Wednesday, October 6, 2010

የአንድ ዕብድ ትንቢት

አንድ ዕብድ አራት ኪሎ ላይ ጆሊ ባር ፊት ለፊት ቆሞ «ወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ይከፈላል፣ በስድስት ይከፈላል» እያለ ቡትቶውን እየጎተተ ይጮኻል፡፡ አጠገቡ የነበሩ ጋዜጣ ሻጮች «ዝም በል፣ ዕብድ፣ ተነሣብህ ደግሞ፤ማን ይከፍለዋል ደግሞ፤ መዓት አውሪ» አሉና ሊያባርሩት እጃቸውን ወነጨፉ፡፡ እርሱም በተራው ከት ብሎ ሳቀና «የዕውቀት ማነስ ችግር አለባችሁ፡፡ ኩላሊታችሁ ችግር አለበት፡፡ የኛ ሰው መከፋፈል ልማዱኮ ነው፡፡ በዝባዥ እና ተበዝባዥ፤ አድኃሪ እና ተራማጅ፤ ፊውዳል እና ፀረ ፊውዳል፤ ኢምፔሪያሊስት እና ፀረ ኢምፔሪያሊስት፤ አብዮተኛ እና ፀረ አብዮተኛ፤ ሕዝባዊ እና ፀረ ሕዝብ፤ ልማታዊ እና ፀረ ልማት፤ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ኪራይ ሰብሳቢ» መልሶ ከት ብሎ ሳቀ፡፡

ቀጠለ «ወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በስድስት ይከፈላል» አለና የቀኝ እጁን መዳፍ ጠቅልሎ እንደ ጡሩንባ ነፋው፡፡

«ምን ተብሎ ነው የሚከፈለው» አሉት አንድ ጋዜጣ የሚያነበቡ አዛውንት፡፡

«ጥሩ ጥያቄ ነው» አለና ጉሮሮውን በስላቅ እንደመጠራረግ ብሎ «የሚበላ፣ የሚበላ /'በ' ይጠብቃል/፣ የማይበላ፣ የሚያባላ፣ የሚያስበላ፣ የሚያብላላ ተብሎ ይከፈላል» ይህንን ሲናገር በአካባቢው የሚያልፉትን የብዙዎችን ጆሮ ለመሳብ ችሎ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም መንገዳቸውን ገታ አድርገው ያዳምጡት ጀምረዋል፡፡

«እስኪ ተንትነው» አሉት እኒያ አዛውንት ጋዜጣቸውን አጠፍ አድርገው፡፡

«'የሚበላ' ማለት ጤፍ መቶም መቶ ሺም፣ መቶ ሚሊዮንም ቢገባ መገዛቱን እንጂ የተገዛበትን የማያውቅ፤ በጋዜጣ ካልተጻፈ፣ በሬዲዮ ካልተነገረ በቀር የኑሮ ውድነቱ የማይነካው፤ የውጭ ምንዛሪ ቢጠፋም ባይጠፋም ዶላር የማያጣ፣ ወረፋ ቢኖርም ባይኖርም ባንክ እምቢ የማይለው፣ ጨረታውን ሁሉ ለማሸነፍ የሚያስችል ድግምት ያለው፤ ተራራ ቁልቁለት መውጣትና መውረድ ሳያስፈልገው ቤቱ ቁጭ ብሎ ሚሊየኖችን የሚያፍስ፤ ሰው ሁሉ በእጁ የጠቀለለው በእርሱ ጉሮሮ የሚያልፍለት፤ ሰው ሁሉ የጎረሰው በእርሱ ሆድ የሚቀመጥለት፣ ሰው ሁሉ ሮጦ እርሱ ሜዳልያ የሚሸለም፣ ለመብላት እንጂ ለመሥራት ያልተፈጠረ ማለት ነው፡፡

«'የሚበላ' ማለት ደግሞ ጉቦ ለመስጠት፣ ኪራይ ለመክፈል፣ ግብር ለመክፈል የተፈጠረ፡፡ ምንም ሕግ አክብሮ ቢሠራ አንዳች ጉርሻ ካላጎረሰ ሥራው የማያልቅለት፤ ለመጋገር እንጂ ለመብላት ያልታደለ ማለት ነው፡፡ 'ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት' ሲባል አልሰማችሁም፡፡ የርሱም ነገር እንደዚህ ነው፡፡ ለመበላት የተፈጠረ ነውና ሕገ ወጦቹ ተቀምጠው እርሱ በሕጋዊ መንገድ እየሠራ እና እየኖረ እርሱ ነው የሚከሰሰው፤ እርሱ ነው የሚጉላላው፡፡ እዚህ አንዳንድ ሠፈር ያሉ ቀበጥ ወላጆች ለልጆቻቸው ሁለት ሁለት ሞግዚት ነው አሉ የሚቀጥሩት፡፡ አንዷ አሳዳጊ ናት፡፡ አንዷ ደግሞ ልጁ ሲያጠፋ የምትመታ ናት፡፡ ልጃቸው እንዳያመው እርሱ ባጠፋ ቁጥር እርሷ ትመታለች፣ እርሷ ታለቅሳለች፡፡ እነዚህም እንደ እርሷ ናቸው፡፡

«'የማይበላ' የሚባለው ለቁጥር የሚኖረው ነው» አለና ወደ ሕዝቡ ዘወር ብሎ «አሁን ለምሳሌ እኔ እና እናንተ ጥቅማችን ለቁጥር ነው» ሲል ብዙዎች በፈገግታ አዩት፡፡ «አዎ እኛኮ ቁጥሮች ነን፡፡ ቁጥር ደግሞ ምዝገባ እንጂ ምግብ አያስፈልገውም፡፡ የኛ ሥራ መመዝገብ ነው፤ መብላት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲቆጠር እንካተታለን፤ ሲበላ ግን አንካተትም፤ ርዳታ ለማግኘት እናስፈልጋለን፤ እርዳታውን ለመቀበል ግን አናስፈልግም፡፡ ስለዚህ ቁጥር ነን ማለት ነው፡፡ ወደፊት እንጀራን በቴሌቭዥን ዳቦንም በፊልም ነው የምናየው፡፡ ወደፊት ምግብ ቤቶች ሁለት ዓይነት ክፍያ ያዘጋጃሉ፡፡ አንዱ ለሚበላ፣ አንዱ የሚበላውን ለሚያይ፡፡ እኔ እና እናንተ ገባ ብለን ምግብ እና አመጋገብ አይተን እንወጣለን፡፡

እንጀራ በሰማይ እኔ በእግሬ ሆኜ
አልደርስበት አልኩኝ ባክኜ ባክኜ

የተባለው በ'ፍካሬ ሕዝብ መጽሐፍ' ላይ የተጻፈው ትንቢት ይፈጸማል፡፡

«'የሚያባላ' የሚባለው ደግሞ ከሚበላው ተጠግቶ ለበይዎች እንደ 'ሀፒታይዘር' የሚያገለግል ነው፡፡ አያችሁ የሚበሉት መንቀሳቀስ አይወዱም፣ ውቃቢያቸው ይጣላቸዋል፤ ስለዚህም የሚያባላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ የሚቀበሉ፣ የሚያቀባብሉ፣ የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ እንደነዚያ ጠግበው ባይበሉም ትርፍራፊ ግን አያጡም፡፡ እነዚያ ግንድ እነዚህ ሥር ናቸው፡፡ እነዚያ ሆድ እነዚህ ግን እጅ ናቸው፡፡ የነዚህ ጥቅማቸው ከምርቱ ሳይሆን ከቃርሚያው ነው፡፡ በሞያቸው፣ በልምዳቸው፣ በአፍ ቅልጥፍናቸው፣ በመመቻመች ችሎታቸው ከሚበሉት ይጠጉና 'እባክህ ጌታዬ እንዲበላ ብቻ ሳይሆን በልቶ እንዲያተርፍም አድርገው' እያሉ እየጸለዩ ይኖራሉ፡፡ እነዚያ የሚበሉት ምግብ ሲዘጋቸው የሚያባሉትን ይሰበስቡና ይጋብዟቸዋል፡፡ ታድያ እነዚህ መታ መታ እያደረጉ ሲበሉ የነዚያም የምግብ ፍላጎታቸው ይከፈትላቸዋል፡፡ ምናልባትም የሚበሉት ካልተስማማቸው የሚያባሉት ይታመሙላቸዋል፡፡

«አንድ ጊዜ አንድ ገበየሁ የሚባል ሰው በምኒሊክ ጊዜ ነበር አሉ»

«እ..............ሺ» የሚል የቀልድ ምላሽ ከከበበው ሰው አገኘ፡፡

«እና ገበየሁ በወቅቱ ለነበሩት አቡን አገልጋይ ሆነና የተጣላውን ሰው ሁሉ እያስገዘተ እጅ እግሩን አሣሠረው፡፡ ይህንን ያዩ ያገሩ ሰዎች

ገብሽ መች ቀሰሰ ከየትስ አምጥቶ
ይወጋናል እንጂ ካቡን ተጠግቶ

ብለው ገጠሙለት አሉ፡፡

«'የሚያስበላ' የሚባለው ደግሞ የተሰጠውን ሥልጣን፣ ዕውቀት እና ኃላፊነት ተጠቅሞ የሚበሉትም እንዳይራቡ የማይበሉትም እንዲጠግቡ ማድረግ ሲገባው 'ላለው ይጨመርለታል' እያለ መሬቱን ሲቸበችብ፣ ግብር ሲቀንስ፣ ያልተፈቀደ ዕቃ ሲያስገባ፣ ሕገወጥ የሆነ መመርያ ሲያስተላልፍ፣ የሚውል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሀገር የሚያስበሉ ናቸው፡፡ ስሕተቱን፣ ጥፋቱን፣ ሕገ ወጥነቱን፣ ጉዳቱን፣ በኋላ ዘመን የሚያመጣውን መዘዝ እያወቁ እኔን ምን ቸገረኝ ብለው ለበይዎች የሚስማማውን ብቻ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነርሱም አይጠቀሙም፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሀገራቸው ማረሚያ ቤት ነው፤ እነሆ ነገ ግዳጃቸውን ሲፈጽሙ እንደ ሸንኮራ ተመጥጠው፣ እንደ ሙዝ ልጣጭ ተልጠው ይወድቃሉ፡፡»

'የሚያብላላ' ይህ ደግሞ ለመብላት የሚያመች ሕግ ፣መመርያ፣ አሠራር እንዲዘረጋ የሚያደርግ፣ የሚበሉት አጋጣሚዎችን ሁሉ እንዲጠቀሙ መንገድ የሚያመቻች፤ ከበሉም በኋላ በተቻለ መጠን የበሉትም ፣አበላላቸውም ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው የሚያመቻች ነው፡፡ መንግሥት ለበጎ ብሎ የዘረጋውን አሠራር፣ ያወጣውን መመርያ እና ያዋቀረውን መዋቅር እርሱ እንዴት ለበይዎች እንደሚስማማ ያጠናል፣ ያመቻቻል፣ ያስፈጽማል፡፡ ከመመርያው እና ከአሠራሩ ጋር የሚሄድ ደረሰኝ፤ ዶክመንት፣ ማስረጃ፣ ያዘጋጃል፤ አበላሉን ያሳልጠዋል፡፡ እነዚህ የጨጓራ አሲድ ናቸው፡፡ የጨጓራ አሲድ የበላነውን እንዲዋሐደን አድርጎ ይፈጨዋል፣ያስማማዋል፡፡ እነዚህም እንደ ጨጓራ አሲድ ይፈጩታል ያስማሙታል፡፡

«አንተ ይህንን ትንቢት ከየት አመጣኸው» አሉት አንዲት እናት ገርሟቸው፡፡

«በዕብድነቴ ነዋ እናቴ፤ አዩ እዚህ ሀገር ካላበዱ በቀር ብዙ ነገር አይገለጥልዎትም፡፡ እንዲገለጥልዎት ከፈለጉ እንደ እኔ ማበድ አለብዎ፡፡ ለነገሩ እዚህ ሀገር ዕብዱ ብዙ ነው ግን ዓይነቱ ልዩ ልዩ ነው» አላቸው፡፡ «ደግሞ የዕብድ ምን ዓይነት አለው፤ ሁሉም ያው ነው» አሉት እኒያው እናት የነጠላቸውን ጫፍ ወደ ትከሻቸው እየመለሱ፡፡

«ተሳስተዋል፤ አዩ ይህም ቢሆን ካላበዱ በቀር አይታይዎትም፡፡ ብዙ ዓይነት ነው ዕብዱ፡፡ የመጀመርያው ያበደና ማበዱን እንደኔ የተረዳ ነው፡፡ ሁለተኛው አብዶ ማበዱን እያወቀ ግን ማመን የማይፈልግ ነው፣ እንደ ብዙዎቻችሁ፤ ሌላው አብዶ ግን ማበዱን ባለማወቁ የተምታታበት ነው፡፡»

«ቆይ አንተ ችግሩ ብቻ ነው የተገለጠልህ፤ መፍትሔውን አልገለጠልህም፤ ማበድህ ካልቀረ ለምን ከነ መፍትሔው አታብድም ነበር» አሉት እኒያ አረጋዊ፡፡

40 comments:

 1. meለምን ከነ መፍትሔው አታብድም waw

  ReplyDelete
 2. wood danil ante ewnetGna ethiopiawe neh::
  Yawuriwen(yakdemow ebbe )erkus tgebar eyagatek
  bemehoneh egziabeher yebarkeh::ende ato gebeYehun Yalu hasawe bezuwoch nachew qoYetew
  hezebunme enedaYeblute amelake tolobelo Yasewgedacwe ::anete gene nurelege breta egeziabeher kanet gare yehune amen::

  ReplyDelete
 3. እኔ የት ነኝ? እስቲ እራሴን ልመርምር...
  1.የሚበላ፣ 4.የሚያባላ፣
  2.የሚበላ /'በ' ይጠብቃል/፣ 5.የሚያስበላ፣
  3.የማይበላ፣ 6.የሚያብላላ፡፡


  1.ያበደና ማበዱን እንደኔ የተረዳ ነው፡፡
  2.አብዶ ማበዱን እያወቀ ግን ማመን የማይፈልግ ነው
  3.አብዶ ግን ማበዱን ባለማወቁ የተምታታበት ነው

  ReplyDelete
 4. hai danil egeziabeher yebarkeh berta::

  ReplyDelete
 5. nice Dani bless you

  ReplyDelete
 6. wey dany degemo men ayenet ebed ametahe?

  ReplyDelete
 7. Lekas Mabed tiru new!!!!
  Gin min waga alew awko ayitabed. Bichal noro ahun neber mabed.
  Thank u Dn. Daniel.

  ReplyDelete
 8. አብደዋልና ቦዘኔ ከምትላቸው ሰዎች ቁም ነገር አይጠፋምና እናዳምጣቸው።

  ReplyDelete
 9. +++

  አንድ ላይ ካበድን ሁላችንም በአንድ ጊዜ ባለ መድኃኒት ስለምንሆንና አሁንም ስለማንግባባ ምናለ ለአንድ ለአንድ ቀን በየተራ ብናብድና እንደ እርሱ ቢገለጥልን?

  ReplyDelete
 10. Wey Dani,
  Berta bicha....

  ReplyDelete
 11. Hi,dani,giziew ye fekire neway ebdiet zemenew newu.egziabehere hulachenenm yitebeken.

  ReplyDelete
 12. Qale hiwoten yasemalen Amen !!!

  gud saysema mesekerem ayeteba yebal yele

  eysgereme yemiastemer new. enam Dani ahuenm tegawen yabezalek legam masetewalun yadelen Amen

  ReplyDelete
 13. I love it abo.

  keep it moving.

  tsegawun yabizalih..

  ReplyDelete
 14. Thank u Dani! keep it on please?! God may help U.

  ReplyDelete
 15. kalehiwot yasemalin!!

  yawum eko esu bedegu gize abdo new.ahun tewodede!!

  ReplyDelete
 16. ''እብድ '' የሚለው ቃል በ አራሱ አንፃራዊ ነው።ምክንያቱም በ ብዙ አብዶች መሃል ጤነኛ ሰው ቢኖር እብድ ይባላልና። አና ሰዎች በምንሰራው በጎ ስራ እብድ ብሉን ምናልባት አነሱ አብደው አኛ ጤነኛ ሆነን ስለሚሆን በደንብ ማጤን አለብን ማለት ነው ጎበዝ።አይመስላችሁም? ጉዱ ካሳ በ ፍቅር አስከ መቃብር መፅሐፍ ውስጥ አውነት በመናገሩ አብዷል ያሉት ነበሩ። ሆኖም ያበዱት አነርሱ ነበሩ።
  gb22

  ReplyDelete
 17. hi DANI you are very brilliant on looking our society problems and your literature concerning the cause,effect and the solution to our country and our Ethiopian orthodox church problem is very interesting please keep your comment may the sun of virgin Mary gives u more wisdom ,health and long live. from behailu girma

  ReplyDelete
 18. ነገርን ነገር ያነሳዋል አሉ ...

  ይኼው 4 ኪሎ ጆሊ ባር አካባቢ የታየው ዕብድ ነው ፤ ባለፈው መገናኛ ድልድይ ሥር ፤ ሰው ፈጣሪውን 'ሰላም አውለኝ' ብሎ ወደየጉዳዩ ለመሄድ ሲጣደፍ ... " አለም ዘጠኝ ነው! ... ዘ . ጠ .ኝ ነው! ... ሐበሽም ዘጠኝ አይነት ነው! " እያለ ሲጮህ ነበር። ወቸ ጉድ አሁንማ አንድኛውን ለይቶለታል ማለት ነው ... መገናኛ እኮ ጨርቁንም አልጣለ ነበር ... ደግሞም " ትንቢት " አልነበረም የሚለው ... " ዛሬ! ... አ . ሁ . ን! " ነበር የሚለው። ... ታዲያ የዛን ዕለት ... ለወትሮው ፡ ካሰበበት በጊዜ ለመድረስ ቀንዶ / Higer Bus / ላይ ለመፈናጠጥ ፣ ባስና ሚኒባስ ለማግኘት ሲሯሯጥ ፣ ሲገፋፋና ሲጎሻሸም የሚያረፍደውን የመገናኛ ሰው ቀልብ ገዝቶ እና ባንድ አገር ሰው ተከቦ ... በማበዴ አገኘሁት በሚለው ነጻነት በመጠቀም ... አሁንም አሁንም " አለም ዘጠኝ ነው! ... ዘ . ጠ .ኝ ነው! ... ሐበሽም ዘጠኝ አይነት ነው! " እያለ ነበር ፤ ለነገሩ ሥርዓት አስከባሪዎችም ጭምር " ደግሞ ዛሬ ምን ይለፈልፍ ይሆን? " በማለት ከሰዉ ጋር አብረው ከበው ማርፈዳቸው ይህንኑ ነጻነቱን ቢያጸድቁለት አይደል?

  መገናኛ ባሰማው ዲስኩር ፡ 4 ኪሎ መጥቶ ከዘረዘራቸው ከስድስቱ ፦ የሚበላ፣ የሚበላ /'በ' ይጠብቃል/፣ የማይበላ፣ የሚያባላ፣ የሚያስበላ፣ የሚያብላላ ፤ ሌላ የሚብላላ ፣ የሚባላ/'ባ' ይጠብቃል/ እና የማያስበላ የሚሉ መደቦችን ጨምሮ " ሐበሽ ዘጠኝ አይነት ነው! " እያለ ሲጮህ ነበር፡፡ ... መቸም ተናግሮ አናጋሪ አይጠፋምና ... ከበው ከቆሙት መሃል ፤ አንድ በትከሻው ቀበቶዎችን ፤ በእጆቹ ደግሞ የጫማ ገበሮችን የተሸከመ ወጣት ግማሽ አስተውሎቱን ድንገት ለሚመጣ ገበያተኛ ሰጥቶና አንገቱን አስግጎ ፤ በተሰላቸ ድምጽ " አንተ መዓት ጠሪ ፣ ለፍላፊ ዕብድ ፤ ደሞ ዛሬ ምን መዓት ይዘህ መጣህ? " በማለት ጠየቀው ... ዕብዱም የሳቁን ምክንያት እርሱ ራሱ በሚያውቀው ፤ ከት ብሎ ስቆ ... አገሬውን ሁሉ በዘጠኝ መደብ የመደበበትን ዝርዝር መተንተኑን ቀጠለ ... እዚህም እዚያም እየረገጠ ፣ አሁንም አሁንም " ብታምኑም ባታምኑም አለም ዘጠኝ ነው! ... ዘ . ጠ . ኝ ነው! ... ሐበሽም ዘጠኝ አይነት ነው! " እያለ ፣ ደግሞ ደጋግሞ እየሳቀ የዘጠኙንም አይነት ዝርዝር በአንድ ጊዜ ወጣው ፤ ... የስድስቱ አይነት ዝርዝር 4 ኪሎ ላይ እንደዘረዘረው ነበር ... ስለቀሩት ሦስቱ የተናገረው ደግሞ የሚከተለውን ነበር ...

  የሚብላላ ፦ እዚህ ላይ ሲደርስ ቀበቶ ተሸክሞ ወደቆመው ወጣት ዞሮ ፤ ጠበቅ ያለ እውቂያ ያላቸው በሚመስል አኳኋን " ሰማህ? ... የሚብላላው እንደ ጓደኛህ አይነቱ ዕድለ ቢስ ነው ፤ እሱነቱ ከዚህም ከዚያም በሚነፍሱ ነገሮች የተመሰረተ ነው ፤ ሲፈጥረው ለምን? እንዴት? የሚባል ነገር የማያውቅ ፤ በድንግዝግዝ የሚጓዝ አይነት ነው ... ድንገት አንዱ ተነስቶ ' እነ እንቶኔ የደከምህበትን እየበሉት ነው ... ያስበሉት ደግሞ እነ እገሌ ናቸው ' ፤ ያለው እንደሆነ ማስረጃና መረጃ ፤ ግራና ቀኝ ሳይል ሲብላላ ፣ ሲተራመስ ፣ ሲራገም ፣ ሲወቅስ ይቆይና ፤ ሌላው ተነስቶ ደግሞ ' አይ እነ እገሌማ አይደሉም ፤ እነ እንቶኔ እንጅ ' ያለው እንደሆነ ያለ አመክንዮ ሲወቅሰው የነበረውን እገሌን በቅጡ ይቅርታ ሳይጠይቅ እንቶኔን ሊያጠፋ ሲብላላ የሚኖር ነው። ... ነገሮችን የመፈተሽ ልምድ ስለሌለው ብልጣብልጦች ይጠቀሙበታል ፤ የሚበሉትን ለማግኘት ኃይል እንዲሆናቸው ሲያብላሉት ሲያብላሉት ይከርሙና ፤ መሻታቸው ሲፈፀም አናውቅህም የሚሉት ነው።

  ይህን ብሎ አይኑን ከወጣቱ ላይ መልሶ ትንፋሽ ሲወስድ ... የዕብዱ ጓደኛውን ጠቅሶ መናገር ያላስደሰተው ባለቀበቶው ወጣት ፤ የሚቀጥለውን ዝርዝር ለመስማት መጓጓቱን ለመደበቅ እየተጠነቀቀ " የሚባላውስ? " አለው? ... ዕብዱ ቀጠለ ...

  " የሚባላው? ... የሚባላው? ... የሚባላውማ ፦ ዕድል ያልቀናው ነዋ ፤ ምስኪኑን ገፍቶና ደሃዋን አስለቅሶ ያላቸውን እንዳይቀማ ጊዜና ቦታ ስላልፈቀደለት ፤ ከበላተኛውም አፍ እንዳይመነትፍ ወኔና ብርታት ስለሌለው ፤ በይውንም ፣ ተበይውንም በአንድ ጨፍልቆ በነገር ጅራፍ የሚገርፍ ነው። ... ለእርሱ የተበዮች እሮሮና ለቅሶ እኩል ከበይዎች ተድላና ደስታ ያስጠላዋል። እርሱን አስፈቅደው እንደሚበሉ በላተኞችን ሲተች እንኳ ' መብላቱንስ ብሉ እሺ ፤ ግን እንዲህ አድርጋችሁ ባትበሉ ፣ እንዲህ አድርጋችሁ ደግሞ ብትበሉ ፣ ይህንን ደግሞ ባትበሉ ' እያለ ለሚሰማው ... ሁልጊዜ እርሱ በላተኛ የሚሆንበትን ዘመን በመናፈቅ እንደሚኖር ያሳብቅበታል። ይህን ጊዜ ከበውት የቆሙ ሁሉ አንድ ላይ አውካኩ ፤ እርሱ ግን ንግግሩን በመቀጠል ... " እጣ ፈንታውንም የሚባላ ያደረጉት እነርሱ ይመስል ፤ በተበዮች ብሶት ላይ ነዳጅ መጨመር የሚያስደስተው ነው። " በማለት የዚህኛውን መደብ ብይኑን ፈፀመ።

  ከዚህም በኋላ በድጋሚ ትንፋሽ ወስዶ " በመጨረሻ ... " ሲልና በንግግሩ እጅጉን የተገረሙ አንዲት እናት " ወቸ ጉድ! የዕብድ ቀን አያልቅም አሉ ... የማያስበላውስ? " ሲሉ አንድ ሆነ። ... አየት አድርጓቸው ፈገገ አለና ...

  " በመጨረሻ እውነተኛ የሐበሽ ሰው አለ " በድጋሚ ረገጥ አድርጎ " እውነተኛ! " በማለት ቀጠለ ... " የማያስበላው ፦ ይኼኛው ባንዱ ላብ ሌላው ለምን ይበላል? ፤ ባንዱ ድካም ሌላው ለምን እረፍት ያደርጋል? ፤ ... የሚል ነው። " አለና " ግን ... ግን ይቅርባችሁ እንዲህ አይነቱ ጥቂት ሰው ነው ፤ ብዙ ሰው አይወደውም ፤ ይጠላዋል ... እናንተም ትጠሉታላችሁ ... እናንተም ትጠሉታላችሁ " ብሎ እንደማቀርቀር አለ ፤ ባቀረቀረበትም በለሆሳስ " እናንተም ትጠሉታላችሁ " የሚለውን ደግሞ ዝም አለ ... ዝምታውን ላዬ ፤ ከደቂቃዎች በፊተ ሲጮህና ሲወራጭ የነበረ አይመስልም ነበር። ... ከብቦት የነበረውም ሰው ለአፍታ ባለበት ከእርሱ ጋር አርምሞ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ሁለት ሶስት ሆኖ የመጣው ፤ በነገሩ እየተወያየ ፤ ለብቻውም የመጣ አንገቱን እየወዘወዘና ከንፈሩን እየመጠጠ ወደየጉዳዩ ተበተነ። ... እርሱም ...

  ReplyDelete
 19. ዳኒ እግዚአብሄር በረከቱን ያብዛልህ በጣም ጥልቀት ያለው ትምህርት ነው የሰጠህን እና አምላካቺን እግዚአብሄር የእውቀት አድማስህን ያስፋልህ. ዳኒ ምንያህል እንደምትጠቅምህ አላውቅም ግን እቺን አስተያየት ልለግስልህ "እብድ" የሚለው ቃል ወይም አነጋገር ካንተ ሞያዊ ስብእና ጋር የማይሄድ ስለሆነ በተሻለ አማርኛ ብትቀይረው ለማለት ያህል ነውአ መሰግናለሁ.

  ReplyDelete
 20. የማይበላ እንዳያስበላ ያብላላOctober 8, 2010 at 1:25 PM

  «ቆይ አንተ ችግሩ ብቻ ነው የተገለጠልህ፤ መፍትሔውን አልገለጠልህም፤ ማበድህ ካልቀረ ለምን ከነ መፍትሔው አታብድም ነበር» አሉት እኒያ አረጋዊ፡፡

  አይ አባቴ
  ያበደውስ ከዋንኛውና ከመጀመርያው መፍትሔ ጋር ነው
  "ችግሩን ማጋለጥ"

  kalehiwot yasemalin!

  ReplyDelete
 21. ከብሄረ ጅማ
  ዳኒ ዛሬ ደግሞ ልዩ ነው ቅኝትህ ቁም ነገር ያለው ሱፍ እና ከረባት ከለበሰ አይደለም ምክንያቱም ይፈራሉ ይሸማቀቃሉ ይህ እብድ ግን የሀገራችንን ነባራዊ እውነታ ከሞላ ጎደል ቃኝቶታል??????????????

  ReplyDelete
 22. Dani you are realy special and VIP person for this country. So be free from Wudasie Kentu and do more using your special gift from God. I wish you all the best

  ReplyDelete
 23. ስለ እብድ ከተነሳ አንድ ‹‹እብድ›› ያለውን ልንገራችሁ በእኛ ሰፈር ጋር ሲያልፍ ልጆች እየተከተሉ አባባ እብዱ እያሉ ይጮሃሉ….ከዚያም ዞር አለና ‹‹ሂዱ ከዚ ድሮም የኢትዮጵያ ህዝብ ተፋፍሮ ነው እንጂ ሁሉም አብዷል›› ብሎ ሲናገር ልጆቹን ብቻ ሳይን ሁላችንንም ፈገግ አሰኘን፣፣ እውነት ነው በመከፋፈል አብደናል… በቅናት አብደናል….ክፉ ስራን እርስበርስ በመሰራራት አብደናል…….አሁን አሁን ደግሞ የኑሮ ውድነቱም አሳብዶናል፣፣
  Harry from Addis

  ReplyDelete
 24. የእብዱ ትንቢት እየተፈጸመ ለመሆኑ አስረጅ ካስፈለገ !! የሀገሪቱን ገጽታ ላስቃኛችሁ ! ሚዲያዎቻችን የተተከለውን ዛፍ፣ የተገነባውን መንገድ እና ድልድይ … እንጂ የእብዱን ትንቢት ፍጻሜ አይነገሩንም እኮ !
  የኢትዮጵያ ሌላኛው መለኳ ይህንን ይስላል፤
  •በዓለም ላይ ኮንትሮባንድ በእጅጉ ካጠቃቸው ሀገሮች ሁለተኛ
  •በዓለም ላይ በምሁራን ፍልሰት ሦስተኛ (ከሰለጠነው የሰው ኃይሏ 75 በመቶ በስደት ይኖራል)
  •በዓለም ላይ በአስቸጋሪ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሦስተኛ
  •በዓለም ላይ ሚስቶቻቸውን በሚያጎሳቁሉ እና እጅግ በሚደበድቡ ባሎች አንደኛ
  •በእናቶች ሞት በዓለም ላይ ካሉት ሀገሮች አንደኛ
  •በኤች አይ ቪ በሽታ አራተኛ (ሦስተኛ ሆነናል የሚሉም አሉ፡፡ እኔ ግን የተጻፈ መረጃ አላገኘሁም)በዓለም ላይ በትራፊክ አደጋ ከተጎዱ ሀገሮች አንደኛ (በዓመት ብቻ 1800 ሰዎችን ለሞት፣ 7000 ሰዎችን ለአካል ጉዳት አርባ ሚሊዮን ብርን ለኪሳራ የዳርገናል)
  •ሥራ አጥነት በየአመቱ በሁለት እጥፍ የሚጨምርባት
  •65 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ በፍጹም ድህነት ውስጥ የሚኖርባት
  •ከጠቅላላ ሕዝቧ 20 በመቶው የአእምሮ በሽተኛ የሆነባት (15000000 ህዝብ አከባቢ መሆኑ ነው)
  •50 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት ልጆቿ በምግብ እጥረት የሚሰቃዩባት
  •በየዓመቱ 5000 ሰዎች በስጋ ደዌ በሽታ የሚጠቁባት
  •50000 ሕጻናት ከልብ ሕመም ጋር የሚወለዱባት
  •አንድ ሚሊዮን አይነስውራን የሚኖሩባት (ከጠቅላላው ሕዝቧ1.5 በመቶ መሆኑ ነው)
  ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ይህ ብቻውን ግን ለትንቢቱ ፋጻሜ ማሳያ ይመስላል፡፡ ሁሉንም መረጃዎች የሰበስብኳቸው በተለያዩ ጊዜያት ከታተሙ የመንግስት እና የግል ጋዜጦች እንዲሁም በቴሌቪዥን ከተላለፉ ፕሮግሞች ነው፡፡

  ReplyDelete
 25. OMG, Dani...
  I am not expert of literature at all but with your article above, I have practically seen what it means to be a "writer!".
  God bless you Man
  Go ahead!

  ReplyDelete
 26. "እብድና ሰካራም የልቡን ይናገራል"አሉ የቤተ ከህንቱም የቤተ መንግስቱም ሰዎች ከእብዱ ንግግር የሚመሩት ሀዝብ ሥራቸውን እንዴት ባለ ትዝብት እንደሚያይባቸው ቢገነዘቡ እንዴት መልካም ነበረ!!!ኸረ ምን በወጣቸው
  ትንሹ እብድ ከሾላ

  ReplyDelete
 27. እብደቴ ናፈቀኝ

  እውነትን በካባ አሳምሮ በውሽት
  መተወን የማይሆን ማንዛዛት
  የጤንነት ሥራ መቅጠፉ ሰለችኝ
  ሃቅ የማወራበት እብደቴ ናፈቅኝ

  ተክለአብ ጥቅምት 1995
  ወዲ ገበያን ሳይ (አስመራ ውስጥ የታወቀ እብድ ነው)

  ReplyDelete
 28. D.Daniel Let God bless you>

  ReplyDelete
 29. It is good view keep it up.

  ReplyDelete
 30. ቃለህይወት ያሰማልን የሚባለው ቃለህይወት ወንጌል ሲነገር፣ ሲሰበክ፣ ወይም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሲተላለፍ ብቻ ነው። አንዳንድ አንባቢዎች ምርቃታችሁን አስተካክሉ።

  በትህትና

  ReplyDelete
 31. dany Kemibe'law Yemibelaw(hodamu) bezto balebet seA't Yih article wosagn new.i mean exploitors are more the the resource now, lekas abdo menager yishalal Gimgema yelewmna. megelel yelwumna.Fetari andebetun yistih.

  ReplyDelete
 32. ዕብዱ ይናገር ዘንድ ስለታዘዘ ከነገ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ብቻ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ትከታተሉ ዘንድ በትህትና ይጋብዛል፡፡ ጥያቄ ቢኖራችሁ መጨረሻ ላይ ማቅረብ ትችላላችሁ፡፡

  ReplyDelete
 33. ዳኒ፥ ችግሩ ሀቅ ነው:: ያልተገለጠልን መፍትሄው ነው::
  የመፍትሄው አካል ለመሆን ምን እናድርግ? እኔ ልመልሰው ያልቻልኩት ጥያቄ ነው::
  ምናልባት የአመለካከት ለውጥ፣መተማመን፣ የአገር ፍቅርና ተጠያቂነት ካዳበርን ልንወጣው እንችላለን:: ካልሆነ ግን ወቃሽ ተወቃሽ ሆነን እንኖራለን እንጂ የሚፈፀመው ትንቢት አልመኝም::

  ReplyDelete
 34. ዳኒ እግዚአብሄር በረከቱን ያብዛልህ በጣም ደስ ይላል
  እኔ የት ነኝ? እስቲ እራሴን ልመርምር ካልኩ በኃላ አገኘሁት ...
  አሁን ለመፍትሄ የሚሆነን ሃሳብ አክልልንና እንስተካከልበት::

  ያለሜ ነኝ

  ReplyDelete
 35. my brother with horebil statistics, from where did you get it? please post your sources.

  ReplyDelete
 36. TRU IYITA
  GOOD ALE FERENGI
  DANI GONDAR METEHI ESKAYH CHEKOLHU
  BETRETU ADEGE NEGN

  ReplyDelete
 37. I identified my place in this fantastic classification.Thank you DDK!!

  ReplyDelete
 38. dros yemisema joro enji yeminager andebet meche tefa! lesewochu amlak semi joro yistachew!! antenim amlak yirdah yihe betam tilik neger new mekniatum lechigir hulu yemejemeriyaw mefthe chigirun magalet new.

  ReplyDelete
 39. What ever it is, this very amazing for me.
  1. The thing or the example itself.
  2. The way of the explanation, and
  3. The time which you raise it etc.
  Please, Keep it up I hate the more talkative ones, the more disturbances who are living only for their bad stomach.
  For me we have hope for the near future. Believe me. But we should have do our parts responsibilities in everywhere and every time.
  C.

  ReplyDelete