Tuesday, November 30, 2010

ወደ ደረስጌ ማርያም ክፍል ሦስት

         የደረስጌ ዕቃ ቤት
 
                           የወርቅ ከበሮ

 የደረስጌ ካህናት በአንድ ነገር ይመሰገናሉ፡፡ ደጃች ውቤ ከሰጡት ቅርስ እና ንዋያተ ቅድሳት መካከል አንድም እስካሁን አልጠፋም፡፡ በጣልያን ዘመን እንኳን ቤተ ክርስቲያንዋን ለመዝረፍ የመጣውን ጣልያን ቀጥታ ከዚህ በኋላ አልደርስም እነዲል አድርጋዋለች፡፡ በ1928 ዓም መጋቢት ሦስት ቀን ጣልያን በደብርዋ ላይ ያዘነበው የአውሮፕላን ቦንብ እንኳን እሳቱ ጢሱ አልነካትም፡፡

Saturday, November 27, 2010

ወደ ደረስጌ ማርያም ክፍል ሁለትበደረስጌ በር አጠገብ ያሉት እድሜ ጠገብ ዛፎች
 
ብርዳማው የመካነ ብርሃን ሌሊት አለፈ፡፡ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ የወረዳው የባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ባለሞያ የሆነው አደራጀው አካባቢውን የሚጎበኙትን ሁሉ ከቡና በሚመረጠው ፈገግታ ለማስተናገድ ያለው ዝግጁነት ያስቀናል፡፡ እርሱ መካነ ብርሃን ላይ ባይኖር ኖሮ ጉብኝታችን ሁሉ ውኃ ይበላው ነበር፡፡

የደረስጌ ማርያም ካህናት በግብርና ሥራ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡ ክህነትን እንደ ሥራ ማየትኮ በቅርብ ዘመን የመጣ ጠባይ ነው፡፡ ቀደምቶቻችን እያረሱ የሚቀድሱ እና የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡

   ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን


Thursday, November 25, 2010

ጉዞ ወደ ደረስጌ


የስሜን ተራሮች
  ከጎንደር ተነሣን፤ እኔና ሙሉቀን ዘጎንደር፡፡ አንዳንዶቹ የልደታ ምክትል መልአከ ስብሐት ይሉታል፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ስለሆነ፡፡ የምንጓዝበትን መኪና ያመቻቸልኝ የአዲስ አበባው ሙጨ ነው፡፡ ምንም እንኳን 3500 ቢያስሰክፉንም፡፡ ከጎንደር ወደ ጃናሞራ መውጫው በር ብልኮ ይባላል፡፡

መኪናችንን አስፈታትሸን እና ነዳጅ ሞልተን ከብልኮ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ እስከ ዳባት ያለው መንገድ ከጎንደር ተራሮች አንፃር እንደሜዳ የሚቆጠር ነው፡፡ ሜዳ በሌለበት ዳገት ሜዳ ይሆናል ሲባል አልሰማችሁም፡፡

ፀሐይ እና ብርድ ለማሸነፍ ይፎካከራሉ፡፡ በመካከል እኛ ካፖርት በመልበስ እና በማሞቅ ዕንቆቅልሽ እንሠራለን፡፡ የወገራ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችውን አምባ ጊዮርጊስን አለፍናት፡፡ መኪናዋ እህም፣ እህም፣ እህም እያለች ታዘግማለች፡፡ ቻይና እዚህም አለች፡፡ ይህንን የስሜን መንገድ እንደ ጨጓራ ትገለብጠዋለች፡፡ ከጎንደር ወደ ደባርቅ የሚወስደው መንገድ በአዲስ መልኩ እየተሠራ በመሆኑ በተለዋጭ መንገድ እንፈጨዋለን፡፡

Sunday, November 21, 2010

ለቤተ መጻሕፍትዎ

                                              የፒያሳ ልጅ

ደራሲ -  ፍቅሩ ኪዳኔ

አከፋፋይ - ዓይናለም የመጻሕፍት መደብር

ዋጋ - 70 ብር

የታተመበት ዓመት - 2001 ዓም

ከጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ለብዙ ዘመናት የሠራው፤ የመጀመርያውን የስፖርት ዘገባ በሬዲዮ በቀጥታ ያስተላለፈው፣ በኢንተርናሽናል ስፖርት ፌዴሬሽኖች የፕሬስ ኮሚሲዮን እና በ1986 የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ የፊፋ የአንዱ ምድብ የፕሬስ ኃላፊ የመጀመርያው ጥቁር፤ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበራት መሥራች ፍቅሩ ኪዳኔ በሚያምር የአራዳ ቋንቋ ስለ ፒያሳ ልጆች በ457 ገጾች ያወራናል፡፡

Wednesday, November 17, 2010

መልስ በሞባይል

እስኪ እዚያው ጎንደር ውስጥ አንድ ቀን እናሳልፍና ዐፄ ፋሲል ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ቁጭ ብለን ከመምህራኑ ጋር እናውጋ፡፡

እኔ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ስማር በፈተና ሰዓት የሆነ አንድ ነገር ሁሌም ትዝ ይለኛል፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥ አንድ ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡ ከእርሱ ቀድተው ለማለፍ የተዘጋጁ ደግሞ ብዙ ተማሪዎች፡፡ ታድያ ፈታኙ መምህር ጥብቅ ሆነና ዓይኑን እንደ ሰጎን ዓይን ተከለባቸው፡፡ ሊያነቃነቅ አልቻለም፡፡ የፈተና ማብቂያው ሰዓት ደግሞ እንደ ጎርፍ እየተንደረደረ ይነጉዳል፡፡

ከጎበዙ ተማሪ አጠገብ ያለው አንዱ ተማሪ አንዳች ነገር ዘየደ፡፡ መልሱን ከጎበዙ ተማሪ ቀዳና በአንድ ቁራጭ ወረቀት ላይ አሰፈረው፡፡ ከዚያም ከእርሱ ወንበር ባሻገር ያለው ተማሪ መምህሩን ለጥያቄ ጠራው፡፡ መምህሩ ጎንበስ ብሎ ያኛውን ተማሪ ሲያስረዳ ይኼኛው ተማሪ የመልሱን ወረቀት ከመምህሩ ጀርባ ላይ በፕላስተር ለጠፈው፡፡

Tuesday, November 16, 2010

አርዮስ - በሁለት ሰዓልያን ዓይን

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥዕል ታሪክ የሰዓሊዎችን ኅሊና ከሚስቡት ክስተቶች አንዱ ጉባኤ ኒቂያ ነው፡፡ በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ ላይ ጉባኤ ኒቂያ በሰዓልያኑ ዓይን በሚገባ ይገለጣል፡፡ ለዛሬ ሁለት ሰዓልያን እንዴት እንደገለጡት እንይ፡፡ የአዞዞ ተክለ ሃይማኖት እና የደረስጌ ማርያም ሰዓልያን አርዮስ በጉባኤ ኒቂያ እንዴት እንደተወገዘ በሚከተሉት መልኩ ገልጸውታል፡፡


የሰዓልያኑን ሥዕል ለመረዳት የጉባኤ ኒቂያን እና የአርዮስን ታሪክ በሚገባ ማወቅን ይጠይቃል፡፡
በደረስጌ ማርያም ሰዓሊ ዓይን


በአዞዞ ተክለ ሃይማኖት ሰዓሊ ዓይን

Sunday, November 14, 2010

ለቤተ መጻሕፍትዎ

የመጽሐፉ ርእስ    ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀት

አዘጋጅ    ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ሥላሴ ተፈራ

አሳታሚ   የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ

ዘመን 2002 ዓም

የገጽ ብዛት 320

ስለ ደራሲው

ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ሥላሴ የቤተ ክህነትን ትምህርት በሚገባ የተማሩ ሊቅ ናቸው፡፡ አዲስ ዓለም ማርያም ሄደው ንባብ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ እና ድጓ ተምረዋል፡፡ ዋሸራ ደግሞ ቅኔ ከነ አገባቡ ቀስመዋል፡፡ ጎንደር ላይም አቋቋም፣ መዋሥዕት እና ዝማሬ ተምረዋል፡፡ በአዲስ አበባ በኣታ ለማርያም ገዳም የሐዲሳት ትርጓሜ ተምረው በ1965 ዓም በድፕሎማ ተመርቀው ዲፕሎማቸውን ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ አግኝተዋል፡፡ በዘመናዊ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩ ሲሆን ጥናት እና ምርምር ማድረግን እንደ ባህል ይዘውታል፡፡

ሊቀ ጉባኤ ለትምህርት በተጓዙባቸው ቦታዎችም ሆነ በኋላ ለምርምር በተጓዙባቸው ቦታዎች የሚገኙትን ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት በማገላበጥ ስለ ብራና መጻሕፈት አዘገጃጀት፣ አጻጻፍ፣ እና አጠባበቅ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

ስለ መጽሐፉ

መጽሐፉ ከ10ኛው መክዘ ያሉትን የብራና መጻሕፍት ይዳስሳል፡፡ ስለ ግእዝ ፊደላት፣ ስለ ብራና መጻሕፍት አስፈላጊነት፣ በጥንታዊው የግእዝ ሥነ ጽሐፉፍ ስለሚገኙ የጽሑፍ ምልክቶች፣ስለ ቁም ጸሐፊዎች፣ ስለ ብራና መጻሕፍት አቀማመጥ እና ለብራና መጻሕፍት ማዘጋጃ ስለሚያስፈልጉ መሣርያዎች ዝርዝር መረጃ ይሰጣል፡፡

እግረ መንገዱን በጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ስለሚገኙ ተጨማሪ አገራዊ መረጃዎች ዕውቀት እንገበይበታለን፡፡ የትኞቹ የብራና መጻሕፍት ምን እንደያዙ እና የት እንደሚገኙ ይናገራል፡፡

ስለ አባቶቻችን የብራና መጻሕፍት የተሻለ ዕውቀት ለማግኘት ይህንን መጽሐፍ ከማንበብ የተሻለ አማራጭ የለውም፡፡

መጽሐፉን በየመጻሕፍት መደብሩ ማግኘት ይቻላል፡፡

መልካም ንባብ


Saturday, November 13, 2010

ጎንደር ስትረሳ እና ስታስታውስ

ጎንደር ቁስቋም በጥንታዊው ዕቃ ቤት ውስጥ
ዘመናዊ ሙዝየም ገንብታለች
አሁን የጎንደር ከተማ መነቃቃት ጀምራለች፡፡ መንገዶቿ አስፓልት እየለበሱ ነው፡፡ ሪል እስቴቶችም ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ ታላላቅ ሕንፃዎችም እየበቀሉ ናቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ሙዝየሞችን በማሠራት ላይ ናቸው፡፡

ጥንታዊቷ የእቴጌ ምንትዋብ ቤተ ክርስቲያን ጎንደር ቁስቋም በጥንታዊው ዕቃ ቤት ውስጥ ዘመናዊ ሙዝየም ገንብታለች፡፡ የአስራ ስድስተኛውን እና የሥራ ሰባተኛውን ዘመን የሚያሳዩ ንዋያተ ቅድሳት፣ የወግ ዕቃዎች እና መጻሕፍት ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ምንም እንኳን ቦታው ጠበብ ያለ ቢሆንም የአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሕንፃ በመሆኑ ጉብኝቱን በታሪክ ላይ መሄድ ያደርገዋል፡፡

አስጎብኝው መሪጌታ ዳንኤልም መጻሕፍቱን ያነበቡ፣ታሪኩን የጠገቡ፣ አክበሮትን ከትኅትና ጋር የተላበሱ መሆናቸው በእቴጌ ምንትዋብ የግብር አዳራሽ የተጋበዛችሁ ያስመስላችኋል፡፡ ሕንፃው ሲሠራ መስኮት ስላልነበረው መብራት በማይኖር ጊዜ ጧፍ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ቅርሶቹን ለእሳት አደጋ ሊያጋልጣቸው ይችላልና በተለ ይም በአሜሪካ እና በአውሮፓ የምትገኙ የቅርስ እና የታሪክ ወዳጆች በኤሌክትሪክ ቻርጅ ተደርጎ ለረዥም ሰዓት ሊያገለግል የሚችል ጠንካራ ባትሪ ብትልኩላቸው ስማችሁ ሁልጊዜ በጸሎት ይታሰብ ነበር፡፡

የእቴጌ ምንትዋብ አዳራሽ እና ቤተ መንግሥት በደርቡሽ ጊዜ ፈርሶ ትዝታን ብቻ እያሳየ ቆሟል፡፡ የዓባይን መነሻ አገኘሁ ያለው የ17ኛው መክዘ አሳሽ ጄምሰ ብሩስ የኖረው እዚህ ቦታ ነው፡፡ እቴጌ ምንትዋብ ልዩ ክብካቤ ታደርግለት ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠናበት የነበረው ቤት ዛሬ ፍርስራሹ ይታያል፡፡

በአጣጣሚ ሚካኤልም ሙዝየም ተከፍቷል
እንደ ቁስቋም ሁሉ በአጣጣሚ ሚካኤልም ሙዝየም ተከፍቷል፡፡ በተለይም የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት ጎብኝዎች ከሚወጡበት በር አጠገብ መከፈቱ ለጎብኝዎቹ ምቹ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

ጎንደር ላይ ሀገረ ስብከቱም ሙዝየም ከፍቷል፡፡ በተለይም የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ሊቁ የሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ/ አቡነ ጴጥሮስ/ ቅርሶች ከአደጋ ተርፈው ለሙዝየም መብቃታቸው አስደናቂ ነው፡፡ ታሪኩን እና ቅርሱን ጠብቀው ለዚህ ወግ መዓርግ ያበቁትን አባ ሙሉንም ያስመሰግናቸዋል፡፡ በገንዘብ እንግዛዎት ተብለው እምቢ አሉ፡፡ በባለ ሥልጣናት ትእዛዝ ከደመወዝ እና ከሥራ ቢከለከሉም ቅርሱን ያለ ተረካቢ አልሰጥም አሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ሕዝብ እና መንግሥት ባለበት ለትውልድ አስረከቡ፡፡ ምናለ እንደ አባ ሙሉ ያለ አሥር ቢሰጠን፡፡

የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት እያንዳንዳቸው ሙዝየም ሊኖራቸው በተገባ ነበር፡፡ በውስጣቸው ገና ትውልድ ያላያቸው ብዙ ቅርሶች ይዘዋልና፡፡ መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም የተተከለችበትን ሦስት መቶኛ ዓመት በቅርቡ ልታከበር በዝግጅት ላይ ናት፡፡ ከዚህ በዓል በተያያዘም ሙዝየም ለመገንባት አስበዋል፡፡

ጎንደር ላይ ሁለት አሳዛኝ ቅርሶች አሉን፡፡

ከሸዋ መጥተው ጎንደር ወንበር ዘርግተው ያስተምሩ የነበሩ አለቃ ወልደ አብ የተባሉ መምህር ነበሩ፡፡ መቼም በጥንቱ ባህላችን ሰው ሞያው እንጂ ሀገሩ አይጠየቅም፡፡ እር ሳቸው ደግሞ ደረስጌ ሄዱና መምህር ወልደ ሚካኤል የተባሉትን አምጥተው በትምህርት አሳደጓቸው፡፡ አለቃ ወልደ አብ ሲያርፉ መምህር ወልደ ሚካኤልየ ግምጃ ቤት ማርያምን ትምህርት ቤት ተረክበው ማስተማር ቀጠሉ፡፡

መምህር ወልደ ሚካኤል እያስተማሩ እያሉ ደርቡሽ ጎንደርን ሊያቃጥል መጣ፡፡ ብዙዎቹ ሲሸሹ እርሳቸው ግን «መከራ ታዝዞብናልና እናንተ ሽሹ፤ እኔ ግን ጉባኤ አላጥፍም» ብለው እያስተማሩ እያሉ ከዘጠኝ ተማሪዎቻቸው ጋር በደርቡሽ ሰይፍ ተሰይፈው ዐረፉ፡፡

እኒህ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ መምህር የተቀበሩት
 እዚያው ግምጃ ቤት ማርያም ከግቢው በር በስተ ቀኝ በኩል ነው
እኒህ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ መምህር የተቀበሩት እዚያው ግምጃ ቤት ማርያም ከግቢው በር በስተ ቀኝ በኩል ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምንም ዓይነት ምልክት የለውም፡፡ እንዲህ ዋኖቻችንን እየረሳን ነገ ሌላ «ዋና» ከየት እናገኛለን፡፡ የደብሩም ሰዎች ሆኑ ሌሎቻቸን ቢያንስ መምህር ወልደ ሚካኤል ለሃይማኖታቸው እና ለጉባኤያቸው ሲሉ ተሰውተው እዚህ ቦታ ላይ መቀበራቸውን ምልክት ልናደርግላቸው ይገባል፡፡

እዚያው ግምጃ ቤት ማርያም በጀርባ በኩል ደግሞ እንደዚሁ በመረሳት ላይ ያለ ታሪክ አለ፡፡ የዐፄ ቴዎድሮስ አማካሪ የነበረው ፕላውዴን የተቀበረው ግምጃ ቤት ማርያም ነው፡፡ ፕላውዴን በምጥዋ የእንግሊዝ ቆንስል ሆኖ ነበር የተሾመው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሲነግሡ ወደ ጎንደር መጣና ከንጉሡ ጋር ተገናኘ፡፡ ንጉሥ ቴዎድሮስም በመልካም ሁኔታ ተቀበሉት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከእርሳቸው አልተለየም ነበር፡፡


ፕላውዴን የተቀበረበት ቦታ
በብረት አጥር ታጥሮ ተቀምጧል፡፡
ነገር ግን የሰርዶ ዓይነት በቅሎበት
 ሙጃው እንጂ መቃብሩ አይታይም

በመካከል ታመመና ለሕክምና ወደ ሀገሩ ሲሄድ የልጅ ጋረድ ሽፍቶች አገኙትና በደፈጣ ጦር ክፉኛ አቆሰሉት፡፡ ጥቂት ቀናትም ቆይቶ በጥር ወር 1853 ዓም ዐረፈ፡፡ ግምጃ ቤት ማርያምም ተቀበረ፡፡

ፕላውዴን የተቀበረበት ቦታ በብረት አጥር ታጥሮ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን የሰርዶ ዓይነት በቅሎበት ሙጃው እንጂ መቃብሩ አይታይም፡፡ በላዩ ላይ የነበረው ጽሑፍም ጠፍቷል፡፡ ይህ ቦታ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሚያሳዩት ቦታዎች አንዱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለወዳጆቿ የምትሰጠውን ቦታም ያሳያል፡፡ ፕላውዴን እንግሊዛዊ ሆኖ እንደ ኢትዮጵያውያን የኖረ ነው፡፡ ታድያ ምነው ዝክረ ታሪኩን ዘነጋንበት?

ጎንደር ላይ እንቆይ፤ ሌላም እናያለን፡፡ ለመሆኑ በጎንደሩ ዐፄ ዮሐንስ ዘመን በዕንባ ስለ ተሳለችው ሥዕል ሰምተው ያውቃሉ?


Wednesday, November 10, 2010

የእጨጌ ቤቶች

የጎንደር ከተማ ካሏት ጥንታውያን ቅርሶች መካከል የቀድሞውን ዘመን የታላላቅ ሰዎች የቤት አሠራር ጥበብ የሚያሳዩት የእጨጌ ቤቶች አንደኞቹ ናቸው፡፡ ስለ ጎንደር ከተማ ቅርሶች ሲነሣ ስማቸው የማይታ ወሰው እነዚህ ቅርሶች ተከባካቢ በማጣቸው የተነሣ እየፈረሱ እና ከታሪካቸው ጋር ለማይገናኝ አገልግሎት እየዋሉ ነው፡፡

የጎንደር ከተማ ስትነሣ የፋሲል ግንብ፣ የፋሲል መዋኛ እና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ናቸው በብዛተ የሚጠቀሱት፡፡ በከተማዋ ወስጥ ግን ከምድር በላይም ሆነ ከምድር ሥር ያልታወቁ እና የተዘነጉ አያሌ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከአርባ አራቱ አድባራት መካከል ወደ ሰባት ያህሉ ጠፍ ሆነው ፍርስራሻቸው ቀርተዋል፡፡ የአንዳንዶቹ ቦታቸው ባለመከለሉ ለአሳዛኝ ግፍ ተዳርገዋል፡፡ ለምሳሌ የሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ቦታ ዛሬ መጸዳጃ ቤት ሆኗል፡፡

የዐፄ ዮሐንስ ቀዳማዌ ዜና መዋዕል እንደሚነግረን በ1672 ዓም ዮሐንስ የተባሉ የአርመን ጳጳስ በግብፅ በኩል አድርገው የአቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተረፈ ዐፅም ይዘው ወደ ጎንደር መጥተው ነበር፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተስፋፋው ገዳማዊ ሕይወት መሠረት የነበሩ እና በኋላም አርመን /ቆጵሮስ/ ሄደው ያረፉ አባት ናቸው፡፡

ዜና መዋዕሉ እንደሚነግረን ይህ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዐፅም ያረፈው በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ይህንን ታሪክ የሚያውቅ የአካባቢው ሽማግሌም ሆነ ሊቅ አላጋጠመኝም፡፡ ምናልባትም ስለ ጎንደር አድባራት ጥናት በማድረግ ላይ ያለው ኢንጅነር መላኩ እዘዘው ይደርስበት ይሆናል፡፡

እንደላይኞቹ ቅርሶች እየተዘነጉ ያሉት ሌሎቹ ሀብቶቻችን የእጨጌ ቤቶች ናቸው፡፡ የእጨጌ ቤቶች ክብ ሆነው በትናንሽ ድንጋዮች የተገነቡ ናቸው፡፡ ድንጋዮቹ የተያያዙት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በሚቦካ ጭቃ መሆኑን ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ ከግድግዳው ወገብ ከፍ ብሎ የግድግዳ አካፋይ የሆኑ ድንጋዮች ወይንም እንጨቶች ይገቡባቸዋል፡፡ የጣራው መያዣም በእነርሱ ላይ ያርፋል፡፡

ቀድሞ የእነዚህ ቤቶች ጣራ ሣር እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ቆርቆሮ ለብሰዋል፡፡


ዋናው እና ትልቁ የእጨጌ ቤት በወራሾቹ አማካኝነት ተሽጦ የሙስሊሞች መስገጃ ሆኗል

እነዚህ ቤቶች ለእጨጌዎች እና ለተከታዮቻቸው ማረፊያ የተገነቡ ናቸው፡፡ ቅርፃቸውም ቤተ ንጉሥ የሚባ ለውን የክብ ቅርጽ ይዟል፡፡ የአንዳንዶቹ ቅሬት እንደሚገልጠው ጥንት ጉልላት ወይንም መስቀል የነበራቸው ይመስላል፡፡

ደብረ ብርሃን ሥላሴ የሚገኘው የደብሩ የታሪክ መዝገብ የመጀመርያው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ወደ ጎንደር የመጡት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በነገሠ በሦስተኛው ዓመት መሆኑን ይገልጣል፡፡ ይህም በ1603 ዓም መሆኑ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን ሥላሴ የታሪክ መዝገብ እጨጌው የመጡበት ምክንያት ሱስንዮስ ደንቀዝ ላይ ቤተ መንግሥት ሲቆረቁር ለደብረ ሊባኖስ ይገባ የነበረው ግብር በመቅረቱ እነደሆነ ይገልጣል፡፡ እጨጌው ወደ ጎንደር የመጡት ከ47 መነኮሳት ጋር ነበር፡፡ መልእክተኞቹ ጉዳያቸውን ለዐፄ ሱስንዮስ አቀረቡ፡፡ ንጉሡም ልምከርበት ጊዜ ስጡኝ አላቸው፡፡ እነርሱም ቆዩ፤ ወዲያውም ክረምት ገባ፡፡ ንጉሡ ለመነኮሳቱ መክረሚያ በአካባው ያለ ሀገር ሰጣቸው፡፡

ክረምቱ ካለፈ በኋላ ሱስንዮስ ውሳኔውን ነገራቸው፡፡ በሸዋ ያለው ለንጉሡ የሚገባው ግብር ለደብረ ሊባኖስ እንዲሆን፣ እርሱ በደንቀዝ ከተማ ስለሚመሠርት እጨጌው ታቦት ይዘው ወደዚያ እንዲመጡ ነገራቸው፡፡

እጨጌው እና ማኅበሩ ታቦታቸውን ይዘው በአምሐራ በኩል መጡ፡፡ በወቅቱ እጨጌ የነበሩት በትረ ወንጌልም ታምመው በአምሐራ ሀገር ሞቱ፡፡ በአትሮንሰ ማርያምም ተቀበሩ፡፡ ማኅበሩ ሁሉ ታቦቱን እና መስቀሉን ይዘው መጥተው ዐፄ ሱስንዮስን በእንፍራ ንዝ አገኙት፡፡ የእጨጌውንም ሞት ነገሩት፡፡ ታላቅ ኀዘንም ተደረገ፡፡ ማኅበሩም የሚተካውን እጨጌ መርጠው አቀረቡ፡፡ አባ አብርሃምም እጨጌነት ተሾመ፡፡

የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ማረፊያ ፈርቃ ላይ ተደረገ፡፡ በዚያም እያሉ እጨጌ አብርሃም ዐርፈው እጨጌ ዘሚካኤል ተሾሙ፡፡ የሃይማኖት ክርክር እና ጦርነት የተነሣው በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡ እጨጌ ዘሚካኤል በመከራው ዘመን ዐርፈው እጨጌ በትረ ወንጌል ተተኩ፡፡ አልፎንዙን የተከራከሩትና

ረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ
ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ

ተብሎ የተቀኘላቸው እርሳቸው ናቸው፡፡

ዐፄ ፋሲል ለፖርቹጊዞች ተሰጥቶ የነበረውን ርስት ለደብረ ሊባኖሶች መለሰላቸው፡፡ እጨጌው እና መነኮሳቱም ወደ አዞዞ መጥተው ዛሬ አዞዞ ተክለ ሃይማኖት በሚባለው ቦታ ሠፈሩ፡፡ ከዚያም ዐፄ ፋሲል የጎንደርን ከተማ ሲቆረቁሩ የእጨጌውም ቦታ ወደ ጎንደር ተዛወረ፡፡ እንግዲህ የደብረ ሊባኖስ እጨጌዎች ወደ ጎንደር የመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡

እጨጌዎቹ በጎንደር ከተማ ሲቀመጡ ይጠቀሙባቸው የነበሩት ቤቶች ናቸው «የእጨጌ ቤቶች» የሚባሉት፡፡ እኔ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ሆነን ባደረግነው አሰሳ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ቤቶችን አይተናል፡፡ ጠንካራ ፍተሻ እና ጥናት ቢደረግ ግን ከዚህ የሚበልጡ ማግኘት ይቻላል፡፡

አንዳንዶቹ ቤቶም ማድቤቶች ሆነው ለእሳት ተዳርገዋል፤ ሌሎቹም መጠጥ ቤቶች ሆነዋል፡፡ ዋናው እና ትልቁ የእጨጌ ቤት በወራሾቹ አማካኝነት ተሽጦ የሙስሊሞች መስገጃ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ ግድግዳቸው በስሚንቶ ተገርፏል፤ ሌሎች ቀለም ተቀብተዋል፡፡

እነዚህ ቤቶች የሀገሪቱ ታሪክ አካል ናቸው፡፡ ለጎንደር ከተማ ደግሞ ፈርጦች ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን የነበረውን የቤት አሠራር ጥበብ ሕያው ሆነው ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ አያያዛቸው ከቀጠሉ ግን ተረት ይሆናሉ፡፡ ሲሆን ወራሾቹ ካሳ ተክፍሏቸው ቤቶቹ በቅርስነት ብቻ እንዲጠበቁ ቢደረግ፤ ያም ካልተቻለ አጠቃቀማቸው ታሪካዊ ይዞታቸውን በማይለቅበት መንገድ እንዲሆን ቢደረግ መልካም ነው፡፡

ስለእነዚህ ቤቶች መረጃ በመስጠት የተባበሩኝን ኢንጂነር መላኩን፣ ዶ/ር ዳኜን እና ዲያቆን ሙሉቀንን እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡


Monday, November 8, 2010

ዓይናማው የአዞዞ ሰዓሊ

በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት የተተከለውን የአዞዞ ተክለ ሃይማኖትን ቤተ ክርስቲያን ሲጎበኙ በሦስት ነገሮች ይደነቃሉ፡፡ የመጀመርያው ከጎንደር ዘመን በፊት የነበረውን የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር የሚያዩበት አጋጣሚ ስለሚፈጠርልዎት ነው፡፡ ምንም እንኳን በየዋሕነት አንደኛው ግድግዳ ቀለም ተቀብቶ የታሪ ልዋጤ ቢደርስበትም በአንድ በኩል ግን ከነ ምልክቱ ያዩታል፡፡ በተለይም ከግድግዳው በላይ የተለጠፉት የነገሥታቱ ምልክቶች ጥንታዊነቱን ያሳያሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ዘመናት ተጠብቀው የቆዩት ቅርሶች ናቸው፡፡ ከግራኝ በኋላ እና ከጎንደር በፊት ያለውን ጥበብ የሚያሳዩ መጻሕፍት፣ደወሎች፣ነጋሪቶች፣አልባሳት እና መስቀሎችን ታገኛላችሁ፡፡

ሦስተኛው የዓይናማው የአዞዞ ሰዓሊ ሥዕሎች ናቸው፡፡ ስሙን በሥዕሎቹ ላይ ያላሰፈረው የ1960ው ይህ ዓይናማ ሰዓሊ መጽሐፍ፣ ታሪክ እና ባህልን ልቅም አድርጎ ያውቅ እንደነበር ሥዕሎቹ ይመሰክራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ ቅደም ተከተል ከነ ስማቸው ሥሎ አቆይቶናል፡፡ የደብረ ሊባኖስን እጨጌዎች ከቅደም ተከተላቸው እና ከስማቸው ጋር የቤተ መቅደሱን ዙር ግድግዳ ሞልቶ በቅርስነት አቆይቷቸዋል፡፡ በጣና ገዳማት ውስጥ እንደምናየውም በእርሱ ዘመን የነበረውነ ተግባረ እድ የሚያመለክቱ ዘመን ቀረስ ሥዕሎችንም በመቅደሱ በር ግራ እና ቀኝ ስሏቸዋል፡፡

በአዞዞ ከሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች አንዱ በጎንደር የነበረው የፕሮቴስታንት ሚሲዮናዊ የማርቲን ፍላድ ስም የተጻፈበት ደወል ነው፡፡ «የፍቅር መንሻ፣ ከማርቲን ፍላድ» ይላል፡፡ ማርቲን ፍላድ (1831 - 1915 እኤአ) በጎንደር የነበረ ጀርመናዊ ሚሲዮን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ በመተርጎሙ ይታወቃል፡፡ ማርቲን ፍላድ በተለይም ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋር በፍቅርም በጠብም ሠርቷል፡፡ እንደ እኔ ግምት ይህንን ደወል የሰጣቸው ለዐፄ ቴዎድሮስ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በደወሉ ላይ «Gegossen von Christian vogt In Stuttgart 1879 » ይላል፡፡ ምናልባት ጀርመንኛ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ታድያ ምናለ ጀርመን አያሌ ወዳጆች አሉን፡፡ አንዱ ተርጉሞ ይነግረን ይሆናል፡፡

ከአዞዞ ሳልወጣ አንድ ሃሳብ ላቅርብ፡፡ «የአዞዞ ታሪካዊ ቦታዎች ወዳጆች ማኅበር» የሚል አቋቁመን እነዚያን በመጥፋት ላይ ያሉትን ቅርሶች ብንጠብቅ ምናለ፡፡ ዐቅሙ እና ፍላጎቱ ያለው በፌስ ቡክ በኩል ያሰባስበን እና አንዳች ሥራ እንሥራ፡፡ ያለ በለዚያ «ጽጌረዳ እና ደመና» የሚለው የከበደ ሚካኤል ትንቢታዊ ግጥም ይደርስብናል፡፡

ከአዞዞ እንውጣና ወደ ዋናው ከተማ ወደ ጎንደር እንግባ፡፡ ለመሆኑ ጎንደር ከተማ ውስጥ ስላሉት «የእጨጌ ቤቶች» ሰምተው ያውቃሉ? በኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡

Sunday, November 7, 2010

አዞዞ ትጣራለች

 አሁንም አዞዞ ላይ ነው ያለሁት፡፡
ከግራኝ ወረራ በኋላ እና ከጎንደር ዘመን በፊት ከነበሩት የመንግሥት መቀመጫ ከተማዎች አንዷ ናት አዞዞ፡፡ ምናልባትም ከጎንደር በፊት የመጨረሻዋ ከተማ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይህንን ታሪኳን የሚመሰክሩ አያሌ ጥንታውያን ቅርሶች ከመሬት በላይ እና ከመሬት በታች ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል በራሳችን ላይ እንደምንቀልድ ለማወቅ የፈለገ ሰው አዞዞ የቀበረቻቸውን እና እንደ ዋዛ የጣለቻቸውን ቅርሶች መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡
 
ከጎንደር ዘመን በፊት ከነገሡት ነገሥታት መካከል ኃያል የነበረውና ለሃይማኖት ግጭት መነሻ የሆነው የዐፄ ሱስንዮስ የአዞዞ ቤተ መንግሥት እየፈራረሰ ይገኛል፡፡ ከፊሉን ቤተ መንግሥት መሬት ውጦታል፡፡ ከፊሉን ደግሞ የአካባቢ ከብቶች ይታከኩታል፡፡ ገበሬዎችም ያርሱበታል፡፡ ዙርያውን ዳዋ ውጦት ለቅርሶቻችን ግዴለሽ መሆናችንን ይመሰክርብናል፡፡

Saturday, November 6, 2010

ከአዞዞ እስከ ጃናሞራ

ሼህ አብደላስጥ አባ ከርቤ

ወደ ጎንደር ከተማ ልትገቡ ጥቂት ሲቀራችሁ አዞዞ የተባለውን ጥንታዊ ከተማ ታገኙ ታላችሁ፡፡ ጎንደር ከመቆረቆሯ በፊት የተከተመው ይህ አካባቢ ይበልጥ የሚታ ወቀው በአዞዞ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ ከ300 ዓመታት በፊት የተተከለው ይህ ታላቅ ደብር ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር የቆየ ግንኙነት አለው፡፡ ታሪኩን በነገው ዕለት እተርክላቸኋለሁ፡፡ ለዛሬ ወደ ሼህ አብደላ ሰጥ አባ ከርቤ ልውሰዳችሁ፡፡

የአካባቢው አፈ ታሪክ እንደሚናገረው እኒህ ሰው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበሩ ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን አዞዞ ላይ የሱስንዮስን እምነት አልቀበል ያሉ 500 የአዞዞ እና የአካባቢው መነኮሳት ታርደዋል፡፡ እነርሱ የታረዱበት ቦታ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ ነበር፡፡ እኒህ ሰው ከሩቅ ሀገር ወደ ጎንደር ሲመጡ በቦታው የተተከለው ቀስተ ደመና ይታያቸዋል፡፡ በነገሩ ተገርመው ወደ ቦታው ሲመጡ መነኮሳቱ ሃይማታችንን አንለውጥም ብለው እየታረዱ ነው፡፡ ሼህ አብደላም ይህ በረከት አያምልጠኝ ብለው ቀረቡ፡፡ አንገታቸውንም ለሰይፍ ሰጡ፡፡ ወዲያውም ከሰማዕታት ጋር ተቆጠሩ፡፡ የተቀበሩበት ቦታ ከአዞዞ ፊት ለፊት ተራራው ላይ ይታያል፡፡ መታሰቢያቸው በየዓመቱ ትንሣኤ በዋለ በሦስተኛው ቀን ይደረጋል፤ እስላሞቹም ክርስቲያኖቹም በቦታው ይገኛሉ፣ ብለው የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል፡፡

አስደናቂው የሼህ አብደላስጥ አባ ከርቤ ታሪክ ይበልጥ ሊጠና የሚገባው ይመስለኛል፡፡

አዞዞ ተክለ ሃይማኖት

Tuesday, November 2, 2010

ድንጋይ ስድብ ነው ወይ?

አንዳንድ ጊዜ በተለምዶ የተቀበልናቸው፤ እኛም ሳንመረምር ዝም ብለን የምናደርጋቸው እና የምንናገራቸው ነገሮች፣ የያዙት እውነታ ከሚታወቀው በተቃራኒ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ አለ፡፡ ትምህርት የማይገባውን፣ ሰነፉን እና ደደቡን፣ ሥራ ጠሉን እና ዘረጦውን ለመግለጥ «እገሌ ድንጋይ ነው» እንላለን፡፡ የሌላውን ሀገር አላውቅም እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንዲያ ብሎ መሳደብ እና ድንጋይን ለውጥ ለሌለው፣ ለሰነፍ እና ለሥራ ጠል አእምሮ ምሳሌ ማድረግ የምንችል አይመስለኝም፡፡