Tuesday, September 14, 2010

አባ ሐና

በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው የጠፋ ሁለት ገብረ ሐናዎች አሉ፡፡ አለቃ ገብረ ሐና እና አባ ገብረ ሐና ጂማ፡፡ ሕዝቡ ሁለቱንም ባለ ውለታዎች በተሳሳተ መንገድ ተረዳቸው፣ ታሪካቸውንም በተሳሳተ መንገድ አስተላለፈው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሼክስፔሩን ሻይሎክ ያህል ገብጋባ ናቸው እየተባሉ የሚጠሩት አባ ሐና ጂማ ማን ናቸው? ለምንስ ገብጋባ ሰው «አባ ሐና» ተብሎ ሊጠራ ቻለ? አብራችሁ ቆዩ፡፡

እስከ 1953 ድረስ ከ30 ዓመታት በላይ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስለነበሩት ስለ አባ ሐና ጂማ በተመለከተ በቂ የሆነ የተጻፈ መረጃ የለም፡፡ በአፈ ታሪክ ግን ገብጋባ ናቸው እየተባለ ይነገራል፡፡ የዚህ ብሎግ አዘጋጅ ለማሰባሰብ የሞከረው ታሪካቸው ግን ይህን የሚያስተባብል ሆኖ አግኝቶታል፡፡

የአባ ሐናን ትውልድ እና ዘመን በተመለከተ ታኅሣሥ 26 ቀን 1953 ዓም ታትሞ የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ «አባታቸው ፊታውራሪ ጂማ አባ ጋርጠው፣ እናታቸው ወ/ሮ እሰዩ እንደሚባሉ፤ የተወለዱትም በ1889 ዓም እንደሆነ» ይገልጣል፡፡ ትውልዳቸውንም ጎጃም እነብሴ ነው ይላል፡፡ እኔ ግን በሌላ መረጃ የፊታውራሪ ጂማ አባ ጋርጠው ትውልድ ሰሜን ሸዋ ነው የሚል አይቻለሁ፡፡ ለ30 ዓመታት አብረዋቸው በቤተ መንግሥት ከአባ ሐና ጋር የግምጃ ቤት ሹም በመሆን የሠሩት አቶ አርአያ ተገኝ እንደሚገልጡት ደግሞ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረሞ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምናልባትም የአባታቸው ስም «ጅማ» መሆኑን ስናይ ሚዳ ወረሞ የኦሮሞ ተወላጅ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ አባታቸው የሰሜን ሸዋ ሰው ናቸው ከሚለው ጋር ስናስተያየውም የአቶ አርአያ ገለጻ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ትክክለኛው ስማቸው አባ ገብረ ሐና ጅማ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ለማሳጠር አባ ሐና እያለ ስለጠራቸው ይሄው ተለምዶ ቀረ፡፡

ጋዜጣው እንደሚተርከው አባታቸው ፊታውራሪ ጅማ ልዑል መኮንንን ተከትለው ወደ ሐረር በመውረዳቸው አባ ሐና የተወለዱት ሐረር ነው፡፡ እስከ የልጅነት ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት አሳልፈው በ1902 ዓም በልዑል መኮንን ግቢ ማገልገል ጀመሩ፡፡ መነን መጽሔት የካቲት /መጋቢት 1953 እትም እንደሚገልጠው እስከ 1910 ዓም የልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ አሽከር ሆነው ከቆዩ በኋላ ጠፍተው ደብረ ሊባኖስ በመሄድ መነኮሱ፡፡ አልጋ ወራሽ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑም በቤተ መንግሥቱ ሥራ እንዲረዷቸው ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡

እንደ አቶ አርአያ ትረካ ግን አባ ሐና መጀመሪያ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብተው በመመንኮስ ገዳማውያኑን በረድእነት ያገለግሉ ነበር፡፡ እንጨት በመስበር፣ ውኃ በመቅዳትና በየቀኑ ከ50 ያላነሰ ዳቤ በመጋገር በአገልጋይነታቸው የተመሰገኑ ነበሩ፡፡ በሚያዝያ 27 ቀን 1953 ዓ.ም የምስካየ ኅዙናን ገዳም የተምሮ ማስተማር ማኅበር ያሳተመው በራሪ ጽሑፍም «ቀድሞም በምናኔ ገዳምን አበው መነኮሳትን አሥራ ሁለት ዓመት በተልእኮ በመርዳታቸው ስመ ጥሩ እንደ ነበሩ ያሉት በቃላቸው የሞቱትም በመንፈሳቸው አስተላልፈውላቸው ይገኛል» ይላል፡፡ የቅዳሴ ትምህርት መማራቸውንና ዜማ እንደሚያውቁ አቶ አርአያ ይናገራሉ፡፡ ለዜማ የሚሆን ድምፅ ግን እጅግም አልነበራቸውም፡፡

ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሥልጣን እንደ ያዙ ወደ ደብረ ሊባኖስ ወርደው አንድን የበቁ አባት «አብያተ ክርስቲያናትን ለማሠራት አስበናል ሀብታችንን ተቆጣጥሮ ለሀገራችንም ለቤተ ክርስቲ ያናችንም በአግባቡ እንዲውል ለማድረግ ሁነኛ ሰው ያስፈልገናልና ምን እናድርግ)» ብለው አማከሯቸው፡፡ እኒያም አባት «ይህን የመሰለውን ሥራ ከአባ ሐና በቀር ማንም አይሠራውም» ሲሉ መለሱላቸው፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴና አባ ሐና የተገናኙት በዚህ መንገድ ነበር ይላሉ አቶ አርአያ፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አባ ሐናን ከደብረ ሊባኖስ አምጥተው የግምጃ ቤቱ ኃላፊ አደረጓቸው፡፡

አቶ አርአያ አንደሚገልጡት አባ ሐና ሲበዛ መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ ከሥጋና ከመጠጥ ተከልክለው ሽሮና ጎመን ነበር የሚበሉት፡፡ እንዲያውም በቤተ መንግሥቱ «የአባ ሐናን ሽሮ አምጡልን» እየተባለ ይጠየቅ እንደ ነበር ያስታውሱታል፡፡ ቤታቸው አንዲት ጠበባብ ክፍል፣ መኝታቸው ከደረቅ አልጋ ላይ እንደ ነበር በቅርብ የሚያውቋቸውና ብዙ ጊዜ በሥራ ምክንያት እየመሸባቸው በአባ ሐና ቤት ያድሩ የነበሩት አቶ አርአያ ይገልጣሉ፡፡

በዚያ ጊዜ ገና መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በሚገባ ባለመደራጀታቸው አባ ሐና ብዙ ኃላፊነት ተሸክመው ነበር፡፡ ለአብያተ ክርስቲያናት መሥሪያና ለገዳማት መርጃ የሚውለውን ማደራጀት፡፡ ለጦሩ ልብስና ቀለብ ማዘጋጀት፣ የንጉሡን ትእዛዝ ለሚመለከተው ማስተላለፍ፣ ለቤተ መንግሥቱ የሚሆነውን ምግብና ቁሳቁስ ማዘጋጀት፣ ንጉሡ የሚሸልሙትን አልባሳትና ሌሎች የወግ ዕቃዎች ማደራጀት፣ወዘተ በእርሳቸው ኃላፊነት ላይ የወደቀ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ ኃላፊነታቸው የተነሣ እስከ ምሽቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አምሽተው ይሠሩ እንደ ነበር አቶ አርአያ ያስታውሱታል፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን ከምሽቱ ዘጠኝ ሰዓት ገብተው በአባ ሐና ቤት ምግብ ባለመኖሩ አቶ አርአያ ጦማቸውን አደሩ፡፡ አባ ሐና ያንን ለንጉሡ በመናገራቸው 300 ብር አበል እንዲቀበሉ እንዳደረጓቸው ያስታውሳሉ፡፡

አባ ሐና ጅማ ሠራተኞችን በፍቅር ማሠራትን እንጂ በበላይነት ማዘዝን አይወዱም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሥራቸው የነበሩትን አገልጋዮች ሥራ ባለበት ቦታ በጋራ የመሥራት ባሕልን አስለምደው ነበር፡፡ ሠራተኞቹ ሲያገለግሉ ውለው ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ከአራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ በገዛ ገንዘባቸው ሥጋ ገዝተው ማብላት ማጠጠጣት ልማዳቸው ነበር፡፡ በዚህም አገልጋዮቹ ይወዷቸው ነበር፡፡

ከአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድሮው ቤተ መንግሥት በስተ ጀርባ /በአፍንጮ በር በኩል/ ለቤተ መንግሥቱ ያቋቋሙት የአባ ሐና ወፍጮ የሚባል ነበር፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ብዙ የአብነት ተማሪዎችን ከደመወዛቸው እያወጡ ይረዷቸው ነበር፡፡ ብዙ ወላጅ የሞቱባቸውን ሕፃናት ይረዱ እንደ ነበር ገንዘቡን በማከፋፈል በተግባር የተሳተፉት አቶ አርአያ ይገልጣሉ፡፡

አባ ሐና በጠባያቸው ቁጣና ቂም አያውቁም፡፡ ብዙ ሰዎች በክፉ ሲናገሯቸው «ዝለለው» እያሉ ያልፏቸው ስለ ነበር አባ ሐና «ዝለለው» በማለት የሚጠሯቸው ነበሩ፡፡

አባ ሐና ገብጋባ የሚለውን ስም ያተረፉት በራሳቸው ጠባይ ሳይሆን በቤተ መንግሥቱ የአሠራር ችግር የተነœ መሆኑን በዚያ ጊዜ በልጅነት አባ ሐናን የሚያውቋቸውና ቤተ መንግሥት ያገለግሉ በነበሩት አባታቸው ምክንያት ወደ ቤተ መንግሥቱ እየገቡ አባ ሐናን ለማወቅ የበቁት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ይገልጣሉ፡፡ እንዲያውም «አባ ሐና «escape goat» /በኦሪቱ ባላጠፋው ጥፋት የሕዝቡን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ በረሃ የሚለቀቀው ፍየል/ ናቸው» ሲሉ ሊቀ ጉባኤ አስረድተዋል፡፡

በቤተ መንግሥቱ የነበረው የመጀመርያው የአሠራር ችግር ንጉሡ የግምጃ ቤቱን ዐቅም ሳያገናዝቡ ቃል መግባታቸው ነው፡፡ ይህ ንጉሡ ይገቡት የነበረው ቃል ከግምጃ ቤቱ ዐቅም በላይ ሲሆን አባ ሐና ያለውን ብቻ ለመስጠት ይገደዱ እንደ ነበርና ይህም ከተቀባዮቹ ጋር በግምጃ ቤት ሹምነታቸው ያጣላቸው እንደነበረ አቶ አርአያ ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ንጉሡ ቢሰጡኝም አባ ሐና ከለከሉኝ እያሉ የሚናገሩ ሰዎች ስማቸውን አጥፍተውታል፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ በተለይም ከ1933 ዓ.ም በኋላ ግምጃ ቤቱ በጣልያን ስለ ተዘረፈ ባዶ ነበር፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ለጃንሆይ የሰጠው መጠነኛ ገንዘብ ብቻ ነበረ፡፡ አርበኞቹ እየመጡ ሲፎክሩ ንጉሡ ይህን ያህል ገንዘብና ልብስ ይሰጠው ብለው ያዝዛሉ አባ ሐናም ያለውን አብቃቅተው ይሰጣሉ፡፡ ይህ ተግባር በብዙ አርበኞች ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡ 25ኛው ዓመት ኢዮቤልዩ እስኪከበር ድረስ በቤተ መንግሥቱ የሀብት ችግር እንደ ነበር በቅርብ የሚያውቁት አቶ አርአያ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ወቅት በተለይ አባ ሐናን በእጅጉ አሳጥቷቸዋል፡፡

አባ ሐና ግን « እኔኮ የንጉሡን ሸክም ተሸክሜ የምኖር ነኝ» እያሉ በደሉን በመሸከማቸው ይደሰቱበት ነበር፡፡

አባ ሐና ምንም መልካም ስም ባያተርፉባቸውም ብዙ ገዳማትና አድባራት እንዲረዱ፣ እንዲጠገኑና አዲስ እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡ «ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አጠገብ ሆነው በመንፈሳዊው ረገድ ያለውን ኃላፊነት እየጠበቁ እንዲያስፈጽሙ ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ምቾቱ ሳያታልላቸው፤ ትሩፋታቸውንና ትህርምታቸውን ሳይከለክላቸው፤ ከርዳታቸው ሳይወጡ፤ ከመሥመራቸው ሳይናወጡ፤ በቤተ ክርስቲያን በኩል ያለውን የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አደራ በታላቅ ትጋትና ታማኝነት ጠብቀው ትልቅ መገናኛ ድልድይ በመሆን የፈረሱት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሠሩ፣ያረጁትም እንዲታደሱ፣ ካህናቱ በየጊዜው የሚደርስባቸው ችግር እንዲወገድላቸው ለግርማዊነታቸው እያቀረቡ ያስፈጽሙ ነበር» በማለት በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር ማኅበር ያሳተመው የመታሰቢያ ወረቀት ያመሰግናቸዋል፡፡

አባ ሐና ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው ሰው እንደ ነበሩ ለማስረዳት አቶ አርአያ አንድ ገጠመኛቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ ቀን ዕቃ ለማፈላለግ ከተማዋን ሲዞሩ ውለው ከምሽቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ ራስ መኮንን ድልድይ ሲደርሱ አባ ሐና አቶ አርአያን «እባክህ እግዚኦ ብለህ አዚም» ይሏቸዋል፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋቡት አቶ አርአያ «በዚህ ምሽት የምን እግዚኦታ ነው?» ይላሉ፡፡ «አይ ዝም ብለህ እግዚኦ በል» ይሏቸዋል አባ ሐና፡፡ አቶ አርአያም «እግዚኦ» ብለው ያዜሙላቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ አባ ሐና አንድ ጥያቄ ጠየቋቸው፡፡ ለመሆኑ «እኔ የማን ነኝ? የእግዚአብሔር ነኝ እንዳልል አንድም ቀን አቡነ ዘበሰማያት ብዬ ጠይቄው አላውቅም? የሕዝቡ ነኝ እንዳልል አይ አባ ሐና ይለኛል፣ ታድያ እኔ የማን ነኝ?» ሲሉ ከባድ ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ አቶ አርአያም «የማንም አይደሉም፤ የእግዚአብሔር ነዎት፡፡ ለዚህ ሥራ ያመጣዎት እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሳይጨነቁ እርሱ ያመለከተዎትን ብቻ ይሥሩ» አሏቸው፡፡ ይህ ጉዳይ እስከ ንጉሡ ደርሶ አቶ አርአያን እንዳስመሰገናቸው ይተርካሉ፡፡

የምስካየ ኅዙናን ገዳም የመጀመሪያው አስተዳዳሪና ገዳሙ እንዲጠናከር ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት አባ ሐና ነበሩ፡፡ ገዳሙ በልማት ራሱን አንዲችል፣ ገዳማውያኑ በሥርዓት እንዲኖሩ ጥረት አድርገዋል፡፡ እንዲያውም በቤተ መንግሥቱ አንዳች ጠቃሚ ንብረት ሲያገኙ «ለምስካየ ኅዙናን ይሁን» እያሉ ንጉሡን አስፈቅደው ይወስዱ እንደ ነበር ይነገራል፡፡

የተምሮ ማስተማር ማኅበር እንዲጀመር፣ አባላቱ እንዲበዙና ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ መኳንንቱና መሳፍንቱ አባል እንዲሆኑ፣ በሀብት እንዲበለጽግ ታላቅ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ገዳሙ ባረፉበት ቀን ያሳተመው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡

አባ ሐና ሌላው የሚታወሱበት ሥራ የደብረ ሊባኖስን ቤተ ሰሊሆም የደካሞች መርጃ ገዳም እንዲመሠረት ማድረጋቸው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ዘመን ያገለገሉበትን ገዳም ደብረ ሊባኖስን በሚያስፈልገው ሁሉ ለመርዳት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡

አባ ሐና ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች እንዲሾሙ የሚፈልጉ ሰው እንደ ነበሩ ሟቹ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ ይናገራሉ፡፡ መንግሥቱ ንዋይን፣ አቡነ ማቴዎስን /ለታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ሊቀ ሊቃውንትነት/፣አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህን፣ ወዘተ እየጠቆሙ ያስሾሟቸው እርሳቸው ነበሩ፡፡

ሌላው አባ ሐና የሚታወሱበት ነገር ለመነኮሳት የሚሆን አዲስ አለባበስ ያመጡ መሆናቸው ነው፡፡ ረዘም ያለ ካፖርትና ሱሪ መልበስን በስደት ወቅት ኢየሩሳሌም ሄደው ሳለ ተመልክተው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያስተዋወቁት እርሳቸው ናቸው፡፡

አባ ሐናና መንግሥቱ ንዋይ ከጥንት ጀምሮ ወዳጆች ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ ወደ ገዳማት መብዐ ለመላክ መኪና የሚጠይቁት ከእርሱ ነበር፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዕለት አባ ሐናና አቶ አርአያ ወደ ብራዚል ለንጉሡ የሚላክ ቡና እያፈላለጉ ገበያ ነበሩ፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጡ ነገሩ ሁሉ እንዳልነበር ሆኗል፡፡ ታላላቅ ባለ ሥልጣናት እየተያዙ ታሥረው ነበር፡፡ አባ ሐና ግን በመንግሥቱ ንዋይ መኪና እንዲቀመጡ ተደርገው ይዟቸው ሲዞር ነበር የዋለው፡፡

በመጨረሻ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉ ሲታወቅ የተያዙት ባለሥልጣናት እንዲገደሉ ሃሳብ ሲቀርብ መንግሥቱ ንዋይ ራስ ስዩምና አባ ሐና እንዲለቀቁ ሃሳብ ነበረው፡፡ ግርማሜ$ ንዋይ ግን በዚህ ሃሳብ አልተስማማም፡፡ ስለዚህም እርሱ ራሱ በጥይት መትቶ ረቡዕ ለኀሙስ ሌሊት ታኅሳስ 3 ቀን 1953 ዓም ገደላቸው፡፡ እሑድ ዕለትም ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡

ሲሞቱ ዕድሜያቸው ወደ 70 ይጠጋ እንደ ነበር አቶ አርአያ ገምተዋል፡፡ እርሳቸው ካረፉ በኋላ የሚጠሏቸው ሰዎች አንዲት ሥራ ቤት ውስጥ ታገለግል የነበረች ሴት በገንዘብ አታልለው ወደ እቴጌ መነን ላኩ፡፡ እርሷም ሁለት ልጆቿን ይዛ ቀርባ «ከአባ ሐና የወለድኳቸው ናቸውና ውርስ ይገባኛል» አለች፡፡ እቴጌ መነን ተናድደው «አባ ሐና ከአንቺ ጋር ይህን የመሰለ ነገር የሚፈጽምበት ቀርቶ እህል የሚቀምስበት ጊዜ የሌለው ሰው ነው፡፡ ይህ ስሙን ለማጥፋት ያቀዳችሁት ነው፡፡ በሉ ያዟትና እውነቱን ታውጣ፡፡» ብለው ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትዮዋ ደንግጣ በገንዘብ ተገዝታ ይህንን መፈጸሟን በግልጽ ተናገረች፡፡

ምንጭ፡ የቃል አስረጅ፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ የነበሩ፤አቶ አርአያ ተገኘ፣ በቤተ መንግሥት የግምጃ ቤት ሹም የነበሩ፤ ሟቹ ብጹእ አቡነ ማቴዎስ፤ የተምሮ ማስተማር ማኅበር ሚያዝያ 27 ቀን 1953 ዓ.ም ያሳተመው ወረቀት፤ ፋንታሁን እንግዳ፣ታሪካዊ መዝገበ ሰብ፣ 2000 ዓም፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታኅሣስ 26፣ 1953፤ መነን መጽሔት፣ የካቲት/ መጋቢት፣ 1953 ዓም


24 comments:

 1. እንኳን አደረሰህ

  ዛሬ ደግሞ ቤተ መንግስቱ አካባቢ አዋልከን አባ ሃናንም አስተዋወከን ይህ ጽሁፍ ከ አንድ ትልቅ መጽሐፍ ብዙገጽ ካለው ይበልጣል ።

  ጤናውንና ሰላሙን ያብዛልህ

  ReplyDelete
 2. አምደ ሚካኤልSeptember 14, 2010 at 10:22 AM

  ጥሩ ስራ ሰርተው ታሪካቸው (ገድላቸው) የተደበቀ ወይም ያልተነገረላቸው ብዙ አበው ስላሉ እንዲህ እስነብበን ወንድማችን
  እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ይጠብቅልን (ዲ/ዳንኤል ራስህን እየጠበቅህ ከእግዚአብሔር ጋር)

  ReplyDelete
 3. I admire the work attitude of aba Hanna.He is exampliary in this respect.

  ReplyDelete
 4. Many thanks Dn. Please keep in digging out such unheard and unread stories of our celebrated fathers.

  stay blessed

  ReplyDelete
 5. ዲያቆን መሐሪ ገብረ ማርቆስSeptember 14, 2010 at 1:16 PM

  ሊቀ ጉባኤ አበራ ያሉትን ሰውየው የንጉሡ በደል ተሸካሚ በግ የመሆናቸውን ጉዳይ በሌላ አቅጣጫ በRyszard Capuciniski የተጻፈው “The Emperor” ውስጥ አንብቤ ሲነገረኝ ካደግሁትና እርሱም (ባህላዊው ፕሮፓጋንዳ- መጽሐፍ ቅዱስን ተተግነን “ክፉ ወሬ” ልንለውም የምንችል ይመስለኛል) በውስጤ ካሳደገው ክፉ “የአባ ሐና” ምስል ጋር ተዛምዶው የተቃርኖ ቢሆንብኝ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡

  የደራሲው ኮሚዩኒስታዊ ጠገግን የሙጥኝ ያለ ነገሮችን የመፈከሪያ መንገድ እንዲሁም ንጉሣዊ ሥርዓቱንና ንጉሡን በጥቅሉ አጠይሞ የመመልከት አካኼድ ውጤት ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ አሁን ጥርጣሬዬ ተወግዷል፡፡

  በል ስለ አለቃ ገብረ ሐና ደግሞ እንደዚሁ አስነብበን፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ቦታ ያቀረብከው ሥራ እንዳለህ አውቃለሁ፡፡

  ተባረክ አቦ!

  ReplyDelete
 6. ከምጥው ለአንበሳ
  እንዲህ ፈልፍለህ እውነቱን ንገረን እንጂ ። የስንቱ ሰው ታሪክ ባልሆኑ ሰዎች ተበላሽቶል ጎበዝ
  ኤልዛቤልም በኤልያስ ላይ ተነሳች የኣንተን ነፍስ እንደ አንዱ ነፍስ ባላደርግ አማልክት ይህንን ያርጉብኝ ይህንንም ይጨምሩብኝ ብላ ዛተች ኤልያስም ነፍሱን ያድን ዘንድ ሸሸ። ዛቲ ለመቅበስ
  ከበዓሉ በኃላ ደጀ ሰላም ለመቅመስ ስገባ የሰላሁት ወሬ እንደአባ ገብረሃና ታሪክ የተሳሳተ ነው ወይስ እውነት ከራስህ ካልሆነ ለማንኛውም ኤልዛቤል እየለየላት መምጣቱን ያሳያል። ዛሬ ለንስሐ ጊዜ ተሰጥቷታል። አለበለዚያ ኢዩ ይላክባታል።

  ReplyDelete
 7. ለእኔ ሁሉም አዲስ ነው ዳኒ የኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተት እነዳይፈጠር እና በተሳሳተ መረጃ እንዳይገለፅ የአቅምህን እየሞከርክ ነውና እግዚያብሔር ይስጥልን። በርታ

  ReplyDelete
 8. ሶስተኛው፡የጽሑፉ፡አካል፡እንዲህ፡ ይላል፦

  "ጋዜጣው እንደሚተርከው አባታቸው ፊታውራሪ ጅማ ል
  ዑል መኮንንን ተከትለው ወደ ሐረር በመውረዳቸው አባ
  ሐና የተወለዱት ሐረር ነው፡፡ እስከ የልጅነት ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት አሳልፈው በ1902 ዓም በልዑል መኮንን
  ግቢ ማገልገል ጀመሩ፡፡ መነን መጽሔት የካቲት /መጋቢ
  ት 1953 እትም እንደሚገልጠው እስከ 1010 ዓም የልዑል
  አልጋ ወራሽ ተፈሪ አሽከር ሆነው ከቆዩ በኋላ ጠፍተው ደ
  ብረ ሊባኖስ በመሄድ መነኮሱ፡፡ አልጋ ወራሽ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑም በቤተ መንግሥቱ ሥራ እንዲረዷቸው ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡"

  ልዑል፡መኮንንን፡ሲል፡ልዑል፡ራስ፡መኮንንን፡ማለቱ፡መሁኑ
  ን፡ቢመለከት፡አንባብያንን፡ይረዳል።

  ወረድ፡ብሎም፡"እስከ 1010 ዓም የልዑል አልጋ ወራሽ ተ
  ፈሪ አሽከር ሆነው ከቆዩ በኋላ ጠፍተው ደብረ ሊባኖስ በ
  መሄድመነኮሱ፡፡ዓመተ፡ምሕረቱ፡የጽፈት፡ግድፈት፡ስለሚታ
  ይበት፡ተስተካክሎ፡1910 ተብሎ፡ይታረም፡ዘንድ፡አሳስባለሁ።


  የያዝነውን፡ዘመነ፡ሉቃስ፣የምሕረትና፡የበረከት፡ያድርግልን!

  ስለ፡ተዋሕዶ-ኢትዮጵያ፡በጸሎትና፡በሥራም፡እንበርታ!

  እመ፡ብርሃን፡ትርዳን!አሜን።
  ሳሙኤል፡ዘአሰቦት።

  ReplyDelete
 9. Dear Dn. Danile,

  Thank you very much for sharing us the right truth abour Aba Hanna.

  ReplyDelete
 10. ከደብረ ቁስቋም
  ሰላም ለዚህ ቤት
  ወንድማችን በእውነት ተልቅ ግንዛቤ ነው ያስጨበጥከን ምክንያቱም እስከዛሬ ድረሰ አባ ሀናን የምናውቃቸው በስስታምነታቸው ፤በንፉግነታቸው ነበር ለካስ ታሪክ ተቀይሮ ኖርዋል በውነት እውነተኛ ያባቶች ታሪክ እንዲህ እውነቱ ወጥቶ ስናነበው ደስ ይላል.ቃለ ህይወት ያሰማልን.
  ቅድስተ ቅዱሳን ሰአሊተ ምህረት አቁራሪተ መአት ድንግል ማርያም ኢትዮጵያ ሀገራችንን ቤተ ክርስትያን እናታችንን ትጠብቅልን.
  አሜን

  ReplyDelete
 11. ብዙውን የማገልገልም የመገልገል ጊዜየን የኖርኩት ምስካዬ ኅዙናን ገዳም ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡ የገዳሙ መንፈሳዊ ጸጋ ሁሌም ስለሚያስደምመኝ ለሥፍራው ተግቶ የሚጸልይ ወይንም ቃል ኪዳን ያሰጠው ጻድቅ መኖር አለበት የሚል እምነት ነበረኝ፡ በተለይም የመሥራቹን የአባ ሐና ጅማን መንፈሳዊ ህይወት ከገዳሙ ውጭ ያሉ ሰዎች እንደሚሉት ሳይሆን የሌሎችን በደል ተሸክመው የኖሩ ቅዱስ ሰው መሆናቸውን ስረዳ መቃብራቸውን ለመጎበኘት ደብረሊባኖስ ወረድኩ:: የአባታችን የአባ ሐና ጅማን የመቃብር ሐውልት የዋርካ ዛፍ መሃል ለመሃል ከፍሎት መብቀሉን ስመለከት ስለ አባ ሐና ቅድስና እግዚአብሔር ማረጋጫ እንደሰጠኝ አምኛለሁ::

  ዳኒ እግዚአብሔር ይባርክህ:: ረጅም የአገልግሎት ዘመን ይስጥህ::

  ReplyDelete
 12. +++

  ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ጤናውንና ሰላሙን ያብዛልህ:: ጥበቃዉ አይለይህ::

  ታዲያ ዳንኤል ራስህን እየጠበቅህ ከእግዚአብሔር ጋር

  ድንቅ ታሪክ: እንዴት እንደሚጣፍጥ : ይገርማል::

  ምን በድለዉ? ለምድን ነዉ ግን የገደላቸዉ"ስለዚህም እርሱ ራሱ በጥይት መትቶ ረቡዕ ለኀሙስ ሌሊት ታኅሳስ 3 ቀን 1953 ዓም ገደላቸው፡፡ እሑድ ዕለትም ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡"

  ለቀጣዉ ያድርሰን

  ReplyDelete
 13. Egziabhier yistilign dn.daniel our God says "Z world hates me"this indicates it also hates peoples of GOD like st.atnatious,aba hana jima as u have said.but u tell me about real history of aba hana & what he did in z government and in spritual aspects.i wish to have such fathers today that can stand for others than for themselves;not only fathers but we z youth must bear in mind what aba hana did..
  GOD BLESS U ,YOUR WORK&YOUR LIFE

  ReplyDelete
 14. እሌኒ ከሲራክዩስSeptember 15, 2010 at 6:32 AM

  በእውነት ድንቅ አባት ነበሩ:: መንፈሳዊ አገልግሎት ምን አይነት ሊሆን እንደሚገባ በስራ ያሳዩ አባት ናቸው:: በረከታቸው ይደርብን!

  ReplyDelete
 15. በሰው ፊት ተንቀው በምግባር ያበቡ
  ከስጋ ክብር ይልቅ ለነፍስ የሚያስቡ
  እንደነ አባ ሐና ህጉን የጠበቁ
  በቃል ብቻ ሳይሆን በሕይወት የኖሩ
  ኧረ ብዙ ናቸው አምላክ የሚያውቃቸው
  ብፁዕ የተባሉ በበጎ ስራቸው፡፡

  ቢናቁ ቢጠሉ በምድራዊ እይታ
  ባልሰሩት ሐጢአት ባልዋሉበት ቦታ
  ዋጋችው ከፍ ይላል በላይኛው ጌታ፡፡

  ReplyDelete
 16. ብዙ ሰዎች እውነተኛ ማንነታቸው ተደብቆ ያለስማቸው ስም ተሰጣቸው፡፡ አንደኛውን አባት አሳወቅከን ሌሎቹንም እንዲሁ ትገልጥልን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳህ፡፤
  ቃለ ሕይወት ያሰማልን
  ካሳሁን

  ReplyDelete
 17. dany leka aba hanna menfesawe neberu?

  ReplyDelete
 18. አብርሃም ሰሎሞን ዘሚኒሶታSeptember 17, 2010 at 7:15 AM

  ወይ አባ ሐና ለካስ የንጉሥ ገንዘብ እያለቀብዎት ሲያብቃቁ ነው የኖሩት። እኔ በቤቴ አባ ሐና ማለት ገብጋባ እንጂ ባጀት አስተካካይ አይመስለኝም ነበር። ከእንግዲህ እንዴት እና ለምን ሳልል ዝምብዬ አልፈርድም። እኔም ስንቱን ሰው አባ ሐና እያልኩ መርጌበታለሁ። አሁን ግን የተረዳሁት ያ አባ ሐና ያልኩት ሰው ኑሮውንና ችግሩን ያለእርሱ የሚያውቅለት እንደሌለ ነው። ባላውቅዎትም አባ ሐና በማለት መተረቻ አድርጌዎት በመኖሬ ይቅር ይበሉኝ። የግርማሜ ንዋይን ነገር መነሻውን ስለማላውቅ ፍርዱን ለእግዚአብሔር ብያለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ዳንኤል ክብረትን ከልብ አመሰግናለሁ።

  ReplyDelete
 19. aman menenu semait taema leza alem-semaetat Yezichin alem taiem be ewunet naku...

  man Yihun ke zih temiro rasun YmiYastakakil?

  ReplyDelete
 20. YE BEREN WULETA WESEDEW.... ALE GEBEREW.
  NEGERU LEKA ARENBA ENA KOBO NORUWAL...
  Dn.Dani ante endih eytsafik egna bananeb gin wurd kerasachihu malet tichilaleh. Lelam anten yemiteka lij ayasatan.
  edmen yedililin

  ReplyDelete
 21. Dn. Daniel,
  I don’t know if you realized it but you just fulfilled the promise that God gives to His servants. God always promises the people He chooses by promising to bless the people that write and read the lives of His Servants. Reading Aba Gebre Hana’s history (Gedle) was a blessing. Thank you for revealing the truth. Egziabhair Wagahin Yikfelih!
  Kelehiwot Yasemalin!
  Ameha Giyorgis
  DC

  ReplyDelete
 22. ከምቀርባቸው ሰዎች ውስጥ በገንዘብ አያያዙ ቆንጠጥ ያለ ሰው ሲያጋጥመኝ አባ ሀና የማለት ልምድ ነበረኝ ከንግዲህ ግን እርም ብያለው

  ReplyDelete
 23. Woye Daniel, Yetkeberwen felfeleh Astemarken
  Kale hiwot Yasemah
  Egiziabher Yetebekeh
  Makeda

  ReplyDelete