ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ማኅበር ጽ/ቤት የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ እንዲህ ልንገራችሁ፡፡
በዚህ ማኅበር ጽ/ቤት ውስጥ በጽዳት ሠራተኛነት የምትሠራ እኔ ለጊዜው ስሟን ራሔል ብዬ የምጠራት ልጅ አለች፡፡ ሲፈጥራት አይጥ የሚባል ነገር ትጠላለች አሉ፡፡ ምን እርሷ ብቻ ብዙዎቻችን ስለ አይጥ እየተነገረን ካደግነው ተረት እና ምሳሌ አንፃር ነው መሰል አይጥን ማየት እና መንካት ቀርቶ ማሰብም ይከብደናል፡፡
መቼም እንጀራ የማይጥለው ነገር የለም፡፡ የወደዱትን አስትቶ የጠሉትን ያስይዛል፤ በሚያናድደው አስቆ፣ በሚያስቀው ያስለቅሳል፡፡ ደግሞ በኛ ሀገር የሰዎችን ሥነ ልቡናዊ የኋላ ጫና እና አመለካከት ተረድቶ ከሥራቸው ጋር ማጣጣም የሚባል ነገር እምብዛም አልተለመደም፡፡ በአንዳንድ የሠለጠኑ ሀገሮች እንዲህ ለማድረግ ባህሌ አይፈቅድም፣ ሃይማኖቴ ይከለክላል፣ ለዚህ እና ለዚያ አለርጂ ነኝ፣ እንዲህ እና እንዲያ ያለ ነገር ያስደነግጠኛል ብሎ አስቀድሞ መናገር ወይንም በኋላ ማስረዳት ይቻላል፡፡
ባይሆን ችግሩ ሥነ ልቡናዊ ችግር ነው ብለው ካመኑ የሚቀርፉበትን መንገድ አለቆች ይፈጥራሉ፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ ለሠራተኛው የሥራ ደኅንነት በሚያመች መንገድ ያሠማሩታል፡፡
ራሔል ያለችው እዚህ ሀገር ነውና ይህ አልገጠማትም፡፡