Tuesday, August 3, 2010

የብርጭቆው ወይስ የምንጩ ውኃ ክፍል 2

ባለፈው ሳምንት የቤተ ክህነቱን አጭር ታሪክ እና ያጋጠመውን ፈተና ማየት ጀምረን ነበር እንቀጥላለን

ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያን ጳጳሳት መመራቷ የራሱ የሆነ ጥቅም እና ጉዳት ነበረው፡፡ ከጉዳቱ አንዱ ጠንካራ፣ በዘመናት የተፈተነ እና ሥር የያዘ ቤተ ክህነት እንዳይኖረን ማድረጉ ነው፡፡ የቤተ ክህነቱን ሥራ ነገሥታቱ እና ግብፃውያን ጳጳሳቱ ከካህናተ ደብተራ ጋር ብቻ በመሆን ማከናወናቸው የቤተ ክርስቲያንዋን እድሜ ግማሽ እንኳን ያለው ቤተ ክህነት እንዳይኖረን አድርጓል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ብቸኛ የትምህርት ተቋም በነበረች ጊዜ ለራስዋም ሆነ ለሀገሪቱ የሚሆን የተማረ የሰው ኃይል ታመረት ነበር፡፡ ለቅዳሴው፣ ለማኅሌቱ፣ ለአቋቋሙ፣ ለሰዓታቱ፣ ለትርጓሜው፣ ለቅኔው፣ለድጓው የሚሆን የሰው ኃይል ራስዋ በራስዋ ታወጣ ነበር፡፡ ቤተ ክህነት በዘመናዊ መንገድ ሲቋቋም ግን የሕግ ጉዳይ፣የሂሳብ ጉዳይ፣የሥራ አመራር ጉዳይ፣ የመዝገብ አያያዝ ጉዳይ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ ጉዳይ ጉዳዮቿ ሆኑ፡፡

ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ማቀድ፤ ኦዲት ማድረግ፣ ሕንፃዎችን በዘመናዊ መንገድ ማሠራት እና ማስተዳደር፤ ዘመናዊ ት/ቤቶችን ማቋቋም እና ማስተዳዳር፣ የጤና ተቋማትን ማቋቋም እና ማስተዳደር፣ የንግድ ቦታዎችን ማስተዳደር ወዘተ ተጨማሪ ሥራዎቿ ሆኑ፡፡

ነገር ግን ለእነዚህ ተግባራት የሚሆን የሰው ኃይል ማምረቻ የላትም፡፡ ከሚያመርቱ ተቋማትም አትወስድም፡፡ በሚሊዮን ብሮች ታንቀሳቅሳለች፤ በበቂ የሰው ኃይል የተደራጀ የፋይናንስ መምሪያ ግን የላትም፡፡ ሌላው ቀርቶ «ፒች ትሪ አካውንቲንግ» እንኳን እንደ ናፈቃት ሊቀር ነው፡፡ አንዱ ደብር ገንዘብ ላይ ይተኛል፣ ሌላው ደብር ጧፍ ይለምናል፡፡ ተመሳሳይ ሞያ ያላቸው አገልጋዮች በቦታ መለያየት ብቻ የሰማይ እና የምድር ያህል ርቀት ያለው ደሞዝ ያገኛሉ፡፡

የ35000 አብያተ ክርስቲያናት የሕግ ጉዳይ ይመለከታታል፤ ነገር ግን በቂ የሰው ኃይል የያዘ የሕግ መምሪያ የላትም፡፡ ስንት በፒ ኤች ዲ፣ ስንት በዲግሪ? ስንት በዲፕሎማ የተማረ፤ የራስዋንም የሕግ ሥርዓት የጠነቀቀ ባለሞያ አሠማርታለች? ቢባል መልሱ ከባድ ነው፡፡

ብዙ ሕንፃዎች ታስገነባለች፣ አንድ ክፍለ ከተማ እንኳን ያለውን የግንባታ ባለሞያ የላትም፡፡ አያሌ ዘመናዊ ት/ቤቶች በሥርዋ አሉ፤ ነገር ግን የትምህርት ሚኒስቴር በሥርዋ የላትም፤ አያሌ የጤና ተቋማት አሏት፣ ነገር ግን የጤና ቢሮ አላደራጀችም፤ ብዙ ይጠበቅባታል፣ ነገር ግን ቢያንስ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የላትም፡፡ ከ45 ሚሊዮን በላይ ምእመን አላት፤ ነገር ግን ከ3000 በላይ የሚታተሙ መጽሔት እና ጋዜጦች የሏትም፤

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መመለሱ እና ደቀ መዛሙርትን ማፍራቱ እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም አደረጃጀቱ ግን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚያስፈልጋት የሰው ኃይል አንፃር ባለመቃኘቱ ችግርዋን ሊቀርፍላት አልቻለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲን መንፈሳዊ እና ዓለማዊ/secular/ ኮርሶችን እንዲሰጥ አድርጎ ማዋቀር ይቻል ነበር፡፡ በአንድ በኩል ነገረ መለኮትን በሌላ በኩል አስተዳደርን፣ ሕግን፣ የሂሳብ አያያዝን፣ የቅርስ አጠባበቅን፣ አንትሮፖሎጂን፣ ፊሎሎጂን፣ የኮምፒውተር ሳይንስን፣ ታሪክን፣ ኢኮኖሚክስን እና ሌሎችን የተማረ፤ በሁለት በኩል የተሳለ የሰው ኃይል እንዲያፈራ ቢደረግ ኖሮ ቤተ ክርስቲያን የት በደረሰች ነበር፡፡

እነ መልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ፣ እነ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ፣እነ አለቃ አያሌው፣ እነ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ እና ሌሎቹም በዕውቀት እና በሕይወት ያስጌጧት ቤተ ክህነት ዛሬ ለጋዜጠኛ መልስ ለመስጠት የሚበቃ ሰው እያጣች መምጣቷ የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል፡፡ አንድ በዘመድ የተቀጠረ ጨዋ ሰው በአንድ የቤተ ክህነት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደርጋል አሉ፡፡ ሊቁ ደግሞ ከኋላው ተቀምጠዋል፡፡ የርሱ ደመወዝ 1500 ብር፣ የርሳቸው ደመወዝ 400 ብር ነው፡፡ በንግግሩ መጽሐፍ ጠቀስኩ ይልና ግእዙን ይሰባብረዋል፡፡ ሊቁ አላስችላቸው ብሎ «ምናለ መጀመርያ ብትማር» ይሉታል፡፡ እርሱም ዘወር ብሎ «ብማርማ ኖሮ እንደርስዎ በ400 ብር ደመወዝ መቅረቴ ነበር» አላቸው አሉ፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ እንኳን የመንግሥት መ/ቤቶችን አሠራር ለማስተካከል ስንት ጊዜ ማሻሻያ ተደርጓል፤ መዋቅር ተቀይሯል፣ ቢፒ አር እና ካይዘን ተተግብሯል፡፡ ቤተ ክህነት ግን መዋቅሯን ለማስጠናት፣ለማሻሻል፣ እንደ ቢ ፒ አር እና ካይዘን የመሳሰሉ የአሠራር ማሻሻያ መንገዶችን ለመተግበር አልሞከረችም፡፡ ቢያንስ ሩቅ ሳትሄድ ከመንግሥት እንኳን መማር አልቻለችም፡፡

እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት ሥር የሰደደ እና ከትናንት ጀምሮ የተያያዘ የአሠራር ችግር መኖሩን ነው፡፡ ዛሬ የምናየው የአሠራር ችግር የእነዚህ ሁሉ ትብትቦች ውጤት ነው፡፡

እናም እነዚህ በሽታዎች በአጠቃላይ መልኩ የሚፈታ፣ ምንጫቸውን የሚያስተካክል ነገር ካልመጣ በቀር፣ እንደኔ እምነት ሰዎችን በመቀያየር ብቻ የቤተ ክህነቱን አሠራር ውጤታማ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመጥን ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ታድያ መፍትሔው ምንድን ነው?

እንደኔ እንደኔ የቤተ ክህነትን ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ መፍትሔዎች አራት «መ»ዎች  ናቸው፡፡

1/መረዳት፡    የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዞ፣ የነበረባትን ፈተና እና የቤተ ክህነቱን የችግር ምንጮች በሚገባ መረዳት ማለት ነው፡፡ ከስሜታዊነት፣ ከወገንተኛነት እና ለእኔ ይድላኝ ከሚሉ ስሜቶች ርቀን፤ ችግሩን በሚገባ መገንዘብ አለብን፡፡ ችግሩን በሚገባ ካልተረዳን፤ የቤተ ክህነትን እና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ልዩነት ካልተገነዘብን፤ የምንሰጠው መፍትሔ «እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውን እንዳትነ ቅሉት» የተባለውን የወንጌል ሕግ የሚያፈርስ ይሆናል፡፡

2/መሳተፍ፡   የቤተ ክርስቲያንን ፈተናዎች በምኞት እና በቅን ሃሳብ፣ በቁጭት እና በመብከንከን ብቻ መፍታት አይቻልም፡፡ ራስን የመፍትሔው አካል ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ከምኞት እና ከንዴት ያለፈ ተግባር ያሻል፡፡ በእግር ኳስ ሜዳ ዋንጫ በተመልካች ድጋፍ እና ፍላጎት አይመጣም፡፡ በተጨዋቾች ጥንካሬ እና ተጋድሎ እንጂ፡፡ ዋንጫ በተመልካች ድጋፍ የሚመጣ ቢሆን ኖሮ የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ መውሰድ የነበረባት ደቡብ አፍሪካ ነበረች፡፡

በክርስትና ጉዞም ያለ ክርስቲያኖች ሱታፌ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ አንዳንዶች የሚፈልጉት ነገር እንዲሁ እንዲመጣ ይሻሉ፡፡ አንዳንዶችም የተወሰኑት ሰዎች በሚያደርጉት ተጋድሎ እየተደሰቱ ይቀመጣሉ፡፡ ሌሎችም እናንተ ለምን እንዲህ አታደርጉም? ለምን እንዲህ ወይንም እንዲያ አይደረግም? እያሉ ስለጠየቁ ድርሻቸውን የተወጡ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን መፍትሔ አያመጣም፡፡ እያንዳንዳችን የምንችለውን ስናደርግ እንጂ፡፡

አንዳንዶቻችን ደግሞ «አሁን የኔ ብቻ መሮጥ፣ መጋደል፣ መፍጨርጨር ምን ለውጥ ሊያመጣ ነው? እነ እገሌ እና እነ እገሌ ዝም ብለው፣ እነ እገሌ የተውትን እኔ ምን አለፋኝ? አሁን ለመሆኑ እኔን ማን ከሰው ሊቆጥረኝ ነው?» ይላሉ፡፡ አንድ ነገር እናስብ፡፡ በማቴ 25 ላይ ጌታችን በዳግም ምጽአት ይጠይቃቸዋል የተባሉትን ጥያቄዎች እናስብ፡፡ «ተርቤ ለምን አላበላኸኝም?» አለ እንጂ «ረሃብን ከምድረ ገጽ ለምን አላጠፋህም?» አላለም፡፡ «ታሥሬ ለምን አልጠየቅኸኝም?» አለ እንጂ «እሥር ቤቶችን ለምን አላጠፋህም?» አላለም፡፡ ይህ ምን ያሳየናል? የዐቅማችንን ማድረጋችንን እንጂ ጠቅላላውን ችግር መፍታታችንን እግዚአብሔር አይጠይቅም ማለት ነው፡፡ ችግሩን መፍታት መቻል እና ለመፍትሔው አስተዋጽዖ ማድረግ ይለያያሉ፡፡ ለመፍትሔው መነሣት የኛ፤ ችግሩንም መፍታት የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፡፡

3/መሠዋት፡ ክርስትና በመስቀል ላይ የተመሠረተ ነውና ያለ መሥዋዕትነት ሊጓዝ አይችልም፡፡ ከመስቀል የወረደ ክርስትናም ክርስትና አይሆንም፡፡ ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ካልተዘጋጀን፤ ምንም ዓይነት ችግርን አንፈታም፡፡ የምናጣው ክብር፣ ዝና፣ ስም፣ ገንዘብ፣ ሥልጣን መኖር አለበት፡፡ መሸነፍን መቀበል አለብን፡፡ ይህ ነው ሰማዕትነት፡፡ ጌታችን ተሸንፎ አሸነፈ፡፡ እኛስ? ክንፍ ለማግኘት እግርን ማጣት ያስፈልጋልኮ፤ እኛስ?

ብዙዎቻችን ምናችንም እንዲነካ አንፈልግም፡፡ በሚጋደሉ ሰዎች ላይ ግን እንፈርዳለን፡፡ ጥቂት መሥዋ ዕትነትም ለመክፈል ዝግጁ አይደለንም፤ ብዙ ሃሳቦችን ግን እንሰነዝራለን፡፡ እነ እገሌን እንዲሠው እንጎተ ጉታለን፤ እኛ ግን የእሳቱ ጢስ እንኳን እንዲነካን አንሻም፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው «ሰማዕትነት አያምልጥህ» ይሉ ነበር፤ የአሁኖቹ ደግሞ «ሰማዕትነት አይድረስብህ» ነው የምንለው፡፡ ዋንጫው ከተገኘ «አለንበት» እንላለን፤ ዋንጫው ከጠፋ ግን «እኔ የለሁበትም» ነው መልሳችን፡፡ ታድያ እንዴት መፍትሔ ይገኛል፡፡ ለመሆኑ በተጋድሎ እንጂ በስብሰባ የተሸነፈ ሰይጣን አለ? በሰማዕትነት እንጂ በሃሳብ ብዛት ድል የተደረገ ፈተና አለ?

መሥዋዕትነቱን ከባድ የሚያደርገው ከቤተ ክርስቲያን ችግር የሚያተርፉ ወገኖች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ችግሩን ይፈልጉታል፡፡ በችግሩ ቤተ ክርስቲያን ብትጎዳም እነርሱ ያተርፋሉና፡፡ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን አንድ ከሆነች «የላይ ፈሪ የታች ፈሪ» እያሉ የሚያምታቱ ሰዎች ቦታ ያጣሉ፤ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርዋ ከተጠናከረ ያለ ዕውቀት እና ያለ ዐቅም በዝምድና ብቻ ውጭ መውጣት ይቀራል፤ ያለ ችሎታ እና ያለ በቂ ሕይወት መመንኮስ ይቀራል፣ ክህነት መቀበል ይቀራል፣ መሾም ይቀራል፣ የቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ሥርዓት ከተስተካከለ መዝረፍ ይቀራል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ከጠነከረ እዚህም እዚያም ቤተ ክርስቲያን መክፈትና ገንዘብ መሰብሰብ ይቀራል፤ ያለ ችሎታ እና ብቃት ጵጵና ማግኘት ይቀራል፤ ስለዚህም ችግሩ እንዲቀጥል ይፈለጋል፡፡

እስኪ ተመልከቱ ቀድሞ ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ተአምር ሰምተው ነበር የሚመለሱት፤ እምነቱ፣ ጠበሉ፣ ገድሉ፣ ድርሳኑ ያደረጉትን ተአምር ይሰማሉ፡፡ እኛ ግን ምንድን ነው የምንሰማው? ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ እገሌ እና እገሌ ተደባደቡ፣ ተለያዩ፣ እንዲህ እና እንዲያ ተባባሉ፣ እንዲህ ያለ ሥርዓት ፈረሰ፤ እንዲህ ያለ ኑፋቄ ተሰጠ፡፡ ጆሮዎቻችንኮ በጎ ነገር ናፈቃቸው፤ ይህ እንዲመጣ ግን ተጋድሎ እና ሰማዕትነት የግድ ይላል፡፡ «እንበለ መከራ ኢይትረከብ ጸጋ» ነውና፡፡ ያለ ሕማማት ፋሲካ የለም፡፡

4/መንፈሳዊነት፡ የመጨረሻው፣ ግን ወሳኙ ነገር ነው፡፡ መንፈሳውያን በሌሉበት ቦታ መንፈሳዊ ነገር መፍትሔ አያገኝም፡፡ መንፈሳዊነት ማለት የሃይማኖትን ትምህርት ማወቅ፤ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፤ የቃል ጸሎትን መሸምደድ፣ የቤተ ክርስቲያንን መዓርጋት መያዝ፤ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ማገልገል ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ መንፈሳዊነትን የሚያጎለብቱ ነገሮች እንጂ በራሳቸው መንፈሳዊነት አይደሉም፡፡

መንፈሳዊነት ኑሮ ነው፤ አመለካከት ነው፤ ሕይወት ነው፤ ቅኝት ነው፡፡ መንፈሳዊነት በፈሪሃ እግዚአብሔር ተቃኝቶ፤ በቃለ እግዚአብሔር ተመርቶ፤ መንፈሳዊን ጥበብ ገንዘብ አድርጎ ውስጥን መለወጥ ነው፡፡

አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በምንም መንገድ ካልፈራ፤ ቃለ እግዚአብሔርን ከተለማመደው፤ የማያምንባቸውን ነገሮች ለሥነ ሥርዓት ሲል ብቻ የሚያደርግ ከሆነ፤ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ነገር ከስሕተቱ ካላቆመው፤ «እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር» ከሚባልበት ደረጃ ደርሷል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው የተአምራት ቅጣት እንጂ ምክር እና ተግሣጽ አይመልሰውም፡፡

በመሆኑም የሳኦልን ኃጢአት የሚመክት የዳዊት መንፈሳዊነት፤ የኤልዛቤልን ኃጢአት የሚመክት የኤልያስ መንፈሳዊነት፤ የድርጣድስን ኃጢአት የሚመክት የጎርጎርዮስ መንፈሳዊነት፤ የብርክልያን ኃጢአት የሚመክት የዮሐንስ አፈወርቅ መንፈሳዊነት፤ የግራዚያኒን ኃጢአት የሚመክት የአቡነ ጴጥሮስ መንፈሳዊነት፤ ያስፈልጋል፡፡

አንድ የጥንት አባት «በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቁ ችግር የሚፈጠረው መንፈሳውያን ያልሆኑ ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ ሲሠሩ ነው» ብሎ ነበር፡፡ ያልመነኑ ሰዎች ከመነኮሱ፤ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ከቀሰሱ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁት ሰዎች ካስተማሩ፤ ደመወዝ፣ቤት እና መኪና የሚያጓጓቸው ሰዎች ከጰጰሱ፤ ፍትፍት ያልሰለቻቸው ሰዎች ባሕታውያን ከሆኑ፤ የዘር ዛር ያልለቀቃቸው ሰዎች የሁሉ አባት ከተባሉ፤ከራሳቸው ጋር ያልታረቁ ሰዎች ለታራቂነት እና አስታራቂነት ከተቀመጡ፤ መንፈሳዊነት ሽታውም ጠፍቷል ማለት ነው፡፡

ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ለመንፈሳዊ ችግሮች የታክቲክ እና የቴክኒክ እንጂ የመንፈስ መፍትሔ ስንፈልግ የማንገኘው፡፡

አንዳንድ ጊዜኮ እኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለን፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ከእኛ ውስጥ ወጥታለች፤ እኛ በክርስትና ውስጥ ነን፤ ክርስትና ግን ከእኛ ውስጥ ወጥቷል፤እኛ በክህነቱ ልብስ ውስጥ ነን፤ ክህነቱ ግን ከእኛ ውስጥ ወጥቷል፤ እኛ በስብከቱ ቀሚስ ውስጥ ነን፤ ስብከቱ ግን ከውስጣችን ወጥቷል፡፡ እኛ በገዳም እንኖራለን፤ ገዳማዊ ሕይወት ግን በኛ ውስጥ የለም፡፡ ለአንዳንዶቻችን ጵጵስና ፕሮፌሽን ነው፤ ቅስና ፕሮፌሽን ነው፣ ሰባኪነት ፕሮፌሽን ነው፤ ምንኩስና ፕሮፌሽን ነው፤ዝማሬ ፕሮፌሽን ነው፣ እንደ ጥብቅና፣ እንደ ንግድ፣ እንደ ሕክምና፣ እንደ ጋዜጠኛነት፣ እንደ ምሕንድስና፣ የእንጀራ ማግኛ ሞያ፡፡ ታድያ እንዴት መንፈሳውያን መሆን ይቻላል?

በመጽሐፈ መነኮሳት እንደ ተጻፈው በቤተ መንግሥት ውስጥ ሆነው እንደ ቤተ ክህነት የሚኖሩ፣ በቤተ ክህነትም ሆነው እንደ ቤተ መንግሥት የሚኖሩ ነበሩ፤ አሉ፡፡ ይሁዳ በአካል ከክርስቶስ ጋር ነበር፤ ልቡ ግን ከነ ሊቀ ካህናት ቀያፋ ጋር ጌታን ለመስቀል ያድማል፤ ማርያም እንተ እፍረት በአካል ከአመንዝሮች ጋር ነበረች፤ ልቧ ግን ክርስቶስን ይፈልግ ነበርና ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፡፡ ይሁዳም ልቡ ወዳለበት ሄደ፤ ማርያምም ልቧ ወደ ነበረበት መጣች፡፡ ለመሆኑ ከሁለቱ ሰዎች መንፈሳዊው ማን ነበር?

በአንድ ወቅት አንድ አባት የተናገሩትን እዚህ ላይ ማንሣት ያስፈልጋል፡፡ ለስብሰባ ወደ አንድ መንግሥታዊ ድርጅት ሄጄ ከባለሥልጣናት ጋር ተሰብስቤ ነበር፡፡ በስብሰባው መካከል አንደኛው ባለ ሥልጣን በግእዝ ሲጠቅስ ሰማሁት፤ ተገረምኩ፡፡ ስብሰባው ሲያበቃ ጠብቄ ያንን ሰው «አንተ የቤተ ክህነት ሰው ነህ እንዴ? ቅድም አንድ ነገር ስትናገር ሰምቼሃለሁ» አልኩት፡፡ ሰውዬውም «አዎ ነኝ፤ ምነው ገረመዎት እንዴ» አለኝ፡፡ «የቤተ ክህነት ሰው እንዲህ ባለ ሥፍራ ይኖራል ብዬ አልገምትም ነበር?» ብዬ መለስኩለት፡፡ እርሱም «አባቴ የቤተ ክህነት ሰውኮ በየቦታው አለ፡፡ የቤተ ክህነት ሰው የሌለው ቤተ ክህነት ውስጥ ብቻ ነው» አለኝ ብለው ነገሩን፡፡

ዋናው መፍትሔው ይሄው ነው፡፡ የቤተ ክህነት ሰው በቤተ ክህነት እንዲያገለግል ማድረግ፡፡

እኔ በቀጣይ ማክሰኞ የማቀርባቸው ሃያ ዝርዝር የመፍትሔ ሀሳቦች  አሉ፡፡ የእናንተንም አስቡበት፡፡ ጊዜው አንድ ልብ ሆነን ለአንዲት እምነት የምንነሣበት ነውና፡፡


62 comments:

 1. በስመ ሥላሴ አሜን።

  ቃለ ሕይወት መምህር

  ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ አንባቢያን።

  " እያንዳንዳችን ...
  ቤታችንን ..
  ብንጠርግ ... ብናፀዳ
  አዲስ አበባችን ... ምን ያህል በፀዳ "
  * * * * * * * * * * * *
  የማይመስል ነገር ... የማይሆን ግርግር
  ... የቆሻሻ ክምር ...
  'ራሱ ቆሽሾ ሌላውን ሊያቆሽሽ ባሰፈሰፈ አገር።


  ይህችን ግጥም ቢጤ ፦ በአንድ ወቅት በመዲናችን በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክፍለሃገር ከተሞች ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኖ ለሰነበተና ለቅፅበት ታይቶ ለጠፋ የፅዳት ዘመቻ ነበር የሞነጫጨርኳት ...

  በወቅቱ የዘመቻ ባህሪይ ከሆነ ትኩሳትና ስሜታዊነት የተነሳ የከተሞችን ገፅታ በመቀየር ሒደት የተለያዩ እና ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራት ሲሰሩ እንደነበረ የብዙዎቻችን ትውስታ ነው። ... የሆኖ ሆኖ ወደ ዘመቻ የተገባው የህዝቡን አመለካከት በማሳደግ በኩል በቂ ስራ ሳይሰራ በመሆኑ የተጠበቀው አዲስ አበባን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብ ከፍፃሜ ሳይደርስ ... የአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህም በአዲስ አበባ ባምቢስ እና መገናኛ ድልድይ አካባቢየሚገኙ ቦታዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ... አምረውና ተውበው ለህዝብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አውርተን ሳንጨርስ ወደቀደመ የቆሻሻ መነኻሪያነታቸው ተመልሰዋልና ... እንዲህም ማለቴ በጊዜው የነበረውን መነሳሳት ፤ የዚህንም መነሳሳት ግምባር ቀደም ተዋናይ ፦ የአርቲስት ጋሽ አበራ ሞላን ዋጋ ለማሳነስ ( ቸርችል ቪውን የመሰሉ ምሳሌ የሆኑና ይበል የሚያሰኙ ስራዎች የዚህ መነሳሳት እሳቤ ውጤቶች ናቸውና ) ሳይሆን የህዝቡ የአመለካከት ለውጥ ዘመቻውን ሊቀድመው ይገባ ነበር ለማለት ነው። ...

  ዛሬም ታዲያ በቤተ-ክህነታችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ ከእኛ ከምእመናን የሚሰሙት የመፍትሔ ሀሳቦች በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔርን መንጋ ይጠብቁ ዘንድ በተሾሙ የቤተክርስቲያን መሪዎች ስር ፤ ሰማያዊውን መንግስት ተስፋ ስለማድረግ ምክንያት ስለሚኖር ክርስቲያናዊ ኑሮ ያለን አመለካከት በፅዳት ዘመቻው ወቅት እንደነበረው ያለ ደካማ ስለመሆኑ የሚያሳብቁ ናቸው። ... እርግጥ ፦ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ አስተዳደራዊ ችግር እንዳለ ከቤተክርስቲያኑ አመራሮች ተግባራት መረዳት ይቻላል ፤ ... ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ፤ በጎ ከሆነውም ፈቃዱ ፈቀቅ ከማለታቸው የተነሳ። ... ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳ አንድ አብይ ጥያቄ ደግሞ አለ ... ' ምን ያህሎቻችን መልካሙን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መረዳት እንችላለን? ' የሚል ...በተለይ ደግሞ ልበ-አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ " ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ " መዝ 142 ፦10 ማለቱ ፤ ፈቃዱን መረዳት ፦ 'ራስን የተወደደ መስዋት አድርጎ ከማቅረብ ጋር ወደ ፈጣሪ ሊፀለይበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ያመለክታልና ጥያቄው የበለጠ ከባድ ይሆናል። ... እንዲህስ ስለሆነ ፤ ከበደላችን የተነሳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የምንቸገር እኛ በቤቱ ለሆነው ችግር መፍትሔ እንዴት ሊታየን ይችላል? ... ከሁሉ በፊትስ ራሳችንን በጌታ ፈቃድ ስር ማኖር አይቀድምምን? ...

  ብዙዎቻችን እንደሰውሰውኛ መልካም ብለን ያሰብናቸውን እሳቤዎች ሁሉ አምላክም የሚወዳቸውና ቅቡል አድርጎ የመቁጠር የተሳሳተ አመለካከት ይታይብናል ... ይህንን ነጥብ በምሳሌ ለማየት በቅዱስ መጽሐፍ በ 1ኛ ሳሙ 8-15 ሰፍሮ የሚገኝን ታሪክ እናንሳ ፦ በእስራኤል ላይ ፈራጅ የነበረ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ኢዮኤልንና አብያን በእርሱ እግር ሾማቸው ፤ ልጆቹ ግን ረብ ( ጥቅም ) ለማግኘት ብለው ከእርሱ መንገድ ወጡ ፤ ፍርድንም አጓደሉ ... እንዲህም በሆነ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች እየሆነ ካለው ነገር የተነሳ ተጨነቁ ፤ ... አባታቸውስ እያለ እርሱ ይገስፃቸዋል እርሱ ካረፈ በኋላ እንዴት ያደርጉናል ብለው ...ታዲያ በነገሩ ብዙ ከመከሩ በኋላ ለነርሱ መልካም የመሰላቸውን ሀሳብ ወደ ሳሙኤል አመጡ ... ንጉስ አንግስልንም አሉት ... መልካም ያሉት ሀሳባቸው መዓትን እንደሚያመጣባቸው የሚያዩበት መንፈሳዊ ዐይን አልነበራቸውምና ... እግዚአብሔር አምላክ በሳሙኤል አማካኝነትይንግስልን ስለሚሉት ንጉስ ክፋት እንኳ እየነገራቸው መልካም ስላሉት ሀሳብ ፈፅመው አንሰማም አሉ ... እኛም ዛሬ ከቅድስት ቤተክርስተቲያን ቅንዓት የተነሳ የቤተ-ክህነት አስተዳደራዊ ችግር እንዲህ ቢደረግ ፣ እንዲያ ደግሞ ቢሆን ፣ እገሌ ቢነሳ ፣ እገሌ ደግሞ ቢሾም ፣ መንግስት ጣልቃ ቢገባ ፣ ... ይፈታል በማለት መላምቶችን ስንመታ እንሰማለን ... ታዲያ እዚህ ላይ ...' ቤተክርስቲያናችን እንዲህ በመሰለ ፈተና ውስጥ ሆና እኛ ልጆቿ አንዳች መላ መፈለጋችንን ነውር አድርገህ ማቅረብህ ነውን? ' ... የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው .... ነገር ግን ይህን ማለቴ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ " እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2 እንዳለ በነገሩ ውስጥ እጃችንን ከማስገባታችን አስቀድመን አካሔዳችን ምን መምሰል እንደሚገባው ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል ለማለት ነው።

  ምንም እንኳ ስለቤተ-ክህነት አስተዳደር በጥልቀት የማውቀው ነገር ባይኖረኝ ፤ ለመንፈሳዊ ዓላማ የተቋቋመና በመንፈስቅዱስ መሪነት የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ ተቋም እንዲህ ጊዜያዊ ችግር በሚገጥመው ጊዜ ፤ መፍትሔው ሊገኝ የሚችለው በእግዚአብሔር ፈቃድና ፣ እርሱ በሚወደው አካሔድ ፤ በመንፈሳዊ ሥልት ብቻ እንጅ በሌላ ከአለም በሆነ ዘዴ እና ምድራዊ ሀሳብ በበረታባቸው ሰዎች ጣልቃብነት እንዳልሆነ እምነቱ አለኝ። ... እንዲህስ ከሆነ ዘንዳ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ምንድን ነች? ... እንዴትስ እንወቃት? ... እርሱ የሚፈቅደው ፤ መንፈሳዊው አካሔድስ እንዴት ያለ ነው? ... ለሚሉት ጥያቄዎቻችን ሁሉ እኛ እርሱን ፈጣሪያችንን ከጉዳዮቻችን ፊት ማስቀደማችንን ፤ በጥቂቱ በመታመን ከገለጥን ወዲያ የሚመለሱልን ይሆናሉ!!! ... ያኔ የችግሩን መፍቻ ቁልፍ እናገኘዋለን!!! ... ከዚህም ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን መምህራን ትክክለኛውን ጎዳና ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበውን መንገድ በማመላከት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ሊወጡ ይገባቸዋል። ... እኛም በፅኑ መሻትና ፣ በበጎ ህሊና ወደ ፈጣሪያችን ልናመለክት ያስፈልገናል እላለሁ ፤ ደግሞም ስለራሳችን ብቻም አይደለ ... መንጋውን ሊጠብቁ ስለተሾሙትም ሁሉ እንጅ ... እንዲህ ማድረጋችን በራሱ ስለእግዚአብሔር ቤት እና ስለስርዓቱ ያለንን አመለካከት እና መረዳት ትክክለኛነት ያሳያልና ...

  የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የምህረት ፊቱን ይመልስልን።
  አሜን።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር።  23/11/2002Tromso, Norway

  ReplyDelete
 2. Egziabher yistilin,

  Ene be asteyayet yemisetut hasaboch beteley
  -Berta Dani,
  -Ketilibet,
  -Girum tsihuf new...etc
  malet asteyayet adelem. Eshi asteyayet new binilim enkua,bians bians yihe beteley Betekihnetin betemelekete yewetut tsihufoch le bizu sewoch yemidersubetin mengedoch mefeleg balen akim le policy awchiwim hone kin hasab lalachew wegenoch hulu endianebut ena ye gara hasab endiyizu maregu new ye egna ye anbabiwoch mina yemihonew.Alezia bravo Dani,...bilen bicha zim kalin min waga alen biye asibalehu.Gin enem bravo Dani biyalehu.

  ReplyDelete
 3. ዲ/ን ዳንኤል ሰላም ላንተ ይሁን።
  ክፍል ሁለትን በጉጉት ነበር የምጠብቀው ከጠበኩት በላይ እኔ በቤተ ክህነት ዙሪያ የነበረኝን አመለካከት በእጅጉ የለወጠ ሆኖ ነው ያገኘሁት። እግዚአብሔር አምላክ በፀጋ ላይ ፀጋ ይደርብልህ። አሁን አንተ እንዳልከው ጊዜው አንድ ልብ ሆነን ለአንዲት እምነት የምንነሣበት ነውና ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከመቼውም ይልቅ አንድ ልብ አንድ ሀሳብ ሆነን በእግዚአብሔር ቸርነት እና በቅዱሳኑ ምልጃና በረከት ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ጊዜ ነው። በቀጣይም ጥሩ ጥሩ የመፈተሔ ሃሳቦች ከአንባብያንም ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ። አኔም ወደፊት የምለው ይኖረኛል።
  ቸር ያሰማን።

  ReplyDelete
 4. we better wait for the next part but I simply say its superb

  ReplyDelete
 5. «የቤተ ክህነት ሰውኮ በየቦታው አለ፡፡ የቤተ ክህነት ሰው የሌለው ቤተ ክህነት ውስጥ ብቻ ነው»
  እግዚአብሔር ይርዳን

  ReplyDelete
 6. በስመ እግዚአ ኩሎ
  ዲያቆን ዳንኤል እንድምን ነህ፡፡
  ይህ ሃሳብ በሁሉም ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የሚገኝ ግን ያልተገለጸ ሃሳብ በመሆኑ ደፍረህ አምላክ በሰጠህ ጸጋ እንዲህ አሳምረህ በማቅረብህ የእውቀት አምላክ እውቀትህን ያብዛልህ እላለሁኝ፡፡መፍትሄ ሃሳቦችም ጥሩ ናቸው ግን ጠለቅ ብለው ቢገቡ፡፡በተጨማሪም ይህ ነገር እንዴት ወደተግባር እንቀይረው የሚለውን ሃሳብም ከመፍትሔዎች ጋር ብትገልጽልን ለምሳሌ በመንግስት በኩል ቤተክህነቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ምክንያቱም በጥናት የተደገፈ ችግሮች መፍትሔወቻቸው ለህዝብና ለሃገር የለው ጤቀሜታ ለመንግስት ቢቀርብ የሚደግፈውና ወደትግበራ እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል በተጨማሪም እንደአምላክ ፈቃድ በቅርብ አመታት ሀገራችን ወደ ጥሩ የሃብት ደረጃ ትገባለች ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን ይህን አሰራር ይዛ ከቀጠለች የግጭት መነሻ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ እናም መፍቴሔህን ይህን እድገት ታሳቢ ያደረገ ቢሆን እላለሁኝ፡፡ በተጨማሪም በስፋት ለመወያየት የጥሙራህን በአካል እንገናኝ የሚል ፕሮግራም ብታዘጋጅ በጣም ጠቃሚ ሃሳቦችን ለመሰብሰብና ተፅእኖ ለማሳደር ትችላለህ፡፡መሰረቱ ግን አምላክ ነውና ልቡና ይስጣችው እላለሁ፡፡
  በተረፈ አምላካችን ይህን ችግር ፈትተን ንፁህና ስርዓትዋን የተስተካከለች ቤተክርስቲያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ይርዳን፡፡
  ወስብሐት ለአምላክነ ወለ ወላዲቱ ድንግል

  ReplyDelete
 7. በእውነት ቃለ ህይወት ያሰላልን፡

  ውድ ወንድማችን ምን እናድርግ ቁጭት ብቻውን ዋጋ የለውም ወደ ተግባር ለመለወጥ ምን እንስራ?

  ከተስፋ ሱዱዳን ሰ/ትቤት አቡዳቤ

  ReplyDelete
 8. You thought,said and wrote samethings so many times.That is the very thing I would like to appreciate of you. I am not saying they were and are valueless but you have to wait to see the fruit (30,60 or 100).Pls keep it up and GOD be with you all the time as he was.

  ReplyDelete
 9. egezeabher amelak edmene ktena gar yestehe yehene setseflhe betam weste azno beneberebet seate new

  ReplyDelete
 10. "ጊዜው አንድ ልብ ሆነን ለአንዲት እምነት የምንነሣበት ነውና፡፡"

  አግዚአብሔር እንደዚ እንድንሆን ይርዳንና ለእኛ ግልፅ አድርጎ ለማየት እንዲመቸን መልካም እንጠብቃለን ግን ዳኒ የሆነ አዚም የተደረገብን አይመስልክም እሰቲ ከላይ ያሉትን ራሱ በደንብ እናስተውላቸው፡፡ቅድመ ተከተሉ ግን

  1/መንፈሳዊነት፡
  2/መረዳት፡
  3/መሳተፍ፡
  4/መሠዋት
  ሌላ ምንም አሳብ የለኝም ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete
 11. Hellow Dn. Daniel
  I really appreciate your four principles of "መ".
  Yared L.

  ReplyDelete
 12. Egziabher yibarkih lela yemilibet ewket yelegnm

  ReplyDelete
 13. Alawekeme mene enedemelehe egeziabehere yewekete ademasune asefeto yisetehe tebareke tebaki meleake yizezelehe enede hasabehe egname tesatafi honene ferewune lemayete egeziabehere yiredane

  ReplyDelete
 14. Oh God...
  Really very important message.
  i will wait your 20 solutions and i will try
  to put myself at least in one.
  Kalehiwot Yasemalene Dn. Daniel.

  ReplyDelete
 15. We will wait the 20 detailed solutions,thank you D.n Daniel Kibret. All Ethiopian Orthodox tewahido belivers will work together.

  May God save our Church.

  ReplyDelete
 16. Thank you Dn. Danel, here we are coming to the solution and we are understanding what to do and from where we should start.

  Blessings

  ReplyDelete
 17. hi dani it is nice view

  habtamu aware

  ReplyDelete
 18. woow d.dani this is really Amazing, now we have to fight our Enemies.

  ReplyDelete
 19. መልካም እይታ ነው:: እግዚአብሔር የቅድስት ቤተ ክርስትያናችንን ትንሳኤ ያቀርብልን ዘንድ ጸሎቴ ነው:: ድካምህን ለሚበልጥ ጸጋ ያድርግልህ!

  ReplyDelete
 20. በጣም ግሩም እይታ ነው። ቃለ ህይወት ያሰማልን። "ችግርን በሚገባ መረዳት የመፍትሔው ግማሽ አካል ነው" ይባላልና ባለንበት ዘመን ከምናያቸው የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የተነሳ የምንይዘውን የምንጨብጠውን አጥተን ለምንቃጠል ምን ማድረግ እንዳለብን በ 4ቱ "መ"ዎች የተጠቃለለ ምክር ሰጥተኸናል። ወደፊት የምታስነብበንን የመፍትሔ ሃሳቦች ለመተግበር አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው የቤተክርስቲያን አስተዳደር ተሳታፊ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የለውጥ ተቃዋሚዎች ብዙ ናቸውና አሁን ያለው አሰራር ከተመቻቸው ግለሰቦች ሊመጣ የሚችለውን ተቃውሞ ለመቋቋም በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። በተለይም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ምዕመናን የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር አሁን ያለበትን አስከፊ ሁኔታ ተገንዝበው ይህም እንዲሻሻል ባለስልጣናቱ ለለውጥ መዘጋጀት እንደሚገባቸው ማሳየት ይኖርብናል። ምዕመናን እስካሁን በዝምታ ስንመለከት ቆይተናል። ከዚህ በላይ ዝምታ የት እንደሚያደርሰን መገመት ከባድ አይደለም።

  ReplyDelete
 21. I think the four possible solutions are the best and basic for our holy church.Once we are willing to take a step to fulfill all possible or suggested solution, the remaining will be left for God. There is a saying that runs as " If it is God's will, it is God's bill".

  May God Bless you.

  ReplyDelete
 22. I was expecting this,We really needed the analysis and a discussion on the remedies. Taking temporary and narrow scoped measures will not provide us a consistent solution.
  Our church has highly preserved the spirituality and Grace of the Holy Spirit,which nobody did.But we need now to work on the managerial and educational structure to succeed in having a transparent and fair system of providing service.Evenif we have no idea how our thoughts would play the role in the near future,it concerns each of us.We Belong to God and this Church who has kept us on the right track.
  With ur motivation I take my assignment.

  ReplyDelete
 23. ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ከክፉ ይጠብቅህ እኔ ካህን ነኝ ግን እስካሁን በምሰማው በማየው ከማዘን ባለፈ የመፍትሔው አካል ለመሆን አስቤም አላውቅም ነበር አሁን ግን ነቅቻለሁ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋቻለሁ << ንቃህ ዘትነውም ወተንሥእ እሙታን ወያበርህ ለከ ክርስቶስ>>

  ReplyDelete
 24. ምነው ዳኒ ባትጀምረው ብዬ ነበር። ሳትጨርሰው ወዴት መጣህ ክፍል ሁለትን ሳታሳየን
  ሌላ ክፍል ሶስት ። ሆነብኝ ይሄ ። ወይስ ቀዳማቂ ቃል ብሎ ወንጌሉን ጅመሮ በመልአኩ
  የጀመርከው የማትጨርሰውን ነው የታባለውን ሆነብህ? ሊሆን ይችላል በአንድ ወቅት አ
  ዲሱ መንበረ ፐትርከና ሲሰራ አንድ ምዕመን አንድ ብር የሚል መርሐ ግብር ተነድፎ ነበረ
  አስፈጻሚዎች በአገሪቱ ያሉ ካህናት ነበሩ። ገንዘቡ ቢሰበሰብም ለምን እንደዋለ ግን ግልጽ
  አልነበረም። በፓትርያሪኩ ስም የሚነግዱ ዘመዶቻቸውና ግብር አበሮቻቸው የውሃ ሽታ ።
  አድርገውታል ። ታዲያ ጉዳዩ ቀስ በቀስ መንግስት ጋር የደርሳል ወቅቱ ሙሰናን በሃገሪቱ ሚዲያ እየተወገዘ ያለበት ሰዓት ነበር። ከመንግስት አካላት ጉዳዩን የሚከታተሉ ተመደቡ
  ገና ማጣራቱን ከቤተ ክህነት ሲጀምሩ ብዙ አይን ያወጣ ዝርፊያ ከትላልቅ አድባራት ጸሐፊዎች ጋር ባለ ግንኙነት ተፈጽማል።
  ተባባሪ የሆኑ ሁሉ ከሥራቸው እንዲነሱ ጫና ተደረገና ተነሱ። የዋናውም የቅርብ ቤተ ሰቦች ከተባረሩት ውስጥ ይገኛሉ።
  ገና ሲጀመር ብዙ ጉድ የታየበትና በቀላሉ ሊታለፍ የማይችል የማይፈታ መሆኑን ያዩት አጣሪዎች የታዘዙትን ሳይጨርሱ ለጠቅላይ ሚንስቴሩ ለመለስ ዜናዊ ሪፖርት ሲያቀርቡ በሉ
  ከዚህ በላይ የተከደነው ቢከፈት ሽታውና ክርፋቱ እኛንም ላያስቀምጠን ይችላልና እዛው እንደተዘጋ ይቆይ ጊዜ ይፈተዋል ማለታቸው የነገር ነበር ። ጅማሬ መልካም ነበር ከባድ
  መሆኑን አዩት ብዙዎች የሚያነካካ ሆ ኖ ተገኝቶልና ። ዳኒም በአንደኛው ክፍል ጀምረህው ነበር ግን ,,, የጠቅላይ ምኒስቲሩ አመለካከት አንተም ጋር መጣ መሰለኝ መቼስ ምን ይደረግ እርሳቸው እንዳሉት የቤታችንን ጉዳይ ጌዜ ብቻ ሳይሆን የቤቱ ባለቤት የፈተዋል ።
  ብርታቱን ያድልህ።

  ReplyDelete
 25. +++ Kalehiwot Yasemalin Dn. Daniel,
  "አንዳንድ ጊዜኮ እኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለን፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ከእኛ ውስጥ ወጥታለች፤ እኛ በክርስትና ውስጥ ነን፤ ክርስትና ግን ከእኛ ውስጥ ወጥቷል፤እኛ በክህነቱ ልብስ ውስጥ ነን፤ ክህነቱ ግን ከእኛ ውስጥ ወጥቷል፤ እኛ በስብከቱ ቀሚስ ውስጥ ነን፤ ስብከቱ ግን ከውስጣችን ወጥቷል፡፡ እኛ በገዳም እንኖራለን፤ ገዳማዊ ሕይወት ግን በኛ ውስጥ የለም፡፡ ለአንዳንዶቻችን ጵጵስና ፕሮፌሽን ነው፤ ቅስና ፕሮፌሽን ነው፣ ሰባኪነት ፕሮፌሽን ነው፤ ምንኩስና ፕሮፌሽን ነው፤ዝማሬ ፕሮፌሽን ነው፣ እንደ ጥብቅና፣ እንደ ንግድ፣ እንደ ሕክምና፣ እንደ ጋዜጠኛነት፣ እንደ ምሕንድስና፣ የእንጀራ ማግኛ ሞያ፡፡ ታድያ እንዴት መንፈሳውያን መሆን ይቻላል?"
  Hulachin Binistekakel wodefit Menfeswi Sew tetki tiwulid mafrat yichal neber! Neger gin Yeterkabi tiwul negerim manim asibobet ayawukin "enae kemotihu Sar ayibkel alech ..." endemibalew Enibla enteta nege enmotalin begna bekirstiyanoch eyetesebeke new zarae!!!

  Yekidusan Amlak yirdan

  ReplyDelete
 26. ይገርማል ጥሩ የምፍትሄ ሀሳብ ነዉ ያቀረብከዉ ቀጣዮቹንም በጉጉት እጠብቃለሁ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ መንፈሳዊ ኮጅሌ ለመግባት መስፈርቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ስለምፈልግ ብትነግረኝ

  ReplyDelete
 27. This is one of the solution “ goro lebalebetu bada new” those people in the position trying to lead our church. let if some one have access to them let to log in danielkebret.com may be one day they will learn some thing from him.
  Mamo.

  ReplyDelete
 28. ወንድሜ ዳንኤል፡

  ከአምላካችን ከእግዚአብሄር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ጸጋ ላንተ ይሁን፡፡

  ክፍል ሁለትን በተጣበበ ጊዜ ውስጥ አነብቤ ጨረስኩት፡፡ ሰሞኑን ውስጤን እያደማ ያለው ነገር እረፍት ነስቶኝ ነበርና፡፡

  ዝርዝር የመፍትሄ ሃሳቦችህን ሳላይ ብዙ ማለት አግባብ አልመሰለኝም፡፡ ይሁን አንጂ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ግን ጥቂት ወኔ አላጣሁም፡፡

  በቅድሚያ-

  • አካፋን አካፋ ማለት የጀመርክ መሰለኝና ስጋት ብጤ ገባኝ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‘ደማቸው መራራ ነው” ምናልባት አንተም፡፡ የቀድሞዎቹን ደግዬ አባቶች ሚና በመጠቀስ … ቤተ ክህነት ዛሬ ለጋዜጠኛ መልስ ለመስጠት የሚበቃ ሰው እያጣች መምጣቷ የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል፡፡… ያልከው አነጋገር ለጠላት በር ይከፍት ይሆንን.. እኔ ግን በሃሳብህ በጣም እስማማለሁ፡፡
  • እንዲሁም …ከ45 ሚሊዮን በላይ ምእመን አላት፤ ነገር ግን ከ3000 በላይ የሚታተሙ መጽሔት እና ጋዜጦች የሏትም… ያልከው ነገር ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰሉ ማህበራት ያላቸውን አስተዋጽኦ ከግንዛቤ ውስጥ ጨምሩዋል ወይ… ወይስ እነርሱን ከቤተ ክህነት (ከቤተ ክርስቲያን አላልኩም)ለመለየት የተጠቀምክበት አገላለጽ ነው፡፡ èዳህን እንዳትረሳው …
  • …እናም እነዚህ በሽታዎች በአጠቃላይ መልኩ የሚፈታ፣ ምንጫቸውን የሚያስተካክል ነገር ካልመጣ በቀር፣ እንደኔ እምነት ሰዎችን በመቀያየር ብቻ የቤተ ክህነቱን አሠራር ውጤታማ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመጥን ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፡፡… ያልከው ነገር በመሰረቱ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ምንጩ ችግር የለበትም.. ነካከታችሁ አታደፍርሱብኝ ..የሚል ሰው በቦታው ከተቀመጠ (ከአለ) ሰዉን መቀየር ቁልፍ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፤፤ አንተም በጸሁፍህ እንደገለጽከው አሁን በቦታው የተሰገሰጉት ሰዎች እነማን ናቸው ብሎ ማሰብ የግድ ይላል፡፡ መቃውና (ብዕሩና) ማህተሙ ያለው በነዚህ ሰዎች እጅ ከሆነ… እንዴት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል?! እዚህ ይ ግን መስማማት ይገባናል ቢዬ አምናለሁ፡፡ ባንስማማም ችግር የለም፡፡ አለመስማማት ደምና ስጋችን እየሆነ ነውና፡፡


  ጣለው ነኝ
  ከወደ ምስራቅ

  ReplyDelete
 29. ዳኒ አምላክ አብዝቶ ይባርክህ ሁላችንም በዚ ጉዳይ ሱባኢ እንግባ እባካችሁ እባካችሁ

  ReplyDelete
 30. "በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።

  በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤

  ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ " ፊል1:27

  ReplyDelete
 31. Kale hiyyyyyyyyywot yasemalin!!! yemitebekibinin endinaderg amlak yirdan!

  ReplyDelete
 32. Hi Dani,
  Ejig betam yerekahubet tsihuf new. Egziabhere tsegawun yichemirilih.
  Menager yemifeligew and neger bicha new: bezih alem yeteleyaye sewu ale. Andandu nechun tikur malet yemiwod andandu demo yerasu yehone yetifat teliko yalewu yinoral. Enam bewudasem satitabey, bemetifo negerim tesfa satikorit yejemerkewun neger atibikeh ketil. Ene endakime begenzebim hone bemuya contribute lemareg gin kal egebalehu.

  tsegawun yabizalih

  ReplyDelete
 33. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 34. selam dnani, betam tiru ,bene asteyet betcrtsyan(our church)ante yaneshawen neteboch lemetegber wdehola yemayelu sewech yemetefu aymeselgme chegeru gen enzeh sewech endet tesesebasbew hibret mefter yichelalu hegewetoch hegawi behonubet astedader weste endet meserat yicallale. chegerun mawek ande neger hono wedmfthew endet enhed? legezew yalegen mfthe wode dageaw Leul Egzabher malkes bech new. "Egzabeher hoy ebakhen wede egana eye"negede, nevada

  ReplyDelete
 35. በአሁኑ ጊዜ በእውነት ልቤ የሚናፍቀው እና
  የሚፈልገው ለአህዛብና ለመናፍቃን አሳልፎ
  የሰጠንን እና አሳፍሮ መልስ ያሳጣንን የቤተ ክህነት
  አስተዳደር ችግር ተቀርፎ ማየት ነው እና ሁላችንም
  አስተያየት ከመስጠት እና ከማማት ወጥተን
  የቻልነውን የምንስራበት ጊዜ እየቀረበ ነውና
  እንንቃ፡፡እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ ዲ. ዳንኤል ስላንተ
  የምለው የለኝም፡ የምመኝልህን ሳይሆን የሚያስፈልግህን
  እመብርሃን ታድርግልህ!፡፡ በተረፈ ይህን የመሰለ
  የመፍትሄ እና አስተማሪ ሀሳብ(ጹሁፍ) የኢንትርኔት
  አክሰስ ላላቸው ብቻ ስለሚውል እንደቀድሞ በጋዜጣ
  ቢወጣ መልካም ነው ብዬ አስባለው፡፡

  ReplyDelete
 36. ዲ/ን ዳንኤል ሰላመ እግዚአብሔር ካንተ ጋር፣ ከአንባቢወችህ ጋርም ይሁን።
  በምንሰማውና በምናየው ነገር ሁሉ ውስጣችን በተቃጠለበት፣ ባዘነበትና መፍትሄው ምንይሆን እያልን ግራ በተጋባንበት ወቅት አንተን የመሰለ ባመነበት ጉዳይ ላይ ፊት ለፊት ወጥቶ በቤተ ክርስቲያናችን ያለውን ችግር እስከ መፍትሄው የሚጠቁም ሰው ማግኘታችን እንዴት ትልቅ ነገር መሰለህ? እግዚአብሄር ይስጥህ።
  ጉዳዩ እስከነ ችግሩ እንዲኖር የሚፈልጉ በጉያዋ ውስጥ የሚኖሩ፣ ጉዳዩ ሲነካካ እንደ እብድ የሚያደርጋቸው፣ የጥቅም መሰረታቸው ከችግሩ ጋር የተቆራኘ ሰወች እንዳሉ ለሁሉም ግልጽ ነው። ከእነዚህም እግዚአብሄር ይጠብቅህ።
  ሁሉም ወደ ስራ መግባት ስላለበት ግን ቢያንስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን እንደዚህ የመሰሉ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግሮች እስከ መፍትሄ ጠቋሚነት የሚዘረዝሩ ጽሁፎች ከተለያዩ ድህረ ገጾች በሚቻለው መንገድ (በኢሜል፣ በፌስ ቡክ፣ በበራሪ ጽሁፍም ሆነ በሌላ መልኩ) በተለይ ሃገር ቤት፣ በስደት በምንገኝበትም አለም እንዲዳረስ ማድረግ ብንችል። እኔ ከነጓደኞቼ ይህንኑ ስራ ጀምረናል። ኢንተርኔት ለማግኘት ለማይችሉም የቤተ ክርስቲያኒቷ መሪወችም ቢሆን ማዳረስ ብንችል።
  ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ጸጋ አይለየን።

  አቤ ነኝ ከምስራቁ አሜሪካ።

  ReplyDelete
 37. Dn Daniel,
  Can you collect all these articles and publish it. Your one article is better than this time's books....
  Egziabher Birtatunina Teninetun Yistih

  ReplyDelete
 38. አየ ዳኒ የችግሩን መፍትሔ ለመፈለግ መነሳት የኛ መፍትሔ መስጠት የእግዚአብሔር ታላቅ ጥቅስ ታድያ ሁሉ እንዳንተ አያስብ !!

  ReplyDelete
 39. Daniel your "afewerk" for the next generation. God may always give u strength to speak the truth and help your church. I wish people like u (if there are more) have a place in bete kehenet.

  ReplyDelete
 40. it is very touching article i also to say something being Christan means being Jesus Christs
  so we should be practical not just follows of rules. yes i believe that we should be together and find the solution spiritually.

  ReplyDelete
 41. Zelafto DebretiguhanAugust 4, 2010 at 10:45 AM

  D.N, Kalehiwot Yasemalin. Ene Gin Eski Mejemeriya erasachinin enfetish new yemilew. Be ewnet Le Kiristos endemigeba eyenorin newen? bilen enteyik.Lerasachin hiwot subae enigba. Keza behuala Egziabher legna yemiyasfeligenin Yisetenal(Tiru Eregnochin Chemiro malet new) yetamene Amlak newena.

  CHERNETU YIRDAN,AMEN.

  ReplyDelete
 42. እንደእኔ እንደእኔ ዐራቱን የ “መ” ሕጎች በአንድ አስፈላጊ ነገርግን ጨርሶ ባጣነው ሌላ የ “መ” ሕግ ላይ የሚመሠረቱ ይመስለኛል፡፡ እርሱም መስማት ነው፡፡ ለመንፈሳዊነቱም፣ ለመሳተፉም፣ ለመስዋዕትነቱም ለመረዳቱም መጀመሪያው እርሱ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡

  ምናልባት እዚህ ላይ “ማንን እናድምጥ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ እኔ ላሉብን ችግሮች ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ማድመጥ እመርጣለሁ፡፡

  ሀ. በቅዱስ ቃሉ ዘወትር የሚናገረንን እግዚአብሔርን
  ለ. በመንፈሳዊ ብርታታቸው ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ያለፉና እገለገሉ ያሉ አበውን፣ አኃውንና አኃትን
  ሐ. አብረውን ያሉ ወንድሞቻችንን

  በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት በኖረው ራስ-በቅ ሥርዓት (Autocratic system) የተነሣ ይመስላል የበላዮቻችንን እንጂ አቻዎቻችንንና የበታቾቻንን የማድመጥ (እረኛ ምን ይላል እያሉ የመሰለል አላልኩም፡፡) ባህል የለንም ብል ሳይቀል አይቀርም፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ችግሮች ሲፈጠሩ የምንወያየው “መፍትሔ ይሰጠናል፡፡” ብለን ከምናስበው የበላይ አካል ጋር ወይም የበላዮቹ እኛው ከሆንን ደግሞ ከተከበረው እኔነታችን ጋር ሲሆን የሚታየው፡፡ አቻን ማድመጥ ውርደት፣ ታናናሾችንም መስማት የቅስም መሰበር ምልክት አድርገን የምናየው ይመስለኛል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ያለው የማኅበረሰባችን መዋቅር በቁጥጥር እንጂ በንግግር ላይ ተመሥርቶ አላየሁትም (ለተጨማሪ ሐሳብ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በኢኮኖሚክ ፎከስ መጽሔት ላይ የታተመለትን ንግግሩን ማበብ ጠቃሚ ነው፡፡) ቁጥጥር ደግሞ ብዙውን ጊዜ የጠብና የክርክር እንጂ ዘላቂ የሥርዓት ምንጭ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ሕይወት ትምህርት ቤት መሆኗን ብናምንም የትምህርት ውጤቱ ለውጥ (አንዳንዴ ሥር ነቀል) እንደሆነ መቀበል የሚቸግረንም በዚሁ ከማድመጥ መደመጥን በሚመርጠው ሶፍትዌራችን (“ባህል የአእምሮ ሶፍትዌር ነው፡፡” እንዲሉ የባህል ሊቃውንት) የተነሣ እንደሆን እጠረጥራለሁ፡፡ በተራዛሚው ስናስበውም የዚህ ባህል ውጤቶች የሆኑት ጳጳሳትም ይሁኑ የሀገር መሪዎች ሶፍትዌራቸው በዚህ መንገድ ሲመራቸው ቢታይ አይደንቅም፡፡
  በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊው የሕይወት አነዋወራችን ብስለትን ሳይሆን ዕልቅናን የመፍትሔ ምንጭ አድርገን በመውሰዳችን የተነሣ ብርቱ ነቂሳዊ አስተሳሰብ ያላቸውን አሳቢዎቻችንን ለማስተናገድ ፈቃደኞች አይደለንም፡፡ ለየትኛውም ሰው ሁለት ጎራ እያበጀን “ወይ ከእኛ ወይ ከእነርሱ!” የሚል አካኼድ ይቀናናል፡፡ ከእኛ ጋር ያልሆነውንም ለማሳመን ሲያቅተን ከማድመጥ ይልቅ በጠላትነት ፈርጆ መደፍጠጥ ይቀናናል፡፡ ቤተክህነትን ቤተትክነት እስከመባል ያደረሳትም ይኸው ነቂሳዊ አስተሳሰብን በነቂሳዊ አስተሳሰብ ሳይሆን በኃያል ቃላት ውርዋሮና በሰይፍ የመደፍጠጥ ከነገሥታት የተወረሰ አባዜ ነው- መቼም የሐሳብ ነጻነትን ካጎናጸፈን ልዑል አምላክ የተገኘ አይሆንም፡፡ አለቆቻችን ምንም ያህል ክፉዎች ቢሆኑ አለቆች ስለሆኑ ብቻ እደ ትኩስ ሥጋ ተንቀጥቅጠን እንደ ብረት ተቀጥቅጠን እንገዛለን፡፡ ይህም የአቻዎንንና የብስል አሳቢዎቻቸንን ብቻ ሳይሆን ዘወትር በቅዱስ ቃሉ የሚናገረንን እግዚአብሔርንም እንዳንሰማና በከንፈራችን ብቻ የምናከብረው እንድንሆን አድርጎናል- ልቦቻችን ለአለቆቻችንና እንደሰው ሳይሆን እንደ መንጋ ለሚነዱን ማለቂያም ለሌላቸው ክፉ ፍላጎቶቻችን በመንቀጥቀጥ በመገዛት “ቢዚ” ናቸውና፡፡

  ስለዚህም መፍትሔዎች ሁሉ አቻዎችን፣ ብሱላንንና እግዚአብሔርን ከመስማት ሊጀምሩ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ “ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” እንዲል ወንጌል፡፡

  ReplyDelete
 43. በሰመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
  ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር አምላክ ጸጋህን ያብዛልህ መቼም የቤተ ክህነት የአስተዳደር እና ሌሎች ችግሮች ቢነገር አያልቅም አንተ እንዳልከው ዳኒ 4 ቱን የ‹‹መ›› መፍትሔ ይዘን ያለፈውን ትቶ ለመፍትሔ መገስገስ ይሻላል ቸግሮቻችንን ተረድተን ሁላችንም ተረባርበን ስለሃይማኖታችን በመቆርቆር በፍጹም መንፈሳዊነት እና ቅንነት በተሞላበት አሰራር በማገልገል ቤተክርስቲያናችንን ከውርደት መታደግ አለብን እግዚአብሔር ይርዳን. ተክለማርያም

  ReplyDelete
 44. igzi'abher bechernetu yimelketen lela min ybalal
  ahun ahun be bebete chrstianachin yemideregu negeroch ahzab inkuwan ayadergutm.
  dn dani ingdi min yibalal yemibalewn alkew igzi'abher beseteh tsega.
  igzi'abher beneger hulu yibarkih

  ReplyDelete
 45. Thank you dani,

  I can not write any thing , I have preferred silence,

  ReplyDelete
 46. I read the article. It is fine and as one of the readers commented most of the points raised are not new for most of us.
  No one will expect to get all these problems solved over night. So the question will be 'Where shall we start?' in addressing the problems.
  In my view, the followers of the church are not complaining because the church have no modern organization or management. Rather spirituality of the fathers is what matters. If it was simply lack of modern knowledge the solution will be very simple but that is not the case. Do we have the right spiritual leaders? that is what we need to ask. If we get that the other problems will be solved gradually.
  So the focus must be on 'where to start the change????????????'
  May God, the almighty , show us the renascence of our church.

  ReplyDelete
 47. I AM LIDETU DAGNE from KIRKOS ,
  i am attending your essay every week and it is interesting.I and my friend deacon TESHALE DOCHE like it.KEEP IT UP

  ReplyDelete
 48. LIDETU DAGNE FROM KIRKOS
  DANY your articles are interesting i read it together with my friend Dn.TESHALE

  ReplyDelete
 49. ማክሰኞ ኛፈቀኝ

  ReplyDelete
 50. lidetu dagne from kirkos
  it is interesting issue keep it up

  ReplyDelete
 51. ዘ ሐመረ ኖህAugust 4, 2010 at 5:28 PM

  በስመ ሥላሴ ፩ዱ አምላክ አሜን
  የእግዚአብሔር ሰላም ለዲ/ዳንኤልና ለመላው እድምተኞቹ ሁሉ ይሁን አሜን
  ከዳዊት አብራክ ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ
  አዳም በሲኦል በኖረ በውርደት አንገቱን ቀብሮ ...
  ዛሬም እግዚአብሔር እነደ ዲ/ዳንኤልና መሰል ወንድሞችን በዚህ በቀውጢ ዘመን ባያስቀርልን ኖሮ እያንዳንዳችን ወደራሳችን እንድንመለከት የመፍትሄ አካልም አንድንሆን የሚያዘጋጁን ወንድሞች ባያስቀርልን ኖሮ እየጠፋ ያለውን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንና የውስጥ አስተዳደር እንዲሻሻል አጠቃላይ የቤተ ክህነትን ችግር ከነመፍትሄው የሚያቀርቡልንን ወንድሞች ባያስቀርልን ኖሮ ወንጌል እንዲስፋፋ እምነታችንና ታሪካችን ከኛ አልፎ በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ እያደረጉልን ያሉትን ወንድሞች ባያስቀርልን ኖሮ እንደተዋረድን ግራ ገብቶን እንደማንቀር ተስፋ የሚሰጡንን ወንድሞች ባያስቀርልን ኖሮ የሚጠብቀንንና የሚያሰማራንን እረኛ እንዳጣንና በየዱሩ ተበትነንም እንደማንቀር ተስፋም መጽናኛም የሆኑንን ወንድሞች ባያስቀርልን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር ? እግዚአብሔር ሠማያዊውን ዋጋ ይክፈላችሁ ከክፉ ሁሉ ጠብቆ የምታስቡትንና የምታደርጉትን ሁሉ ያሳካላችሁ አሜን ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክብር

  ReplyDelete
 52. Selam Daniel

  Looking forward to hear the 20 solutions! አሳብ በምክር ትጸናለች፥ በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ። ምሳሌ 20:18
  Dearest I am spiritually poor ethiopian fellow. But I always think there is something I can contribute...I never dared to participate in any ministry except the custom going and coming to church. Your idea has encouraged me...may be this will open opportunity for me and other expats to work on something significant. Please share us your ideas.
  Prayerfully yours!

  ReplyDelete
 53. hello dani,

  this is another interesting issue, ene yemilew gin hulachnim sile betekerestiyanachin yeminaseb ena yeminikoreker "could u please start praying? be ezeh binijemer "filesetan" subaye biniyez?"

  egziabher yiredam

  weladite amelkam ateleyen

  "Ethiopia enjuchuan wede egizabher tizeregalech"

  amelak yitadegen

  amen

  ReplyDelete
 54. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡
  ይህ የመፍትሄ ሐሳብ ግን አብዛኛው ምእመን እንዲሰማውና ሁሉም በአንድ ልብ እንዲነሳ ነጻ የሆነና ለሁሉም የሚዳረስ ጽሁፍ የሚዘጋጅበት መንገድ ቢፈጠር የሚል ሀሳብ አለኝ ፡፡
  በተረፈ ሁላችንም ለእኔ ብለን እንስማ፡፡

  በእርሱ መመስረቷን አካሉ መሆኗን
  በእርሱ ደም መዋጀት በእርሱ መገዛቷን
  ፈተና ቢበዛም በእሳት ውስጥ ማለፏን
  እንደሚጠብቃት እንደሆናት አጥር
  እንደምትታሰብ እንደሚያያት ዘወትር
  የሰጎኑ እንቁላል መስቀሉ ይመስክር፡፡

  ReplyDelete
 55. .....ተንስኡ ለፀሎት!

  ReplyDelete
 56. May God Bless You!!

  ReplyDelete
 57. the one you writing as Eyob G please stop to write such unclear message

  ReplyDelete
 58. I also would like to say keep it up. But I don't have any comment because I know nothing about our church.your message makes me alert.

  ReplyDelete
 59. ቃለ ሂይወት ያሰማልን !! እግዚአብሄር በእድሜ በጤና በፀጋ ይጠብቅልን!! ብዙ ቁምነገሮችን አግኝቼበታለው የሰማውትን እንድኖርበት እግዚያብሄር ይርዳኝ፡፡

  ReplyDelete
 60. Egziabeher kale hewotenn yasemalen lehezbachenm lhagerachenem lekedest betekerstianachenem yemibejewn gize yametalen hulachen bezih bthomachen gize selaehulum negere abezethen methely aleben. Yedengel Maryam amalagenet ye Egziabeher cherent khulachen gara yehun Amen.

  ReplyDelete