Sunday, September 19, 2010

ለጠላት አንድ ሺ፣ ለወዳጅ አንድም

የዓለም የወዳጅነት ቀን ሲከበር አንድ ወዳጄ እንዲህ የሚል ጥቅስ ላከልኝ «ጠላትህ ወዳጅህ ይሆን ዘንድ አንድ ሺ ዕድል ስጠው፤ ወዳጅህ ጠላትህ ይሆን ዘንድ ግን አንድም ዕድል አትስጠው»፡፡ እነሆ ይህ ጥቅስ ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡

እውነት ነው በዚህ ዓለም ላይ ወዳጅ እንደ ማፍራት የከበደ፤ ጠላት እንደማፍራትም የቀለለ ነገር የለም፡፡ እሥራኤልን ያህል ሳኦል፣ ዳዊት እና ሰሎሞን አንድ አድርገው የገዟትን እና ገናና መንግሥት የነበራትን ሀገር ለውድቀት የዳረጋት የሮብዓም ከንቱ ንግግር ነበር፡፡ አያሌ ወዳጆችን ሊያፈራበት የሚችለውን ንግግር ጠላት ማፍርያ አደረገውና የእሥራኤልን ጠላት ከእሥራኤል መካከል አሥነሣባት፡፡

በአባቱ ዘመን የነበረው ቀንበር የተጫናቸው ወገኖቹ መጥተው «አባትህ ያከበደብንን ቀንበር አቅልልን» ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም በአባቱ በሰሎሞን ዘመን የነበሩት አማካሪዎች የነገሩትን ትቶ ከብላቴኖች ጋር ተማከረና «ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔም በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል፤ እኔም በጊንጥ እገርፋችኋለሁ» ብሎ ተናገራቸው፡፡

ይህ ንግግሩ እሥራልን «ሰማርያ» እና «ይሁዳ» ብሎ ለሁለት ከፈላት፡፡ ከዚያ በኋላ የደረሰው የእሥራኤል ውድቀትም በመከፋፈሏ ምክንያት የተከሰተ ነበር፡፡

ሮብዓም የሕዝቡን ቀንበር ባያቀልል እንኳን በመልካም ንግግር በመናገር፣ ለምን ቀንበሩን እንደ ማያቀልም በማስረዳት ቢያንስ ሕዝብን ከማስቆጣት እና ጠላትን ከማፍራት ይድን ነበር፡፡ ሌላውን ወገን በማስቆጣት፣ በማበሳጨት፣ በማናደድ እና በማስቀየም ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡በማስ ረዳት፣ በማግባባት እና በማሰለፍ እንጂ፡፡ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ባለ ሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች እና ሌሎችም የሚናገሯቸው ንግግሮች እንደ ጨው የተቀመሙ መሆን አለባቸው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ንግግራቸው የሮብዓምን ውጤት ሊያመጣ ይችላልና፡፡

በተለይም መሪዎች የሚናገሯቸው ንግግሮች ፍቅርን፣ አክብሮትን፣ ትኅትናን እና ትኁትነትን የሚያንፀባርቁ፤ ለማናደድ እና ለማበሳጨት ሳይሆን ለማስረዳት እና ለማሳመን የሚቀርቡ፤ አግቦ እና ሽሙጫ፣ ትዕቢት እና ስላቅ የተሞሉ ሳይሆን ዕውቀት እና ተጠየቅ፣ የሃሳብ ልዕልና እና የመረጃ ብልጫ፣ ጨዋነት እና ብልህነት የተሞሉ መሆን አለባቸው፡፡

ዐፄ ምኒልክ በእምባቦ ጦርነት ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተዋግተው ባሸነፉ ጊዜ የጎጃም ጦር ተማረከ፤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ተያዙ፡፡ ያን ጊዜ ዐፄ ምኒልክ «ጠላት አሳስቶህ ነው እንጂ አንተ በኔ ላይ አትዘምትም ነበር» እያሉ ቁስላቸውን በማጠብ እና በራሳቸው በቅሎ በመጫን ነበር ተሸንፎ ሊሸፍት የነበረውን የጎጃም ጦር በፍቅር የመለሱት፡፡ እንዲያውም በአድዋ ጦርነት ከልዩ ልዩ ጎሳዎች፣ ነገዶች፣ የመጡ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው እንዲዘምቱ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ የዐፄ ምኒሊክ ጠላትን ወዳጅ የማድረግ ስልት ነበር ይባላል፡፡

አንዳንዶቻችን ጠባያችንን እና አቋማችንን እኛ ሳንሆን ሌሎች እንዲወስኑ እንሰጣቸዋለን፡፡ ደግነታችን በክፉዎች፣ ለጋስነታችን በስስታሞች፣ ሰላማዊነታችን በጦረኞች፣ ሕግ አክባሪነታችን በሕገ ወጦች፣ ታማኝነታችን በአጭበርባሪዎች ይወሰናል፡፡ የአንድ ዳኛ ፍትሐዊነት የገዛ ጠላቱ በችሎቱ ሲቀርብ መለወጥ የለበትም፡፡ ፍትሐዊ ከሆነ ፍትሐዊነቱ ጠላቴ ነው ለሚለውም ሰው መሆን አለበት፡፡ የአንድ ሰው ቸርነት ንፉግ ሰው ሲገጥመው መቀየር የለበትም፡፡ እርሱ ለጋስ መሆን ያለበት ከራሱ አቋም አንፃር እንጂ ንፉግ እስኪያጋጥመው ድረስ መሆን የለበትም፡፡

እንዲያውም አንዳንዴ በሕይወት ያሉት ጠላቶች አልበቃን ብለው ከሞቱትም ወገን ጠላት ለማፍራት ስንጥር የምንገኝበት ጊዜ አለ፡፡ «እገሌ ጠላቴ ነው፣ እገሌ በወገኖቼ ላይ እንዲህ አድርጓል፤ እገሌ በዚህ ጎሳ እና ነገድ ላይ ይህንን እና ያንን አድርጓል» እያልን ከሞቱ መቶ እና አምስት መቶ ከሆናቸው ሰዎች መካከል ጠላት ለማፍራት መከራ በማየት ላይ ነን፡፡

ለመሆኑ ሰዎች ለምን ጠላቶቻችን ይሆናሉ?

በገዛ ንግግራችን ወዳጅም ጠላትም መፍጠር እንችላለን፡፡ ሌላው ቀርቶ «እባክዎ፣ እግዜር ይስጥልኝ፣ ይቅርታ፣ አዝናለሁ፣ ተሳስቻለሁ» ወዘተ የሚሉትን ቃላት ገንዘብ በማድረግ እንኳን ያለ ብዙ ወጭ ብዙ ወዳጅ ማግኘት እንችል ነበር፡፡ በተለይ በኛ ልማድ የአክብሮት ቃላት ከከተሞቻችን የተሰደዱ ይመስላሉ፡፡ ማመናጨቅ፣ አንጠልጥሎ መጥራት፣ መቆጣት፣ ከፍ ዝቅ ማድረግ፣ ቦታውን ይዘውታል፡፡ አስተናጋጆች፣ የጥበቃ ሠራተኞች፣ የየመሥሪያ ቤቱ ባለ ጉዳይ ተቀባዮች፣ ባለ ሥልጣኖች፣ ፖሊሶች፣ ዳኞች፣ የእምነት አባቶች የትኅትና እና የአክብሮት ቃላት ድርቅ መትቶናል፡፡ «እባክዎ» «በሞቴ» የሚሉት ቃላትማ «ጥፊ፣ ሂጂ፣ ብረሪ» አለኝ ብለው ሳይሸሹ አይቀሩም፡፡

የአንዳንዶቹ ጥላቻ ከመረጃ እጥረት ነው፡፡ ስለኛ ያላቸው መረጃ ከሚያስፈልጋቸው በታች ይሆንና በቀረው ቦታ አሉባልታ እና ወሬ ይሞሉበታል፡፡ ከዚያም ወዳጃቸውን መጥላት ይጀምራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የተሳተ መረጃ ከማግኘታቸው ይመነጫል፡፡ አንዳንዶቻችን የሰማነውን ሁሉ ያለ ምንም ጥርጣሬ እናምናለን፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማፈላለግ፣ ከሌሎች ምንጮችም ለመስማት፣ ብሎም ባለቤቱ እንዲናገር እድል ለመስጠት አንፈልግም፡፡ በዚህ የተነሣ ከተሳሳተ መረጃ ተነሥተን የተሳሳተ ውሳኔ እንወስናለን፡፡

አንዳንዶቻችን ደግሞ ልዩነትን ሁሉ ጠላትነት አድርገን ስለምንወስደው ነው፡፡ የኛን ሃሳብ የማይቀበለውን፣ በሄድንበት መንገድ የማይሄደውን፣ ያልነውን የማይደግመውን፣ ካዘዝነው ምግብ የተለየ የሚያዝዘውን፣ ከምናምነው ውጭ የሚያምነውን፣ ከለበስነው ውጭ የሚለብሰውን ሁሉ ጠላት አድርገን እንወስደዋለን፡፡ አሜሪካኖች በቀዝቃዛው ጦርነት ይከተሉት እንደነበረው አሠራር «ወይ ከኛ ወገን ወይንም ከጠላቶቻችን ወገን» ብለን እንፈርጃለን፡፡ በዚህም የተነሣ በሃሳብ ተለይተውን ነገር ግን ወዳጆቻችን ሊሆኑ የሚችሉትን አካላት ጠላቶቻችን እናደርጋቸዋለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ወረተኞች እና ነገን የማናስብ በመሆን ለዕለቱ ብቻ የሚሆን ነገር ስንናገር እና ስናደርግ በዘመናት ውስጥ ጠላቶችን እናፈራለን፡፡ የምናደርገው እና የምንናገረው ነገር ከመርሐችን እና ከአቋማችን የሚመነጩ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከመረጃ እና ከማስረጃ መነሣት ቢችሉ መልካም ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ብንሳሳት እንኳን ስሕተታችን ተችዎችን እንጂ ጠላቶችን አያፈራም፡፡

አንድ ወቅት የሚፈጥረውን ሞቅታ እና አጋጣሚ በመጠቀም፣በወቅቱ የተነሡ መሪዎችን፣ ባዕለ ጸጎች፣ ታዋቂ ሰዎች ወይንም ዘመነኞችን ለማስደሰት ሲባል ብቻ በአእምሮ ስካር የሚነገሩ እና የሚደረጉ ነገሮች ታካዊ ጠላቶችን ያፈራሉ፡፡

በአንድ ወቅት ዐፄ ቴዎድሮስ ደጃች ካሣ እየተባሉ ከደጃች ጎሹ ጋር በጉር አምባ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ ከጦርነቱ በፊት አንድ ደጃች ጎሹን ተከትሎ የሄደ አዝማሪ

አያችሁት ብያ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ይዞ ጉር አምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ

ወርደህ ግጠምበት በሽንብራው ማሳ

ብሎ በደጃች ካሣ ላይ የፌዝ ዘፈን ይዘፍናል፡፡ ጦርነቱ ተከናውኖ ደጃች ጎሹ ድል ይሆናሉ፡፡ አዝማሪውም ይያዛል፡፡ ደጃች ካሣም «ለምን እንዲህ ብለህ ሰደብኸኝ» ይሉታል፡፡ እርሱም ባደረገው ነገር ተጠጥቶ

አወይ ያምላክ ቁጣ፣ አወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ለካስ ሥራ ሲያጣ

ሽመል ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

ብሎ በራሱ ፈረደ ይባላል፡፡ ጦርነት የገጠሟቸውን ደጃች ጎሹን በልቅሶ ያስቀበሩት ደጃች ካሣ አዝማሪውን ግን በሽመል አስመቱት ይባላል፡፡ አሁን ምን ክፉ አናገረው? ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ ክፉ ከመናገር ስለ ደጃች ጎሹ አይናገርም?

አንዳንዴም ሳናስበው የምናደርገው እና የምንሠራው ነገር ወዳጆቻችንን ጠላቶቻችን የሚያደርግበት ዕድል አለ፡፡ ለአንዳንዶቻችን ጥሩ መናገር ማለት ብዙ መናገር ይመስለናል፡፡ ጥሩ መናገር ማለት ግን በቂ ዕውቀት፣ ሃሳብ፣ መረጃ እና ጥበብ ያለበት ንግግር እንጂ የቃላት ድሪቶ አይደለም፡፡ ንግግሮቻችን ዕውቀት፣ሃሳብ፣ መረጃ እና ጥበብ ሲጎድላቸው ወደ መለካከፍ፣ መሰዳደብ፣ መወራረድ፣ ይዘቅጣሉ፡፡ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቡድን መሰዳደቦችን እና መቀላለዶችንም ያመነጫሉ፡፡ በዚህ መካከል የሚያመልጡ ነገሮች ብዙ ወዳጆችን ያሳጣሉ፡፡

ሌላው መንሥኤ ደግሞ ተጣጣፊነት ነው፡፡ አቋም እና ወጥነት የሌለው ጉዞ፡፡ እንደ ቦይ ውኃ የመሬቱን ሁኔታ፣ እንደ እስስት የአካባቢውን ሁኔታ፣ እንደ ሱፍ የፀሐዩን አቅጣጫ እያዩ መተጣጠፍ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጠባይ ዛሬ ያስደሰትነውን ሰው ነገ እንድናስከ ፋው ስለሚያደርገን ጠላት እንጂ ወዳጅ አያፈራልንም፡፡ አንድን ነገር የማናደርገው እንደሆነ በምክንያት እና በዘለቄታ አናድረገው፤ የምናደርገው እንደሆነም እንዲሁ፡፡ የማንሄድ ከሆነ በምክንያት እና ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ አንሂድ፤ ከሄድንም እንዲሁ፡፡ ምክንያቶቻችን እና አቋሞቻችን እንደየሁኔታው የሚቀያየሩ ከሆነ የትናንቱን ስለምንረሳው ከራሳችን ጋር የማይጣጣም ነገር ከመፈጸም ወደኋላ አንልም፡፡

ለአንዳንዱ ሰውኮ እንኳን ሌላ ወዳጅ ሊያፈራ የገዛ ጠባዩ፣ ምላሱ፣ ዓይኑ፣ እጁ፣ አመሉ፣ ጠላቱ የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ ሳያስብ ቃል እየገባ የገዛ ቃሉ ያዳኝበታል፤ ሳያስብ እየፈጸመ፣ ዛሬ የሚፈጽ መውም ከትናንቱ ጋር እየተጋጨ፣ የገዛ ሥራው ጠላቱ ይሆናል፡፡

ሰው ዓላማ እና አቋም ያለው፣ ምክንያታዊ እና ዘለቄታዊ ሲሆን እኮ የሚወድደው እንኳን ቢያጣ የሚያደንቀው አያጣም፡፡ የሚቃወሙት እና የሚጠሉት ሰዎች እንኳን ሲያመሰግኑት፣ ሲያደንቁት እና ሲያሞግሱት ይሰማል፡፡ ዛሬ በስደት የሚኖሩት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም «የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች» በሚለው መጽሐፍ ላይ ስለ አንድ ባለ ሥልጣናቸው ተጠይቀው ነበር፡፡ እኒህ ባለ ሥልጣን ከመጀመርያዎቹ የደርግ ባለ ሥልጣናት አንዱ ናቸው ነገር ግን ሃይማኖተኛ እና ጸሎተኛ ነበሩ፡፡ እኒህ ባለ ሥልጣን ታምመው ስለ ነበሩ በመንግሥቱ ፈቃድ ስዊዲን ተልከው በዚያው ቀርተዋል፡፡ ታድያ መንግሥቱ ስለ እኒህ ሰው «ከማንም ሾክሿኳ ኮሚኒስት ነኝ ባይ እንደ እርሳቸው ያለ ሃይማኖተኛ ይሻለኛል» ነበር ያሉት፡፡

ክርስትናቸውን ሳይቀይሩ፣ በክርስትና ሕግ መሠረት ኖረው ነገር ግን ሙስሊሞች የሚወድዷቸውና የሚያከብሯቸው ክርስቲያኖች፤ እስልምናቸውን ሳይቀይሩ እንድ እስልምና ሕግ ኖረው፣ ነገር ግን ክርስቲያኖች የሚወድዷቸውና የሚያከብሯቸው ሙስሊሞች አሉኮ፡፡ እነዚህ ሰዎች እውነተኛ እና ቀጥተኛ ሰዎች በመሆናቸው ሰዎች ከእምነት አስተምሯቸው እንኳን ባይማሩ ከጥንካሬያቸው፣ ከዓላማ ጽናታቸው፣ ከእምነት ፍቅራቸው፣ ከደግነታቸው፣ ከመንፈሳዊ ብቃታቸው፣ ከቀጥተኛነታቸው፣ ይማሩባቸዋል፤ በእነዚህም ምክንያት ያደንቋቸዋል፡፡ ያከብሯቸዋል፡፡

ሶቅራጥስ እና አፍላጦን፣ ዲዮጋን እና አርስጣጣሊስ እምነታቸው አረማዊ፣ ሀገራቸው ግሪክ፣ ቁም ነገራቸውም ፍልስፍና ነው፡፡ የኦርቶዶክስ እምነትን አያውቁትም፤ በዘመናቸውም አልነበረም፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሰዎች ኑሮ፣ የኑሮም ፍልስፍና፣ ሰብአዊነት እና ለሰው ልጅ ኑሮ ያደረጉት ተጋድሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ክብር እና ፍቅርን አትርፎላቸዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውም ወደ ግእዝ ተተርጉመዋል፡፡ «አንጋረ ፈላስፋ» ተብሎ እንደ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ይነበባል፡፡

የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው፡፡ ነገር ግን ከሊቀ ጵጵስናው መንበር በራሱ ጊዜ መንኖ በረሃ በመውረድ የኖረው የቅድስና ኑሮ ለሁሉም አርአያ የሚሆን በመሆኑ ንስጥሮስን የሚቃወሙት አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ የርሱን ትምህርት እና ሕይወት ይከተሉታል፣ ያደንቁለታል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ከአራቱ የመጻሕፍት ጉባኤያት አንዱ የርሱ መጽሐፍ ነው፡፡

የበርለዓም መጽሐፍ የሕንድ ብርሃማኒስቶች መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ግእዝ ቋንቋ ተተርጉሞ እንደ አንድ የሃይማኖት ማስተማርያ ሲያገለግል ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ የክርስትናው ሊቃውንትም የብርሃማኒስቶችን መጽሐፍ «እንዲል በርለዓም» እያሉ ይጠቅሱታል፡፡ ዘመን እና ድንበር ተሻግሮ ወዳጅ ማፍራት ማለት ይህ ነው፡፡

በንጹሕ ሥራቸው፣ በዘላቂ ዓላማቸው እና በእውነተኛ ሕይወታቸው ምክንያት እንዲህ ዘመን እና ድንበር ተሻግረው ወዳጅ የሚያፈሩ ያሉትን ያህል በተቃራኒው ዘመን እና ድንበር የማይሽረው ጠላት የሚያፈሩም አሉ፡፡

ወዳጅ ስንል በዙርያችን ያሉ የምናውቃቸውን ሰዎች ብቻ በማሰብ እንዳናጠብበው፡፡ ወዳጆች ዘመናትን ተሻግረውም ይገኛሉ፡፡ በተለይም ለእውነት የሚቆሙ ሰዎች ዘመነኛ ወዳጆች አይኖሯቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዘመንም ስለሚቀድሙ በዚያ በዘመናቸው እንደ እብድ፣ እንደ ጅል፣ ዘመን እንደ ማይገባው እና እንደ ቅዠታም ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በኋላ ግን እነርሱ የወጡበት ተራራ ላይ ሌላውም ሰው መውጣት ሲጀምር፤ እነርሱ ያዩትንም ማየት ሲችል የበደላቸው ይቅርታ ይጠይቃቸዋል፡፡ የጠላቸው ይወድዳቸዋል፣ ያልተረዳቸው ይረዳቸዋል፣ ያዋረዳቸው ያደንቃቸዋል፡፡ እነ ሶቅራጥስ እና እነ ጋሊሊዮ ይህንን ዕድል ካገኙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ነቢያቱ ኢሳይያስ እና ኤርምያስም በዘመናቸው እውነት ቢናገሩ በመጋዝ ተሰንጥቀው፣ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ ግን «ሕዝብ ዘኢየአምረኒ ተቀነየ ሊተ» እንደሚለው የማያውቃቸው ሰው ሁሉ ወደዳቸው፡፡

አያሌ ምሁራን እና ሊቃውንት ግን በገዛ እጃቸው ሰሞነኞች እየሆኑ፣ ከአእምሮአቸው ይልቅ ሆዳቸውን እያዳመጡ፣ ከብእር ይልቅ ገንዘብ እየገዛቸው ወዳጆቻቸውን ሁሉ ጠላቶቻቸው አድርገዋቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘመን ሲያልፍ የገዛ ልጆቻቸው እና ዘመዶቻቸው እንኳን የእገሌ ልጅ ነን፤ የእገሌም ዘመድ ነን እንዳይሉ አድርገዋል፡፡

እናም የኑሮ መሥመራችን እና ፍልስፍናችን፣ ተግባራችን እና ንግግራችን ቢቻል ጠላቶቻችንን ወዳጆች የሚያደርግ፣ ባይቻል ወዳጆቻችንን ጠላቶቻችን የማያደርግ፤ ወይም በሌላ በጓደኛዬ አገላለጥ «ወዳጆቻችን ጠላቶች እንዲሆኑ አንድም ዕድል የማይሰጥ፤ ጠላቶቻችን ግን ወዳጆቻችን ይሆኑ ዘንድ አንድ ሺ ዕድል የሚሰጥ» ቢሆን መልካም ነው፡፡22 comments:

 1. Bless you dani.

  your View is incredible, most of our educated Ethiopians are victim of this problem, May God help us to come to out thought.

  ReplyDelete
 2. "የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው፡፡"
  ወዳጄ ዳንኤል፤ ይህ አባባል ጅምላነት ያለበትና የማር ይስሐቅን ማንነት በደንብ ያልገለፀ፣ የቤተክርስቲያናችንን ሥነ ቅዱሳን ጉዳይ ጥያቄ ላይ የሚጥል በመሆኑ ቢስተካከል ጥሩ ነው። ቅ/ይስሐቅ በጽሑፎቹ አንድም ነቅ ያልተገኘበት ኦርቶዶክሳዊ ፀሐፊ ነው። ምናልባት ስለ ማንነቱና ጽሑፎቹ በደንብ ልትመለስበት ትችላለህ፤ እንዲህ በወፍ በረር የሚነገሩ ነገሮች ግን መዘዛቸው ብዙ ነው።

  ReplyDelete
 3. The best thought of moral code.

  ReplyDelete
 4. ዲ. ዳንኤል በታም ጥሩ ነዉ የሁላችንንም ሕይወት የዳሰሰ ነው እውነት ነው ባአንድ አላማ ፣ባንድ ሀሳብ እንድንጸና እግዚአብሔር ይርዳን ዛሬ ዓለሙን ያጠፋ ወላዋይነት ነው ዛሬ ካንዱ ጋራ ነገ ደግሞ ሀሳብ በመቀየር ከሌላው ጋር በማለት እውነት እነደሸሸን እንኖራለን አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ይስጠን።

  ReplyDelete
 5. wow wow! if im not exagrating, this is the core. it is so impressive that "those who stand for the truth usually don get followers at their time but later." i really appreciate U verry much and obliged to thank u from the bottom of my heart. by the way i always feel like this but im not living the way im feeling. WE NEED TO CHANGE OUR BAD TRADITIONAL BELIEVES AND PRACTICES AS A COUNTRY TO GROW AND SEE A BETTER TOMORROW. coz it is the bad traditions which hamper progess and better changes.

  ReplyDelete
 6. ዲ. ዳንኤል በታም ጥሩ ነዉ የሁላችንንም ሕይወት የዳሰሰ ነው እውነት ነው ባአንድ አላማ ፣ባንድ ሀሳብ እንድንጸና እግዚአብሔር ይርዳን ዛሬ ዓለሙን ያጠፋ ወላዋይነት ነው ዛሬ ካንዱ ጋራ ነገ ደግሞ ሀሳብ በመቀየር ከሌላው ጋር በማለት እውነት እነደሸሸን እንኖራለን አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ይስጠን።

  ReplyDelete
 7. ዲያቆን ዳንኤል
  መግቢያ ያደረግሀት መልዕክት ለእኔም ደርሳኝ ለመፈጸም እግዚአብሄር ይርዳኝ እያልኩ ነበር፡፡ በአፅንኦት እንዳስበው ስላደረግኸኝ የእግዚአብሄር በረከት ይብዛልሕ

  ReplyDelete
 8. Dear Dn.Daniel

  "የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው፡፡"
  ወዳጄ ዳንኤል፤ ይህ አባባል ጅምላነት ያለበትና የማር ይስሐቅን ማንነት በደንብ ያልገለፀ፣ የቤተክርስቲያናችንን ሥነ ቅዱሳን ጉዳይ ጥያቄ ላይ የሚጥል በመሆኑ ቢስተካከል ጥሩ ነው።

  Thank you My God bless you and Our tewhedo church

  U.S.A. ALEXANDRIA, VA.

  ReplyDelete
 9. ባለንበት ዘመን ላለው እውነታ መልካምና ገላጭ ጹሁፍ ነው:: የማር ይሳቅ ጸሀፊ የአባ ይሳቅ ነገር ግን ማብራሪያ የሚያስፈልገው ይመስላል ለብዙዎቻችን እንግዳ ነገር ነው::

  ReplyDelete
 10. ዳኒ በጣም እንወድሀለን በርታልን

  ReplyDelete
 11. በስመ ስላሴ አሜን።
  ይህን ጽሁፍህን ብዙ በአስተዳደር ላይ ያሉ ሰዎች ቢያነቡት ጥሩ ነበር።
  በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ እንደ አጼ ምኒልክ ወዳጅ ማፍራትን የምንማርበት የለም። እኚህ ንጉስ ባይሆኑ ኖሮ የአድዋ ድል ባልኖረ፣ ስልጣን ሲይዙ ብዙ ደም በፈሰሰ፣ አገሪቱ በሰላም ባልኖረች። እኚህ አባት ለህዝባቸው አዛኝ ለሀይማኖታቸው ቅን፣ አእምሮአቸው ክፍት፣ አርቀው አሳቢ ትክክለኛ ሰው ነበሩ፡ አንድ ሀውልት አይደለም በየከተማው ብናሰራላቸው ይገባቸው ነበር።

  ወደ እኛ ስንመለስ ብዙ ነገሮችን ማለት እንችላለን። ከብዙ በጥቂቱ ሰባኪዎቻችን እነ ጋንዲን፣ማርቲን ሉተር ኪንግን ሳያውቁ ሲያንቋ ሽሹ ሰምቻለሁ። ምንም እንኳን በሀይማኖት ባይመስሉን ጥሩ ስራ ሰርተው መሞታቸውን ማመን ይገባል። ለመሆኑ ሀይማኖታችንን በአሜሪካ ጥቁሮች ለመስበክ እንኳን ይህን (በጋራ የሚያግቡንን ነገሮች ልንጠቀም ይገባል)። የማርቲን ሉተር ኪንግን ልደት ሲከበር እንኳን ያሬዳዊ ዜማን ብናቀርብ ፍቅርንና መቻቻልን ለሰበከ ሰው ይገባው ነበር እነሱም በእኛ ሀይማኖት በተደነቁ ነበር እላለሁ። እነ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲሁ ዝም ብለው ወንጌልን አልሰበኩም።
  ጥሩ ጽሁፍና አስተማሪ ነው። ቃለ ህይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 12. I was thnking that who must read this article.Is he or she or they are reading this article.I wish!!!Please I,HE,SHE,YOU,THEY....ALL LET US READ THE ABOVE MATERIAL AND TRY TO NOT ONLY UNDERSTAND BUT INTERNAILIZED with us it is really a preferable guide to our life.Don't you think?.
  gb22

  ReplyDelete
 13. Great as always. Dn Daniel, Addisu amet beshiwech tsifeh yeshiwochin libona yemitaberabet amet endihonilih emegnalehu. Egziabher bante lay adiro eyastemaren endehone bemigeba teredichalehu. Beteley lene yihe dihire gets tiliku timihirt bete new.

  Egziabher Ethiopian yibarikilin

  ReplyDelete
 14. I appreciate the message it tells as .Great! Dani keep it ever.God be with you!

  ReplyDelete
 15. Dear Dn. daniel don't put controversial word like the one that you mention in the above article about mar yshak such words don't have any value for your viewer and it is also vary far from the orthodox teaching

  ReplyDelete
 16. ደብረ ቁስቋም
  ሰላም ለዚህ ቤት በርግጥ ፅሁፉ ለሁሉም ሰው መልእክት አለው ነገር ግን የማርይሳቅና ያንጋረ ፈላስፋ ፀሃፊያን ጉዳይ ግን ከቻልክ አጠር ያለና ግልፅ ማብራርያ ልትሰጠን ይገባል ምክንያቱም በጣም አስገራሚ ነገር ነው ለኔ የሆነብኝ መፅሀፍቱን አይቻቸዋለሁ በጣም መካሪዎች ናቸው.
  እግዚአብሄር አምላክ ኢትዮጵያ ሀገራቸንን ቤተክርስትያን እናታቸንን ይጠብቅልን

  ReplyDelete
 17. Selam Dn.Daniel,it is really good article. Could you please give explanation about የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው?

  ReplyDelete
 18. ልብ የሚነካ ጽሑፍ ነው፣ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 19. kale hiwot yasemalin Dn.Daniel!
  Could you give us some explanation about የማር ይስሐቅ pls?

  ReplyDelete
 20. Dn Daniel, Tsegazalih Egziabher Yibzalih.

  Please respond to what u wrote about የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው?

  ReplyDelete
 21. I like the message ,BUT "የማር ይስሐቅ ደራሲ ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ እንዲያውም ንስጥሮሳውያን ከሚባሉት ወገን ነው፡፡

  Dn Dani it needs more elaboration, so u have to elaborate it.

  ReplyDelete
 22. Nice view.Thank you.

  ReplyDelete