Saturday, July 31, 2010

ቅኝ አልተገዛንም?


አባት ሁልጊዜ ለልጁ ስለ ሀገሩ ታሪክ እና ወግ ይነግረዋል፡፡ በተለይም አንድ ነገር ደጋግሞ ያነሣለት ነበር፡፡ «ኢትዮጵያ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ተለይታ ቅኝ ያልተገዛች፣ራስዋን ችላ የኖረች ሀገር ናት፡፡ የራስዋ ፊደል፣ የራስዋ የዘመን አቆጣጠር፣ የራስዋ ባሕል ያላት ናት» ይለዋል፡፡ አንድ ቀን ታድያ ልጁ ጥያቄ አነሣ፡፡ «ኢትዮጵያ ግን በእውነት ቅኝ አልተገዛችም የሚል፡፡ እናም አባቱን መሞገት ጀመረ፡፡
«አባዬ ግን በእውነት ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ቅኝ አልተገዛችም? ወይስ ለሞራሌ ብለህ ነው ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ናት እያልክ የምትነግረኝ» አለው ልጁ፡፡
አባትዬውም ደንግጦ «ምነው ልጄ ምን አዲስ ነገር ተገኘ? ይህኮ እኔ የፈጠርኩት አይደለም፡፡ ዓለም በሙሉ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ የትኛውንም መጽሐፍ አገላብጥ፣ የትኛውንም ሊቅ ጠይቅ፣ ይህንኑ ብቻ ይነግሩሃል» አለው፡፡
ልጁም «ይህ ከሆነማ ሆኗል ተብሎ የሚታሰበውና የሚታየው ነገር ይለያያል» አለው፡፡
«እንዴት ማለት» አለ አባት፡፡
 
«ኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛቷ ሆኗል ተብሎ የሚታሰበው ነገር ነው፤ የሚታየው ነገር ግን ቅኝ ተገዝታ የኖረች ብቻ ሳይሆን አሁንም ቅኝ እየተገዛች መሆንዋን የሚያሳይ ነው» 
አባት ግራ ገብቶት ልጁን ትኩር ብሎ አየው፡፡ «መቼም የዛሬ ልጆች ተፈላሳሚዎች ናችሁ፡፡ የማታመጡት ነገር የላችሁም፡፡ እኛ አሜን ብለን የተቀበልነውን ነገር ሁሉ መጠራጠር አመላችሁ ሆኗል፡፡ ምን አግኝተህ ነው ይህንን ያልከው ሲል ጠየቀው፡፡
«ለምሳሌ በቀደም ዕለት እኔና አንተ እዚያ ቢሮ ሄድን፡፡ ታስታውሳለህ አለው ልጁ፡፡ «አዎ እና ምን ተፈጠረ አለው አባት፡፡
«በር ላይ የተፈጠረውን ታስታውሰዋለህ ልጁ መልሶ ጠየቀ፡፡
«ምን ተፈጠረ? ተፈተሽን ገባን፡፡ አለቀ» አለው አባት፡፡
«በጣም ጥሩ እኔ እና አንተ ተፈትሸን ገባን፡፡ ከእኛ አጠገብ የነበረው ፈረንጅ ግን ሰላምታ ብቻ ቀርቦለት ገባ፤ ለምን? እኔ እና አንተ ግብር ከፋይ የዚህች ሀገር ዜጎች ነን፡፡ እኔ እና አንተ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፈሰሱ እያልን ዘወትር የምናነሣቸው አባቶቻችን ልጆች ነን፡፡ ነገር ግን እኛ አንታመንም፤ ስለዚህ ተፈተሽን፡፡ ፈረንጁ ግን ታማኝ ነው፤ እናም ሳይፈተሽ በጥሩ ፈገግታ ገባ፡፡ እኛ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ ተብለን እንጠረጠራለን፤ ፈረንጁ ግን ንጹሕ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
«ሆሆ» አለ አባት፡፡ «እና ይሄ ከቅኝ ግዛት ጋር ምን አገናኘው
«ቆይ ቆይ ታገሠኝ፡፡ እዚያ ቢሮ ብቻ አይደለምኮ፡፡ ታላላቅ በዓላት ሲከበሩ በየአደባባዩ ሐበሻ ሆነህ ፎቶ ግራፍ ላንሣ፣ ፊልም ልቅረጽ ብትል ጠባቂው አያሳልፍህም፡፡ ፈቃጁም በመከራ ነው የሚፈቅድልህ፡፡ እርሱም ቢሆን ዘመድ ካገኘህ፡፡ ፈረንጅ ከሆንክ ግን መልክህ ብቻ ይበ ቃል፡፡ የፈለግከውን ብትቀርጽ፣ የፈለግከውን ብታነሣ ማን ጠያቂ አለህ፡፡ እስኪ ወደ ታሪካዊ ቦታዎች ሂድ፤ ለሐበሻ ያልተፈቀዱ ቦታዎች ለፈረንጅ ክፍት ናቸው፡፡ አንተ የማታገኘውን መረጃ ፈረንጅ በቀላሉ ያገኘዋል፡፡
«አጎቴ ከውጭ ሀገር የመጣ ጊዜ ትዝ ይልሃል? ምሳ ሊጋብዘን እዚያ ሆቴል ገባን፡፡ እኔ መጀመርያውኑም እንዲህ ያሉ ፈረንጅ የሚያዘወትራቸው ሆቴሎች መሄዱን አልፈለግኩትም ነበር፡፡ ደግሞም ተናግሬያለሁ፡፡ ግን ከሄድን በኋላ ያልኩት ነው የደረሰው፡፡
«ምን ተፈጠረ፤ ነበርኩ አይደለም እንዴ
«አዎ ነበርክ፡፡ ነገር ግን አንተ ቅኝ ግዛትን መሬት ላይ ነው የምትፈልገው፤ እኔ ደግሞ ሰው ላይ፡፡ አንተ ስለ ድንበር የምታስበው በምዕራብ፣ በምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በደቡብ እያልክ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ድንበሩን ከመካከላችን ነው የምፈልገው፡፡
«እኛ ነበርን ወደ ሆቴሉ ቀድመን የገባንው፡፡ ወንበር ይዘን የተቀመጥነው፡፡ ነገር ግን አስተናጋጆቹ ሁሉ ፈረንጆቹን ለማስተናገድ ነበር ሽር ጉድ የሚሉት፡፡ እኛ ተቀምጠን ከኋላችን የመጡት ፈረንጆች ቀድመው ተስተናገዱ፡፡ አጎቴ ነገሩ ስላልገባውና የአስተናጋጆቹ ንዝህላልነት ብቻ ስለመሰለው ከራሱ ሀገር ጋር አወዳድሮ ተናደደ፡፡ በኋላም በመከራ ነው የታዘዙን፡፡ የሚገርመው ነገር የምግብ ዝርዝሩን ሳየው አንድም ኢትዮጵያዊ ምግብ አላገኘሁም፡፡ ለኔ አልገረመኝም፡፡ እዚያ ቤት የሚጠበቀው ፈረንጅ እንጂ ሐበሻ አይደለም፡፡ አንተም እንድትሄድ የሚጠበቅብህ ፈርንጀህ ነው፡፡ ተወው ምግቡን፡፡ ምግቡ የተጻፈበት ቋንቋ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ብቻ ነው፡፡ አንዳች የሀገርህ ቋንቋ የለውም፡፡ ከምግብ ዝርዝሩ ውስጥ ምን የሚል የእንግሊዝኛ ቃል እንዳየሁ ታውቃለህ?
«ምን አየህ ደግሞ? ዛሬ ለጉድ ነው መቼም አመጣጥህ» አለው አባቱ እየጓጓ፡፡
«ታንግ ኤንድ ሰንበር ይልልሃል ምግቡ»
«ታንግ ኤንድ ሰንበር ደግሞ ምንድን ነው?»
«እይውልህ ምላስ እና ሰንበር የሚለውን ለመግለጥ ነዋ፡፡ ምግቡን ሲያፈረንጁት እኮ ነው፡፡ ምናለ መጀመርያ በአማርኛ፣ ከዚያም ስሙን በእንግሊዝኛ፣ ቀጥሎ ስለ ምግቡ ባሕል እና ይዘት መጠነኛ ማብራርያ ቢሰጡ፡፡ አይ ቅኝ ያልተገዛ ሕዝብ፡፡
«ቋንቋ አለን ግን አንጽፍበትም፡፡ ቁጥር አለን ግን አናስብበትም፤ ባሕል አለን ግን አንኮራበትም፡፡ እስኪ ቻይናን እያት፡፡ መላውን ዓለም በቻይና ምግብ ቤት ስታጥለቀልቀው፡፡ የሠራተኞቹ አለባበስ፤ የምግብ ቤቱ ስም፤ ስሙ የተጻፈበት ቋንቋ፤ የምግቦቹ ስያሜ፣ ስያሜያቸው የተጻፈበት ቋንቋ፣ ግድግዳው ላይ የተጻፈው እና የተሳለው ነገር፣ የሚቀርብበት ዕቃ ምኑ ቅጡ ቤጂንግ ያለህ ነው የሚመስልህ፡፡
«እስኪ ዘመዶችህን እያቸው አባዬ፤ ኢትዮጵያዊውን ስምኮ ድራሹን እያጠፉት ነው፡፡ በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ ስሞች መጠራት እየቀረኮ ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን የስም ፍልስፍና ቢቻል የልጆችህ ስም ከአራት ፊደል ያልበለጠ፣ ለቁልምጫ የሚያመች እና ያልተለመደ ይሁን የሚል ነው፡፡ ይህ አይደለም ግን ችግሩ፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማሟላት እየተረባረብን ያለነው የፈረንጅ ስሞች ላይ ነው፡፡ ልክ ቅኝ የተገዙ አፍሪካውያን የሀገራቸውን ነባር ስሞች እየዘነጉ በቅኝ ገዥዎቹ ስሞች እንደተጠሩት እኛም ያንን መንገድ ሳንወረር እየተከተልነው ነው፡፡
«የነገው ትውልድ የሚወጣባቸውን ትምህርት ቤቶችንስ ታያለህ? የሚያስተዋውቁትኮ ብቁ ኢትዮጵያዊ መምህር አለን ብለው ሳይሆን አንዳች ፈረንጅ እኛ ትምህርት ቤት ያስተምራል እያሉና እርሱን በቴሌቭዥን እያሳዩ ነው፡፡ ምን ያድርጉ ይህ ቅኝ ያልተገዛ ሕዝብ ይህንን ነው የሚወደው፡፡ ማንዴላ ለነጻነት የተደረገ ረዥሙ ጉዞ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ አስተናጋጆቹን እና ፓይለቶቹን ኢትዮጵያውያን ሆነው ሲያገኟቸው የተሰማቸውን ስሜት ይህ ቅኝ ያልተገዛ ሕዝብ አያውቀውም፡፡
«እስኪ የትምህርት ቤቶቹን ስሞች እይ፤ አጸደ ሕፃናቱም፣ አዳዲስ የግል ኮሌጆቹም በአብዛኛውኮ ኢትዮጵያዊ ስም የላቸውም፡፡ እነዚህ ሦስት ዓመት በነጻነት ኖረች በምትባል ሀገር የተከፈቱ፣ እነዚህ ፈረንጆች ሳይደፍሯት በነጻነት ኖረች ተብሎ በሚዘመርላት ሀገር የሚያስተምሩ፣ እነዚህ ቅኝ ሳንገዛ ድንበራችንን አስከብረን ኖርን እያሉ ልጆቿ በሚፎክሩላት ሀገር ያሉት ትምህርት ቤቶች ፈረንጅኛ ስያሜን በፈረንጅኛ ካልሰጡ ያደጉ አይመስላቸውምኮ፡፡ ከሀበሻ ገና ይልቅ የፈረንጅ ክሪስማስ የሚያከብሩት ትምህርት ቤቶቻችን በርግጥም ቅኝ ግዛት ያልነካን መሆናችንን ይመሰክራሉ፡፡
«የቻይናን፣ የጃፓንን እና የሕንድን ፊልም ያየ ሰው ሰዎቹ ኢትዮጵያውያን ሆነው ቢሠሩት እንኳን የቻይና፣ የሕንድ እና የጃፓን ፊልም መሆኑን ማወቅ ይችላል፡፡ እዚያ የሚያየው ባሕል እና ኑባሬ፣ እዚያ የሚታየው ሥርዓት እና ወግ፣ እዚያ የሚደረገው ድርጊት፣ ሃሳቡ እና አመለካከቱ የቻይና፣ የሕንድ፣ የጃፓን ነው፡፡ እስኪ አባዬ ብዙዎቹን የኛን ሀገር ፊልሞች ተመልከት፡፡ ሰዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ባናውቅ ኖሮ የኢትዮጵያ ፊልም መሆኑን እንዴት እናውቅ ነበር? ደግነቱ ብዙዎቹን የፊልም ተዋንያን በድራማ እና በቴሌቭዥን ማስታወቂያ አስቀድመን ማወቃችን ጠቀመን እንጂ፣ ተቀጥረው ለሌላ ሀገር የሚሠሩ ነበር የሚመስለን፡፡
«አለባበሱ፣ ቤቱ፣ መኪናው፣ ባሕሉ፣ ጠባዩ፣ ምኑ ነው ኢትዮጵያዊ? ሃሳቡ እንኳን ሳይቀር የፈረንጅ ሃሳብኮ ነው፡፡ ፈረንጅ መንገድ ለመንገድ የሚታኮስ ፊልም ስለ ሠራ እኛም በሰላም ሀገር፤ ለዚያውም ከስንት ዓመታት በኋላ ባገኘናት ቀለበት መንገድ ላይ የሚታኮስ ፊልም መሥራት አለብን? የፍቅር ፊልሞቻችን እንኳን የፈረንጅን የፍቅር ጠባያት ነው የሚያሳዩን፤ ሐበሻ አያፈቅርም? ሐበሻ የፍቅር ዘፈን የለውም? በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማልኛ፣ በአፋርኛ ፍቅር የለም? ለመሆኑ ሐበሻ ሃሳብ የለውም፤ ተረት የለውም፤ ጉዳይ የለውም፤ ለፊልም የሚበቃ ኑሮ የለውም፣ ለፊልም የሚበቃ ታሪክ የለውም? ቅኝ ሳንገዛ ሦስት ዓመት በነጻነት ኖረን፣ ድንበር አስከብረን፣ ለፊልም እንኳን የሚበቃ ነገር እንዴት አላተረፍንም? 
«ይሄ ዘርፋፋ ከናቴራ ለብሶ፣ ቀበቶ የሌለው ቦርፋፋ ሱሪ ሶርቶ፣ እንደ ባሕታዊ ሠንሰለት ታጥቆ የሚሄደው የሀገሬ ወጣት እውነት ቅኝ ያልተገዛ ነው? አሜሪካውያን ጥቁሮች ለምን ይህንን ዓይነት ልብስ እንደለበሱ ያውቀዋል? በዚያ የባርነት እና የልዩነት ዘመን ቀበቶ እንዳያደርጉ፣ ዘርፋፋ ልብስ እንዲለብሱ ለምን ይደረግ እንደነበር ይገባዋል? እነማን ከትውልድ ሀገራቸው በሠንሠለት ታሥረው ለባርነት እንደተዳረጉ? እነማንስ በተወሰዱበት ሀገር በሠንሰለት ታሥረው በከባድ የጉልበት ሥራ እንደ ተሰቃዩ ያውቀዋል? እነዚያ ለሦስት መቶ ዓመታት የነበረባቸውን ስቃይ ለማስታወስ ያደርጉታል፤ ሌላውን ባህላቸውን አጥፍተውባቸዋልና ይህንን ባህላቸውን ያጠፋባቸውን ታሪክ በመከራ ይስቡታል፡፡ ታድያ ቅኝ አልተ ገዛም ያልከው ወገኔ ይህንን ሲለብሰውስ ምን ማለቱ ነው?
«እና አባዬ ምናልባት መሬቱ ቅኝ አልተገዛ ይሆናል፡፡ እርሱም ቢሆን ያጠራጥረኛል፡፡ መሬት ማግኘቱ አንዳንዴ ከሀገሬ ሰዎች ይልቅ ለውጮቹ ሲቀናቸው አያለሁና፡፡ የርሱም አመለካከት ተቀይሮ ይሆናል፡፡ እኛ ሰዎቹ ግን ልባችን ቅኝ የተገዛ ይመስለኛል፡፡ ይልቅ ሆኗል ብለን በምናስበውና በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንጀምር፡፡ ምናልባት እየሆነ ያለው ሆኗል ብለን ከምናስበው የተለየ እንዳይሆን፡፡»
 አባት ትኩር ብሎ ነበር ልጁን የሚያየው፡፡ እርሱም በልጁ ላይ ሆኗል ብሎ የሚያስበውና እየሆነ ያለው ተለያይቶበት፡፡


66 comments:

 1. ብዙውን እውነታ ልጁ አስተዋለ:: ማስተዋሉን ይስጠንና መለስ ብለን እራሳችንን እንድንሆን ፈጣሪ ይርዳን::

  ReplyDelete
 2. ለልጆች ሁሉ ነገር ይገለጽላቸዋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል! ራሳችንን መሆን ካቆምን ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ልጆቻችንን እንደ ቀድሞው ወጋችን እናሳድግ፡፡ ከታሪክና ከትውልድ ተወቃሽነት እንድናለንና! እኔስ የድርው ዘመን ናፈቀኝ፡፡
  ዲ/ን ዳንኤል! ላንተ የሚናገር አንደበት የሰጠህ አምላክ ለኛ ደግሞ አስተዋይ ልቡና ይስጠን! እግዚአብሔር ይባርክህ!
  አምሐ ገብርኤል ከጀርመን

  ReplyDelete
 3. የተባለው ነገር ሁሉ እውነት ነው ። ይሄ ራስን አለማወቅ ፥ባህልን አለመጠበቅ መሰረቱ ምንድነው? የምንስ ተጽእኖ ነው ? ቀጣዩን ትውልድስ መታደግስ ይቻላል ???

  ReplyDelete
 4. Thanks Dn Daniel. Very sharp analysis.

  ReplyDelete
 5. Good Article. God bless ur mind

  ReplyDelete
 6. + + +

  Very good insight! Dn.Dani ene girim yemilegne demo yeminikorijachew negeroch tenkro mesratin, tesfa yalemkuretin, hulem memarin yemesaselutin sayihone tirki mirkiwin mehonu new, min ale bahilachinin tebiken yemiyanitsewin bicha binikorij?

  ReplyDelete
 7. Where is the next part of the previous blog archive? Did you forget that you wrote at the end of that writing "to be continued"?

  ReplyDelete
 8. እግዚአብሔር ይባርክህ!አምላክልቡና ይስጠን!

  ReplyDelete
 9. በጣም የሚገርም ፅሁፍ ነው በትክክል ልባችንማ በቅኝ ተገዘቷል፡፡ ማንነታችን ባህር ተሻግሯል፡፡ ብቻ ልቦናችንን ይመልስልንና ከዚህ የስሜት ቅን ግዛት አምላካችን ይታደገን፡፡
  መስቲ

  ከአዲስ አበባ

  ReplyDelete
 10. really impressive. how matured that boy is ? no doubt that we r loosing our identity .z eastern world though influenced by z western culture 4 a long period of time r still protecting every aspect of their culture but things r paradox with us.we all should think over it thanks d/Daniel God be with u for ever

  ReplyDelete
 11. an amazing overview God and St. Marry bless you this is the real and surprising one that discourages me!! why! but if you see dani. most of us(Ethiopians) we are don't consider differently for whites probably some of us may think like every thing found in ethiopia is also there, this shows us we are PROUD OF US I have a white friend and "he told me always ethiopians love their culture...even the most of the time we you dont consider white different from your citizen". Anyways even though some of us act like this as you stated, most ethiopians dont think and act like this? you can talk most ethiopians found in abroad is come to ethiopia and they marry ethiopian here or find there and ...this shows.....the reverse that you think...THANK YOU for the time being

  ReplyDelete
 12. Thanks D/N Daniel

  I am so Excited on this issue. Let me tell you a true story:
  Once an Ethiopian who has been living in Holand Came to Ethiopia With his polish friend for Epiphany (Timket. The polish was allowed to get in Up to the arks (Tabots)and the Habesha was not allowed.
  You know what the Polish said " I am first in Holand and first in Ethiopia". This sentence is painful for me.
  You Ethiopians, disgracing Habesha means, disgracing yourself.

  D/N Daniel, please write more more and more

  ReplyDelete
 13. wow betam astemari new Dn.Dani EGZIABHER yeageleglot zemenehen yebarekeleh,

  ReplyDelete
 14. Yedingel Mariam leje Abzeto tsegawen Yisteh D/n Danile .Let’s start from this instant to educate every one in every place that our right over our country must be most important .let’s start mouth networking to convince our natives specially those work in hospitality industry based on what was said by D/N Daniel kibret .As it is maintain our warm welcome reception to the foreigners.
  God bless Ethiopia
  Sami from Abware

  ReplyDelete
 15. wow betam mekarina astemari new.Dn Daniel EGZIABHER ye agelegelot zemenehen yebarekeleh.Amen
  welete senebet
  ke sweden

  ReplyDelete
 16. ዘ ሐመረ ኖህJuly 31, 2010 at 12:11 PM

  ሰላም ለዳኒና ለታዳሚዎቹ መሬታችን ሳይሆን ጭንቅላታችን አስተሳሰባችን ቅኝ ተገዝቷል ወይም ሳናውቀው ተሰርቀን በሌላ ተተክቷል በሀሃገር ቤትም በውጭም የሚገኘው ወገኔና እኔ አብዛኛው የውጭውን ሀገር ኑሮ ቋንቋ ቅጥ ያጣ አለባበስና የጸጉር ማንጨብረርን ንቅሳትን ወዘተ ናፋቂና አድራጊ ነን በእጅ ያለውን እንቁና ወርቅ አሽቀንጥረን ጥለን ከመዳበም ከቆርቆሮም የረከሰውን አፍቃሪና አግበስባሾች ነን እነቻይናና ጃፓን ብቻ ሳይሆኑ ቀረብ ብለው የሚገኙትን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮቸን ራቅ ካሉት የአውሮፓንና የላቲን አሜሪካ ሀገሮችን ምሳሌ ብናደርግ ጥሩ ትምህርት በሆነን ነበር ለነገሩማ እንደ ታሪካችን ቢሆንማ ኖሮ ለእነዚህ ሃገሮች ምሳሌ መሆን የሚገባን እኛ ነበርን እነዚህ በስደት እንኳን የሚገኙ የነዚህ ሀገር ሕዝቦች ከራሳቸው አልፍው በውጪ ለሚወለዱ ሕጻናቶች የየሃገራቸውን ቋንቋ ባሕል ታሪክና እምነት ጠብቀው እንዴት እንደሚያስተምሩና ለልጆቻቸው እንደሚያወርሱ ትንሽ ዞር ብለን ብንመለከት እጅግ እናፍራለን ብዙ ሕጻናቶች እየጠፉብን ነው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚግባቡበት ቋንቋ እየቸገራቸው ነው እንደ ጥንት አባቶቻችን ውድና ብርቅዬ ቋንቋችንን ባሕላችንን ታሪካችንን ምትክ የማይገኝላትን እምነታችንን ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልዳችን ካላስተላለፍን በእውነት ከእንስሳ አንሻልም ለዚህም ሕዝብ መንግስትና ቤተ እምነቶች የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ጥንት ጃፓን እንዲህ ከመሰልጠኗ በፊት ሕጻናቶቿን በእውቀት ይሰለጥኑ ዘንድ ወደ ውጭ ልካቸው ስለ ተፈጠረው ነገር እባክህ ዳኒ በኔ በሰባራው ብዕር ሳይሆን በተባ ብዕርህ እስኪ አንተ ተርከው በሃገር ቤት ቅድሚያ ሁሉ ነገር ለፈረንጅ እየሆነ በገዛ ሀገራችን ስደተኛ ወይም ሁለተኛ ዜጋ መሆን ከጀመርን ዘመናት ተቆጠረ ቅድሚያ ሁሉ ለፈረንጅ ሲሆን ያየ የሃገሬ ሰው እኔም ፈረንጅ ብመስል ወይም እንደ ፈረንጅ ብሆን በነገር ሁሉ ቅድሚያ አገኛለሁ ብሎ ይሆን የፈረንጅ ኮተት ሲጎትት ጊዜውን የሚፈጀው መፍትሄ ከራስ ይጀምራልና ከራሳችን እንጀምር ዛሬ ከመንግስትንና ከቤተ እምነቶች ብዙም የምንጠብቀው ነገር ያለ አይመስለኝም ነገር ሁሉ የተገላቢጦሽ መሆን ከጀመረ የሰነበተ ይመስለኛል ቢሆንም እጅ መስጠት አይኖርብንም ከማንም አንጠብቅ ለማለት ነው እግዚአብሔር አምላካችን በነገር ሁሉ እውነትን የሚያስተምረንንና እያየነው የማናስተውለውን እየሰማነው የማናዳምጠውን እያወቅነው የማንተገብረውን ድክመታችንን እንድንመረምር የሚያደርጉንን ወንድሞች አያሳጣን ከአይን ያውጣልን ቸር ይግጠመን

  ReplyDelete
 17. እጅግ ግሩም እይታ ነው። መቼ ይሆን ወደ ልቦናችን የምንመለሰው? አገራዊ አመለካከት እንደ ሁዋላ ቀር የሌሎችን ባሕል መቀላወጥ እንደዘመነኛ መታየት መቼ ይሆን የሚቀረው? ይህ የሁላችን የቤት ስራ ቢሆን?

  ዲ/ን ዳንኤል እግዚአብሔር ይጠብቅህ።

  መንግስቴ
  ከጀርመን

  ReplyDelete
 18. ዲ/ን ዳንኤል፦

  እግዚአብሔር ይስጥልን። የተነሱት ነጥቦች ሁሉ በጣም በጣም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸዉ። ዳሩ ምን ያደርጋል አእምሮአችን ተበላሽቶአል። ፈረንጆቹ በምኑም በምኑም አድርገዉ አእምሮአችንን ሰልበዉታል። ወገኔም ያወቀ እየመሰለዉ ባህሉን ጥሎ እኮበለለ ነዉ።

  የኛና የፈረንጅ ነገር ከተነሳ እኔ ሁሌ የሚገርመኝ በኤርፖርት (Airport) የሚደረገዉ ነገር ነዉ፤ የፈረንጅ ሀገር ኤርፖርት ስንደርስ የሀገሩ ዜጋ ፓስፖረቱን እያሳየ ሰተት ብሎ በተከፈተለት በር ወደ ሀገሩ ሲገባ ዜጋ ያልሆነ ግን ብዙ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል፡ ፓስፖርቱና ሌሎች መረጃዎቹ በጣም ይፈተሻሉ። የኛዉ የኢትዮጵያ ኤርፖርት ስንደርስ ግን የተገላቢጦሽ ነዉ፤ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ የስቃይ ሰልፍና እንግልት ይጠብቅሃል፤ ለምን ተመልሰህ መጣህ ያህል ጥያቄ ነዉ የምትጠየቀዉ። ዜጋ ካልሆንክ ግን ችግር የለም። "ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለዉም" እንደተባለዉ እኛዉ ሀገራችንን ካላከበርንና ከላስከበርን ፈረንጁ ምን ያድርግ?

  ከብሪታኒያ

  ReplyDelete
 19. ግሩም ነው። ለተፈጠረብን ችግር እኛው ራሳችን በሰከነ የምንፈታው?

  ReplyDelete
 20. ኃ/ገብርኤልJuly 31, 2010 at 4:14 PM

  ዲ/ን ዳንኤል ሰላም ላንተና ለዚህ የጡመራ መድረክ ታዳሚዎች ይሁን።
  የዛሬው ፅሁፍህ በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደሚያጠነጥን አስቀድሜ አልወቀው እንጂ እንዲህ አይነቱን ልብ የሚነካና እኔ ማነኝ፣ምንስ እየሰራሁ ነኝ፣ ምንስ እሰራ ዘንድ ይጠበቅብኛል ወዘተ አይነት ጥያቄዎችን በህሊና የሚያጭር እንደሚሆን ጥርጥር አልነበረኝም በቀደሙት ሰራዎችህ አውቅሃለውና። እንደጠበኩትም ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ።
  በእውነት ለመናገር ይህ ርዐሰ ጉዳይ በጣም አሳሳቢና አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ የሚያስፈልገው ነው(ኃላፊነትን ወስዶ የሚያስተካክለውን ግን አምላክ ይወቀው)። ውድ አንባብያን አንድ ሁልጊዜ በህሊናዬ የሚመላለስ ነገር ላንሳ፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በየዓመቱ የአድዋን በዓል እናከብራለን። በበዓሉም ቀን ሁል ጊዜ እንደሚባለው ጀግኖች አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሃገራችን ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር አቆይተውልናል ይባላል። አንድ ጥያቄ ላንሳ ለመሆኑ በዚያን ጊዜ የነበሩ አባቶቻችን ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ለምንድነው??? ኢትዮጵያ በኢትዮጰያነቷ ፀንታ እንድትኖር መሆኑ ግልፅ ነው። ቁም ነገሩ የኢትዮጵያ በኢትዮጵያነት ፀንቶ የመኖር መገለጫዎች ምንድናቸው??? ከላይ በወንድማችን የተዘረዘሩት አይደሉምን??? እነዚያ አባቶቻችንና እናቶቻችን ዘመናዊ የጦር መሳርያ ነበር ያጡት እንጂ ዘመናዊ የማንነት አስተሳሰብ በደማቸው ነበር። አሁንም እኔን ጨምሮ በዚህ ትውልድ ደም ውስጥ የጠፋው ይህ ዘመናዊ የማንነት አስተሳሰብ ነው። መቼም እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ቻይ ነው ታድያ አስቲ ጉዳቸውን ልይ ብሎ በዚያን ጊዜ ያንን ዘመን የማይሽረውን ታላቅ ተጋድሎ የፈፀሙትን፣ አይደለም አይተውት ሰምተውት እንኳን በማያውቁት የመርዝ ጋዝ እንዳይሆኑ የሆኑትን አባቶችና እናቶች ካንቀላፉበት ቀስቅሶ ቀና ብለው አሁን ያለውን ነገር እንዲያዩ ቢያደርጋቸው ምን ይሉ ምንስ ያደረጉ ይሆን??? እኔ ግን ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? ያንን ጣልያን የተጠቀመበትን የመርዝ ጋዝ አስመጥተው የመረዙንም ኃይል 100 አጥፍ አስደርገው ሙልጭ ያደርጉን ነበር ምክንያቱም እኛ የሞትንላቸው የሀገራችን ህዝቦች አልቀው በምትካቸው ሌሎች ህዝቦች በሀገራችን አየኖሩ ነው ብለው ስለሚያስቡ። እንጂ መቼም አነሱ ያንን ሁሉ መራር መስዋዕትነት የከፈሉለት ህዝብ እንዲህ ይሆናል ብለውማ እንዴት ያስባሉ???
  ቸር ያሰማን።

  ReplyDelete
 21. Thanks dani,

  Girum eyita new. sile endezih ayinet issue sititsif betam des yilal. Please write more on such kinds of issues. And I promise to read, change myself and share the info to other people.

  tsegawu yibzalih

  ReplyDelete
 22. mesfin ke abu dhabiJuly 31, 2010 at 7:37 PM

  selam lek betam yemiyastemer new berta egziabeher yebarkeh

  ReplyDelete
 23. hilarious....touching.....inspirational.....the real story of post colonization in ethiopia....'generation gap'

  ReplyDelete
 24. wow! Danieal, Getachen Eyesuse Kirsotse yebarkehe!

  ReplyDelete
 25. Thinks D/N Daniel ''God'' & SAT MA
  RRY blessed u..

  ReplyDelete
 26. Dn. Dani

  Betam tilike ena weketun yetebek tsehuf new. ye amaregna software silelelegn be englizegna ye amaregna atsatsaf lemetsaf tegedichalehu.

  Lemehonu be ahunu gezie sile ethiopiawit yemichenek teweled ale woye? melesun le eyandandachin litewew ena esti ezeh USA kemetahu yegetemegnin ena yetazebekuten lawesachehu. Ezeh balehubet akababi bezu ye ethiopiyaweyan lejoch "Amaregna" kuankua lemawerat sichegeru lememeleket chiyalehu. amaregna alemaweratu yemibesew degemo adegew wede ezeh hager bemetute lay new. beatekalay welajoch le lejochachew amaregna lemasetemar felagotum yelachewem yeh degemo "teteki tewelede" endanagegni yaderegenal. keminim degmo yasazenegni welajochachewen siteyekachew yesetugn meles "Amaregna min yaderegelachewale, wonze ayashagerachew? min yasechenekale" betam new yedeneketekut manineten meshet min yebalal?
  meseleten? woyes?

  le hulachinim masetewalen yeseten

  ReplyDelete
 27. Hi Dani

  Thank you for writing on this issue. The past 7 years have been in Canada, to tell you the truth where ever the place I go I get more respect and good treatment here in Canada. SO sometimes I wonder where is my birth place? If I go to government office, Banks, Clinics, Airport, Restaurants... if I arrive first they serve me first. But in my birth place in Addis Ababa ... Shame on ...

  God bless Ethiopa and Canada.

  ReplyDelete
 28. selam selam dani we have a problem to reade the web the font is not dispalyng please tell us what to do

  ReplyDelete
 29. "በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?" ኤር.13:23

  እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ "አዎን ጌታ ሆይ፥ ይለውጣል!"

  ReplyDelete
 30. እጝዛብር ይስጥክ ወንድሚ ...በጣም ልብ የሚነካ ነው,, አወ ብዙ ሰውች እንደ ጥቁር አሚርካዊ አክት ሲያደርጉ ነው የሚታዩት .....ለዚክ ደግሞ ተጤይቂው እኝ ...እስኪ ስንት አችን ነን ለወንዶሞቻ ወይም ለህቶች ሰለ ባህላችን የምንነግራቸው... በተለይ ከአገራችን ውጭ ተውልደው
  ያደጉ ልቸውች ሰለ ኢቲዮ ታሪክ ምንም አያውቁም.....

  ReplyDelete
 31. ዲ/ን ዳንኤል እግዚእብሄር ጤናና እርጅም ያገልግሎት ዘመንን ያድልልን:: ትልቅ ነገር ነው ያነሳኽው:: ልጁ ልክ ብሎአል እዎ ቅኝ ተገዝተናል እየተገዛንም ነው:: እኛ ሁላችንም ሃገራችንን እንወዳለን እንል ይሆናል እሁንም ደፍሮን ጦር ይዞ መሬታችንን ለሚነካ ጠላት ህይወቱን ገብሮ ቅጥሩን የሚያስከብር ወገን እንዳለን እናውቃለን ነገር ግን አሁን ጠላት ቅኝ ለመግዛት በጦር መምጣት አያስፈልገውም ከምንም በላይ የሆነው ማንነታችንን እስከመተው ድረስ በፈቃደኝነት ተገዝተናል:: አሁን እንዴት እራሳችንን እንሁን ነው? እያጣነው ያለውን ማንነታችንን እንዴት እንጠብቀው ነው? ትልቁ ጥያቄ? እኔ አገር ቤት ሄጄ የታዘብኩት ነገር ቢኖር ባሁን ግዜ በከተማ ያሉ ቤተሰቦች ማንነታችንን ከማሳሰብ ፋንታ በልጆቻቸው ዘመናዊ ብለው በሚጠሩት አስተሳሰብ እየተቀየሩ እንደሆነ ነው ታዲያ አኛ ለሚቀጥለው ትውልድ የምናቀብለው ምን አለን?

  ReplyDelete
 32. ISSAIAS FROM OAKLANDAugust 1, 2010 at 11:43 AM

  መጀመሪያ ይህን የመሰለ አስተዋይ ጭንቅላት ለሰጠህ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው አንድ ሁልግዜ የሚያሳስበኝ ግን እነዚህን ያንተን ጽሁፎች የሚያነቡት ጥቂት የማንበብ ፍላጎት ያላቸው ያውም የኢንተርኔት አክሰስ ካላቸው ማለቴ ነው ግን በምን መልኩ ለአብዛኛው ማህበረሰብ ኢትዮጵያም ላለው እንዲሁም በውጭ ላለው ኢትዮጵያዊ ሊዳረስ የሚችልበት መንገድ ይኖር ይሆን ምክንያቱም እንዲሁ ተነበው እና አድንቀን የምንተዋቸው ብቻ አይደሉም ለውጥ ማድረግ ልንጀምርባችው የሚገባን ጉዳዮች ናችው ምናልባት አንተም በዚህ ጉዳይ ሃሳብ ካለህ ጥሩ ካልሆነም እስኪ እንወያይበት

  ReplyDelete
 33. This is great and true saying and analysis.
  keep it up Dear Dani.

  ReplyDelete
 34. I do not like this article. It is full of critics or too critical. I like to learn from the other perspective. I want to see and learn our positives.I want to see and learn others positives as well- We need to learn a lot from weasterns. This article encourage to praise ours and condemn/ignore others. ofcourse, this the way of most preachers(EOTC).

  ReplyDelete
 35. ለሀገራችን ህዝቦች ትኩረት አለመስጠታችን ፤ ዜጎቻችን ፈረንጅን ለመሆን ተመኙ አደረጉትም፤ ሜ ባልኩ ፍየሌን ከፈልኩ አይደል ተረቱ። ሌሎች ሀገራት በሆነ አጋጣሚ ያጡትን ማንነታቸውን በባትሪ አና በሚሊዮን ፕሮጀክት ሲፈልጉ አኛ ወደ እነሱ ውድቀት መጓዛችን ምን ይሉታል? ፈረንጅን ሳይሆን ፈረንጅንትን ፍራ። በመላው የሀገራችን ክፍሎች የምንመለከተው ይህንን ነው፤ ይባስ ብሎ ማንነታችንን እንደፈለጉ እንዲያጠፉ የነገ ሀገር ተረካቢ ማፍሪያዎች የሆኑትን ት/ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎችን በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዲዉሉ ተገደረገ። ከዚያስ ምን አይነት አመለካከት ያለው ትውልድ ይፈጠር ይሆን? እርግጠኛ እንሁን ከብሩ ጀረባ ሌላ ተልኮ መኖሩን።
  ዲቲ ዘባሕር ዳር
  እመቤታችን አስራት አገሯን ትጠብቅልን

  ReplyDelete
 36. ዲ. ዳንኤል አሁንም ጤና እና እድሜ ይስጥህ፡፡
  መቼ ይሄ ብቻ አስተውላችሁ ከሆነ እንደፋሽን
  ዘመኑ እየተከተለ ያለውን የባሕል ልብሳችንን
  አዘመነው (አሳደግነው) ተብሎ በፋሽን መልክ
  የሀበሻ ጨርቅ ብቻ በመጠቀም ስፌቱን(ዲዛይኑ)
  ግን ፍጹም ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ማድረግ ቀኝ
  የተገዛው አህምሮአችን ያመጣው አስፈሪ ችግር
  ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው በሚዲያ ላይ ያሉ
  አቅራቢዎች ወንዶች በሱፍ ልብ ስፌት የተስራ
  ኮት ለብስው የእከሌ ብሔር ልብስ ሲሉ መስማት
  ያሳፍራል፡፡ ሴቶችም በሀበሻ ጨርቅ አጭር ቀሚስ፡
  ሱሪ፡ አጭር ቦዲ እና የሌላውን አለም ዲዛይን
  ለብስው የባህል ልብስ ለበስን የሚያስብለን ቀኝ
  ያለመገዛታችንን ከሚቃወም ትውልድ የመጣ
  የቁጭት እና በቀኝ የመገዛት ናፋቂነት ችግር ይመስለኛል፡፡
  ብቻ በባህል ልብሳችን ላይ ባለው የቀኝ መገዛት
  ችግር ብዙ ማለት የቻላልና ጥናት ተደርጎ
  ብንወያይ ጥሩ ነው፡፡ ዲ ዳንኤልም በዚህ ዙሪያ
  አስተዋይ ሀሳብና ጹሁፍ እንደምታቀርብ ተስፋ
  አደርጋለሁ፡፡ አስተዋይ ልቡና ለሁላችን የስጠን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 37. egizabhere edmena tena yesthe.yelbeanew yemtisfew,

  ReplyDelete
 38. Hi danie

  it was very touchable

  did you forget about the continution of the last part. you were telling us about pope Tekelhaymanote please finish it. you stop by saying to be continue, remmberre

  ReplyDelete
 39. "ሀበሻ የ ፍቅር ዘፈን የለዉም?".........አለዉ፡፡እና ቢኖረዉስ?....ይዝፈን?
  ገላትያ 5፡21

  ReplyDelete
 40. ዳኒ የብርጭቆው ወይስ የምንጩ ውሀን ተከታይ ክፍል ነበር የጠበቅሁት ለምን ይሄንን ደገምከው?

  ReplyDelete
 41. ውድ ዲ. ዳንኤል በትክክል ገልጸዋል አርበኞች የለበሱትስ I Love Ethiopia አይደል የሚል

  ReplyDelete
 42. ከሆነ ...

  የ'ነኛ ለ'ኛ ... ሁነኛ
  ከሆነ
  የ'ኛ ለ'ኛ ... መናኛ
  ከሆነ
  የ'ኛ ለነ'ኛ ... ዝነኛ
  እንዴት ሆነ?

  ReplyDelete
 43. አቦ ደጋግመህ ጻፍ፡፡
  እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡
  መዝ...

  ReplyDelete
 44. EGZIABHIER BEANDIM BELIELAM YINAGERAL SEW GIN AYASTEWLIM...AYDEL YETEBALEW?AMLAKACHIN AHUNIM YINAGERAL YEMSEMA YISIMA ...WUDU DN.DANIEL ANTE GIN ENDEZIH AYNET GENBI TSIHUFOCHIN TSAFILIN.

  EGZIABHIER YIBARIK TEGIBAREKE WEMEWAELIKE.

  KALEHIWOT YASEMAH

  ReplyDelete
 45. ማስተዋሉን ይስጠን...Kalehiwot Yasemalin!
  Ameha Giyorgis & Fikrte Mariam

  DC/VA area

  ReplyDelete
 46. Wow what a mind is this absolute way of expression for any person wonder full!
  Mamo

  ReplyDelete
 47. The way I understood Daniel's view :if we are not to look into ourselves, value our culture, heritage and think in our own way; instead take the ferenj's line of thinking, we can not claim we are not colonized. This is not to mean emulating good values from others is not important; rather to say what we emulate is not technology, civilization but harbour things that are not constructive in any way. God bless u Dani. Nigatu W.

  ReplyDelete
 48. I think before making such a judgment we should be asking the following two questions:
  1. What does being Ethiopian mean?
  2. What put this generation to this state of being?

  The answer for those questions will be far from easy to be answered in a comment on blog; but I think, as far as we want to see this next generation free from all the cultural amnesia those are the first questions to answer. Culture is not something which we can build overnight rather it is the sedimentation of Social- propaganda (to say in Jaques Elul's phrase). As we all know, propaganda is effective when it is told over and over and over again even if it is a tall tale or a big lie. So, culture is a well sedimented propaganda which uses all the media of communication in a society to stabilize.

  Yes, we were able to kick the Italians out. Yes, we were able to shovel off the Britons conspiracy to make us one of its protectorate colonies in 1941 and 1942. The bosses of the time were so witty in preserving their throne; but they didn't seem to see the mind colonization through the so called MODERN EDUCATION, which predominantly was a western and undomesticated system.

  One westerner who visited the country during that time said that the country's education system was composed of three alien things:

  The indigenous students who had, almost, no idea what the western culture looks like

  The foreign teachers who, on their own turn, were alien to this culture of the Black continent

  The teaching materials particularly the text books which were entirely imported from the European countries.

  This is part and parcel of the factors that led to the cultural amnesia and the crazy revolution which ended in blood.

  Anyway, God bless you Deacon Daniel

  Keep writing

  ReplyDelete
 49. Dear Dn.Dani,I Just finished your new book" ye hulet...".I bought it for my 3 friends as agift.I know most of them during "addis neger"but,i read it as new.I'm also enjoying your blog.I'm a catholic(i mean i had no chances to read Orthodox's books & your writings provided me to know more about blessed orthodox church.) by immpressed by your ideas.If we think more we ethiopian have much more unity than.... dani keep it up.blessings,
  Ashenafi Gedion,ethiopia.

  ReplyDelete
 50. ዲ/ን ዳንኤል ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛልህ
  ቅኝ ባለመገዛታችን የሚቆጭ ትውልድ ባፈራንበት ወቅት በመጻፍህ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በእውነት አሁን አሁን ሳስበው ቅኝ ያለመገዛታችን የሚያኮራን ሳይሆን የሚያሳፍረን እየመሰለኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንሠለጥን ነበር ብለው የሚያስቡ ሥልጣኔ ማለት የባዕድ ሀገርን ቋንቋ ማቀላጠፍ፣ የራስን የሚያኮራ ባህል ትቶ ለምን እንኳ እንዳደረጉት የማናውቀውን የአውሮፓውያንን ባህል መከተልን እንደ ዕድገትና እንደሥልጣኔ በመቁጠር የኢትዮጵያን ኢትዮጵያዊ መልኳን እያበላሸነው ነው፡፡ የልጆቻችን ስሞች፣ የንግድ ቤት ስያሜዎቻችን፣ ለልጆቻችን ት/ቤት ስንመርጥ የምናስቀምጠው መስፈርት (ከሁሉም አደገኛው ደግሞ ይህ ነው) አለባበሳችን፣ አነጋገራችን፣ አካሔዳችን፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ በአጠቃላይ እኛነታችን እኛን ሳይሆን ባህር ማዶ ተሸግሯልና ያሳዝናል፡፡ ይህን ጽሑፍ ሳነብ አንዲት ጓደኛዬ በጣም ቆጭታ የተናገረችውን ነገር አስታወሰኝ “ምናለ ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንግሊዘኛ ወይ ፈረንሳይኛ አቀላጥፈን እንናገር ነበር” አለችኝ በጣም ቆጭቷት! ኢትዮጵያዊ ሆኖ በእንግሊዘኛ አቀላጥፎ የሚናገር የሌለ ይመስል፡፡

  Addis Ababa Ethiopia

  ReplyDelete
 51. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ይህ ነገር ማንነትን መርሳት/Identity crises/ የሚባለው ነው፡፡ ብዙውን ተናግረህዋል፡፡ እኔም ገጠመኜን እንካችሁ፡፡ አንድ ቀን ፍርድ ቤት ከአንድ ወጣት ጋር ወረፋችን እስከሚደርስ መጨዋወት ጀመርን፡፡ ምን ሆነህ ነው አልኩት፡፡ አንድ ቻይናዊ የኮምፔርሳቶ ጅርጅት ባለቤት ሰራተኛውን በሞራሌ ይደበድባል ተደበደብኩ ብሎ ክስ ይመሰርታል፡፡ አይ ደብዳቢው እሱ/ሀበሻው/ ነው ብሎ ቻይናዊው መልሶ ይከሰዋል፡፡ በX-ray የተደገፈ መረጃ ያለው ሀበሻው ነው፡፡ ስላልታመነ ምስክር ተጠራ፡፡ ይህንን ታሪክ የነገረኝ ወጣት ለምስክር መቶ ነበር የፍርዱ ውሳኔ ምን እንደሆነ ባላውቅም ገረመኝ፡፡

  በተጨማሪ ባለ እንብርት እያሳዩ የሚሄዱትንስ የት አደረካቸው ዳኒ!!!!

  ይቆየን

  ReplyDelete
 52. ዳኒ በደንብ ገልፀከዋል እግዚአብሔር ይባርክህ ።

  ReplyDelete
 53. One of the depressed person reads all those articles or collections (downloaded from the internet, about depression) to get solutions for his sever depression for the previous ten months. He read and reread those collections when he gets depressed and most of the time he gets temporary relief. He decides to implement what he has got from the internet as a solution. But, immedialtely after some hours, he gets confussed about his sins, about God, about religion, about work, about relationships, about work collegues, about families, about the world, etc. if he reads in the morning, he will be upset in the afternoon or if he reads in the afternoon, his mood changes in the evening. Sometimes he decides to be a real Orthodox Christian and he plans to meet his Godfather and to go to church. But, after leaving the office, he thinks that the Protestants are right especially regarding the Holy Spirit, so that he plans to meet some followers of a protestant church to get their real teachings. When he goes to his home after class, he meets with his families, staunch Orthodox Christians. Then, his mood will be changed to orthodoxy. When he prepares to sleep, he could not pray to God. To which God shall he pray? To the orthodox or to the protestant? So, he sleeps silently. In the morning, he goes to work with depressed mood. He reads different things from the internet and mostly inclined to the solutions given by the protestant churches. Then he thinks that he will go to one of the protestant church to receive the Holy Spirit, Jesus, God. After that, he starts to discuss about religion with his work collegues in the office. Most of them are orthodox. So, he starts to confuse and he wants to be an orthodox Christian. When he goes to the evening classes, he meets with his friends, some protestant, and some orthodox. Then he pretends to be an orthodox. Again, at home, his moods immediately changes to protestant. This person is known as an orthodox. He doesn’t want to go to Orthodox Church. He doesn’t read any of the teachings except the Bible. So far, he hasn’t attended any of the protestant churches. He deslikes any spiritual teachings, discussions, visits, etc. he wants to be alone at home. He doesn’t listen to any radio or TV programs. He deslikes reading newspapers, magazines, bulletines. He deslikes his jobs. He deslikes history, culture, politics, etc. What do you have for such kind of person?

  ReplyDelete
 54. he is ryt so indet inmelisew?

  newist

  ReplyDelete
 55. Thanks as usual, Dani!! (As I couldn’t type Amharic, I would have my reflection just in English)

  I think that a lot has to be done in preserving our own unique culture/traditions. It is understandable that the very rapid global interconnection and constant and readily flows (of goods, capital, people, knowledge, images, crime, pollutants, drugs, fashions, and beliefs) across territorial boundaries aided by the various technological advancements have greatly been influencing the deeply held values and beliefs of the society towards our own culture and tradition. For this, particularly, internet, radio, CDs and satellite television play a prominent role in shaping our understanding and construction of meanings that don’t coincide with our own cultural practices. Similarly, the constant travel of the local people to the West due to social, political, economic and some other reasons has also equally contributed in bringing about undesirable changes that subsequently deteriorate the culture and tradition of the local people.
  As discussed by Dani, nowadays it is not uncommon for most of us, especially the youths, to behave like Westerns perhaps with a view to call and accept the Western culture as the correct one due to the observable global political-economic dominance which is ignorance rather. Because, a given society’s culture/tradition can never be as such an old or modern and in no way that it can be substituted by another, the so called modern, as it defines who we are in general. It is all about our own history, language, music, values, beliefs,...which are often associated with our identity.
  I think that first and for most, families need to take a concerted action through communication as they are basis for knowledge and further development of their children as far as culture is concerned. This would in turn create a good family relationship with mutual trust, respect and wanting the best for others. The families need also to get help in clearly understanding their own traditional assets than letting the western cultural to masquerade...
  Second, different institutions (like religious, educational and state owned as well as civic societies) should be conscious of the vital importance of retaining one’s own tradition and then they should exert the maximum effort towards its end. It is very evident that the American culture is dominating everywhere-like their Macdonaldization of the world- but I can see that those developed countries, like European countries, are doing their level best to make sure that their own tradition, say language, is never compromised…but in our case, no one really cares. Do we have to justify it for the mere fact that we are poor …I don’t think because it doesn’t require as such a huge investment or technology in order to preserve it and be the pride both to ourselves and Africans….

  ReplyDelete
 56. እነ ቻይና፧ህንድ፧ ለሎች በመካከለኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሱት ባህላቸዉን ትተዉ የለላ ሀገረ ዘይበ ስለተከተሉ ሳይሆን የራሳቸዉን ይዞ ልማታቸዉን ስላጣጣፉ ነዉ።እኛማ በለላዉ ባህል አኑዋኑር ተተብትበን በየት በኩል እንደግ? በልጁ የተነገረዉ የአሁኑን ሁነታ ግልጥ አድርጉዋል።

  ReplyDelete
 57. Hi Dani, Thanks for sharing your view. But why are they (the ferengies) given more attention, why are they given priorities? Is it because of their color? I don't think so. In my opinion the question is not color, rather it is money. Most of us assume that they spent more. This is wrong attitude by itself. In my opinion the solution is to be strong economically.

  ReplyDelete
 58. Dani, you said it all so clearly. Thank you. So what is the solution?

  ReplyDelete
 59. do samething tochange this we all are with you.
  God bless ethiopiaand you!

  ReplyDelete
 60. እኔ በታም የሚገርመኝ እና ሁል ጊዜ የማስበው ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ወዳጅ ፤ እንግዳ ተቀባይ እነደሆኑ ሁልጊዜ የሚነገር ነገር ነው፡፡ ያልገባኝ ነገር ግን አገር ማን እንደሆነ ነው፡፡ እንደኔ ከሆነ አገር ማለት መሬት አይደለም ህዝብ እንጂ ሰው የገዛ አገሩን ህዝብ ሳይወድ እና ሳያከብር ለሌላ አገር ዜጋ ቅድሚያ እየሰጠ አገሬን እወዳለሁ ቢል እዉን ይህ ይታመናል እግዚአብሔርም እኮ እኔን ለመውደድ መጀመሪያ አጠገባችሁ ያለውን ባልንጀራችሁን ውደዱ ነው የሚለው፡፡ ለሁሉም ግን ይህን ለመቀየር ሁላችንም ከራሳችን ስንጀምር ነው.

  ReplyDelete
 61. የዚህ የውስጣችን ቅኝ የመገዛት ጉዳይ በጣም
  የሚያሳዝንና እራስን መሆን የሚያሳጣ ነው፡፡
  አመጣጡ ግን ከትምህርት ቤቶች እና ከስደት
  ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡ትልቁን ሚና የሚጫወተው ትምህርት ቤት ነው
  ከገመና ድራማ የትምህርት ቤቶችን ሁኔታ መረዳት በቂ ነው

  ReplyDelete
 62. hulum ehunet new erasachnn enhun

  ReplyDelete