከሚ ያሳጡን፣ እንዲህ እንደ ፍጥሞአውያን ሠልጠን ያለ ሙዝየም ሠርተው ቢያሳዩን ምናለ፡፡ እነርሱም ከልመና ይወጡ ነበር፡፡ እያልኩ ተቆጨኹ፡፡
ነገሩ እዚህ ያሉ መነኮሳት የዋዛ አይደሉም፡፡ ሁሉም ቢያንስ አንድ ዲግሪ በአንድ ትምህርት የያዙ ናቸው፡፡ አሁን ገዳሙን የሚያስተዳድሩት አባት እንኳን የመነኮሱት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተው ለብዙ ዓመታት ከሠሩ በኋላ ነው፡፡ ከተሰሎንቄ ዩኒቨርሲቲ እኤአ 1998 ዓም በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን በየጊዜው በሚያሳትሟቸው የጥናት ወረቀቶች አማካኝነትም 2000 ዓም ኦራዲያ ከተሰኘ የሮማኒያ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል፡፡ እስካሁን ድረስም አምስት መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡
ስለ ደሴቲቱ እና ስለ ገዳሙ ታሪክ የሚገልጡ ፖስት ካርዶች፣ መጻሕፍት፣ ፊልሞች፣ ሥዕሎች እንደ ልባችሁ ታገኛ ላችሁ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ገዳም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ቪዲዮ ለማንሳት ክልክል ነው የሚል ማስታወቂያ እንጂ የተነሣ ቪዲዮ አታገኙም ነበር፡፡
በገዳሙ ካየኋቸው ነገሮች ሁሉ ልቤን የነካኝ 15ኛው መክዘ ቱርኮች ደሴቲቱን በያዙዋት ጊዜ የቱርኩ ገዥ ገዳሙ እንዳይነካ፣ ወደ ውስጥም መነኮሳቱ ከፈቀዱለት ሰው በቀር ማንም እንዳይገባ፣ ግብርም እንዳይጠየቅ፣ ቅድስናውም ተጠ ብቆ እንዲኖር በማለት ያወጀው አዋጅ ነው፡፡ ዐዋጁ በሚጠቀለል ብራና ተጽፎ እና ተፈርሞበት ግድግዳው ላይ ተሰቅ ሏል፡፡ የቱርኩ ገዥ ሃይማኖቱ ሙስሊም ነው፡፡ ነገር ግን የማላምንበት ነገር ሁሉ አያስፈልግም ሳይል ለደሴተ ፍጥሞ ገዳም ያደገረው ቸርነት እና ያወጀው ዐዋጅ 500 ዓመታትን ተሻግሮ ለዛሬ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
የቅዱስ ዮሐንስን ገዳም ጉብኝት አጠናቅቀን ወጣን፡፡ በገዳሙ በስተ ጀርባ በኩል ወደ ታች የሚወርድ አውቶቡስ አገ ኘንና ተሳፈርን፡፡ እናም በጉጉት ወደምንጠብቀው ቦታ አመራን፡፡ ስንደርስ 800 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ገዳም ነው ያገኘነው፡፡ ዙርያው በነጭ ግንብ ታጥሮ ግጥምጥም ያለ ነው፡፡ አርባ ሁለቱን ደረጃዎች አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አንድ ዋሻ አገኘን፡፡
እነሆ ደረስን፤ ቆምንም፤ ቅዱስ ዮሐንስ 95 ዓም ራእዩን የጻፈበት ዋሻ ውስጥ ገባን፡፡ የዋሻው ግድግዳ ጥቁር መልክ አለው፡፡ የዋሻው ቁመት ከመካከለኛ የሰው ቁመት ትንሽ ከፍ ያለ ነው፡፡ ገባ እንዳላችሁ ወደ ቀኝ ስትዞሩ ዮሐንስ ራእዩን ያየበትን ቦታ በብረት ፍርግርግ ታጥሮ ታገኙታላችሁ፡፡ ከአጠገቡ ራእዩን እያየ ሲነግረው ደቀ መዝሙሩ አብሮ ኮሮስ ራእዩን የጻፈበት አትሮንስ የመሰለ ዐለት ይገኛል፡፡
ዓይናችሁን ዘቅዘቅ ስታደርጉ ከጸሎት በኋላ ያርፍበት የነበረው ሥፍራ ዐለቱን ወደ ውስጥ በመሠርሰር የተሠራ የአንገት መደገፊያ፤ ከመሬት ለመነሣት የእጆቹ መደገፊያ የነበረ ከዐለት የተፈለፈለ መያዥያ በብረት ምልክት ተደርጎበት ይታያል፡፡
በዓለም ክርስቲያኖች እና ተመራማሪዎች ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ ያለው አስደናቂው የዮሐንስ ራእይ በድምጥያኖስ ዘመነ መንግሥት የተጻፈው እዚህ ነው፡፡ አቡቀለምሲስ ዮሐንስ ከኤፌሶን ከተማ ተይዞ በግዞት ወደዚህ ደሴት በመምጣት ለሁለት ዓመታት መቆየቱን የአካባቢው ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
አካባቢው ጸጥ ረጭ ያለ ነው፡፡ ድምፅ የሚባል ነገር አይሰማበትም፡፡ የመጡ ጎብኝዎች ሁሉ በጸጥታ ነው በቦታው የሚቆሙት፡፡ ወደ ኋላ 2000 ዘመናት ያህል ትነጉዱና አብራችሁ ራእይ ታያላችሁ፡፡ እኔም ምናለ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ራእይ ባየሁ ብዬ ተመኘሁ፡፡ የመጣ እና የሄደ ሁሉ እንዲህ ትሆናለች እያለ በሌለ ተስፋ ከሚሞላን ቁርጥ ያለውን የነገ ዕጣ ፈንታዋን ዐውቀን በጊዜ ብንገላገል ምናለ፡፡ ከዚህ ጥቁር ዐለት በነጭ ሰሌዳ ተጽፎ አንዳች ራእይ ቢታየኝ ምናለ፡፡
ከዋሻው መግቢያ ከላይ ያለው ዐለት ለሦስት ተሰንጥቋል፡፡ በቦታው የሚገኙ መዛግብት እንደሚሉት ዮሐንስ ራእዩን የገለጠለትን ድምፅ ሲሰማ ዘወር ባለ ጊዜ የተሰነጠቀ ነው፡፡ የሰነጠቀውም የሰማው ድምፅ ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር ያገናኙታል፡፡
በዚያ ቦታ ለሁለት ሰዓታት ያህል ቆየን፡፡ ከዚያም ታሪኩን እና ጸጥታውን ተሰናብተን ወጣን፡፡ ወደ አቴና ለመመለስ የምሽቱን መርከብ መጠበቅ አለብን፡፡ ምን ችግር አለው እንደ ሀገራችን የተጠበሰ በቆሎ ከመንገድ ላይ ገዝተን ወደቡ አጠገብ ቁጭ አልን፡፡ ደግነቱ እዚህ ሀገር ምች የሚባል ነገር የለም፡፡
ጉብኝቱ የተደረገው በሰኔ  2001 ዓም ነበር

ይህ ጽሑፍ በአዲስ ነገር ጋዜጣ ወጥቶ ነበር

12 comments:

 1. thanks for sharing us it is to much impressive trip,the things you wished to see a prophecy about Ethiopia really really it was a fabulous expression.may the prayer of st.John be with us forever!
  Antonio Mulatu from Mekelle

  ReplyDelete
 2. ደግነቱ እዚህ ሀገር ምች የሚባል ነገር የለም፡፡

  ReplyDelete
 3. Please correct the template. It doesn't show pictures. Any technical help?

  ReplyDelete
 4. ዳኒ

  "እኔም ምናለ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ራእይ ባየሁ ብዬ ተመኘሁ፡፡"
  አልክ?

  እንደ እንደኔ መጪውን አውቀን ተስፋ ከምንቆርጥ እንዲሁ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል እያልል፣ ለውጥ ይመጣል ብለን ተስፋ እያደረግን እና የተሻለ እንዲሆልንን እየጣርን ብንኖር ሳይበልጥ አይቀርም እላለሁ። እስቲ አስበው የዛሬ 2 ዓመት (ሰኔ 2001 ዓም) ላይ ሆነህ አሁን ያለችበትን ሀገርህ ላይ እንደምትሆን ብታውቅ ኖሮ መኖር የሚያጓጓህ ይመስልሃል?

  በእርግጥ በትንሹ አንድ ነገር እመኛለሁ። ይህ የአምስት ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ኢትዮጵያን ይለውጣት ይሆን ? ለሚለው የሁሉም ጥያቄ መልስ ቀድሞ ማወቅ። የሚሳካ ካልሆነ ከአሁኑ ተለዋጭ እቅድ (Plan B) እንዲዘጋጅ ነዋ!

  ምንም እንኳን ራእይ ተግልጦልኝ ብለህ አይደለም ሰፍረህ ቆጥረህ፣መርምረህ ተመራምረህ ማስረጃ ይዘህ ብትመጣም የሚሰማህ ባይኖርም።

  ReplyDelete
 5. Kale hiwot yasemalin Dn Daniel.
  St. John saw the revelation for the whole world...including Ethiopia ...what's ahead for us is already written down in the book. I was surprised when i read this because me and my sister from Minnesota were just discussing about St. John and his works. As soon as we finished talking I wanted to vist your site and i came across this writting. Egziabher yibarkih. Atlanta.

  ReplyDelete
 6. ዳኒ ጉብኝትህን ስላካፈልከን በጣም አመሰግናለው፡፡
  የግሪክ መነኮሳት ታሪክ ለመጠበቅ ያላቸውን ዕውቀት
  እንዲት መጠቀም እንደቻሉ የተገነዘብክ ይመስለኛል፡፡
  እኛ ይህንን ለማድረግ ያልቻልነው የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን
  የዕውቀት ችግር ስላለብን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምሁሮቻችን ዕውቀታቸውን
  ለስራ ከማዋል ይልቅ ለትችት እና ለተንኮል ማዋል ስለሚመርጡ ነው፡፡
  የሀገራችን ሰው የሚያስተባብረው እና የሚመራው ካገኝ ጉልበት እና ገንዘቡን ብቻ
  ሳይሆን ሕይወቱን እየከፈለ የኖረ ህዝብ ነው፡፡

  ReplyDelete
 7. Dani,

  I can't see the pictures.

  What shall I do?

  ReplyDelete
 8. ሰላም ደ ዳንኤል
  ስላካፈልከን የሚገርም እይታ እግዚአብሄር ይስጥልን ያንን ቅዱስ ቦታ ለመርገጥ በመቻልህ እድለኛ ነህ!
  እንደየት አይነት የአሰተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልገን የሚያሳይ ነው የሚመለከተው አካል ለቱሪዝም መስኮቻችን ተገቢውን ትኩረት ቢሰጥ መልካም ነው እያንዳንዳችንም የድርሻችንን እንቆንጥር
  በርታ እግዚአብሄር በፀጋው ይጠብቅህ መልካም የልደት በአል ይሁንልህ

  ReplyDelete
 9. የቅዱስ ዮሐንስ በረከትናረድኤት አይለየንና የዮሐንስ ራእይ ሳነብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ነች ትዝ የምትለኝ ለምን ቢባል ዮሐንስ በራእይው ያየው ሥርዓት ሁሉ እኛ ቤተክርስትያን በተግባር ይታያልና ነው። በየጊዜው የሚነሱ አገልጋዮች ሥርዓቱን እየሸራረፉ እያጠፉብን ነው እንጂ አሁንም ሰማያዊው ሥርዓት ከኛ ዘንድ አለ። ዳኒ ቸር ያሰማህ

  ReplyDelete
 10. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዲ/ን ዳንኤል።በጣም ደስ የሚል ነገር ነው በእውነቱ። ያንን ሁሉ ጉዞ አድርገህ በዓይንህ ያየኸው፣በእጅህ የዳሰስከውና የተሳለምከው የታላቁ አባት ቅዱስ ቦታ ታላቅ በረከት አለውና እግዚአብሔር አምላክ የበረከቱ ተካፋዮች ያድርገን።አሜን።

  ReplyDelete
 11. Ever since i learned about St. John Weldenegodguad i was always amaized on how strong he was in his belief. He was the only deciple that followed the Lord to the cross. He was given our holy Mother Emebetachinin. I always wondered how he was feeling when he was in Fitimo Deset. Talak Abat New, Ye Kiristina Mechreshaw eseke Meskel Dires Metsinat endehone Yastemare abat. Egziabher ke Bereketu yasatifen Amen. And Thank you D/N Daniel mechem ande ken i will hope to go visit Fitimo and be at that place God bless.

  ReplyDelete
 12. "Geta eko new" Kidus Yohanes ketenagerew.

  Yihin yaderege Egziabher new antem hedeh ayteh legna beayne hilinachn Fitimo deset Kidus Yohanes gar dersen yemetanew.

  Estub new!

  ReplyDelete