Tuesday, December 14, 2010

አል ሙሳማህ

አሜሪካ፣ አትላንታ ውስጥ ነው፡፡ አንዲት ሜክሲካን እና አንዲት ኢትዮጵያዊት አብረው አንድ መሥሪያ ቤት ይሠራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊቷ አንድ ችግር ገጥሟት ያቺ ሜክሲካን ሥራዋን እንድትሸፍንላት ትነግራትና ትቀራለች፡፡ በማግሥቱ ስትመጣ ሚክሲካኗ አልሸፈነችላትም ነበርና ተቀጣች፡፡ ይህ ነገር ወዳጃችንን አስቀየማትና ሜክሲካኗን ዘጋቻት፡፡ ሜክሲካን ሆዬ ብትል ብትሠራት የተዘጋውን ማስከፈት አልቻለችምና «ምን ሆነሽ ነው?» ብላ ወጥራ ያዘቻት፡፡ «ሥራሺን እሸፍንልሻለሁ ካልሺኝ በኋላ በመቅረትሺ አስቀጥተሽኛልና ተቀይሜሻለሁ» አለቻት፡፡ ያቺም ሚክሲካን «ሶሪ» አለቻት፡፡


ከ «ሶሪው» በኋላ ሜክሲካን ሆዬ እንደ ጥንቱ ልትጫወት ብትሞክር ነገሩ ያው ነው፡፡ ከዚያም ለሥራ ባልደረቦቿ «ምን ሆና ነው ደግሞ?» ብላ ጠየቀቻቸው፡፡ «ስላስቀጣሻት ተቀይማሻለች» ብለው ነገሯት፡፡ ያቺ ሜክሲካንም «እንዴ ለርሱማ ሶሪ ብያታለሁኮ» አለች ይባላል፡፡ እርሷ ለ «ሶሪ» ያላት ቦታ እና ወዳጃችን ያላት ቦታ ተለያይቶ ነው ችግሩ፡፡

«ይቅርታ» የሚለው አራት ፊደል፣ ያዘለው ነገር ከቃል በላይ ነው፡፡ ይቅርታ በንግግር ብቻ የሚገለጥ አይደለምና፡፡ ይቅር ለማለትም ሆነ ይቅርታ ለማድረግ የተዘጋጀ ልቡና ይጠይቃል፡፡ ያልተዘጋጀ መሬት እንደማይዘራበት ሁሉ፣ ለይቅርታ ቀድሞውኑ ያልተዘጋጀ ልብም ይቅርታን ሊያበቅል አይቻለውም፡፡

ይህንን የይቅርታ ልቡና ለማዘጋጀት ደግሞ ሃይማኖት እና ባህል ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ በሚከተለው እምነትም ሆነ ባዳበረው ባህል ውስጥ የይቅርታ ልምድ እና ሥርዓት ከሌለው በትምህርት እና ስለ ይቅርታ ጥቅም በማወቅ ብቻ ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይቅርታ ለመጠየቅም ይሁን ይቅርታ ለማድረግ ማኅበረሰቡ ራሱ ከይቅርታ የተሠራ ማኅበረሰብ መሆን አለበት፡፡ በማናቸውም ጥቃቅን ስሕተቶች ይቅርታ ለመጠየቅ እና ለማድረግ ዩተዘጋጀ ማኅበረሰብ በግዙፍ ጉዳዮችም ይቅርታ ለማድረግ እና ለመጠየቅ አይከብደውም፡፡

አንድ አባት ልጃቸው በፍርድ ቤት እንደተቀጣ ይነገራቸዋል፡፡ አባትም ደንግጠው «ምን አድርጎ?» ብለው ይጠይቃሉ፡፡ «የሰው ዕቃ ሰርቆ ነው» ይሏቸዋል፡፡ አባትዬውም «ልጄን በሐሰት ከስሰው አስፈርደውበት እንጂ እንዲህ አያደርግም» ብለው ጮኹ፡፡ «ኧረ እርሱ ራሱ ነው ሰርቄያለሁ ብሎ ያመነው» ይሏቸዋል፡፡ «የኔ ልጅ ሰርቄያለሁ ብሎ ሊያምን አይችልም» ብለው አባት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ «ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃሉን ሲናገር ሰምተነዋል» ቢባሉም ፈጽሞ አይደረግም ብለው ጸኑ፡፡ «እንዴት ነው የርስዎ ልጅ ከሰረቀ ሰርቄያለሁ ብሎ የማያምነው?» ብለው ሲጠይቋቸው «ያላባቱ ከየት ያመጣዋል» አሉ ይባላል፡፡

እውነታቸውን ነው፡፡ በቤታቸው ሰርቆ መሸለም፣ ከተያዙም መሸምጠጥ እንጂ ጥፋትን ማመን የሚባል ባህል ከሌለ በድንገት እንዴት ልጃቸው ጥፋቱን ሊያምን ይችላል? ከአባቱ ያልወረሰውን፣ ከማኅበረሰቡ ያልተማረውን፣ ከቤቱ የሌለውን ከየት ያመጣዋል? ነው ክርክራቸው፡፡ ርግጥ ነው፡፡

አንድ የሀገር መሪ፣ አንድ የፖለቲካ መሪ፣ አንድ የአካባቢ ባለ ሥልጣን፣አንድ የቢሮ ኃላፊ፣ አንድ የሀገር ሽማግሌ፣ አንድ የጦር መሪ፣ አንድ የሃይማኖት አባት፣ አንድ ታዋቂ ሰው፣ አንድ ነጋዴ፣ አንድ ዲፕሎማት፣ «አጥፍቻለሁ፣ እዚህ እዚህ ላይ ተሳስቼ ነበር፣ ይቅርታ አድርጉልኝ» ማለት እንዲችል ከተፈለገ አንድ ሕፃን ልጅ ይህንን በድፍረት እና ከልቡ ሊለው ይገባል፡፡

አንድ ማኅበረሰብም በድንገት ይቅር አይልም፡፡ ይቅር የማለት ልማድ ከሌለው በቀር፡፡ በታሪኩ ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ገጠመኝ፣ በዚህ ረገድ ሊነገርላቸው የሚችሉ ጀግኖች፣ በዚህ መንገድ የተፈታ ችግር፣ የዳበረ ባህላዊ ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ በተረቶቹ፣ በሥነ ቃሉ፣ በይትበሃሉ፣ በአባባሎቹ፣ በዘፈኖቹ፣ በቀረርቶዎቹ፣ በንግግሩ፣ በወጉ ውስጥ የሚንፀባረቅ የይቅርታ ባህል ያሻዋል፡፡ ይቅርታ ጠያቂውን እና አድራጊውን ጀግና የሚያደርግ፣ ከይቅርታ በኋላ ነገሮችን ከቂም በቀል የሚያጠራ፣ ልማድ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡

ከሱዳን በስተ ምዕራብ የሚኖሩት የመካከለኛዋ አፍሪካ ሕዝቦች ቻዳውያን እጅግ የሚያስቀና የይቅርታ ባህል አላቸው፡፡ «አል ሙሳማህ» ይሉታል፡፡ የቻድ ብሔራዊ ቋንቋ በሆነው ዐረብኛ «ይቅር በለኝ/በይኝ» ማለት ነው፡፡

ማንኛውም የቤተሰብ አባል የቀኑን ውሎውን ፈጽሞ ወደ መኝታው ከመጓዙ በፊት ሌላውን የቤተሰብ አባል «አል ሙሳማህ» «ይቅር በለኝ/ በይኝ» ብሎ ይጠይቃል፡፡ የተጠየቀውም ሰው ከልቡ ይቅር ይላል፡፡ ቻዳውያን «ያ ሁላችንም ወድቀን፣ ከመኖር በታች፣ ከመሞት በላይ ሆነን የምናሳልፈው ሌሊት ምን እንደሚያመጣ አናውቅም፡፡ ምናልባት በሌሊት አንዳች ነገር ተከስቶ መለያየት ቢመጣ እንደ ተኳረፍን እና እንደ ተጣላን፣ ቅር እንደተባባልን እና እንደ ተቀያየምን መቅረት የለብንም» ብለው ያምናሉ፡፡

«አንዳንድ ሰው ቅሬታውን በግልጥ ይናገራል፤ አንዳንዱ ደግሞ በልቡናው ያስቀምጠዋል፡፡ የአንዳንዱ ሰው ኩርፊያ ፊቱ ላይ ይነበባል፤ አንዳንዱ ደግሞ ውስጡ ጨልሞ ላዩ ይበራል፤ አንዳንዱ ሾተል ሲስል ይታያል፤ አንዳንዱ ግን የበቀልን ሾተል በልቡ እየሳለ ጥርሱ ግን የደስታ ፈንድሻ ይረጫል፡፡ እናም ያኮረፈን ካላኮረፈው፣ የተቀየመውን ካልተቀየመው፣ ደስተኛውን ከኀዘንተኛው መለየት ከባድ ነውና «አል ሙሳማህ» ብሎ ሁሉንም ይቅርታ መጠየቁ መልካም ነው» ነው የሚሉት ቻዳውያን፡፡

እነርሱ ሲተኙ ብቻ አይደለም፡፡ መንገድ ለመሄድ ሲነሡ፤ ጠዋት ወደ ሥራ ሲሠማሩ፣ ልጆች ወደ ት/ቤት ሲሄዱ፣ እንዴው ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ሲለያዩ «አል ሙሳማህ» ይባባላሉ፡፡ «የወጣ ሰው ምን እንደሚሆን አይታወቅም» ይል የለ የሀገሬ ሰው፡፡ እንደ ተቀያየሙ በመለያየት የዘለዓለም ፀፀት ለምን እናተርፋለን? ያንንስ ሰው ለምን በክፉ እናስበዋለን፣ በልባችን ውስጥስ ፍቅር እንጂ ጥላቻ ለምን ዋናውን ቦታ ይይዛል? ነው የቻዳውያን እምነት፡፡

«አል ሙሳማህ» እኛም ጋር ያስፈልጋል፡፡ በባለሥልጣናት መካከል፣ በእምነት መሪዎች መካከል፣ በፖለቲከኞች መካከል፣ በዲያስጶራው መካከል፣ በትውልድ መካከል፣ በቤተ ሰብ መካከል፣ በባል እና ሚስት መካከል፣ በአለቃ እና ምንዝር መካከል፣ በመምህር እና ተማሪ መካከል፣ በሠፈርተኛ መካከል፣ በጓደኛሞች መካከል «አል ሙሳማህ» ባህል መሆን አለበት፡፡

በቻዳውያን ባህል ይቅርታ መጠየቅ የማያስፈልገው የሰው ዓይነት የለም፡፡ ሰውዬው ባለ ሥልጣንም ሆነ ተራ፣ ባልም ሆነ ሚስት፣ሕፃንም ሆነ ሽማግሌ፣የተማረም ሆነ ማይም፣ ሀብታምም ሆነ ድኻ፣ እንግዳም ሆነ ነባር፣ አሠሪም ሆነ ሠሪ፣ መሪም ሆነ ተመሪ ይቅርታ መጠየቅ ግዴታው ነው፡፡ ይህንን የሚያስገድደው ሕጉ አይደለም ባህሉ ነው፡፡

በሌላም በኩል ይቅር ያለማለትም መብት ለማንም የለውም፡፡ ምንም ዓይነት ጥፋት ቢሆን በይቅርታ መሻር ይችላል፡፡ ይቅርታ ከቃላቱ በላይ ኃይል ያለው ከብዙ የገንዘብ፣ የጨጓራ፣ የትውልድ፣ የቢሮክራሲ ኪሳራ የሚታደግ ኃይል ነው፡፡ እናም ከመተኛት፣ ከመለያየት፣ ወደ ሥራ ከመሄድ፣ ወደ ትምህርት ከመጓዝ በፊት ነገሮች ሁሉ በይቅርታ መቋጨት ቢችሉ እንዴት መልካም ነው፡፡

እኛ ይቅርታ የሚያስፈልጋቸው የታሪክ ምእራፎች አሉን፡፡ በየአጋጣሚው እንዲህ የተባለ ማኅበረሰብ በዚህኛው ማኅበረሰብ ላይ ግፍ ፈጽሞ ነበር፤ የዚህ አካባቢ ሰው በዚህ አካባቢ ላይ እንዲህ ያለ ጭፍጨፋ አካሂዶ ነበር እያልን የምንተርካቸውና በየመጽሐፎቻችን በጉልሕ ሥፍራ የምንጽፋቸው ታሪኮች አሉን፡፡ እነዚህ ታሪኮች ቂምን ከማብቀል እና ትውልድን ከማራራቅ ያለፈ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ ችግሩ ይኖር ይሆናል፤ ተደርጎም ይሆናል፡፡ ነገር ግን አባቶች ጮርቃ የወይን ፍሬ በልተዋል ብሎ የልጆችን ጥርስ ማጠርሳት ግን ትርፉ ጊዜ ጠበቅ ፈንጂ መሥራት ነው፡፡

ይህንን መሰል ያለፈ ታሪካችንን «አል ሙሳማህ» ብለን ብንዘጋው ምናለ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የለብኝም፣ ይቅርታ ማድረግም የለብኝም ከሚለው አስተሳሰብ ከወጣን ነገሩ በጣም ቀላል ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ማድረግ የሌለበት የለምና፡፡ ሁላችንም ይቅርታ የምንጠይቅበት ጉዳይ አለ፤ ይቅር የምንልበትም ጉዳይ አለ፡፡

የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አብቅቶ የደርግ ዘመን ሲተካ ታሪካችን የተቋጨው በደም ነው፡፡ አንድን የታሪክ ምእራፍ በደም ዘጋነው፡፡ ችግሩ ደም ታሪክ አይዘጋም፤ ያመረ ቅዛል እንጂ፡፡ በይቅርታ ተዘግቶ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ብዙ ነገሮች ተረስተው፣ በአዳዲስ ታሪኮች ተተክተው ጠባሳችን ይሽር ነበር፡፡ ግን አልታደልንም፡፡

ከደርግ ወደ ዘመነ ኢሕአዴግ ስንሸጋገርም ያንን የታሪክ ምእራፍ በይቅርታ ለመዝጋት አሁንም አልታደልንም፡፡ ምንም እንኳን እንደ ደርግ ዘመን መጨፍጨፍ እና መረሸን ባይኖርም ደርግን ጨምሮ ከ66 እስከ 74 ዓም ለተፈጸመው ቀይ እና ነጭ ሽብር፣ መገዳደል እና መረሻሸን ዋና ተዋንያን የሆኑ አካላት ቂም እንደተያያዙ፣ እንደ ተካሰሱ እና ራሳቸውን ከደሙ ንጹሕ ለማድረግ ገድል እና ድርሳን እንደጻፉ ነው አሁንም ያሉት፡፡ አጥፍቼ ነበር ብሎ ይቅርታ የጠየቀም ሆነ ይቅርታ ያደረገ አካል የለም፡፡

አንዳንዶቹም ከሀገር መውጣታቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጥረውት ምንም ዓይነት የፀፀት ስሜት ሳይሰማቸው ራሳቸውን እንደ ጀግና ይቆጥሩታል፡፡ ለአንዳንዶቹም ከ1974 ዓም በኋላ ሌላ ዘመን የመጣ ሁሉ አይመስልም፤ ይውደም እና ይቅደም፣ እናቸንፋለን እና እናሸንፋለን፣ እንደመስሳለን እና እንቆራርጣለን፣ እንመታለን እና እንበረቅሳለን አሁንም የአፋቸው ማሟሻ ቃላት ናቸው፡፡

የጉዳዮቹ መሪ ተዋንያን ተብለው የተያዙት የደርግ ባለ ሥልጣናትም ይቅርታም ሳይጠይቁ፣ ይቅርም ሳይባሉ እዚያው እሥር ቤት ሆነው አንድ በአንድ በሞት ይጠራሉ፡፡ ምንም እንኳን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሊከበር፣ የሕግ ልዕልናም ሊገለጥ የሚገባው ቢሆን አንድን የታሪክ ምዕራፍ ያለ ይቅርታ በሞት መዝጋት ግን የቀድሞዎቹን ስሕተት መድገም ይመስለኛል፡፡

እነዚህ ሰዎች በይፋ ይቅርታ ቢጠይቁ፤ የተጎዱትም በይፋ ይቅር ቢሏቸው ከሞት ፍርዱ እና ከእሥራቱ በላይ ለዚህች ሀገር ይጠቅማታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የማሠር ታሪክ ሞልቶናል፡፡ የመግደልም ታሪክ በሽ ነው፡፡ የይቅርታ ታሪክ ግን እጥረት አለብን፡፡ ገዳይ ጀግኖች ሞልተውናል፡፡ ይቅር ባይ ጀግኖች ግን እንጃ፡፡ እስኪ የይቅርታ ጠያቂ እና የይቅርታ አድራጊ ጀግና ይኑረን፡፡

እነርሱም እሥር ቤት ሆነው ከሚቀጡት ቅጣት ይልቅ ከእሥር ወጥተው ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል በማየት፣ከተራው ሕዝብ ጋር በመገናኘት፣ ዘወትራዊ ኑሮውንም በመኖር ውስጣቸው በራሱ የሚቀጣው ይበልጣል፡፡ እስኪ ይውጡና ለምን እንደዚያ እንደሆነ በግልጥ ይነግሩን፣ ከእነርሱ ታሪክ ምን እንደ ምንማር ይመስክሩልን፣ በሃያዎቹ የእሥር ዘመናት ጊዜ አግኝተው ያለፈውን ሲገመግሙት ምን እንደተሰማቸው እስኪ ይተርኩልን፤ እስኪ ስለማናውቃቸው ታሪኮች በነጻነት ይጻፉልን፡፡ ዋናዎቹ ምስክሮች ካለፉኮ ያንን ታሪክ ከየት እናገኘዋለን?

«አል ሙሳማህ»

እስኪ በቤተ ሰብ፣ በሠፈር፣ በቢሮ፣ በማኅበር፣ በጓደኛ፣ በትዳር፣ በንግድ አጋርነት፣ የይቅርታ ባህልን እንልመድ፡፡ የታወቀ ጥፋት ስናጠፋ ብቻ አይደለም፤ ይቅር በሉ ተብለንም አይደለም፡፡ ይቅር ካላለከኝ በሚል ተግዳሮትም አይደለም፡፡ እንደ ቻዳውያን ነገሩን ባህል እናድርገውና ማንም ሳይጠይቀን «ይቅር በሉኝ» ማንም ሳያስገድደን «ይቅር ብያለሁ» እንበል፡፡ ከመተኛታችን፣ ከመለያየታችን፣ ከስብሰባችን፣ ከጉባኤያችን፣ ከፖለቲካ ክርክራችን በኋላ «አል ሙሳማህ» እንባባል፡፡ አሮጌው ዓመት ሲያልቅ፣ ከተሾም ንበት ቢሮ ስንቀየር፣ ሥራ ስንለቅ፣ ኃላፊነት ስናስረክብ «አል ሙሳማህ» እንበል፡፡

«አል ሙሳማህ»

                 ይህ ጽሑፍ በሮዝ መጽሔት ላይ የወጣ ነዉ


29 comments:

 1. አዎ ከአፋችን ብቻ ሳይሆን ከልባችን ይቅር መባባልን እንልመድ ለልጆቻችንም መልካም ነገርን እናስተምር፡፡

  ላጠፋውት ጥፋት ለበደልኩት በደል
  ፈጣሪ እንዲምረኝ ይቅርም እንድባል
  አል ሙሳማህ ብያለው ለበደለኝ ሁሉ
  ይህን ያዛልና የፈጣሪ ቃሉ

  ReplyDelete
 2. አዎ ከአፋችን ብቻ ሳይሆን ከልባችን ይቅር መባባልን እንልመድ ለልጆቻችንም መልካም ነገርን እናስተምር፡፡
  ላጠፋውት ጥፋት ለበደልኩት በደል
  ፈጣሪ እንዲምረኝ ይቅርም እንድባል
  አል ሙሳማህ ብያለው ለበደለኝ ሁሉ
  ይህን ያዛልና የፈጣሪ ቃሉ

  kassahun From Addis Ababa

  ReplyDelete
 3. It is a great idea I appreciate it ...
  But for the case of empowered persons of Derg I read from "Ethiopian reporter" that religious fathers are going to apologize Ethiopian people in behave of them it says
  የደርግ ባለሥልጣናትን ሕዝቡ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው የሃይማኖት መሪዎች ሊለምኑ ነው

  ReplyDelete
 4. በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉትን የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናትን፤ ጉዳት የደረሰበትም ይሁን ድርጊታቸውን በታሪክ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው፣ አራት የሃይማኖት መሪዎች ታህሣሥ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. ሕዝቡን በይፋ ሊለምኑ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

  ReplyDelete
 5. Dani

  Why you stop the histroy on Derg? Still killing is common practice in current government. Do you know , if you write, just finish it, unless donot touch some sensetive issue. I hope you know how much most ethiopian heart is bleeding with current government. Please I am begging you , do not forget those people mascured in addis in 2005. Al musam

  ReplyDelete
 6. You Expressed things which we know in a way we can understand and feel it.
  It is a nice view Dani
  Keep it up
  Even though so many persons may appreciate u in your writings and tasks there may also be so many spiritual wars in your spiritual life.
  So Please Pray ! Pray ! Pray ! so that to withstand the different wars you may face in the future.
  I am saying this not because u do not know or you don not do it but just for the sake of the church activity so that u may serve the church and the people more in the future

  ReplyDelete
 7. it is very interesting proverb for us.Danie GOD blase u. u post a good idea for all Ethiopian

  ReplyDelete
 8. what a wonderful message really we Ethiopian are not endowed with this culture. apology is something we learn from families, friends and society. we are always rushing for revenge rather than excuse. but still we can make a difference by giving a lesson to ourselves and the younger generation. apology and discussion should be one part of our daily life. thanks Dani, may the peace of God be with u and families forever.
  From Mekelle.

  ReplyDelete
 9. በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉትን የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናትን፤ ጉዳት የደረሰበትም ይሁን ድርጊታቸውን በታሪክ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው፣ አራት የሃይማኖት መሪዎች ታህሣሥ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. ሕዝቡን በይፋ ሊለምኑ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተ...

  ReplyDelete
 10. አል ሙሳማህ ዳኒ አንዴ ጉባኤ አዘጋጅተን ከነገርንህና ትኬት የአውሮፕላን ከቆረጥን በኃላ
  ቀርተሐል። በዚህ በጣም ተቀይሜህና አዘኜ ነበረ። አሁን ግን በዚህ ጽሁፍ አስተማሪነት ብዬሃለሁ።
  ጆርጅያ አትላንታ።

  ReplyDelete
 11. ኡፍ... ዳኒ ቁልቁል አንደሚንደረደር ኃይለኛ ጅረት ከምኔው ከሥር አደረስከኝ፡፡ ድንቅ ነጽሮት፡፡ ከታሪኩ አወቃቀሩ፡፡ ቻዳውያንስ እንዴት ያስቀናሉ፡፡ ታድለው፡፡
  ከታሠሩትስ ትውልድ ከመጥፎ ሥራቸው ይማራል፡፡ ፖለቲካውን እንርሳውና ከምቀኝነታችን፣ ከመለያየታችን፣ ከሥርዓት አልባነታችን፣ መሬት ላይ ከሚያንፏቅቀን ደካማ የሥራ ባህላችን፣ ጣሪያ ከነካው ውሸታችንና አለመተማመናችን፣ በሃይማኖት፣ በሥልጣን፣ በንግድ... ሰበብ ሕዝብን በመዝረፍ ከተጠናወተን ሌብነታችንስ ማን ምን ይማራል? ምንም፡፡
  አሁንስ ትውልድ ከእኛ የሚማረው ነገር አለ ለማለትም ሳያስቸግር አይቀርም፡፡ ይህንን ሁሉ ችግራችንን ስናስብ በእውኑ የጥንቷ ኢትዮጵያ ይህች ናት? የሚል ጥያቄም ያስነሳል? ለማንኛውም ሁላችንም በየቤታችን የቻልነውን ያህል የትውልድ ግንባት መሠረት ከአሁኑ እንጣል፡፡
  በተረፈ ዳኒ በቁንጽል ግንዛቤ ከፖለቲካ ጋር ሊያላትሙህ ከሚሹ ራስህን ጠብቅ፡፡
  ድንግል ትከተልህ!
  ሄኖክ

  ReplyDelete
 12. Dn Daniel, Kale hiwot yasemalin.
  Thank you for bringing up this issue.This is an important issue we all Ethiopians and Tewahido followers should have a big discussion about. I just want to share my experience.I had a friend who one time asked me to be his best man and I was unable to do it because of a valid reason. After that incident the guy had a grudge and his attitude (towards me) was not good.I tried so many times to befriend with him but his personality kept changing drastically. I didn't have any choice but to leave him alone. All i wanted say is that Please don't go to church with a grudge!!! we can fool people but Not GOD. Egziabher yistilin.

  ReplyDelete
 13. "...የማሠር ታሪክ ሞልቶናል፡፡ የመግደልም ታሪክ በሽ ነው፡፡ የይቅርታ ታሪክ ግን እጥረት አለብን፡፡ ገዳይ ጀግኖች ሞልተውናል፡፡ ይቅር ባይ ጀግኖች ግን እንጃ፡፡ እስኪ የይቅርታ ጠያቂ እና የይቅርታ አድራጊ ጀግና ይኑረን፡፡..." እዚህ ጋር ስደርስ አነባሁ…. :: በእያንዳዶቹ ጽሑፎችህ የራሴንና የማኅበረሰቤን ትክክለኛውን ገፅታ ስለምታሳየኝ አመሰግናለሁ፡ ዲ.ን ዳንኤል አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ::

  ይህ ባህል ስለሌለን መሰለኝ: በመንገድ ላይ እንደ ድንገት ስንጋጭ ምን አያስተውልም/አታስተውልም እንላለን:: አንዳንዶቻችን ይባሱን: ወይ ጉድ ይሄውላችሁ በጠዋቱ ለከፈኝ/ለከፍችኝ እንላላን:: በፈጠራችሁ እዚህ ላይ መልከፍን ምን አመጣው? በአስተሳሰብ ባደጉ ማኅበረሰብ ቢሆንማ ሁለቱም አካላት "I am so sorry, really I am" ይባባላሉ:: ከዚያም አልፈው "I owe you coffee,… I am Mr x and you? ":: አያስቀናም? ? በሕፃንነታችን ከጐረቤት ሕፃናት ጋር ተጣልተን አሸንፈን ከመጣን ጐበዝ የኔ ልጅ እንባላለን፡፡ እያለቀስን ከገባን ግን ወላጆጃችን ምን ለዚህ ተሸንፈህ ነው ቅንዳሹን አትለውም ይሉናል፡፡ ባንፃሩ ደግሞ በአስተሳሰብ ባደጉ ማኅበረሰብ ውስጥ ፡ “ sonny go and say sorry to your friend” ልጃቸው ተበደለ አልተበደለም አይደለም ጥያቄያቸው፡፡ አባት ልጅ በሚያጠፋበት ጊዜ “ come sonny say daddy sorry ” ፀጉሩን እየደባበሰው በፍቅር ያስተምረዋል፤ በአደገ ጊዜም አባቱን ይሆናል፡፡ ለነገሩማ እኛም እኮ የአባቶታችን ነን፤ ያስተማሩን እንፈጽማለን፡ እምቢ አሻፈረኝ፡ እሱ ይቅርታ ካልጠየቀኝ እኔማ ብሞትም አላደርገውም እንላለን፡፡

  “Train up a child in the way he should go: and when he is old, he will not depart from it.” Proverbs 21:6 የሚለው የአምላካችን ቃል ሁሌም ከእኛ ጋር እንዲኖር እመኛለሁ፡፡ ለዚህም ነው ዲ.ን ዳንኤል“ «አጥፍቻለሁ፣ እዚህ ላይ ተሳስቼ ነበር፣ ይቅርታ አድርጉልኝ» ማለት እንዲችል ከተፈለገ አንድ ሕፃን ልጅ ይህንን በድፍረት እና ከልቡ ሊለው ይገባል” ያለው፡፡ በሕፃንነታችን ካልተማርነው ከየትም አናመጣውምና፡፡ እስኪ ልጆቻችን እኛ ባለፍንበት መንገድ አይለፉ!!!!!

  ReplyDelete
 14. ዳኒ ...ልቤን ነው የነካው ዛሬ ጠዋት ነው መንገድ ስጓዝ ርቀታችን ቅርብ በመሆኑ ሲዞር መታኝና የቅርታ ካመለቱ በፊት ይቅርታ ቀድሜ አልኩት ከዛማ የተናገረኝ በጣም አጸያፊ ነበር …. ግን ተጎጂው እኔ …ጉንጬ የተቃጠለ የኔ ደግሜ ይቅርታ ስለው የባሰ ተናደደ ግን ለምን ….. ሀብቱ ከ አዋሬ

  ReplyDelete
 15. AL musamah
  I'm from Atlanta Ga too. I took the weekend off from my work to listen to your preaching and when i heard that you are not comming i was very dissapointed. Kale hiwot yasemalin.

  ReplyDelete
 16. በየአገሩ እንዴት መልካም ባህሎች አሉ? ዲ/ን ዳኒ ሌሎቹንም እንዲሁ…እኔ ለሁሉም እስከዛሬ ባለው “አል ሙሳማህ” ብያለሁ

  ReplyDelete
 17. Kale Hiwot Yasemalin memerachin.

  Hulum Tsewawun Yansa ena berawu bekul hulegize ena beagbabu Almusamah yibel enem "Almusamau" beyalehu lalefewu lewedefitum bezihu eketelalehu.

  Abet endet des yilal leyikerta yetezegaje libe yikerta yemiteyikewu biyata enkuan hedo yikerta teyiko yaluten weyinem yetefeterutin chigeroch lemeftat endemiter yayehubet ena yetemarkubet wedefitem betegbar eyayehu ena enem eyaderegku yemenorebet newu ena wedimachin keante bizu temirenal ahunim bessefiwu entebikalen Dani yeagelgilot zemenehin yabzaleh yitebekeh beyalehu.

  ReplyDelete
 18. ግን እነዚህ ቻዳውያን በዘልማድ ነው «አል ሙሳማህ» የሚባባሉት ወይንስ በጠብና በግጭት ጊዜ «አል ሙሳማህ» ከተባባሉ ጠቡንና ግጭቱን ይረሱታል?

  በዘልማድ በአፍ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን የሚከብደን አይመስለኝም ጠዋት ማታ «አል ሙሳማህ» እንባባላለን፡፡ እነሱ የሚባባሉትከልብ ከሆነ ግን በጣም እድለኞች ናቸው ለእኛም አቀበት የሚሆንብን ይመስለኛል፡፡

  እግዚአብሔር የይቅርታ ልብ ይስጠን፡፡

  ReplyDelete
 19. wongel Felege AbrihamDecember 15, 2010 at 8:26 AM

  ቂመኛ ሰው ‹‹ የሰይጣን ስልቻ ›› ነው ፡፡

  ReplyDelete
 20. Dani, sweety words are coming through you from the Almighty God who Sacrificed Himself for the same purpose you mentioned. When there could not be found one capable of doing the merciful act, He descended from the Most High and gave us full forgiveness without reservation. This is Love, this is forgiveness, now in the period of New Testament. I hope we are called to follow his footsteps, nothing else. Leaders by example in this world are in scarcity, especially in our Mother Church. All of you guys who come across to read this message, Let us bring ourselves in the footage of the Lord and the Saviour Jesus Christ. Let us Forget the past quit from whatever and put ourselves in a different but joyous platform.
  Dani do not forget that this comment also encompasses you. I wish all Ethiopians seat on the chair of Al musamah.

  ReplyDelete
 21. አንድ አባት የተናገሩትን አስታወሰኝ ታላቅ የቤተክስቲያን አባት ናቸው ከእርሳቸውም ጋር አብረው የሚያገለግሉ ሌላ አባት አሉ አንዳንዴ በአገልግሎት ላይ ትንሽ ይገስጾቸውና ወደ ባእታቸው ወይንም ማረፊያቸው ይገቡና ትንሽ ቆይተው ይመለሱና ወደሌላው አባት ቤት በመሄድ ያንኳኩና ምነው ሲሏቸው እባክህ ይቅር በለኝ ውዳሴ ማርያም ማድረስ አቃተኝ ወይንም መጸለይ አቃተኝ ይላሉ እኛም አባት ተነስተው ይቅር ይላሉ ከዚያም ወደ ማረፊያቸው ገብተው ጸሎታቸውን ያደርሳሉ በጠዋት ተነስተውም ለረዳት አገልጋያቸው የሚወዱትን ያውቃሉና ሻይ እራሳቸው አፍልተው ያቀርባሉ። ይቅርርታን የመሰለ የለም ምሽቱም ምሽት ንጋቱም ንጋት ስራው ስራ ውሎውም ውሎ የሚሆነው በይቅርታ ሲታጠር ነው ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 22. HI DANI THANKS FOR ALL
  KEYIKIRETA BELAYE MINE ALA?MINIM
  YE ETHIOPIA HIZIBE YIKIRETA YADIREGILACHEWU,AND THEN NISEHA GIBETAWU BESEGAWEDEMU NATSETAWU WEDE YEMAYIKAREBET BETE BESELAM BIHADU BETAM DESE YILAGNALE,AND KIREWUNE ZEMENACHEWUN DEGIMO YEBEGO ADIRAGOTE SIRAWOCHINE EYASERU YINURU,KE ENASU ABIRAKE LETAGIGNUTEM LIJOCHACHEWU MELAKAM TARIKE YIHONILACHEWAL,FIKIRE YASHENIFALE,KE TILACHA MINI YIGAGNALE

  ReplyDelete
 23. ሠይፈ ገብርኤልDecember 15, 2010 at 12:24 PM

  ሠላም ዲ/ን ዳንኤል

  በማስቀደም፣ የጀመርከውን መልካም ሥራ ልዑል እግዚአብሔር እንዲያስፈጽምህ ፈቃዱ ይሁን።

  “አል ሙሳማህ” በሚል ርዕስ ያስነበብከን የይቅርታ ጉዳይ ላይ ሁለት ጥያቄዎች ላቅርብ፦

  1ኛ፡ የይቅርታ ሥርዓት ጨርሶውኑ በሀገራችን የለም ለማለት ይቻላል? አልጎለበተም፣ ሀገራዊ አልሆነም ሌላ ጉዳይ ነው። ጥቂት ምሳሌ በጥያቄ መልክ ላንሳ።

  ሀ) በቤተክርስቲያናችን የቅዳሴ ሥርዓት ዲያቆኑ “ጸልዩ በእንተ ሰላም ፍጽምት ወፍቅር ተአምኁ በበይናቲክሙ በአምኃ ቅድሳት” ብሎ ሲያውጅልን እጅ የምንነሳሳው ይቅርታ መጠያየቃችን አይደለም?

  ለ) የየዕለቱ ፅዋ ማኅበር መርሀግብር ከመጠናቀቁ በፊት ሙሴው ተነስቶ “ለሙሴ፣ ለደርገ ሙሴ፤ ዓይኑ በሳሳ፣ እጁ ባዳላ፤ ባለቤት ጠላው በቀጠነ፣ ቆሎው ባረረ፣ ዳቦው በቀነበረ፣ ማሩን ይላሉ።” ብሎ ካወጀ በኋላ እርሱም፣ ግልገል ሙሴውም፤ ባለቤቱም (አዝካሪው) በማኅበሩ ፊት ይወድቃሉ። በዚህ ጊዜ ማኅበሩ በሙሉ ተነስተው ባንድ ድምጽ፦ “ሙሴው ዓይኑ አልሳሳም፣ እጁ አላደላም፤ ባለቤት ጠላው አልቀጠነም፣ ወይነ ቃና ነው፤ ዳቦው አላረረ ኅብስተ መና ነው፤ ወሰው ወሰው፣ እንዲህ ያለ የለም” ብለው ደስታቸውን በጭብጨባና በዕልልታ ይገልጣሉ። (ምንጭ፦ አባ ጎርጎሪዮስ (1974)፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ)። ይህ ታዲያ የሚጣፍጥና የማይጠገብ የይቅርታ ሥርዓት አይደለም?

  2ኛ፡ ለመሆኑ “አል ሙሳማህ” ለቻድ ምን ፈየደላት? ታሪኳን በመጠኑ እንዳጤንኩት የርስ በርስ ግጭትና ከጎረቤቷ ሱዳን ጋር እንደተናከሰች አይደለም ያለችው? በመርህ ደረጃ መልካም ቢሆንም ከልማድ እንጂ ከልብ የመነጨ የይቅርታ ሥርዓት አልምሰለኝምና ለኛ ብዙም የሚያስተምረን አልመሰለኝም።

  የኛም የይቅርታ ሥርዓት ማለፊያ ቢሆንም ምን ረባን ትለኝ እንደሆነ፣ እኔ መልስ እንደሌለኝ ከወዲሁ ልንገርህና እረፈው። ጥያቄውን ወደአንተው ወይም ወደ ታዳሚዎችህ ልመልሰውና እስቲ ትንሽ እንወያይበት። የኛም እንደቻዶቹ ከአንገት በላይ ወይም ልማድ ብቻ ሆኖ ይሆን?

  ከልብ የመነጨ የይቅርታ ዘመን እናፍቃለሁ።

  ReplyDelete
 24. Selam Dn. Daneal Thankyou so much.it is very true and we do have to take in our heart how *sorry* means for other part of the world.If we think about *sorry* it will help to keep our health too ,like to forgive somebody means free of stress,blood presure,cancer,headace and helps to sleep well.So beside religous aspect it helps to our health.Thankyou so much Dn. Daneal

  ReplyDelete
 25. at this very moment I can't learn from your writing rather teach me from your deeds ! "almusama for Amistos'"

  ReplyDelete
 26. I agree with SeifeGebriel's comment above.

  ReplyDelete
 27. ዲ/ን ዳኒ በመጀመሪያ በጹሁፍህ ውስጥ የገረመኝ እና ደስ የሚል አገላለጽ ብዬ ያልኩትን ላስቀድም፡
  «ይቅርታ» የሚለው አራት ፊደል፣ ያዘለው ነገር ከቃል በላይ ነው፡፡ ይቅርታ በንግግር ብቻ የሚገለጥ አይደለምና፡፡ ይቅር ለማለትም ሆነ ይቅርታ ለማድረግ የተዘጋጀ ልቡና ይጠይቃል፡፡ ያልተዘጋጀ መሬት እንደማይዘራበት ሁሉ፣ ለይቅርታ ቀድሞውኑ ያልተዘጋጀ ልብም ይቅርታን ሊያበቅል አይቻለውም፡፡ ድንቅ አባባል።
  በተረፈ ግን ከላይ ሠይፈ ገብርኤል ያነሳው ጥያቄ በጣም ተገቢ ስለሆነ ዲ/ን ዳኒ ብትመልስልን ደስ ይለኛል። እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ።

  ReplyDelete
 28. To Seife gebriel:
  I wish was able to write it in Amharic, but that is my laziness and forgive me for doing so. The points you raised are like norms not practices of a daily life.
  The 'amha kidist be beinatine' in the middist of the liturgy is being performed as a norm, where the mental element is absent. Here what we need to think about is the practicability of the same from the bottom of our heart. All of our laities should be told to do it from knowing what they are saying. As you well know most attendants of the holy liturgy are not fully aware of what they are saying and doing.
  The same practice that you mentioned on the 'Tsewa' is nowadays practised with very little. Which cannot represent the followers of the church, while the concept of forgiveness is a wider phenomena. Of course I would agree with you that, such values which are running away from the eyes of this generation should be collected and developed. We need to strive to restore them in the day to day life of the society as a whole. This what I understood from Dani.

  ReplyDelete