Wednesday, November 10, 2010

የእጨጌ ቤቶች

የጎንደር ከተማ ካሏት ጥንታውያን ቅርሶች መካከል የቀድሞውን ዘመን የታላላቅ ሰዎች የቤት አሠራር ጥበብ የሚያሳዩት የእጨጌ ቤቶች አንደኞቹ ናቸው፡፡ ስለ ጎንደር ከተማ ቅርሶች ሲነሣ ስማቸው የማይታ ወሰው እነዚህ ቅርሶች ተከባካቢ በማጣቸው የተነሣ እየፈረሱ እና ከታሪካቸው ጋር ለማይገናኝ አገልግሎት እየዋሉ ነው፡፡

የጎንደር ከተማ ስትነሣ የፋሲል ግንብ፣ የፋሲል መዋኛ እና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ናቸው በብዛተ የሚጠቀሱት፡፡ በከተማዋ ወስጥ ግን ከምድር በላይም ሆነ ከምድር ሥር ያልታወቁ እና የተዘነጉ አያሌ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከአርባ አራቱ አድባራት መካከል ወደ ሰባት ያህሉ ጠፍ ሆነው ፍርስራሻቸው ቀርተዋል፡፡ የአንዳንዶቹ ቦታቸው ባለመከለሉ ለአሳዛኝ ግፍ ተዳርገዋል፡፡ ለምሳሌ የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ቦታ ዛሬ መጸዳጃ ቤት ሆኗል፡፡

የዐፄ ዮሐንስ ቀዳማዌ ዜና መዋዕል እንደሚነግረን በ1672 ዓም ዮሐንስ የተባሉ የአርመን ጳጳስ በግብፅ በኩል አድርገው የአቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተረፈ ዐፅም ይዘው ወደ ጎንደር መጥተው ነበር፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተስፋፋው ገዳማዊ ሕይወት መሠረት የነበሩ እና በኋላም አርመን /ቆጵሮስ/ ሄደው ያረፉ አባት ናቸው፡፡

ዜና መዋዕሉ እንደሚነግረን ይህ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዐፅም ያረፈው በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ይህንን ታሪክ የሚያውቅ የአካባቢው ሽማግሌም ሆነ ሊቅ አላጋጠመኝም፡፡ ምናልባትም ስለ ጎንደር አድባራት ጥናት በማድረግ ላይ ያለው ኢንጅነር መላኩ እዘዘው ይደርስበት ይሆናል፡፡

እንደላይኞቹ ቅርሶች እየተዘነጉ ያሉት ሌሎቹ ሀብቶቻችን የእጨጌ ቤቶች ናቸው፡፡ የእጨጌ ቤቶች ክብ ሆነው በትናንሽ ድንጋዮች የተገነቡ ናቸው፡፡ ድንጋዮቹ የተያያዙት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በሚቦካ ጭቃ መሆኑን ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ ከግድግዳው ወገብ ከፍ ብሎ የግድግዳ አካፋይ የሆኑ ድንጋዮች ወይንም እንጨቶች ይገቡባቸዋል፡፡ የጣራው መያዣም በእነርሱ ላይ ያርፋል፡፡

ቀድሞ የእነዚህ ቤቶች ጣራ ሣር እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ቆርቆሮ ለብሰዋል፡፡


ዋናው እና ትልቁ የእጨጌ ቤት በወራሾቹ አማካኝነት ተሽጦ የሙስሊሞች መስገጃ ሆኗል

እነዚህ ቤቶች ለእጨጌዎች እና ለተከታዮቻቸው ማረፊያ የተገነቡ ናቸው፡፡ ቅርፃቸውም ቤተ ንጉሥ የሚባ ለውን የክብ ቅርጽ ይዟል፡፡ የአንዳንዶቹ ቅሬት እንደሚገልጠው ጥንት ጉልላት ወይንም መስቀል የነበራቸው ይመስላል፡፡

ደብረ ብርሃን ሥላሴ የሚገኘው የደብሩ የታሪክ መዝገብ የመጀመርያው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ወደ ጎንደር የመጡት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በነገሠ በሦስተኛው ዓመት መሆኑን ይገልጣል፡፡ ይህም በ1603 ዓም መሆኑ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን ሥላሴ የታሪክ መዝገብ እጨጌው የመጡበት ምክንያት ሱስንዮስ ደንቀዝ ላይ ቤተ መንግሥት ሲቆረቁር ለደብረ ሊባኖስ ይገባ የነበረው ግብር በመቅረቱ እነደሆነ ይገልጣል፡፡ እጨጌው ወደ ጎንደር የመጡት ከ47 መነኮሳት ጋር ነበር፡፡ መልእክተኞቹ ጉዳያቸውን ለዐፄ ሱስንዮስ አቀረቡ፡፡ ንጉሡም ልምከርበት ጊዜ ስጡኝ አላቸው፡፡ እነርሱም ቆዩ፤ ወዲያውም ክረምት ገባ፡፡ ንጉሡ ለመነኮሳቱ መክረሚያ በአካባው ያለ ሀገር ሰጣቸው፡፡

ክረምቱ ካለፈ በኋላ ሱስንዮስ ውሳኔውን ነገራቸው፡፡ በሸዋ ያለው ለንጉሡ የሚገባው ግብር ለደብረ ሊባኖስ እንዲሆን፣ እርሱ በደንቀዝ ከተማ ስለሚመሠርት እጨጌው ታቦት ይዘው ወደዚያ እንዲመጡ ነገራቸው፡፡

እጨጌው እና ማኅበሩ ታቦታቸውን ይዘው በአምሐራ በኩል መጡ፡፡ በወቅቱ እጨጌ የነበሩት በትረ ወንጌልም ታምመው በአምሐራ ሀገር ሞቱ፡፡ በአትሮንሰ ማርያምም ተቀበሩ፡፡ ማኅበሩ ሁሉ ታቦቱን እና መስቀሉን ይዘው መጥተው ዐፄ ሱስንዮስን በእንፍራ ንዝ አገኙት፡፡ የእጨጌውንም ሞት ነገሩት፡፡ ታላቅ ኀዘንም ተደረገ፡፡ ማኅበሩም የሚተካውን እጨጌ መርጠው አቀረቡ፡፡ አባ አብርሃምም እጨጌነት ተሾመ፡፡

የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ማረፊያ ፈርቃ ላይ ተደረገ፡፡ በዚያም እያሉ እጨጌ አብርሃም ዐርፈው እጨጌ ዘሚካኤል ተሾሙ፡፡ የሃይማኖት ክርክር እና ጦርነት የተነሣው በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡ እጨጌ ዘሚካኤል በመከራው ዘመን ዐርፈው እጨጌ በትረ ወንጌል ተተኩ፡፡ አልፎንዙን የተከራከሩትና

ረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ
ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ

ተብሎ የተቀኘላቸው እርሳቸው ናቸው፡፡

ዐፄ ፋሲል ለፖርቹጊዞች ተሰጥቶ የነበረውን ርስት ለደብረ ሊባኖሶች መለሰላቸው፡፡ እጨጌው እና መነኮሳቱም ወደ አዞዞ መጥተው ዛሬ አዞዞ ተክለ ሃይማኖት በሚባለው ቦታ ሠፈሩ፡፡ ከዚያም ዐፄ ፋሲል የጎንደርን ከተማ ሲቆረቁሩ የእጨጌውም ቦታ ወደ ጎንደር ተዛወረ፡፡ እንግዲህ የደብረ ሊባኖስ እጨጌዎች ወደ ጎንደር የመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡

እጨጌዎቹ በጎንደር ከተማ ሲቀመጡ ይጠቀሙባቸው የነበሩት ቤቶች ናቸው «የእጨጌ ቤቶች» የሚባሉት፡፡ እኔ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ሆነን ባደረግነው አሰሳ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ቤቶችን አይተናል፡፡ ጠንካራ ፍተሻ እና ጥናት ቢደረግ ግን ከዚህ የሚበልጡ ማግኘት ይቻላል፡፡

አንዳንዶቹ ቤቶም ማድቤቶች ሆነው ለእሳት ተዳርገዋል፤ ሌሎቹም መጠጥ ቤቶች ሆነዋል፡፡ ዋናው እና ትልቁ የእጨጌ ቤት በወራሾቹ አማካኝነት ተሽጦ የሙስሊሞች መስገጃ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ ግድግዳቸው በስሚንቶ ተገርፏል፤ ሌሎች ቀለም ተቀብተዋል፡፡

እነዚህ ቤቶች የሀገሪቱ ታሪክ አካል ናቸው፡፡ ለጎንደር ከተማ ደግሞ ፈርጦች ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን የነበረውን የቤት አሠራር ጥበብ ሕያው ሆነው ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ አያያዛቸው ከቀጠሉ ግን ተረት ይሆናሉ፡፡ ሲሆን ወራሾቹ ካሳ ተክፍሏቸው ቤቶቹ በቅርስነት ብቻ እንዲጠበቁ ቢደረግ፤ ያም ካልተቻለ አጠቃቀማቸው ታሪካዊ ይዞታቸውን በማይለቅበት መንገድ እንዲሆን ቢደረግ መልካም ነው፡፡

ስለእነዚህ ቤቶች መረጃ በመስጠት የተባበሩኝን ኢንጂነር መላኩን፣ ዶ/ር ዳኜን እና ዲያቆን ሙሉቀንን እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡


7 comments:

 1. ዘ ሐመረ ኖህNovember 10, 2010 at 3:04 PM

  ዲ/ን ዳኒ በርታ በመንግስት ደረጃ መሰራት የሚገባውን ሥራ በሌለ አቅምህ ብቻህን እየሰራህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳህ ይጠብቅህም፡፡ ለመሆኑ አጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለውና ጢስ አልባው ኢንዱስትሪ የሚባለው፣ በመላው ዓለም ያሉ ሃገራቶች በየሃገራቸው እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገቡበት፣ ከገቢም አልፎ የማንነት መለኪያና መኩሪያ መሆኑን የሚገልጹበት በሃገራችን የቱሪዝም ኮሚሽን ይባል የነበረው በውኑ በሕይወት አለ? ካለ ምን እየሰራ ይሆን? እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና እውነተኛ ልጆቿን ያስባት አሜን፡፡

  ReplyDelete
 2. Selam Ena Tena Yistiliin::

  How about some ethiopian with no internet access? We should think to share this lesson to most ethiopian . But many of us havenot internet access.If we use church news paper that will be ok.
  alex

  ReplyDelete
 3. መምህር ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  እውነትም አገሪቷ ያላት ቅርስ
  የተዋህዶ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ፡፡

  እግዚአብሔር እማማ ኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡ አሜን ፡፡

  ReplyDelete
 4. dani the great keep up what you are doing .i proud of you .
  God bless you man

  ReplyDelete
 5. Dani go ahead, extract more & tell us more facts about our surroundings that enable us to be conscious about so many ruins of buildings in our locality.Your works forced us to give our ears for the stories of our elders & to open our "naked eyes" thereby pay attention for our treasures.
  ቶሎ ቶሎ ንገረን በንዝህላልነታችን ብናፍርም እንሰማሃለን-ደስ እያለን።እኔ እምለው የልደታዎቹ የእነ እማማ አበዜ፡ ግራዝማች ሰጤ፡ የነ ቻይና (ልጅየው)...የእጨጌዎቹ የነበረ ይሆን እንዴ?

  ReplyDelete
 6. Hi Wolde Esdros, I was also remembering many other houses of similar style. Ye emama Beze tela bet, the one that we have on the way from Lideta to Felegeabiyot school,the other on the way from lideta church to Fendika....

  It's amusing yedro seferachinin tarik anawkewum!

  Thanks Dani

  Samuel Zelideta

  ReplyDelete