Tuesday, October 26, 2010

እርሻውን ማን ያርመው ?

ከሀገራችን ገበሬ ከምንማራቸው ትምህርቶች አንዱ እርማት ነው፡፡ ገበሬው እንደ አካሉ የሚወደውን መሬት ገምሶ ከስክሶ፣ አርሶ አለስልሶ ይዘራዋል፡፡ ዘሩ ብቅ ሲል ከየት መጣ ያልተባለ አረምም አብሮ ብቅ ይላል፡፡ ታድያ ጀግናው ገበሬ፣ አርበኛው ገበሬ፣ ቆፍጣናው ገበሬ፣ አርሶ በሌው ገበሬ፣ ትእግሥተኛው ገበሬ አረሙን እንዳየ ለስሙ አይደለም የሚጨነቀው፡፡

የጀግናውን እርሻ እንዴት አረም ገባበት፣ የአርበኛውን ማሳ እንዴት አረም ደፈረው፣ የቆፍጣናውን መሬት እንዴት አረም ሄደበት እባላለሁ ብሎ አይጨነቅም፡፡ ሲዘራ ምርጡን ዘር እንደ ዘራ ያውቃል፤ አበጥሮ አንጠርጥሮ እንደዘራ ያውቃል፡፡ እርሱ አረሙን እንዳልዘራው ያውቃል፡፡ አረም ግን ይበቅላል፡፡

ገበሬው ለእርሻው እንጂ ለስሙ አይጨነቅም፤ ለፍሬው እንጂ ለስሙ አይንገበገብም፣ ለምርቱ እንጂ ለስሙ ጊዜ አያባክንም፡፡ አረም የለም፤ አረምም አልበቀለም፤ የኔ እርሻ ምርጥ ዘር ተዘርቶ ምርጥ ዘር ብቻ ነው ያበቀለው፤ ዓይኔን ግንባር ልቤን ደረት ያርገው ብሎ ድርቅ አይልም፡፡ የገበሬው እምነት አንድ ነው፡፡ አረም ሊበቅል ይችላል፤ ግን ሊታረምም ይችላል፡፡ ከተቻለ አረም እንዳይበቅል ይደረጋል፡፡ ከበቀለ ግን አረም ነው ተብሎ በግልጽ ይታረማል፡፡ የስንዴን ስም ላለማጥፋት ሲባል አረም ስንዴ ነው ተብሎ አይታወጅም፡፡

የገበሬው የመጀመርያ ሥራ አረሙን ከምርቱ መለየት ነው፡፡ የተለያየ ጠባይ፣በልዩ ልዩ መንገድ የሚመጡ አረሞች አሉ፡፡ ወፍ የሚዘራቸው፤ ከመሬቱ ውስጥ የነበሩ፣ ምናልባት ከዘር ጋር ሳይታዩ የተቀላቀሉ፣ ጠላት ለተንኮል የዘራቸው፣ ነፋስ ያመጣቸው፣ ሌሎችም ሌሎችም፡፡ ታድያ ጎበዙ ገበሬ ያውቃቸዋል፤ በግብር ብቻ ሳይሆን በስምም ይለያቸዋል፡፡

ገበሬው የአረሙን ዓይነት እና መጠን ያይና ከቻለ ራሱ ብቻውን ያርመዋል፣ካልቻለ ቤተሰቡን ሰብስቦ ያርማል፤ ከዚያም በላይ ከሆነበት ቀየውን ደቦ እና ወንፈል ይጠራል፡፡ «እንዲህ ባለ ቀን አረም ስለማርም እርዱኝ» ብሎ በይፋ ሲናገር አያፍርም፡፡ እንዲያውም ማሳውን ለአረም ባለማስገበሩ ይኮራል፡፡ «አይ ቆምጫናው እጁን አይሰጥምኮ» ተብሎ ይመሰገንበታል፡፡

የቀየው ወዳጆቹም እንዴት በርሱ እርሻ አረም ተገኘበት ብለው አያሙትም፤ አያሳማማ፡፡ እንዲያውም ማልደው ወገባቸውን አሥረው ለአረም ይሠማሩለታል፡፡ ድምፀ መልካሞቹም

           የወይኖ ጌታ የስመ ጥሩ

          የጫሎ ጌታ የስመ ጥሩ

             ማዕበል የመታው ይመስላል ፈሩ

           የወይኖ ጌታ የቀዩ በሬ

          የጫሎ ጌታ የግራ በሬ

         እርፉ እስኪናጋ ኮልኳይ ገበሬ

         አስተራረሱን አገር ያወቀው
 
        ጎተራው በጤፍ የተጨነቀው፡፡

         ከወይኖ ጌታ የገባች አረም

         ከጫሎ ጌታ የገባች አረም

       ዘሯ አይገኝም እስከ ዝንታለም፡፡

እያሉ ያቀነቅኑለታል፡፡ ያወድሱታል፡፡ እውነታቸውን ነው ገበሬው እርሻዬ ሊታረም ይገባዋል ካላለ፤ አረም እና ዘር ካልለየ፣ አረሙንም በጊዜ ካላረመ ምኑን ጀግና ገበሬ ሆነው፡፡ የጀግና ገበሬ አንዱ መለኪያኮ አረሙን መለየት እና በጊዜ ማረም ነው፡፡

ያለበለዚያማ አረሙ ዘሩን ይውጠውና የእህል እርሻ መሆኑ ቀርቶ የአረም እርሻ ይሆናል፡፡ መሬቱም ይበላሻል፤ ገበሬውም ይራባል፤ አገርም ትጎዳለች፡፡ ያውም አገር በሁለት ነገር ነው የምትጎዳው፡፡ በአንድ በኩል ገበሬው ከራሱ ተርፎ ለሌሎች ሊያወጣው የነበረው እህል ይቀራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገበሬውን እርሻ የወረሰ አረም መጀመርያ መንደሩን፣ ከዚያም ወረዳውን በመጨረሻም አገሩን ሁሉ ያዳርሰዋል፡፡

ለዚህም ነው ባህላዊው ገጣሚ÷

        ጉልጓሎውን ትቶ መሸታ ቤት ከርሞ፣

       አረሙንም ትቶ መሸታ ቤት ከርሞ፣

      ዳዋውን አልብሶ ማነኝ ይላል ደግሞ፡፡

ብሎ የገጠመው፡፡

ገበሬ ሆይ ምናለ ይህችን ሞያህን ለኛም ብታስተምረን፡፡ እንዳንተ እርሻችንን በሚገባ ማወቅ አልቻልንምኮ፡፡ እንዳንተም አረሙን ለይቶ መንቀል አልቻልንምኮ፡፡ አንተ ከኔ የተሻለ የራሴን እርሻ የሚያውቀው የለም፡፡ ከኔ የተሻለ አረሙንም ለመለየትና ለማረም የተሻለ አይገኝም ብለህ አንተው ታርመዋለህ፡፡

የኛ ችግራችን ምን እንደሆነ ታውቃለህ? መጀመርያውኑ አረም ሊኖርብን ፈጽሞ አይችልም ብለን እንከራከራለን፡፡ ያ ክርክራችን ደግሞ ጭፍን ክርክር ነው፡፡ አረም ሊኖር የማይችለው እንዲህ እና እንዲያ ስላደረግኩ፣ እንዲህ እና እንዲያ ዓይነት ቴክኖሎጂ ስለተጠቀምኩ ነው ብለን አይደለም የምንከራከረው፡፡ እንዴት የኔ እርሻ ሆኖ አረም ይኖረዋል? እንዴት እገሌ እና እገሌ እያሉበት አረም አለው ይባላል ነው ክርክራችን፡፡ እንዴት ነው አረም በስም እና በታላቅነት ይጠፋል እንዴ?

አረሙን እንኳን እያየነው ለስማችን፣ ለዝናችን፣ ለክብራችን ስንል ስንዴ ነው አረም አይደለም ማለትን እንመርጣለን፡፡ «የኛ ስም ከሚጠፋ አረም ዘር ቢሆን ይቀላል» የሚለውን ብሂል አንተ ታውቀዋለህ?

አንተ ጎበዝ ነህ ወዳጄ እርሻዬ አረም ይዟል ብለህ ራስህ ታርመዋለህ፡፡ ምናለ አንተን የማኅበር ሰብሳቢ እና ዋና ጸሐፊ፣ የፓርቲ ሊቀ መንበር፣ የዕድር ዳኛ፣ የሃይማኖት መሪ፣ የድርጅት መሪ፣ የመሥሪያ ቤት አለቃ፣ ብናደርግህ፡፡ ይኼው ስንቱ አረም በየቦታው ዘር መስሎ ተቀምጦ የለም እንዴ፡፡ አንዳንዱ ከመኖር ብዛት በቅሎ፣ አንዳንዱ በሰው በኩል ገብቶ፣ አንዳንዱን ራሳቸው መሪዎቹ ዘርተውት፣ አንዳንዱን ጠላት ዘርቶት፣ ሌላውንም ከዘር ጋር ተቀላቅሎ ተዘርቶ እያየነው ነው፡፡

ዋናው ችግር አረም መኖሩ አልነበረም፡፡ ባይኖር የተሻ ነበር፡፡ ግን አለ፡፡ ታድያ እንዳንተ ማን ይመን፡፡ ሁሉ አረም የለብንም፤ እኛ ንጹሕ ነን ባይ ሆነ፡፡ አረሙ ደግሞ በቅሎ በቅሎ ይኼው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ሲሆን ሲሆን አረሙ ዘሩን ከመዋጡ በፊት እንዳንተ አረም አለብኝና ላርመው ብሎ መነሣት የአባት ነበር፡፡ ካልሆነ ደግሞ ዘመድ፣ ጎረቤት፣ ጎደኛ፣ ባልንጀራ፣ ባለሞያ፣ ጋዜጠኛ፣ውስጥ ዐዋቂ፣ አላፊ አግዳሚ፣ ታዛቢ፣ ተመልካች «ኧረ ይኼንን እርሻ አረም እየዋጠው ነው፣ አንድ ነገር ይደረግ» ብሎ ሲናገር ተቀብሎ ማረም ይገባ ነበረ፡፡

ጀግናው ገበሬ ያንተን ልብ ሀገሯ የት ነው? ያንተንስ ቆራጥነት ማደርያዋ ወዴት ነው? በቀይ ዕንቁስ የገዛት ማን ነው? ሁሉም ለምን ተነክቼ ባይ ሆነ፡፡ ዐቅም ከቻለ ራስን በራስ ማረም፣ ዐቅም ካልቻለም እንዳንተ እባካችሁ እርሻዬን ለማረም ርዱኝ ብሎ በጠየቅ አሁን ምኑ ያስነውራል? ራሱ አረሙ ሳያስነውር ስለ አረሙ ማውራት ያስነውራል? የአረሙ መኖር ሳያሳፍር ለምን አረም አለ ተባለ የሚለው ለምን ያሳፍራል?

ወዳጄ አንተ ልክ ነህ፡፡ ራስህ አረሙን ቀድመህ ለየኸው፤ ራስህም ማረሙን ጀመርክ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ያሉትን ሰምተሃል አይደል፡፡ አንድ ቀን እልፍኛቸው ውስጥ እያሉ በማታ ከእቴጌ  ጋር ይጋጫሉ፡፡ እቴጌም አንጀታቸው አርሮ ዐፄ ቴዎድሮስን ልክ ልካቸውን ይነግሯቸዋል፡፡ ከእልፍኙ ውጭ ሆኖ የሚጠብቀው የቴዎድሮስ ጋሻ ጃግሬ የእቴጌን ንግግር እየሰማ አንጀቱ ያርራል፡፡ ያ የቤተ መንግሥት ጠላ እና ጠጅ የለመደ ግብረ በላ ጠባቂ እንዴት ጌታዬን ይናገሩታል ብሎ ወዲያ ወዲህ ይንቆራጠጥ ጀመር፡፡

በመጨረሻም ጠባቂው ንዴቱ ከዐቅሙ በላይ ሆነና በሩን ከውጭ በርግዶ ወደ እልፍኙ ዘው አለ፡፡ ንጉሡ እና እቴጌይቱ በሁኔታው ደነገጡ፡፡ «ምንድን ነው?» አሉ ንጉሥ ቴዎድሮስ፡፡ «እንዴት ጌታዬን እመቤቲቱ እንዲህ ይናገሯቸዋል ብዬ ነው» አለ ጠባቂው እሳት እንደ ላሰ፡፡ ቴዎድሮስ ፈገግ አሉ፡፡ «አየህ» አሉት ጠባቂያቸውን «አንተ የምታውቀኝ ለብሼ፣ ተሸልሜ ነው፤  እርሷ  ግን የምታውቀኝ ራቁቴን ነው፤ ልዩነታችሁ እዚህ ላይ ነው፤ በል አሁን ውጣ» አሉት ይባላል፡፡

እውነታቸውን ነው፡፡ ያ አንጋች ቴዎድሮስን የሚያውቃቸው አርድ አንቀጥቅጥ ለብሰው ጎምለል ብለው ሲወጡ ነው፡፡ እቴጌ ግን ሰው የማያውቀውን ያውቁታል፣ ድካማቸውን እና ብርታታቸውን ያውቁታል፤ ጠባሳቸውን እና ቁስላቸውን ያውቁታል፡፡ ጋሻ ጃግሬው ሲነቁ ነው የሚያውቃቸው፤ እቴጌ ግን ሲተኙም ያውቋቸዋል፡፡ ጋሻ ጃግሬው ሲስቁ ነው የሚያውቃቸው፤ እቴጌ ግን ሲያለቅሱም ያውቋቸዋል፡፡ ጋሻ ጃግሬው ሲበረቱ ነው የሚያውቃቸው፤ እቴጌ ግን ሲደክሙም ያውቋቸዋል፡፡ ራቁቴን ታውቀኛለች ያሉት ይህንን ነው፡፡

አንተም ገበሬው፣ እርሻህን ራቁቱን የምታውቀው አንተው ባለቤቱ ነህ፡፡ የውጮቹማ እንደ ለበሰ ነው የሚያውቁት፡፡ ለውጮቹ አምሮ ደምቆ የሚታየውን አንተ ነህ እንከኑን ነቅሰህ የምታየው፡፡ እናም አንተው ራስህ ብታርመው ያምርብሃል፡፡ «ከጠላት ምስጋና የወዳጅ ተግሣጽ ይበልጣል» እንዳለ ጠቢቡ፡፡ መጣፉምኮ «ጴጥሮስን የገሠፀው ጳውሎስ ነው» ነው የሚለው /ገላ 2፣11/፡፡ እውነት ነው፤ የጳውሎስ ያህል ጴጥሮስን ማን ያውቀዋል፡፡ ሌሎች እንደ ለበሰ ነው የሚያውቁት፣ እርሱ ግን ራቁቱን ነው የሚያውቀው፡፡

ራሳቸው ዐፄ ቴዎድሮስስ ባልዋን እና አባቷን የገደሉባት ምንትዋብ የተባለች ሴት

          አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ

         አቃጥሎ ለብልቦ አንድዶ ፈጃችሁ

         ይህንን ሲሰማ ያጎራል ላመሉ

       ማናትም ቢሏችሁ ምንትዋብ ናት በሉ

ብላ ትገጥምላቸዋለች፡፡ እንሾማለን እንሸለማለን ያሉ ለሥራ ያልደረሱ ለመብል ያላነሡ ነገር ለቃሚዎች ከነፋስ ፈጥነው ለቴዎድሮስ ያደርሱላቸዋል፡፡ «ታድያ ባልዋን እና አባቷን ገድዬባት ልታመሰግነኝ ኑሯል እንዴ፤ በሉ ቀለብ ሥፈሩላት፤ ባይሆን እርሷ እውነቱን ትንገረኝ እንጂ» ብለው ያዝዛሉ፡፡ እንዳሉትም እስኪሞቱ ድረስ እውነቱን ስትነግራቸው ኖረች፡፡ መቅደላ ላይ ሲሠው «ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው» ብላ የገጠመች እርሷ ናት ይባላል፡፡

ባይሆን አንዳንዶቻችሁ እንኳን እውነት ተናገሩ እንጂ፡፡22 comments:

 1. Kalehiwot Yasemalen Dn. Daniel.

  ReplyDelete
 2. ዐስበ መምህራንን አብዝቶ ያድልህ!

  ጥቂት ብርታት አግኝተን የታሪክ ገጾችን መገልበጥ ብንችል የምናገኘው አንድ ትልቅ ሐቅ አለ፡፡ ይኸውም እንኳንስ ቤተክርስቲያናችን ችግር ውስጥ ገብታ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እንኳን እበላ ባዩ ሲበዛ ለእውነት ዘብ የሚቆሙ አለኝታዎች ነጥፈውብን አያውቅም ነበር፡፡ እባካችሁ አሁንም እውነት እውነቱን መናገር፣ ስለ እውነት መዘመር እጅግ በጣም ያስፈለገበት ጊዜ ላይ ነንና ስለእውነት ዘብ እንቁም፡፡

  ክርስቶስ እውነት ነው፤ የክርስቶስ መሆናችን የሚታወቀው ስለ እውነት አብዝተን በመዘመር ነው፡፡ “እውነት አርነት ያወጣል!”

  የድንግል ማርያም ልጅ አርነት ያውጣን፤ የእውነት ደቀ መዛሙርት ያድርገን፤ አሜን፡፡

  ReplyDelete
 3. Tiru eyeta new Bertalin.

  ReplyDelete
 4. ባይሆን አንዳንዶቻችሁ እንኳን እውነት ተናገሩ እንጂ

  ReplyDelete
 5. Well said as usual. God Bless You.

  ReplyDelete
 6. ዉድ ወንድማችን
  እ\ር ይትጥልን በጣም ወቅቱን የጠበቀ ፁሁፍ ነው
  ለአባቶቻችን ለመንጋው እረኞች እዉነቱን የሚናገሩሥበት አንደበት እ\ር ይትጣቸዉ

  ReplyDelete
 7. Thank u, for the core of ur message.
  But some of the history which is described at the last part is not about Mentewabe rather about Tiruwork. Please refere and make a correction for all of us.

  ReplyDelete
 8. እግዚያብሄር ይስጥልን።
  ቺግሩ ገበሬውን ሲጀመር ማን አወቀው ።
  ሁሉም አስቀድሞ ናቀው እንጂ ።
  አረም የለም እንዳይባልማ ። ጌታ ከመረጣቸው ፩፪ቱ ሐዋርያት እንኩአ ፩ አረም ነበር ።
  ስለዚህ አረም መኖሩ አይቀሬ ነው ቺግሩ ፣እንደ ገበሬው መለየቱ ላይ እና ያስተራረሙ ስልት ላይ ነው ።
  እግዚያብሄር አረሙ የሚነቀልበትን ቀን ያምጣልን ።
  አሜን ።

  ReplyDelete
 9. Wey Dn. Dani,
  Sintun Temarin bante...
  Egziabher Abzito Yistih...
  Berta....

  ReplyDelete
 10. ዳኒ በአማርኛ ከአንተ ባልሻልም “እርሻውን ማን ያርመው” ቢስተካከል
  “እርሻውን ማን ይረሰው?” “አረሙን ማን ያርመው?” ቢሆን እስማማለሁ ።

  ReplyDelete
 11. ባለንበት ዘመን ፡ ስለ-ቤተ ክርስቲያናችን ችግርና ስለ-ካህናቱ መጥፎነት ፡ በየኢንተርኔቱ ላይ የሚለቀቁ መጣጥፎችን ስናነብ ፡ ብዙ አስደንጋጭና አንድ ጫፍ ብቻ ይዘው የሚነጉዱ ነገሮችን ነው የምናየው ።
  ሁላችንም ሌላውን በመንቀፍ ላይ በአንድ ልብ የተስማማን ያህል ሆኖ ይሰማኛል ። አንድ ሰው በሌላው ስህተት ላይ ብቻ ማነጣጠር ከጀመረ ፤ የራሱ መንፈሳዊ ሕይወት እየደከመ እንደሚሄድና ፡ ስለሌሎቹ ክፋትና ጥፋት ሲነገር እየሰማ ፤ ራሱን “ለካ እኔ ከእነ-ዕገሌ እሻላለሁ ማለት ነው” እያል ፤ በየሌለው ጽድቅ ራሱን እያታለለ ፤ በትዕቢትና በትምክህት መሞላት ይጀምራል ።
  የራስን ድክመት መመልከቱ ፤ በጾምና በጸሎት መበርታቱ ይቀርና ፤ የጽድቁና የመንፈሳዊነቱ መገለጫዎች ሁሉ ፡ ታላላቆችን በመንቀፍና በመተቸት ላይ ብቻ መወሰን ይመጣል ።
  የንስሓ ሕይወትም ይረሳና ፡ በየኢንተርኔቱ ላይ የምናነበውን ተከትለን ። የንስሓ አባቶቻችንና ካሕናቱን በሙሉ በማብጠልጠል “ምን ቄስ አለና ነው ? ንስሐዬንስ ለየትኛው ቄስ ነው የምናዘዘው ? ሁሉም እንዳሉ ሆዳሞችና ዱርዬዎች ናቸው………” እያልን ፤ ለራሳችን ግራ የተጋባ ሕይወት ውስጥ እየገባን መሆናችን ሳያንሰን ፤ ሌሎችንም ውዥንብር ውስጥ እየከተትናቸው ነው ።
  የሆነ ያልሆነውን እየለቃቀምን አደባባይ ካወጣነው እኮ ፡ ማንኛችንም በማንኛችንም ፊት ፍጹም አይደለንም ።

  ስለ አንድ ካህን መጥፎነት ሲነገር የሰማ ሁሉ ፡ “ በእኔ ፊት ደህና ሰው እየመሰሉ ስለሚቀርቡ እንጅ ሁሉም ቄሶች አስመሳዮችና ወንበዴዎች ናቸው………” የሚል ግንዛቤ ውስጥ እየገባ ፡ የካሕናትና የምእመናን ልዩነት እየሰፋ ሄዶ ፡ ከነአካቴው እንዳይቋረጥና ፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዱ ፤ ማስቀደሱ ፤ ሥጋ ና ደሙን መቀበሉ….. እንዳይቆም ያሰጋል ።
  ምክንያቱም ፡ አንድ ምእመን ፡ ስለ ካሕናት መጠፎነት ፡ ጆሮው እስኪበጠስ ያዳመጠውና ፡ ዓይኑ እስኪፈዝ ያነበበው ክፉ ወሬ ፤
  ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆሞ በአእምሮዉ እየተመላለሰ የሚያስቸግረው ከሆነ ፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመሄዱን ነው የሚመርጠው ። ያ ማለት ደግሞ የሃይማኖቱ መጥፋት ዋዜማ ነው ። እስካሁንም ቢሆን ፡ በክፉ ወሬያችን ብዙዎቹንም ወደዚህ ሕይወት ሳናስገባቸው አልቀረንም ።
  እባካችሁ ወገኖች ፤ ተባራሪ ወሬዎችን እየተከተልን በካሕናት አባቶቶቻችን ላይ በማንጣጠር የምንነዛው አሉባልታ ፡ ቤተ ክርስቲያናችንን ለዓለም መሳቂያ ማድረግና ሃይማኖቱንም ማጥፋት እንጅ ሌላ የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም ።
  እኛ ናላችን አስኪዞር የምንጽፈውንና ላገኘነው ሁሉ የምናወራውን ነቀፋና ትችት የሚያዩ ልጆቻችን አኮ ፤ ነገ ጥዋት ሃይማኖቱን ዘወር ብለው አያዩትም ።
  የዛሬዎቹ ምዕራብውያን (ካቶሊኮች) እምነት አልባ ሆነው የቀሩት አኮ ፤ በወቅቱ የነበሩት ወላጆቻቸው በየቤታቸውና በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ቄሶቹ መጥፎነት የሚያወሩትን እየሰሙ ስላደጉና ፡ በሓይማኖቱ ላይ ጥላቻና ንቀት ስላደረባቸው ነው ።
  እኛ ዛሬ ካልነቃንና ፡ መነቃቀፉን ተወት በማድረግ ፡፡ ተቀራርበን መመካክርና መከባበር ካልቻልን ፡ ታላላቅ ካቴድራሎቻችንና ገዳማቶቻችን ነገ ጥዋት መዘጋታቸውና ፡ ያለን ነገር ሁሉ ወደ ታሪክነት እንደሚቀየር ማወቅ አለብን ።

  ReplyDelete
 12. Interesting! the message/core point which I wish our top fathers of the CHURCH and the leaders of our COUNTRY as a whole visit this blog and see them selves. Of course all of us need to pray in order that our country and our church will be led by those who see things, situations and happenings in this sense and act accordingly.

  God bless u Dn Dani

  ReplyDelete
 13. ዳኒዬ በልቤ የማስበውን ለመናገር ይከብደኛል ምክንያቱም በቃላት ለመግለፅ ስለሚከብድ በአጭሩ ግን ተባረክ!!ፀ

  ReplyDelete
 14. TO ANNONYMUS WHO COMMENT ON OCT,27/2010 2:36 AM
  * reader not the blogger
  ግብርና ወይም እርሻ ለስው ልጅም ሆነ ለእንስሶች የሚሆን ምግብን፥ ቃጫንና ሌሎችም በአትክልት ከልማት የሚገኙ ነገሮችን ማምረትና እንስሳ ማርባትን ይሰይማል።


  እራሽ፡ ማሳ ፡ የእርሻ ይዞታ፡፡
  እርሻ፡ የኣዝርዕት መዝሪያና ማብቀያ… ስለዚህ በ እኔ አስተያየት የተመረጠው ርዕስ ይስማማል፡፡
  ወ/ገብርኤል

  ReplyDelete
 15. ዲ.ዳንኤል እግዚአብሔር እውቀትን ይጨምርልህ

  ReplyDelete
 16. ነብዩ ነስጋትህን በከፊል እስማማለሁ ነገር ግን እዚህ ጋር የሚወጡ ችግሮች ለግሳጼ እስከሆነና የሃይማኖቱን መሰረት ያልለቀቁ እስከሆነ ድረስ ክፋት የላቸውም! ገፍቶ ቢሄድ እንኳ ካልተበጠበጠ አይጠራም አይደል! ግድየለም ብለህ አትተወውም ሃይማኖት ነውና!
  በተረፈ ዳኒ ጥሩ ጽሁፍ ነው!

  ReplyDelete
 17. Amen! Our holy fathers, please have the courage of the farmer to unmake all the pitfalls that we have in our church!

  Esdros Zelideta, Gondar

  ReplyDelete
 18. ዲ.ዳንኤል እግዚአብሔር ይስጥልን።
  እውነት ለሁላችን ከበደችን...ስትነገረን ይመረናል..አንቀበልም..
  ድንግል ማርያም የከበደንን ታቅልልን ...የመረረንን ታጣፍጥልን
  እግዚአብሔር እንድንቀበል ይርዳን

  ያለሜ

  ReplyDelete
 19. what awonderfull essay!u wrote awonderfull burninig issue!

  ReplyDelete
 20. Daniel. I am very happey the way you explain tewahedo Haimanot and History. It is very teaching.
  GOD BLESS ETHIOPIA

  ReplyDelete
 21. ውድ Anonymous እርሻ እንጂ አረም አይታረምም።ማረም ማለት ማስተካከል
  ሲሆን የሚስተካከለው እርሻው እንጂ አረሙ አይደለም።አረሙ እራሱ ጥፋት ስለሆነ
  የሚወገደው ክፍል ነወ።ከተሳሳትኩ ይቅርታ።

  ReplyDelete