Thursday, September 2, 2010

የእኔ እይታ


ኃይለ ገብርኤል ከአራት ኪሎ

ውድ አንባብያን እንዴት ሰነበታችሁ? ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን።

እንደምታስታውሱት በክፍል አንድ ባቀረብኩት እይታዬ «መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ማለት ምን ማለት ነው?» በሚል ርዕስ በአነስተኛዋ አዕምሮዬ የተመላለሰውን ሀሳብ ሰንዝሬ ነበር። ከዚያም የኔን ሃሳብ ተከትሎ የተፃፉትን አስተያየቶች አንድ ባንድ ተመለከተኳቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከተኛል ብላችሁ የየራሳችሁን አመለካከት የሰጣችሁን ወንድሞች እና እህቶች ከልብ አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ያክብርልኝ።

በፅሑፉ ውስጥ እንደተመለከታችሁት

1ኛ. በህግ መንግሰቱ ላይ የሰፈረው አንቀፅ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ ዓላማ እና ግብ አንፃር አንድምታው ምንድነው?

2ኛ. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለአኛ ለተከታዮቿ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ለመንግስትም ጭምር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ያደረገችውን እና እያደረገችው ያለችውን አስተዋፅኦ ከብዙ በጥቂቱ ምን ይመስላል?

3ኛ. በአሁኑ ሰዓት እየተመለከትነው ያለነው ችግር የተከሰተው ዛሬ ሳይሆን ቀስ በቀስ እንደሆነና ችግሩም እንዲባባስ ያደረግነው እኛው በዝምታችን ነው

4ኛ. ይሕ ዝምታችን በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ችግሮችን ከማወሳሰብና የመፍቻ ውላቸውን ከማጥፋት የዘለለ ወጤት እንደሌለው ልንገነዝብ ይገባል

5ኛ. ስለዚህ ለማየት የምንናፍቀውን የቤተ ከርስቲያንን አንድነት እና ሰላም እንደናፈቀን እንዳይቀር ማድረግ የሚገባንን እንመካከር። የሚሉትንና የመሳሰሉትን ነጥቦች ለማንፀባረቅ ሞክሬ ነበር:

ይሁን እንጂ አንዳንድ አንባብያን እኔ ለማለት የፈለኩትን ሃሳብ እኔ በፈለኩት መልኩ የተገነዘቡልኝ አልመሰለኝም። ይህንንም በአስተያየቶቻቸው አንፀባረቀውታል። ውድ አንባብያን እኔ ያልኩት አሁንም የምለው ወደፊትም የምለው የቤተ ክርስቲያን ችግሩም ሆነ መፍትሔው ያለው በእኛው በቤተ ከርስቲያን ልጆች እጅ ላይ ነው። ችግሩን ማስፋትና ማወሳሰብ እንችላለን ማቅለልና ማስወገድም እንችላለን። በእርግጥም እየሰማን እንዳልሰማ ካለፍን፣ የግላችንን ኃላፊነት ላለመወጣት በተለያዩ ምክንያቶች ለመሸፈን ከሞከርን፣ ለችግሮቹ መንሰዔ ናቸው እያልን የተለያዩ አካላት ላይ እጃችንን መቀሰር ካላቆምን ችግሩ ችግርን እየወለደ እና እየባሰ እንደሚሄድ ጥርጥር የለኝም። በአንፃሩ ደግሞ ራሳችንን የችግሩም ሆነ የመፍትሔው አካል ካደረግን፣ ባንድም ሆነ በሌላ የእያንዳንዳችንን ኃላፊነት ራሳችን መወጣት እንደሚገባን አምነን ለተግባራዊነቱም አሁኑኑ እንቅስቃሴ ከጀመርን፣ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ እና ለመጪው ትውልድ ጭምር ካሰብን፣ ስለ ግል ጥቅማችን እና ስማችን ትተን የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም ካስቀደምን፣ የዛሬው የእኛ ድካምና ውጣ ውረድ ሳይሆን የነገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ከታየንና ከታሰበን ችግሩን አናቀለዋለን ብሎም እናስወግደዋለን ብዬ አምናለሁ።

የተከበራችሁ ወንድሞችና እህቶች መቼም ችግሩ እንዲፈታ የማይፈልግና ከዚያም በኋላ የሚኖረውን ጥሩ ጊዜ ለማየት የማይናፍቅ አለ ብዬ አላስብም (በተፈጠረው ቸግር ለጊዜያዊ ኑሯቸው ባንድም በሌላ ተጠቃሚ የሆኑ ከሚመሰላቸው በቀር) እየተጠቀሙ መሆናቸው ጠፍቶኝ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ ግን ይህ ዓይነቱ ጥቅም ለእኔ ሞት ስለሆነ ነው። ታድያ ያንን የምንናፍቀውን ጊዜም እንይ ካልን እንዲሁም በዲ/ን ዳንኤል የተሰነዘሩትንና ሌሎች ተጨማሪ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለመተግበርና ችግሩን እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ለመፍታት ሁለት ዓይነት አካሔዶች አሉ ብዬ አስባለሁ። እነሱም፤

1ኛ. የተናጠል (የግል)

2ኛ. የሕብረት(የጋራ)

እስቲ እነዚህን ለየብቻ እንመልከታቸው

1ኛ. የተናጠል ወይም የግል አካሔድ

ይሕ ዓይነቱ አካሔድ አያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እኛ እና ልዑል እግዚኣብሔር በሚያውቀው የምንወጣበት ነው። እያንዳንዳችን የየራሳችን የሆነ ስጦታ ስላለን እንደየስጦታችንና እንደ አቅማችን የምንቀሳቀስበት ነው። በዚህ ውስጥ ከሚካተቱት መካከል የግል ፀሎት አንዱና ዋንኛው ነው። መቼም በዚህ ላይ ብዙ መነጋገር አስፈላጊ አይመስለኝም ግልፅ ነውና። በወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል የተዘረዘሩትን የመፍተሔ ሀሳቦችም እያንዳነዱን በተናጠል መከወን እንችለለን። ነገር ግን ይህ መንገድ ከባድ ነው። ለምን ቢባል እያንዳንዱ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ነኝ የሚል ሰው አቅሙ በፈቀደ መጠን ብርታትና ትዕግስትን ገንዘቡ አድርጎ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ ቀስቃሽና አስታዋሽ ሳያስፈልገው፣ ከስሜታዊነትና ከልጅነት እርቆ፣ በመንፈሳዊ እልህና ቁጭት ተነሳስቶ ስለ አንዲት ሃይማኖቱ ብቻውን የሚጋደልበት ነው። ስለዚህ በእውነት የቤተ ክርስቲያን ጉዳት ጉዳቴ ነው የምንል ከሆነ ነገ ዛሬ ሳንል በዲ/ን ዳንኤል የተዘረዘሩትን የመፍተሔ ሃሳቦች ደግመን ደጋግመን እናንብባቸው ብንችል ወደ ወረቀት እናትማቸውና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያንዳንዳችን መተግበር እንጀምር።

2ኛ. የሕብረት ወይም የጋራ አካሔድ

ይህኛው አካሔድ ደግሞ 20ዎቹን የዲ/ን ዳንኤልን የመፍትሔ ሃሳቦች አና ሌሎችንም ችግሩን ለመቅረፍና ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉንን ሁሉ በሕብረት የምንፈፅምበት ነው። ይህ ዓይነቱ አካሔድ ደግሞ በባህሪው በአባላት መካከል ሃሳብ መለዋወጥን፣ አንዱ ሌላውን መቀስቅስና ማበረታታትን፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሳይሉና ሳይፎካከሩ በመረዳዳትና በመከባበር ተባብሮ መሥራትን፣ ስለ እምነታችን ከጉዳዩ ባለቤት እህቶች፣ወንድሞች፣ እናቶችና አባቶች ጋር በህብረት የምንጋደልበት ነው።

ግን እንዴት??? እዚህ ጋር ነው ዋናው ጉዳይ። በምን መልኩ ነው ችግሩን ለመፍታት በሕብረት መንቀሳቀስ የምንችለው? እስቲ እኔ የሚታየኝን ልሰንዝር።

ማኅበር እናቋቁም

እንዲሆን ወይም እንዲደረግ የምንሻውን ነገር በጋራ ሆነን ለማድረግ ወይም ለማስደረግ፣ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል ድምፅ ለመፍጠር (ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ)፣ ማሰማት የምንፈልገው ድምፅ በፍፁም እውነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለመወያየትና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ፣ እናለማለን ስንል እንዳናጠፋ አካሔዳችንን ለማሳመር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ … ወዘተ በማኅበር ብንደራጅ ያስኬደናል እላለሁ። በማኅበር መሆናችን በተናጠል በምናካሒደው እንቅስቃሴ ወቅት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ለማለፍ አቅም ይፈጥርልናል።

በዚህ ማኅበር ውስጥ በተቻለ መጠን የተለያዩ አካላትን ለማሳተፍ መሞከር ይጠበቅብናል። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ወቅት ማድረግ የሚገባንንና የማይገባንን አየለዩ የሚያሳዩን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ አባቶች ያስፈልጉናል። በ2ኛ ጴጥ 2፡7(8) ላይ እንደምናነበው “ፃድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ስራቸው ፃድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና …” ይላል ይህ ቃል የሚነግረን ፃድቁ አባት ሎጥ በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ እየተገፋ በዚያች በበደልና በክፋት እግዚአብሔርን ባሳዘነችው ከተማ ሲኖር ከክፋታቸው ሳይተባበር ነፍሱን አስጨንቆ ይኖር እንደነበረ ነው። አሁንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው በሚሰራው የጥፋት ስራ ትብብር ሳይኖራቸው ነፍሳቸውን አስጨንቀው የሚኖሩ አባቶች አሉና እነሱን፣ የቃሉ ሙላት ያላቸው ሰባኪያነ ወንጌል ወንድሞች፣ በተለያየ መንገድ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ሳይሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ አገልጋዮች፣ በሃገር ውስጥም በውጪም የሚኖሩ ምዕመናንና ምዕመናት የሚያሳትፍ ሊሆን ይገባዋል።

መቼም የአንድ ማኅበር ማኅበርነቱ የሚታወቀው የተነሳለትን ዓላማ ለማሳካት ህጋዊ ሆኖ ያለ አንዳች ተፅዕኖ መንቀሳቀስ ሲችል መሆኑ ግልፅ ነው። አጥፍተዋል የምንላቸው ግለሰቦች ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ መቼም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ሔደን ክስ አንመሰርትም እዚሁ ሀገራችንን በማስተዳደር ላይ ለሚገኘው መንግስት ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጀመሪያ ህጋዊ መሆን ይጠበቅብናል። ስለዚህ ይህንን ህጋዊ ዕውቅና ማግኘት ይኖርብናል።

አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የመንግስት ስም ፈፅሞ እንዲነሳ የማትፈልጉ እንዳላችሁ ከአስተያየቶቻችሁ ተመለክቻለሁ። ይሁን እንጂ እናንተ የምትፈልጉትን ዓይነት መንግስት የመመስረት አቅሙም ፍላጎቱም ሰለሌለኝ ባለችኝ ትንሽ አቅም እናንተን ለማሳመን መሞከሩን መርጫለሁ። መንግስት ጣልቃ ይግባ ስል የቤተ ከህነቱን ሰራ እሱ ተረክቦ ይስራ ማለት እኮ አይደለም። ወንጌልንም መንግስት ይስበክልን ማለት አይደለም። እኛ ከመንግስት የምንፈልገው ምንድነው? አንደኛ የቤተ ክርስቲያንን ችግር እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ለመፍታት የምናደርገውን እንቅስቃሴ መንግስት ባንድም በሌላ ሊያስተጓጉልብን አይገባም በህገ መንግስቱ ላይ የተወሰነልን መብት ነውና። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው ችግር የሚፈጥሩትን ግለሰቦች አሳማኝ ማስረጃ እስካቀረብንለት ድረስ እንደማንኛውም ዜጋ ለጥፋታቸው ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል በምንም መልኩ ሽፋን ሊሰጣቸው አይገባም። እንጂ ሌላ ተዓምር ይፍጠርልን አላልንም አንልምም። ይህ ማለት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በደሙ የመሰረታትን ልዑል እግዚአብሔርን ዘንግታ አለማዊ መንግስትን ተደገፈች ወይም ተመረኮዘች አያሰኛትም። ወንጀልን ቦታ አይወስነውም የትም ይሰራ የት ያው ወንጀል ነው። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በሚል ሽፋን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንጀል ሊፈፀም አይገባም። እስከዛሬ ለሰሩት ወንጀል ሰሪዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል። ተጨማሪና ተደራራቢ ጥፋቶችም በእግዚአብሔር ቤት ሰፈፀሙ በዝምታ ማለፉ ይብቃ ነው እያልን ያለነው።

መንግስትም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የተቀባ፣ የተፈወሰ፣ የተባረከና ስመ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚጠራ መሆን አይጠበቅበትም ግዴታውና ኃለፊነቱ ነው። ውድ አንባብያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጥሯል እያልን የምንብሰከሰክለትን ቸግር እኮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው የፈጠሩት። ከድሃይቱ መቀነት በሙዳየ ምፅዋት ውስጥ የገባውን ገንዘብ በማንአለብኝነት እንደፈለጉ የሚመዘብሩትና የሚጫወቱበት በስመ ክርስትና የሚነግዱቱ አይደሉም እንዴ? የክርስቲያንነትን መስፈርት በስባሹን ስጋና ደም ያደረጉት እነማናቸው? በቤተ ክርስቲያን ጡት ያደጉት አይደሉምን?

ታድያ እነዚህን ግለሰቦች አስፈላጊውን መረጃ ይዘን ለህግ እንዲቀርቡ ከማድረግ ውጪ ሌላ ምን ምርጫ አለን??? መቼም ከዘራ ይዘን በየቢሯቸው እየገባን ድብድብ አንጀምርም። ወይም ደግሞ እንደ ባግዳድ ነዋሪዎች አጥፍቶ መጥፋት አናካሒድ።

“ባል ፈልገሽ ጢም ጠልተሽ” የሚሉት አንድ ምሳሌ ትዝ አለኝ። መንግስት የዜጎችን መብት የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት አያወቅን ባንድም በሌላ ስለጠላነው ብቻ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አንፈልግም ወይም ሊወጣ አይችልም ብለን ደምድመናል። በተለያየ የግል ፍላጎታችን ምክንያት ለመንግስት ያለንን አመለካከት እዚህ ላይ ማንፀባረቅ ያለብን አይመስለኝም። ይህ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንጂ በመንግስት ላይ ያለንን የግል አቋማችንን የምናንፀባርቅበት አይደለም።

ለዚህም ነው በክፍል አንድ በሰጠሁት አስተያየት ላይ የመንግስትን ኃላፊነትና አስፈላጊውን መረጃ እስካቀረብንለት ድረስ ተፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት ብዬ አንዳንድ ነጥቦችን አንስቼ የነበረው። ነገር ግን የአንዳንዶቻችሁ አስተያየት የሚያሳየው ልክ እኛ እጅና እግራችንን አጣምረን ቁጭ እንበል የእኛን ኃላፊነት መንግስት ይወጣልን ለማለት የተፈለገ አድርጋችሁ እንደወሰዳችሁት ነው። ይህ ዓይነቱ አመለካከት ፈፅሞ ስህተት ነው።

እንግዲህ የመንግሰትን ድርሻ በተመለከተ ቢያሳምናችሁም ባያሳምናችሁም ይህንን ያህል ካልኳችሁ ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስና ስለ ማኅበሩ መቋቋምና ስለ ተጓዳኝ ጉዳዮች ያላችሁን አስተያየት ሰንዝሩና ወይም ሌላ አማራጭ አምጡና በምንተማመንበት መንገድ በፍጥነት 20ውቹን የዲ/ን ዳንኤልን የመፍትሔ ሃሳቦች ለመተገበር እንንቀሳቀስ።

“ወደ ተራራወው ሸሽተህ አምልጥ” ዘፍ. 19፡18

ቸር ያሰማን።

14 comments:

 1. ወንድሜ እግዚያብሔር ይባርክህ ያስቀመጥከዉ ሀሳብ ምንም የሚወድቅ ነገር የለዉም የመንግስት በዚህ ጉዳይ ዉስጥ የመግባቱ ነገር በጣም አስፈላጊ ነዉ መንግስት ሙስናን ይቃወማል እኛ አንድ ከሆንን እና በቂ መረጃዎችን ከሰበሰብን ህግ ፊት የማይቀርቡበት ምንም ምክንያት የለም፥በሀይማኖት ስም የሚነግዱትም እንደዚሁ፤ይልቅስ እኛ ወረተኞች ስለሆንን አዲስ ነገር ስናገኝ እንዳንረሳዉ እባካችሁ ነገሮቹን ቶሎ መስመር እናስይዛቸዉ፤
  የተክልዬ አምላክ ተዋሕዶን ይጠብቅልን
  እንደበደላችን ሳይሆን እንደቸርነቱ

  ReplyDelete
 2. ዲ/ን ዳንኤል -፡ ምስክርነትህ እውነት ነውና አመሰግንሀለሁ፡፡ሆኖም የምንገኘው በአስጨናቄውና በመጨረሻው ዘመን መሆኑን ስለሚያውቅ በህይወታችን መንገድ ላይ መሰናክል ሆነው የሚገኙትን ሀሳዊ መሲህ እግዚአብሄር አምላክ መልአኩን ልኮ ያስወግዳቸው፡፡አሜን፡፡

  ReplyDelete
 3. በስመ ሥላሴ
  ችግሩን ከመቅረፍ አንጻር ይመለከተኛል ያለ ሁሉ በዚህች ብሎግ የሚያሰፍሯቸው ሀሳቦች ጥሩ ጥሩ ናቸው፡፡ይህ ጥረታችን እግዚአብሔር ሲፈቅድ አንድ ቀን እውን መሆኑ አይቀርምና እንቀጥልበት እላለሁ፡፡ ከላይ የተሰነዘረው ሀሳብ ተፈጻሚነት ካለው በጣም ጥሩ ነው ፡፡ እኔ ግን ያልታየኝ ነገር የቤተክርስቲያኒቱ አመራር አካላት እያሉ ማህበር እናቋቁም ብንል ያለ እነርሱ ፈቃድ እንዴት ሊሆን ይችላል ; እነርሱኑ እንዳናስፈቅድ አብዛኛው ሰው የችግሩ ሰለባ ስለሆነ እሺ እንደማይሉን እሙን ነው፡፡ መንግስትም ከእኛ ይልቅ የሚያውቀው በቤተክርስቲያኗ መዋቅር ያሉትን አካላት ስለሆነ ለማስፈቅድ እንዲህ ቀላል አልመሰለኝም፡፡ እንደ እኔ ከሆነ ግን ምዕመኑ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር እንዲሰበሰቡ ካደረገ በኋላ ከመንግስት ጋር በመተባበር ይህንን ኮሚቴ / ማህበር እንዲፈጠር ማድረግ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚያም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ከችግሩ ነጻ የሆኑ የተለያዩ አካለትን ባማከለ ሁኔታ በማህበሩ እንዲካተቱ ማድረግ፡፡ ለጊዜው ግን ይህንን ስራ ለመጀመር በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በመንግሰት ተሰሚነት ያላቸውን ፡ትጉህ እና ተቆረቋሪ ፤ከችግሩ የጸዱ ፤ቀና አመለካከት አላቸው የሚባሉ ካህናት እና ምዕመናን በማዋቀር ህዝቡን በበላይነት እንዲያስተባብሩ መምረጥ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ ይህ በእራሱ አደረጃጀቱ እና አፈጻጸሙ ምን መምሰል እናዳለበት ብዙ ሀሳብ ማንሸራሸር የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡
  የቤተ ክርስቲያናችን አሰራር ችግር ተፈቶ፤ ዝናዋና ክብሯ ተጠብቆ ፤ለአለም ሁሉ ወንጌልን በማድረስ ልጆቿ አድርጋ ለማየት ያብቃን! ለዚህም ፈጣሪያችን በቸርተቱ ይጠብቀን !
  ኃይለ ሚካኤል ከባህር ዳር

  ReplyDelete
 4. ከደብረ ቁስምቋ
  ስላም ለዚህ ቤት
  በርግጥ ሁለቱም ጽሁፎች ግልጽ ናቸው ነገር ግን አንድ አንድዎቻችን ያቆራኘንው ከማይመስል ነገር ጋር ነው ማለትም ፖለቲካዊ አስተሳሰብና መንፈሳዊ አስተሳሰብ እንደሚለያዩ ማወቅ አለብን ስለዚህ ህጉን ተከትለን መሔድ ያለብን ይመስለኛል ለምሳሌ ሁላችንም እንደምናውቀው በቤተ ክርስትያን ውስጥ ሙስና እየተፈጸመ መሆኑን ግማሹ በወሬ ነው የሚሰማው ሌላው ደግሞ በተግባር ያያል ነገር ግን እግዚኦ ብሎ ያልፋል በርግጥ አዎ እግዚኦ ያሚያስብል ነው ነገር ግን እግዚኦ ተብሎ ብቻ መታለፍ የለበትም ያንን ሙስና የሚቀበለውን ሰው ተከታትሎ በቂ መረጃ ከያዙ በሁዋላ ወደ ህግ መውሰድ የገባል ህግ ደግሞ በቂ መረጃ ከቀረበለት ለዛውም በአሁን ሰአት በህገ ወጡ ላይ የማይፈርድበት ምንም ምክንያት የለም:: ስለዚህ ወንድማችን ያቀረበውን ሃሳብ ከግል በደላችን ጋር ባናያይዘው ጥሩ መሰለኝ {ይሔ የቤተ ክርስትያን ጉዳይ ነው}እባካችሁ በፖለቲካው መስክ የበደልንም የተበደልንም ያሸበርንም የተሸበርንም ትንሹንም ትልቁንም እያነሳን ከቤተክርስትየን ጋር አንቀላቅል::ወንጀለኛን ለህግ ማቅረበና ሃይማኖትን ከፖለቲካጋር ማያያዝ የተለያየ ነው::
  <>ዮሐ15:12
  እግዚአብሔር አምላካችን ለቤተ ክርስትያን ሰላም ያውርድልን::

  ReplyDelete
 5. Dear Haile Gebriel from Arat Kilo.
  Sorry, i couldn't explain in Amharic
  Government intervention should be there with limitation. However, with in government there are many enemies of this church, like protestants and muslims. That may be an oportunity for them to atatck our church.

  ReplyDelete
 6. +++
  ማህበር ይቋቋም በተባለው እስማማለሁ ምክንያቱም ያለዚያ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ይሆናል
  ከተጠቀሱት በተጨማሪ ከእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን በተለይ አ.አ ያሉትን ወክሎ የሚገኝ ምእመናን
  ወይንም የሰበካ ጉባኤ አባላት ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩትን የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች , በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ እንዲሁም የህግ ባለሙያዎችን የሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆችን ቢያካትት ማልካም ነው ፡፡
  ግን እንዴት ሰዎችን እናሰባስብ የሚለው ሌላ ጠያቄ ነው።
  ሀ .አንድ ይህን በሎገ መጠቀም ማለት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ለዚህ ብሎግ ስሙን እና የመገኛ መንገዱን ጨምሮ ማሳወቅ

  ለ. ይህ ብሎግ ለማያዪት በግልም ሆነ በጋራ ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ማሰባሰብ።
  ሐ. ለመንግሰት ከማሳወቀወ በፊት መረጃ መሰብሰብ።

  ReplyDelete
 7. dear h/gebreal

  sile mefeteh hasab yakerebekewen begarawem "committee endet mekenes endemichal lela committee enakakum" yetebalew neger endayimeta min medereg alebet? ye wechiwen ena yewesetun lemasetebaberes? yemiluten endet temeleketewetal?

  egziabher betekerestiyanachinen yitebekat

  "hulachinim le tselot eninesa"

  egziabher yestelegn

  ReplyDelete
 8. Can someone please explain how I can write in Amharic on this blog. I don't really have Amharic software loaded on my PC.

  ReplyDelete
 9. I can't agree enough on what has been said in the past and now my H/Gebrel. It's constractive and suggested well. I personaly would suggest, as far as I know D/N Daniel is neutral on this issue and he may know who could do this task as an individual or as a group. Please give us some names you may thing would barre this task. I promise my self to stand behid the names you keep forward towards this fourm.
  Once again May God bless you for the opportunity to speak on behalf of our mother church.
  May God protect our church.

  ReplyDelete
 10. The solution is to reject all until they reconcile themselves.Those who curse one another cannot reconcile us with God.

  ReplyDelete
 11. በግል ከመንቀሳቀስ ይልቅ በጋራ (በማህበር ) መስራቱን እንደምደግፍ በቀደመው አስተያየቴ ጠቅሻለሁ፡፡ ነገር ግን የማህበር ችግር ያለብን አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም በአላማ ከተለዩት በስተቀር አሁን ባሉት ማህበራት መካከል የጋራ መድረክ በመፍጠር አብሮ መስራት ይሻላል ይመስለኛል፡፡

  ኪዳነማርያም ዘድሬዳዋ

  ReplyDelete
 12. ዲያቆን መሐሪ ገብረማርቆስ

  ወንድማችን ኃይለገብርኤል እንደጠቆሙት ችግሮችን ለመፍታት በቀላሉ የሚታሰበውና አዋጭ መስሎ የሚታየው መንገድ ማኅበር መመሥረት ነው፡፡ ግን ከልምዳችንና ከኑሯችን እንደምናውቀው ቤተክርስቲያናችን በአሁን ጊዜ ያለባት ችግር የማኅበራት አለመገኘት ሳይሆን እዚህ እየተወያየንበት የምንገኘውን መዋቅራዊ ዝለት ከመሠረቱ መፍታትን ግባቸው አድርገው የሚሠሩ ማኅበራት አለመኖር ይመስለኛል (አለመወለድ ወይም መጨንገፍ ብልም የምሳሳት አይመስለኝም- አንዳንድ ተስፋ የተጣለባቸው ነበሩና፡፡)

  ጽዋ ማኅበራት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ሰበካ ጉባኤያት ሁሉ በአንድም በሌላም መንገድ የቤተክርስቲያኗ ልጆች የታቀፉባቸው ማኅበራት አይደሉምን? እኔ ሲገባኝ የአብዛኛው ክርስቲያን ጉድለት በአንድ በኩል ችግሩን አለማወቅ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩን ተላምዶ መኖር ነው፡፡ ችግር ደግሞ ሲለመድ ደግሞ መኖሩም ይረሳል- “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል፡፡” አይደል የአማርኛው ተረትስ የሚለው፡፡ የተረሳ ችግር ግን ችግርነቱ ቀርቶ አያውቅም- እያሰለሠ የሚያመረቅዝ ነቀርሳ ይሆናል እንጂ፡፡

  ወንድማችን ኃይለገብርኤል እንዳሉት ማኅበሩ ተቋቋመ ይባል ማን ተብሎ ይሰየም ይሆን? (መቼም ማኅበረ ጦማሪያን እንደማይሆን እሙን ነው፡፡) በየትኛው የቤተክርስቲያኗ መዋቅርስ ውስጥ ይሆን የሚታቀፈው? ከመንግሥት ዕውቅናውን ሲጠይቅስ ምንድነኝ ብሎ ሊጠይቅ ነው? የፖለቲካ ድርጅት? የበጎ አድራጎት ድርጅት? ቸርች? ምን? በቤተክርስቲያኗ መዋቅር ውስጥ ለመታቀፍ ቢፈልግስ አስተዳደራዊ ዝለቱ የተመቻቸው ሰዎች እንዲህ በቀላሉ በሩን ወለል አድርገው ይቀበላሉ?

  የምቾት ዞናቸውን ላለመልቀቅ እስከመጨረሻው እንደሚሟሟቱ ለመጠርጠር አለመቻል አደገኛ የዋኅነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህ ከእነርሱ ጋር የሚደረገው ትግል ብቻውን ማኅበሩ ሊፈታ ያለመውን ተግባር ከመከወኑ በፊት እጅግ ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ዕውቅና ለማሰጠት በሚደረግ ሩጫ እንዲያባክን ያደርጋል፡፡

  በሌላም በኩል የችግሩ ዐበይት ተጠቃሚዎች ከዕውቅናው በፊት “መናፍቅ! ፖለቲከኛ! የፖለቲካ ዓላማ ያነገበ! ፀረ- መንግሥት!” ወዘተ. የሚል ቀለም በተቀባ መግነዝ ጠቅልለው ከቤተክርስቲያን ውጪ የመወርወር “ታላቅ” ዐቅማቸውን እንደሚጠቀሙ አለማሰብ ጭፍን የዋኅነት ይመስለኛል፡፡ አንዴ ከቤተክርስቲያኗ መዋቅሮች ውስጥ ከተወጣ ደግሞ መመለሱ እጅግ ከባድ ነው(እንደው “ፈጽሞ አይሆንም!” ባንል እንኳ)፡፡ ይህም እንኳን ለነገ የምንመኘው ለውጥ ሊሳካልን ቀርቶ አሁን እያደረግን ያለውን የመነቃቃትና የመወያየት ዕድል እንኳ ማግኘቱን እጅግ ከባድ ሳያደርገው አይቀርም፡፡

  የሚቋቋመው ማኅበር ኅቡዕ ማኅበር ከሆነ ያ ሌላ ነገር ይሆናል፡፡

  እንደሚገባኝ የችግሩ ምንጮች መዋቅሩ እንዳይሠራ ያደረጉት መዋቅሩ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያትም መዋቅሩ በሙሉ ዐቅሙ ከሠራ ለእነርሱ ቦታ እንደሌለው ስለሚያውቁ እንደሆነ አስባለሁ፡፡

  በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ማድረግ ያለብን ሌላ ማኅበር ማቋቋም ሳይሆን በመጀመሪያ እነዚህ ጥቂት የችግሩ ተጠቃሚዎች በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሱት ያለውን ችግር በማሰብ መነቃቃቱን በእያንዳንዳችን ውስጥ መፍጠር የሁላችን የዚህ የጡመራ መድረክ ተሳታፊዎች ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ እናስብ፤ እንጸልይ፤ እንመርምር፡፡

  በመቀጠልም ይህንን መነቃቃት ወደ ሻይ ጠረጴዛችን፣ ወደ ቡና ረከቦቶቻችን፣ ወደ ምሳ ግብዣዎቻችን፣ ወደ ቤተዘመድ ጉባኤዎቻችን እንውሰደው፡፡ እያንዳንዱ ምእመን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የካህናትና የማኅበራት ወይም የጥቂት ስለእግዚአብሔር ደጋግመው ሲናገሩ የሚሰሙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን የእርሱ ጉዳይ እንደሆነ እንዲያስብ፣ እርሱ ካላሰበ ነገ የሥጋ ልጅ እንጂ በመንፈስ እርሱን የመሰለና ከእርሱ የተሻለ ተተኪ ትውልድ ማግኘት እንደማይቻል ሊነገረው ይገባል፡፡ ምን መደረግ እንዳለበት መፍትሔ እንዲሻ ማሳሰብ ይጠበቅብናል (እኛ መፍትሔ ሰጪዎች አይደለንምና)፡፡

  ያኔ ጾታ ምእመናን የታቀፉባቸው የቤተክርስቲኗ መዋቅሮች ከድንዛዜ ይወጣሉ፡፡ ማኅበራታችን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን፣ ሰበካ ጉባኤዎቻችን ይነቃሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዳይ የእያንዳንዳችን ጉዳይ መሆኑን አውቀው ይነሣሉ- እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ችግሮችን እያዩ “አንተው ፍታው!” እያሉ መኖር ሳይሆን ማድረግ የሚጠበቅብንን ማድረግ መሆኑን ይረዳሉ፡፡ አድርጉ የሚባሉትን ብቻ የሚያደርጉ ሳይሆኑ “ለምን?” ብለው የሚጠይቁ፣ አስፈላጊ ከሆነም “ለሰው ከምንታዘዝ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡” ብለው በአጽንዖት የሚመልሱ ይሆኑልናል፡፡

  ያኔ የችግሩ ተጠቃሚዎች ወይ ንስሐ ገብተው ይመለሳሉ፤ አልያም ተንጓለው ይተፋሉ፡፡ ሁሉም ሓላፊነቱ ምን ድረስ እንደሆነ ዐውቆ ይሠራል፡፡ መንግሥትም አጥፊውን ለመቅጣት ይመቸዋል፤ በመንግሥትነቱም ይገደዳል፡፡

  አለበለዚያ የማኅበሩን ችግር (ቤተክርስቲያን ራሷ ማኅበረ ምእመናን ናትና) በሌላ ማኅበር ለመፍታት መሞከር የኮሚቴ መብዛትን ለመቀነስ የተቋቋመው ኮሚቴ ዓይነት ነገር አይሆንም ብላችሁ ነው?

  ReplyDelete
 13. To KaleAb
  Use this wesite to write in Amharic http://freetyping.geezedit.com/
  After you write on this program, use copy/paste procedure.No need of download the program.
  Damay

  ReplyDelete
 14. Hello the blogger, I have posted a comment about biblical meaning and function of church. Why don't you post it.are you sensoring those message that doesn't praise you or that doesn't agree with your idea?

  ReplyDelete