Tuesday, August 31, 2010

ችግር ነን መፍትሔ ?

ሁለት መኪኖችን ብቻ አጨናንቃ የምታሳልፍ መንገድ ነበረች፡፡ ሁለቱ መኪኖች ሲተላለፉ ጎንና ጎናቸው ሊነካካ ለጥቂት ብቻ ነው የሚያመልጡት፡፡ ነገር ግን ሾፌሮቹ ሁሉ ለምደውታልና በቀላሉ ፈገግ እያሉ ይተላለፋሉ፡፡

አንድ ቀን አንድ ለምድር ለሰማይ የከበደ ወፍራም የትራፊክ ፖሊስ መሐል መንገድ ላይ ቆሞ በግራ እና በቀኝ የሚተላለፉትን ተሽከርካሪዎች «እለፉ እለፉ» ይላል፡፡ መኪኖቹ መተላለፍ ስላልቻሉ ከሚሄደው የሚቆመው በዛ፡፡ በተለይማ ትልልቆቹ የጭነት መኪኖች መተላለፍ አልቻሉም፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ ግራ ገባው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም እንኳን መንገዱ ጠባብ ቢሆንም እንደዚያ ቀን ያለ መጨናነቅ ግን ታይቶ አይታወቅም፡፡ መኪኖቹ ቀስ ይሉ ይሆናል እንጂ አይቆሙም፡፡

«ዛሬ ምን ተፈጠረ፣ ምን ዓይነት ሾፌሮች ናቸው ደግሞ ዛሬ የመጡት፣ ምን ዓይነት የተረገመ ቀን ነው» እያለ ያማርራል፡፡ በሾፌሮቹ እና በመኪኖቹም ላይ ይቆጣል፡፡ አልቻለም እንጂ እየሳበ ሊያሳልፋቸውም ይፈልጋል፡፡ «የኔ አባት በአንድ እጁ መቶ መኪና ያቆማል» ብላ አንዲት ሕፃን ልጅ ለጓደኞቿ ነገረቻቸው አሉ፡፡ «እንዴ ምን ዓይነት ስፖርተኛ ቢሆን ነው?» ብለው ቢጠይቋት «አይ ስፖርተኛ አይደለም የትራፊክ ፖሊስ ነው» አለች እየተባለ የሚነገረው ለርሱ ነው እያሉ ይሳሳቃሉ፡፡

የትራፊክ ፖሊሱ የትራፊክ መጨናነቁ የመጣበት ምክንያት አልተገለጠለትም፡፡ ምንም እንኳን መንገዱ አስቸጋሪ፣ መሠራት ሲገባው ሳይሠራ የኖረ፣ እንኳን ሁለት መኪኖችን አንድን መኪና በደንብ የማያሳልፍ ቢሆንም የዛሬው መጨናነቅ ግን ለየት ያለበት ምክንያት ግን አልተገለጠለትም፡፡

እየቆየ መናደድ እና ክፉ ቃል መናገር ጀመረ፡፡ ሾፌሮቹን ጮኸባቸው «ዛሬ ምንድን ነው የኾናችሁት?» እያለ አፈጠጠባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሾፌር በመስኮቱ ብቅ ብሎ «ወንድሜ አንዱ ችግርኮ አንተው ነህ» አለው፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ ከጠዋት ጀምሮ የለፋው ድካሙ ትዝ አለውና «እንዴት ይህንን ሁሉ ስደክም እያየህ ችግሩ አንተም ነህ ትለኛለህ?» አለው፡፡ ሾፌሩም፡፡ «በዚህ በጠባብ መንገድ ተራራ የምታህል ሰውዬ ስትጨመርበት በምን እንለፍ፡፡ አንተኮ መፍትሔ የሰጠህ መስሎሃል እንጂ ችግር እያበባስክ ነው፡፡ እስኪ ከመንገዱ ወጣ በልና የሚሆነውን እየው» አለው፡፡

የትራፊክ ፖሊሱ ለተወሰነ ጊዜ ሲያቅማማ ከቆየ በኋላ ከመንገዱ መሐል ወጣ፡፡ ያን ጊዜ ሲጨናነቁ የነበሩት መኪኖች እንደ ቀድሟቸው መተላለፍ ጀመሩ፡፡ ምንም እንኳን የመንገዱ ችግር እንዳለ ቢሆንም የቆሙት መኪኖች ግን መንቀሳቀስ ቻሉ፡፡

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ የቆምን ሰዎችም ይህንን ጥያቄ መጠየቅ አለብን፡፡ እኛ ለቤተ ክርስቲያን ችግሮች መፍትሔ አመጣን ወይስ እኛው ራሳችን ችግሮች ሆንን?

ኢትዮጵያውያን አበው ጵጵስና አይሾሙ በሚል በኋላ የመጣ ሕግ ምክንያት 117 ጳጳሳትን ከግብጽ አመጣን፡፡ ቋንቋችንን አያውቁም፣ ከሀገሪቱ ስፋት አንፃርም በቂ አይደሉም፣ ደግሞስ ኢትዮጵያ ከማን አንሳ ነው ሰዎቿ ብቁ አይደለም የሚባሉት? ብለን ከግብጻውያን ጋር ተከራክረን ጵጵናን አመጣን ፡፡

ይህንን ለማየት ብዙ አበው ወደዱ ግን አላዩም፣ የኛ ዓይኖች ግን ንዑዳን ክቡራን ናቸው፤ ኢትዮጵያን አበው ኢትዮጵያውያንን ሲሾሙ፤ ሕዝቡም በየአካባቢው ጳጳሳትን ሲያገኝ ተመልክተዋልና፡፡

ግን ግብፃውያን ይሾሙበት ከነበረው ዘመን ምን ያህል ለውጥ አመጣን? ምን ያህል ስብከተ ወንጌልን አሰፋፋን? ምን ያህል በየገጠሩ ደረስን? ምን ያህል አዳዲስ ሕዝቦችን ለወንጌል ጠራን? ምን ያህሉ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተምረው፣ አምነው፣ ተጠምቀው፣ ተክነው፣ ጰጵሰው ለማየት በቃን?

የክህነት እና የምንኩስና አሰጣጡ ከግብፃውያን ዘመን ይልቅ የተሻለ ሆነ? የራሳችን ሲኖዶስ በስንት የቀኖና ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ወሰነ? ስንት ያረፉ ቅዱሳን በሲኖዶሳችን «ቅዱስ» ተብለው ተወሰነላቸው፡፡ መጻሕፍት ተቆጥረው ተሰፍረው በሲኖዶሱ ጸደቁጥ ዛሬ የራሳችን ሲኖዶስ እያለን «ዓሣ ይበላል አይበላም? ስቅለት በማርያም ዕለት ሲውል ይሰገዳል አይሰገድም» የሚሉት እንኳን ውሳኔ አጥተው እያጨቃጨቁን አይደለም»

የቤተ ክህነቱ አሠራር የሀገር ልጆች ሲይዙት ምን ያህል ተቀላጠፈ» ግብጽ ድረስ ከመሄድ አዲስ አበባ ድረስ መምጣት ቀላል ሆነ» ለግብጻውያን ይገበር የነበረው ወርቅ እና ብር ቀርቶልናልን» የጵጵስናው መዓርግስ ከግብጻውያኑ ዘመን ይልቅ ዛሬ ይበልጥ በሕዝቡ ዘንድ ተከበረን»

የጵጵስና ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ችግር ሆነ ወይስ መፍትሔ»

ወንጌል በሚገባ አልተሰበከም፣ የጥንቱ አካሄድ አያስኬድም፣ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ መንገድ ሕዝቡን ማስተማር አለብን ብለን አያሌ «ሰባክያን» ተነሣን፡፡ ነጠላም፣ ጋቢም፣ ቀሚስም፣ ወይባም፣ ካፖርትም ደርበን በየመድረኩ ቆምን፡፡ ከመሐል ከተማ እስከ ዳር ሀገር፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ ዞርን፡፡ ሕዝቡም እሰይ ሰባክያን አገኘን፣ ቃለ እግዚአብሔርን ተማርን፣ ሃይማኖታችንንም ዐወቅን ብሎ ደስ አለው፡፡

ለመሆኑ ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕዝቡ ቆራቢ ሆነ? በመናፍቃን መወሰዱ ቀረ? ባዕድ አምልኮ ቀረ? ገባው ወይስ ተደናገረ? ቲፎዞ ነው ወይስ ደቀ መዝሙር ያፈራነው? ለመሆኑ በኛ ዘመን ስንቶቹ ዐፄ ካሌቦች ሥልጣናቸውን ትተው መነኑ? ስንቶቹ አቡነ ሳሙኤሎች ተነሥተው በአንበሳ እየሄዱ አስተማሩ? ስንቶቹ ክፍለ ዮሐንሶች በዕውቀት ከበሰሉ በኋላ መነኑ? ስንቶቹ ላሊበላዎች አዲስ ተአምር ሠሩ? ስንት እግዚእ ኃረያ እና ጸጋ ዘአብ ተገኙ? ምንድን ነው ያፈራነው ፍሬ?

እኛ ባልነበርን ጊዜ ዘንዶ ይረግጡ፣ አንበሳ ይረግጡ፣ በደመና ይወጡ የነበሩት ቅዱሳን በስብከተ ወንጌሉ ዘመን የት ሄዱ?

ሕዝቡ ጥቅስ ዐወቀ፤ ዐውቆ ግን ምን አደረገ? ማይክራፎኑ አደገ፣ የስስብከቱ መድረክ ጨመረ፣ የሰባኪው ቀሚስ ተለወጠ፣ የሰባኪው የኑሮ ሁኔታ ተለወጠ፣ ትምህርቱ ከብራና ወደ ዲቪዲ ተሻሻለ፣ ከዶግማ ትምህርት ወደ ቀልዳ ቀልድ ተቀየረ፣ ሰውን ከማዳን ሰውን ወደ ማስደሰት ተሸጋገረ፣ የተማሩ ሊቃውንት ያልተማረውን ሰው ማስተ ማራቸው ቀርቶ ያልተማርን ሰባክያን ያልተማረውን ሰው ማስተማር ጀመርን፡፡

የማይጾም የሚጾመውን፣ የማይጸልይ የሚጸልየውን፣ የማያስቀድስ የሚያስቀድሰውን ወደ ሚያስተምርበት ዘመን ደረስን፤ ሕዝቡን ከቤተ ክርስቲያን ወደ አዳራሽ፣ ገድል እና ተአምር ከመስማት ቀልድ እና ጨዋታ ወደመስማት አሸጋገርነው፡፡ እኛ ባልነበርንበት ዘመን ምንም ያልሆነ ሕዝብ ሰባክያን በዙ በሚባልበት ዘመን በአሥር ዓመት ውስጥ 10% ቀነሰ፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች አናፈራለን ብለን የእገሌ ተከታይ አፍርተን አረፍነው፤ ከቤተ ክርስቲያኑ ቁጥር ይልቅ በኛ ዘመን ጫት ቤቱ በለጠ፡፡

ታድያ እኛ አሁን ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ችግር ነን ወይስ መፍትሔ?

«ነይ ነይ እምዬ ማርያም» እየተባለ የተዘመረው መዝሙር አይበቃም ብለን ተነሣን፡፡ መናፍቃን ሕዝቡን በመዝሙር ከሚወስዱት በመዝሙር እናስቀረው ተባለ፡፡ ዘማርያን መጡ፣ የብስ ረገጡ፡፡ መዝሙር አወጡ፡፡ ካሴት አስቀረጡ፡፡ በየሦስት ቀኑ አንድ የመዝሙር ካሴት እስከመውጣት ደረሰ፡፡ መዝሙር ከጠፋበት ዘመን ተነሥተን መዝሙር የበዛበት ዘመን ላይ ደረስን፡፡ ቤቱ፣ ሻሂ ቤቱ፣ ታክሲው፣ የቤት መኪናው፣ ጫት ቤቱ ሁሉ መዝሙር በመዝሙር ሆነ፡፡

ሕዝቡም በቋንቋችን፣ የሚገባን መዝሙር አገኘን ብሎ ደስ አለው፡፡ ዘማርያኑም «በምስጋና ምድሪቱን ከደንናት» ብለው ተኩራሩ፡፡

ለመሆኑ የያሬድ ዜማ ይበልጥ ታወቀ ወይስ ጠፋ? በመዝሙር በኩል መናፍቃንን ተከላከልን ወይስ አስገባን? ድምፃዊው በዛ ወይስ ዘማሪው? መዝሙር አገልግሎት ሆነ ወይስ ሥራ? ዝማሬ ጽደቅ ሆነ ወይስ ሞያ? ሕዝቡን ከዘፈን አመጣነው ወይስ ከቅዳሴ አስወጣነው? የዘማርያኑ ኑሮ ነው ወይስ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ነው የተለወጠው? ሕዝቡ መንፈሳዊ መዝሙር ነው የሚገዛው ወይስ በእናቱ ዘፈን በአባቱ መዝሙር የሆነ? ሕዝቡን ወደ ጸጥታ ወደብ ወሰድነው ወይስ አጨቃጨቅነው? አስማማነው ወይስ አለያየነው? የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስፋፋን ወይስ የራሳችንን አመለካከት? ታድያ እኛ ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ችግር ነን ወይስ መፍትሔ?

ነዳያንን ለማብላት፣ ገዳማትን ለመጎብኘት፣ ገዳማትን ለመርዳት፣ጽዋ ለመጠጣት፣ ስብከተ ወንጌል ለማስፋት፣ የሞያ እገዛ ለማድረግ፣ ወዘተ ተብሎ ማኅበራት እንደ እንጉዳይ ወጡ፡፡ ሕፃኑ፣ ወጣቱ፣ ሽማግሌው፣ ወንዱ፣ ሴቱ ማኅበርተኛ ሆነ፡፡ አንድ አልበቃ ብሎ አንድ ሰው ሁለት ሦስት ማኅበር ገባ፡፡

ቤተ ክህነቱ በሚገባ አልሠራም፣ ገዳማት አድባራቱ ተጎድተዋል፣ መዘምራን ተለያይተዋል፣ ሰባክያን ተራርቀዋል፣ እየተባለ የማኅበር ዓይነት መጣ፡፡ ሌላው ቀርቶ በየበኣታቸው ይጸልያሉ የሚባሉት ባሕታውያንም ማኅበር አቋቁመናል አሉ፡፡ በሰማይ የሚበሩ፣ በምድር የሚሽከረከሩ፣ በባሕር የሚኖሩ ሁሉ ማኅበር መሠረቱ፡፡ የተማሩ፣ ያልተማሩ፣ ለመማር ያላሰቡ ማኅበር ኖራቸው፡፡

ቤተ ክህነቱ ተረሳ፡፡ ሁሉም በየራሱ መሮጥ ጀመረ፡፡ ዋናው ሞተር እንዲሠራ እናደርጋለን ብለው የተቋቋሙ ማኅበራት ለራሳቸው ሞተር ሆኑ፡፡ ቤተ ክህነትም ሳያውቃቸው፣ ቤተ ክህነቱንም ሳያውቁት ቀጠሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዋናው ችግር አይመለከተንም ብለው ማሉ፡፡ ዕንቅርቱን ትተው ንቅሳቱ ላይ አተኮሩ፡፡ ገብተው ከመሥራት ይልቅ ወጥተው መተቸትን መረጡ፡፡

እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉም በየራሳቸው ነው የሚጓዙት፡፡ ለመተባበር፣ ለመነጋገር፣ አይፈልጉም፤ አያስቡምም፡፡ በአንድ መንገድ እየተጓዙ ይገፋፋሉ፡፡ አንድ ቦታ እየሠሩ፣ ይነጣጠቃሉ፡፡ ብዙዎቹ ማኅተም እንጂ ራእይ የላቸውም፡፡ አባል እንጂ ዓላማ ይጎድላቸዋል፡፡ የትኛውን ገዳም እንደሚረዱ እንጂ የትኛውን ችግር እንደሚፈቱ አያውቁም፡፡

ሕዝቡ እነርሱን ተስፋ አድርጎ እንዲቀመጥ አደረጉት፡፡ ለጥያቄዎች መልስ፣ ለችግሮች መፍትሔ፣ ለጨለማው ብርሃን ከእነርሱ ይጠብቃል፡፡ እነርሱ ደግሞ «ሀ- ራስክን አድን» ብለው በራሳቸው አጀንዳ ተጠምደዋል፡፡ «ቤተ ክርስቲያናችን» ማለት ትተው «ማኅበራችን» ማለት ጀምረዋል፡፡ «የቤተ ክርስ ቲያናችን ልጅ» መባሉ ቀርቶ «የማኅበራችን ልጅ» ሆኗል ቋንቋቸው፡፡

ቤተ ክህነቱን ያስተካክላሉ ሲባሉ እነርሱ ራሳቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቤተ ክህነቶች ሆነዋል፡፡ አሠራርን ያስተካክላሉ ሲባሉ እነርሱ ራሳቸው በተወሳሰበ፣ ግልጽነት በጎደለው እና ኋላ ቀር በሆነ አሠራር ተተብትበዋል፡፡ የገንዘብ አያያዛቸው፣ የርዳታ አሰጣጣቸው፣ የአባላት አመዘጋገባቸው፣ የሪፖርት አቀራረባቸው፣ የፋይል አያያዛቸው፣ የዶክመንት አደረጃጀታቸው፣ የስብሰባ አካሄዳቸው ከቤተ ክህነቱ የባሰ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተገላገሉትን ቢሮክራሲ እነርሱ ወሰዱት፡፡ ለጉባኤ እና ለድግስ ብሎም ሞቅታ ላለበት ተግባር እንጂ ለአገልግሎት የሰነፉ አባላት መናኸርያ እየሆኑ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ፈተና ማኅበራት ካልነበሩበት ዘመን ይልቅ በበዙበት ዘመን ብሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን ቦታ የያዙት በማኅበራት ዘመን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሐውልት መቆም የጀመረው፣ የፎቶ ፖስተር በዐውደ ምሕረት የተሰቀለው፤ የቤተ ክርስቲያን ያልሆነ ትምህርት በዐውደ ምሕረት መሰጠት የጀመረው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ተዳክሞ ግለሰቦች ቦታውን መያዝ የጀመሩት በማኅበራት ዘመን ነው፡፡

አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ

ከንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ

አንድ ሰው የችግሩም የመፍትሔውም አካል መሆን አይችልም፡፡ መጀመርያ የችግሩ አካል ከመሆን መላቀቅ መቻል አለበት፡፡ አንድ ሐኪም ለአንድ በሽተኛ መድኃኒት የሚያዝዘው እንዲያድነው ወይንም እነዲያሽለው እንጂ እንዲገድለው መሆን የለበትም፡፡ ቀዶ ጥገና ያደረገ ሐኪም ቀጥሎ ኢንፌክሽን እንዳይከተል መከላከልም አለበት፡፡

በደርግ ዘመን ኮሚቴ በዝቷል ይቀነስ ሲባል ኮሚቴ የሚቀንስ ሌላ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወሰነ እየተባለ የሚተረተው ቀልድ ቀልድ ብቻ አይደለም፡፡ የተሰጠው መፍትሔ ችግሩን የሚጨምር እንጂ የሚፈታ አለመሆኑን የሚያሳይም ነው፡፡

አሁንም የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመፍታት ተብለው የመጡ መፍትሔዎች እና የተቋቋሙ አካላት በራሳቸው መታየት አለባቸው፡፡ በርግጥ እነዚህ መንገዶች እና አካላት ችግር ጨምረዋል ወይስ መፍትሔ አምጥተዋል? እነርሱ ራሳቸውም ራሳቸውን ማየት አለባቸው፡፡ ምንድን ነው ያመጣነው ለውጥ? ካለመ ኖራችን መኖራችን ምን ይጠቅማል? የቆምነው በትክክለኛው መንገድ ላይ ነውን? ብለን መጠየቅ አለ ብን፡፡ እስኪ 2003 ዓም ከመምጣቱ ወይንም ከማለፉ በፊት ከላይ የተጠቀስነው አካላት ራሳችንን እንመርምር፤ በተለይም አመራሮቹ ወይምን ዋና ዋናዎቹ አሁን የምንሄድበትን መንገድ ከወቅቱ ችግሮች እና ተግዳሮቶች አንፃር እንመዝነው፤ ከዚያም ችግር ሳይሆን መፍትሔ የሚያደርገንን አቅጣጫ እንተልም፡፡ ያለበለዚያ ግን ምንን ምን ቢመራው ሁለቱም ወደ ገደል ይሄዳሉ የተባለው ይፈጸምብናል፡፡


30 comments:

 1. Dear brother,I've nothing to say; God bless YOU." GORO YALEW YISMA!"

  ReplyDelete
 2. +++

  የእግዚአብሔር ቃል ስራውን ሳይሰራ አይመለስምና በተዳጋጋሚ ተግሳጽን መስማት ለማስተዋል ይረዳልና ጽሑፎችህን እወዳቸዋለሁ። አንድ ያልገባኝና ሰሞኑን በተለያዩ አንደበቶች መስማት የጀመርኩት የጵጵስናን ሹመትና መንበሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንደችግር የማዬት ወይንም «የችግራችን መንስዔ ይሆንን?» ብሎ የመጠራጠሩ ጉዳይ ግን አልገባህ እያለኝ ነው። መንበረ ተክለሃይማኖትን እንደ መንበረ ማርቆስ ሁሉ እንደ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ካለማዬት ነውን? ወይንስ ምንድን ነው? በእርግጥ አሁን ጥልቅ ችግር ውስጥ ስለሆንን «ምን ከተለወጠ ወዲህ ነው እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ የገባነው? » ብሎ ለማጥናት መሞከሩ ጉዳቱ ባይታዬኝም ይህ ነገር በተደጋጋሚ ማንሳቱ በተለይ ደግሞ ብዙ አድማጭ ባላችሁና «እገሌ ተናገረ እግዜር ተናገረ» ብሎ ልቡን ሰጥቶና «የቤተ ክርስቲያን ድምጽ» ነው ብሎ የሚሰማ ብዙ ተማሪ ባላችሁ መምህራን ሲሆን ሃሳቡን እናንተ «ኢንዶርስ» እንዳደረጋችሁት ስለሚታይ ብታስቡበት መልካም ይመስለኛል። ለእኔ ግን ከእነ እሾኹዋ በእጃችን ያለችዋን ጽጌረዳ ትሻለኛለች! ዞር ብዬ አይቼም ልጠራጠራት ድፍረቱና ዝግጁነቱ የለኝም።

  ጵጵስናው በግብጻዊያን እጅ እንደ ዳረጎት እይተጣለለን ቢቀጥል ኖሮ ይህ ችግር ላለመፈጠሩ ምን ማስረጃና ማስተማመኛ አለን?

  ሰንደቅ አላማ

  ReplyDelete
 3. ዳኒ ችግሮቹን በሚገባ አስቀምጠህልናል በዚሁ ልዩ ሁኔታ መፍትሄዎችን እባክህ እስኪ
  ግን በሚገርም ሁኔታ ችግሮቹን እንዳስተውል አድርገሀኛል 10x
  ሊ.ስ.አዩ

  ReplyDelete
 4. Hi Dn. Daniel, I appreciate your effort. It doesn't make sense for the creators of the problems. I think they try to find a way to chase you rather than learning from their mistakes. Don't worry GOD will chase them back because they are against him. However, it doesn't mean that I am free from accountability. The message helped me to investigate myself.How much is my contribution to these mistakes.
  GOD bless you.
  Mesfin Agegnehu

  ReplyDelete
 5. We are for the most part, contributing to the problem and being the problem itself. We like to talk a lot and listen a little bit. We are tifozo for the most part. We just like to see our own view and nothing else. May Amlak help us understand our short comings amen.

  ReplyDelete
 6. ከደብረ ቁስቋም
  ዲ.ዳንኤል ጽሁፉ በጣም ጥሩ ነው::
  ሁላችንንም እራሳችንን እንድንመረምር የሚያደርግ ነው በመጀመሪያ አንድ ሰው ከራሱ ሲታረቅ ነው ሰውን ይቅር ለእግዚአብሔር ሊል የሚችለው ከዛ ባሻገር ይህንን የሚያነቡ የቤተ ክህነት ሰዎች ጥሩ ትምህርት ይቀስሙበታል ብዬ አስባለሁ ::
  እግዚአብሔር ልቦናችንን ያብራልን.
  ድንግል የቤተ ክርስትያንን ትንሳኤዋን ታምጣልን.

  ReplyDelete
 7. kale Hiwot yasemah! yemilew tiliku mirikate new. Anbibe erasen melewet kechaliku ketesatifo yibeltalina zim biye be adinakot lilifew.Eme amilak TItebikih Dn.Dani

  ReplyDelete
 8. Qale hiwoten yasemalen

  yalekew hulu menm yalehone aydelem tekekel new awo goro yalew ysema

  gen gen kene yemitebekew mendenew ye haymanote feker aleg gen ene men maderg yemechelew aleg kene men yetebekal ? eski le tadamiwocheh men maderg endalebn ke manebbeb yelefe ebakeh tekumen
  YE KEDUSAN AMELAK TSEGAWEN YABEZALH Amen

  ReplyDelete
 9. +++
  በስመ ሥላሴ ትቀጠቅጥ ከይሴ

  ዳ/ን ዳንኤል በመሰረት ሃሳብህ የምስማማ ቢሆንም የማይጋፉትን ባላንጋራ በጥበብ ማለፍ ደግሞ የቅዱሳን አባቶቻችን ጥበብ ነበረ:: እዉነተኛ የቤተ/ያን ልጆች ሃሳብህን ይጋሩታል ነገር ግን ከመሞት መሰንበት ይሻለኛል ብዪ ወፍጮ እፈጫለሁ ........ ይባላ የለ:: አሁን ያሉት ማህበራት የሚችሉትን ባይሰሩ ኑሮ አሁን ከአለንበት የባሰ ችግር ቤተ/ያን ይገጥማት ነበር በተለይ ምዕመናን:: ዳኔ የተጋፈጡ አባቶች እኮ ከአገልግሎታቸዉ ታግደዉ በግዞት ሁነዉ ያለች ዘመናቸዉን እንኳ ሳያገለግሉ አልፈዋል:: አንዳንዶቹም አባቶች እንደምናየዉ ነዉ እየተቃጠሉ ያለእድሜያቸ እየሄዱነዉ:: ስለዚህ እንጹም እንጸልይ እግዚአብሔር በጊዜዉ ሁሉን ያከናዉናልና:: አንተም ከአገልግሎትህ ሌሎችም ማህበራት ከአገልግሎታቸዉ ሳይታጎል ባለችን አገልግሎት ተገተን የእግዚአብሔርን ቀን እንጠብቅ የሚል ሃሳብ አለኝ:: ሌላ ደግሞ እሳቱን ለማጥፋት በአንደየ እሳቱ ዉስጥ ከመግባታችን በፊት እሳት ፈጥረዉ እሳቱን የሚያቀጣጥሉትን በተንሽ በትንሹ ማስቀረት ይሻላል የሚል ተሞክሮ አለኝ:: ዳ/ን ዳንኤል በዚህ ዘመን ሆነን የወርቃማዉን ዘመን እናገኛለን ማለት የሚቻል አይሆንም በወንጌሉ እንዳለዉ በመጨረሻዉ ዘመን ላይ ነን እና::

  ረዴተ እግዚአብሔር አይለየን::
  ከዝዋይ

  ReplyDelete
 10. ዳኒ ጉድ ነው አዲስ ነገር አገኘሁ ታንኪው ከአቴንስ

  ReplyDelete
 11. እሌኒ ከሲራክዩስSeptember 1, 2010 at 6:24 AM

  + + +
  በአንድም በሌላም መንገድ እስካሁን ችግሮች ነበርን፡፡ አሁን ይህንን ስለተረዳን ልክ እንደ ትራፊክ ፖሊሱ እራሳችንን ከችግርነት ብናስወጣ ለመፍትሔው አንድ እርምጃ ተራመድን ማለት ነው። ቃል ህይወት ያሰማልን ዲ/ን ዳኒ

  አምላከ ቅዱሳን ይጠብቅህ!

  ReplyDelete
 12. First of I want to say that I always admire your mastery of the Amharic language, your unique ability to explore topics from multiple vantage points. But I also have a great deal I disagree with.
  To the rest of the readers I want to say please try to bring in your own views into the discussion. I know this blog is called "Daniel Kibret's views" but that doesn't mean we all have to share his views. It seems to me you all wait until he says something, then applaud cheerfully and praise the infallible.

  Okay D. Daniel, since you have raised the question, I ask you the same questions. Are you part of the problem or the solution? You spend a great deal of time and energy pointing out and explaining all the issues that plague our church and our country. You say everyone of us are guilty to some degree.
  How do you see your role? Have you had a time for introspection? You are inviting us all to look at our role critically. Why don't you be the first one to come forward with your own shortcomings if you have any.
  You have been the face of Mahibere Kidusan and most vociferous leader of the movement to defend the "mother church" from alleged heretics. You have preached passionately to the youth to stand up and defend their church, fight the good fight. So what is the final outcome of your effort?

  Since we have to be mirrors to each other, here is my opinion of you


  Dear D. Daniel,
  Since I come to know you as through your teachings I have instantly become your disciple. I have defended you against critics numerous times and proudly proclaimed that you are one of the golden children of our church. But over the years I have grown more troubled by some of your teachings, your actions and inactions and the movement you have come to represent.

  In your interview with Deje Selam, you have defended yourself against accusation that you have radicalized the youth. Well I am one of your accusers. I have seen many churches who have existed peacefully for a long time break up into peaces because the youth rebelled against the clergy or the governing committee. What is more radical than that? I have witnessed church elders and clergy ridiculed and insulted by "mezemerans". I have heard the word heretic or "menafiq" used against true servants of our church who never raised any questions on the dogma. If this is not radical, I don't know what it is.

  You said our holly synod is not even discussing whether we can eat fish or not. The problem is that we don't have a climate that encourages this kind of discussion. If anyone raises any question on the church canons, he/she is immediately labeled a heretic and casted out. Aba WoldeTinsae is one such victim. He is now widely considered a heretic among your followers.
  It is now considered unorthodox to listen or sing music even in a wedding. It has to be mezmure which nowadays is so much like the music as you have stated above. When did it become a sin to sing in a weddings? I have heard you criticize "mezemerans" who insist on having music on their wedding. If this is not radical, I don't know what it is

  I am not saying that you are responsible for all the actions taken by your followers but I do think you are guilty of not reprimanding them and in some cases guilty of inciting this maddness. I also think you are guilty of disparaging the church leaders and elders. I know you are passionate about the church and you may even have more theological knowledge that most of our leaders but that doesn't give you a license to criticize everyone as you please.

  sometimes it is better to be kind than clever.

  I still think you are a great asset to our church and our society in general but you need to show a little more humility and tone down your rhetoric.

  ReplyDelete
 13. Deacon Mehari Gebremarqos

  Dear Brothers, I think, it would be better to the church and for ourselves if we start to have some kindness and positive thinking. Stop accusing each other. Let’s start finding the solution and let’s start it from within ourselves. It is really a pity to see people who seem to be highly concerned on the same issue nagging and squabbling all the times. Deacon Daniel is trying what he can do to make the church’s future better than what it is now.

  What we are trying to start here is not canonical changes rather it is changing the structure which worries us most. All these rank and file of problems which we are having now sprout from the very nature of structural decadence. The structural decadence in turn is the result of spiritual indolence which is ruling the entire religious software of our psyche. According to my perception, that’s where Deacon Daniel is trying to point at, basically. He is saying, we have to bring the structural change soon in order to emancipate our church from these stumbling problems via changing ourselves and our spheres of influence like Mahiberats, Sebeka Gubaets, friends, etc. If you want change start it from who you are then extend it to where you are. That’s what he is saying.
  That’s what should be done. Share dreams of changing the future; listen to each other; share views; share ideas; share your souls in prayer. This will lead you to action. Stop squabbling because that’s what decadence needs to prevail for long.

  ReplyDelete
 14. BESMEAB WWOLD WMENFESKIDUS AHADUAMLAK AMEN!

  First of all I want to thank God the almighty for his unlimited love and boundless mercy against all our trespasses.
  Dear Dacon Daniel I am one of the admirers of your sermons they are very focused objective and presise your topic selection and presentation is fabulous.In generalyou are a good preacher I PRAY god give you his grace abundantly.

  I also have some advices if you accept them my advices are the following
  1 On your teachings and sermons please please focus on peae love and unity because these are the most out standing pillars of our Lord.2 Accept corrections and love those who corrects you .Love ur enrmies if u have some.thank u and GOD BLESS U

  ReplyDelete
 15. As has always been, Dn. Daniel has raised a wide range of issues that plagued our church and stifled it from reaching out to those who need it dearly, both locally and internationally.

  Now we need to get down to the practical solution and not limit ourselves to identifying problems.You have raised lots of problems; how r w3e supposed to coordinate our effort to curb the situation and encourage dialogue among the stakeholders? who will be responsible to coordinate such effort?
  It is high time we should put our wisdom to this end. I do not mean the problems you have been raising were not important; rather they made us to know the weaknesses with in our church. It only means that we just want to see the problems solved, involving all stakeholders. God bless you!

  ReplyDelete
 16. I thank You the above writer

  ReplyDelete
 17. I thank you the above commenter except the issue of Aba Woldetinsae

  ReplyDelete
 18. የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቅቀቅ

  ReplyDelete
 19. Dear readers
  I have one comment on the comments. When we write comments, why many people use anonymous? It is hard to give ideas on specific comments and make the discussion live. So could you please a nick name, as I did, when you write comments? Dear Dn. Daniel could you please write a notice for all the audience about this?

  Thank you

  ReplyDelete
 20. ዲ/ን ዳንኤል-፡ምስክርነትህ እውነትነውና በይወት መንገድ ላይ ቆመው መሰናክል የሆኑትን ሀሳዊ መሲህ እግዚአብሄር መልአኩን ልኮ በፍጥት ያስወግዳቸው፡፡አሜን፡፡

  ReplyDelete
 21. የተከበራችሁ የዚህ የጡመራ-መድረክ እድምተኞች ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ።
  በዚህ መድረክ ላይ መሳተፋችን እንደው ለተሳትፎ ብቻ እንዳይሆንና መማማሪያና መመካከሪያ እንዲሆነን እንዲሁም የምንሰጠው አስተያየት ለሌሎች በግልፅ እንዲረዳቸው አስተያየቶቻችንን የምንፅፈው በኣማርኛ ቢሆን ይመረጣል። ሊያስቸግራችሁ ይችላል ነገር ግን ለበጎ ነውና እስቲ እንደምንም ብላችሁ ሞክሩት።
  አመሰግናለሁ።

  ReplyDelete
 22. ኃ/ገብርኤል ከአራት ኪሎSeptember 2, 2010 at 3:44 PM

  ዲ/ን ዳንኤል ሰላም ላንተና ለዚህ መድረክ እድምተኞች ይሁን።
  “ችግር ነን መፍትሔ” በእኔ እይታ፤
  የትራፊክ ፖሊሱ መንገዱ መሀከል የገባው እንደኃላፊነቱ የትራፊክ ፍሰቱን ሊያሳልጥ፣ በህይወትም ሆነ በንብረት ላይ አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከል፣ ባለማወቅ ቀለል ያለ ስህተት የሚሰሩትን ሾፌሮች በምክር ከስህተታቸው ሊመልስ፣ከሹፌርነት ሙያና ስነምግባር ውጪ በመነቀሳቀስ አጥፍተው ለመጥፋት የሚፋጠኑትን ደግሞ በህጉ መሰረት ሊቀጣ ነው። ለዚህም ነው ያለ አንዳች ማወላወል በልበ ሙሉነት ሲንቀሳቀስ የዋለው። በሌላም በኩል ስራውን እየከወነ ያለው በቅንነትና በልበ ንፁህነት ስለነበረ የፈለገውን የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት ባለማየቱ ቀኑን መራገም፣ ማማረር፣ ሾፌሮቹን መቆጣት ባስ ሲልም መናደድና ክፉ ቃላትን መሰንዘር የጀመረው። ሌላው የትራፊክ ፖሊሱ በዚያ መንገድ ላይ የቆመው ጥፋት መሆኑን አውቆና ይህንን በማድረጉም ሌላ ጥቅም ፈልጎ እንዳልሆነ የሚያሳየን ነጥብ ደግሞ ለትራፊኩ መጨናነቅ አንዱ ምክንያት እርሱ እንደሆነ ሲነገረው ምንም እንኳን ይህ ንግግር የእርሱን ልፋትና ትጋት ያላገናዘበ ቢመስለውና “አንተኮ መፍትሔ የሰጠህ መስሎሃል እንጂ ችግር እያበባስክ ነው ስለሆነም እስኪ ከመንገዱ ወጣ በልና የሚሆነውን እየው” የሚለው የመፍትሔ ሃሳብ ሲሰጠው ትንሽ ቢያመነታም ግትርነት ተጠናውቶትና ስለ ትራፊክ ህግ እናንተ ልታስተምሩኝ ነው እንዴ? ይህማ ልጅ ለእናቷ ምጥ ማስተማር ነው በማለት ጭምር ሳይገዳደራቸው ሃሳባቸውን ተቀብሎ ተግብሯል። በመሆኑም ተሽከርካሪዎቹ በለመዱት መልኩ እንቅስቃሴያቸውን ጀመሩ ችግሩም ተፈታ።
  በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ የቆምን ግለሰቦች ግን አቋቋማችን ከትራፊክ ፖሊሱ አቋቋም ባንድም በሌላ በእጅጉ ይለያል። የትራፊክ ፖሊሱን ሁሉም በዚያ መንገድ የሚያልፍ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ ፊትለፊት ይመለከተዋል ጥፋቱንም ልማቱንም ሁሉም ያየዋል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ የቆምነውን ግለሰቦች ግን እኩይ ግብራችንን ስናከናውን የሚመለከቱን ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኛው ህብረተሰብ የሚመለከተው በክፉ ግብራችን ምክንያት የሚከሰተውን አሳዛኝ ውጤትን ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ የቆምን ግለሰቦች አቋቋማችን እንደ ትራፊክ ፖሊሱ በየዋህነት አይደለም በክፋት እንጂ የምናጠፋውም እንሰራለን ብለን ሳይሆን ሆን ብለን ለማጥፋት ነው። እያጠፋችሁ ነው ስንባል እንኳን ከክፉ ግብራችን ተፀፅተን በመመለስ ፋንታ በክፋት ላይ ክፋትን፣ በበደል ላይ በደልን፣ በጥፋት ላይ ጥፋትን እያበዛንና እየከመርን እንሔዳለን።
  የትራፊክ ፖሊሱን እንደተናገረው ሾፌር በመስኮት ሳይሆን ጆሯችን ላይ መጥተው ቢጮሁብንም እንሰማለን እንጂ አናዳምጥም በእኛ ምክንያት የተፈጠረውንና እየተፈጠረ ያለውን ጉዳት አፍንጫችን ላይ ቢያስቀምጥልንም እናየዋለን እንጂ አንመለከተውም። ምክንያቱም የምናጠፋው ጥፋት ጥፋትነቱ ለሌሎች እንጂ ለእኛማ ሆድ መሙያችን፣ ካባ መደረቢያችን፣ ፎቅ መስሪያ ቢዝነሳችን ነው። ስለዚህ የፈለገው ቢጮህ ቢንጫጫ “ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ” እያልን ቢዝነሳችንን ማጧጧፍ ነው።
  በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ ቆመን ቤተ ክርስቲያን ለምታካሂደው መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ደንቃራ የሆንን ግለሰቦች እንደ ትራፊክ ፖሊሱ በአንድ ሾፌር ተግሳፅ ከጥፋታችን አንመለስም። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ይባል የለ። የተኛነውም አተኛኘት ስልታዊና በዕቅድ የተደገፈ በመሆኑ ለቀስቃሽም ያስቸግራል። በእንደዚህ ሁኔታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንገድ ላይ የቆምን ግለሰቦች እንዴት ያለ ወረንጦ ነቅሶ እንደሚያወጣን አይገባኝም።
  ጵጵስና ከግብፅ ወደ እትዮጵያ መምጣቱ ችግር ሆነ ወይስ መፍትሔ በሚለው ነጥብ ላይም ዲ/ን ዳንኤል ማስተላለፍ የፈለገው ቁም ነገር ድርጊቱን መቃወሙ አይደለም። ከፅሑፉ ጭብጥ እኔ እንደተመለከትኩት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች መተዳደር መጀመሯን ማንም የቤተ ክርስቲያን ልጅ አይቃወመውም። አያስበውምም። ነገር ግን በድርጊቱ ምክንያት ልንጠቀምበት የሚገባንን አልተጠቀምንም፣ ማድረግ የሚገባንን አላደረግንም፣ ማደግ የሚገባንን ያህል አላደግንም፣ መቅረት ያለበትን ነገር አላስቀረንም መለወጥ ያለብንን ያህል አልተለወጥንም፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለነተናዊ እንቅስቃሴ መታየት የነበረባቸውና ዘመኑን የዋጁ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ክንዋኔዎች አልታዩም ነው።
  የዚህ ምክንያት ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንገድ ላይ አውቀንም(በአብዛኛው) ይሁን በስህተት አደገኛ አቋቋም የቆምን ግለሰቦች አለን። ከመንገዱ ላይ እንነሳ፣ ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋ ረዥም ነውና ያስቀመጥነውን ደንቃራ እናንሳላት፣ መለወጥ በሚገባት መልኩ ትለወጥ፣ ማደግ ያለባትን ያህል ትደግ። አሁን ዋናው ጥያቄ እንደ ትራፊክ ፖሊሱ አንድ ሾፌር አይደለም በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ሾፌሮች ተሰብስበው ችግር ፈጣሪዎቹ እናነተ ናችሁና ከመነገዱ ላይ ፈቀቅ በሉ ብንባልም አሻፈረኝ ብለን በአቋማችን ፀንተናል ይባስ ብለንም ሌሎች መንገዶችንም በባትሪ እየፈለግን የትራፊክ ፍሰቱን እያጨናነቅን እንገኛለን። ታድያ ይህ ክፉ ተግባራችን መቋጫው ምንድነው??? ምን ብንደረግ ነው ከጥፋታችን የምንመለሰው??? ማን ምን እስከሚያደርገን ነው የምንጠብቀው??? ከክፋታችንና ከበደላችን ትብብር ሳይኖራቸው በቅንነትና በፍፁም ፈሪሃ እግዚአብሔር ኃለፊነታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ልጆች ጥፋታችንን እያዩ ዝምታቸው እስከ መቼ ነው??? ምን ማድረግ ነበረባቸው??? ምንስ እያደረጉ ነው???
  ቸር ያሰማን

  ReplyDelete
 23. That is right.
  New direction of solving our church's problem is needed.Bothe spritually and mentally.
  Ewnet

  ReplyDelete
 24. Dear Dn. Daniel
  God bless you
  I agree with all of the comments by the above people. But the question is how to start and where to start. Some people at Awassa are committed to start the change by inviting spiritual leaders from BETEKIHINET for discussion. But response was physical damage and hurt in front of God’s house. It happened on a couple of two Sunday Kidase time. People were asking to correct the wrong doing of some church officials and preachers. But they call police to get out those people stand for truth. So what can they do more than this, more than bleeding in the compound of the church? It is shame to see people fighting in the church. I am confused. There are identified problems, identified causes and identified solutions. But when and how to start is a big question. “ yemesiwat gize bemetana meswat honene betekiristainin badanat”
  Tewahido lezelalaem tinur
  (Long live Tewahido)

  ReplyDelete
 25. አምደ ሚካኤልSeptember 7, 2010 at 9:17 AM

  I have nothing to say on this comments.Because it is very nice

  ለመሆኑ የያሬድ ዜማ ይበልጥ ታወቀ ወይስ ጠፋ? በመዝሙር በኩል መናፍቃንን ተከላከልን ወይስ አስገባን? ድምፃዊው በዛ ወይስ ዘማሪው? መዝሙር አገልግሎት ሆነ ወይስ ሥራ? ዝማሬ ጽደቅ ሆነ ወይስ ሞያ? ሕዝቡን ከዘፈን አመጣነው ወይስ ከቅዳሴ አስወጣነው? የዘማርያኑ ኑሮ ነው ወይስ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ነው የተለወጠው? ሕዝቡ መንፈሳዊ መዝሙር ነው የሚገዛው ወይስ በእናቱ ዘፈን በአባቱ መዝሙር የሆነ? ሕዝቡን ወደ ጸጥታ ወደብ ወሰድነው ወይስ አጨቃጨቅነው? አስማማነው ወይስ አለያየነው? የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስፋፋን ወይስ የራሳችንን አመለካከት? ታድያ እኛ ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ችግር ነን ወይስ መፍትሔ?

  ReplyDelete
 26. Dani, perfect what you said but becareful not to embark to our mahber (MK). What I read resembles like that. this is b/c ..,.

  ReplyDelete
 27. በዚህ ፅሁፍ ብዙ አስተያየት ጠብቄ ነበር ዳኒ ጨርሶብን ነው እንዴ? አይመስለኝም ግን ምን ሆነን ነው? ዝምታችሁም ነገሩ አስተያየት ሊሆን ይችላል እኔ ግን አልገባኝም

  ReplyDelete
 28. ማኅበራችን....?
  ሕዝቡ እነርሱን ተስፋ አድርጎ እንዲቀመጥ አደረጉት፡፡ ለጥያቄዎች መልስ፣ ለችግሮች መፍትሔ፣ ለጨለማው ብርሃን ከእነርሱ ይጠብቃል፡፡ እነርሱ ደግሞ «ሀ- ራስክን አድን» ብለው በራሳቸው አጀንዳ ተጠምደዋል፡፡ «ቤተ ክርስቲያናችን» ማለት ትተው «ማኅበራችን» ማለት ጀምረዋል፡፡ «የቤተ ክርስ ቲያናችን ልጅ» መባሉ ቀርቶ «የማኅበራችን ልጅ» ሆኗል ቋንቋቸው፡፡

  ቤተ ክህነቱን ያስተካክላሉ ሲባሉ እነርሱ ራሳቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቤተ ክህነቶች ሆነዋል፡፡ አሠራርን ያስተካክላሉ ሲባሉ እነርሱ ራሳቸው በተወሳሰበ፣ ግልጽነት በጎደለው እና ኋላ ቀር በሆነ አሠራር ተተብትበዋል፡፡ የገንዘብ አያያዛቸው፣ የርዳታ አሰጣጣቸው፣ የአባላት አመዘጋገባቸው፣ የሪፖርት አቀራረባቸው፣ የፋይል አያያዛቸው፣ የዶክመንት አደረጃጀታቸው፣ የስብሰባ አካሄዳቸው ከቤተ ክህነቱ የባሰ ሆነዋል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተገላገሉትን ቢሮክራሲ እነርሱ ወሰዱት፡፡ ለጉባኤ እና ለድግስ ብሎም ሞቅታ ላለበት ተግባር እንጂ ለአገልግሎት የሰነፉ አባላት መናኸርያ እየሆኑ ነው፡፡

  ReplyDelete
 29. Christianity is not always to talk about negatives,we all are know that this world are not fair and full of sin.Our lord already told us. So as a Christian what we should be is "above the law" and discus and share our love, heart full thanks to our GOD.dear brother why you always talk about negatives...are you a simple writer or a preacher? i am confused. please follow the path of our forefathers not our flesh thing or emotion.If i offend u please forgive me.

  ReplyDelete
 30. dn leul
  ...look daniel, asking such a critical question may show ur deep insight on such issues and may let others to identify the trouble maker!but what i need is just to see u preaching about our personal spiritual life. because if all are blamers...

  ReplyDelete