Wednesday, September 29, 2010

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚጀምረው ስንት ሰዓት ላይ ነው?

ዓርብ ለቅዳሜ ምሽት፣ ጳጉሜን አምስት 2002 ዓም ማታ በኢትየጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረውን የአዲስ ዓመት ዋዜማ እያየሁ ነበር፡፡ ከአሜሪካ የገባሁት በዚያው ቀን ነበርና ዕንቅልፌ ሊስተካከልልኝ ስላልቻለ በደንብ ነበር የተከታተልኩት፡፡ እኩለ ሌሊት ሊደርስ ሲል ግን አንድ አሳዛኝ ነገር ተከሰተ፡፡

የማከብራቸው አርቲስቶች ወደ መድረኩ ተሰባስበው ወጡና በዚያች ታሪካዊት ቀን ታሪካዊ ቀን ታሪካዊውን ስሕተት ሠሩት፡፡ እኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ሊሆን ሽርፍራፊ ሰኮንዶች ሲቀሩ «አዲሱ ዓመት ሊገባ ስለሆነ እንቁጠር» አሉና ወደ ኋላ አሥር፣ዘጠኝ፣ ስምንት፣ እያሉ እስከ ዜሮ ቆጠሩ፡፡ ከዚያም ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ አዲሱ ዓመት ገባ ብለው ዐወጁ፡፡

Tuesday, September 28, 2010

መስቀሉ የት ነው ያለው? ክፍል ሁለት

ባለፈው ጽሑፍ ላይ የጌታችንን መስቀል በተመለከተ ጥንታውያን መዛግብት ምን እንደሚሉ በመጠኑ ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ ለዛሬ ደግሞ እነዚህን መዛግብት ከሀገራችን መዛግብት ጋር እናስተያያቸዋለን፡፡

መስቀሉ እንዴት ጠፋ?

የሀገራችን ሊቃውንት እና መዛግብት መስቀሉ እንዴት እንደ ጠፋ የሚተርኩት ታሪክ የጥንታውያኑን መዛግብት የተከተለ ነው፡፡ በመስከረም 16 እና 17 የሚነበበው ስንክሳራችን የጌታችን መስቀል በጎልጎታ በጌታችን መቃብር እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ አይሁድ በመስቀሉ እና በመቃብሩ የሚደረገውን ተአምር አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውንም ያትታል፡፡ እስከ 64 ዓም አይሁድ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ በ64 ዓም አካባቢ ግን አይሁድ ራሳቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ዐመጽ ጀመሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡

አይሁድ መስቀሉን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችንን መቃብር የተቆጣጠሩት እና ክርስቲያኖች እንዳይገቡ ያገዱት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ጎልጎታ የከተማዋ ጥራጊ እንዲደፋበት አዘዙ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት አልነበሩም፡፡ ክርስቲያኖች ግን በጌታችን መቃብር አካባቢ ዋሻዎችን ፈልፍለው ይገለገሉባቸው ነበር፡፡

Thursday, September 23, 2010

መስቀሉ የት ነው ያለው?

በእምነት ታሪክ ውስጥ የታሪክ፣ የአርኬዎሎጂ እና የቅርስ ጥናት ሰዎችን ያስጨነቁ ሁለት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ታቦተ ጽዮን እና ጌታ የተሰቀለበት መስቀል የት ነው ያሉት? የሚሉት ጥያቄዎች፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ አሰሳዎች፣ ቁፋሮዎች፣ መዛግብትን የማመሳከር ሥራዎች፣ አሉ የተባሉ የይዞታ ጥያቄዎችን የመመርመር ፍተሻዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ግን የዓለም ቅርሶች መናኸርያ የሆነችው ኢትዮጵያ ሁለቱንም በተመለከተ ለዓለም የምትገልጣቸው ነገሮች አሏት፡፡


ሰሞኑን በሀገራችን ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል በመከበር ላይ በመሆኑ «ለመሆኑ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል የት ነው ያለው?» የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ያሉ መረጃዎችን እንቃኝ፡፡

የመስቀሉ መጥፋት

Sunday, September 19, 2010

ለጠላት አንድ ሺ፣ ለወዳጅ አንድም

የዓለም የወዳጅነት ቀን ሲከበር አንድ ወዳጄ እንዲህ የሚል ጥቅስ ላከልኝ «ጠላትህ ወዳጅህ ይሆን ዘንድ አንድ ሺ ዕድል ስጠው፤ ወዳጅህ ጠላትህ ይሆን ዘንድ ግን አንድም ዕድል አትስጠው»፡፡ እነሆ ይህ ጥቅስ ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡

እውነት ነው በዚህ ዓለም ላይ ወዳጅ እንደ ማፍራት የከበደ፤ ጠላት እንደማፍራትም የቀለለ ነገር የለም፡፡ እሥራኤልን ያህል ሳኦል፣ ዳዊት እና ሰሎሞን አንድ አድርገው የገዟትን እና ገናና መንግሥት የነበራትን ሀገር ለውድቀት የዳረጋት የሮብዓም ከንቱ ንግግር ነበር፡፡ አያሌ ወዳጆችን ሊያፈራበት የሚችለውን ንግግር ጠላት ማፍርያ አደረገውና የእሥራኤልን ጠላት ከእሥራኤል መካከል አሥነሣባት፡፡

በአባቱ ዘመን የነበረው ቀንበር የተጫናቸው ወገኖቹ መጥተው «አባትህ ያከበደብንን ቀንበር አቅልልን» ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም በአባቱ በሰሎሞን ዘመን የነበሩት አማካሪዎች የነገሩትን ትቶ ከብላቴኖች ጋር ተማከረና «ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔም በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል፤ እኔም በጊንጥ እገርፋችኋለሁ» ብሎ ተናገራቸው፡፡

ይህ ንግግሩ እሥራልን «ሰማርያ» እና «ይሁዳ» ብሎ ለሁለት ከፈላት፡፡ ከዚያ በኋላ የደረሰው የእሥራኤል ውድቀትም በመከፋፈሏ ምክንያት የተከሰተ ነበር፡፡

Wednesday, September 15, 2010

ቺፋን ለማ

የዛሬን አያርገውና ቻይናዎች ከ30 ዓመት በፊት ችግርን በታሪክ ብቻ ሳይሆን በአካልም ያውቁት ነበር፡፡ አለንጋውን ይዞ ገርፏቸዋል፤ ጥርሱን አውጥቶ ነክሷቸዋል፤ ጥፍሩን አርዝሞ ቧጭሯቸዋል፡፡ ሀገራቸው በታሪካዊ ቅርሶቿ እና በጥንታዊው ሥልጣኔዋ ካልሆነ በቀር ከድህነቷ ውጭ ሌላ መታወቂያ አልነበራትም፡፡

መቼም ከሠሩ የማይገኝ፣ ከለፉ የማይሰናኝ የለምና ጥረው ግረው በወዛቸው ሀገራቸውንም ስማቸውንም ቀየሩት፡፡ እነሆ ቻይናም በዓለም ሁለተኛዋ የኢኮኖሚ ኃያል ሀገር ለመሆን በቃች፡፡ ቻይና በኦሎምፒክ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ወርቅ መሰብሰብ ጀመረች፡፡

Tuesday, September 14, 2010

አባ ሐና

በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው የጠፋ ሁለት ገብረ ሐናዎች አሉ፡፡ አለቃ ገብረ ሐና እና አባ ገብረ ሐና ጂማ፡፡ ሕዝቡ ሁለቱንም ባለ ውለታዎች በተሳሳተ መንገድ ተረዳቸው፣ ታሪካቸውንም በተሳሳተ መንገድ አስተላለፈው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሼክስፔሩን ሻይሎክ ያህል ገብጋባ ናቸው እየተባሉ የሚጠሩት አባ ሐና ጂማ ማን ናቸው? ለምንስ ገብጋባ ሰው «አባ ሐና» ተብሎ ሊጠራ ቻለ? አብራችሁ ቆዩ፡፡

እስከ 1953 ድረስ ከ30 ዓመታት በላይ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስለነበሩት ስለ አባ ሐና ጂማ በተመለከተ በቂ የሆነ የተጻፈ መረጃ የለም፡፡ በአፈ ታሪክ ግን ገብጋባ ናቸው እየተባለ ይነገራል፡፡ የዚህ ብሎግ አዘጋጅ ለማሰባሰብ የሞከረው ታሪካቸው ግን ይህን የሚያስተባብል ሆኖ አግኝቶታል፡፡

Tuesday, September 7, 2010

የሴቶች አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን


የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጀመርያ በፖርቹጋሎች፣ በኋላም በእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች በደረሰባት መከራ ዐቅሟ ተዳከመ፡፡ መንበረ ­ፓትርያርኩ የነበረበት ሶርያም በደረሰበት ጫና ምክንያት ሕንድን ለመርዳት አልቻለም፡፡
1806 እኤአ ወደ ፕሮቴስታንቶች ማሠልጠኛ እየገቡ በተማሩ አገልጋዮች ምክንያት «ቤተ ክርስቲያን በወንጌል አልተመራችም´ የሚል ንቅናቄ ተጀመረ፡፡ ቀጥሎም «ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋል´ የሚል እንቅስቃሴ ተቀጣጠለ፡፡ የተሐድሶ ኮሚቴ የሚባልም ተቋቁሞ ምልጃ ቅዱሳን፣ በዓለ ቅዱሳን፣ ነገረ ማርያም፣ ክብረ ሥዕል፣ ቅዳሴ፣ ጾም እና መጻሕፍተ ቅዱሳን እንዲቀሩ ወሰነ፡፡

Friday, September 3, 2010

ግመሎቹም ይሄዳሉ ውሾቹም ይጮኻሉ

ሟቹ የ «እንደ ቸርነትህ´ መዝሙር ደራሲ ዶክተር ኢሳይያስ ዓለሜ እንዲህ ይላሉ፡-

አንድ አባት አህያውን እየነዳ ከልጁ ጋር መንገድ ጀመረ፡፡ እልፍ እንዳለ ሰዎች ተመለከቱትና «ምን ዓይነት ሞኞች ናቸው፤ እንዴት አህያ እያለ በእግራቸው ይሄዳሉ´ በማለት ተቿቸው፡፡ አባትም ትችቱን ሲሰማ ሀሳቡን ቀየረ፡፡ ሁለቱም አህያዋ ላይ ወጡና መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደሄዱ ሌሎች ሰዎች አዩዋቸውና «እንዴት ያሉ ጨካኞች ናቸው፤ እንዴት አንድ አህያ ለሁለት ይጋልባሉ´ ብለው ራሳቸውን ነቅንቀውባቸው ጥለዋቸው ሄዱ፡፡

አባትዬውም ከአህያዋ ላይ ወረደ፡፡ እርሱ ከኋላ አህያዋን እየነዳ ልጁን በአህያዋ ጭኖ ጉዞውን ተያያዘው፡፡ የተወሰነ መንገድ ከተጓዘ በኋላም ሌሎች መንገደኞችን አገኘ፡፡ እነዚያም መንገደኞች አባት እና ልጁን አዩና «አይ ስምንተኛው ሺ፤ አያሳየን የለ፤ ልጁ በአህያ ተቀምጦ ሽማግሌ አባቱን በእግሩ ያስኬደዋል፡፡ አበስኩ ገበርኩ´ ሲሉ ሰማ፡፡

Thursday, September 2, 2010

የእኔ እይታ


ኃይለ ገብርኤል ከአራት ኪሎ

ውድ አንባብያን እንዴት ሰነበታችሁ? ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን።

እንደምታስታውሱት በክፍል አንድ ባቀረብኩት እይታዬ «መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ማለት ምን ማለት ነው?» በሚል ርዕስ በአነስተኛዋ አዕምሮዬ የተመላለሰውን ሀሳብ ሰንዝሬ ነበር። ከዚያም የኔን ሃሳብ ተከትሎ የተፃፉትን አስተያየቶች አንድ ባንድ ተመለከተኳቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከተኛል ብላችሁ የየራሳችሁን አመለካከት የሰጣችሁን ወንድሞች እና እህቶች ከልብ አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ያክብርልኝ።