Tuesday, September 28, 2010

መስቀሉ የት ነው ያለው? ክፍል ሁለት

ባለፈው ጽሑፍ ላይ የጌታችንን መስቀል በተመለከተ ጥንታውያን መዛግብት ምን እንደሚሉ በመጠኑ ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ ለዛሬ ደግሞ እነዚህን መዛግብት ከሀገራችን መዛግብት ጋር እናስተያያቸዋለን፡፡

መስቀሉ እንዴት ጠፋ?

የሀገራችን ሊቃውንት እና መዛግብት መስቀሉ እንዴት እንደ ጠፋ የሚተርኩት ታሪክ የጥንታውያኑን መዛግብት የተከተለ ነው፡፡ በመስከረም 16 እና 17 የሚነበበው ስንክሳራችን የጌታችን መስቀል በጎልጎታ በጌታችን መቃብር እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ አይሁድ በመስቀሉ እና በመቃብሩ የሚደረገውን ተአምር አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውንም ያትታል፡፡ እስከ 64 ዓም አይሁድ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ በ64 ዓም አካባቢ ግን አይሁድ ራሳቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ዐመጽ ጀመሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡

አይሁድ መስቀሉን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችንን መቃብር የተቆጣጠሩት እና ክርስቲያኖች እንዳይገቡ ያገዱት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ጎልጎታ የከተማዋ ጥራጊ እንዲደፋበት አዘዙ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት አልነበሩም፡፡ ክርስቲያኖች ግን በጌታችን መቃብር አካባቢ ዋሻዎችን ፈልፍለው ይገለገሉባቸው ነበር፡፡

ዛሬ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ክልል የሚገኘው ጎልጎታ በዚያ ዘመን ከከተማዋ ውጭ ነበር፡፡ ጌታንም የሰቀሉት ከከተማ አውጥተው ነው፡፡ አይሁድ የከተማ ጥራጊ መድፊያ እንዲሆን የፈለጉትም ቦታው ከከተማ የወጣ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡

ይህ ታሪክ በስንክሳራችን ከተጻፈው ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

መስቀሉ የት ተቀበረ?

አንዳንድ አካላት የሚተርኩት ታሪክ በስንክሳራችንም ሆነ በጥንታውያን መዛግብት ከተገለጠው የተለየ ነው፡፡ በመስከረም 17 እና በመጋቢት 10 የሚነበበው ስንክሳራችን መስቀሉ የተቀበረው በዚያው በጎልጎታ እንደሆነ ይተርካል፡፡ «የጎልጎታን ኮረብታ ባስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው» ይላል፡፡ አንዳንድ አካላት ግን መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ጉድጓድ ቆፍረው እንደቀበሩት ይገልጣሉ፡፡

በስንክሳራችን የተገለጠው እና መስቀሉ የተቀበረው በጎልጎታ ነው የሚለው ታሪክ በሦስተኛው እና በ4ኛው መክዘ ከነበሩት የታሪክ ጸሐፊዎች ገለጻ ጋር አንድ ነው፡፡ በ380 ዓም አካባቢ የተወለደው ታሪክ ጸሐፊው ሶዜማን መስቀሉ የተገኘው ከጎልጎታ መሆኑን መዝግቦ አቆይቶናል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ በጎልጎታ ተቀብሮ ነበር የሚለው የስንክሳራችን ትረካ ከግብጽ፣ ከሶርያ እና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ስንክሳር ትረካ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃም እሌኒ ንግሥት መስቀሉን ቆፍራ ያወጣችበት እና በኋላም የመስቀሉን ቤተ ክርስቲያን የሠራችበት ቦታ የሚገኘው በዚያው በጎልጎታ፣ ያውም ከኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ገዳም ሥር ነው፡፡

በመሆኑም መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ቀበሩት የሚለው ሃሳብ የሚያስኬድ አይመስልም፡፡

መስቀሉ እንዴት ተገኘ?

መስቀሉ እንዴት እንደ ተገኘ በቤተ ክርስቲያናችን የሚገለጠው ታሪክ ከሌሎች ጥንታውያን መዛግብት ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ መስቀሉን ያወጣችው የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ መሆንዋን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡

እሌኒ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም ስትገባ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመጀመርያው በኢየሩሳሌም ከ132 እስከ 135 በተደረገው እና ከተማዋ ፈጽማ በጠፋችበት ጦርነት ምክንያት ክርስቲያኖች ከከተማዋ ርቀው መኖራቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ መስቀሉን በጎልጎታ ከቀበሩ በኋላ መጀመርያ ጥራጊ መድፋታቸው ሲሆን ሦስተኛው ንጉሥ ሐድርያን በ135 ዓም የኢየሩሳሌምን ገጽታ የቀየረውን አዲስ ፕላን በማውጣት ከተማዋን እንደገና መሥራቱ፤ በጎልጎታም ላይ የቬነስን መቅደስ መገንባቱ ነው፡፡ የቬነስ መቅደስ መገንባት ክርስቲያኖች ወደ አካባቢው ፍጹም እንዳይቀርቡ አስከላከላቸው፡፡

ንግሥት እሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ገብታ ያደረገችውን ስንክሳራቸውን እንዲህ ይተርከዋል «እርሷ በመጣች ጊዜ የጌታችን የክርስቶስን መቃብር እስካሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሰቃየቻቸው፤ ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው፤ የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ» ይላል፡፡ በሌላም በኩል የመጋቢት 10 ቀኑ ስንክሳር ታሪኩን ያውቃል የተባለውን አንድን አይሁዳዊ አሥራ በማስጨነቅ ምሥጢሩን እንዳውጣጣችው ይገልጣል፡፡ ይህ አገላለጥ ከጥንታውያን መዛግብት አገላለጥ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ዞሴማን አልተቀበልኩትም ቢልም አንድ አይሁዳዊ ሽማግሌ ለንግሥት እሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ እንዳሳያት የሚተርከው ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ኪርያኮስ የተባለ አረጋዊ ነገራት እየተባለ ከሚተረከው ጋር ተመሳይ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ አይሁዳዊ ስለ ዕጣንም ሆነ ጸሎት ሊናገር የሚችል አይመስልም፡፡ ይህ ሃሳብ ምናልባት በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአቡነ መቃርዮስ ይሆናል፡፡

እስካሁን እኔ በሌሎች መዛግብትም ሆነ በስንክሳራችን ላይ ያላገኘሁት «ደመራ ተደምሮ ጢሱ አመለከተ» የሚለውን ታሪክ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ጢሱ ለመስቀሉ መስገዱን ይገልጣል፡፡ እሌኒ ንግሥት ክርስቲያናዊት እናት እንደ መሆንዋ መጠን አይሁድ የሰጧትን መረጃ ብቻ ተቀብላ ቁፋሮ አታስጀምርም፡፡ በአይሁድ የተነገረው በጸሎት እንዲረጋገጥ አድርጋለች፡፡ ያን ጊዜ ጸሎት ተደርጎ ዕጣን ሲታጠን ጢሱ ወደ ጎልጎታ አመለከተ፡፡ ይህንን በተመለከተ መዛግብትን ማገላበጥ ይቀረናል፡፡

በዓለ መስቀል እንዴት ተወሰነ?

በኢትዮጵያም ሆነ በግብጽ ያሉ ስንክሳሮች ላይ መስቀሉ የተገኘው መስከረም 17 ቀን መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ቁፋሮው መቼ እንደተጀመረ በትግጠኛነት የሚገልጥ መረጃ አላገኘሁም፡፡ የኛ ሊቃውንት ቁፋው መስከረም 17 ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መጠናቀቁን ይገልጣሉ፡፡ በወቅቱ ከነበረው ቴክኖሎጂ አንፃር ሊወስድ ይችላል፡፡ መጋቢት 10 ቀን ግን ራሱን የቻለ ታሪክ አለው፡፡ መስቀሉ በፋርሶች ከተማረከበት በንጉሥ ሕርቃል ተመልሶ ወደ ጎልጎታ የገበባበት ቀን ነው፡፡

የቀድሞ አባቶች ታክን ከታሪክ ማገናኘት ልማዳቸው ነውና መስቀሉ መጋቢት 10 ቀን ወደ ጎልጎታ እንዲገባ ያደረጉት ቀድሞ ከተገኘባት ቀን ጋር ለማስተሣሠር ሊሆን ይችላል፡፡ በስንክሳራችን መስከረም 16 ቀን በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው በንግሥት እሌኒ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት በመስቀሉ የተባረኩበት ቀን መሆኑን ይነግረናል፡፡ መስከረም 17 ቀን ደግሞ ቅድስት እሌኒ መስቀሉ በተገኘበት በጎልጎታ ያሠራችው የመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ነው፡፡

ነገር ግን በዐቢይ ጾም በዓል ስለማይከበር የመስቀሉ በዓል ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት ቀን በመስከረም 17 እንዲከበር ሊቃውንት ሥርዓት መሥራታቸውን ስንክሳሩ ይነግረናል፡፡

እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገባ?

ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደገባ ሁለት ዓይነት ታሪኮች አሉ፡፡ አንዱ ከግብጽ ሁለተኛው ከኢየሩሳሌም፡፡ ለመስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት የሆነው በዐፄ ሠይፈ አርእድ ተፈጥሮ የነበረ ችግር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የግብጽ ሡልጣኖች በግብር እያመካኙ የግብጽ ክርስቲያኖችን ባሰቃዩዋቸው ጊዜ ንጉሥ ሠይፈ አርእድ እስከ ደቡብ ግብጽ እየዘመተ ወግቷቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ የንግድ መሥመሩን ከለከለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ እና ከኑቢያ የሚሄደው ዕቃ ተቋረጠ፡፡

ሁኔታው ከሥጋት ላይ የጣላቸው የግብጽ ሡልጣኖች በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የጣሉትን ቀንበር አላሉ፡፡ የግብጹ ጳጳስ እና ሡልጣኑ ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ መልክተኛ ላኩ፡፡ በጉዳዩም በኢየሩሳሌም የነበሩት ፓትርያርክ ዮሐንስ ገቡበት፡፡ አቡነ ዮሐንስ የመልክተኞቹ መሪ ሆነው መጡ፡፡

በጊዜው በዙፋኑ ላይ የነበረው ዐፄ ዳዊት ስለነበረ እርሱም ንግዱን ላይዘጋ ሡልጣናቱም ክርስቲያኖቹን ላያጉላሉ ተስማሙ፡፡ ለስምምነቱ ማሠርያ ይሆን ዘንድም ከጌታ ግማደ መስቀል እንዲመጣለት ንጉሥ ዳዊት ጠየቀ፡፡ ሡልጣኑም ተስማማ፡፡

በ1387 ዓም ግማደ መስቀሉን የሚያመጡ ሊቃውንት ወደ ካይሮ ተላኩ፡፡ መልክተኞቹ ለሡልጣኑ የሚሰጥ በ20 ግመል የተጫነ ስጦታ ይዘው ነበር፡፡ ዐፄ ዳዊት አስቀድሞ ሃሳቡን ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአቡነ ዮሐንስ ነግሯቸው ስለነበር እርሳቸው ሉቃስ የሳላትን ሥዕል፣ ኩርአተ ርእሱ የተባለውን የጌታ ሥዕል እና ግማደ መስቀሉን ላኩለት፡፡ ግማደ መስቀሉ መስከረም 16 ቀን ተጉለት ገብቶ ንጉሡ ባሳነፁት ቤተ ክርስቲያን የቀመጠ፡፡ /ተክለ ጻድቅ መኩርያ፣ ከይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል፣ ገጽ 116-118/

በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ለመቀበል ዐፄ ዳዊት ወደ ስናር ወርደው ነበር፡፡ በዚያም ባዝራ ፈረስ ጥላ ስለረገጠቻቸው ሞቱ፡፡ ግማደ መስቀሉም በስናር ቆየ የሚል ታሪክም አለ፡፡ ይህንን ታሪክ ለመቀበል የሚከብደው በወቅቱ ሱዳን በዐረቦች መወረሯንስናርም ለግዛታቸው ቅርብ የነበረ መሆኑን ስናስበው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ከዐፄ ዳዊት እስከ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ሠላሳ ዓመታት በዚያ ተቀመጣ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የተክለ ጻድቅ መኩርያ ትረካ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

በሌላም በኩል ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም መጣ የሚለው ታሪክ በወቅቱ ኢየሩሳሌም ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በ1187 ዓም ሳላሕ ዲን ኢየሩሳሌምን ከያዛት በኋላ መስቀሉ ከአካባቢው ተሠውሯል፡፡ የሮም ነገሥታትም እርሱን ለማግኘት ተደራድረው አልተሳካላቸውም፡፡ የመስቀል ጦረኞችም ቢሆኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ሌሎችን ንዋያት አመጡ እንጂ መስቀሉን አላገኙትም፡፡

እንደ እኔ ግምት ግማደ መስቀሉን ያገኘነው ከእስክንድርያ መሆን አለበት፡፡ ንግሥት እሌኒ የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናትን ሠርታ ስታጠናቅቅ የቁስጥንጥንያ፣ የአንፆኪያ እና የእስክንድርያ አባቶች ካህናትን ልከዋል፡፡ ግማደ መስቀሉ ወደ እስክንድርያ የገባው በዚያ ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በኋላም ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ሲጠይቅ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ላደረገው ውለታ ልከውለት ይሆናል፡፡ በሌላም መልኩ ሡልጣኑም ግፊት ማድረጉ አይቀርም፡፡

አያሌው ተሰማ የተባሉ ምሁር «ታሪክ ነው ገበያ፣ የሁሉ መዋያ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ያገኘው ዓባይን ገድቦ ግብፆችን በማስጨነቅ ነው ይላሉ፡፡ ሁኔታው ያሰጋቸው የግብጽ ባለ ሥልጣናት ለላኳቸው መልክተኞች ግማደ መስቀሉን እንዲሰጧቸው በመጠየቃቸው ሡልጣናቱ ግብፃውያኑን አባቶች ተጭነው እንዳሰጧቸው ይተርካሉ፡፡

ደመራ

የደመራ በዓል መላዋን ኢትዮጵያ ከሚያስተሣሥሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት የደመራ በዓል መነሻ ንግሥት እሌኒ ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ስለ ንግሥት እሌኒ በተጻፉት ጥንታውያን መዛግብት ሁሉ ይህንን የሚደግፍ ነገር አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ቤት ሲከበር አበው ሊቃነ ጳጳሳት መስቀሉን ይዘው ችቦ አብርተው እየዞሩ መባረካቸውን የሚገልጡ መዛግብት አሉ፡፡

ኢትዮጵያውያንም ይህንን በመያዝ የመስቀልን በዓል በደመራ በዓል ማክበር ጀምረዋል፡፡ ደመራ የአባቶቻችን የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ እንጂ ከውጭ አልመጣም፡፡ የጌታችንን ጥምቀት በዓል ታቦቱን በበዓለ ከተራ ይዞ በመውረድ እና በበዓሉ እንዲመለስ ሥርዓት እንደሠሩት ማለት ነው፡፡

የደመራ ሥርዓት ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ በተመሳሳይ ሰሞን እና ሥርዓት ይከበራል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ወርቃማው የክርስትና ዘመን የሚባለው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን እስከ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያለው ዘመን ነው፡፡ የመስቀል ደመራ ሥርዓት በደቡብ ውስጥ የሠረፀው እና መከበር የጀመረው በዚህ ዘመን ወይንም ቀደም ብሎ መሆን አለበት፡፡ አንድን ሥርዓት ባህል ለማድረግ ብዙ መቶ ዓመታት ያስፈልጋልና፡፡

በደቡብ ግራኝ ሊያጠፋቸው ካልቻሉ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶች አንዱ መስቀል ነው፡፡ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጉራጌ፣ በከፋ ሸካ ከነ ክብሩ እና ሞገሡ አሁንም ይከበራል፡፡ አንዳንድ ሕዝቦች ትምህሩ ጠፍቶባቸው እንኳን ሥርዓቱን አልረሱትም፡፡

ይህ ነገር የደመራ በዓል ከግማደ መስቀሉ መምጣት በፊት በሀገራችን ሊኖር እንደሚችል ያመለክታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዜና መዋዕሎችን እና መዛግብትን ማገላበጥ ገና ይቀረናል፡፡

በሌላም በኩል የደብረ ታቦርን እና የአዲስ ዓመት መለወጫን በዓል በደመራ እና በችቦ የማክበሩ ባህላችን ደመራ ከመስቀል በዓል ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን ፍንጭ ይሰጠናል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይህንን ችቦ የማብራት ሥርዓት ከጥንት ሀገራዊ ባህል እና ከኢየሩሳሌም መብራት የማውጣት ሥርዓት የቀመሩት ይመስላል፡፡ በኢየሩሳሌም ከጌታ መቃብር በየዓመቱ ለበዓለ ትንሣኤ መብራት የማውጣት ሠርዓት ነበር፡፡ ይህ ሥርዓት ልዩ ልዩ የፈትል እና ዘይት መብራቶችን በአንድነት አስተሣሥሮ ይዞ መውጣት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በኢትዮጵያዊው ችቦ በመወከል በበዓል ቀን እንዲበራ ሥርዓት የሠሩልን አባቶች በረከታቸው ይደርብን፡፡

ግሼን እና ግማደ መስቀሉ

ግማደ መስቀሉ የተቀመጠው በግሼን ማርያም መሆኑን በገዳሙ የሚገኘው መጽሐፈ ጤፉት ይናገራል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት መስቀሉን በመስቀልኛ ቦታ አስቀምጥ የሚል ራእይ ለዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በመገለጡ ነው፡፡ አምባ ግሼን ከንጉሥ ይኩኖ አምላክ ጀምሮ የነገሥታቱ ልጆች የሚቀመጡባት ቦታ ነበረች፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ይነግሥና ሌሎቹ በግሼን በምባ ይቀመጣሉ፡፡ በዚያ ቦታ ለነገሥታቱ ልጆች የተሠራ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ መንግሥት እና የወግ ዕቃ ቤት ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የግእዝ መጻሕፍት ቦታዋን በልዩ ልዩ ስም ይጠሯታል፡፡ «ደብረ ነገሥት» የነገሥታት ቦታ፣«አምባ ግሼን»፣ ደብረ ከርቤ፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግሼንን የሚያውቃት እንደ ሌሎቹ የነገሥታት ልጆች ተይዞ በአምባው ታሥሮ በነበረ ጊዜ ነው፡፡ ዐፄ ዳዊት ያመጣውን ግማደ መስቀል ለማክበር ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያሰበበት ምክንያት ነበረው፡፡ በመጀመርያ እንደ ታሪክ ነገሥቱ ከሆነ መስቀሉ የነበረበት ቦታ እና ዘርዐ ያዕቆብ የነገሠበት ቦታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም ተጉለት ውስጥ ነው የነበሩት፡፡ በሌላም በኩል ዘርዐ ያዕቆብ ለመስቀል ልዩ ፍቅር ስለነበረው መስቀሉን ለጊዜው ከተሠራለት ቦታ በዘላቂነት ተጠብቆ ወደሚቆይበት ቦታ ለማዛወር ፈለገ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ያንን ራእይ ያየው፡፡

እስካሁን የሚገርመው ነገር መስቀሉ በግሼን አምባ ከተቀመጠ በኋላ ምእመናኑ እንዴት ይሳለሙት እንደነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም አምባው በወታደሮች የሚጠበቅ እና የነገሥታቱ ልጆች ብቻ ይገቡበት የነበረ ቦታ ነበርና ነው፡፡ ግራኝ አምባውን ለመስበር ሁለት ጊዜ አለመቻሉን ስንረዳ አምባው ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ያሳያል፡፡ ምናልባት ምእመናን እንደልባቸው ወደ አምባው መግባት የቻሉት ከግራኝ በኋላ አምባው የነገሥታት ልጆች ወኅኒ መሆኑ ሲቀር ነው፡፡ በጎንደር ዘመን ደግሞ ወኅኒው ወደ ወኅኒ አምባ በመዛወሩ ምእመናኑ እንደ ልብ መግባት ችለዋል፡፡

የግራኝ ሠራዊት ወደ አምባው በወጣ ጊዜ የካቲት 22 ቀን 1532 ዓም የነገሥታቱን የወግ እቃ መዝረፋቸውን እንጂ ግማደ መስቀሉን ለማውጣት መሞከራቸውን አይገልጥልንም፡፡

አሁን ያለውን የእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ዐፄ ምኒሊክ ሲሆኑ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ደግሞ እቴጌ መነን ናቸው፡፡ /ልዑል ራስ እምሩ ኃ/ሥላሴ፣ ካየሁት ከማስታውሰው፣ ገጽ 168፣ 169/

እስካሁን ትክክለኛ ምክንያቱን ያላገኘሁት ግሼን የግማደ መስቀል መንበር ሆና እያለ በዓለ ንግሡ በመስከረም 21 ለምን እንደ ሆነ ነው?

ግማደ መስቀሉን በተመለከተ ሊጠኑ የሚገባቸው ነገሮች

1. ኢትዮጵያ ጥንተ ክርስቲያን ሀገር ሆና፣ በጎልጎታ ጥንታዊ ገዳም የነበራት ሀገር በመሆንዋ፣ ገዳምዋም ከመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በመሆኑ ግማደ መስቀሉን እንዴት ሳታገኘው ቀረች?

2. ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በ348 ዓም በጻፈው ጽሑፍ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሳለም የሚመጡ ሁሉ ከመስቀሉ ቁራጭ ይወስዱ እንደ ነበር ገልጧል፡፡ ታድያ ኢትዮጵያውያን ሳያመጡ ቀሩን? ተጨማሪ ጥናት በተለይ በጣና ገዳማት፣ በትግራይ እና በኤርትራ ገዳማት ይቀረናል፡፡

3. ስለ ግማደ መስቀሉ አመጣጥ ግብጻውያን መዛግብት ምን ይላሉ?

4. ግማደ መስቀሉ በየት በኩል መጣ? ከስናር ወደ ግሼን ወይስ ከስናር ተጉለትግሼን፡፡ በተለይም በተጉለት አካባቢ ተጨማሪ መረጃዎች የማፈላለግ ሥራ ይቀረናል፡፡

5. ስለ መስቀል በዓል አከባበር በዜና መዋዕሎቻቸን እና በገድሎቻችን የሚገኙ ተጨማሪ መረጃዎች ካሉ?

እስኪ የምትችሉ በርቱ፡፡27 comments:

 1. really really i like it,it is an interesting history of finding the true cross of our God Jesus Christ. please keep on what you are doing,may the peace of Lord be with you forever!

  ReplyDelete
 2. ሲሎንዲስ ዘአውሮፓSeptember 28, 2010 at 3:56 PM

  Dear Dn Daniel,the entire study is a real piece of work.

  እስከዛሬም ልንወያይበትና መዛግብትን ልናገላብጥበት የሚገባ ትልቅ ጉዳያችን ነበር።
  በዘመን ርዝመትና አሁን ባለንበት የድህነት ስም ምክንያት ከሀገራችንና ከሃይማኖታችን ጋር ተያይዘው የሚነሱ ታሪኮች ሁሉ ተረት ተረት የሚመስሏቸው ጥቂቶች አይደሉም።
  መዛግብትን ማገላበጡ አለዕውቀትና ሆን ተብሎ የገቡ አንዳንድ ከቤ.ክ አስተምህሮ ጋር የማይሄዱ ጉዳዮችን ለመለየት ይረዳል።ለሁሉም ሀገራዊና ሀይማኖታዊ ታሪኮች መልስ ባይሰጥም እንኳን።የመስቀሉን ታሪክ በተመለከተ የተጠቀሱት መዛግብትና የታሪክ ጸሐፍት ይበልጥ ታሪካችንን እንድናምነውና በደንብ ፈትሸን ለሌላውም በሚገባ እንድናሳውቀው የሚገፋፉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው።
  የደመራውን ሥርዓት መነሻ በተመለከተ እኔ የመጀመሪያውን ምልከታ እጋራለሁ፣ንግስት እሌኒ ከፓትርያርኩና ሌሎች መንፈሳውያን አባቶች ጋር በመሆን እግዚአብሔርን በጸሎት እንደጠየቀች አምናለሁ።በቤ.ክ የጸሎት ሥርዓት ዕጣን ሲታጠን ጢሱ ወደ ጎለጎታ አመለከተ የሚለውም አሳማኝ ሆኖ እንደተባለው ይህን የሚያብራሩ መዛግብትን መመርመር መልካም ነው።ደመራ የመደመር ባህሉ ከአዲስ ዓመትና ከቡሄ ጋርም የተያያዘ ነው ተብሎ ለተጠቀሰው ግን ይህ በሁሉም የሀገራችን ክፍል ባህል እንዳልሆነ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ይመስለኛል።እኔ እስከማውቀው ድረስ በሰሜኑ አካባቢ ይህ እምብዛም አልተለመደም፤በመሐል አገርና አካባቢው ግን ጎልቶ ይታያል።ፍተሻው ያስገረመኝ ከዚህ ሁሉ ዘመን ቅብብሎሽ በኋላ እንኳን በመረጃ አያያዝ የምናደንቃቸው የውጪው መዛግብት እኛ ከምናውቀው ብዙም የሚለይ ታሪክ አለመያዛቸው ነው።ልብ የሚሞላ ተጨማሪ መረጃ ሌሎች መዛግብት ከሌላቸው በእምነት የተቀበልኩት ታሪክ በልቤ ይኖራል።እግዚአብሔር በመስቀሉ ላይ የገለጸው ፍቅር ሁላችንንም ለሰማያዊ ክብር ያብቃን።

  ReplyDelete
 3. Now I am so happy. All my unanswered questions have been answred correctly.
  Edmewon Yistihna Tsafilin.

  This is what every one was looking and our church's stand.

  ReplyDelete
 4. I don't understand why you ignored "Dirsane Meskel" which could have served as an important source for such article. Infact, Dirsane Meskel does have all the answers for any historical questions regarding the Holy Cross.

  ReplyDelete
 5. ደብረ ቁስቋም
  በእውነት የሚገርም እይታ ነው እርግጠኛ ነኝ ረጅም ግዜ የወሰደ ጥናት ነው.ዛሬ ቤተክርስትያንዋ የሚያስፈልጋት እዲህ አደርጎ ለመንጋው የሚ ብራራ በሁለቱም ሳይድ የተሳለ ሰይፍ ማለት ይሄ ነው.እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው በቁጥር 1 ላይ ለነበሩን ጥያቄዎች በሙሉ ተመልሱዋል የረጋወተት ቅቤ ይወጣዋል ማለት ይሄ ነው.ወንድማችን እጅግ የሚገርም እይታ ነው በርታ በርታ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሄር መላ ቤተሰብህን ከሰይጣን ፈተና ይጠብቅልህ የበላየሰብ እመቤት አትለይህ በእውነት በርታልን እኔበራሴ ትልቅ እውቀት ነው ያገኘሁበት አያቹ ለሰዎች በደፈናው እንዲህ ነው ከማለት እንደኔ እንደኔ እንዲህ በጥናት የተደገፈነገር ያሳምናል ደግሞም ያስመሰጋናል.በዚህ አጋጣሚ ወንድሞቼና እህቶቼ {tewahido.org}ለይ ያለወነ የወነድማቸንን አነደ ሆነን ችግሩን አንፍታ ሠይስ ቸችሩ ሰሲታ አነድ እንሁን ያልሰመችሁት እባካችሁ ስሙት.
  አምላከ ቅዱሳነ ሁላችንን ይጠብቀን.

  ReplyDelete
 6. Great job Dn Daniel.

  Dear Anonymous,
  If you know "Dirsane meskel", please do your part and share us. The writer has researched based on what he has read. he also invite everyone to look for additional sources that could answer questions raised in the article. So, please, dirshahin teweta eski by bringing at least some quotes from "dirsane Meskel". we visit this site to learn.
  God Bless you all.

  ReplyDelete
 7. KaleHiwot Yasemalen Dn. Daniel.
  once when i was visiting Daga Estifanod monastry in tana the monk showed as the stripe in the middle of the hand cross and he said the small stripe is from the true cross.may be if it helps to research further on it.

  ReplyDelete
 8. ዲ/ዳንኤል እግዚአብሔር ያበርታህ የዚህ አይነቱ ስራ በአጅጉ ሊተጋበት ያስፈልጋልና ለሁላችንም እግዚአብሔር መነሳሳትን ያድለን አንተንም እድሜውን ያድልህ

  ReplyDelete
 9. Qale Hiwot yasemalene Rejem Edma, Tenawen ena Yestega balebet yehone Amlake Tesegawen Atrefrfo Yestelegn. Ejeg Yemiyareka Rejmun yemesqel tarik bachruna bemigeba melk newena yasqemetkew Berta Egziabhare Beberketu hulam Yegognlegn.

  ReplyDelete
 10. ስለ ጽሑፉ እግዚአብሔር ይስጥህ:: ጥሩ መነሻ ቢሆንም ብዙዎቹ የአንተን አስተያዬትና መላምት ያንጸባረቅህባቸው ናቸው:: ታሪክ ተቀባይነት የሚኖረው የጽሑፍ ማስረጃ ሲኖረው ብቻ ነው እንዴ? ስለ ቅ/መስቀሉ መጥፋት፣ መገኘትና ስለ ደመራ በዓል አመጣጥ የሚተርኩትን እኮ አልጠቀስህም ማለት ይቀላል::

  "በወቅቱ ይህ አይሁዳዊ ስለ ዕጣንም ሆነ ጸሎት ሊናገር የሚችል አይመስልም፡፡ ይህ ሃሳብ ምናልባት በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአቡነ መቃርዮስ ይሆናል፡፡" አይሁድ ጠቢባን እንደመሆናቸው ኪርያኮስ ይህንን እንዴት ላይመክር ይችላል? ዕጣን መጠቀም የተጀመረው በሐዱስ ኪዳን ከሆነ ያንተ ሐሳብ ያስኬዳል::

  "1. ኢትዮጵያ ጥንተ ክርስቲያን ሀገር ሆና፣ በጎልጎታ ጥንታዊ ገዳም የነበራት ሀገር በመሆንዋ፣ ገዳምዋም ከመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በመሆኑ ግማደ መስቀሉን እንዴት ሳታገኘው ቀረች?" አሁን ግማደ መስቀሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም እያልህ ነው ወይስ ከእስክንድርያ ከመምጣቱ በፊት ማለትህ ነው?

  ReplyDelete
 11. Good Job.
  ቃለ ህይወት ያሰማልን። ጤና እድሜውን ያድልልን።

  ReplyDelete
 12. Hello there,
  I've been following this blog the past 5 months. And I'm happy that I have come to know a lot of things about my Church and other stuffs. This time I want to say something because like my brothers and sisters I was confused by your presentation about the finding of True Cross. In fact, yesterday at home we were all confused by it. I want to ask the following questions
  1. Are you saying that the whole story about the finding of the True Cross which we have been learning is not true?
  2. If (Which I doubt it) it is not true, where can we find the true story?
  God Bless You!!

  ReplyDelete
 13. Minew Weyra Kena kenawun bitayina Yalaweknewun kawokut binmar

  ReplyDelete
 14. ቃለ ህይዎት ያሰማልን ውድ ዎንድማችን(አባ መስጠት) በአገልግሎት በጸጋ ይጠብቅልን!
  እንደኔ መነሳት የሚገባቸው ተነስተዋል ብየ አምናለሁ፡፡ነገር ግን ወንድማችን እንዳለን ያለን እናዋጣ በአፋዊ ያሉትን(አይታመኑም ማለቴ አይደለም) በጽሑፍ እናርጋቸው፡፡አሁን በመሰረታዊነት ክፍት ከተተዉት መካክል መልስ ያላችሁ አካፍሉን፡፡ለምሳሌ ከላይ ዳጋ እስቲፋኖስ ሰማሁት እንዳሉት፡፡በተለይ ግን ስለደመራ አመጣጥ በሚገባ ማወቅ ይጠበቅብናልና እስቲ አንብበን እንገናኝ ፡፡

  እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን!!

  ReplyDelete
 15. This is good view.there r many traditional sayings w/c contradict each other.for eg.tabote tsion endet wed Ethiopia endegebach.we have been using z traditional saying that it was brought by Minilik first but studies showed that(the sign&seal,the relic Quest) different history of entery.can u say some thing about zis?

  ReplyDelete
 16. "ደመራ የአባቶቻችን የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ እንጂ ከውጭ አልመጣም፡፡"
  ለማለት የፈለከው ገብቶኛል ግን አባቶቻችን ስንል...ከውጪ ያሉትን ጭምር ስለዚ...
  (አስተያየቱን በቅንነት አንብበው አንተ ካነበብከው ይበቃኛል ፖስት አታድርገው)

  ReplyDelete
 17. ጊዜው የመረጃ ነው የተሰጠንን መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች በመረጃ ለመመለስ የአቅማችንን እንሞክር ከእግዚያብሔር ጋራ
  አሁን በጣም የታሪክ ሽሚያ ስላለ እንደዚ አይነት ልጆች ቤተ ክርስቲያን ስለሚያስፈልጋት ሁላችንም እንበርታ ማንም ሲወለድ እንዲ ሆኖ አልተወለደምና።

  ReplyDelete
 18. የመስቀል ደመራ የተጀመረው በንግስት እሌኒ ዘመን የአንድን ነገር ደስታ ለመግለጥ ችቦ ይዞ ደመራ ደምሮ በእሳት በማቀተአጠል ነበር:: በዚህም ምክንያት ንግስት እሌኒ መስቀልሉን አውጥታ ስትመለስ ደመራ በመደመር ችቦ በማብራት ደስታዋን እየገለጠች ወደ ሀገሩዋ ስለተመለሰች በዚህ ምክንያት ነው::
  ሌላው ደግሞ መስቀሉ ያለበትን ቦታ ለማወቅ ደመራ አስደምራ ከተጸለየ በሁላ ደመራው ሲለኮስ ጭሱ ወደላይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ያለበትን ጠቁሞ አሳየ:: ቅዱስ ያሬድ ሰገደ ያለውም ከዚህ ጋር ይስማማል::
  ዳቆን ዳኒኤል ያቀረበውን ጥናታዊ ጽሁፍ ሲደመርበት ታሪኩን ዬበለጠ እውን ያደርገዋል ያጎላዋልም::

  ReplyDelete
 19. It is difficult to forward research-based ideas in oral society (which is typical of us: Ethiopian).

  What has been written by Dn. Daniel is based on survey of available documents on the issue.

  Now if anyone has come across any document that contradicts this, we are wel-come to transpire it. Otherwise, why should we be weird?

  This generation is asking fundamental questions regarding our church history and related issues. If we want to keep this generation, such questions must be answered with tangible analysis and documents(in fact apart from the dogmatic part). This calls for systematic studies that convince the generation. Yalinihin gid tekebel malet aychalim. Otherwise we can't keep the generation within the church. There are people who shivers while they see something based on evidences. Do they mean that we be part of the tewahido church only by "afetarik"?

  Tesfa

  ReplyDelete
 20. kalhiwot yasmalen
  alex .a

  ReplyDelete
 21. Great Dn Daniel-our big brother. Thank you very much. Keep it up please.

  ReplyDelete
 22. I am of the opinion that Ethiopia is not a country with an oral society. Our fathers left a number of written sources about our religion, politics,social life and even scientific background. It is a recent discovery that we have A HOLY BIBLE written in the fifth century when the western world was not that much advanced. The general statement that western historians hold about African society is not true for Ethiopia.

  It is the responsibility of this generation to search for a written evidence. Our fathers toil day and night. Thy left as a written documents which have an awesome information about our History. They also pave the way for many scientific discovery. The Westerners Knew this well more than the owners of the documents. Professor Getachew Haile Said that YETALAKUA ETHIOPIA TARIK METSAF TEJEMERE ENJI ALALEKEM. It is also true that our religion is the major part of our history.

  So it is better not to be confused while we have got such a piece which is rich in evidence but not exhaust all of them as He himself admitted. Rather lets contribute our share by investigating other documents.

  Thanks Dani For Your Initiation. May GOD Be With You All The TIME, Amen!

  ReplyDelete
 23. ቃለ ህይወት ያሰማልን። ስለ መስቀሉ ጥሩ ትምህርት አግኝቼበታለሁ።
  ግማደ መስቀሉን በተመለከተ ሊጠኑ የሚገባቸው ነገሮች ላልከው ሀሳብ ለመስጠት ያክል ግሼን ከመሄዱ በፊት ብዙ ቦታ ላይ እንዳረፈ እሰማለሁ ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ጉንዶ መስቀል(ደራ) ሰሜን ሸዋ ውስጥ የሚገኝ ከተማ ነው እዚህ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ እንደተቀመጠ ይናገራሉ። የቦታውም ስያሜ ከዛ የመጣ ነው። እንዲያውም መስቀለ ኢየሱስ የሚባል ቤ/ክርስቲያን አለ ግማደ መስቀሉ እንደ ነበረ የሚያሳይ የመስቀል ቅርጽ መሬት ላይ ተሰርቶ ይታያል። ሌላው በቦታው ላይ ያሉ ከርስቲያኖች ለመስቀሉ ያላቸው ፍቅር ከሌላው ከርስቲያን ለየት ያለ መሆን ከነሱ ጋር አብሯቸው እንደቆየ አመላካች ነው ይህውም ሁሉም ቤተሰብ ከልጅ እስከ አዋቂ በየ አመቱ የ6ቀን መንገድ በእግራቸው በመሄድ ግሸን መክበራቸው ነው።በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ ሰሜን ሸዋ ሌላም ቦታ ላይ ተቀምጦ እንደነበር ይነገራል የኔ አስተያየት እነዚህ ቦታዎች በመስቀሉ ዙሪያ ላልተመለሱ ጥያቄዎች መልስ ልናገኝባቸው እንችላለንና ጎራ ብለን መጸሐፍትንና ታሪኮችን እንፈትሽ "ቤተ ክርስቲያን መልስ አላት" እላለሁ

  ReplyDelete
 24. when i was in Weldia town i heard the "gubta",on the hill(along the way from debre gelila to tinfaz)around st.georgis church, was formed by the time the True CROSS was rested for a moment being taken to Ambasel. i don know wheather it helps. thaks a lot.

  ReplyDelete
 25. It is very interesting, Daniel I hope There are so
  many monastery and ancient hidden churches in Ethiopia, Who knows, WE might gate Big BRANA BOOK
  LIKE THE DEAD SEA SCROLLS.
  DURING THE TIME OF YODIT AND GRANGNE AHMED MOST OF
  OUR CHURCH AND HISTORY BRANA WAS IN FIRE IT COULD
  BE ONE OF THEM

  ReplyDelete
 26. ቃለ ህይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 27. በጣም አስተምረሀናል. እግዚኣብሄር አገልግሎትህን ይባርክልህ. ቃለ ህይወት ያሰማልን. ስለ ተዋህዶ እምነትና የስንክሳር ትምርቶችን ተአምሮች እንድታስተምረን በትህትና እንጠይቃለን.

  ReplyDelete