Monday, December 6, 2010

ብርሌ

በአንድ የገጠር ደብር አንድ ታዋቂ ሊቅ ነበሩ፡፡ እኒህ ይህ ቀረህ የማይባሉ ሊቅ ምንም ዓይነት ስሕተት አያልፉም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስሕተቶችን ያርማሉ፡፡ እርሳቸው ለሰው ሳይሆን ለእውነት የቆሙ ነበሩ፡፡ የጎደለ ካለ ይሞላሉ፡፡ የተጣመመ ካለም ያቃናሉ፡፡ ታላቅ ነው ብለው አይፈሩም፣ታናሽ ነው ብለው አይደፍሩም፡፡

አንድ ጊዜ አንድ ተምሬያለሁ ያለ ብርሌ የሚባል ሰው እዚያ ደብር ይቀጠራል፡፡ ታድያ ብርሌ ዕውቀት በዞረበት የዞረ አይመስልም፡፡ ያልተማረውን ሳይሆን የተ ማረውን መቁጠር ይቀላል፡፡ እንኳን ምሥጢር ሊያደላድል ንባብ አይሆንለትም፡፡ ነገር ግን «አላዋቂነትን ምላስ፣ ቁስልን ልብስ ይሸፍነዋል» እንደሚባለው ነገር እንደ ተልባ የሚያንጣጣ ኃይለኛ ምላስ ነበረ፡፡ ለሊቃውንቱ የሚሆን ቢያጣ ለባልቴቶች የሚሆን ነገረ ዘርቅ ነበረውና ሠፈሩን ሁሉ በአንድ እግሩ አቆመው፡፡ ሴት ወይዘሮው ወንድ መኳንንቱ ሁሉ እጅግ ወደደው፡፡

ታድያ ብርሌ ጠዋት ጠዋት የሰው ትኩረት እስባለሁ ብሎ ተአምረ ማርያም ሊያነብ ይነሣል፡፡ ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ «ተአምሪሃ» ይላል፡፡ «ሃ» ን ወደ ላይ እያነሣ፡፡ ሊቁም አትሮንሱ አጠገብ ተቀምጠው «ማርያም አትነሣም፣ ተጣይ ናት» ይሉታል፡፡ በግእዝ ንባብ ሕግ «ማርያም» የሚለው ስም ሲነበብ ንባቡ ይወርዳል እንጂ አይነሣም ማለታቸው ነው፡፡ ብርሌም በአላዋቂነቱ ሳያፍር «አለመማሬ በሕዝብ ፊት ተገለጠብኝ» ብሎ ቂም ይይዛል፡፡ ሊቁ በየጊዜው ንባቡን እያረሙ አስቸገሩት፡፡

ብርሌ ሊቁን የሚበቀልበት ተንኮል ሠራ፡፡ ተአምረ ማርያም ማንበቡን ተወ፡፡ ምእመናኑ ቅሬታ ተሰምቷቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም በየምእመኑ ቤት እየዞረ «እኔ ተአምረ ማርያም ሳነብብ ሊቁ የማርያምን ስም አታንሣ ስላሉኝ ነው» እያለ አድማ ቀሰቀሰ፡፡ የማያስተውል ሕዝብ እና ኮለል ያለ ውኃ በፈለጉት መንገድ ይነዳልና ሕዝቡ በሊቁ ላይ ቂም ያዘባቸው፡፡

አንዳንድ ምእመናንም ለብርሌ «እስኪ እርስዎ ተአምሩን ያንብቡና ሊቁ የማርያምን ስም አታንሣ ሲሉዎት እንስማ» አሉት፡፡ ብርሌም እሺ ብሎ በቀጣዩ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ተአምረ ማርያሙን አውጥቶ «ተአምሪሃ» ብሎ ንባቡን አንሥቶ አነበበው፡፡ ሊቁም እንደ ልማዳቸው «ማርያም አትነሣም» ይሉና ያርሙታል፡፡ ብርሌምም ወደ ሕዝቡ ዞሮ «እይውላችሁ ምእመናን ማርያምን አታንሣ እያሉ እኔ ማንበብ አልቻልኩም» አለና ተናገረ፡፡

ሕዝቡም ሆ ብሎ በሊቁ ላይ ተነሣ፡፡ ከደብሩ ካልወጡ ብሎም ዐመፀ፡፡ ሊቁም ማወቃቸው ጥፋት ሆኖ ባልተማሩ እና በማያስተውሉ ሰዎች ግፊት ደብሩን ለቅቀው ሄዱ፡፡

ለመሆኑ እንዴት ነው መስማት ያለብን? የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉስ ትክክል ናቸውን? መምህር ደጉ ዓለም ካሣ «እውነትን የሚያስንቅ ውሸት፣ መውጋትን የሚያስንቅ መሳት አለ» ይላሉ፡፡ ፎርጅድ ብር ከእውነተኛው ብር የተሻለ መልክ እና ንጽሕና አለው፡፡ ታድያ የዋሓን እንዴት እንለየው? አንዳንድ ጊዜ ለውሸትም ማስረጃ የሚመስል ነገር ሊኖረው ይችላል፡፡ ልቡናን እና አእምሮን ማስተባበር፣ ነገሮችንም ረጋ ብሎ መመርመር ካልተቻለ በግንፍልተኛነት ሊያስወስኑን የሚችሉ ለስሜት ስስ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በተለይም ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ነገሮች በአላዋቂነት እርሻ ላይ ከተዘሩ የሚያፈሩት ፍሬ አደገኛ ነው፡፡

በተለይም ለምንወዳቸው ነገሮች ስሜታችን ስሱ ነው፡፡ ሰዎችም ይህንን ስስ ብልት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ብርሌ ሕዝቡ ለእመቤታችን ያለውን ፍቅር ነው ለራሱ ጥቅም የተጠቀመው፡፡ ሕዝብ፣ ሀገር፣ ደኅንነት፣ ትዳር፣ ልጅ፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ ሃይማኖት፣ ዓይነት ነገሮች ለነ ብርሌ የተመቹ ናቸው፡፡

ከሌሎች ነገሮች ይልቅ ባል ስለሚስቱ፣ ሚስትም ስለ ባልዋ የሚሰሙትን ፈጥኖ ለማመን ቅርቦች ናቸው፡፡ አንዳንድ ፍቅር ጥርጣሬን በውስጡ ያዘለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለነ ብርሌ ያመቻቸዋል፡፡ ሰው የሚያየው ማየት የሚፈልገውን ነው፤ የሚሰማውም መስማት የሚፈልገውን፡፡ በጎ ነገር ለመስማት ራሱን ያዘጋጀ ሰው የሚሰማው ሁሉ በጎ ነው፤ በተቃራኒውም ለክፉ ራሱን ያዘጋጀ ሰው እንዲሁ፡፡

በልጅነታችን ስለ ጅብ እና ጭራቅ ስለሚነገረን በጨለማ ስንወጣ ጎቶውን እና ድንጋዩን ሁሉ ጅብ እና ጭራቅ አድርገን እንስለው ነበር፡፡ በጨለማ ውስጥ ጭራቅ ይኖራል ብለን ስለምናምን ጉቶው ጥፍሩን አስረዝሞ፣ምላሱን አሹሎ፣ ጥርሶቹን አግጥጦ፣ዓይኖቹን አፍጥጦ ይታየን ነበር፡፡ ጭራቅ ለማየት ተዘጋጅተን ነበርና «ጭራቅ እናይ ነበር»፡፡

ሚስቱን ከወንድ ጋር ባያት ቁጥር ለመጠራጠር አስቀድሞ የተዘጋጀ ባል እውነት ለሚመስሉ ውሸቶች ተጋላጭ ነው፡፡ ከሚስቱ ጎን የቆመ ወንድ ሁሉ ሲያቅፋት እና ሲስማት ብቻ ነው የሚታየው፡፡ በጣም እንደሚበር መኪና ለመገልበጥ በጣም እንደሚዋደዱ የሚዋደዱ ባል እና ሚስትም ለመጣላት ቅርብ የሆነ የለም፡፡ ጋሽ ግርማ ከበደ «ሰው በሚወድደው ነገር ይፈተንበታል» ይላልና በምንወዳቸው ሰዎች የምንፈ ተነውን ያህል በምንጠላቸው ሰዎች አንፈተንም፡፡

አንድ ሰው ውሳኔው የተስተካከለ እንዲሆን ልቡና እና አእምሮ ያስፈልገዋል፡፡ ልቡና ሃይማኖትን፣ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን፣ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡ አእምሮ ደግሞ ዕውቀት፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ማመዛዘን፣ ማነፃፀር፣ ማዛመድ እና የተጠራቀመ ልምድ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡

አንድ ሰው ነገሮችን በዕውቀት እና በርጋታ፣ በማመዛዘን እና በትእግሥት የሚመ ዝናቸው ከሆነ ከአስመሳይ ውሸቶች ጀርባ ያለውን እውነት የማግኘት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ እነ ብርሌ ሁለት ነገሮችን በመሥራት የተካኑ ናቸው፡፡ እውነት የሚመስሉ ውሸቶችን እና የተቀናበሩ ውሸቶችን፡፡

አልቅሰው፣ ተቅለስልሰው እና ራሳቸውን አዋርደው የሚናገሩ ሰዎች ድርቅ ብለው ከሚናገሩ ሰዎች ይልቅ ሰዎችን የማሳመን ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሽማግሌዎች፣ ፖሊሶች እና ዳኞች ዕንባ ማፍሰስ በሚችሉ ሰዎች ቶሎ ልባቸው ይሰበራል፡፡ የኔ ቢጤው ፈጣጣ ደግሞ «ዓይነ ደረቅ» ለመባል ቅርብ ነው፡፡

ለመሆኑ ግን ነገሮችን ከማመን ነው ወይስ ከመጠራጠር ነው መጀመር ያለብን?

በተለይም የሌሎች ሰዎችን እንከን በተመለከተ አንዳች ነገር ስናይ ወይንም ስንሰማ፣ ነገሩ የሚያሳምን ነገር እንኳን ቢመስል መጀመርያ ግን ሙሉ በሙሉ ማመን የለብ ንም፡፡ ለጥርጣሬ ቦታ መኖር አለበት፡፡ በዚያ ወቅት ከሰማነው እና ካየነው ነገር ይልቅ ሌላ ነገር ቢኖርስ? ደግሞስ ባለቤቱ ራሱ የሚነግረን ሌላ ነገር ካለስ? የሆነው ነገር በሌላ ባህል፣ መንገድ፣ እምነት፣ ርእዮት የተለየ ትርጉም ቢኖረውስ? የሚደረገውን ነገር ራሱ ሰውዬው ሳያውቀው እያደረገው ቢሆንስ) ሌሎችም ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

አሜሪካ ውስጥ አንድ የሰማሁት ታሪክ አለ፡፡ ከሃያ ዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ ሐበሻ ወገናችን ሚስቱን ገድሏል ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ያ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት በቀረበ ቁጥር አንገቱን እንደ ደፋ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕጉ ብዙ ነገር ይዘረዝርና «ይህ ሰው ከሁሉም በላይ የሠራው ነገር ስለፀፀተው አንገቱን እንደ ደፋ ነው» ይህም የፀፀት ስሜት guilty conscious እንደ ተሰማው ያሳያል» ብሎ ያቀርባል፡፡ ዳኛውም አዘውትረው የሚያዩት ነገር ነበርና ይቀበሉታል፡፡

በኋላ ግን ጠበቆቹ በኢትዮጵያውያን ባህል አንገት መድፋት የጨዋነት እንጂ የፀፀት ስሜት መግለጫ እንዳልሆነ፤ እንዲያውም ባላደረገው ነገር ለዚህ በመብቃቱ ማዘኑን እንደሚገልጥ የባህል ኤክስፐርት አስቀርበው አስመሰከሩ፡፡ ዳኛውም በነገሩ ተገርመው ነጻ ለመውጣቱ እንደረዳው ከኢትዮጵያውያን ጠበቆች ሰምቻለሁ፡፡

እንደ ብርሌ ያሉት ይህንን አጋጣሚ ለራሳቸው ማስረጃ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ አላዋቂነትን ተንተርሰው ዐዋቂነትን ይከስሳሉ፡፡ አጋጣሚዎችንም ከሁኔታዎች ጋር ያቀናብራሉ፡፡

በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያልተወሰነበት ሰው ሁሉ ነጻ ሰው ተብሎ የመታሰብ መብት አለው የሚባለው ይህንን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አስቀድሞ ዳኛው ሰውዬውን ወንጀለኛ ሊሆን ይችላል ብሎ በማሰብ ነጻ ለመሆኑ ማስረጃ የሚፈልግ ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ የጠረጠረውና ደስ ያለው ሰው ሁሉ በከሰሰው ቁጥር ነጻ መሆኑን ሲያስረዳ መኖሩ ነው፡፡ የማስረዳት እና የማሳመን ጫናም በከሳሹ ላይ መሆኑ ቀርቶ በተከሳሹ ላይ ሊሆን ነው፡፡

አንዳንድ ተከሳሾች የፀጉራቸው፣ የልብሳቸው፣ የፊታቸው ገጽታ ማኅበረሰቡ ስለ ጨዋነት ከሚሥለው ገጽታ የተለየ በመሆኑ ምክንያት የመጠርጠር እና ሊያደርጉ ይችላሉ የመባል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ምናልባትም የሚናገሩበት የቋንቋ ዘዬ ከተለመደው ጨዋዊ አነጋገር ወጣ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ያን ጊዜ «ይኼማ በደንብ ያደርጋል» የመባል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ልቡና እና አእምሮ ያለው ዳኛ ግን የሚመስለው ነገር ቢያገኝም ለጥርጣሬው ግን ቦታ ይኖረዋል፡፡ ምናልባት ባያደርግስ? ብሎም ይጀምራል፡፡

በፍትሕ ጉዞ ውስጥ አንዱ አከራካሪ ነገር «ሰውዬው ወንጀለኛ ተብሎ ማስረጃው ነው መፈለግ ያለበት ወይስ ማስረጃው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ሰውዬው ወንጀለኛ መባል ያለበት» የሚለው ነው፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ መጀመርያ ሰውዬው ተይዞ ነው በሰውዬው ልክ መረጃ የሚፈለገው፡፡ ማስረጃ መፈለግ እና ማስረጃ ማቀናበር ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡

በሀገራችን «አንገት ደፊ አገር አጥፊ» የሚል አባባል አለ፡፡ አንገት ደፊ ሰው ጨዋ ነው፣ ምንም ነገር አያውቅም፣ አንገተ ሰባራ ትኁት ነው ተብሎ የመታሰብ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ሰው ጥፋት ቢያጠፋ እንኳን ማንም እርሱ አደረገ ብሎ ለመቀበል ዝግጁ አይደለም፡፡ ማኅበረሰቡ የሚጠይቃቸውን አፍአዊ የጨዋነት መመዘኛዎች ያሟላልና፡፡ በዚህም የተነሣ አንገት ደፊው የፈለገውን ዓይነት ወንጀል ቢፈጽም «ዱርዬ ናቸው፣ አስቸጋሪ ናቸው፣ ጋጠ ወጥ ናቸው» በሚባሉ ሰዎች እየተመካኘ ስለሚኖር በድብቅ አገር ያጠፋል፡፡

በሀገራችንም አንድ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ ቡዳ ሰው ይበላል የሚለው ነገር እንዴት እንደ መጣ የሚነገር ታሪክ፡፡

ሰውዬው ደግ ሰው ነበረ አሉ፡፡ ማብላት ማጠጣት የሚወድድ፡፡ ታድያ ሰዎች ይቀኑበት ነበር፡፡ ሁሉ ይወደው ነበርና፡፡ በሬ አርዶ ቅርጫ ባከፋፈለ ቁጥር መግዛት ለማይችሉ ድኾች እርሱ ይገዛና ደብቆ ይሰጣቸዋል፡፡ ታድያ ይህንን የሚያውቁ ምቀኞች የሰው ሥጋ ይበላል ብለው አወሩበት፡፡ ወሬው ውስጥ ለውስጥ ተወራ፡፡

አንድ ቀን ቅርጫ ተከፋፍሎ ሰው ሁሉ የድርሻውን እየወሰደ እያለ የመንደር ውሻ ሾልካ ወደ ጓዳ ትገባለች፡፡ ያ ሰው ይህንን ያይና «ኧረ ያንን የሰው ሥጋ ውሻ እንዳይወስደው» ብሎ ለባለቤቱ ይነግራታል፡፡ ቅርጫ ወሳጁ ሁሉ ክው ይልና በእጁ የያዘውን እየተወ ተጣድፎ ከአካባቢው ይጠፋል፡፡ ከዚያም «የሰው ሥጋ እንደሚበላ ሰማን፣ እኛው በጆሯ ችን ሰማን» የሚሉ ሰዎች አገሩን አጥለቀለቁት፡፡ የርሱ ልጆችም ሰው በላ ቡዶች ተብለው ቀሩ ይባላል፡፡

ይህ አፈ ታሪክ የማኅበረሰባችን ችግር ለመጠቆም የተተረከ ነው፡፡ እውነት ስለሚመስሉ ውሸቶች፡፡ ሰውዬው «የሰው ሥጋ» በቤቱ አስቀምጦ ነበር ወይ? መልሱ «አዎ ነው»፡፡ «የሰው ሥጋ በቤቴ አለ» ብሎ የተናገረ ማነው? ራሱ ሰውዬው፡፡ ነገር ግን «የሰው ሥጋ» የተባለው ባለቤትነትን እንጂ ከሰው አካል የተገኘ ሥጋ መሆኑን አልነበረም የሚያመለክተው፡፡ ጥቂት እውነት የመሰለ ነገር በውስጡ ስላለ ነው ሰዎችን ለማሳመን የበቃው፡፡

አጭበርባሪ ነጋዴዎች ሙዝን ከቅቤ ጋር፣ በርበሬንም ከሸክላ አፈር ጋር እንደሚ ያቀርቡት ሁሉ፤ ለነ ብርሌ ሰዎችን ለማታለል ቀላሉ ዘዴ ጥቂት እውነት የተቀላቀለበት ውሸት ማቅረብ ነው፡፡


50 comments:

 1. አጭበርባሪ ነጋዴዎች ሙዝን ከቅቤ ጋር፣ በርበሬንም ከሸክላ አፈር ጋር እንደሚ ያቀርቡት ሁሉ፤ ለነ ብርሌ ሰዎችን ለማታለል ቀላሉ ዘዴ ጥቂት እውነት የተቀላቀለበት ውሸት ማቅረብ ነው፡፡

  ReplyDelete
 2. Thank you D. Daniel, this is remarkable story which touches each one of us. It is based on fact, opinion and tells. I think we should read and learn from it. At the end let us try to listen, observe, and touch before we judge.....Thank you and May God gives you strength and more wisdom. Amen.

  ReplyDelete
 3. Thank you D. Daniel, this is remarkable story which touches each one of us. It is based on fact, opinion and tells. I think we should read and learn from it. At the end let us try to listen, observe, and touch before we judge.....Thank you and May God gives you strength and more wisdom. Amen.

  ReplyDelete
 4. tnx Dani yaa, we know that there are so many people who desire to dwell on the expense of others. what we should do is being rational rather than emotional,examining everything before accepting it as a general true.when we suspect we gonna believe through time.may God bless you and all your families.

  ReplyDelete
 5. አሳቡ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡እኔ ግን ጥያቄ አለኝ፡፡ቤ/ን ውስጥ ዓለማዊ ፤ዓለም ላይ ደግሞ መንፈሳዊ፣እውነተኛ ሊቃውንት መንገድ ዳር አፈኛና አሳበ ባልቴት በመቅደስ የሆኑበት ምስጢሩ ምን ይሆን? ለሕዝቡ ያልተመቸው ነገር ግን እውነት የሆነ ነገር ሲነገር፣ከአሁን በፊት ያልደረሱበት ነገር ግን ሐቅ የሆነ ነገር ሲቀርብ ሰውን ጴንጤ መናፍቅ በማለት ለድንቁርና እንደ ካባ መጠቀም በቂ ባልሆነ መረዳት ውስጥ ሆኖ መቀባጠር እኛ ቤ/ን የተለመደና እየጨመረ ያለ ኢ ሚዛናዊነት ነው፡፡አንተስ በዚህ ላይ ምን ትላለህ? አመሰግናለሁ!

  ReplyDelete
 6. Dear Daniel, it was really very interesting!by the way, «አንገት ደፊ አገር አጥፊ». I had known the proverb for long time, but it is just after this article that I understood the meaning. Thank you for your advise to avoid my bad character.

  ReplyDelete
 7. ...ማርያም አትነሳም..፣
  ...ኧረ ያንን የሰው ሥጋ ውሻ እንዳይወስደው..፣
  ማስተዋሉን ይስጠን!!!
  *ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ለነገሩ ብርሌ አንድ ቀን መንቃቱ አይቀርም
  ...ጭራቅ ለማየት ተዘጋጅተን ነበርና «ጭራቅ እናይ ነበር»፡፡
  ...ከሚስቱ ጎን የቆመ ወንድ ሁሉ ሲያቅፋት እና ሲስማት ብቻ ነው የሚታየው.
  *አዘገጃጀታችንን እናስተካክል

  ReplyDelete
 8. thank you Dani (Ks.Tilahun)

  ReplyDelete
 9. «እውነትን የሚያስንቅ ውሸት፣ መውጋትን የሚያስንቅ መሳት አለ»

  ReplyDelete
 10. በጣም አስተማሪ ፅሑፍ ነው ዲ/ን ዳንኤል። እግዚአብሔር አምላክ ፀጋውን የብዛልህ።

  ReplyDelete
 11. Thanks Dn.Daniel.

  May God give you more blessings.

  Really very intersting story and way of teaching.Not only this but also there are many traditions that people hold on up to the grave having wrongly cotted stories.
  Any way do your best, who knows one can change the world.

  ReplyDelete
 12. The story represents the current state of the EOTC very very very well. thanx.

  ReplyDelete
 13. «እውነትን የሚያስንቅ ውሸት፣ መውጋትን የሚያስንቅ መሳት አለ» This is happening every day ......bebetechristian weste. Emebrhan terdane.

  ReplyDelete
 14. THANK YOU DANI!!!!!!!!!!! I love this

  ReplyDelete
 15. የማያስተውል ሕዝብ እና ኮለል ያለ ውኃ በፈለጉት መንገድ ይነዳልና ሕዝቡ በሊቁ ላይ ቂም ያዘባቸው፡፡

  ሕዝብ፣ ሀገር፣ ደኅንነት፣ ትዳር፣ ልጅ፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ ሃይማኖት፣ ዓይነት ነገሮች ለነ ብርሌ የተመቹ ናቸው፡፡

  These are the major problems that we are dealing with every day in America.

  G from MN,USA

  ReplyDelete
 16. selam memhr dn.daniel bemejemerya selam na tena lersona lebetesebot hulu yhun eyalkung enie msetew comment kaleng ya hulu post mtadergutn tshufoch aytayenm yalew abzagnaw na yehone solution felguln Araya tekie ke kampala Debre Bsrat St Gebriel amesegnalehung

  ReplyDelete
 17. wow amaizing tarik. please keep up with what ure doing. egzer yebarkih

  ReplyDelete
 18. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ፡፡

  የዘመኖቹን ብርሌዎች ምን እንበላቸው ?

  ጃንቦ፡፡

  ReplyDelete
 19. ልቡና ሃይማኖትን፣ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን፣ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡ አእምሮ ደግሞ ዕውቀት፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ማመዛዘን፣ ማነፃፀር፣ ማዛመድ እና የተጠራቀመ ልምድ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡

  ReplyDelete
 20. "አላዋቂነትን ምላስ፣ ቁስልን ልብስ ይሸፍነዋል"

  "የማያስተውል ሕዝብ እና ኮለል ያለ ውኃ በፈለጉት መንገድ ይነዳል"

  "እውነትን የሚያስንቅ ውሸት፣ መውጋትን የሚያስንቅ መሳት አለ"
  ይህኛው ወጣ ያለ ህይታክ በጣም ናፍቆኝ ነበር። አመሰግናለው
  ዳኒ በትክክለኛው ሰዓት። ወድጄዋለው

  ReplyDelete
 21. Endezih Ayenetochen Berlye Atettubachew::

  ReplyDelete
 22. የማይበላ እንዳያስበላ ያብላላDecember 7, 2010 at 11:13 AM

  "ለነ ብርሌ ሰዎችን ለማታለል ቀላሉ ዘዴ ጥቂት እውነት የተቀላቀለበት ውሸት ማቅረብ ነው፡፡"

  ብርሌ
  Fool me once, shame on you; fool me twice, shame on me.

  ReplyDelete
 23. Memhir Daniel bewnwet silebirilewoch yanesahew neger hulunim hibreteseb yemimeleketina behulachinim guada eyetefeseme yale neger new.Bewnet betam bizu neger new yetemarkubet negerochin mamezazen mechale endalebin yisemagnale yihinin neger behagerawi gudayim binimeleketew bene Birle ayenet mochlafoch hagerachin eyalat endelelat yewelad mechan honalech ena tilik timirt new yagenghubet Egziabher Tsegawun yabzalih elalehu kezih yeblete lemesrat yabkah Amen... Wondimu from Addis Ababa

  ReplyDelete
 24. tnx dani!
  So what can we say about those people represented by "Birillie"? They are always thinking to keep their personal benefits at the expense others. To hide their fault always they accuse people struggling for truth.

  lenegeru, zemenu wushet yebezabet silehone, " wushet sibeza ewnet wihonal" ayidel yetebalew.

  Any ways let God make them rational and think of others mislead by them and as a result losing their rationality.

  ReplyDelete
 25. very wonderful article, God bless you.

  ReplyDelete
 26. እዚህ አሜሪካ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ህብረተቡን እያወናበዱ አሉት “ሀገረ ስበክት”፣ “ቃላ ዓዋዲ” “ሲኖዶስ” የተባሉ ቃላቶች ናቸው። ቃላቶቹ አያስፈልጉም ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ሁሉም አዋቂውም አላዋቂውም እንደፈለገ ስለሚጠቀምበት ለአብያተ ክርስቲያናት መከፋፈል፣ ለምዕመኑ መለያየት ምክንያት ሆነዋል። አነደኛው ወገን “ሀገረ ስብከት”፣ “ቃለ ዓዋዲ” የሚለውን አንደ መርህ ቃል አድርጎ ቤተ ክርስቲያን ለመምራት ይሞክራል፣ ክርስቲያናዊ ሕይውት ግን የለውም፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ አነዚህን ቃላቶች መስማት አይፈልግም። የሚገርመው ነገር አነዚህን ቃላቶች መስማት የማይፈልገው ክፍል ጥላቻውን የዘሩበት እነዚህን ቃላቶች እንወዳለን የሚሉ ክፍሎች ናቸው። በእኔ አስተያያት ሁለቱም ወገኖች ክርስቲያናዊ ሕይወት አላይባቸውም። ሁለቱም ወገኖች ስለ ቃላቶቹ ጥልቅ ግንዛቤ የላቸውም። አንድ ቀን አንድ ምዕመን “ቃለ ዓዋዲ” እፈልጋለሁ አሉኝ ። እኔም ነበረኝና አመጣልዎታለሁ አልኋቸው። በሌላ ቀን “ቃለ አዋዲውን” ስሰጣቸው “ይህንን እኮ አይደለም የምለው እኔ ያልኩት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን መምሪያ የሆነውን ቃለ አዋዲውን ነው አሉኝ። እሳቸው ቃለ አዋዲው የመሰላቸው እንደ ስንክ ሳር ወይም እንደ ወንጌል አይነት ትልቅ መጽሐፍ መስሏቸው ነበር። ግለሰቡ ስለ ቃለ አዋዲ አስፈላጊነት በሰፊው ሲሰብኩ የነበሩና አብያት ክርስቲያናት በቃለ ዓዋዲ መመራት አለባቸው ብለው ምዕመኑን ጥራዝ ነጠቅ ቃላትን ከቃለ አዋዲ እየጠቀሱ ምዕመኑን እንደ “ብርሌ” የሚያወናብዱ ሰው ናቸው። የቃለ ዓዋዲውን መጽሐፍ ግን አንድም ቀን አይተዉት፣ አንብበውት አይተውቱም አያውቁም።
  በሌላ ጊዜ አንድ ሌላ ካህን “ከቃለ ዓዋዲ ነው ያገኘሁት ብለው ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት “ጥቅስ” ነበር። ይህንን “ጥቅስ” ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን መቆርቆራቸውን የመገልጹበት “ጥቅስ” ነው። ካህኑ ሲናገሩ “ቃለ ዓዋዲው እንደሚለው” ብለው ስለሚጀምሩ የሚሰማውም ምዕመን ከልቡ ያዳምጣቸዋል። ካህኑ የሚጠቅሱትን አባባል በተደጋጋሚ በመስማቴ፣ አባባሉም ደግሞ እንዴት እውነት ሊሆን ይቻላል የሚል ጥያቄ ስለጫረብኝ፣ ቃለ ዓዋዲውን ይዤ በመሄድ ይህ የሚሉት “ጥቅስ” የት ጋ ነው ያለው አልኳቸው። ሊያሳዩኝ አልቻሉም። ይልቁንም ደግሞ እሳቸው ከሚሉት በተቃራኒ የተጻፈ “ጥቅስ” አሳየኋቸው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ካህኑ እንደጠላት አይተውኝ መስቀል እንኳን አያሳልሙኝም።
  ሌላም ሌላም እንደ ብርሌ አይነት ሰዎች፣ ብርሌዎች የሞሏቸው ማህበራት ቤተ ክርስቲያንንና የዋሁን ምዕመን ሲያወንብዱት ይኖራሉ። “አውነት የሚመስል ውሸት” ቤተ ክርርስቲያናችንን የመታ መቅሰፍት ነው።
  ሰላም ሁኑ ዳኒና አንባቢዎቹ።

  ReplyDelete
 27. +++ Ejege yetwededk wendmach QHY BERELE betam astemari teshuf new. Lebona yesten"አንድ ሰው ውሳኔው የተስተካከለ እንዲሆን ልቡና እና አእምሮ ያስፈልገዋል፡፡ ልቡና ሃይማኖትን፣ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን፣ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡ አእምሮ ደግሞ ዕውቀት፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ማመዛዘን፣ ማነፃፀር፣ ማዛመድ እና የተጠራቀመ ልምድ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡"+++ Ketoronto akbari betseboch

  ReplyDelete
 28. ቃለ ሕይወት ያሰማልንና ሊቁ “ማርያም አትነሳም” ያሉት “ተአምሪሃ” የሚለውን ቃል አንስቶ (ዘንጥሎ) በማንበቡ ሳይሆን “ማርያም” የሚለውን ቃል አንስቶ (ዘንጥሎ) በማንበቡ ነው::

  ReplyDelete
 29. ዲ|ን ነገረ በምሳሌ ጠጅ በብርሌ እንዲሉ እያንዳንዳችን
  ራሳችንን እንድንመረምር ይመክረናል ልብ ያለው ልብ
  ያድርግ ጆሮ ያለው ይስማ ተብሎአልና
  ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 30. Mr. Birilae reminds us of most of our what political and religious leaders are. So is our clergy - just the same birlae is the one who still runs the show.

  ReplyDelete
 31. አይ ዳኒ ወርቄን በብርሌ ብርሌን በወርቄ አሁን እኔ ከምሰራበት አካባቢ ጋር አሰናስዬ ሳጤናቸው ለዚህች አገርና ለልጆቸ አዝናለሁ፡፡ በደህናው ቀን የሞተ ወይም የተሰደደ ምንኛ የታደለ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡
  ዲምፕል

  ReplyDelete
 32. ንጉሴ ግ.(ደ/ዘ)
  ዲ/ን ቃለ ሕይወት ያሰማልን! እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን እንጅ ለአላፊ ነገር ስንቱን ነገር አድርገናል ላነበበዉ ይህ ትልቅ መልዕክት ነዉ፡፡

  ReplyDelete
 33. Dn. Daniel
  I suppose to the member of /Sinodos/ go to monerstry.lemin yasedibunal hawltu lemin ayefersim.

  ReplyDelete
 34. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱሰ አሜን

  ወድ ዲ. ዳንኤል ቃለ ህይወት ያስማልን ለሰሙም ለወርቁም እኔም ያቅሜን ልበል፡፡

  ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በማቴ 13 ስለ ዘር ሲያስተምር፡፡ ጌታ ሆይ እንክርዳዱን ማን ዘራው አሉት ሐዋርያት ጌታም ጠላት ዘራው እንንቀለው አያ ክፉውን እነቅላለው ስትሉ መልካሙን እንዳትጎዱት እስከ መከር ጠብቁ እንዳለ አንድ ሰው መልካም ዘርን ከእንክርዳድ ለመለየት ጎበዝ ገበሬ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሰለዚህ እስከ መከር መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ስሜታዊነት ሲጨምር ማስተዋል የቀንሳልና ለዚህም ነው መጻጉ ያዳነውን ጌታ ሳያመሰግን የሄደው፡፡ በክርስትና መስተዋል ግድ ነውና፡፡ አለበለዚያ መልካሙን ፍሬ እንዳንነቅል፡፡

  የአለም ፍርድ ሁሌም የታወቀ ነው ገጽን በማየት ስለሆነ የጌታችን ግን ልብን ሰለሚያይ ይሄ ለክርስቲያን አይደንቀውም፡፡ ጥፋት በጋሻው እውነትን ሊያርቅ አይችልም እስከ መከር ነው እንጂ፡፡

  ወስብሃት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
 35. Dani thank you so much!!! KALE HIWOT YASEMALEN

  ReplyDelete
 36. i like every thing u said but i don't thing that "alemawqe" will be hidden "bmelase".i remember an orthodox church father teaching about "melase",he teaches with an example about "ensera",he said "what ever is seen on the body of the 'ensera' comes to be seen when it is full inside".Therefore ones "alaemaweq" canot be covered up by his "alamaweq" rather it will be known that he is "alawaqi" by what he said.now the question how come a "berele" becomes famous? will be answered like "because the listeners are not smart enough to differentiate between 'awaqi' and 'alawaqi'".another way of saying my point goes like "how is it possible for the USA citizens to select their president judging from what he said and yet they r successful? the answer will be most of the people can differentiate between 'awaqi' and 'alawaqi'"

  ReplyDelete
 37. Dn Dani, great analogy! This a story that can point both outward and inward. From the very beginning, it is my belief and wished many times to be wrong, we are shaped to accept what we hear without asking how or why? Even teachers get offended if you ask them this questions and it is considered as a taboo to ask such questions when it comes to religious leaders. We just have to accept what they say!!! However, that is what made us vulnerable to "brilie's". Let us stop believing in what we hear and learn to research facts! "sayayu yamenubegne betsuane nachewe" yemilewe teqese ezihe ga yemisera ayemeslegneme negere gene alebotawe teqeme laye welo bezuwochachene yezo gedele gebetual

  ReplyDelete
 38. dear dani may God bless your life

  ReplyDelete
 39. The title "Berele" doesn't serve justice for such a wonderful article.The reason I said that is becasue I choose what to read based on the title of the article.In this case, I thought it has to do with drinking, "teJ" or even how the "berele" itself is made or how it came to be in Ethiopia.This is exactly the essence of the article and how a small fraction of truth, in this case the name " Berele",can be misunderstood or even misrepresented.I stand corrected on my pre-formed assumptions.However, would you kindly choose a title for your articles that would reflect the content.
  "Qale Hiwot Yasemalen" Amlake Qedusan Yetebeqeh!
  Mulugeta(from Vancouver)

  ReplyDelete
 40. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ፡፡

  የዘመኖቹን ብርሌዎች ምን እንበላቸው ?

  ReplyDelete
 41. qale hiwot yasemalen dani

  ReplyDelete
 42. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ከዘመናችን ብርሌዎች ይጠብቀን!!

  ReplyDelete
 43. bizu egig betam bizu negher astemarken egzihabher yetebkeh

  ReplyDelete
 44. ጥሩ አስተማሪ ጽሁፍ ነው::> ስንቱን ሰው ተጠንቅቆ ይዘልቀዋል እንደኔ ሃሳብ የነዚህ አይነት የኑሮ ፈተናዎችን ለማለፍ ስለእውነት ስለ ንጹህ ህሊና መኖር ይሻላል እላለሁ::

  ReplyDelete
 45. የምታስተላልፈው መልዕክትና ቃሎች በጣም ይመቹኛል፡፡ እግዚአብሔር ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 46. Astemari new. betam arif.

  ReplyDelete
 47. የማያስተውል ሕዝብ እና ኮለል ያለ ውኃ በፈለጉት መንገድ ይነዳል

  ReplyDelete