ሁለት መኪኖችን ብቻ አጨናንቃ የምታሳልፍ መንገድ ነበረች፡፡ ሁለቱ መኪኖች ሲተላለፉ ጎንና ጎናቸው ሊነካካ ለጥቂት ብቻ ነው የሚያመልጡት፡፡ ነገር ግን ሾፌሮቹ ሁሉ ለምደውታልና በቀላሉ ፈገግ እያሉ ይተላለፋሉ፡፡
አንድ ቀን አንድ ለምድር ለሰማይ የከበደ ወፍራም የትራፊክ ፖሊስ መሐል መንገድ ላይ ቆሞ በግራ እና በቀኝ የሚተላለፉትን ተሽከርካሪዎች «እለፉ እለፉ» ይላል፡፡ መኪኖቹ መተላለፍ ስላልቻሉ ከሚሄደው የሚቆመው በዛ፡፡ በተለይማ ትልልቆቹ የጭነት መኪኖች መተላለፍ አልቻሉም፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ ግራ ገባው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም እንኳን መንገዱ ጠባብ ቢሆንም እንደዚያ ቀን ያለ መጨናነቅ ግን ታይቶ አይታወቅም፡፡ መኪኖቹ ቀስ ይሉ ይሆናል እንጂ አይቆሙም፡፡