Thursday, October 14, 2010

ከቺሊ ስማይ ሥር

ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ የመጨረሻው የማዕድን አውጭ ከጉድጓዱ ውስጥ ወጥቶ ነበር፡፡ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሆኗል፡፡ ለ69 ቀናት የጠበቅናቸው እነዚህ ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከ622 ሜትር ጉድጓድ ውስጥ ወጡ፡፡ የቺሊ ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ፔኔራ «እግዚአብሔር ከምንወጣው በላይ የሆነ ፈተና አይሰጠንም» እንዳሉት እውነትም የሚወጡት ፈተና ሰጥቷቸዋል፡፡ የሀገሬ ሰውስ «ማከኪያውን ላይሰጥ እከኩን አይሰጥም» ይል የለ፡፡

ቺሊ ውስጥ ሳን ሆዜ በተባለ የማዕድን ማውጫ ቦታ ይሠሩ የነበሩ 33 ሠራተኞች የመውጫ መንገዳቸው ተዘግቶ ዋሻ ውስጥ መቅረታቸው የተሰማው የዛሬ 69 ቀን ነበር፡፡ ቺሊያውያን እና መላው ዓለም ደነገጠ፡፡ አዘነ፡፡ ምን ሊሆን ይችላል? እያለም ፈራ፡፡ ረዥሙን ቱቦ ሠርቶ፣ ቴክኖሎጂውንም ተጠቅሞ እነዚያን ሰዎች ለማውጣት ቢያንስ አራት ወር ይፈጃል፡፡ እንዲያውም ከገና በፊት የማይታሰብ ነው ተባለ፡፡

ፀሐይን ሳያዩ፣ በቂ ምግብ ሳያገኙ፣ አስፈላጊው ሕክምና ሳይደርሳቸው፣ ነገ ምን እንደሚሆን ሳያውቁ፣ ከቤተ ሰቦቻቸው ተለይተው እንዴት ይከርማሉ? ሙቀቱን እና ቅዝቃዜውን እንዴት ይችሉታል? ያልተነሣ የጥያቄ ዓይነት አልነበረም፡፡

የቺሊ መንግሥት በተለይም ፕሬዚዳንቱ ሴባስቲያን ፔኔራ አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደረግ አስታወቁ፡፡ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ እና የማዕድን ሚኒስትሩ ጉዳዮችን ሁሉ በቅርብ ይከታተሉ ነበር፡፡ አሜሪካ እና ጀርመን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ፡፡ የቺሊ ሊቀ ጳጳስ ጸሎት ዐወጁ፡፡ ሕዝቡ በየቤተ ክርስቲያኑ ከተተ፡፡ ባለ መሰልቸት እና ባለማቋረጥ በመላ ቺሊ ጸሎት ይደረግ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከ22 ሰዓታት በላይ በፈጀ የማውጣት ርብርብ ሁሉም የማዕድን ሠራተኞች ከ622 ሜትር ጉድጓድ በተአምር ወጡ ፡፡

ይህንን ዓለም እንደ ልብ ሰቃይ ፊልም በንቃት የተከታተለውን የ33 የማዕድን ሠራተኞች ታሪክ፤ ይህንን የቺሊያውያን አንድነት፣ አርበኛነት እና የሃይማኖት ጽናት የታየበትን ታሪክ፤ ይህንን ከ300 የሚዲያ ተቋማት የመጡ 2000 ጋዜጠኞች የተከታተሉትን ልብ አንጠልጣይ የሰው ልጅ ታሪክ ስመለከት ብዙ ነገሮች በኅሊናየ ይመጡ ነበር፡፡

H#ለት መቶኛ የነጻነት በዓሏን በቅርቡ ያከበረችውን ቺሊን ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅኳት በአሥራ አንደኛ ክፍል የታሪክ መጽሐፍ ስለ ቺሊ አብዮት ስንማር ነው፡፡ በዓለም ላይ አሥቸጋሪ የሆነ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ተዘርግቶባቸው ከነበሩ ሀገሮች አንዷ ነበረች ቺሊ፡፡ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የገባቸው በቅርቡ ነው፡፡

መጀመርያ ነገር የሚደነቀው የቺሊ መንግሥት እውነታውን ተገንዝቦ የወሰደው ርምጃ ነው፡፡ ችግሩን ከመሸፋፈን እና አልተደረገም ብሎ ከመካድ ይልቅ የሆነውን ነገር ተገንዝቦ ለቺሊ ሕዝብ እና ለዓለም ገልጸ፣ የሚቻለው ነገር ሁሉ እንደሚደረግ ቃል ገባ፡፡ ከምድር ወለል 622 ሜትር ርቀው ለነበሩት የማዕድን ሠራተኞች ፕሬዚዳንቱ ቀርበው የሆነውን ነገሯቸው፤ ቃላቸውን ሰሟቸው፤ አጽናኗቸው፤ ጥቂት ጊዜ ይፈጃልና አይዟችሁ አሏቸው፡፡

መንግሥት የፕሬስ ማዕከል በአካባቢው አቋቁሞ በየሰዓቱ እየሆነ ያለውን በግልጽ ይናገር ነበር፡፡ ምን እንደተደረገ፣ ምን እንደታሰበ፣ ከጉድጓዱ ውስጥ ያሉት ሠራተኞች ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ የቺሊ ሕዝብ እና ዓለም በየጊዜው በቂ መረጃ ያገኝ ነበር፡፡ ተደብቆ የሚፈለግ፣ ተሸሽጎ የሚጋለጥ፣ ባለ ሥልጣን ብቻ የሚያውቀው፣ ሕዝብ የሚያጉረመርምበት መረጃ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የቺሊ መንግሥት ምናልባት 30 ጋዜጠኞችን ነበር የጠበቀው፡፡ ነገር ግን ከ2000 በላይ ጋዜጠኞች አካባቢውን በመሣርያ ዎቻቸው አጥረውት ነበር የከረሙት፡፡

ሰውን ከመርዝ በላይ የሚገድለው ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡ ከምድር ወለል ርቀው የነበሩት እነዚያ የማዕድን ሠራተኞች ስንቃቸው ተስፋ ነበረ፡፡ በየጊዜው በሚላክላቸው መልእክት አማካኝነት ተስፋቸው ይለመልም ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በጸሎት እና በቃለ እግዚአብሔር አማካኝነት ትልቅ መጽናናትን እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ እንዳለው «ምናልባት አስቸኳይ የሕክምና ርዳታ የሚፈልግ ሰው ቢኖር ኖሮስ፣ የልብ ድካምን የመሰለ ችግር ቢከሰት ኖሮስ፣ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ነገር ተከስቶስ ቢሆን» መልሱ አንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቷል፡፡

የዋሻ መደርመሱ ከመድረሱ በፊት የፈረቃ መሪ የነበረው ሉዊስ ኡርዝዋ ያከናወነውን ነገር አስቡት፡፡ እያንዳንዱን የማዕድን ሠራተኛ በሦስት ፈረቃ ከፍሎ በማስተባበር፣ ሥራ በመስጠት፣ አመጋገባቸውን እና የጤና አጠባበቃቸውን በመምራት፣ ተስፋቸው እንዲለመልም በማድረግ፣ በውጭ ከነበሩት የነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር በየጊዜው እየተገናኘ በመሥራት፣ ያከናወነው የመሪነት ተግባር፡፡

መሪ ማለት ይህ ነው፡፡ ሕዝቡን ከመከራ የሚያወጣ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይጨነቅ፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ አእምሮውን ሳያጣ፣ ሳይረበሽ እና ሳይርበተበት መፍትሔ የሚያስብ፡፡ ከደረሰው ችግር ይልቅ ሊመጣ የሚገባውን መፍትሔ የሚያስብ፡፡ ተረጋግቶ የሚያረጋጋ፤ ወስኖ የሚያስወስን፤ ጸንቶ የሚያጸና፡፡ ብርሃን አይቶ የሚያሳይ፡፡

ሉዊስ ኡርዝዋ ከሁሉም በመጨረሻ ነው የወጣው፡፡ መሪ ማለት ይኼ ነው፡፡ ራሱን ለሚመራቸው ሰዎች የሚሠዋ፤ ለመከራ ራሱን ለጥቅም ሌሎችን የሚያስቀድም፡፡ መሪ እረኛ ነው፤ መሪ አባት ነው፤ መሪ ሩኅሩኅ ነው፡፡ ሕዝቡን ስለ ራሱ ሳይሆን ራሱን ስለ ሕዝቡ የሚሠዋ፡፡ እኔ አለቃችሁ ነኝ፤ ብዙ ነገር የሠራሁ ነኝ፣ ብዙ የደከምኩ ነኝ ስለዚህ ቅድሚያ ይገባኛል አላለም፡፡ ሁሉም ወዳጆቹ ወጥተው ካልተጠናቀቁ ዕረፍት እንደማ ይኖረው አስቧል፡፡ እናም መጨረሻ ወጣ፡፡ ፕሬዜዳንቱ «ሉዊስ ዛሬ የሺፍት መሪነትህ ሥራ ተጠናቀቀ፤ መርተሃል፣ አስተባብረሃል፣ መሥዋዕትነት ከፍለሃል፤ አሁን ጨርሰሃል፤ መሪ ማለት አንተ ነህ» ነበር ያሉት፡፡

ይህ አጋጣሚ ቺሊያውያን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የታዩበት ነው፡፡ ወታደሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ካህናት፣ ሐኪሞች፣ መሐንዲሶች፣ መሪዎች፣ ሁሉም ለአንዲት ሀገር የሚጠበቅባቸውን አደረጉ፡፡ ለቺሊ «የበረከት መከራ» ነው የሆነላት፡፡ መሪዎቿ ይህንን መጥፎ አጋጣሚ የሕዝቡን አንድነት፣ ጽናት፣ ሀገራዊ ስሜት፣ መተሳሰብ እና መቀራረብ ለማምጣት ተጠቅመውበታል፡፡ ከሕዝባቸው ጋር በመሥራት ፍቅራቸውን እና ክብራቸውን አሳይተዋል፡፡

ሠላሳ ሦስት የማዕድን ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ ቺሊያውያን በጠቅላላው ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ ከነበሩበት የመከራ ጉድጓድ ወጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ፔኔራ «ቺሊ ከ69 ቀናት በፊት በነበረችበት ሁኔታ ላይ አይደለችም፤ ሌላ ሀገር ሆናለች» እንዳሉት፡፡

የሚገርሙ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የማውጣቱን ዕቅድ መርተዋል፤ ተከታትለዋል፤ በመጨረሻም ከመጀመርያው ሰዓት ጀምረው በቦታው ተገኝተው ጸልየዋል፣ አልቅሰዋል፣ ተደስተዋል፤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ አባት ሁሉን አቀፉ፡፡ እንደ መሪ ተከታተሉ፣ እንደ ዜጋ ዘመሩ፣ እንደ መንፈሳዊ ጸለዩ፣ እንደ ሰው አነቡ፡፡ ሁኔታውን በስልክ ወይንም በሪፖርት አይደለም የተከታተሉት፤ ስብሰባ ላይ ወይንም በዓል ላይ አልነበሩም፤ እንደ ሠራተኞቹ ልብሳቸውን ለብሰው በቦታው ነበሩ፡፡ ለ22 ሰዓታት ያህል በቦታው ቆመው እያንዳንዱ የማዕድን ሠራተኛ ሲወጣ ጨብጠውታል፣ አቅፈውታል፣ ስመውታል፣ አበረታተውታል፡፡

ከሠራተኞቹ ጋር ሲያወሩ፣ ከቤተሰቦች ጋር ሲመካከሩ፣ ሲስቁ እና ሲጫወቱ ላየ ፕሬዚዳንት አይመስሉም ነበር፡፡ እኔ ፍርሃት ሳይሆን አክብሮት፣ በሕዝብ እና በመሪ መካከል ርቀት ሳይሆን ፍቅር ነበር ያየሁት፡፡

የተቀበሩትን የማዕድን ሠራተኞች የማውጣቱ ሂደት የተጀመረው በስብሰባ አይደለም፡፡ በጸሎት ነው፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ልቡናውን አቅንቶ ጸልዮአል፡፡ መሪዎች እና ሕዝብ እንደ ነነዌ ሰዎች አንድ ሆነው የእግዚአብሔርን ረድኤት ጠይቀዋል፡፡ የለመኑትን የማይነሣ፣ የነገሩትን የማይረሳ አምላክም ረድቷቸዋል፡፡ ለዚህም ነበር ፕሬዚዳንት ፔኔራ «እግዚአብሔር ባይረዳን ኖሮ» ያሉት፡፡

ሕዝብ እግዚአብሔርን ሲያስቀድም፤ መሪዎች ከእግዚአብሔር ረድኤት ሲጠይቁ፤ ቅድሚያውን ለፈቃደ እግዚአብሔር ሲሰጡ፡፡ ስሙን በክብር ሲጠሩ እና ሲያመሰግኑ መስማት ያስቀናል፡፡ በእውነቱ የቺሊያውያንን ጸሎት የሰማ እኛንም ይስማን፡፡

ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠው ቦታ የሚገርም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እዚያ ዋሻ ውስጥ የቀሩት ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ነው፡፡ የተከበሩ ዜጎች ናቸው፡፡ እነርሱን ያፈሩ፣ የተንከባከቡ እና የነፍሳቸው ቁራጭ የሆኑ ቤተሰቦቻቸው ክቡራን ናቸው፡፡ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከመጀመርያው ጀምሮ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ የማውጣቱ ሥራ ሲጀመር በቦታው ተገኝተው አይተዋል፡፡ ወዳጆቻቸው ከጉድጓዱ ሲወጡ በእንባ ተቀብለዋቸዋል፡፡ የሀገር መሠረቱ ቤተሰብ ነውና ተገቢውን ቦታ አግኝተዋል፡፡

«ቺሊያውያን በመሆናችን ኮራን» ነበር የሚሉት ቺሊዎች በየጎዳናው፡፡ ለምን አይኮሩ፡፡ አገር አንድ ሆኖ ሥራ ሲሠሩ አዩ፡፡ የሠላሳ ሦስት ሰዎች ጉዳይ ጉዳያችን አይደለም የሚለውን ከመሪዎቻቸው አልሰሙም፡፡ ታሪክን በአይናቸው እንጂ በሪፖርት አልሰሙም፡፡ ክፉ እና ደጉን ከመሪዎቻቸው ጋር ተካፈሉ፤ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዳው ልባቸው በታሪካዊው ሥራቸው ተጠገነ፡፡ ከተለመደው ዓለም ርቃ በላቲን አሜሪካ ደቡብ ጥግ ያለችው ቺሊ በዓለም ሕዝቦች ልብ ውስጥ ገባች፡፡

ከተቻለ ችግር አይምጣ፤ ከመጣም በሚጠቅመን እና በሚያፋቅረን መንገድ እንወጣው፤ ደግሞም እንማርበት፡፡ ፕሬዚዳንት ፔኔራ «ካለፈው ትምህርት ወስደናል፤ በቀጣይ የማዕድን አወጣጥ መንገዳችንን እንፈትሻለን፤ እናስተካከክላለን» ነበር ያሉት፡፡ የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ «ስሕተት ባይኖር ኖሮ ሰው እንዴ ይሻሻል ነበር» እንዳለው ለተማረበት ስሕተት የዕድገት እና የለውጥ መነሻ ይሆናል፡፡ ሲሸፋፍነው የሚኖር ግን ጠባዩ እስኪመስል ድረስ ይደጋግመዋል፡፡

ሌሎችን ወደ ላይ ለማውጣት ስድስት ባለሞያዎች ወደ ታች ወረዱ፡፡ ከፍ ለማድረግ ዝቅ አሉ፡፡ ሠላሳ ሦስቱን የማዕድን አውጭዎች አውጥተው ሲጨርሱ እነርሱ ጉድጓዱ ውስጥ ነበሩ፡፡ የተላኩበትን ተግባር ሲፈጽሙ mission Cumplida አሉ፡፡ እኛስ? አላሉም፡፡ እነርሱ ሌሎችን እንደረዱ ሁሉ ያመኑት እግዚአብሔር እነርሱን አይረዳም እንዴ፡፡


47 comments:

 1. እንዴት ያለ ነገር ነዉ። በእውነት አሁን አንተ ወንድማችን እስክትናገረው ድረስ አላስተዋልኩትም ነበር። እንዴት ግን ያሰቀናል። እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ መሆን። አቤት እግዚአብሄር ሲፈቅድ እንዴት ነገሮች ደስ እንደሚያሰኙ አየን። እኛንም ይፍቀድልን። -ጸሎት ይሰራል እኮ፣ ዘንግተነዋል።

  ቃለ ህይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 2. GIRUM NEWU. EGZIABEHER EGNANIM ANDINETUNINA TSINATUN YISTEN.

  ReplyDelete
 3. «ምናልባት አስቸኳይ የሕክምና ርዳታ የሚፈልግ ሰው ቢኖር ኖሮስ፣ የልብ ድካምን የመሰለ ችግር ቢከሰት ኖሮስ፣ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ነገር ተከስቶስ ቢሆን» መልሱ አንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቷል፡፡....

  የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ «ስሕተት ባይኖር ኖሮ ሰው እንዴ ይሻሻል ነበር» እንዳለው ለተማረበት ስሕተት የዕድገት እና የለውጥ መነሻ ይሆናል፡፡ ሲሸፋፍነው የሚኖር ግን ጠባዩ እስኪመስል ድረስ ይደጋግመዋል፡፡
  Egziyabher yistlen Daniel

  ReplyDelete
 4. ዋዉ ዳኒ ግሩም እይታ ነዉ እሂ እኮነዉ ከሌሎች ጸሃፊዎች የሚለይህ ማለት ወቅታዊ፤ታሪካዊ፤ሀይማኖታዊ፣ፖለቲካዊ ፤ግለሰባዊ፤ሀገራዊ…………….የመሳሰሉትን ጉዳዮች ሁሉም ሰዉ እንዲገባዉ አድረገህ በምሳሌአዊ አነጋገርህ ስትጽፈዉ በእዉነት ነብስ ነገር ነዉ

  ReplyDelete
 5. ዋዉ ዳኒ ግሩም እይታ ነዉ እሂ እኮነዉ ከሌሎች ጸሃፊዎች የሚለይህ ማለት ወቅታዊ፤ታሪካዊ፤ሀይማኖታዊ፣ፖለቲካዊ ፤ግለሰባዊ፤ሀገራዊ…………….የመሳሰሉትን ጉዳዮች ሁሉም ሰዉ እንዲገባዉ አድረገህ በምሳሌአዊ አነጋገርህ ስትጽፈዉ በእዉነት ነብስ ነገር ነዉ

  ReplyDelete
 6. thanks dn.Dany for ur interesting litrature & how did u it interesting inorder 2 teach me,we ETHIOPIAN for z seek of our unity using z challenges we faced,z important of praying and z importance of allowing our God to lead us&our activities by asking him 2 make us strong to pass z chalenges we faced.
  i wish all z best 4 u!!!
  GOD BLESS U

  ReplyDelete
 7. ልዩ እይታ ነው በጣም አስተማሪ
  ህብረትን አመልካች ፍቅር አዘካሪ
  በፀሎት ሲታገዝ አንድነት ሃይል ነው
  ችግርን ይፈታል መፍትሔ መንገድ ነው፡፡

  የቺሊን ጎዳና ሁሉም ቢማርበት
  አገር ትለማለች ይፈጥራል አንድነት
  ትህትና ፍቅር መስዋዕትነትን
  ትዕግስትን ጽናትን ከልብ መዋደድን
  አስተማሩ ለዓለም ፍጹም አንድነትን ፡፡

  መሪው በትህትና ህዝቡ በጸሎቱ
  የተማረው ክፍል ምሁሩ በእውቀቱ
  ለሌላው በማሰብ ሲተጋ ኃላፊው
  ዘገባ በማቅረብ ፀና ጋዜጠኛው ፡፡

  የሃይማኖት መሪ ካህናት አባቶች
  መምህራንና ዲያቆናት ወንድሞች
  አዛውንት ወጣቶች ሴቶች ህፃናቶች
  ሁሉም ትምህርት ይውሰድ
  ከቺሊ ጀግነኞች፡፡

  ReplyDelete
 8. "ስሕተት ባይኖር ኖሮ ሰው እንዴ ይሻሻል ነበር» is good.However there are many faults we did not learn from it.For those who are able to do it, and try it fault will be ameans for solution.but in such situations the most and important thing is to pray and let every thing to God to finish it. we are nothing other than the help of God.He is the means and the end or relult.Having this in mind the love between people and the government to its citizen and kingdom is required. Earthly Governors should act minimally to love their citizen as the heavenly Governor loves maximmaly.This is what ፕሬዚዳንት ፔኔራ do

  ReplyDelete
 9. ዲያቆን መሐሪ ገብረማርቆስOctober 14, 2010 at 8:56 AM

  በአንድ ወቅት እክፍል ውስጥ ስንማር መምህሬ ያሉትን ላካፍል፡-

  እኛ ልክ እንደ ውሾች ነን፡፡ ውሾች ከሰፈራቸው ውጪ ሌላ ውሻ ሲመጣባቸው ተባብረው፣ አንዱ በንክሻ፣ አንዱ በግፊያ፣ አንዱ በጩኸት፣ ሌላው ጥርሱን በማሾል ደብድበው አስፈራርተው፣ አሸማቀው ያባርሩታል፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንዲት አጥንት ላይ ሲነካከሱ፣ ሲቦጫጨቁ፣ ሲፋለሙ ታገኛላችሁ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ታሪክ የሚነግረን እንደዚህ መሆናችንን ነው፡፡

  እንዳለመታደል ሆኖብን የኛ አንድነት፣ መተባበር፣ መፈቃቀር የሚመጣው “የውጪ” ብለን የምፈርጃቸውን ጠላቶቻችንን ለማጥፋት ብቻ ነው፡፡ የተመለከትኳቸው የታሪክ መጻሕፍትም ሆኑ በሕይወት የኖርኩባቸው ዘመናት በአንድ ቃል የመሰከሩልኝም ይህንኑ ነው፡፡ የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አቀንቃኞች እኛን ቢያጤኑን ኖሮ የሰው ልጅ ከጦጣ መሰል ፍጥረት መጣ የሚለው አስተምህሯቸውን ቀይረው ወደ ውሾች ሳይመለከቱ ይቀራሉ ብላችሁ ነው?

  የቺሊው ታሪክ እኛ ሀገር ቢሆን ኖሮ አቤት የአሉባልታው፣ የሐሜቱ፣ ተጠያቂውን በአጽንዖትና በቁጣ በተመሉ ዓይኖች መፈለጉ፣ የሚጠሩ ስብሰባዎች ብዛት፣ የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ብዛት…!

  ReplyDelete
 10. GOD BLESS U DANIEL, AHUN KETAREDEW MUKUT SAYKER TIRE SIGA BEHAWAZE ABELAHEN EKO. WAW AWESOME...

  ReplyDelete
 11. If this was happened in Ethiopia I don't think they can make it on the ground.Because we lost unity and trust each other.So there were no prayer and no solution at all.I never heared since 1967 E.C any of our leader attend the church.they scare of people and people scare of them. They might think leave for ever.Any way God bless the world.

  ReplyDelete
 12. ትጉህ እረኛ !
  ከሰሞኑ የቺሊያውያን የማዕድን አውጪ ሰራተኞች ጉዳይ ብዙ ነገር አስተምሮናል በአንድ በኩል የእግዚአብሄርን ድንቅ ሥራ ፤ በሌላ በኩል የመንግስትን ለዜጎቹ ያለውን ትልቅ ሃላፊነት ፡፡ በእውነቱ የቺሊያውያን ነገር በጣም ነበር የሚገርመው አጋጣሚ ሆኖ በሲኤንኤን በቀጥታ እየተላለፈ ስለነበር እኔም ስከታተለው ነበር ፡፡
  ከሁሉም ነገር እጅግ የሚያስደንቀው መንግስት የሰጠው ትልቅ ትኩረት ነበር ፡፡ መንግስትና ሕዝብ እንዲህ ለአንድ ዓላማ በአንድነት ሲቆሙ እንዴት ያስደስታል ታዲያ ለሕዝብ የቆመ መንግት ትጉህ እረኛ ማለት ይህ አይደለም ትላላችሁ ?

  ReplyDelete
 13. Thank u very much Dn. Daniel for your fast, timely, and interesting analysis.
  God BLESS u.

  ReplyDelete
 14. ድንቅ ምልከታ ነው ዲ/ን ዳንኤል።
  ፟ከምድር ወለል ርቀው የነበሩት እነዚያ የማዕድን ሠራተኞች ስንቃቸው ተስፋ ነበር። ፟
  ድንቅ ነው። ፟ተስፋ የሌለው ራእይ አያይም ፟ ይባል የለ።

  ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ፍስሃ ጽዮን

  ReplyDelete
 15. መለያየት ሞት ነው!  አቤት አቤት እኛ

  እኛ ...

  ተጎዳን ክፉኛ

  እንዲህ ተለያይተን

  እጅግ ተነጣጥለን

  ስንገኝ ለብቻ

  ድህነት ... በሽታ ... ወጡብን ዘመቻ።

  **************************

  ለዘመቻ አፀፋ

  ፍቅራችን ቢሰፋ

  ብንሆን በህብረት

  በፍቅር ባንድነት

  ዘማቹ ባፈረ

  ጉዳት ብሎ ነገር ... ድ ... ሮ ... ጥንት በቀረ።

  ReplyDelete
 16. Good comment for us and our leaders. I say the time is now to unit for aborting feminism in ETHIOPIA. GOD bless u & Ethiopia

  ReplyDelete
 17. God bless you Dani

  ReplyDelete
 18. ልዩ እይታ ነው ዳኒ እግዚአብሄር ይባርክህ እግዚአብሄር ካልሰራ ሰራተኞች በከንቱ ይደክማሉ
  ነውና መሪና ተመሪ እግዚአብሄርን ሲይዙ እንዲህ ይሆናል መሪ የራሱን ክብር ሳይጠብቅ ለሰው ህይወት ሲጨነቅ አየን ፈጣሪ እንደ ቺሊው አይነት መሪ የምናይበትን ጊዜ ያቅርብልን
  አንተንም በፀጋው ይጠብቅህ
  ለምለም ዮሃንስ

  ReplyDelete
 19. Dear Dani,

  I was following the chilli cause eagerly for two reason: 1, as you well-presented the unity of every chilli citizen for the solution, secondly the engineering solution to drill the 622m bore. When the first miner arrive on surface my eye filled with tears. I asked God when will you give us this kind of leader, when will you give as this kind of unity. This morning when I open my pc , I got your on time report. Well written positive article. The Chilli miner had only one thing when they were underground , hope. Just as chilli miner have great hope to come on the surface, let us hope one day Ethiopia will be on the surface. Thanks,

  Hope

  ReplyDelete
 20. ዘይስማንጉሰOctober 14, 2010 at 3:10 PM

  እጹብ ድንቅ ነው ወንድማችን ዳንኤል! ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
  እርግጥ ነው ግሩም አንድነት ነው ያየነው፡፡እንዲያውም እንዲህ እያሰብኩ ነበር፤ቺሊ በምትታወቅበተ እግር ኳስ ብትረሳም በ33ቱ ተጨዋቾች/miners እንደገና ገነነች፡፡
  የፕሬዚዳንቱ(ከነባለቤቱ)፣ማእድን ሹመኛው፣ሰራተኞች/ባለሙያዎች፣…ህብረት ግሩም ነበር፡፡ግን እጅግ የገረመኝ ገብተው ያወጡትና መጨረሻ የወጣው(ሉዊስ፡፡ እንዲህ አይነት ሙሴ እግዚአብሄር ያድለን!

  አውሮፕላኑ እኮ ቀልጦ ቀረ፤እስኪ እንዲያው በሞቴ ያሳያችሁ እነርሱ ተገልበጥ ብለው አልገለበጡት ምን አደባበቃቸው እኛም ብናውቅ፣ስንት አመት ለፍተው አገራቸው ናፍቃቸው፣እናት አባታቸውን ለመጦር/ለመጠየቅ የሚመጡ ነበሩ’ኮ፡፡ታዲያ መረዳት ካለባቸው ወገን ዘመድ ቢረዳቸው ካልቻልን ደግሞ እንደ ፔኔራ ‹አቤት የረዳት ያለህ›ብንል ምን አለ ጎበዝ፡፡ እንደው የእኛዎቹ የሆነች ነጭ አይጥ መርከብ ውስጥ ብትሞት የሚሸፋፍኑ ይመስለኛል፡፡

  እግዚአብሄር መከራን ያርቅልን! እ…እ. እንዲውም መከራ የራቀልን በእኛ የጽድቅ ስራ አይመስለኝም፤የቅዱሳኑ(እነ አባ ተ/ሃይማኖት) አጽም እንዳይጋለጥ በመጨነቅ ነው እላለሁ፡፡አይ እኔማ…

  Any way Dani u showed me the other face of it!

  ReplyDelete
 21. If u want to be like Chillians, we need to have two important things
  1. being positive thinker
  2. avoiding selfishness
  As to me this are the pillars of Unity. let's evaluate our selves in terms of the two pillars and work towards them.
  thanks,
  G/mariam ZBSH

  ReplyDelete
 22. Yetwdedk wendmachn kehulu befit yemlew QHY abzto yasmah ye Amlak seran yegardbn meskin Ye ethiopia lejoch lebona yestan bezu astemari tsehuf new leb yenkale betly bezh zemn nenewen astawsun " ሕዝብ እግዚአብሔርን ሲያስቀድም፤ መሪዎች ከእግዚአብሔር ረድኤት ሲጠይቁ፤ ቅድሚያውን ለፈቃደ እግዚአብሔር ሲሰጡ፡፡ ስሙን በክብር ሲጠሩ እና ሲያመሰግኑ መስማት ያስቀናል፡፡ በእውነቱ የቺሊያውያንን ጸሎት የሰማ እኛንም ይስማን፡፡ Denk yesu seran letmert enji leknfer metata aydrgben Selamun yabzalh +++ Bekirstos akbari betseboch toronot

  ReplyDelete
 23. Atnaf
  የሚገርሙ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የማውጣቱን ዕቅድ መርተዋል፤ ተከታትለዋል፤ በመጨረሻም ከመጀመርያው ሰዓት ጀምረው በቦታው ተገኝተው ጸልየዋል፣ አልቅሰዋል፣ ተደስተዋል፤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ አባት ሁሉን አቀፉ፡፡ እንደ መሪ ተከታተሉ፣ እንደ ዜጋ ዘመሩ፣ እንደ መንፈሳዊ ጸለዩ፣ እንደ ሰው አነቡ፡፡ ሁኔታውን በስልክ ወይንም በሪፖርት አይደለም የተከታተሉት፤ ስብሰባ ላይ ወይንም በዓል ላይ አልነበሩም፤ እንደ ሠራተኞቹ ልብሳቸውን ለብሰው በቦታው ነበሩ፡፡ ለ22 ሰዓታት ያህል በቦታው ቆመው እያንዳንዱ የማዕድን ሠራተኛ ሲወጣ ጨብጠውታል፣ አቅፈውታል፣ ስመውታል፣ አበረታተውታል፡፡

  Waw dani betame yamimasagunu president Nachew menealebet amelak fekedo lengame endazihe ayinet meri bisaten eske berteten ensaley GOD BLESS ETHIOPIA.
  DANI PLEASE CONTINUE ...CONTINUE...WITH GOD

  ReplyDelete
 24. አሜን ወአሜን!October 15, 2010 at 1:14 AM

  ወንድም ዳንኤል እግዚአብሔር ይባርክህ!
  እግዚአብሔር አምላክ አብርሆተ ልብ ስለሰጥህ አመሰግነዋለሁ። ወደፊትም ጌታ በውስጥህ ያስቀመጠውን መልዕክት በድፍረት ይዘህ እንደምትወጣ ተስፋ አደርጋለሁ። በቺሊ አገር ከተከሰተው ልንማር የሚገቡንን ብዙ አንኳር ትምህርቶች በጥሩ ሁኔታ አስቀምጠህዋል። እግዚአብሔር አምላክም በዚህ ውስጥ ብዙ መልካም ነገሮችን አፍልቋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ሶስት ማእድን ቆፋሪዎች ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኝ አድርገው መቀበላቸው ነው።ሙሉ ዜናውን በሚቀጥለው ሊንክ ማየት ትችላላችሁ።
  http://www.breakingchristiannews.com/articles/display_art.html?ID=8294
  እግዚአብሔር አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን! አሜን ወአሜን!!

  ReplyDelete
 25. WoW ዳኒ በእውነቱ ግሩም ዕይታ ነው፡፡የጽሁፎችህ ይዘት ሁሉንም የህይወት ዘርፍ የሚዳስስ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡አሁንማ እኔ በማወራቸው ርዕሶች ዙሪያ ሁሉ ላይ ዲ/ን ዳንኤል በዚህ ጽሁፉ እንዳለው በማለት በመጥቀስ የንግግሮቼ ማጣፈጫ ቅመም ሆነሃል፡፡ለእኛ ከእውቀት ጥበብህ እንዳካፈልከን የቅዱሳን አምላክ የማያልቀውን ጥበቡን ይግለጥልህ፡፡
  አዜብ ዘሚኒሶታ

  ReplyDelete
 26. Oh! GOD would you open my blind eyes to see things posetively like my brothers and sisters?

  Dany GOD bless you and let him lead you up to the end of you life .

  ReplyDelete
 27. Thank you it is so interesting Please go head.

  ReplyDelete
 28. Dani

  Endgena methu,

  ' yegl adng ' ymil denbngam alh? It is good,

  ReplyDelete
 29. Hello Daniel!

  Thanks for your article. As to me this and the one about Alemayehu Tewodros are the articles that are flawless. Keep up with this works. I know the difficulties (both material and social) that you are experiencing.

  However, when it comes to writing and teaching about the eternal life (the true teaching of life- EOTC teachings)for the public, I say that among other things we need guidance from Him. You know, St. Paul the greatest apostle didn't come to teach about the Kingdom of God by himself but he was called, prepared and led by Him. It is easy, in fact very much easy to teach about rocket engineering or any of so called high tech sciences/and technologies for someone than to teach about God's Kingdom. I'm not talking about the material or technical difficulties involved here. It is well above that. We are talking about saving souls.

  Thanks.
  Anbabi.

  ReplyDelete
 30. Qale hiwoten yasemalen ahuenm ewketunena tegawen yabezalek Amen ´!!!!!

  awo EGZIABHER talk new ke mederm west kemederm belay yetem benehon tebakiachen esu becha new

  ene enkuan egeg ye EGZIABHERN sera new yadenekut andem saymot saygoda eskemecheresahw seat tebakotu ysedenekal KEBER MESEGANA yehn laderege EGZIABHER !!!!!!!!!!!!!

  dani le hagerachen endeante aynetun asteway ena menfesawi kenat yalebetn ersu AMELAKACHEN yazegagelen engi yega neger tekedeno yebesel new

  le meriwochachen mastewalun yadelelen !!!!!!

  teru eyeta melekam mastewal new !!!!!!! Astewlek endenastewel taderegenalek enam YE agelegelot zemenehen yarezemelek Amen

  ReplyDelete
 31. live watch eyaderegekute nebere last time gene endiehh alastewalekutem nebere rejeme edemiee wendemachene!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 32. Waw Dani, it is a very nice constructive reflection. We have similar history in Adwa. However, now we are unable to solve critical problems as a society or as a group. Why ?????????????????????????????? Let God visit us with his wisdom..

  ReplyDelete
 33. እኔ ግን የአንተ ነገሮችን የምታይበት መንገድ ነው የሚደንቀኝ:: ድንቅ ተስጥኦ ነው ዲ/ን ዳንኢል:: ጸጋውን ያብዛልህ ትልቅ ትምህርት ነው::

  ReplyDelete
 34. oh Dani I don't know what I am to say for you it is so interesting. God bless you more Amen!

  ReplyDelete
 35. Thanks Dani!Qale Hiywet Yasemalen.Melkam Eregnam Yesten!!
  "Beewnet Le Egziabhere ye misanew neger Aleni?"

  ReplyDelete
 36. K. Tetemke From AddisOctober 20, 2010 at 10:22 AM

  These peoples have stayed for these much days with hope. Assume, if the had no hope, what would happen? Let's think a while being in their place. This remembers me the life in the Hell, though it is too diminutive to compare with Hell. Please let's repent from our sin and be ready for the kingdom of God and to escape from the adversity of Hell.
  Thank you Dani.

  ReplyDelete
 37. Dani

  Egiziabiher min ainet masitewal sete?

  Egiziabiher endezi ainet meri bealemawiw kerto bemenfesawi miriyachin basayen.

  mahi

  ReplyDelete
 38. Daniel I like the report. God is good all the time

  ReplyDelete
 39. ምንም አዲስ ነገር አላስነበብከንም ለምን ከእኛ ሀገር ጋር አታነፃጽርልንም ያ ቢሆን ትንሽ ይሻል ነበር በል ደህና ሁን..

  ReplyDelete
 40. አንተ የላኩትን ጽሑፍ አታወጣም.

  ReplyDelete
 41. D.Danniel your perspective is like "EAGLE" in any direction in any idea in any small up to big issue in our country up to the end of the world edge.
  When was the ETHIOPIAN LEADERS start to meet people with face to face with out any procedure,why people and leaders to discuss any thing freely.Some king of Ethiopia the name given like mother "EMIYA" this name give according to the approaches of people. Why today? Today leaders of Ethiopia with a very difficult military surrounding from Aratkilo to Bole Airport the people of Addisababa in the road in avert difficult militarily keeping. It is continue for the last 30th years. Your perspective was a very constructive idea please continue up to ..........
  GOD BLESS ETHIOPIA.
  ........................................Atnaf.....

  ReplyDelete
 42. Hmmmmmmmmmmmm!!! Legitimacy and inclusiveness lies in the heart of their success.

  Joro yalew mesmatin yisma!

  God bless you!

  Esdros ZeLideta, Gondar

  ReplyDelete
 43. ቺሊ
  አልፎም አይረሳ ኖሮም ሇታሪክ ነው፥
  የአምላክ ጥበቡ ሁሌም እንግዳ ነዉ፥
  ብቻ የሚገርመዉ ሁሌ ሚያሳዝነዉ፥
  የሰዉ ልጅ ከዚህም አሇመማሩ ነዉ።
  በዛች በላቲኗ በዛች ትንሽ ሃገር፥
  ድንገት በደረሰ አይነተኛ ችግር፥
  ዓሇም ጉድ ተሰኘ ታየ በዙ ነገር፥
  ታየ ድንገት መጥፋት ታየ ዳግም መኖር፥
  በሰባ ቀናቶች ታየ ብዙ ነገር፥
  የሰዉ ጥንካሬ የአምላክ ተአምር፥
  የባንዲራን ትርጉም የሃገርን ፍቅር፥
  የመሪነት ሚና የዜጎችን ክብር።
  እንዲህ ነው ሃላፊ እንደዚህ ነው መሪ፥
  ሃገር የሚያስጠራ ዜጎቹን አክባሪ።
  ዜጋዉ ሲጎዳበት እንቅልፉን የሚያጣ፥
  ከገባበት ገደል ቆፍሮ ሚያወጣ፥
  ሲደሰቱ ስቆ ሲያዝኑ አብሮ አዝኖ፥
  በረሃ የሚያደር የሆኑትን ሆኖ፥
  እንደዚህ ነዉ ጎበዝ የወገኑ ፋኖ።
  ግብዝ ዜጎች ገድሎ እሬሳ ሲከምር፥
  ሌላዉ አንድ ሊያድን ሲጨነቅ ሲዳክር፥
  ስንቱን ጉድ ታቀፈች አቤት እቺ ምድር!
  ምናሇ እነመሇስ ከነዚህ ቢማሩ፥
  በቀራቸዉ እድሜ ቁም ነገር ቢሰሩ፥
  ከልፈታቸዉ በፊት አንድ ቅን ቢኖሩ!
  በዚህ በጎ ስራ ምናሇ ቢቀኑ፥
  ከኮሪያ ገዝተዉ ዶክተር ከሚሆኑ፥
  ሇተንኮል ሇልጥፋት እንዲህ ከሚፈጥኑ፥
  በህዝብ ተወደዉ መሃይም በሆኑ፥
  ወይም ቺሊ ሄደዉ ፍቅርን ባጠኑ።

  ReplyDelete
 44. ጽላት ዕድለኛ ናት፡፡

  ReplyDelete
 45. try to mention ours.we have so much...unity is our identity.isn't it Dani?please always don't blame us.thank u.

  ReplyDelete
 46. ይህን ያነበብሁት ዛሬ ነዉ። እንባዬ ከቁጥጥሬ ዉጭ እየፈሰሰ።

  ReplyDelete