ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን እና የበጎ ነገር ወዳጆች ሁሉ ሲከታተሉት ነበረ፡፡ ጉባኤው በሦስት ነገሮች የተሻለ ገጽታ ነበበረው፡፡
1/ የብጹአን አባቶች አንድነት በተሻለ ጎልቶ የወጣበት በመሆኑ
2/ የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት በመሆኑ
3/ የሃሳብ ክርክር እንጂ የጡንቻ ክርክር ያልታየበት በመሆኑ ናቸው፡፡
ጉባኤው ይህንን የመሰለ መልክ እንዲኖረው ያደረጉ ምክንያችም ነበሩ፡፡ የመጀመርያው እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን ጋር መሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የተለያት ብትሆን ኖሮ መንፈሳችን በተስፋ መቁረጥ እንደተሞላ ይቀር ነበር፡፡ አንድ ስሙ ያልተገለጠ የኢየሩሳሌም ተሳላሚ ተናገረው ብሎ ጄምስ ብሩስ እንደገለጠው «ብንወድቅም እግዚአብሔር ግን ከወደቅነው ከኛ ጋር ነበር»፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ እኛ የማናውቃቸው፣ እግዚአብሔር ግን የሚያውቃቸው ቅዱሳን የጸለዩት ጸሎት መልስም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ መልኩ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያበረከቱ ምእመናን፣ ባለሞያዎች፣ ሽማግሌዎች ወዘተ ውጤትም ነው፡፡ እንደ ገናም አያሌ ሚዲያዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ችግሩን ሊፈታ በሚችል መልኩ መንቀሳቀሳቸው ያመጣው የቤተ ክርስቲያን ድል ነው፡፡