ኃይለ ገብርኤል ከአራት ኪሎ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የአምላከ ቅዱሳን የልዑል እግዚአብሔር ሰላምና ፍቅር ከዚህ የጡመራ መድረክ ጦማሪ (ዲ/ን ዳንኤል) እና ከመላው የመድረኩ እድምተኞች ጋር ለዘላለም ፀንቶ ይኑር፤ አሜን።
የተከበራችሁ ወንድሞችና እህቶች፤ ሁላችንም እንደምናውቀው ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል በዚህ የጡመራ መድረኩ አማካኝነት በቅርብም በሩቅም ያለነውን ያለ ማንም ጎትጓችና ቀስቃሽ ልዑል እግዚአብሔር ባነሳሳው መጠን ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይል ዘወትር በየሳምንቱ ማክሰኞና አርብ ከቅርቡ ጀምሮ ደግሞ ቅዳሜ አንዳዴም እንደአስፈላጊነቱ በሌሎቹም ቀናት በመጠቀም በአንዲት መአድ (የዳንኤል እይታዎች)ምግበ ነፍስና ምግበ ስጋን ሲመግበን ቆይቷል፣ አሁንም እየመገበን ይገኛል፣ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ወደፊትም ከዚህ በበለጠ ያጠግበናል።
ይህንን የጡመራ መድረክ ከጀመረ ወዲህ በተለያዩ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች እና አስተሳሰቦች ላይ በእርሱ እይታ አንጥሮ አውጥቶ ለነገሮች ያለን ግንዛቤ እንዲጎለብት እንዲሁም የአስተሳሰብ አድማሳችን እንዲሰፋ፣ በመንፈሳዊ እና በስጋዊ ተጋድሏቸው አንቱታን ያተረፉ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በስጋቸው ከመቃብር በታች የሆኑ ወገኖቻችን በህይወት እያሉ የሰሯቸው በጎ ስራዎች አንፀባራቂ እንደነበሩ ሲያመላክተንና ይህ ስራቸውም ለትውልድ እንዲተላለፍ ሲተጋና እኛንም የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ታሪካችንን ጠንቅቀን እንድናውቅ ሲያስገነዝበን፣ በመንፈሳዊ ህይወታችንም ማወቅ ያለብንን እንድናውቅ እና የሚጠበቅብንን ክርስቲያናዊ ግዴታ እንድንወጣ ሲመክረን እና ሲያነቃቃን ቆይቷል።