አባት ሁልጊዜ ለልጁ ስለ ሀገሩ ታሪክ እና ወግ ይነግረዋል፡፡ በተለይም አንድ ነገር ደጋግሞ ያነሣለት ነበር፡፡ «ኢትዮጵያ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ተለይታ ቅኝ ያልተገዛች፣ራስዋን ችላ የኖረች ሀገር ናት፡፡ የራስዋ ፊደል፣ የራስዋ የዘመን አቆጣጠር፣ የራስዋ ባሕል ያላት ናት» ይለዋል፡፡ አንድ ቀን ታድያ ልጁ ጥያቄ አነሣ፡፡ «ኢትዮጵያ ግን በእውነት ቅኝ አልተገዛችም?» የሚል፡፡ እናም አባቱን መሞገት ጀመረ፡፡
«አባዬ ግን በእውነት ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ቅኝ አልተገዛችም? ወይስ ለሞራሌ ብለህ ነው ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ናት እያልክ የምትነግረኝ» አለው ልጁ፡፡
አባትዬውም ደንግጦ «ምነው ልጄ ምን አዲስ ነገር ተገኘ? ይህኮ እኔ የፈጠርኩት አይደለም፡፡ ዓለም በሙሉ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ የትኛውንም መጽሐፍ አገላብጥ፣ የትኛውንም ሊቅ ጠይቅ፣ ይህንኑ ብቻ ይነግሩሃል» አለው፡፡
ልጁም «ይህ ከሆነማ ሆኗል ተብሎ የሚታሰበውና የሚታየው ነገር ይለያያል» አለው፡፡
«እንዴት ማለት» አለ አባት፡፡