Tuesday, November 2, 2010

ድንጋይ ስድብ ነው ወይ?

አንዳንድ ጊዜ በተለምዶ የተቀበልናቸው፤ እኛም ሳንመረምር ዝም ብለን የምናደርጋቸው እና የምንናገራቸው ነገሮች፣ የያዙት እውነታ ከሚታወቀው በተቃራኒ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ አለ፡፡ ትምህርት የማይገባውን፣ ሰነፉን እና ደደቡን፣ ሥራ ጠሉን እና ዘረጦውን ለመግለጥ «እገሌ ድንጋይ ነው» እንላለን፡፡ የሌላውን ሀገር አላውቅም እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንዲያ ብሎ መሳደብ እና ድንጋይን ለውጥ ለሌለው፣ ለሰነፍ እና ለሥራ ጠል አእምሮ ምሳሌ ማድረግ የምንችል አይመስለኝም፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ፊደል አመጣጥ ሊጠየቅ የሚችለው መረጃ ድንጋይ ነው፡፡ ቀደምት ሳባውያን ታሪካቸውን እና የጉዞ ዘገባቸውን፣ ንግግራቸውን እና እምነታቸውን ጽፈው ያስቀመጡት በድንጋይ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የምንጠቀምበት እና የምንኮራበት ፊደል እንዴት እና ከየት ተገኘ ብለን ብን መረምር የመረጃው ባለቤት ድንጋይ ነው፡፡ ፊደላችንን ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩትን የጥበብ መሣርያዎቻችንን፣ የጦር መሣርያዎቻችንን፣ የእህል ዓይነቶቻችንን ፣ የምንጠቀምባቸውን ከብቶች፣ የዛፎቻችንን እና የማዕድናት ሀብቶቻችንን እንኳን የምናገኘው ከድንጋይ ላይ መረጃዎቻችን ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጥንቱ ግዛት ከየት ተነሥቶ የት ይደርስ እንደ ነበር፣ ማን ማን የተባሉ ሕዝቦች በአኩስም መንግሥት ሥር ይተዳደሩ እንደ ነበር፣ የትኞቹ ቦታዎች በጦርነት ገብረው እንደ ነበር፣ የትኞቹ ቦታዎች ወርቅ፣ የትኞቹስ ቦታዎች አልማዝ፣ የትኞቹስ ቦታዎች ዕንቁ ይገብሩ እንደ ነበር የጥንቱን መረጃ የያዘው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ነው፡፡

ለመሆኑ የኢትዮጵያን የብዙ ሺ ዓመታት ታሪክ የድንጋይ ያህል አሟልቶ የሚያውቀው አለ? ለቅድመ ጽሑፍ ታሪካችን ምስክሩ የአኩስም እና የደቡብ ትክል ድንጋዮች ናቸው፤ ለአኩስም ዘመን ታሪካችን ምስክሩ በአኩስም አካባቢ እና ባሕር ተሻግሮ በየመን የተገኙት የድንጋይ ጽሑፎች ናቸው፡፡ በዘመኑ የተጻፈ የታሪክ መረጃ የለም ተብሎ በባለ ታሪኮች ዘንድ «የጨለማ ዘመን» እየተባለ ስሙ የጠፋው የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ታሪካችን እንኳን ሕያው ምስክሩ የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፣ ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት በኋላ ለመጣው የመካከለኛው ዘመን ታሪካችንም ከጦርነት የተረፉን መረጃዎቻችን በየዋሻዎቹ የምናገኛቸው መዛግብቶቻችን ናቸው፤ የጎንደር ዘመንም አሻራዎቹ ከድንጋይ የተሠሩት ግንቦቻችን ናቸው፡፡ ሐረር ለነበረው ሥልጣኔ እና ታሪክ ሕያው ምስክራችን ከድንጋይ የተሠራው የሐረር ግንብ ነው፡፡ እናም ሦስት ሺም እንበለው ሰባት ሺ የኛን ታሪክ ከድንጋይ በተሻለ ማን ያውቀዋል፡፡

በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ሙስሊም ጦርነት በተመለከተ እንኳን በሁለቱም ወገን ከተጻፉት ታሪኮች ሌላ ምስክር የምናገኘው በድንጋይ ላይ ነው፡፡ የት የት ቦታዎች ጦርነቱ ተደረገ? በወቅቱ የድል በለስ እየቀናው የመጣው የኢብን ኢብራሂም አሕመድ አልጋዚ ወታደሮች እና ተከታዮች የት ቦታ ላይ ተቀበሩ? በመጨረሻም አሕመድ አልጋዚ የት ቦታ ድል ሆነ? እያልን ብንጠይቅ በወቅቱ የነበረውን ታሪክ የምናገኘው «የግራኝ» ድንጋይ በመባል ከሚታወቁት እና በወቅቱ ከተተከሉት ትክል ድንጋዮች ይመስለኛል፡፡

ሀገራችን በጦርነት ስተታመስ፤ ሕዝቦቿም ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ሲከላከሉ የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛው ታሪካችንም የጦርነት ታሪክ ነው ይባላል፡፡ በዚህም የተነሣ አያሌ ታሪካዊ መዛግብትን አጥተናል፡፡ መጻሕፍቱ፣ ሥዕላቱ፣ ደብዳቤዎቹ፣ ንዋያቱ እና የወግ ዕቃዎቹ እየተቃጠሉም፣ እየተዘረፉም፣ በአፈር እየተበሉም አልቀውብናል፡፡ የተረፉትም ቢሆኑ እድሜ ለድንጋይ በየዋሻዎቹ ተደብቀው፣ ከአፈር መበላት እና ከእሳት፣ ብሎም ከቀበኛ የተረፉልን ናቸው፡፡ እነዚህ የድንጋይ ምሶሶ እና የድንጋይ ወጋግራ ዘርግተው የተፈጠሩ የድንጋይ ዋሻዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ አሁን የምንኮራባቸውን የብራና መጻሕፍት፣ ንዋያት እና የወግ እቃዎች አጥተን ተረት ብቻ ወርሰን በቀረን ነበር፡፡

እነዚያ የድንጋይ ዋሻዎች ንብረቶቻችንን ብቻ ሳይሆን በእነዚያ የጦርነት እና የመከራ ጊዜያት እናቶቻችንን እና አባቶቻችንንም አስጠልለው አትርፈዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ተራሮች ሥር የሚገኙት እና «ዋሻ እገሌ» እየተባሉ የሚጠሩት ለቁጥር የሚታክቱት ዋሻዎቻችን፣ የባሌው ሰብስቤ ዋሻ እና የጋሞጎፋው የቦረዳ ዋሻ ለዚህ ምስክሮ ቻችን ናቸው፡፡

ቀደምቶቻችን ሰማይ ሰማዩን ብቻ ሲያዩ አልኖሩም፡፡ ምድር ንም በሚገባ ዐውቀዋት ነበር፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ የምናገኛቸውን የድንጋይ ጥበቦቻችን የተሠሩባቸው ዐለቶች ተመሳሳይ ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚያ ጠቢባን ድንጋዮቹን በሁለት መመዘኛ ነው ሲመርጧቸው የኖሩት፡፡ ቅርጽ ለማውጣት የሚያስችል እና ረዥም ዘመን ለመኖር ዐቅም ያለው፡፡ በሁለቱም ተሳክቶላቸዋል፡፡ የሚገርመው ግን እነዚህን መመዘኛዎች የሚያሟላውን ድንጋይ ለማወቅ የሚጠይቀውን የጂኦሎጂ ዕውቀት ከየት አገኙት? የሚለው ነው፡፡

አንድ ሊቅ «ኢትዮጵያውያን ማለት ድንጋይ ሲያናግሩ የኖሩ ሕዝቦች ናቸው» በማለት የተናገረው እውነቱን መሆን አለበት፡፡ መሬቱን ፈልገው፣ ድንጋዩን አጥንተው፣ መርጠው እና አለዝበው ዘመናትን የሚሻገር የሥልጣኔ አሻራ መተው የቻሉት ድንጋይ የማናገር ችሎታ ስለነበራቸው መሆን አለበት፡፡ እነዚያን ድንጋዮች ቤት ብቻ አይደለም የሠሩባቸው፡፡ መሠዊያቸውን፣ መስቀሎቻቸውን እና ደወሎቻቸውንም ሠርተውባቸዋል፡፡ በወሎ፣ በጎንደር እና በጣና ገዳማት የምናገኛቸው የድንጋይ ደውሎች ድምፃቸው ከመዳብ እና ከብረት ደውሎች ይበልጣል፡፡ ለዚህ የተስማማውን፣ ድምፅ ሊያወጣ የሚችለውን የድንጋይ ዓይነት በምን ዐወቁት? ወይስ ያን ጊዜ የጂኦሎጂ ትምህርት ነበረ እንዴ?

ምናልባትም ቀደምቶቻችን የተፈተነ ሕይወትን የሚወድዱ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በቀላሉ ከእንጨት፣ሣር እና ቅጠላ ቅጠል ሊሠሯቸው ይችሉ የነበሩትን ነገሮች ከባድ ከሆነው እና ልዩ ችሎታን እና ቴክኖሎጂ ከሚጠይቀው ከድንጋይ ለመሥራት የፈለጉት ተፈጥሮን ለመፈተን፣ ዕውቀትንም ለመገዳደር ይመስለኛል፡፡ የጀግንነታቸው አንዱ መገለጫም ጠላትን በመቋቋም ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን ተፈታትነው በማስገበርም ጭምር እንዲሆን ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ በዚህ መልኩ መከራን ተቋቁሞ ማለፍን አስቀድመው ከተፈጥሮ ጋር ባደረጉት ትግል ስለ ለመዱት ሳይሆን አይቀርም እነዚያን ክፉ ጊዜያት ታሪክ እና ቅርስን ጠብቀው ለማሳለፍ የቻሉት፡፡

ክርስቲያንም ሙስሊምም ያልነበሩት ቀደምት የዳአማት መንግሥታት ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ነው፣ በክርስትናቸው የታወቁት የዛግዌ ነገሥታት እና ሕዝቦችም ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ነው፡፡ ሙስሊም የተነበሩት ግዛቶቻችን እና ሕዝቦችም ታሪካቸውን ያቆዩት በድንጋይ ላይ ነው፡፡ በትግራይ፣ በላስታ እና በጎንደር ከ3000 በላይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እናገኛለን፡፡ በአርጎባ «ራሳ» አካባቢ ደግሞ አርጎባዎች «ቱሉል» ብለው የሚጠሯቸው ወደ 3000 የሚጠጉ በባለሞያ የተቀረጹ የድንጋይ ምስሎች እናገኛለን፡፡ እናም፣ ምንም በሃይማኖት ብንለያይም ሥልጣኔያችን ግን በድንጋይ ላይ ሠፍሮ አንድነታችንን ይመሰክርብናል፡፡

ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትስ ቢሆን ከድንጋይ በተሻለ ማን ይመሰክረዋል፡፡ አንድ ሰው እንዳ ለው «እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡፡

ድንጋይም እንዲሁ ነው፡፡ ከሰሜን አኩስም እስከ ባሌ ተራሮች፣ ከምዕራብ ኦጋዴን እስከ አሶሳ፣ ኢትዮጵያ በታሪካዊ የድንጋይ ሐውልቶች የተሞላች ናት፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የድንጋይ ሐውልቶች ከመቃብር እና ከታሪካዊ ሁነቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸው ነው፡፡

የአኩስም ሐውልት በታላላቅ የአኩስም ነገሥታት መቃብር ላይ መታሰቢያ ሆኖ ቆሟል፡፡ ከአዲስ አበባ ደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ጀምሮ በሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ በሰሜን በአዋሳ ሐይቅ፣ በምዕራብ ደግሞ በአባያ ሐይቅ ተከብቦ የሚገኘውና ከ150 በላይ ታሪካዊ ሥፍራዎችን የያዘው የድንጋይ ሐውልቶች ስብስብ፣ እንደ ሰሜኑ ሁሉ የመቃብር ሥፍራዎችን እና ታሪካዊ ሁነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአርሲ እና ባሌ የምናገኛቸው ሐውልቶችም ይህንኑ የሰሜን እና ደቡብ እሴት ተጋርተው፣ አንድነታችንንም መስክረው ይሄው ዛሬም ይታያሉ፡፡

ድንጋይ ሥልጣኔያችንን ብቻ ሳይሆን ጀግንነታችንንም ሲመሰክር የኖረ ነው፡፡ መሣርያ እንደ ልብ ባልነበረበት በዚያ ዘመን ሉዓላዊነታችን ታፍሮ፣ ድንበራችን ተከብሮ፣ የኖረው በድንጋይ ጭምር ነው፡፡ ቆንጥር ለቆንጥር መወርወር፣ ተራራ ለተራራ መኖር የለመደው ሐበሻ በተራሮች ጫፍ መሽጎ ይለቅቀው በነበረው ናዳ ያለቀውን ጠላት ያህል ሌላው መሣርያችን መጨረሱን እጠራጠራለሁ፡፡ ከሜዳማ አካባቢዎች ይመጡ የነበሩት አብዛኞቹ የውጭ ጠላቶች ከመሣርያችን በላይ መቋቋም ያቃታቸው ለሀገሩ ልጅ ብቻ ይበገር የነበረውን መልክዐ ምድራችንን ነው፡፡

እናም ድንጋይ የታሪካችን፣ የፊደላችን፣ የሥልጣኔያችን፣ የእምነታችን፣ የቀጣይነታችን፣ የአንድነታችን፣ የኅብራችን መገለጫ ከሆነ «ድንጋይ» እንዴት ስድብ ይሆናል?

55 comments:

 1. ውድ ዳኒኤል
  ነገሮችን የምታይበት መስኮት ይመቸኛል፡፡ይህን ችሎታህን መገንዘብ የቻልኩት በኢትዮጵያችን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት የቁልቁለት ጉዞውን በጀመረበት ዋዜማ ነበር፡፡
  ያ የቁልቁለት ጉዞ ከተገባደደ በኋላ ይችን ዛሬ ተክዘህ የምታስተክዘንን ዌብሳይት በቅርቡ ካሳተምከው መጽሃፍህ ላይ አድራሻዋን አገኘሁና ይኸው ባግርኛ የተጻፈ መውድስም ሆነ እንጉርጉሮ አለያም ጉሮ ወሸባየ ባይኔ በብረቱ ዉል ሲልብኝ አምሮቴን ላማስታገስ ወደዌብሳይትህ ጎራ ማለትን ከጀመርሁ ሰንበትበት ብያለሁ፡፡
  ዳኒኤል በእውነት እልሃለሁ ስለድንጋይ የጻፍከው አንቱ የተሰኘ ጽሁፍ ነው፡፡ማየትና ማስተዋል ለቻለ ግዙፍ መልእክት አለው፡፡መልእክቱም ሲጠቃለል ማንናውም ነገር ያለ እንበለ ምክኒያትአልተፈጠረም፡፡ሁሉም ነገር በቦታው መተኪያ የለውም፡፡አይደለም ድንጋይ መርዝ እንክዋን በተገቢው መንገድ ከተቀመመ መድሃኒት ነው፡፡ጎጅ የሚሆነው መጠኑ ካለፈ ብቻ ነው የሚል መልእክት፡፡
  ወደአርአስተ ጉዳዩ ወደ ድንጋይ ልመለስና፤የሰውልጅ የስልጣኔ ዘመን የሚጀምረው የድንጋይ ዘመን ተብሎ ከሚታወቀው ጊዜ ጀምሮ ነው፡በእንግሊዝኛ አጠራር ዘስቶን ኤጅ የሚባለው፡፡ብረትንና መሰል መሳያዎችን መጠቀም የቻለው ከድንጋይ ዎይም ከቡልጭት ዘመን በኋላ ነው፡፡
  በነገራችን ላይ የድንጋይን ዉለታ የሚያጣጥለው በገጠሬነትና በስልጣኔ መካከል ያለው ወገናችን እንጅ ገበሬው አይደለም፡፡
  እንዲያውም አይነኬ አይደፈሬ የተባሉ ድንጋዮች ቋጥኞች ግሬደርና ደማሚት ሲያፈርሳቸው ያገራችን ገበሬ እንጉርጉሮውን በሚከተለው ስንኝ ይገልጠዋል፡፡
  ድንጋይ አይሞትም ነበር ሞት ተፈረደበት
  እየከሰከሱ መኪና ነዱበት፡፡ በማለት
  ውድ ዳኒኤል እግዚአብሄር መቀኛ ከተባለው ብል ይጠብቅህ፡፡

  ReplyDelete
 2. Hi Dn. Daniel,
  bedingay astakeh ye tarikachinin tilket silamelaketiken des bilognal. Mastewalunim adinikeyalehu. Titlu gin ayimetinim...
  Dingay yemilew agelalets telewachi zeyibe new. like 'jib', wusha endeminlew.
  ante bayehewu ayinet kehedin minim ayinet neger sidib lihon ayichilim. mikiniyatum hulum neger melkam neger linorew silemichil new.
  dingay endesidib yetewosedew, alemelewoti, alemesmat ena alemeredat bahriyat silemitayubet new. bizu yemibelan sewu 'jib' binilewu sidib new. neger gin ye jibin melkam negerochi lemisale abiro mebilat, gulbetegnanet, fetan yemilutin kayen degmo sidib ayihonim malet new. Lemasredat felige ayidelem, ante yebelete tawukewaleh. neger gin bizuw tarikachin bedingay lay endale lemasayet sibal zeyibeyawi agelaletsun sihitet masmesel asfelagi ayimeslegnm.
  Belela Anegager, yezih tsihuf title "ye dingay wuleta woyim dingay ena ye ethiopia tarik tisisir tebilo bikerb" betam yeteshale yihonal.

  yezewotir anibabih

  ReplyDelete
 3. derom kewntgna ethiopiawi endh ytebqal kalhiwot yasemaln

  ReplyDelete
 4. Thanks Dani. in fact Dingay appears to be a name, not an insult in European countries. A good old colleague from that part of the world is called Sten. Wikipedia says "Sten" is a Scandinavian male given name. Literally meaning "stone", it derives from a literal translation of "Peter" into the North Germanic languages. Germans use the "Stein" as a name with the same meaning. There are also a number of names associated with different types and aspects of stone including in the bible. http://www.thinkbabynames.com/search/1/stone

  ReplyDelete
 5. Great insight it is!

  ReplyDelete
 6. ድንጋይ ስድብም ይሆናል
  ዲ.ዳንኤል ድንጋይን በጥሩ ተግባሩ በመግለጽህ ደስ ብሎኛል ነገር ግን፤
  የተለያዩ የጽሑፍ መረጃዎቻችንን የያዘው ድንጋይ፤ ታሪካችንን በዋሻ መልክ ደብቆ ያቆየው ድንጋይ፤ በሐውልት መልክ የቆመው ድንጋይ፡ ወዘተርፈ. ሁሉ እኮ የታደሉ ድንጋዮች ናቸው፤ ተመረጠው ጥቅም ላይ የዋሉ። እስቲ በሌላ መልኩ እንመልከተው
  መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ የሚደናቅፍህ ድንጋይ ፤ሰውን ለመፈንከት የሚያገለግለው ድነጋይ፤ እመሀል መንገድ ላይ መኪና የሚገለብጠው ድነጋይ፤ ሰውነትህ ውስጥ በጠጠር መልክ ገብቶ የኩላሊት በሽታን የሚያሸክምህ ድንጋይ፤ አረ ስንቱ… ታዲያ በዚህ አንጻር ‘’ድንጋይ” ስድብ አይሆንም ትላለህ?
  በሌላስ በኩል ድንጋይን መልካም/ወይም መጥፎ የሚያሰኘው ተጠቃሚው ሰው ይመስለኛል። አባቶቻችን ድንጋይን ለመልካም ነገር አዋሉተ፤ሥራ ሰሩበት። የማያስፈልጉ ‘’ድንጋዮቸን’’ ግን ትተዋቸዋል።
  እናም ‘’ድንጋይ’’ እንደኔ እንደኔ ፤ካለው አገልግሎት በተጨማሪ እንዴት ለስድብስ አይሆንም?

  Be'erog

  ReplyDelete
 7. Aydelem, kifu limad honobin betachinin mergechachinin mengedachinin hulu enisadebalen.

  ReplyDelete
 8. Dingay is used as "sidib" because of its relative permanency. It is also very slow to change its nature due to weather and other calamities.

  ReplyDelete
 9. Really interesting. Yihin crititical thinking skill yeseteh Amlak yimesgen.

  ReplyDelete
 10. +++
  ጥሩ ነበር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ አራቀህዉ:: ድንጋይ በመጽሐፍ ቅዱስ በመልካም ምሳሌነት ከዘፍጥረት እስክ ራዕይ ዮሐንስ ድረስ ብዙ ተብሎአል እኮ ምነዉ አንድ ጥቅስ እንኳን? አልነኪ ተጠጠጋጊ ነው የሆነው ነገሩ:: ርዕሱ ጥሩ ነው ብልቱ ግን ውበት ይጎለዋል:: ደግሞ ጥበብን/ታሪክን ተበድሮ ወስዶ ከማን አንሸ የተጠቀመስ ከመቸ ወዲህ ነው ጥበበኛ/የታሪክ ባለቤት ሆኖ እንደባለታሪክ ሊወራለት የሚችለው:: ባለቤትነት ማለት ጀማሪ የሆነ ማለት ነው:: ተሳስቼ ከሆን እታረማለሁ::

  በርታ ረዴኤተ እግዚአብሔር አይለይህ::

  ReplyDelete
 11. ግሩም እይታ ነው! ... እኔንም እንዲሁ ከማይገቡኝ ስድቦች መሃል " የሴት ልጅ " የሚለው አንዱ ነው። ...  እናንተን ... " የሴት ልጅ " አሏችሁ?  ' የሴት ልጅ ' ተብላችሁ

  በእጅጉ የከፋችሁ

  እጃችሁን ... እስቲ ልያችሁ

  / በቃ! ... በቃ! ... በጣም በዛችሁ /

  ይኼ መስፈርት ያሻዋል ... ልብ ብላችሁ አድምጡ

  ያገባናልም ስትሉ ... ቶሎ ወደ ዳር ውጡ።

  *****************************

  በመጀመሪያ ...

  በኑሮ ትግል ያልተረታ

  በውሽንፍሩ ያልተፈታ

  የእናቱ ወኔ ያለው

  እርሱ ካለ እንየው

  የለም?

  ******************************

  በመቀጠል ...

  ማጣት ያላሟጠጠው

  ' ልጄ ... ልጄ ... ' የሚያስብለው

  ፍቅሯ ያለው

  እርሱም ካለ እንየው

  እርሱም የለም? ...

  *******************************

  እህ ...

  ታዲያ ለምን ከፋችሁ?

  እናንተ ' የሴት ልጅ ' አይደላችሁ።

  

  ReplyDelete
 12. በትንታኔዉ መሰረት ድንጋይ ስድብ አይደለም በሌላ መልኩ እንጂ

  ReplyDelete
 13. Dn. Dan

  Sure, Ethiopian history<=> Ston, You expreesed it well. I impressed with the head, cheast, hand, heap, leag dances.

  Wish you all the best

  ReplyDelete
 14. what a view!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 15. yemigerm eyta.yakenaberkibet aemiroh yetsafkibet ejih yebarek.

  ReplyDelete
 16. It seems ordinary fact but the writer revealed the fact from the true nature, and use of the material so it is a deep view. Yes, perfectly! Historians, archeologists, geologists, folklorists, philologists, anthropologists, and linguists (in general humanists) depend on a stone to bake their bread or to protect their life. Thus, a stone is far better than human beings. Thank you for analysis.

  ReplyDelete
 17. ዳኒ እናመሰግናለን፡፡
  እንደኔ ገን እነደ አገባቡ ይመስለኛል ሰው በባህሪው ሁልጊዜም ለለውጥ የተዘጋጀ መሆን አለበት ያለዚ ግን የድንጋ ጠባይ የሆነውን ለረጅም ጊዜ አለመለወጥን ይወስዳል ያኔ ለሰው የሚገባ ጠባይ ስላልሆነ ስድብ ይሆንበታል፡፡
  "if you change your self, the change will change you" የሚለውም ጣጣ ይደርስበታል
  ለምሰሌ፡-አንድ ሰው ሌላ ሰውን "እከሌ እኮ ውሻ ነው" ቢል ለባለቤቱ ታማኝ ነው፣የጌታውን ንብረት በአግባቡ ይጠብቃል እና ሌላ ጥሩ የሆኑ የውሻ ግብሮችን ላማለት ብሎ ነው ወይስ......
  ስለዚ ለኔ ድንጋይም ውሻም እንዳገባባቸው ነው ግን ልማዱ እንደለመድነው ነው፡፡

  ReplyDelete
 18. የማይበላ እንዳያስበላ ያብላላNovember 3, 2010 at 11:00 AM

  " እነዚያ ጠቢባን ድንጋዮቹን በሁለት መመዘኛ ነው ሲመርጧቸው የኖሩት፡፡ ቅርጽ ለማውጣት የሚያስችል እና ረዥም ዘመን ለመኖር ዐቅም ያለው፡፡"

  ጞጆ ልትቀልስ አፈር መደልደሏ
  ስንጥቅ መሰረቱን ሳትደፍን ሳትሞላ
  ለትውልድ የሚሆን ላይፀና በችላ
  ሌት ተቀን መልፋቷ እስኪደቅ አካሏ
  ይቺ ባላ አደራ ሞኝ ናት ተላላ

  ReplyDelete
 19. አረ ዳኒ ምን አይነት ዕውቀት ነው ግን እግዚአብሔር የሰጠህ? ተባረክ! ፅ

  ReplyDelete
 20. ሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትስ ቢሆን ከድንጋይ በተሻለ ማን ይመሰክረዋል፡፡ አንድ ሰው እንዳ ለው «እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡፡......Very interesting observation

  ReplyDelete
 21. That is perfect, Daniel. In spite of all those and other usages, 'rock' is used for insulting in Ethiopia for at least three reasons:

  1) the very nature of its hardness is not to the benefit of the rock itself, but for the defence/advantage of other things/people.

  2)that it is used to build cemetries and has symbolic meaning that transcends contemporary societies- that it is in such cases about the dead and the past. Also rocks used in such contexts- in cemetries- are feared and hated by at least most people. They are associated with evils, ghosts, and all the bad spirits.

  3) hard rocks are non-porous- they do not admit the passage of gas or liquid through pores. So 'stupid' people do not consider and benefit from the ideas/suggestions/comments/decisions of other people.

  Best,

  ReplyDelete
 22. እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 23. ድንጋይ የታሪካችን የፊደላችን የሥልጣኔያች ወዘተ…. መገለጫ ቢሆንም፤ ድንጋይን የስድብ ቃል ያደረገው፤ ይጻፍበትም አይጻፍበትም ይወቀርም አይወቀርም ለረጅም ዘመናት እራሱንና ይዘቱን ሳይለውጥ በመቆየቱ ነው፡ አልለወጥ ያለውን ሰው ድንጋይ የሚባለው፡፡ (አለመለወጥ ለድንጋይ ጥቅም ቢሆንም ለሰው ግን በሽታ ነው)

  በጣም ያስደሰተኝ ‹‹እስክስታ›› ኢትዮጵያን አንድ ሰው ማድረጉ ነው፡፡ ማስተዋል ያለበት እይታ ነው፡፡

  ማሂ

  ReplyDelete
 24. ...እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡፡

  THANKS A LOT DEAR DANIEL

  ReplyDelete
 25. Amazing. Astonishin view

  ReplyDelete
 26. yakenaberkibet aemiroh yetsafkibet ejih lewedefitem endihu yemianitsewen melkamun begowen hulu endiakerbilin tenana bereket yesteh.

  ReplyDelete
 27. Hello, My name is Bogdan from Romania!
  My blog address is: http://bogdanstelistul.blogspot.com/
  Can we be friends??
  Thank you!!
  For those who do not understand use Google Translate (top right) and select your language!!!

  ReplyDelete
 28. dany ebakeh wel geze safe anyalkebhem
  betam ewedhalew the chcago

  ReplyDelete
 29. dany betam ewedhalew
  ebakeh wel geze safe
  the chcago

  ReplyDelete
 30. ዲያቆን መሐሪ ገብረ ማርቆስNovember 3, 2010 at 5:20 PM

  እንክት አድርጎ ስድብ ይሆናል!

  እውነት ነው አንተ መምህሬ በተመለከትህበት ዐውድ አስገብተን ስንመለከተው “ድንጋይ” የሚለው ቃል ስድብ ሊሆን አይችልም፡፡ አንዳንድ የድንጋይ ጠባዮችን የተመለከትን እንደሆነ ግን ቃሉን የምንመለከትበት ዐውድ ይቀየራል ፍቺውም እንዲሁ፡፡ ድንጋይን ስድብ ከሚያደርጉት ጠባያቱ መካከል የሚከተሉት ሊጠቀሱ የሚችሉም ይመስለኛል፤

  ሀ. ድንጋይ ማሰብ አይወድም፡፡ ግድ የለሽ ነው፡፡

  ሁልጊዜም መሪ፣ ገሪ ይፈልጋል፡፡ መሪው ያደረገውንም ይሆናል፡፡ መሪው እስጢፋኖስን እንዲወግርለት ሲልከው የእስጢፋኖስን ማንነት ከማየትና ከማሰብ ይልቅ ዝም ብሎ ተወርውሮ እስጢፋኖስን መግደል ይቀለዋል፡፡ “ለምን?” ብሎ አይጠይቅም፡፡ በትእዛዝ የመጣ ነገር ሁሉ ለእርሱ “ጽድቅ” ነው፡፡ መብቶቹም ሆነ ግዴታዎቹ ምን እንደሆኑ በስሚ ስሚ፣ የወሬ ወሬ ካልሆነ በስተቀር አያውቃቸውም፡፡ ቆም ብሎም አይመረምራቸውም፡፡ ምክንያቱም አይወድማ! አሳቢዎቹን ያኑርለት እንጂ እርሱ ምን በወጣውና ያስባል?

  ለ. ድንጋይ ብልኀትና ፈሊጥ አያውቅም፡፡ ግትር ነው፡፡

  ራሱን ከሁኔታዎች ጋር አመቻችቶ ህልውናውን ከማስጠበቅ ይልቅ ፀሐይና ዝናብ፣ ቅዝቃዜና ሙቀት ተፈራርቀውበት ወደአፈርነት እስኪለውጡት ይጠብቃል፡፡

  ሐ. ድንጋይ ከስሕተቱ አይማርም፡፡

  ትናንት የወረደችበት ፀሐይ ነገም ከነገወዲያም ትመጣለች፤ ትቀጠቅጠውማለች፡፡ አምና ያኮማተረው ቁርና ቅዘዝቃዜ ዘንድሮም ሆነ መጪው ዓመት ላይ ይመጣሉ፡፡ ድንጋይ ግን ተለውጦ፣ ከስሕተቱ ተምሮ አይቆያቸውም ይልቁንም እዚያው ባለበት ተቀምጦ ይጠብቃቸዋል፡፡ ችግርን ለመፍታት ሳይሆን ለመልመድ ይጥራል፡፡ ችግሩ ግን ስለተለመደ ብቻ ችግርነቱ አይቀርም- ለማጅ ተብዬውን መቃብር ያወርደዋል እንጂ፡፡

  መ. ድንጋይ አካባቢውን አይመረምርም፡፡

  የያዘው ጎዳና ለህልውናው ይጥቀም አይጥቀም፡፡ ይበጅ አይበጅ ለድንጋይ ጉዳዩ አይደለም፡፡ አካባቢውን የሚረዳበት ስሜትም ለእርሱ ባዕድ ነው፡፡ ስለዚህም ዘለዓለም የአካባቢው ባርያ እንጂ የአካባቢው ሥሉጥ ተቆጣጣሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁኔታዎች ይገዙታል እንጂ ሁኔታዎችን አይመራም፡፡

  ለምን?

  ድንጋይ ስለሆነ፡፡

  እውነት እንነጋገር ከተባለ ብዙዎቻችን ለቤተክርስቲያናችን፣ ለሀገራችን ጉዳዮች ድንጋዮች ሳንሆን የምንቀር አይመስለኝም፡፡

  ReplyDelete
 31. በእዉነት ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ጸጋ በረከቱን ያብዛልህ ፡፡ ለመሆኑ ይህን ማን አስተዉሎ ያዉቃል ፡፡ሁሉም ሰዉ ስድብን ሲያስብ አፉ ላይ መጀመሪያ የሚመጣለት ድንጋይ ሂድ ከዚህ የሚል ነዉ፡፡ እግዚአብሔር ለሁላቸንም ማስተዋሉን ይስጠን፡፡ዳኒዮ ገና ብዙ ያላሰተዋልናቸዉን ታሳዉቀነቀለህ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

  ReplyDelete
 32. You are making a landmark history. What makes Ethiopian people one and one. Thank you

  ReplyDelete
 33. Eshohn be eshoh dngayn be dngay wtetama ayhonm ende?

  ReplyDelete
 34. ድንጋዩ ሳይሆን ድንጋይ መባል ስድብ ነዉ!
  ድንጋዩማ ሊቅ፣ ጠቢብ ባለእዉቀት ካገኘ ገራገር ነዉ እንዳደረጉት ይሆናል። ለዚያም ታዲያ መዶሻና መሮ ሚስማር ተረባርበዉበት ነዉ ዉስጡን የሚያስፈትሸዉ። በመወቀሩ ቅር ባይሰኝም የዉስጡን ማን ያዉቅለታል። ያገሬ ባልጩት ከዓመት ዓመት ዉሃ ሲፈስበት ትንሽ እንኳ ፉት የማይለዉ ጥቁር ድንጋይ እንጂ ምን ሊባል። ከፈጣሪዬ አታጣላኝና እዉነት ተመስክሮለት የማይገባዉን ፣የህዝብ እንባና መከራ ትንሽ የማያመዉን፣ በታሪክ ተወቃሽነት ስሙ ተዘግቦ እያለ በጀግንነት የሚጀነነዉን ደፋር ጸሎተኛ ድንጋይ አይደለም ካልከኝ በል አንተ ስም አዉጣለት። ለኔ ግን ስሙ ድንጋይ ነዉ። ብዕሩ ዘአትላነታ

  ReplyDelete
 35. I love this article. You're gifted . You know things and you reflect them perfectly. It's like a reflection in the water. Thank God! You're our treasure.

  ReplyDelete
 36. ዘ ሐመረ ኖህNovember 4, 2010 at 6:24 AM

  ዳ/ን ዳኒ እግዚአብሔር ይስጥልን በዚህ ዘመን የሃገራችንንና የሕዝባችንን አንድነት ብዙዎቻችን ማወቅም መግለጽም ሲያቅተን ግኡዛን ድንጋዮች አንደበት ካለን ሰዎች በላይ እየነገሩን ነው እኛ ግን ዛሬም ማስተዋሉ ጠፍቶን በዘር በቋነቋና በሃይማኖት ልዩነት እንድንፋጅ የሃገርና የሃይማኖት ጠላቶቻችን ባዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ ወድቀናል መቼ ይሆን የምንባንነው ትንሽ ማስተዋል ቢኖረን ከአውሮፓዎቹ ድንበር አልባ ሕብረት የኛዎቹ ተናጋሪ ድንጋዮች ይበልጥ አስተማሪዎች ነበሩ ብዙ የተለያዩ አገሮች በባሕልም በቋንቋም በምንም ሳይመሳሰሉ አንድ ሆነው ወደ ሕብረት ሲመጡ እኛ ግን በአንድ ሃገር ላይ አንድ መሆን አቅቶናል ለምን ጠላቶቻችን ባዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ መውደቃችንን ማወቅ አልቻልንም ስለዚህ እባካችሁ እንንቃ በመልካም እንቀየር በፍቅር እና በአንድነት ተነስተን ሰው እንሁን አመሰግናለሁ

  ReplyDelete
 37. እንደሁኔታዉ ነዉ

  ReplyDelete
 38. according to the condition

  ReplyDelete
 39. @ ዲያቆን መሐሪ ገብረ ማርቆስ
  ‹‹ድንጋይን ስድብ ከሚያደርጉት ጠባያቱ መካከል የሚከተሉት ሊጠቀሱ የሚችሉም ይመስለኛል፤›› በማለት የዘረዘርካቸው
  ሀ. ድንጋይ ማሰብ አይወድም፡፡ ግድ የለሽ ነው፡፡
  ለ. ድንጋይ ብልኀትና ፈሊጥ አያውቅም፡፡ ግትር ነው፡፡
  ሐ. ድንጋይ ከስሕተቱ አይማርም፡፡
  መ. ድንጋይ አካባቢውን አይመረምርም፡፡
  ግዑዝ ለሆነው ድንጋይ የሚቻለው አይደለም፡፡ ስለሆነም ከድንጋይ ማሰብን፣ብልሀትን፣ፈሊጥን፣ከስህተት መማርን፣አካባቢን መመርመርን መጠበቅ የለብንም፡፡ ይህ ጠባይ ለግዑዛን አልተሰጠምና፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ማሰብ፣ብልሀት፣ፈሊጥ፣ከስህተት መማር፣አካባቢን መመርመር ሲችል ባለማድረጉ እንደ ድንጋይ እነዚህን ማድረግ ተሳነው ሊባል ይችላል፤ልክ ዳዊት ሰውስ ክቡር ፍጥረት ሆኖ ሳለ እንደ እንስሳ ሆነ እንዳለው፡፡
  ለነገሩ ሰው እንቅፋት መታኝ እንጂ መች መታውት ይላል፡፡ እንግዲ ድንጋዩ ተንቀሳቅሶ ጠብቆ አልመታው አይቶ መራመድ የሚችል ራሱ ሰውየው ሆኖ ድንጋዩን ለመኮነን እንጂ፡፡
  ለሁሉም አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር መጥፎ የሆነ ፀባያችንን ያስወግድልን፡፡
  ለ ዲያቆን ዳንሄልም ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡
  ካሳሁን
  ከአዲስ አበባ

  ReplyDelete
 40. sele abune Pawlos Atiyat bich kmawrat Yesrute seneti sera ale Yemariya Universtiy Yasemlsu betochn Yasemlsu .....

  Hwlitu ktsra behala mafirsu tikmu altaygne kegudatu beker bezu birr fesobti mafirsi lmene?

  Rut

  ReplyDelete
 41. መምህር ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  እንደኔ እንደኔ
  ድንጋይ ስድብ አይደለም፡፡

  የሚያደናቅፈውም ድንጋይ እኮ አደናቃፊ ስለሆነ ማንሳት እንጂ ከስድብ ጋር ምን አገናኘው?

  ለምሳሌ ብርቱካን ስድብ ነው?

  ካልሆነ ብርቱካንም እኮ የተበላሸ ከሆነ ይጎዳል ሌሎቹም እንዲሁ፡፡

  ReplyDelete
 42. ዳ/ን ዳኒ
  በጣም የሚገርም እይታ ነው በተለይ የሚከተለው አገላለጽህ

  "ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትስ ቢሆን ከድንጋይ በተሻለ ማን ይመሰክረዋል፡፡ አንድ ሰው እንዳ ለው «እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡፡"
  እግዚአብሔር ይስጥህ።

  ReplyDelete
 43. First and foremost it is not appropriate to conclude an idea based on analogy. Analogy serves to compare and illustrate something cogently in order to print clear image in human mind. Let alone in different species, nonliving things and living things, it is entirely mistaken to have a conclusion between similar entities based on analogical facts. For instance Mr. x and Mr. y born in the same year, they took the same level of education, in all criteria. But both grew up in different continent, the first in the united state and the latter in Ethiopia. Because both are human being equally, because both are learned for that matter an education from the same faculty and same curriculum, they are not expected to bring the same achievement in the real world. The common factors for the two individuals may serve to base an analogy and say something comparatively. But the conclusion that serves for Mr. y do not serve for Mr. x .so that we can conclude analogy serves only for comparing and contrasting purpose as well as to create clear picture in human minds, for instance to demonstrate the operation of solar system , the rotation of electron proton and the sort. Therefore it is entirely wrong to conclude based analogy that has for that matter different unit of measurement, the case in point is between mankind and stone. The worst part of analogy is also its serves for deceptive argument. For instance, to divert an issue to side issue and to relate the fact happened in a given country by making analogy with another country. Meaning to say you can compare one fact of Ethiopia to the fact of any country outside Ethiopia. But you cannot conclude based on that comparison since both countries are found in different course and situations
  Thanks Dani

  ReplyDelete
 44. Dani

  Weqesa kens alalkuhim, esti bmiketelew tiruwin negrachinn tsaf.... wekash yehonk eko meslng...

  ReplyDelete
 45. tekelewolde the sodoNovember 4, 2010 at 9:57 PM

  Aye enena Dinegayi!!! Eseti ahune mezenune?

  ReplyDelete
 46. Sam from Nairobi,

  Thanks Dani, It gives at least the other view of Stone. But being stone on the other side is insult as my view.

  ReplyDelete
 47. Deacon Daniel and Deacon Mehari, I'm amazed by both of your views! Please continue this...(You know what I mean)

  ReplyDelete
 48. ለካስ ኢትዮጵያ የተሸመነችው ከእስክስታ ነው!

  ይህን ጽሑፍ እያነበብኩ ሳለሁ ትዝ ያለኝ አንድ ጥቅስ "...ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሳለት እግዚአብሔር ይችላል፡፡" የሚለው ነው፡፡

  "Ancient Secrets of the Bible" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አሥር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓበይት ክንውኖችን የሚዳስስ የምርምር ዘገባ ፊልም እየተከታተለኩ ነው፡፡ በእውነቱ በእነዚህ የዲቪዲ ፊልሞች ላይ ምሁራኑ የሚወዛገቡትም ሆነ ማስረጃ የሚያጣቀሱት በአብዛኛው ዳንኤል እንደገለጸው የድንጋይ ላይ አሻራዎችን በመመራመር ነው፡፡ እነዚህን ዲቪዲዎች ለማግኘት የምትችሉ የዚህ አምድ ተከታታዮች የዳንኤልን እይታ ሳይሸሽ ሳይበላሽ እንደወረደ ታገኙታላችሁ፡፡

  በዚህ ጽሑፍ ሁለት ቁምነገሮችን አግኝቼበታለሁ፣

  1ኛ - ድንጋዮች ከእኛ ይልቅ በዘመናት ሂደት ውስጥ ባለመዛነፍ መናገር መቻላቸውን ነው፡፡ አብርሃም አባት አለን ለማንም ሲበጅ አላየንምና ቢከፍቱት ተልባ እንዳይሆን እንደድንጋዮቹ ባለአሻራ /መረጃ ያለው ሰው እንድንሆን ማስተማሩ፡፡
  2ኛ - ኢትዮጵያዊነት የሽመና ውጤት መሆኑን ለማሳየት የተጠቀመበት ዘይቤ ነው፡፡ የጥበብን አካል አልፈልገውም ብዬ መዝዤ ማውጣት የማልችለውን ያህል ኢትዮጵያዊነት በዚያ ስልት በግሩም ሸማኔ የተዘጋጀ ጥበብ መሆኑን ነው፡፡

  ግሩም እይታ .... ምርጥ አስተምህሮ

  ReplyDelete
 49. ዳኒ በጣም አመሰግናለሀሁ ጥሩ ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከእንግደዲህ ሰውን ለምርቃት ካልሆነ ድንጋይ አልልም፡፡ ግን ያንተን ጽሀሁፍ ያላነበበ ቢያገጋጥመኝ ምን እንደሚያደርገኝ አስብ፡፡ በሌላ መልኩ ከብዙ ስድቦቸቻችን አንዱን ቀንሰሀል፡፡ የስድብ ደሀ አይደለንም እንጂ በዚህ ቅር የሚሰኘኙብህ ብዙ ነበሩ፡፡ በዚሁ ቀጥል፡፡
  ታገል

  ReplyDelete
 50. Daniel,

  Slow down, please. You think you are thinking deep. Apparently not.

  No doubt Stone is stone and when you apply it to humans it is definately stone. It is because stone is stone that serves the terrible human without objection. For stone, it ok if you write on it, break it appart, deficate or urinate on it etc. If any brain- carrying human obeys such kinds of atrocities like you and me do at this point, he or she is stone and it is big insult. Humans as humans should not act like stones unless they are sensless, lifeless like stone.

  Lets not be like stones!

  Ameseginalehu

  ReplyDelete
 51. ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ በእድሜ በጸጋ ይጠብቅልኝ፡፡
  ታገል በሀሳብህ እስማማለሁ፡፡
  ድንጋይ ለምንወደው ነገር ብንጠቀምበት እመርጣለሁ፡፡
  ድንጋይ ስድብ መሆን አለበት ብላችሁ የምትገዳደሩት ግን ምን እያላችሁን ነው?
  ስድብ ይቀጥል? እኛ ግን በተረዳ ነገር እንዲህ እናነባለን
  ወደ ኤፌሶን ሰዎች
  4፥29
  ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።

  ወደ ቆላስይስ ሰዎች
  3፥8
  አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ።

  እባክህ በነካ እጅህ ስለውሻና አህያ ምትለንን በለን?
  እንደው በመድኃኔዓለም ውሻ፡አህያ ስድብ መሆን ነበረባቸው?

  ReplyDelete
 52. ሐመር መፅሔት ላይ ‘’ክስ’’ በሚል ርእስ የፃፍከውን እዚህ ቢቀርብስ ዳኒ?

  ReplyDelete
 53. ለኮሜንት ጸሃፊዎች
  እባካችሁ አስተያየት ስትሰጡ ከቀኝም ከግራም እያመዛዘናችሁ ቢሆን
  የጽሁፉ ደጋፊዎችም ምዕመን ሆናችሁ
  ተቃዋሚዎቹም ጠላት
  ይሀ ባህሪያችን ላለፉት አመታት ለሀገራችን ዋላ ቀር መኖን ምክንያት አልሆነም ትላላችሁ

  ReplyDelete
 54. i like you brother. keep it up!!!!!!!! have a nice time to you and all your family.

  ReplyDelete
 55. ዳኒ ጥሩ እይታ ነው፤
  ነገር ግን ለማስተላለፍ የፈለከውን ማንኛውም ቁም ነገር ከእግዚአብሄር የዘላለም ሃሳብ ከሆነው የማዳን እውነት ጋር ማያያዝ ብትችል የበለጠ ጥሩ ይሆናል።
  ሃዋሪያው “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።
  አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ “ እንዳለ
  ዳኒ ጥሩ እይታ ነው፤
  ነገር ግን ለማስተላለፍ የፈለከውን ማንኛውም ቁም ነገር ከእግዚአብሄር የዘላለም ሃሳብ ከሆነው የማዳን እውነት ጋር ማያያዝ ብትችል የበለጠ ጥሩ ይሆናል።
  ሃዋሪያው “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።
  አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ “ እንዳለ

  ReplyDelete