Tuesday, August 17, 2010

እንደእኔ እንደእኔ...

ሲሎንዲስ ዘአውሮፓ

 የዲ. ዳንኤል የመፍትሔ ሃሳቦች መንፈሳዊ ምክርንና ተግባራዊ አካሄዶችን ያካተቱ ነበሩ፤ለዚያም ነው አንዳንዶቹ ጥቅል የሚሆኑት።ዲ. ዮሐንስ ያነሳሀቸው ነጥቦችና አካሄዶች ለዘላቂ መፍትሔ የሚበጁ ተግባራዊ አካሄዶች ናቸው።አሁንም ግን ከእነዚህ በፊት ሊደረጉ የሚገባቸውና ወደ ተጠቀሱት መንገዶች የሚያመጡ ጅምሮች ያስፈልጉናል፤አለበለዚያ አሁንም የምንቆመው ጥቅል (abstract) የሆኑ ዕቅዶች ላይ ነውለምሳሌ 'እንዲህ ብናደርግ' ተብለው ለተጠቀሱት አሳማኝ መፍትሔዎች ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራው አካል አሁንም ግልጽ አይደለም

እንደእኔ እንደእኔ...

1.የቤተ ክህነቱን አሰራር የከለለው መጋረጃ መከፈት አለበት

የሚነሱት የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ለመወያየትም ሆነ ለመስራት ከምዕመናን ብቻ ሳይሆን ከቤተ ክህነትም ተነሳሽነት መኖር፣እንዲኖርም መሰራት አለበት።ለዚህ ደግሞ አስተዳደራዊ አካሄዶችን የሰወረው መጋረጃ መከፈት አለበት።በሌላው ዘንድ የጠፋውንና ምዕመኑ የያዘውን ፈሪሃ እግዚአብሔርና መንፈሳዊነት ተጠቅመው የቤተ ክህነቱ መጋረጃ እንደ መቅደስ መጋረጃ እንዲታይ የሚፈልጉ ሐናንያውያን አሉ። በየአጥቢያው የሚመረጡ የሰበካ ጉባኤ አባላት የምዕመኑ ተወካይ ናቸውና ቢያንስ አበይት የቤተ ክርስትያን አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን አውቀው ለምዕመኑ እንዲያሳውቁ ብሎም ልዩ ውሳኔዎች ሲሰጡ እንዲገኙና እንዲሳተፉ መደረግ አለበት።እንደአማራጭ ቤተ ክህነቱ በየ2 ወይም 3 ወሩ የሚያወጣው አስተዳደራዊ የኅትመት ውጤት፣ለምዕመኑ በመረጃ የሚደርስበትና አስተያየት የሚቀበልበት ድረ ገጽ መክፈት..የመሳሰሉ ጅምሮች ሲፈጸሙ ግልጽ ወደሆነና ለውይይት ወደሚያመች መንገድ ይወስዱናል። እናም እንደ አንድ የቤተ ክርስትያን ምዕመን አስተዳደራዊ አካሄዶችን የማወቅና የመሳተፍ ድርሻችንን ልናስጠብቅ ይገባል ባይ ነኝ፤ ለጊዜው ይህን ጥያቄ ልናነሳ ልንወያይ የምንችለው በየቤተ ክርስትያኑ በሚገኘው የሰበካ ጉባኤ በኩል ነው...መቀሳቀስና መንቀሳቀስ ያስፈልጋል

2.መሪነቱን ይዞ የሚያስፈጽመውን አካል መወሰን

በምዕመኑ የሚነሱትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለቤተ ክህነት የሚያደርስና መልሱንም የሚያሳውቅ ጉዳዩን ጀማሪ አካል ያስፈልጋል(በመጠኑ ተጠቅሷል)።እስካሁን ባለው መዋቅር ይህ አካል ከቤተ ክርስትያን አሰራር ውስጥ ያለ መሆን ካለበት ሊሆን የሚችለው ብቸኛ አካል ማኅበረ ቅዱሳን ነው።ነገር ግን እርሱም እስካሁን ወደ ሁሉም ምዕመን እንደሚፈለገው የደረሰ አካል አይደለም፤ጥቂት የማይባል ሰውም ለጊዜው በተሳሳተ መልኩ ተረድቶታል። እኔ ይህን አካሄድ ብመርጥም ሌላው አማራጭ ምዕመናንን ማዕከል ያደረገ ኅብረት መመስረት ነው፤እንዴት ይመስረትና ከቤተ ክህነቱ ጋር ችግሮችን መወያየት እንዴት ይጀምር የሚሉት ከዚህኛው አማራጭ ጋር የሚመጡ ጥያቄዎች ናቸው...በዚህም ሆነ በዚያ ይህ አስተዳደራዊ ችግር ይመለከተናል፤የሚበደለው ከቤተ ክርስትያን የምናገኘው መንፈሳዊ አገልግሎትም ነው፤የሚባክነው ንብረታችን ነው...ይህንንም አካል የመወሰን ወይም የማቋቋም ሙሉ ነጻነት አለን፣የተሸፋፈነ አስተዳደራዊ ውሳኔና አሠራር ማብቃት አለበት

3.እንደሚመለከተን ማመንና መሳተፍ

ይሄ አስተዳደራዊ ችግር አረም ነው፣ስንዴውን አያጠፋም ግን ምግቡን ይሻማል።

የቤ.ክንን አስተምህሮ ለጊዜው አይቀይር ይሆናል የእኛን ጉዞ ግን ይፈታተናል፤ባላት አቅም ሁሉንም ወደበረቱ እንዳትሰበስብ አቅሟን ያዳክማል ንብረቷን ያባክናል።ወንድሞቼ ዘመኑ ተቀይሯል፤አሁን ድንጋዩን ካላነሱ ከመቃብር መጠራት የለም።ድርሻ አለን፤በትዕቢት ሳይሆን በመንፈሳዊ ቅንዓት የምንወጣው።በመልካሙ ጊዜ አባቶቻችንም በየዋሃት ተመላሰሱ፤እረኞቹም ቢያንስ ሰውን ፈሩ። ስለቤተክርስትያን ጉዳይ ሲነሳ እንደሦስተኛ ወገን ከውጪ ከመመልከትና ከማማት ወጥተን ባለው አጋጣሚ ሁሉ ያመንንበትን መናገር መስራት አለብን።ቢያንስ በሰንበተ ክርስቲያን ቤ.ክ ስንሳለም ወደፊት ልናይ ስለምንችለው ዝብርቅርቅ ለልጆቻችን ምንድንነው የምንነግረው? ችግሩ የበለጠ ሲከፋኮ እንደምዕራቡ ዓለም እያንዳንዳችንን ከቤቱ ሊገፋ ይታገላል. .በቤታችን!?

አንድ እህቴ ያጋጠማትን ጠቅሼ ላብቃ...ታክሲ ላይ በአጋጣሚ አጠገቧ የተቀመጠ ሰው ነው፤በምቾት የተንገላታ የሚመስል።ታክሲው በቤ.ክ አጠገብ ሲያልፍ ስትሳለም ያይና ስለ ቤ.ክ ጨዋታ ይጀምራል።

ወሬው መሐል ላይ እንዲህ አላት

'በዚህ ዘመንኮ ቢዝነስ ያለው ቤ.ክ ነው፤እኔን ውሰጅ በቅርቡ ...ሀገር ቤ.ክንን ወክዬ ሄጄ ነበር ሌላውን ቢዝነስ ተይውና ክፍያው እራሱ ነፍስ ነው።አንቺ ብቻ የምትቀርቢው ሰው ይኑርሽ አሪፍ አሪፍ ቦታ እየተወከልሽ ትላኪያለሽ...' ሌላም ሌላም ዝርዝርና ተራው ምዕመን የማያውቃቸው የአስተዳደር ጉዳዮችን መዘክዘክ ቀጠለ። የሚወራልዎት እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?ለመፍትሄው ካልሰራን የዚህ ዓይነት ሰዎች ናቸው ተራብተው በሽታቸውን የሚያዛምቱት፤እኛንና ቤተክርስትያንን ወክለው በአደባባይ የሚቆሙት!

አምላከ ቅዱሳን በማይመረመር ጥበቡ ወደመፍትሔ ይምራን፤ድርሻችንን የምናውቅበትና የምንወጣበት ማስተዋል ያድለን፣ለበጎ ሥራ ያስተባብረን።

3 comments:

 1. This comment has been removed by a blog administrator.

  ReplyDelete
 2. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን.
  ሰላም ለዚሕ ቤት
  በመጀመርያ የዲ.ዳንኤልን ሀሳብ በሙሉ እስማማለሁ ነገር ግን አንድ ነገር አለ ወንድማችን ዲ.ዳን በስብከቱ እንዳለው ቀኑ አርብ ነው. ታድያ ብዙ ሀሳቦች በጽሁፍ ተጽፈዋል ነገር ግን አርብ ሊመሸ ዓልቻለም አርብ ካልመሸ ቅዳሜ አይመታም ቅዳሜ ካልመታ እሁድ ትንሳኤ የለም ማለት ነው.ዋናው የምንፈልግው ደግሞ የቤ.ክን ትንሳኤዋን ነው.ስለዚ መፍትሔው መጻፍ ብቻ አይመስለኝም:: የምንችል በአካል ተገናኝተን ማህበር መመስረትናተቀራርበን መነጋገርና መልካሙን ነገር መወሰን ከዛም ወደስራ መግባት.በአካል መገኝት የማንችል በጸሎትና በገንዘባችን መራዳት ይኖርብናል ካለበለዚያ ሁሉም ነገር አርብ ላይ እንዳል እንዲሁ በወሬናበንትርክ በአሉባልታ ለሚቀጥለው ትውልድ ይተላለፋል ስለዚሕ ከአሁኑ ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ.እናም መፍትሔው መሰባሰብ ይኖርብናል ባይ ነኝ በውነት ወንድማችን በጽሁፍም ስብከት በድምጽም ስብከቶቹ ብዙ ብሎናል በሙሉ ስብከቶቹ ክርስትያኖችን ለሰላምና ለስራ የሚያነሳሱ ናቸው:: ክርስትያናዊ ህይወት ዋናው ቁምነገሩ ወሬ ላይ ሳይሆን መልካም ስራ ላይ ነው::ስለዚህ እባካችሁ ልንሰባሰብ የምንችልበትን ሀሳብም ብናቀርብ መልካም ነው እላለሁ::እግዚአብሔር የቤተ ክርስትያን ትንሳኤዋን ያሳየን::{ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ}የሐዋ13:15 መስፍን ከአቡ ዳቢ

  ReplyDelete
 3. ሰላምታ!!!
  Dear ሲሎንዲስ ዘአውሮፓ, beloved brother in Christ!
  Thank you for sharing us the great ideas.
  "1.የቤተ ክህነቱን አሰራር የከለለው መጋረጃ መከፈት አለበት::" That is really good thing to start on.

  Bless you!

  ReplyDelete