Thursday, December 16, 2010

ምሽግ ቆፋሪዎች


እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት ከጦርነት ጋር ኖረናል፡፡ ሀገራችንን ከባዕዳን ጠብቀን ሀገረ አግዓዝያን ለማድረግ የመጡብንን ከመከላከል የተሻለ አማራጭ አልነበረንም፡፡
ሽፍቶች ከሽፍቶች፣ ዐማፅያን ከመንግሥት፣ መንግሥት ከዐማፅያን ስንዋጋ ኖረናል፡፡ እኛም በኩራት «ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን ጦርነትን መሥራትም እንችልበታለን» እያልን እስከ መናገር ደርሰናል፡፡
ታሪካችን ሲመዘዝ ማጉ ነፃነት ቢሆንም ድሩ ግን ጦርነት ሆኖ ይገኛል፡፡ የምንዋጋው ጠላት ባይኖረን እንኳን በሰላም ወደሚኖሩት አራዊት መንደር ብቅ ብለን ዝሆን እና አንበሳ፣ አጋዝን እና ነብር ገድለን በመምጣት እንፎክራለን፡፡ የባሰ ሰላም ካጋጠመን ደግሞ ጦር አውርድ ብለን እንጸልያለን እያሉ አንዳንድ የቀድሞ ድርሳናት ያወጉናል፡፡
ታድያ ይህ በጦርነት አድገን በጦርነት መኖራችን በአንድ በኩል ጀግና እና አልደፈር ባይ፣ ዘመናዊ ጦር ታጥቀው የመጡትን በባህላዊ ቆራጥነት እና በሀገር ፍቅር ወኔ የሚገዳደር እና የሚያሸንፍ ሕዝብ ሲያፈ ራልን፣ በአንድ በኩል ደግሞ የራ ጠባሳ ጥሎልናል፡፡ መቼም አንከን የሌለው መድኃኒት አይፈጠርም፡፡
ኢትዮጵያን የነፃነት ሀገር ያደረጋት ከሕዝቦቿ ቆራጥነት በተጨማሪ የመልክዐ ምድሯ ቆራጥነትም ጭምር ነው፡፡ እዚያው ተወልዶ እንደ ዝንጀሮ ገደል ለገደል ሲወጣ ሲወርድ ላላደገ ሰው ምድሪቱ አስቸጋሪ ናት፡፡ ሐበሻ ምድርን መምረጥ፣ ምሽግ መቆፈር እና መከላከል፣ ከዚያም ማጥቃት ያውቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ ሕይወታችንን የምሽግ ሕይወት አድርጎታል፡፡
ቀደምት ከተሞቻችን ለምሽግ እንዲያመች ዙርያውን በተራራ በተከበበ ቦታ ወይንም ደግሞ ራሳቸው በተራራ ላይ የተገነቡ ናቸው፡፡ ቤተ መንግሥቶቻችን ለምሽግ በሚያመች መንገድ የተሠሩ ናቸው፡፡ ይህ ባህላችን እስከ ቅርቡ የጦርነት ታሪካችን ዘልቆ ኢሕአዴግ ሲገባም በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ምሽጎች ተሠርተው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የድንጋይ ምሽጎችም በቅርስነት ዛሬም 19 ዓመታት በኋላ ይታያሉ፡፡
ከቤቱ ይልቅ ለግቢው ጥንካሬ የምንጨነቀው ይኼው የምሽግ ባህል ይዞን መሆን አለበት፡፡ ጠንከር እና ከፍ ያለ ማንንም የማያሳይ ግቢ የትልቅ ሰው ግቢ ይባላል፡፡ ከምድር ወደ ፎቅ ስንወጣም ይኼው ተከተለንና በየኮንደሚኒየሙ ምሽጎችን እናያለን፡፡ በተለይም የሕንፃውን ጥግ ማግኘት የቻሉ ወገኖቻችን በተቻላቸው መጠን በረንዳውን አጥረው አንበሳ ግቢ ያስመስሉታል፡፡ ዕረፍት የሚሰማቸው እና ርካታ የሚያገኙት ምሽግ ሲኖራቸው ነውና፡፡
በየአዳሪ ትምህርት ቤቱ ብትገቡ እልፍ አእላፋት ምሽጎችን ታያላችሁ፡፡ በአንድ ክፍል አሥር እና አሥራ አምስት ሆነው የሚኖሩ ተማሪዎች የሚመሽጉት ቢያጡ አልጋቸውን ይመሽጋሉ፡፡ ዙርያዋን በአንሶላ ወይንም በጋቢ ያጥሯታል፡፡ እንደ ቀበሮ በር የጠበበች መግቢያም ያበጁላታል፡፡ ያን ጊዜ መንፈሳቸው ደኅንነት ይሰማዋል፡፡ ነፍሳቸውም ዕረፍትን ታገኛለች፡፡
ሂዱ ደግሞ በየቢሮው፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ የየራሱን በግንብ የታጠረ ቢሮ ካላገኘ እንደተበደለ አድርጎ ነው የሚቆጥረው፡፡ ቆልፎ የሚቀመጥበት፣ ቢቻል የብረት በር ያለው ቢሮ ማግኘት መታደል ነው፡፡
እዚህ አዲስ አበባ በአንድ አዲስ ሕንፃ ውስጥ መሐንዲሶቹ እስከ ወገቡ ኮምፔልሳቶ ከወገቡ በላይ ደግሞ መስተዋት የሆነ ቢሮ እንዲሠራ ያደርጋሉ፡፡ በየቢሮው የተመደቡት ሠራተኞች ቢሮውን መረከብ በጀመሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ መስተዋቶቹ ሁሉ በሰፋፊ ጋዜጦች ተሸፈኑና የካራማራን ምሽግ መስለው ቁጭ አሉ፡፡ ጭራሽ ይባስ ብለው ኃላፊዎቹ ቢሮውን ሲረከቡ ደግሞ «አንዲህ ያለው አሠራር ለደኅንነታችን አያመቸም» አሉና መስተዋቱን አስነቅለው በኮምፔልሳቶ ጠረቀሙትና መሽገው ቁጭ አሉ፡፡
ለደንበኞች ቅርብ የሆኑ ሠራተኞች በቀላሉ ከደንበኞቻቸው ጋር እየተያዩ እንዲሠሩ ተብሎ በየመሥሪያ ቤቱ የመስተዋት ቢሮዎች እየተገነቡ መጥተዋል፡፡ በሠራተኞቹ ኅሊና ውስጥ ያለው የምሽግ ቆፋሪነት ባህል ስላልለቀቀን ግን በተቻለ መጠን በካርቶን፣ በጋዜጣ፣ በመጋረጃ እና ሠልጠን ያሉት ደግሞ በትልልቅ ሥዕሎች መስተዋቱ እንዲሸፈን ይደረጋል፡፡ ምናልባትም ከሁለት ዓመት በኋላ ብንሄድ መስተዋቶቹ ተሰባብረው በላሜራ እና በኮምፔልሳቶ ተተክተው መስተዋቱ «ነበር» ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ስብሰባ ወይንም ጉባኤ ተጠርቶ ሰው ወደ አዳራሽ ሲገባ እስኪ ተመልከቱ፡፡ ሁሉም ጥግ ጥጉን እየፈለገ መቀመጥ ይጀምራል፡፡ ወደ መሐል እና ወደ ፊት ተሰብሳቢዎቹን ለማምጣት ፕሮግራም የሚመሩት አካላት መለመን ወይንም ማስነሣት አለባቸው፡፡ ምን ስብሰባ ላይ ብቻ፡፡ ሻሂ ቤት እና ምግብ ቤት ብትገቡ ብዙ ጊዜ በመካከል ላይ ያሉ ወንበር እና ጠረጲዛዎች ባዶዎች ናቸው፡፡ እንግዶቹ ሁሉ ወደ ግድግዳው ጥግ እየሄዱ ምሽግ ምሽግ ይዘው ታገኟቸዋላችሁ፡፡ 
­ጥግ፣ ማዕዘን፣ ሥርቻ፣ ሠወር ያለ ቦታ፣ ከለላ፣ መያዝ የብልህነት ማሳያ ተደርጎም ይታያል፡፡ ምንም ያህል ሰፊ ቦታ በመካከል ቢኖርም አልጋችን ግን ጥግ መያዝ አለበት፡፡ ሶፋው ወንበር ጥግ ከተቻለም የግድግዳው መዓዝን ላይ መቀመጥ አለበት፡፡ ስንበላ ጥግ ይዘን፣ ስንሸና ጥግ ይዘን፣ ስናማ ጥግ ይዘን፣ ስንተኛ ጥግ ይዘን፣ ስንተኩስ ጥግ ይዘን፡፡ ምሽግ ቆፋሪዎች፡፡
በየክርክሩ፣ በየስብሰባው፣ በየውይይቱ፣ እያንዳንዳችን በየምሽጋችን ሆነን መተኮስ እና መከላከል እንጂ ወደ መካከለኛ ቦታ መምጣት የማንፈልገው በዚሁ ልማዳችን ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሁሉም ጥጉን ይዞ፣ ጥጉን አስከብሮ ለመቀጠል እንጂ ሁሉን ሊያግባባ ወደሚችል መካከለኛ ሃሳብ ለመምጣት ፈቃደኛነት የማናሳየው በዚህ የምሽግ ቆፋሪነት ባህል ውስጥ ሆነን ስለምንነጋገር ይመስለኛል፡፡
ነጥብ ማስቆጠር፣ በዝረራ መጣል፣ አንገት ማስደፋት፣ ልክ ልኩን መንገር፣ ውሻ በጨው እንዳይልሰው አድርጎ ማዋረድ፣ አንገቱን መሰባበር፣ ማቅመስ እና ጥንብ እርኩስ ማውጣት የሚሉት አገላለጦቻችን ከመሐል ሜዳ የሚመነጩ ሳይሆኑ ከምሽግ ውስጥ የሚወጡ ናቸው፡፡
ድንበራውያን እንስሳት /territorial animals/ የሚባሉ አሉ፡፡ እንደ አንበሳ፣ ነብር፣ ተኩላ ያሉ ናቸው፡፡ የእነርሱን የመኖርያ ክልል በጠረናቸው ያጥሩታል፡፡ ሌላ እንስሳ ያችን የጠረን ድንበር ተሻግሮ ሊገባ አይችልም፡፡ እርሱም ጠረኑን አሽትቶ ይሸሻል፤ ከገባም እርም እንዲል አድርገው ዋጋውን ይሰጡታል፡፡
እኛ ከእነርሱ እንቅሰመው ወይንም እነርሱ ከኛ ይቅሰሙት አላወቅም እንጂ ይህ ድንበርተኛነት እኛም ይታያል፡፡ በራስ ባህል፣ ልማድ፣ ቋንቋ፣ ጎጥ፣ ጎሳ፣ አስተሳሰብ፣ እምነት እና አሠራር ብቻ ታጥሮ መኖር፡፡ ሌላ ቦታስ ምን ሊኖር ይችላል? ብሎ አለመገመት፡፡ ከጎሳ ውጭ ማግባት ዛሬም ለብዙዎች ይከብዳል፡፡ 88 በላይ ቋንቋ በሚነገርባት ሀገር ብዙዎቻቸን ከራሳችን ቋንቋ ውጭ አልተማርንም፣ እንድንማርም አልተደረገም፡፡
በምሁሮቻችን ዘንድ እንኳን አንዱ ምሁር ስፔሻላይዝ አድርጎ ታዋቂ በሆነበት የዕወቀት መስክ ሌላው እንዳይከተለው ወይንም እንዳይቀላቀለው አጥሮ ነው የሚቀመጠው፡፡ እርሱ ብቻ ሊቅ፣ እርሱ ብቻ ተጠያቂ፣ እርሱ ብቻ ዐዋቂ መሆንን እንደ ልዩ ክብር ያየዋል፡፡ እርሱም ከምሽግ አይወጣ፣ ሌላም ወደ ምሽግ አያስገባ፡፡ እርሱ በሄደበት ሌላው እንዳይሄድ ዱካውን አጥፍቶ፣ መንገዱን ዘግቶ፣ ድልድዩን አፍርሶ፣ መረጃውን ደባብቆ ቁጭ ይላል፡፡
አብዛኞቹ ነጋድያኑም ቢሆኑ በዚያው በምሽግ ቆፋሪነት ባህል ውስጥ ነው ያሉት፡፡ አንድ ዕቃ ያመጣል፡፡ ያመጣበትን አይናገርም፡፡ ብቸኛ ወኪል አድርጉኝ ይላል፤ የሌሎች ዕቃ ከጉምሩክ እንዳይወጣ ጉቦ ሰጥቶም ቢሆን እንዲዘገይ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አንድ ምሽግ ውስጥ ቁጭ ብሎ ይቸበችባል፡፡
ይህ ልማድ ወደ ታች ወርዶ ወርዶ በየሠፈሩ ዕቃ ከሚያወርዱ እና ከሚጭኑ ወጣቶች ዘንድ በመድረሱ በእነርሱ ሠፈር እነርሱን አልፎ ማንም እንዳያወርድ እና አንዳይጭን የተወካዮች ምክር ቤት ያላወቀው ሕግ ደንግገዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መከራከር፣ መነጋገር፣ እምቢ ማለትም አይቻልም፡፡ በእነርሱ ሃሳብ እና ዋጋ መስማማት ግዴታ ነው፡፡ አካባቢ በእነርሱ የሥልጣን ጠረን የታጠረ ክልላቸው ነው፡፡
በእምነት ተቋማትም ዘንድ ይህ የምሽግ ቆፋሪነት ባህል አለ፡፡ በየምሽጉ ሆኖ መታኮስ እንጂ ችግሮ ተወያይቶ እና ተመካክሮ ለመፍታት ወደ መካከል የሚመጣ የለም፡፡ አሸናፊ እና ተሸናፊን ለመለየት እንጂ በየአመንንበት መንገድ እየሄድን ሌላውን ሳንነካ እና ሳንጋጭ እንዴት መኖር እንደሚቻል ለመነጋገር ወደ ሜዳ የሚመጣ የለም፡፡ ሁሉም በየምሽጉ ነው፡፡ ግዳይ መጣጣል፣ የጠላትን ምሽግ መሰባበር፣ መማረክ እና ድል ማድረግ ብቻ ነው የሚታየን፡፡
ዲያስጶራውም እንዲሁ በየምሽጉ ነው የሚኖረው፡፡ ጎንደሬው፣ ጎጃሜው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ ሸዋው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ሶማልያው በየክልሉ መሽጎ ድንበር ይጠብቃል፡፡ ምሽግ ያጠናክራል፡፡ በየሬዲዮ ጣቢያው፣ በየድረ ገጹ፣ በየጋዜጣው፣ በየሰላማዊ ሰልፉ፣ በየስብሰባው ይህንኑ የምሽግ ቁፋሮውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አይገናኝም ይታኮሳል፤ አይከራከርም፣ ያነጣጥራል፣ አይወያይም፣ ይከላከላል፡፡ ከእርሱ ድንበር ውጭ ያለው የዓለም መጨረሻ ነው፡፡
አሁን ወደ መሐል የሚመጣ እና የሚያመጣ ያስፈልጋል፡፡ በየምሽጋችን ተቀምጠን ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ልናኖራት አንችልም፡፡ ምሽግ ለጦርነት እንጂ ለሰላማዊ የዕድገት ጉዞ አይፈይድም፡፡ ገና ከጦርነት አስተሳሰብ የወጣን አንመስልምኮ፡፡ አሁንም በማጥቃት እና መከላከል መርሕ በመጓዝ ላይ ነንኮ፡፡  
እባካችሁ ከየምሽጋችን እንውጣ፡፡
ወደ መሐልም እንምጣ፡፡

ይህ ጽሑፍ በሮዝ መጽሔት ላይ የወጣ ነዉ

38 comments:

 1. ድንቅ ምልከታ እንደተለመደው!እስቲ ወደ መሃል ገባ ብለን እንሞክረው ይሄ መመሽግ አላዋጣንም ጎበዝ ፈረንጆቹ "it is better late than never" አይደል የሚሉት ቢዘገይም እንጀምረዉ

  ReplyDelete
 2. ወልደ ዮሐንስDecember 16, 2010 at 3:47 PM

  ግሩም ጡመራ ነች! ዓይን ገላጭ፡፡

  ReplyDelete
 3. በየምሽጋችን ተቀምጠን ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ልናኖራት አንችልም ፡፡
  በየምሽጋችን አድፍጠን ስንተኩስ
  ጥጋችንን ይዘን ወገን ስናስለቅስ
  እንደተሸሸግን ምሽግ ውስጥ በማድፈጥ
  እየተጫረስን ዘር ቀለም በመምረጥ
  የምንኖረው ኑሮ ስለማያዋጣ
  እባክህ ወገኔ ወደ መሐል እንምጣ
  kassahun from Addis Ababa

  ReplyDelete
 4. dani it is so nice post

  ReplyDelete
 5. ቃለ ህይወት ያሰማህ ዲ/ን ዳንኤል ፀጋውን ያብዛልህ በርታ!!!

  ReplyDelete
 6. Dn. Daniel Kale hiwot yasemalin.
  Don't you think for all these problems to be solved we all need to adopt saying Al Musamah to each other day and night? I think that's a good starter. Egziabher yistilign. Atlanta.

  ReplyDelete
 7. Girume eyeta!!
  But how it is possible? would you tell us some of the ways?

  thanks

  ReplyDelete
 8. Enewta gen meshegachenen wediyaw anedefenew behidet enji. Mene alebate yetekemen yehonal!
  Esti bezih zuriya mene telalachehu?

  ReplyDelete
 9. Ha ha ha ha..... Wey Dn. Daniel? Enem tig layi kuchi biye sanebewu lebichaye eyesakihu nebere. Yihewu zare keMishig wetiche asteyayet setehuh.... gin adera Tegachinin ena "kowasuwan atinkabin"...

  ReplyDelete
 10. it is amazing view.
  dani i wont to say tank you !!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 11. Dear Dn. Daniel,

  What a tasty and insightful idea!

  From The Netherlands

  ReplyDelete
 12. Great insight Dn. Daniel. እውነት ነው። እንዴት ጥሩ አድርገህ ተመልክተኸዋል! የኦርትዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ብጥብጥ ያደረጋት ይህ አይነቱ አእምሮ ዝግነት ሳይሆን አይቀርም። አንዱ መምህር ብዙ ጊዜ ከሚሰማው ትንሽ ዘወር ያለ ነገር ከተናገረ በተለያኩ ምሽጎች ውስጥ ያሉ ቡድኖች ተኩስ ይጀምራሉ። ከተናጋሪው ጋር ቁጭ ብሎ ከመወያየትና ነገሮችን በተሻለ የአእምሮ ክፍትነት እና ክርስቲያናዊ ፍቅር በተሞላበት መልኩ መፍታት ሲቻል። አሁንም ሁሉም መሽጎ ስለሚዋጋ በ 5 ደቂቃ ውይይት የሚፈታውን ነገር ለአመታት ስንጋዋ እንኖራለን። ግን ይገርምሃል ይሄ ችግር የኢትዮጵያውያን ብቻ ችግር አይደለም። ሌላውም በዚህ ጉዳይ ይቸገራል።

  ReplyDelete
 13. That Right D.Daniel.

  ReplyDelete
 14. እውነት ነው ዳኒ ሁላችንም ከዚህ ካልተገባ ባእሪያችን መላቀቅ ይኖርብናል::
  እራሳችንን እንድናይበት ይረዳናል:: በጣም ነው የምናመሰግነው ዳኒ ከዚህ በላይ የምሰራበትን እድሜ ይስጥልን::

  ReplyDelete
 15. Thanks Dn. Daniel
  This is a great view !,keep it up.
  እባካችሁ ከየምሽጋችን እንውጣ
  ወደ መሐልም እንምጣ፡፡
  I will try...

  ReplyDelete
 16. የሚገርም ምልከታ እንደተለመደው!እስቲ ወደ መሃል ገባ ብለን እንሞክረው ይሄ መመሽግ አላዋጣንም!

  ReplyDelete
 17. wow dani,it is nice view and possible,but not esey.and it needs some secrification.so, all we are ready we can.mesheg sebarineteme yegna tarike new eko.

  ReplyDelete
 18. ባለ ታሪኮች ነን ጀግና ወታደር
  ጠላት አባራሪ ምሽግ በመስበር
  በአየር በመምጣት ወደማሐል ገብቶ
  በጨበጣ ውጊያ ጠላትን ድል ነስቶ
  መኖር ይችላል ምሽግን አጥፍቶ

  ReplyDelete
 19. Thanks dani.GOD BE WITH U

  ReplyDelete
 20. እንደእኔ አመለካከት ይህን የምሽግ ፍቅር የወለደው ከአጥሩ ውስጥ ያለው የራሳችን ገመና፣ የራሳችን ሰብእና ስለሚያስፈራን ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ካየኋቸው ታላላቅ ቦታዎችን ከሚይዙት ባህላዊ ዕሴቶች መካከል “ገመና” የምንለው ነገር ከባዱ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ደግሞ ገመና የምንለው ነገር እንዲህ ትልቅ ቦታ የተሰጠው በጎ ነገር በመሆኑ ሳይሆን ለአደጋ የሚያጋልጠን (የእያንዳንዳችን Achilles’ heel) ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ምክንያም “ገመና” ማለት ሰዎች የማያውቁት፣ እውነተኛው “እኔ” ነው፡፡ እውነተኛው እኔ ደግሞ እንደማንኛውም ሰው ድክመቶች ይኖሩታል፡፡ ማሳየት የማንፈልገውም ለዚህ ነው፡፡ በቃ! “እዚህ ቦታ ላይ ደካማ ጎን አለው/ አላት፡፡” መባልን አንፈልግም፡፡ ራሳችን ፍጹም እንዳልሆነ ብናውቅም ሰዎች ፍጹም አድርገው እንዲቆጥሩን እንሻለን፡፡ ፍጹም አድርገው እንደማይቆጥሩን ብንረዳም እንኳ ደካማ ጎናችን በምንም ተአምር እንዲታወቅብን አንሻም፡፡ ለምን? ለጥቃት መጋለጥ አንሻማ!

  እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ምጮቹ ምናልባት ሁለት ነገሮች ሳይሆኑ አይቀሩም፡-
  ሀ. ለእኔ ከእኔ በቀር እውነተኛ ወዳጅ የለውም፡፡ ብሎ ማመን
  ለ. “ከእኔ” ውጪ ካለው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት በእውነት ላይ ሊመሠረት አይችልም፡፡ ብሎ ማመን
  እንዲህ የሚያምን ሰው ሁልጊዜም “ዛሬ ወዳጄ ያልሁት ውስጡ ጠላቴ ሊሆን ይችላል፡፡ በድንገት ጥቃት ሊሰነዝርብኝና ሊያጠፋኝ ይችላል ብሎ ስለሚያስብ ሁል ጊዜም ሊያስጠቃኝ ይችላል ብሎ የሚያስበውን ጎኑን ላለማሳየት ሲል ራሱን የሚደብቅበት ምሽግ ይቆፍራል፡፡

  አንድ “The Moment of Truth” የሚባል አሜሪካዊ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር አለ፡፡ በዚህ ሾው የሰዎች ሰብእናዊ አጥር ይፈርሳል፡፡ አጥሩ ሲፈርስ የሚገለጠው “እውነተኛው እኔ” ደግሞ አንዳንዴ ሞቶ፣ አንዳንዴ በስብሶ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሰይጥኖ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሣ ቤተሰብ ይፈርሳል፤ ትዳር ይበተናል፤ ፍቅር ይበጠበጣል፡፡ ሁል ጊዜ ይህንን ሾው ስከታተል ከፊቴ የሚመጣብኝ የኛ አጥራዊ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የእያንዳንዳችን ምሽግ ቢፈርስ ውስጣችን ያለው እውነተኛው እኔ ምን ይመስል ይሆን? እንወዳችኋለን የምንላቸውን ሰዎች እውነት እንወድ ይሆን? ፈጽሞ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ምሽጉን ለማፍረስ የፈለገ መጀመሪያ የፍቅርን ውኃ ይጠጣ፡፡ ሰዎችን ሳንቀብር ማመን የምንችለው ያንጊዜ ብቻ ነውና፡፡

  ReplyDelete
 21. Just for fun

  Hulunem alesemamam! Ahune ewenet meshige meneyahile enedetekem atachehute new OR Dani selale medegefachehu? Gine eko tikemune yemetawkute setewtu new ezaw tehonoma meche? BEKA ESHI WUTUNA MOKERUTE

  oh bichayene........

  ReplyDelete
 22. Dn. Daniel let Almighty God bless U with his love! 'Hullum kemishigu yiwuta yemilewun endet tayewaleh? lne mishige Kirstos newna!'

  ReplyDelete
 23. ዲ. ዳኒ በእውነቱ ግሩም ዕይታ ነው፡፡ በዓምድህ ላይ ሌላ ሰው እንዳመሰግን ከፈቀድክልኝ ግን መሐሪ ገ/ማርቆስን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ አንተ ችግራችንን ገለፅክልን እሱ ደግሞ መነሻ ይሆናሉ ያላቸውን ምክንያቶች ለመግለጽ ሞከረ ከጥሩ ማበራሪያ ጋር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ችግሮችን ብቻ ማወቅ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብዬ አላስብም እነደዚህ ወንድማችን ለመግለፅ እነደሞከረው የችግሩን መነሻ በትክክል ለማየት እስካልሞከርን ድረስ፡፡ እኔ ግን ይሄ ጽሁፍ የፈጠረብኝ አንድ ጥያቄ አለ ይኸውም ምሽግ መስራት የእኛ የኢትዮጵያውያን ባሕሪ ብቻ ነው ወይንስ የሰው ልጅ ሁሉ ምክንያቱም እዚህ ባለሁበት አሜሪካ እነደኛው አገር በጋዜጣና በኮምፐርሳቶ ምሽግ አይስሩ እንጂ privacy በሚለው የተለመደ ቃላቸው ሰውን አጠገባቸው ያለማስደረስ ባሕል አላቸው፡፡ እናም የነሱ privacy እና የኛ ምሽግ አንድነቱ እና ልዩነቱ አልገባ አለኝ፡፡ እሰቲ በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ግንዛቤው ያላችሁ ጀባ በሉን፡፡መቼም ዳኒ ይህቺ የኔ ምሽግ ናት ሌላ አላስገባም እነደማይል አምናለሁ፡፡
  አዜብ ዘሚኒሶታ

  ReplyDelete
 24. ዲያቆን ዳንኤል ቃለሕይወት ያሰማልን። በእውነቱ የልቤን ስለነካህልኝ (የራሴም ችግር ስለሆነ) ደስ ብሎኛል። በጣም ትልቅ ሃሳብ ነው ያነሳኸው።ለኋላቀርነታችን አንዱና ዋናው ምክንያት ይህ ይመስለኛል። በድጋሚ ቃለሕይወት ያሰማልን በጸጋ ይጠብቅልን።

  ReplyDelete
 25. Selam Dn Daniel

  Thank for your best article. Just I want to read at least in a week our church teaching... You looks you focused on social aspect. But you we know you as the Gospel farmer, so please do that one... thank You

  ReplyDelete
 26. አሜን ወአሜን!December 18, 2010 at 9:18 PM

  ወንድሜ ዳንኤል፤ ጌታ ይባርክህ!
  ታላቅ መረዳት ነው። እኔና መሰሎቼ ከኦርቶዶክስ እምነት ወጥተን የቀረነው ያሉብንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች በመመለስ ፋንታ በጅምላው " መናፍቅ" እያሉ ስለፈረጁን ነው። ጥያቄ ያለበትን ሁሉ፤ አፈታሪኩንና ተረቱን ያልተቀበለውን ሁሉ፤ በጅምላ ክሃዲ፤ ቅጥረኛ ፤...ማለት ምንም ፋይዳ የለውም። እንዳንተ ድልድይ ሰርተው በመነጋገርና በመማማር ፋንታ መኮነንና መወንጀል ምንም እንደማያዋጣ በየቀኑ የሚኮበልለውን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ማየት ብቻ ይበቃል።
  እግዚአብሔር በውስጥህ ስላስቀመጠው የከበረ ስጦታ አመሰግነዋለሁ።
  " ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።" 2ቆሮ 9;15
  አሜን ወአሜን!

  ReplyDelete
 27. ዲ.ን ዳንኤል(አያልቅበት) ገሃድ እውነታ:ግሩም አገላለጽ:: አንዳንዶቻችን ይህንን አንብበንም ከምሽጋችን መውጣት አለመቻላችንን በምንሰጣቸው አስተያየቶች ይፋ በማድረግ ላይ ነንን:: ምሽግ ሠሪነት የሰውልጅ ባህርይ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ቢሆንም እንደኛ እንደኢትዮጵያውያን የጸናበት ግን የለም:: በተለይም ነጮቹ በአብዛኛው በሚያስማማ ጉዳይ ላይ አንድነት ለመፍጠር ልዩነትን እንደቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ ባህል የላቸውም:: የእኛ ጉድማ ምኑ ተዘርዝሮ ያልቃል::
  ኢትዮጵያውያን-የሃገር ፍቅር ከእኛ በላይ ባዮች - ይልቅ አባባላችን ከልብ ከሆነ ነገ ከቀብሯ በኋላ የአዞ እንባ ከማንባት - ዛሬ እንድረስላት! ወሬኞች ነን!
  ሄኖክ

  ReplyDelete
 28. nice view!!!
  we need to change our attitude to wards ourselves!

  ReplyDelete
 29. ወደ መሀል ባንወጣም ቢያንስ መተኮሱን እናቁም.....ከዚያም የመሃሎቹ ሲያብቡ የዳሮቹ እንከተላለን..

  ReplyDelete
 30. እባካችሁ ከየምሽጋችን እንውጣ፡፡
  very interesting dn .daniel. The application lies on us!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 31. እውነት ብለሃል፡፡ ቃለ-ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 32. no word to say more than you raised.
  thank you, his Glory be on you.

  ReplyDelete
 33. Thanx Dany

  It is very profitable messege.

  May LORD be save all of you.

  ReplyDelete
 34. Dn danile
  Y dayaseporaw meshge khulum belay askefe gseta telabesoal. y haymant, yzer, ygosa etc. hulum rasun tekekeligna adrigo new yemikotrew. yeh zemen kzemene mesafent bemin yeleyal???? Yechelema zemen. Bizu leserabet yemiyaschelen resource eyebaken endehone yesemagnal. For the sack of ethiopia we should getout of z misheg and try to understand eachother.

  My other point is for those who r giving unnecessary nicknames (like Ayalkebet) for dani:- Dani is a spritual man and such way of appreacition might not be supported from religious views. ofcourse he is aslo writing on social issuse, eventhough,i prefer if u express ur appreations through personal emails.

  Abiot, k oldenburg Germany

  ReplyDelete
 35. Dn Daniel sile tsihufu egziabher yistilign. Tesmamitognal betam. Abiotim Egziabher yistih sile asteyayetih. Kagere kewotahu gena amet limolagn new, gin ezih ene yeminoribet ager yalu habeshoch mishig ejig betam betam yizegeninal, be min kalat megilets endemichal alawukim. Ende miknyatinet yemikerbew neger demo betam yasikal, "systemu new", woy egna Ethiopiawuyan, hulem tiru lalhonut negerochachin hule yeminasabibew be "system" new. Ayi system!!!, Dani bezih neger lay esti anid yehone neger asinebibenima,

  Ye egziabher cherinet behulachin lay yibza,
  Amen!

  ReplyDelete
 36. thank you. long live for you. you are making good things

  smart mind with smart man
  if we do little we all,we can change

  ReplyDelete