Wednesday, September 15, 2010

ቺፋን ለማ

የዛሬን አያርገውና ቻይናዎች ከ30 ዓመት በፊት ችግርን በታሪክ ብቻ ሳይሆን በአካልም ያውቁት ነበር፡፡ አለንጋውን ይዞ ገርፏቸዋል፤ ጥርሱን አውጥቶ ነክሷቸዋል፤ ጥፍሩን አርዝሞ ቧጭሯቸዋል፡፡ ሀገራቸው በታሪካዊ ቅርሶቿ እና በጥንታዊው ሥልጣኔዋ ካልሆነ በቀር ከድህነቷ ውጭ ሌላ መታወቂያ አልነበራትም፡፡

መቼም ከሠሩ የማይገኝ፣ ከለፉ የማይሰናኝ የለምና ጥረው ግረው በወዛቸው ሀገራቸውንም ስማቸውንም ቀየሩት፡፡ እነሆ ቻይናም በዓለም ሁለተኛዋ የኢኮኖሚ ኃያል ሀገር ለመሆን በቃች፡፡ ቻይና በኦሎምፒክ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ወርቅ መሰብሰብ ጀመረች፡፡

ታድያ እነዚህ ቻይናዎች በድህነቱ ዘመናቸው ዋናው ችግራቸው የረሃብ ጥያቄ ነበረ፡፡ በልቶ ማደር ጠጥቶ መዋል የእያንዳንዱ ቻይናዊ የየዕለቱ ፈተና ነበረ፡፡ ያ እንደ ጉንዳን የሚርመሰመስ፣ እንደ ጎርፍ ውኃ የሚተራመስ ሕዝብ ዛሬን ቢበላ ነገን ለመድገሙ ዋስትና አልነበረውም፡፡

በዚህ የተነሣ የቻይናዎቹ ዕለታዊ ሰላምታ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሆነ፡፡ ቻይናውያን ሲገናኙ «ቺፋን ለማ» «በልተሃልን?» ነበር የሚባባሉት፡፡ መልሱም «አልበላሁም/በልቻለሁ አንተስ እንዴት ነው በልተሃል?» የሚል ነበር፡፡ ልጆቹ፣ ቤተሰቡ፣ አካባው ሁሉ በልቶ ማደሩን ነበር የሚጠያየቀው፡፡ በልቻለሁ የሚል መልስ ከተገኘ እሰዬው ነው፡፡ አልበላሁም ከተባለ ግን ተዛዝኖ እና መንገድ ተመለካክቶ መሰነባበት ነው፡፡

በሌላ በኩል ምዕራባውያኑ ትልቁ ፈተናቸው አካባቢያቸው ነበር፡፡ እንዲህ እንደዛሬ ሙቀት እና ቅዝቃዜውን፣ ነፋስ እና ማዕበሉን፣ በረዶ እና ውሽንፍሩን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዐቅም መቋቋም ከመጀመራቸው በፊት፤ እንዲህ እንደዛሬው የነገውን የአየር ሁኔታ አውቀው ለመዘጋጀት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ብሎም አካባቢያቸውን ለኑሮ በሚሆን መልኩ ማመቻቸት ከመጀመራቸው በፊት ዋናው ችግራቸው ዛሬን ማደር ነገንም ማግኘት ነው፡፡

በዚህ የተነሣም ሰላምታቸው ሁሉ በምኞት የተሞላ፣ ነገን ተስፋ የሚያደርግ ነው «good morning, good evening, good afternoon, good night,» መልካም ጠዋት፣ መልካም ምሽት፣ መልካም ቀን፣ መልካም ሌሊት እያሉ ይመኛሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ደግሞ ትልቁ ጥያቄያቸው የደኅንነት ጥያቄ ነው፡፡ ይህች ሀገር በጦርነት ስትታመስ ነው የኖረችው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳን ቲርሐቅ የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ አንድ ሚሊዮን ጦር አስከትቶ እስከ ታኅታይ ግብጽ ድረስ ዘምቶ ነበረ፡፡

ሀገሪቱ በውጭ ወራሪ እና በርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ፡፡ ሕዝቦቿ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው ሥፍራ ሲዘዋወሩ፤ አሸናፊው ተሸናፊውን ሲያስገብር፤ ተሸናፊው ኃይል አግኝቶ መልሶ ሲያጠቃ ኖረውባታል፡፡ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ፣ ነገሥታቱ እና ልዑላኑ ጎራ ለይተው ሕዝብ አሰልፈው ተጋድለዋል፡፡

በዚህ የተነሣ ይመስለኛል የኢትዮጵያውያን የሰላምታ ባህል ደኅንነትን ማረጋገጥ የሆነው፡፡ «እንዴት አደርክ? እንዴት ሰነበትክ? እንዴት ከረምክ? እንዴት ዋልክ? እንዴት አለህ?» እነዚህ ሁሉ ደኅንነትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ችግሩ፣ መፈናቀሉ፣ መዘረፉ፣ ጦርነቱ ልጆችንም፣ ከብቶችንም፣ ቀየውንም ይመለ ከታልና ሰላምታችን ወደነዚህ ነገሮችም ተራዝሞ ቤቱ ሰላም ነው? ልጆቹ፣ ከብቶቹ ደኅና ናቸው? ቀየው ሰላም ነው? የሚሉ የደኅንነት ጥያቄዎችም ይከተላሉ፡

ይህ ሥነ ልቡና ዛሬ ላለንበት ገጽታ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል፤ የራሱንም ጠባሳ ትቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የርስ በርስ ግንኙነታችን በጥርጣሬ የተቃኘ ነው፡፡ የሰው ዓይን ይፈራል፡፡ ልጆች እንኳን ጡት ሲጠቡ ሰው እንዳያየቸው ይሸፈናሉ፡፡ ዘመናውያን የሚባሉት ወላጆች እንኳን የልጆቻቸውን ጡጦ በካልሲ ሸፍነው ካልሆነ በቀር በአደባባይ አይወጡም፡፡

አንድ ወጣ ወጣ ያለ ሰው አንዳች መሰናክል ሲገጥመው «ምን ዓይን በላው፣ ማን በክፉ አየው» ማለት የተለመደ ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ ጠዋት ተነሥተው ፊታቸውን እና እጃ ቸውን ሲታጠቡ «ቀኝ አውለኝ ከሸረኛ ጠብቀኝ» ይላሉ፡፡ ፍርሃት አላቸው አካባቢያቸውን ይጠራጠሩታል፡፡ በቀኝ መነሣት እና በግራ መነሣት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ሰው የከፋ ነገር ከተናገረ «ምን በግራ ጎኑ የተነሣ ሰው ነው» ይባላል፡፡

ከጥርጣሬ ጋር የተያያዙ አያሌ ብሂሎች አሉን፡፡ ጠርጥር ከገንፎም ይገኛል ስንጥር እያልን ነገሮችን አለማመንን እናበረታታለን፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ብለን ደግሞ ተጠራጣሪነት ከብዙ ነገር እንደሚያድን እንሰብካለን፡፡ በገጠሩ እንኳን የሚጠራጠርን ሰው «አይ ጠርጣራው» እየተባለ ማሞካሸት የተለመደ ነው፡፡

የእርስ በርስ አለመተማመኑ ባህል ከመሆኑ የተነሣ በመርዝ መግደል በየተረቶቻችን ውስጥ ሰፊ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ ቡና ሲፈላ አፍይው ቀድሞ መጠጣት አለበት፡፡ ጠላ ሲጠጣ ቀጅው በእፍኙ አፍስሶ መቅመስ ልማድ ነው፡፡ ምግብ ሲቀርብ ቆርሶ በመጉረስ ማስረገጥ ይጠበቃል፡፡ ጥሩ ነገር ሲታይ እንኳን ዓይን ስለሚፈራ «እትፍ እትፍ» ይባላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ይጎዳል የሚባለው ሰው እንኳን ባህሉን ተቀብሎት ማንም ሳይለው «እትፍ እትፍ» ብሎ ምራቁን በመርጨት ዓይኑን ከክፉ ይከለክላል፡፡

ሰማዩ ሲያቅላላ ጦርነት ሊመጣ ነው፣ ደመናው ሲጠቁር ክፉ ዘመን ቀረበ፣ ወፍ በጠዋት ስትጮኽ ትልቅ ሰው ሊሞት ነው፣ ከሰሉ ሲንጣጣ ነገር ሊመጣ ነው፣ እንጀራው ሊጥ ሲሆን ኑሮ ሊበላሽ ነው፣ ቡናው አተላ ሲሆን ፍቅር ሊደፈርስ ነው፣ እያለ ሰው አካባቢውን ይጠራጠራል፡፡ ሌላው ቀርቶ የደመራው መውደቂያ አቅጣጫ እንኳን ከጦርነት እና ሰላም አንፃር ነው የሚተረጎመው፡፡

ይህ ሥጋት የተሞላ የኑሮ ዘይቤ ሰዎች ራሳቸውን ችለው በድፍረት እና በመተማመን ብቅ እንዳይሉም ይከላከላል፡፡ በንግግሩም ይሁን በችሎታው ቀደም ቀደም የሚለውን፣ ልውጣ ልውጣ ብሎ የሚጣጣረውን ሰው «ወጣሁ ወጣሁ ማለት፤ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ» እያለ ያስፈራራዋል፡፡ መቅደም መንቀዥቀዥ፣ መፍጠን እታይ እታይ ማለት፣ ሃሳብን መግለጥ እና መብትን ማስከበር ከሰው አፍ መግባት፣ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ተደብቆ፣ ሰው ሳይሰማ፣ ነገርን ሁሉ መፈጸም ብልህነት፤ ድብቅነት ምሥጢራዊነት ነው ተባለ፡፡ ይህ ደግሞ ሐሜት ከመረጃ ይልቅ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው አደረገ፡፡ ድምጽን አሰምቶ፣ ራስን ገልጦ መናገር ከሰው አፍ መግባት፣ ብሎም በሰው ጥቁር ምላስ ተገርፎ መውደቅን ያመጣል ስለሚባል ሐሜት በሹክሹክታ ሀገሩን ያምሳል፡፡

ለሀገራቸው አያሌ የሥነ ጽሑፍ ሀብትን ያተረፉ ጥንታውያን ደራሲዎቻችን እንኳን በገዛ ስማቸው ያልጻፉት በዚሁ የደኅንነት ጥያቄ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እርሱ ማነውና? ከየት አመጣው? ሰርቆ ነው እንጂ አሁን የእርሱ ነው? ደግሞ እርሱን ብሎ ጸሐፊ? የሚሉ ነገሮች ይመጡና እድሜያችን ያጥራል ብለው በመሥጋት በብእር ስም እየጻፉ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም የተነሣ አንድ ምሁር እንዳሉት በአባቶቻቸን እንዳንኮራ ሆነናል፡፡

ከፊት ለፊት ካለው ነገር ይልቅ ከጀርባ ያለውን ነገር የመፈለጉ ልማድ የመጠራጠሩ እና ደኅንነት ያለመሰማቱ ውጤት ነው፡፡ ሰውዬው ከአንድ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ይገባና ጥበቃውን ጠጋ ብሎ «ይህ ቤተ ክርስቲያን ለምን መድኃኔዓለም ተባለ» ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እርሳቸውም «አንዳች ነገር ቢኖረው ነው እንጂ ያለ ምክንያት መድኃኔዓለም አልተባለም፡፡ አንድ ነገር ከጀርባው ይኖረዋል፤ መቼም ያለ ምክንያት መድኃኔዓለም አላሉትም» አሉት ይባላል፡፡

አንድ ሰው አንድ ነገር ሲያደርግ ወይንም ሲናገር ያደረገውን ወይንም የተናገረውን ከመመዘን ይልቅ «አንዳች ምክንያት ቢኖረው ነው፤ ከጀርባው አንድ ነገር ቢኖር ነው፤» እያልን ከሚታየው ጀርባ የማይታይ ነገር እንጎረጉራለን፡፡ «ማጅራቱ አባቱን ይመስላል» ያሉትኮ ወደው አይደለም፡፡

ከጦርነቱ በተጨማሪ ድግምት፣ መተት እና ጥንቆላ ዋናዎቹ ማስፈራርያዎች በመሆናቸው ሰው ስሙን እንኳን እንዳይናገር ሥጋት ውስጥ ከተቱት፡፡ ሀብት አለው መባል፣ ልጆች አሉት መባል፣ ንብረት አለው መባል ለክፉ ምልኪ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ ታመነ፡፡ እናም ብዙው ሰው ልጆቹን ሲቆጥሩበት ይከፋዋል፡፡ ሀብቱን ሲዘረዝሩበት የተዘረፈ ያህል ያናድደዋል፡፡

ሃይማኖተኛ ይባሉ የነበሩት ነገሥታት እና መኳንንት እንኳን አንዳንድ ጠንቋይ ወይንም መተተኛ ከየጓዳቸው አያጡም ነበር፡፡ ኮከብ ቆጣሪዎች እና ድግምተኞች ዋና አማካሪዎቻቸው ነበሩ፡፡ መንግሥ ታቸው ደኅንነት አይሰማውም፤ ዙፋናቸው በጥርጣሬ የተሞላ ነበር፡፡ እናም ነገ ይህ ይሆናል የሚል ካላገኙ ዕንቅልፍ አይወስዳቸውም፡፡

ዛሬ ዛሬ በፖለቲካው መስክ፣ በምሁርነቱ ሜዳ፣ በሳይንሱ ዘርፍ፣ በሀብቱ ጎዳና፣ በሥልጣኑ ጉዞ ለምናየው የመጠፋፋት፣ ያለመተማመን እና የመበላላት አባዜ መነሻው ይህ ደኅንነት ያለመሰማት እና የመጠራጠር ልማድ ነው፡፡ ተወዳድሮ ከመሸናነፍ፣ በግልጽ ተነጋግሮ ከመግባባት እና ከመለያየት፣ ከመተማመን ይልቅ መጠራጠር የምናበዛው ከልማድ የወረስነው አዙሪት አልለቀን ብሎ ነው፡፡

በሥልጣን ላይ የሚሆኑት አካላት እንኳን ክፉውንም ደጉንም ለሕዝቡ ነግረው፣ ድክመትንም ጥንካሬንም ግልጽ አድርገው እየተግባቡ ከመጓዝ ይልቅ ደብቀው መጓዝን የሚመርጡት ይኼው አባዜ ይዟቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥያቄያቸውን ሳንሰማ መልሳቸውን የምንሰማቸው መግለጫዎች የዚህ ውጤት ናቸው፡፡

አንዳንድ ተቋማት፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች እና ፓርቲዎች እየሞቱ፣ እየደከሙ፣ እየፈራረሱ፣ እርስ በርስ እየተነታረኩ በአደባባይ ሲወጡ ግን ሰላማዊ፣ ችግር ነክቷቸው የማያውቅ፣ አገር ደኅና የሚሉት ነገሩን በመ ግለጥ ደኅንነት ስለማይሰማቸው ነው፡፡ ችግሩ ተፍረጥርጦ በግልጽ ወጥቶ ከሚመጣው ፈውስ ይልቅ መጠቃቱ፣ አጀንዳ መሆኑ ይበልጥ ይሰማቸዋል፡፡ ድርጊቱ በራሱ ያላመማቸውን ድርጊቱ ሲወራ ያማቸዋል፡፡

ከመድረክ ይልቅ የተዘጋ ቤት፣ ከይፋ ይልቅ ሥውር፣ ከአደባባይ ይልቅ ጓዳ ይበልጥ ደኅንነት ይሰጠናል፡፡ በመረጃ ዘመን፤ ዓለም አንድ በምትሆንበት፤ ኑሮ ይበልጥ ይፋ በሆነበት በዚህ ጊዜ ይህ ልማድ ሳይጠፋ እንዴት ዕድገት ይኖራል?

ዋሽንግተን፣ ዲሲ

ይህ ጽሑፍ በሮዝ መጽሔት ወጥቶ ነበር
40 comments:

 1. God Luck My Brother!

  ReplyDelete
 2. ከደብረ ቁስቋም
  ወንድማችን ጥሩ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን.ከእግዚአብሄር ጋር እራስን መጠበቅ መልካም ነውና እራስህን ጠብቅ እንደ አምላክ ፈቃድ ካነት ብዙ እንጠብቃለን.ድንግል ማርያም ከሁሉ ነገር ትጠብቅህ.
  የቅዱሳን አምላክ የቤተ ክርስትያንን ሰላም ነሺዎች ልቦና ይስጥልን.

  ReplyDelete
 3. Qale hiwoten yasemalen !!! ye agelegelot zemenehen ye KEDUSAN AMELAK yarezemelek tsegawen yabezalek Amen

  ye ethiopiwntachen tebay sigelet yehen yemeselalal ersen ,akebabien batekalay ulun asbekutegena yetesafewen meselen new yagegut
  be hagerachen yelemedenewn behel eko balenebetem besew hager eynatebarekenew engegalen

  abet yehe kefu bahelachenen endet melewt enchel yehon ?

  ReplyDelete
 4. በስመ ሥላሴ አሜን።

  መልካም እይታ ነው! ... ቢሆንም የነጭን ፀዐዳነት ለመግለፅ የግድ ቢጫንም ቀይንም ፣ ሰማያዊውንም ... ሁሉንም ጥላሸት መቀባት አስፈላጊ አልነበረም። ... መተቸት በራሱ እኮ ነገርን ቀላል ያደርጋል። ... ለተነሳንበት ምልከታ ይመቸን ዘንድ በመንገድ የተገኘውን ሁሉ መጨፍጨፍ የሚገባ አይመስለኝም ፤ ደግሞ ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል እንዲባል ያሉንን መልካም ማሕበራዊ እሴቶች አጥብቀን ይዘን የሚጎድሉትን እየሞሉ ፤ የጎበጡትን እያቃኑ ፤ የማይጠቅሙትን እያስወገዱ መሄድ እንጅ ገና ለገና የማይጠቅም ስለታየን ፤ እርሱን በመጠቆም ሂደት ሌሎቹን አቧራ ማልበስ አይገባም። ... እንደምን አደርክ? ፣ እንደምን አረፈድክ? ፣ እንደምን ሰነበትህ? ... የሚሉትን መልካም ብሂሎች ፤ በተለያዩ ዘመናትና ትውልድ ሕዝቡ እርስ በራሱ ያለውን መተሳሰብ ፤ አንዱ ለሌላው ያለውን ግድ ... ሁሉ ወደጎን ገፍቶ ፤ ጦርነትና የእርስ በርስ ጥል ውጤት ነው ብሎ መፈረጅ በእውነቱ ትልቅ ድፍረት ነው።

  " ቀኝ አውለኝ ፤ ከሸረኛ ጠብቀኝ " ብሎ መውጣት ከመቸ ወዲህ ነው ፍርሃት እና አካባቢን መጠራጠር የሆነው? ... በእግዜር ይሁንብን እንዲህ አይነቱ ነገር ሲፃፍም አቦ አቦ ለማለት እንዳንቻኮል ... ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር መሆኑ ተዘነጋ እንዴ? ... መልካም ቀን አድርግልኝ ... ክፉ ከመስራት ጠብቀኝ ... ክፉ ሊያሰሩኝ ፈተና ከሚሆኑብኝ ሸረኞች አርቀኝ ማለትም ፍርሃት ተባለ? ...

  «ወጣሁ ወጣሁ ማለት፤ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ» ... አይደለም እንዴ? ... እርግጥ ነው ስራ ፤ አፍ አውጥቶ ሲናገር እንጅ ፣ ከስራው ታላቅነት የተነሳ ሌላው ሲጠቀም ተጠቃሚው ከፍ ከፍ ሲያደርግ እንጅ ... እንደው የበጠበጠውም ያበጣበጠውም ወጣሁ ወጣሁ ... አቦ አቦ በሉኝ ካለ እጣው እንደተጠቀሰው ነው ... አንድም ለወፍ አልያም ለወንጭፍ ... መቸም እኔ በዕድሜዬ መልካምን ለሚሰራ ሰው ይህ ተረት ሲተረት አይቼ ሰምቼ አላውቅም ... ገና ለገና ሕዝባችን ታላላቅ ስራ የሚሰሩ ሰዎችን የሚገባቸውን ክብር የመስጠት ልማድ የለውም ፤ ሰዎች አዳዲስ ሀሳቦችን ይዘው እንዳይነሱ የሚገባ ነጻነት አይሰጥም ለማለት ትክክለኛውን የተረቱን መልዕክት ሰዎች በተዛባ መልኩ እንዲመለከቱት መግፋት ምን የሚባል ነው።

  " ሃይማኖተኛ ይባሉ የነበሩት ነገሥታት እና መኳንንት እንኳን አንዳንድ ጠንቋይ ወይንም መተተኛ ከየጓዳቸው አያጡም ነበር፡፡ ኮከብ ቆጣሪዎች እና ድግምተኞች ዋና አማካሪዎቻቸው ነበሩ፡፡ " ... እንግዲህ የታሪክ መጻሕፍትን ላነበበ ቀርቶ በወሬ በወሬ እንኳን ለሰማ ሰው እንዲህ ባለ ነገር የሚነሱት ነገስታት እና መኳንንት ጥቂቶች ሆነው እያለ ፤ ሀሳቡን አግዝፎ ባንባቢው ኅሊና ለመሳል ሲባል ብቻ ... ለዛውም " ሃይማኖተኛ ይባሉ የነበሩት እንኳ " የሚል ቅፅል በመቀጸል ሕዝቡ ባጠቃላይ ለነገስታቱ ያለውን ምስል ለማበላሸት መሞከር የሚያስገምት ነው

  ለማንኛውም መተቸት ቀላል ስለሆነ ጸሐፊያችን በተቹት ላይ ሌላ ትችት ለመዘብዘብ አይደለም ግና የነጭን ፀዐዳነት ማሳየት የሚገባው የቀይንም ቀይነት ፣ የቢጫንም ቢጫነት ፣ የሰማያዊንም ሰማያዊነት ጥርት አድርጎ ከማስቀመጥ ጋር ነው ለማለት ነው። ...

  ለመሆኑ ግን እንዴት ነው እንደ ሕዝብ ይህ ሕዝብ ከምዕራባውያኑ ወይም ወደ ሩቅ ምስራቅ ያሉት ሀገራት አላቸው እንደሚባለው ያለ ፤ አዎንታዊ ነገር የለውም እንዴ? ... ማለቴ የሌለውን ለማግኘት እንዲሰራ ፤ የተበላሸውንም እንዲያቀና ወኔ ፣ እልህ ነገር የሚፈጥርለት አንዳች ጥሩ ነገር ... መቸም ምንም ጥሩ ነገር የሌለው ሕዝብ ደግሞ የለ ... ምናለ ታዲያ ባለማወቅ ፣ ባለማስተዋል ፣ በስንፍና ፣ አንዳንዴም እናቅልሃለን በሚሉት ሰዎች በመነዳት ያጠፋውን ፣ ያበላሸውን ነገር ሁሉ እንዲያሰተካክል ተነሳሽነት የሚፈጥርለትን ነገር መናገር ቢያቅተን ፤ ጥፋቱ የጠፋበትን ቦታ ለይቶ እንዳያውቀው ፣ ብዥ እንዲልበት ባናደርገው? ....

  ለነገሩ ለምን እንዲህ ታሰበ አይባልም? ... ቢሆንም ተሳቢው በበዛበት እንዲህ ባለ ሁኔታ ሳቢው ኮረኮንች የበዛበትን ትቶ ሜዳ ሜዳውን ቢሄድ ለማለት ነው ... ማለቴ ከተቻለ ...

  የሚታየውና የሚሰማው ክፉ የሆነውን ይህን ዘመን እግዜር በቸርነቱ ይቀይርልን።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

  ReplyDelete
 5. kale hiwot yasemalin dn.daniel it is good mesage for me b/c greeting to hear some problem due to fear of something leads to doubtfull life.
  may our God keep from doubtfull greeting&life

  ReplyDelete
 6. Dear Dn. Daniel,

  Bundle of thanks! It is a very good critical reflection!

  ReplyDelete
 7. oh! I love it. I think this must be one of your best writing I have read so far.

  We, Ethiopians, are very afraid of each other which is one of the reasons we are unable to solve our differences through dialogue and frequently resort to violence. The other reason, in my opinion, is we can't accept defeat with grace. We are bad losers. We expect others to accept our views but we are not prepared to abandon ours and support others' views.

  Thanks D. Daniel.

  ReplyDelete
 8. You got the root of the problem Dani.We long days when Ethiopians trust Ethiopians!

  ReplyDelete
 9. Thanks Eyob G. for ur amendment!!

  ReplyDelete
 10. “ለነገሩ ለምን እንዲህ ታሰበ አይባልም? ... ቢሆንም ተሳቢው በበዛበት እንዲህ ባለ ሁኔታ ሳቢው ኮረኮንች የበዛበትን ትቶ ሜዳ ሜዳውን ቢሄድ ለማለት ነው ... ማለቴ ከተቻለ ...” ውድ ወንድማችን ኢየብ አንተም ለምን እንደዚህ ተረዳኸው አይባልም ያነሳሃቸው ነጥቦች መልካም ናቸው ብዬ አምናለሁ ግን ከዚህኛው ጽኁፍ አንጻር ሳይሆን አራሱን ችሎ ሲታይ ማለቴ ነው፡፡ ይሁንና ከቺፋን ለማ እኔ የተማርኩት ‘’ከመድረክ ይልቅ የተዘጋ ቤት፣ ከይፋ ይልቅ ሥውር፣ ከአደባባይ ይልቅ ጓዳ ይበልጥ ደኅንነት ይሰጠናል፡፡’’ የሚለውን ነው፡፡ በተረፈ ዳኒ በርታ ድንግል አትለይህ!!

  ReplyDelete
 11. Selam Lnanet Yehun
  Asekdeme Kefettachenen Endenasetwule Sehetetachenen Enedenareme Endeneqoch
  Ymiyadrege Tsehufocene Selakerbekelen
  Egziabehier Tsegahene Yabezaleh.
  Ebakachehu Lhulume Gizea Alewu Senemsgne Meseganawune Mekeble Senewkesemem Mastekakel Yalebeten masetekakel Yenorebenale Beye Amenalhu.
  MBY Zetewahedo

  ReplyDelete
 12. በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች መካሪ ትሆነን ዘንድ ዕውቀቱን እና ማስተዋሉን ለአንተ የሰጠ ፈጣሪን ከልብ አመሰግነዋለሁ፡፡
  ለአንተ ይህንን ጥበብ የሰጠ ለኛም ማስተዋሉን ያድለን፡፡


  ካሳሁን

  ReplyDelete
 13. Dear Eyob G.

  If you had understood the principles of composition, you would have never argued this way. I think Dn Daniel doesn't want the compare and contrast way. He just wanted to focus to one
  of the problems we have and showed the seriousness with evidence from oral literature and real experience. That is fine with me. Teteratarinetachin yemayikad new. hak new. Ene lemisale Europe eyenorku enkua akababiyen alaminim; zuria gebawun mekagnet abezalehu, keminim belay safety alebet yemibal ager eyeneroku i do not feel safe. This feeling is rooted in our thinking.
  Dn Daniel Berta, Egziabher yitebikilin. we need you. you are the source of info, knowledge, strength for us.
  asteyayet sechi kelay endalut gin ke Egziabher gar rasihin tebik. Yegna sew ewunetawun yeminager sew ayasfeligim eyale yemimesilibet zemen lay dersenalina.
  Egziabher Ethiopian yitebikilin

  ReplyDelete
 14. በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች መካሪ ትሆነን ዘንድ ዕውቀቱን እና ማስተዋሉን ለአንተ የሰጠ ፈጣሪን ከልብ አመሰግነዋለሁ፡፡
  ለአንተ ይህንን ጥበብ የሰጠ ለኛም ማስተዋሉን ያድለን፡፡
  ካሳሁን

  ReplyDelete
 15. It was an impressd lecture sofar i read.
  Long live for you and our church.
  Taddese the kal.

  ReplyDelete
 16. Hello Dani,

  I get Excellent information Thank You Very much, Geta Egzehabeher Kantena kebetcboche gare yehune

  ReplyDelete
 17. Dear Eyob G.

  Please be a positive thinker. Dn. Daniel has not concluded that we don't have good qualities but he want to emphasize on what we lack very much that led our people and country to devastation. We can proof this and the outcome is clearly visible in our daily life. But this doesn't mean that we don't have good qualities. If u read his other articles he raised and discussed the good qualities in one way or another. If u are not convinced of his discussion it is better to keep silent instead of writing misleading comment.

  Good luck to you.

  Dn. Daniel keep up the great job.

  ReplyDelete
 18. በስመ ስላሴ አሜን
  ጥሩ ወግ ነው። ነገር ግን አስተያየት ያላቸው ሰዎች አስተያየታቸውን እንዴት እንደሚሰጡ መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል። Eyob G የሰጠው አስተያየት ጥሩ ነበር ነገር ግን ፅሁፉን ብቻ ቢተች ጥሩ ነበር። ከሱ በዃላ የተቃወሙት ደግሞ "Dear Eyob G. If you had understood the principles of composition..." ብለው ተንደርድረዋል። ይህ ደግሞ ሰውን አላዋቂ ያሰኛል። የሰውን ስብእና (personality) ባልነካ መልኩ አስተያየት ብንሰጥ ያማረ ይሆናል።
  በተረፈ-ያለፈውን ዜና (በሻይ ቤት) ሰምተናል...
  እግዚአብሔር ከግብዞች ይጠብቅህ።

  ReplyDelete
 19. A nice piece, perhaps one of the best of yours, Dani.
  The genesis of our siege mentality must have an origin relating to the experience we acquired. As you rightly pointed out, the prevailing unsecured mentality have shaped our outlook for everything, unfortunately. We have a daunting task ahead to get out of such quagmire. Such critical reflections are one way to tackle social problem. While reflecting on our positive sides is good as well as Eyob G put it, the situation we are in warrants reflection on the negative side.

  ReplyDelete
 20. I think the message transmittes wrong ways , it brings doubtes.. not good !!

  ReplyDelete
 21. very touching message.keep it up!
  Le-Ethiopia tasfeligataleh, ke-kentu wudasie 'ena ke-metabey rasikin tebik.
  Good Bless you!

  ReplyDelete
 22. Dear Eyob G.
  I have tried to go through what the blogger has posted and your comment. If I were the blogger, I wouldn't post your comment here. This blog a source of a lot of info both historical and current, knowledge both spiritual and non spiritual for us. In addition to read what the blogger posted we have to encourage him to continue what he is doing. Even if we have something against his idea, we have to reflect that in a friendly manner. But what you did is just in a discouraging way. Your"comment" is as to me is an insult! If you don't agree with my idea read it again. So please, try to reflect your opinion politely and friendly.
  Thank u.

  ReplyDelete
 23. Dn. Daniel
  Tirue milketa new. Neger gin Eyobe endalew yetegeletsut bemulu tikil milketawoch ena melkam andimitawn debko metifo andimitawn yemiatit tsihuf yimesilegnal. Bemehonum Dn. Daniel bezih tsihuf lay techemari mabrariawochin beketay gizie yizeh tiwotaleh biye tesfa adergalehu. Enien endemimesilegn yih guday berasu sefi tinat yemiteyik enj endihu bemilketa bicha tetsifo yemiwota ayidelem.

  ReplyDelete
 24. በስመ ሥላሴ አሜን።

  ለተከበራችሁ የዚህ ጡመራ ተከታታዮች ፦ የእግዚአብሔር ሰላም ይብዛላችሁና እንደምን አላችሁ? ... አስቀድሜ ፦ ከእኔ አለመረዳት ፣ ሐሳቤን በጽሑፍ በመግለፅ ሂደት ካሳየሁት ድክመት ፣ ምናልባትም እናንተ እኔ ልገልጸው የሞከርኩትን ነጥብ ከመሳታችሁ የተነሳ አሳዝኛችሁ እንደሆነ ፤ ባገራችን ወግና ልማድ መሠረት ባጠፋሁ ይቅር በሉኝ ልላችሁ እወዳለሁ።

  እንደኔ አመለካከት የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ይህንን የጡመራ መድረክ በማዘጋጀት ፤ በጎ ብለው ለተነሱበት ዓላማ ይህን ያህል የመድከማቸው ዋና ጉዳይ ፤ ለነገሮች ያላቸው አተያይ ድንቅነት ፣ የሐሳባቸው ምጡቅነትና መልካምነት ፣ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ብልሐት ፣ የቋንቋቸው ምስል ከሳችነት ( ገላጭነት ) ፣ ሌላው ሌላውም ነገራቸው ፤ በእኛ ጽሑፎቻቸውን በምናነበው ሰዎች ኅሊና በጉልህ እንዲሳል ፤ ከዛም የተነሳ አሁንም አሁንም እንድናመሰግናቸው አይመስለኝም ...በመሆኑም እንደ አንድ አንባቢ ፤ እኔም ጽሑፎቻቸውን ካነበብኩ በኃላ ፤ እንደመረዳቴ መጠን ለጽሑፎቹ ምላሽ እሠጣለሁ ... ከላይ እንደሚታየውም የማያስማማኝ ነገር አለ ብዬ ሳምን ፤ ያላሳመነኝን ነጥብ በማንሳት እሞግታለሁ። ... እርግጥ ነው አስተያዬቴ ስሜታዊነት ይነበብበታል ፤ .... ቢሆንም ... ዋናውን ጽሑፍ እራሱ እንኳን ብንመለከት ጸሐፊው ፦ ባይሆን ፣ ቢቀር ፣ ቢታረም ስለሚሉት ክፉ ልማድ ፤ እና ቢለመድ ፣ ቢደረግ ፣ ቢቀጥል ብለው ስለሚያስቡት በጎ ምኞት ሲናገሩ አንዳች ቁጭት እንደሚነበብባቸው መካድ አይቻልም። ... እና እኔም ከራሴ አተያይ የተሰማኝን ቁጭት መግለፄ ነበር ... አልችልም እንዴ? ... የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ጸሐፊው መምህሬ ነበሩ ... ናቸውም ፤ ሆኖም ግን ምንም እንኳን መምህሬ ቢሆኑም የሚያስተምሩኝ ትምህርት ከማውቀው ፣ ከለመድኩትና ከምኖርበት አኗኗር ጋር ሲጋጭ አልያም የተጋጨ መስሎ ሲሰማኝ ለምን? እላለሁ። ... የሚያስተምሩኝ ነገር የማላውቀው ግና ጠቃሚ ቢሆን እንኳን እጠይቃለሁ ... ስለምንነቱና እንዴት እንደሚጠቅመኝ በግልፅ እስኪነግሩኝ ድረስ ... ነገር ግን መምህሬ ስለሆኑና ፤ የታፈሩ የተከበሩ ስለሆኑ ብቻ የተነፈሱት ሁሉ ጠቃሚ ነው ከሚል ጭፍን ድጋፍ ተነስቼ ወደሳቡኝ የምሳብ ተሳቢ መሆን አልፈልግም።

  እርግጥ ነው ጦማሪው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ እርእሶች የተለያዩ ርእሰ ጉዳኦችን የዳሰሱ ጠቃሚ ጽሑፎችን መጻፋቸው ፤ በዚህም እኛ አንባቢዎች ብዙ ቁምነገሮችን እንደወሰድን እኔ ራሴ ምስክር እሆናለሁ። ... ቢሆንም ... እንደኔ እንደኔ ምንም እንኳን እያንዳንዱ ጽሑፍ የያዘው አብይ ቁምነገር ቢኖረውም ... ቁምነገሩን ለማጉላት የሚዥጎደጎደው ትችት ግን ከልክ ያለፈና አፍራሽ ነው እላለሁ። ... ይህ ደግሞ " እኛ ኢትዮጵያኖች መተቸት አንወድም " የሚባል ነገር ያመጣል ፤ እውነት ነው የምላችሁ ይህን በመፍራት ፤ እንዲህ ያለውን ስሜቴን ለመቆጣጠር ብዙ ታግያለሁ ... ነገር ግን አባባሉ በራሱ ደግሞ በተቃራኒው ይህን ትዕግስቴን የሚፈታተን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ... እንደው በእግዜር ከ80 ሚሊዮን በላይ የሚሆንን ሕዝብ በደምሳሳው ስህተቱ ሲነገረው የማይወድ ፣ ትችት ጠሌ ነው ማለት ምን ማለት ነው?... ለክፉ ነገር ሲሆን እኛ ኢትዮጵያኖች እንዲህ ነን እንዲያ ነን ይባላል ... ለመልካም ነገር ሲሆን ደግሞ ምዕራባውያኑን ፣ ወደ ሩቅ ምስራቅ ያሉትን ፣ እንዲያም ሲል ጎረቤቶቻችንን እንጠራለን። .... ግን ለምን? ... ነገሬን የበለጠ ግልጥ ለማድረግ ከመምህሩ ደቀ-መዝሙሩ እንዲባል ጦማሪው ( መምህሬ )ይህች ሀገር እንደ ሀገር ፤ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ ያላትንና ያለውን መልካም እሴቶች ዘንግተውታል እያልኩኝ አይደለም ፤ አብጠርጥረው ያውቁታል! ... ነገር ግን እያልኩኝ ያለሁት እንዲህ ቢደረግ ፣ እንዲያ ደግሞ ባይደረግ እንዲህ ማድረግ እንችል ነበር ፤ እዚህ ደረጃ መድረስ እንችል ነበር ፤ ... በማለት በኅሊናቸው ከሚመላለሰው ቁጭት የተነሳ ቁምነገራቸውን በሚያስተላልፉበት ወቅት ፣ ቁጭታቸው ስሜታዊነትን ወልዷል ... በመሆኑም ከትችቱ አብዝተዋል እያልኩኝ ነው። ( አሁንም ምን ያህል ግልፅ እንደሆንኩ አላውቅም ... ብትረዱኝ መልካም ፤ ባትረዱኝም ሐሳቤን መግለፅ የምችለው ይህን ያህል ብቻ ነው። )

  ሌላው ይህን በመሳሰሉ መንገዶች እንዲህ መገናኘታችን እርስ በርስ ልምዶቻችንን ፣ እውቀቶቻችንንና ሐሳቦቻችንን እንድንለዋወጥ ነውና ብዙው ሰው ከሚያራምደው ሐሳብ ወጣ ያሉ ሌሎች እይታዎች ሲመጡ በትዕግስት ልንነጋገር የሚገባን ይመስለኛል ( ደግሞ እኮ የብዙዎች መስማማት ፤ አንድን ሐሳብ የግድ ትክክል አያስብለውም ) .... እንዲያ ካልሆነ ሐሳብን በነጻነት መግለጥ እንደሚገባ ሲጻፍ ... አዎ ... አዎ ... ትክክል እያልን ፤ ሌሎች ሐሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ የምናስደነብር ከሆነ ... ልክ ነው ... ልክ ነው ማለታችን ካለማስተዋል እንዲሁ የምንለው ይሆንብናል። ( በነገራችን ላይ ይህን ማለቴ አንዳች ነገር እሆናለሁ ከሚል ሥጋት አይደለም ... ይብዛም ይነስም ሐሳቤን መቼ ፣ የት ፣ እንዴት ፣ እስከምን ድረስ መግለፅ እንዳለብኝ አውቃለሁ ብዬ አስባለሁ ... እንዳው በአንድ መድረክ እስከተገናኘን ድረስ ለማለት እንጅ )

  የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር መልካሙን ያመልክተን።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

  ReplyDelete
 25. i know dn. Daniel by addiss neger more. his messages are strong and to the point which shows the current situation tressed from the last history and proberbs.such explanations will enhance our peception. to me he one of the most speakers of life.but while i see those comments, suggession and opinions from the viewers reveal that many of us just reading the upper message of the boger.the ineer message is missed for us.if the inner message is not clear for us it is better to be silent, not to be misleaded and missquated the saying.being silent is called "zereba gidef'"
  better to listen

  ReplyDelete
 26. I like the issue and I like Eyob G's suggestions too. To me both guys are critical thinkers. Had I been in dn. Daniel's shoe, I would have some great point to grasp from what Eyob said. Eyob's anaylises is perfect seen from a perspective. Dani's intention is also clear, clean and positive.
  But some commenters need to have the maturity to entertain opposite ideas. Zim bilo zelo mawugez yetim ayadersim. Look at the points raised from the two guys and take some lesson out of it, that's it.
  To be honest, I like both guys' analisis, both have some meat.
  brother Eyob has just said his opinion, esun siletekawome mawugez ye dani degafinet mehon sayihon dinkurina new. Opinion is opinion, we need to entertain it, tolerate different ideas, learn sth positive out of any thing.... Yetifozo sira anargewu

  dani bertalign, egzer yabertah.

  ReplyDelete
 27. I completely disagree with Bisotegnaw's comment above. I think Eyob's comment belongs in this blog. Look, we don't have to agree with everything that D. Daniel writes in this blog. That doesn't mean we are not encouraging him to continue his work. We all have different views on any given topic and we should not consider any opposing views as an insult.

  I have already said this article of one of the best I've read. It points out one of the root causes of our enduring problems - that is mistrust and suspicious.
  Although Eyob may have missed the real massage D. Daniel is trying to communicate in this article, I do agree that most of D. Daniels writings tend to focus on the bad stuff. That is a little depressing to me. We do have a great deal of good virtues that need to be told. If we are trying to empower people to become a positive force in their environment, then it is wise to remind them of great things they have done in the past and shine light on their potential. It is demoralizing to hear constant negative criticism. So, I hope D. Daniel tell us positive and uplifting stories once in a while or at least give us "comic relief" with a funny story.

  thanks,

  ReplyDelete
 28. ለዚህ ጡመራ ተሳታፊዎች በሙሉ

  በዚህ ጡመራ ላይ በማወጣቸው ሃሳቦች ላይ ሁላችንም መስማማት አይጠበቅብንም፡፡ እንዲያውም መለያየታችን፣ መከራከራችን፣ ከተለያየ አቅጣጫ ማየታችን ነው የሚጠቅመን፡፡ በዚህ ጡመራ ላይ ሃሳብን መሠረት አድርገው የሚሞግቱኝን፣ የሚቃወሙኝን እና ከኔ የተለየም ሆነ የተሻለ ሃጻበ የሚያቀርቡትን ተሳታፊዎች አደንቃለሁ፤ እቀበ ላለሁ፤ አመሰግናለሁም፡፡ የመድረኩ ዓላማም ይኼው ነውና፡፡ በተለይም እንደ ኢዮብ ያሉትን በድፍረት የሚያኄሱትን አደንቃቸዋለሁና በርቱ፡፡
  ዳንኤል ክብረት

  ReplyDelete
 29. የተከለሰ ነገርን ብዙም አንጥላው፤ እንመርምረው እንመዝንው እንጂ፡፡ በቅሎ ከአሀያ እና ከፈረስ
  በመገኘት ጠንካራ መሆኗ፤አዝዕርትን በማዳቀል የተሸለ ምርት እና ጥንካሬ ማግኘት መቻሉ ወዘተ/የተለያዩ ጽንፍ መሆናቸውን እናሰተውል/ ለዚህ አባባል በመጠኑ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አማናለሁ፡፡እንደዚሁ ሁሉ የተቃረኑ ሀሳቦች ሲመጡ ና ሂስ ሲሰጣጡ እኛ አንባቢያን የተሸለ ግንዛቤ እና እውቀት ማግኘት እንድንችል ይረዳና የሚል ግምት አለኝ፡፡
  ዲ/ን ይህ ጥናትህ የሚደነቅ ነው፡፡ በርታልን!!!

  ReplyDelete
 30. Thank you Danni! We need to write our deep analysis on the articles so we can learn from each other. We ought to be critical thinkers including myself.

  ReplyDelete
 31. I share the views of Eyob G.

  ReplyDelete
 32. ጥሩ የመማሪያ መድረክ ነው፡፡
  ሁላችሁንም እግዚአብሄር ይባርክ

  ReplyDelete
 33. ዲ. ዳንኤል ስለ ነገረ ቅዱሳንኳ ሌላ መድረክ ላይ በሰፊው ብታስተምረን ሳይሻል አይቀርም፡፡ አየህ ያለመረጃና በቂ ማብራሪያ ትልቁን ጉዳይ (ሃይማኖታዊውን ጉዳይ) በእንዲህ ዓይነቱ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማንሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል .. መዘዙም ብዙ ነው፡፡ በተረፈ ግን ሥራዎችህ መልካም ናቸው በርታ፡፡

  ReplyDelete
 34. በስመ ሥላሴ
  በቅድሚያ የዚህ ጡመራ ተከታታዮች ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ፡፡
  “ኢዮብ ጂ” በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ተሰጡትንም አስተያየት ተቀብለው ይቅርታ መጠየቅዎ አግባብ ቢሆንም የሰጡት አስተያየት ግን ይቅርታ የሚያስጠይቅ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የዚህ ብሎግ ዓላማ እኔደእኔ አረዳድ የተየያዩ ሓሳቦችን በተለያየ አቅጣጫ ማየት ሐሳባችንን በተገቢው መንገድ በማንሸራር እንድንማማርበት ይመስለኛል እንጂ የወጣውን ጦማር ሁሉ ያልተስማማንበትንና ውስጣችን ያላመነበትን ትክክል ነው እያልን የአድናቆት አስተያየት ብቻ የምንሰጥ ከሆነ ግልጽነት ይጠፋና “ተደብቆ፣ ሰው ሳይሰማ፣ ነገርን ሁሉ መፈጸም ብልህነት፤ ድብቅነት ምሥጢራዊነት ነው ተባለ፡፡ ይህ ደግሞ ሐሜት ከመረጃ ይልቅ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው አደረገ፡፡ ድምጽን አሰምቶ፣ ራስን ገልጦ መናገር ከሰው አፍ መግባት፣ ብሎም በሰው ጥቁር ምላስ ተገርፎ መውደቅን ያመጣል ስለሚባል ሐሜት በሹክሹክታ ሀገሩን ያምሳል፡፡” የተባለው ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ በሰል ያለ ወይም ወጣ ያለ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችን ለምን የተሰማችሁን ተናገራሁ ብለን ማስደንገጥ ያለብን አይመስለኝም፡፡ እኔም “የኢዮብ ጂ”ን ሃሳብ እደግፋለሁ፡፡ ለማንኛውም ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡
  “በዚህ ጡመራ ላይ በማወጣቸው ሃሳቦች ላይ ሁላችንም መስማማት አይጠበቅብንም፡፡ እንዲያውም መለያየታችን፣ መከራከራችን፣ ከተለያየ አቅጣጫ ማየታችን ነው የሚጠቅመን፡፡ በዚህ ጡመራ ላይ ሃሳብን መሠረት አድርገው የሚሞግቱኝን፣ የሚቃወሙኝን እና ከኔ የተለየም ሆነ የተሻለ ሃጻበ የሚያቀርቡትን ተሳታፊዎች አደንቃለሁ፤ እቀበ ላለሁ፤ አመሰግናለሁም፡፡ የመድረኩ ዓላማም ይኼው ነውና፡፡”

  ReplyDelete
 35. ምንም የማንክደው ከላይ የተዘረዘሩትን ፀባያት ብዙዎቻችን የምንጋራቸው ናቸው እንዲህ አይነት ፅሁፎች ደግሞ አላማቸው ያሉብንን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክፍተቶች እያነሱ መወያየትና ቢያንስ ግንዛቤ አግኝተን ቀስ በቀስ እንድናስቀራቸው ነው ጥሩ ጥሩውንማ ሁሌ የምነሰማው ነው ለዚህም ይመስለኛል በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሶዎች ጸለምተኝነትን የሚያስወግዱ ጽሁፎችን እያነበቡ ያሉት ዲያቆን ግን እንዲህ አይነት ጽሁፎችን ስታዎጣ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ሳናውቃቸው የተጣበቁብንን በራስ ያለመተማመን የፀለምተኝነት የድብቅነትና የጠርጣራነት ባህርያቶቻችን የምናርቅባቸው መንፈሳዊና ስጋዊ ጥበቦችን ከመጽሃፍ ቅዱስም ከሳኮሎጅ መፅሃፍቶችም እያጣቀስክ ብታወጋን ጥሩ ነው በተረፈ በርታ

  ReplyDelete
 36. Dany tru Tazbehal ategebachin hono yalayenewn ,betegbar yaderegnewn gin yalastewalnewn masayet qelal neger aydelem .Diro yechigir temsalet yeneberut hulu ahun tarik honew manetsaseriya nachew . Yane Chi fan le ma ? ahun qerto che huan le ma ?honoal Dani ye befit Muq wha le safty teblo neber yteta yeneberew . Ahun Gin It became their part of culture .andu china bet bithed mejemeriya yemiyaqerblh ye moqe wiha new . Inam Medical advantage alew bilo new yemiseth be irgtm linorew yichlal (Specially for hypertension)igna gam bezih melk bitays ?qedmo sigat yeneberew ahun degmo le ingdaw kibr teblo biwesed tiru ayhonm ?

  ReplyDelete
 37. Dany tru Tazbehal ategebachin hono yalayenewn ,betegbar yaderegnewn gin yalastewalnewn masayet qelal neger aydelem .Diro yechigir temsalet yeneberut hulu ahun tarik honew manetsaseriya nachew . Yane Chi fan le ma ? ahun qerto che huan le ma ?honoal Dani ye befit Muq wha le safty teblo neber yteta yeneberew . Ahun Gin It became their part of culture .andu china bet bithed mejemeriya yemiyaqerblh ye moqe wiha new . Inam Medical advantage alew bilo new yemiseth be irgtm linorew yichlal (Specially for hypertension)igna gam bezih melk bitays ?qedmo sigat yeneberew ahun degmo le ingdaw kibr teblo biwesed tiru ayhonm ?

  ReplyDelete
 38. please tell me tell me about trinity I know but I want to know more because some peoples specially muslims and protestants think that we worship 3 gods.

  ReplyDelete