Sunday, June 6, 2010

ተሳቢ

በቀደም ዕለት ነው፡፡ በአንድ ትልቅ አውራ ጎዳና ላይ አንድ የጭነት መኪና ከነ ተሳቢው ይጓዛል፡፡ እየሄደ ቆየና ድንገት ቆም አለ፡፡ ሾፌሩም ከጋቢናው ወረደና ወደ ተሳቢው አመራ፡፡ ሆድ ዕቃውን እና ዳሌውን ፈታተሸው፡፡ ከሳቢው ጋር የተያያዘበትን ገመድም አየው፡፡ ጎማዎቹን መታ መታ አደረጋቸው፡፡ እኔ የሚያደርገውን እንጂ የሚያስበውን ለማየት አልታደልኩም፡፡

ወደ ጋቢናው ተመለሰና መፍቻ ነገሮች ይዞ ወጣ፡፡ አንድ ሌላ ሰውም ዓይኖቹን እየደባበሰ አብሮት ወረደ፡፡ ምናልባት የደከመው ረዳት ይሆናል ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ ለሁለት ተጋግዘው ብረቱን ፈቱና ሳቢውን ከተሳቢው ለዩት፡፡ የመሳቢያውን ብረት መሬት አስነከሱና ተሳቢውን ወደፊት ሳብ አደረጉት፡፡ ከአካባቢው ብቅ ብቅ ያሉ ወጣቶች ልምድ ባለው አኳኋን ቀረቡና ለጥበቃ ሥራ በገንዘብ ተደራደሩ፡፡ ተስማሙ መሰለኝ፡፡ ሾፌሩ እና ረዳቱ ጋቢና ውስጥ ገብተው መኪናውን እያስጓሩ ወሰዱት፡፡ ምስኪኑ ተሳቢ ግን በቆመበት ቀረ፡፡

አይ ተሳቢ፤ አልኩ በልቤ፡፡ የራሱ ጭንቅላት የለው፣ ራሱ መሪ የለው፣ የራሱ ፍሬን የለው፣ የራሱ ጌጅ የለው፣ የራሱ ነዳጅ መስጫ የለው፡፡ የራሱ ማርሽ የለው፡፡ በሳቢው ላይ ተማምኖ እና ሳቢውን ተከትሎ በሄደበት ይሄዳል፤ በቆመበት ይቆማል፡፡ ከወሰደው ይሄዳል፤ ከገተረው ይቆማል፡፡ እርሱ እቴ ወዴት እንደ ሚሄድ አይወስንም፡፡ የሚወስንለት ሌላ ነው፡፡ እርሱ እቴ መንገዱን አይመርጥም፤ መንገድ የሚመርጥለት ሌላ ነው፡፡ እርሱ እቴ መነሻ እና መድረሻውን አያውቅም፡፡ ሌላው ካስነሣው ይነሣል፡፡ ካደረሰው ቦታ ይደርሳል፡፡

አይ ተሳቢ፡፡

እኔም ጠጋ ብዬ «አንተ ግን እስከ መቼ በሌላ መኪና ጭንቅላት ትመራለህ፡፡ ከምትሳብ ለምን ራስህን አትችልም?» ስል ጠየቅኩት፡፡

እኔስ መኪና ነኝ፤ ግን እንደ ሀገር ስንት ዘመን ተስበናል፡፡ ማርክስ እና ሌኒን ሳቢዎቻችን ሆነው ስንት ጊዜ ሳቡን፡፡ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በማርክሲዝም እና በሌኒኒዝም ካልሆነ በራስዋ አንወስንም ብለን ስንሳብ፣ ስንሳብ፣ ስንሳብ ኖርን፡፡ ጎርቫቾብ የሚባል አንድ ሰው መጣና የኮሚኒዝምን መኪና የሆነ ቦታ አቆማት፡፡ እኛም ቆምን፡፡ ከዚያ እነርሱ መኪናቸውን አስነሥተው ጠፉን፡፡ እኛ ተሳቢዎቹ ወዴት እንሂድ፡፡ ቀድሞም ለመሳብ እንጂ ለመሄድ አልተነሣንምና፡፡

አሁንም ያው በሽታ አልለቀቀንም፡፡ ክርክራችን እና አመለካከታችን «ለኢትዮጵያ የትኛው ይስማማታል፤ ኢትዮጵያዊ የሆነ አስተሳሰብ፣ ርእይ እና መንገድ፣ ነገር ግን የምንፈልገው ቦታ ራሳችንን በራሳችን መርተን የሚያደርሰን የቱ ነው?» በሚለው ላይ አይደለም፡፡ አንዱ ወደ ምዕራብ ወስዶን ኢትዮጵያን የአሜሪካ መኪና ይሳባት ይላል፡፡ ሌላው ምሥራቅ ወስዶን ኢትዮጵያን የቻይና መኪና ይሳባት ይላል፡፡ ሳንሳብ ራሳችን መንዳት አንችልም ወይ?» አለና መለሰልኝ፡፡

«ይህ ችግር ግን የአፍሪካውያን ሁሉ አይደለም ወይ?»

«ነው እንጂ፡፡ እምቢ ማለት የሚችሉ የአፍሪካ ሀገሮችኮ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ነው አፍሪካ የአዳዲስ ሀሳቦች መሞከርያ የሆነችው፡፡ በተለይም ቅኝ የተገዙ ሀገሮች የገዥ ዎቻቸው ተሳቢዎች ሆነው ቀርተዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓታቸው፤ የአኗኗር ጠባያቸው፤ የፖለቲካ መርሖአቸው፣ የባንክ ሥርዓታቸው ሁሉ የሚወሰነው በሳቢዎቻቸው ነው፡፡ የራሳቸውን መንገድ እና ፖሊሲ ቀርፀው ከመጓዝ ይልቅ ሳቢዎቻቸው ወደሚወስዷቸው መጓዝን ይመርጣሉ፡፡»

«ቆይ ግን ይህ ነገር ክስተት ነው አመለካከት ነው ? » ስል ጠየቅኩት፡፡

«እንደኔ ክስተት ሳይሆን አመለካከት ነው የሚመስለኝ፡፡ እስኪ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቅ በል፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ የውጭ ሰዎች የሰጡትን ትንታኔ፣ ድምዳሜ እና አቋም ያለ ምንም ጥያቄ እንደ ወረደ ታገኘዋለህ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊውን የቦታ፣ የሰው እና የዕቃ ስም ፈረንጆች በሚጠሩበት አጠራር ሲጠራ ታገኘዋለህ፡፡ እነዚያ የውጭ ሰዎች የሰጡት ትንታኔ እና መደምደሚያ እውነት ይሆን ? እኔ ከእነርሱ ይልቅ ለሀገሪቱ እቀርባለሁ ብሎ መልሶ የሚጠይቅ አታገኝም፡፡ የተሳቢነት በሽታ ስላለ ዝም ብሎ በእነዚያ ሰዎች ጭንቅላት ብቻ መመራት ነው፡፡ እነርሱ ቲዎሪያቸውን ሲቀይሩ ትቀይራለህ፣ እነርሱ አዲስ መጽሐፍ ሲጽፉ ያው እርሱን ጠቅሰህ እንደገና ታስተምራለህ፤ እነርሱ ተሳስተን ነበር ካሉ አንተም ተሳስቼ ነበር ትላለህ፡፡ እነርሱ መጻፍ ሲያቆሙም ያንተም የማስተማርያ ኖት እዚያው እንደ ቆመ ይቀራል፡፡»

«እንዲህ ካልክማ እዚህ እየኖረ አሜሪካ ላይ የሚታሰብለት ብዙ አይደል እንዴ?» አልኩት፡፡

«በደንብ አይተኽዋል» አለኝ፡፡ «የሚለብሱትን፣ የሚበሉትን፣ የሚማሩትን፣ የሚጫሙትን ሁሉ የሚጠ ብቁት አሜሪካ እና አውሮፓ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ነው፡፡ እነርሱ ኢትዮጵያ ተቀምጠው ምንም አያስቡም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚዘንብ አሜሪካ ውስጥ ቢዘንብ ደስ ይላቸዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረ ችግር ይልቅ አሜሪካ ውስጥ የተፈጠረ ችግር ያሳስባቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይልቅ ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ይጸልያሉ፡፡ ከአራት ኪሎ ማርያም ይልቅ ለዲሲዋ ማርያም ይሳላሉ፡፡

«በየቀኑ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ስልክ እየተቀበሉ ስለየሀገራቱ መረጃ ይሰበስባሉ፡፡ ከዚያም እዚያ የኖሩ ያህል ከጓደኞቻቸው ጋር ሲሆኑ ይተነትናሉ፡፡ የመረጃ ምንጫቸው እዚያ ሀገር ያለው ጭንቅላታቸው ነው፡፡ እርሱ ካኮረፈ ያኮርፋሉ፤ ከታመመ ይታመማሉ፤ ጮቤ ከረገጠ ይረግጣሉ፡፡ ወደ ውጭ ስለመሄድ እንኳን ሲያስቡ አንድ ቀን ይህ ሰው ይወስደኛል ብለው በርግጠኛነት ያምናሉ፡፡

«እነዚህ ሰዎች ናቸው ባለፈው ጊዜ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ተናግቶ ጭንቅላቶቻቸው ቀጥ ሲሉ እነርሱም ቀጥ ያሉት፡፡ እየተጎተቱ መሄድን ብቻ ስለሚያውቁ ወዴት ይሂዱ፡፡ ሥራ መፈለግ እና ሥራ መሥራት አልለመዱም፡፡ አንድ በዲግሪ የተመረቀ ሰው ከሚያገኘው በላይ በዶላር እየተላከላቸው ሲያገኙ የኖሩ ናቸው፡፡ ልብሳቸው እና ጫማቸው ከባሕር ማዶ ነው የኖረው፡፡ ታድያ አሁን መኪናው በድንገት ሲያቆም ምን ይዋጣቸው፡፡ ያው እንደኔ መንገድ ላይ መገተር ነው እንጂ» አለ ፈገግ ብሎ፡፡

«አንተ እነርሱን ትላለህ፡፡ እዚህ ሀገር ሆነውስ ተሳቢዎች አሉ አይደለም እንዴ? አንድን ሀብታም፣ ወይንም ባለ ሥልጣን ተጠግተው፣ ሲስቅ እየሳቁ፤ ሲያለቀስ እያለቀሱ፤ ሲከሳ እየከሱ፤ ሲወፍር እየወፈሩ፤ የሚኖሩ ተሳቢዎች አሉኮ፡፡ የት እንደሚሄዱ ፍጻሜያቸውን አያውቁም፡፡ ስለ ራሳቸው በራሳቸው አያስቡም፡፡ የሚሄዱት ያ ሰው በሄደበት ነው፡፡ የሚያምኑት ያ ሰው የሚያምነውን ነው፡፡ የጠላውን ይጠላሉ፤ የወደደውን ይወድዳሉ፡፡ በትልቅ ዋርካ ሥር ያሉ ትንንሽ ዛፎችን ታውቃለህ? እንደዚያ ማለት ናቸው፡፡ ምግባቸውን የሚያገኙት ከዋርካው ነው፡፡ የሚጠለሉትም በዋርካው ነው፡፡

«ታድያ ያ ሰው ቢከሥር፣ ከሥልጣን ቢወርድ፣ ወይንም ጊዜ ቢከዳው እነዚህ ተሳቢዎች ግራ ይገባቸዋል፡፡ የሆነ ቦታ ቆመው ይቀራሉና፡፡ ያላቸው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፡፡ ሌላ የሚስባቸው መፈለግ፡፡»

«ቲፎዞ ከመሆን በቀር የራሳቸው ሃሳብ የሌላቸው ሰዎችስ አታውቅም?» አለኝ፡፡

«ልክ ነህ ዐውቃለሁ» አልኩት፡፡

«እነርሱምኮ እንደ እኔ ተሳቢዎች ናቸው፡፡ እገሌ እንዲህ አለ ከማለት በቀር እነርሱ ራሳቸው የሚሉት ነገር የሌላቸው፡፡ አንብበው፣ ተምረው፣ ወይንም መርምረው ከማግኘት ይልቅ ከሌላ ሰው ሰምተው ብቻ የሚወስኑ አሉልህ፡፡ እነርሱ ማሰብ አይፈልጉም፤ ማንበብም አይፈልጉም፤ ማየትም አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን የሚስባቸው ሰው አላቸው፡፡ ምን ጊዜም የሌላ ሰው ቲፎዞ ይሆናሉ እንጂ በራሳቸው አይቆሙም፡፡»

«የአንድ ታዋቂ ዘፋኝ ወይንም የፊልም ተዋናይ ተሳቢዎች የሆኑስ አላየህም» አልኩት፡፡

«እነዚህ የለበሰውን ለመልበስ፣ እንደ አካሄዱ ለመሄድ፣ እንደ ድምፅ አወጣጡ ለማውጣት፣ እንደ አቆራረጡ ለመቆረጥ፣ እንደ አነጋገሩ ለመናገር፣ እንደ ማይክራፎን አያያዙ ለመያዝ፣ መከራ የሚያዩ ወገኖቻችን ያሳዝኑኛል፡፡ ለምን በራሳቸው ጭንቅላት አይመሩም፡፡ ከሌላውኮ ጥቂት ወስደህ አዳብረህ፣ ካንተ ጋር አስማምተህ አዲስ ማንነት ትፈጥራለህ እንጂ እንዴት የሌላው ፎቶ ኮፒ ትሆናለህ፡፡ ከሌላው መማር ነው እንጂ እንዴት ሌላውን እንዳለ ትቀዳለህ? እንደ እገሌ ጎበዝ ነው ሲባል እንጂ፣ እገሌን ይመስላል ሲባልኮ ጥሩ አይደለም፡፡ በራስ መመራት እንጂ መሳብኮ ደግ አይደለም፡፡»

እንዲህ እያወጋን አንድ ተሳቢ የሌለው የጭነት መኪና መጣ፡፡ ሾፌሩም ከመኪናው ወረደ፡፡ መንገድ ላይ ወደ ቀረው ተሳቢም ተጠጋ፡፡ ሆድ ዕቃውን ሲነካካው ቆየ፡፡ ከዚያም ከሳቢው ጋር የሚገናኝበትን ገመድ ፈታታው፡፡ የጭነት መኪናውን ወደ ተሳቢው አስጠጋና ገጠመው፡፡

«እንዴ ከሌላ መኪና ጋር ልትሄድ ነው እንዴ?» ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የተሳቢ ነገር ይሄውኮ ነው፡፡ የራስህ ጭንቅላት ከሌለህ ያገኘህ ሁሉ ይስብሃል፡፡ ሳቢ ተሳቢውን እንጂ ተሳቢ ሳቢውን አይመርጥም ሲባል አልሰማህም፡፡» አለኝ፡፡

«ታድያ አሁን ወዴት ነው የምትሄደው»

«እንደምሄድ እንጂ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም፡፡ ተሳቢ መሳቡን እንጂ መንገዱን አያውቅም፡፡» አለ፡፡

መኪናው አጓርቶ ተነሣ፡፡ ተሳቢውም ወደማያውቀው ቦታ ሄደ፡፡

ይህ ጽሑፍ ባለፈው ቀዳሜ በሮዝ መጽሔት ላይ ወጥቷል
 

48 comments:

 1. Dani it is a nice picture of most people

  ReplyDelete
 2. +++

  በጣም አስተማሪ ጽሁፍ ነው። ከልብ ወድጄዋለሁ። ያለችኝ አስተያዬት ግን ስለሚቀጥለው ጽሁፍህ ነው። ትንሽ ሞራላችንን ከፍ ለማድረግ እስኪ የምትቀጥለዋን ጽሁፍክን ትውልዱን የሚያሞግስና «እሰየው ይህንን ተግባራችሁን ወድጄዋለሁ!» የምትል አድርጋት። ወቀሳውና ትዝብቱ ብቻ ሲነገረው ሰው በባህርይው ለመማር ያለው ፍላጎት ተመልሶ ዝቅ ይላልና።

  ReplyDelete
 3. minew hulum begiziabiher tizaz besab?
  Egiziabiher tesgawin yabizalih! legnam mastewalun yisten.

  ReplyDelete
 4. KESDROS ZE MISRAKJune 6, 2010 at 9:21 PM

  WOW REALLY IT IS GREAT VIEW AND EXACTLY THE EXPRESSION OF MOST OF THE YOUN GENERATION WHO PREFERS TALKING RATHER THAN WORKING............

  ReplyDelete
 5. Thanks Dani very amazing observation, I've remembered Bewqetu Seyoum's poem
  ከደጅ የወደቀን ያንን ገለባ ልብ
  አድራሻህ ወዴት ነው ብለህ አትጠይቀው
  የነገው ነፋስ ነው አድራሻውን ሚያውቀው

  ReplyDelete
 6. Kale Hiwot Yasemalen Dn. Daniel

  ReplyDelete
 7. If only things were that simple. mechem tichit ende tor newe yemitferaw...ye hasab medegagem yitayal....Ferenj teketelin teketelin bla bla....ay dikuna degu...economiw, poleticaw, hulum be hager wist fikare yesus yemifeta yimeslhal.

  ReplyDelete
 8. Hi Dani,

  It is Amazing article.

  Kale hiwot yaseman, Tesabi kemehon yitebeken

  ReplyDelete
 9. + + +

  egziabeher yistilin Dn Daniel! endemasibew yebefitu nefse geday menesha mikniyat yehe tesabinetachin yimeslegnal, beminisemachew werewoch hulu tesiben, hulunim aminen tekebilen, hulunim lemastelalef sinitir new yan hulu sew yegedelinew. and andema yemisebenin neger tefetroawi maninet erasu maregaget eskisanen dires siniketel enitayalen, min ale yehe tesabinetachin wede-1 akitacha bicha hono wede-egziabhere ena we-de anditua hayimanotachin binisab, yehe be-ewinetu tirgum yalew mesab yihone neber

  Yeselam abat medhane-alem wedmengistu yisaben!
  amlak tibebun yabizalehe wendimachin!

  ReplyDelete
 10. D/n Daniel wud wondimachin yemitmertachewu arstoch hulu egigugin girum nachew enem ewunet lemenager kehon hulunm bewektu ayachewalehu yih ris beteley techeklen yekerenochin egnan mefithe endinfelig yemoterun ena yegasun dirsha yiyizal silezih anibabim anibibo lemetekem antem eskemechereshaw tsegawun abzitolih waga lemekefel yabikan elalehu!

  ReplyDelete
 11. በጣም አስተማሪ ጽሁፍ ነው። እጂግ ደስ ብሎኛል ነገር ግን ዳኒ ካላስቸገርኩህ እባክህ ስለ ማርክሲዝም እና ሌኒኒዝም ትንሽ መረጃና ያለህን አመለካከት ብትጽፍልን ደሰስ ይለኛል ምክንያቱም ብዙ ሰው እነዚህን ቃላት በብዛት ጽሁፎችህ ውስጥ ያገኙታል ነገር ግን በቂ ግንዛቤ ያለን አይመስለኝም፡፡

  ReplyDelete
 12. እራሴን፣ በዙሪያዩ ያሉትን ብዙ ሰዎችን ማንኛችን ሳቢ ማንኛችን ተሳቢ መሆናችንን እያሰብኩ ልክ እንደመስታወት እያየሁበት ነበር ያነበብኩት በጣም አስተማሪ ጹሁፍ ነው፡፡ እራሴንም አንዱ ቦታ ላይ አግኝቼዋለሁ እንደውም ሁጹፉ ስለ ራሴ የነገረኝ ነገር ቢኖር ትእቢተኛ መሆኔን ነው እ/ር በረዳኝ መጠን ለማስተካከል እጥራለሁ (ደግሞም አደርገዋለሁ)፡፡ ዳኒ ድክመታችንን የሚገልጽ ጹሁፉ እ/ር ያመለከተህን በናትህ በተደንብ ጻፍ ውስጤን በጣም በመልካም ነገር እያነጽከው ነው፡፡ እ/ር ይርዳህ፣ ያበርታህ አሜን

  ማኪ
  አ.አ

  ReplyDelete
 13. what surprises me, you present it differently what we see in our daily rutin life! may GOD bless you.

  ReplyDelete
 14. Dani good vision thanks big bro

  ReplyDelete
 15. It's exactly me!, no one else this article is all about...I see no repetition (Degegemosh). The guy who said so may not need it, but for me and those like me, it's all new. I am so fine to see my weakness from all angles, for it's then that my efforts will work to make a better me. Please u knowledgeable guys leave us alone here. If this is not for u, go somewhere else or start ur own and prove ur selves important.

  U ,Dani,keep the good work u've started..I, we need it!
  Glory be to God the Almighty!

  ReplyDelete
 16. it is good.but would you make it balance? this is the "con"what about the "pro"of us.

  dani,ALEGENA ALTENEKAM

  ReplyDelete
 17. Lesebategnaw asteyayet/comment ...
  Tichit besew lay sayihone ,bemiwetaw suhufu lay new mehone yalebet.lemin gilesebawi yihonal? tsuhufu ena tichitu yemayigenagnu nachew, tsuhufu yeminekan kehone kechalin ,betsufu temerten erasachinin mestekakel alebeleziya gin yalenin asteyayet betsuhufu lay mesten binichil tiru ayihonim?

  ReplyDelete
 18. ጥሩ ትዝብት ነው
  ሰው ወደ ልቡናው ተመልሶ እግዚአብሔርን መከተል ቢችል መልካም ነበረ
  የሚደንቀው ሳቢዎቹም ሳይቀሩ አቅጣጫው ጠፍቶባቸው ውሳጣዊ ሰላማቸውን አጥተው ማንነት ፍለጋ ወስጥ ገብተዋል
  "hulum be hager wist fikare yesus yemifeta yimeslhal" ብለህ የተናገርከው ወንድም "ካንተ ውጭ ወደአለው ነገር እየተመለከትክ ጊዜህን ከምታሳልፍ አሁኑኑ ውስጥህን አድምጠህ በሰላም በፍቅር በብልጽግና መኖር እጂግ የተሻለ ጥበብ መሆኑን እነግረሃለሁ"
  እግዚአብሔር ሙሉ አድርጎ ፈጥሮናል ወደ ራሱ ብቻ ተገናኝተን (being spiritually connected to God)በነፃነት እንድንኖር ክርስቶስ ነፃ አውጥቶናል አሜን

  ReplyDelete
 19. በጣም፡ የሚገርም፡ ምልከታ፡ ነው።

  ReplyDelete
 20. Thank you Dn. Danny
  It is very amazing observation...we always prefer the simplest way--like avoiding the cost of thinking. I think Tesabinet is the simplest life style...specially on this days it is how many people lead their life ...the very tipical nature of these people is they want every body to be their Tesby as they are Tesaby to some other one...
  GOD MAY BLESS YOU

  ReplyDelete
 21. BETAM ARIF TSIHUF NEW,ERASACHININ ENDINAY YIREDAL,BETINISHUM BIHON BETILIKU ABZAGNOCHACHIN YEZI TETEKIWOCH NEN.

  ReplyDelete
 22. It is a Very insightfulview as usual!

  ReplyDelete
 23. dear dn dani
  would you write about ማርክሲዝም እና ሌኒኒዝም. i want to know more about it please.

  ReplyDelete
 24. WE do more expect from you D/n Daniel .your so tremendous.We most Ethiopians are "tesabi" from abroad fashions .we better learn superior session and keep away their dreadful civilization
  Sami Nedafrom Abware

  ReplyDelete
 25. Dear Daniel,
  I like your writings. It is becoming a source of hope to me. I saw many of the things you are beautifully writing on your blog time and again. I am convinced that we deserve what we are facing as a nation. We made that to happen to ourselves, we allowed it to ruin our own future and the hope of the future generations.

  I am hoping because if some people like you started challenging themselves and their society by such a wisdom. May be some day we will gradually evolve for better.

  Thank you again
  Keep up the good work

  ReplyDelete
 26. Another great observation!!! Hope everybody who read this article will boldly underline the difference between 'meredadate' and 'meguatete'!!!

  ReplyDelete
 27. ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ የዳኒኤልን ዌብ ሳይት በሁሉም ዌብ ሳይቶች ሃሳብ መስጫ እንዲህ እያደረግን ይህንን የመሰሉ ወርቃማ ጽሁፍ ሌሎች ውንድሞችና እህቶች እንዲያንቡ ብናደርግስ? በዛ ላይ ማስተዋወቃችን ነው. ለዳነኣል የምለው እግዚአብሄር ጽናቱ ይስጥህ.

  http://www.danielkibret.com/2010/06/blog-post_06.html

  ReplyDelete
 28. I just want to say God bless you, your familly and your Job.

  G MN, USA.

  ReplyDelete
 29. በመንፈሳዊ

  እከሌ ይሚባል ሰባኪ ስብከቱ ግሩም ነው የት ነው ዛሬ የሚሰብከው
  ባክህ እሱን ተወው ባህታዊ እንትናን ብትከተል ይሻላል

  Everybody have to have point of reference which is bible. ሐዋርያትም ጌታን ሲጠይቁ
  አንተን በመከተላችን ምን እናገኛለን ብለውት ነበር፡፡ መርጦም ያቆብ፣ዮሐንስ እንዲሁም ጰጥሮስን ደብረ ታቦርን አዩ እኛም መጠየቃችን ወይም መከተላችን የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ መሆን አለበት፡፡ የምናበረታታውን ሐሳብ ግን ማበረታታት አለብን፡፡

  በአለም

  ከሶሻሊዝም፣ሊበራሊዝም፣ማርክሲዝም፣ሌኒንዝም ብዙ መማር የምንችላቸው አሉ ችግሩ ይሔ ብቻ ነው ትክክል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡
  ዲ. ዳንኤል
  ያገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልክ
  የህይወትን ቃል ያሰማህ

  ReplyDelete
 30. +++

  It's an interesting article of yours as usual. YES, we often are TESABIWECH. The bad part here is to stay always being TESABI. Sometimes, it's good to be TESABI for sometime and SABI when possible.

  It reminded me a train in the Western world where SABI & TESABI are one at a time, and move long distance together; but at a point they get separated and the SABI keeps its way forward or stay at a stop but the TESABI(the back part of the train) 'll detach itself and keep its won track. It's to say that we cannot be SABI all the time in every aspect but we can be TESABI for a certain time or until we reach a certain destination and then we 'll be on our own ( SABI). There is also a problem of being SABI all the time; You may face problems as a front mover ( so many challenges are there for front movers)and new things are tested by such SABIwech, too.

  HULGIZE KEMESAB GEN YISEWUREN!

  HG (Mekelle)

  ReplyDelete
 31. It is very intersting obsorvation . But, what I absent from the wrote about sport. Most young ethiopian people are likely to watch and know deeply about the biography of each soccor player in the world. But most young adolesences specially out of addis they can't called the names of ethiopian clubs more three; maight be they are very tired by them. Dni, I will expect some thing related with ethiopian soccer inyour next article. any way thanks for creating this valuable web.

  ReplyDelete
 32. ሸዋደግ ሞላJune 8, 2010 at 11:29 AM

  እጅግ በጣም በጣም በጣም ግሩም እይታ ነው። ተሣቢነት እንዴት ያለ አስቀያሚ ነገር ነው!

  በርታ ዳኒ

  ReplyDelete
 33. ካልህዎት ያሰማልን ጽኁፉን አንብቤ እንደጨረስኩ ከራሴ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ታዩኝ
  1.ምንም በማያውቁ ማለት ጊዚያዊ ጥቅም ለማኘት ብቻ እነሱም ወደማያውቁት መንገድ ብዙ ሰው በሚስቡ ሰዎች የሚሳቡ
  2. እነርሱ ሊኖሩበት ወደማይፈልጉት የጥፋት ቦታ ሰዎችን ስበው የሚያስገቡ እራስ ወዳዶች
  3. ወንድምህን እንደራስሀ ውደድ የሚለውን አምላካዊ ቃል እያወቁ እያስተማሩትም ነገር ግን ወንድሞቻቸውን ለግል ፍላጎታቸው ወደፈለጉበት እየሳቡ ከመስመር የሚያስወጡ ፍላጎታቸው ሲሟላ ተመጦጦ እንደተጣለ ሸንኮራአገዳ የትም የሚወረውሯቸው ያቆሙአቸው ቦታ እንኳን ትዝ የማይላቸው አገልጋይ ወንጌላውያን 'የጌታ ልጆች'
  4. ለቀጠሩቸው ሰራተኞች ለድርጅታቸው ትርፋማት እንዳልደከሙ አእነረርሰሱ በሰራተኞቻቸው ትጋት በተገኘው ሀብት እየተንደላቀቁ ሰራተኞቻቸው መጀመሪያ በተቀጠሩበት ደሞዝ ላይ አቁመዋቸው የጠፉ በየትላልቅ መዝናኛዎች ለማይረባ ነገር ገንዘባቸውን የሚረጩ ባለሀብቶች ሁሉ ትዝ አሉኝ
  ሁሉም ግን የፈጠረው አምላክ በሰጠው አእምሮ እየተመራ ለራሱም ለወገኑም የሚጠቅም የሚበጅ ተግባር ለመስራት 'ከአእምሮ ቅኝ ግዛት' ቢወጣ ይሻላል እላለሁ፡፡

  ReplyDelete
 34. Dn Daniel bizu tshufochin titsfaleh bezihm miknyat ejig bzu mugesawochina misganam yidersehal. lemehonu yekentu wudasen fetena endet malef yichalal? sefa yale mabraria efelgalehu mikinyatum bebzu neger enkifat honobigalina. EGZIABHER keante gar yihun amen!
  YTR.DER (B/DAR)

  ReplyDelete
 35. የሚገምርም አመለካከት ነው፡፡ ጎበዝ ከዚህ ምን እንማራለን፡፡

  ReplyDelete
 36. Please write also about the way out.And also come back to church articles also

  ReplyDelete
 37. dear bro Dani igzi'abher amlakachin iwketun ina tsegawn yabzalh.betam yemigerm hasab neger gin tilik iwket new iyenornbet gin yalastewalnew chigrachin new amlakachin be ante lay adro yastemeren igzi'abher yetemesegene yihun,
  really i miss the next one

  ReplyDelete
 38. ግሩም ጽሑፍ ናት ዳኒ ።

  ReplyDelete
 39. ...imagination....is the key to be a person; well explained D.Dani....God bless U!!

  ReplyDelete
 40. egzabhare yebarkeh yabu dabi debra selam agalegayoche print out eyadaragu lamemanan eyadaresu neawn egzabehare yasbachew

  ReplyDelete
 41. instead of reading for a year or more, it is good to stay for a while with Daniel.Because if we use our intelligent friends wisely, they are books by themselves
  I like Daniel's view.

  ReplyDelete
 42. Kale Hiwot Yasemalin D. Daniel. Egziabhair Tsegahin Yitebiklih!

  Ameha Giyorgis
  DC

  ReplyDelete
 43. It is really great .now everyone who read this message will have a time to think where he was standing .
  thank you Memher Dani

  ReplyDelete
 44. it is realy great opportunity to read from a different angle now is the time to know who is tesabi and who will be sabi.dn daneal God bless you.

  ReplyDelete
 45. «እንዴ ከሌላ መኪና ጋር ልትሄድ ነው እንዴ?» ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የተሳቢ ነገር ይሄውኮ ነው፡፡ የራስህ ጭንቅላት ከሌለህ ያገኘህ ሁሉ ይስብሃል፡፡ ሳቢ ተሳቢውን እንጂ ተሳቢ ሳቢውን አይመርጥም ሲባል አልሰማህም፡፡» አለኝ::የአንዳመት ተውስታው ላይ ተሳቢን ጠቅሳችሁት ነበር እኔ ደግሞ አላነበብኩትም ነበር ቢሆንም አሁንም ቆይቶ አንብቤዋለው ደስ ያላል ዳኒ እናመሰግናለን

  ReplyDelete
 46. ሳሚ(ወ/ሚካኤል)January 24, 2012 at 6:22 PM

  መምህር ዳኒ…በእንዲህ አይነቶቹ ሀገራዊ ምልከታዎችህ ላይ ተመስርቸ ልሰራ ያሰብኩት ትልቅ ጥበባዊ ራእይ አለኝ፡፡እግዚአብሄር ፈቅዶ እንዲሳካና ትውልድን የመቅረጽ አቅምህን እንድታውቀው ይህ የዘወትር ፀሎቴ ነው፡፡
  ካንተ የፈሰሰውን ጅረት በኔ ማሰሮ ቆጥሬ በጥበብ ዳገት ላይ በመቆም የሰዎችን ጥም ለማርካትና የተበላሹበትን የጥቁር አስተሳሰብ ጥላሸት ለማጠብ ስባዝን ታገኘኛለህ ብየ በእግዚአብሄር ታምኛለሁ!!! ይሁን ይደረግ በለኝ ዳኒ!!!
  ዞትር ወደ ሰማየ-ኢንተርኔት አንጋጥጨ እግዚአብሄር ዳንኤል ከተባለው ደመና ከሚያወርደው ዝናብ ማሰሮየን እንዲሞላ በጊዜው ሁሉ ማዝነብን ይሰጠው ዘንድ ስለደመናው እማልዳለሁ!!! አሜን!!!
  ሳሚ(ወ/ሚካኤል)ሰመራ

  ReplyDelete