Tuesday, June 29, 2010

ኤልዛቤል ከታሪክ አንድ ገጽ

ታሪክ ራሱን ይደግማል ይባላል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ምሳሌዎች በአንድ ወቅት ብቻ ተፈጽመው የቀሩ ታሪኮች አይደሉም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በየዘመናቱ የሚከሰቱ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ ለክፉም ሆነ ለበጎ ምሳሌ ሆነው የተጻፉ ታሪኮች፣ ቤተ ክርስቲያንን የመከራ እና የደስታ ዘመናት ተከትለው ይፈጸማሉ፡፡ የዮሐንስ ራእይን ለመተርጎም ከተጻፉ ከግሪክ እና ሶርያ የጥንታውያን መዛግብት ያገኘሁትን ይህንን ትርጓሜ እስኪ ተመልከቱት፡፡

ነገር ግን አንተን የምነቅፍበት ነገር አለኝ፡፡ ሳትሆን ራስዋን ነቢይት ነኝ የምትለውን አገልጋዮቼንም ለጣዖት የተሠዋውን እንዲበሉ እና እንዲሴስኑ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ዝም ብለሃታልና (ራእይ 2÷20)

ኤልዛቤል ማናት?

Saturday, June 26, 2010

171ኛው ሆስፒታል

በዓለም በደረጃው 171ኛ በሆነው ሆስፒታል ውስጥ ነው ከዚህ የሚከተለው ታሪክ የተፈ ጸመው፡፡ ይህ ሆስፒታል ዛሬ አንድ መቶ ሰባ አንደኛ ይሁን እንጂ እጅግ ገናና የሆነ ታሪክ እና ዝና የነበረው ነው፡፡ አያሌ ከባድ በሽታዎችን ድል እየመታ፣ ታላላቅ ሰዎችን እያፈራ፣ ለአንድም ቀን በበሽታ ሳይደፈር የኖረ ሆስፒታል ነው – 171ኛው ሆስፒታል፡፡

አንድ ቀን የሆስፒታሉ አምስት ሠራተኞች ሻሂ እየጠጡ የቆጥ የባጡን ይጨዋወቱ ነበር፡፡ በመካከል ላይ «እኛ ለብዙ ዓመታት በዚህ ሆስፒታል ውስጥ እየሠራን ነው፤ ሆስፒታላችን ግን እናውቃለን በሚሉ ጥቂት ዶክተሮች የተያዘ ነው፡፡ እነዚህ አምስት እና ስድስት ዶክተሮች ብቻ ናቸው ቀዶ ሕክምና እያደረጉ የሚያክሙት፡፡ በዚህ ምክንያትም ገንዘብ፣ ስም እና ዝና ያገኙት እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የጥቂት ዶክተሮች አስ ተዳደር ማብቃት አለበት፡፡ ሁላችንም ይህ ዕድል ያለ አድልዎ ሊሰጠን ይገባል» የሚል ሃሳብ አነሡ፡፡ ይህ ሃሳብ እንደ ሰደድ እሳት በሆስፒታሉ ውስጥ በአንድ ጊዜ ተነዛ፡፡ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ጸሐፊዎች፣ የጤና ረዳቶች፣ መዝገብ ቤቶች፣ አትክልተኞች፣ ምግብ ቤቶች፣ ፋርማሲስቶች፣ የጥገና ባለሞያዎች፣ ግዥ ክፍሎች፣ ሌሎችም ሃሳቡን በመደገፍ ተነሡ፡፡ «ካሁን በኋላ የጥቂት ዶክተሮች የአገዛዝ ዘመን ማብቃት አለበት» የሚለው መፈክር ይስተጋባ ጀመር፡፡

Monday, June 21, 2010

ሦስተኛው ወር


እነሆ የፊታችን ሰኔ 15 ቀን 2002 ዓም ይህንን ጡመራ የጀመርኩበት ሦስተኛ ወር ይሆናል፡፡ በእነዚህ ሦስት ወራት ውስጥ 44 ጽሑፎች ተለቅቀዋል፡፡ በአጠቃላይም በ67 ሀገሮች የሚገኙ አማርኛ አንባቢዎች ተመልክተውታል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት የኢትዮጵያ አንባቢዎች ቅድሚያውን የሚያገኙ ሲሆን የአሜሪካ አንባቢዎች ሁለተኛውን ይይዛሉ፡፡ ካናዳውችም ከጀርመን ቀጥለው አራተኞች ናቸው፡፡

Saturday, June 19, 2010

ወንበሩ ነው እንዴ?

የአመለካከት ለውጥ በሰዎች ኅሊና ውስጥ ካልመጣ አሠራሮች እና መመሪያዎች ብቻቸውን ምን ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ጨለማን መተቸት ብርሃን፣ ክፉን መተቸት ደግነት፣ ኋላ ቀርነትን መተቸት ብቻውን ሥልጣኔ፣ ድንቁርናን መተቸት ብቻውን ዕውቀት አያመጣም፡፡ በሽታውን ተቃውመሃል ማለት መድኃኒቱን ይዘሃል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ረሃብን ታወገዛለህ ማለት ጥጋብን ታመጣለህ ማለት ነው የሚለውን ዋስትና አያሰጥም፡፡ አንዳንዴ በተቃራኒውስ ሊሆን ቢችል?

ጥቂት የገረሙኝን ነገሮች እስቲ መጀመርያ ላካፍላችሁ፡፡ ተራ ሰው እያለ ጨዋ፣ ሰው አክባሪ፣ እንኳን የሰው ገንዘብ ሊወስድ የራሱን አበድሮ የማያስመልስ፣ በሀገሩ ኋላ መቅረት የሚቆጭ፣ በሞሳኞች የሚናደድ፣ በቢሮክራሲ የሚማረር የነበረ ሰው ዕድሉን አግኝቶ ቦታውን ሲይዘው፣ ሲጠላው የነበረውን ነገር ለምንድን ነው በባሰ ሁኔታ ሲፈጽመው የሚገኘው ?

ተራ አገልጋዮች እያሉ ትጉኃን፣ ብቁዐን፣ ቅኑዐን፣ መንፈሳውያን የነበሩ ሰዎች እንዴት ነው የሥልጣኑን ቦታ ሲይዙት፣ ደግነታቸው እና ቅንነታቸው፣ መንፈሳዊነታቸውና ታማኝነታቸው ሁሉ ጠፍቶባቸው «ሥልጣን በቀረባቸው ኖሮ» እስከመባል የሚደርሱት?

Monday, June 14, 2010

የዓለም ዋንጫ በኢትዮጵያ

አሥራ ዘጠነኛው የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ምድር በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ሀገራቸውን የወከሉ ቡድኖች ዋንጫ ለመሳም ይፋለማሉ፡፡ እኔ ግን «የኳስ ብቻ ነው እንዴ ዋንጫ ያለው? የሀገርስ ዋንጫ የለውም እንዴ?» ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ «ሀገር እንደ ቡድን ለዋንጫ አይጫወትም ወይ» እያልኩ አሰላስላለሁ፡፡ እናም ኅሊናዬ «ይጫወታል እንጂ» አለና የሚከተለውን ወግ አወጋኝ፡፡

ባታውቀው ይሆናል እንጂ ሀገርማ እንደ ቡድን ለዋንጫ ይጫወታል፡፡ ይሄው ኢትዮጵያ እንኳን ስንት ጊዜ ለዋንጫ ተጫውታለችኮ፡፡ ታድያ እንደ እግር ኳሱ አይደለም፡፡ በዚህኛው ግጥሚያ ዋንጫ የበላችበትም፣ ያጣችበትም ጊዜ አለ፡፡ በርግጥ በታሪክ መዝጋቢዎች ዘንድ አንድ ልዩነት ተከስቷል፡፡ አንዳንዶች ዋንጫ ካጣችበት ይልቅ የበላችበት ጊዜ ይበልጣል ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ዋንጫ ካገኘችበት ይልቅ ያጣችበት ጊዜ ይበልጣል ይላሉ፡፡

Friday, June 11, 2010

ዝምታ ወርቅ አይደለም

ሰውዬው ከሚስቱ ሌላ አንዲት ሴት ወደደና እፍ ክንፍ አለ፡፡ ልጁን እና ሚስቱን እየተወ ከዚህችኛይቱ ጋር ማምሸት፣ ብሎም ማደር ጀመረ፡፡ በመጨረሻም አንድ ቀን ወደ ሚስቱ መጣና ድንገተኛ የሆነ ጥያቄ አቀረበ፡፡ «እኔ እና አንቺ እንድንፋታ እፈልጋለሁ፤ ለምን ብለሽ ምክንያቱን አትጠይቂኝ፡፡ መፋታት ብቻ እፈልጋለሁ፡፡ ደግሞም ሌላ ቀን አይደለም፣ ነገ እንዲሆን እፈልጋለሁ» አላት፡፡ ሚስቱ በሁለት ነገሮች ተጨነቀች፡፡ በአንድ በኩል ምንም ነገር አትጠይቂኝ ብሏታል፡፡ በሁለተኛ ነገር ልጇ ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ፈተና ልትቀመጥ ጥቂት ቀናት ቀርቷታል፡፡

«ባልፈልገውም፣ ባልስማማበትም፤ ካልክ የግድ እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን በኛ ምክንያት ልጃችን መጎዳት የለባትምና የአንድ ወር ጊዜ ያህል እንታገሥ፡፡» አለችው፡፡ እርሱም አሰበና «ጥሩ አንድ ወር መታገሥ አያቅተኝም፤ ነገር ግን በዚህ አንድ ወር ውስጥ ሽማግሌ መላክ፣ ምክንያቱን መጠየቅ የለም፤ ስለ ፍቺው ማናችንም ምንም ነገር ማንሣት የለብንም፤ በዚህ ቃል ግቢ» አላት፡፡ እርሷም «እስማማለሁ፤ ግን አንተም የምነግርህን ለመፈጸም ከተስማማህ ነው፤ ታድያ በዚህ አንድ ወር ጠዋት ጠዋት ከዕንቅልፌ ስነሣ፣ ማታ ማታም ወደ አልጋዬ ስሄድ ያኔ የሠርጋችን ዕለት አቅፈህ እንደ ወሰድከኝ አድርገህ አቅፈህ ትወስደኛለህ» ስትል ጠየቀችው፡፡ ነገሩ ያልጠበቀው እና ያልተለመደ ዓይነት ቢሆንበትም፣ ቀላል እና ሊያደርገው የሚችል ስለሆነ እሽ ብሎ ቃል ገባላት፡፡

አንዱ ወር ተጀመረ፡፡

Tuesday, June 8, 2010

አለቃ ገብረ ሐና ተረት ናቸው ወይስ እውነት ? ክፍል ሁለት

ብዙዎቻችን ስለ አለቃ ገብረሐና ከልጅነታችን ጀምሮ ሰምተናል፡፡ አለቃ እንዲህ አሉ፣ይህንን መልስ ሰጡ፣እገሌን እንዲህ ብለው ቀለዱበት ወዘተ እየተባለ ተነግሮናል፡፡ታድያ ዘመኑ እየረዘመ ሲመጣ በብዙዎች ዘንድ አለቃ በተረት እንደነ ስንዝሮ የምናውቃቸው ሰው ናቸው ወይስ በዚህች ምድር አካል ነሥተው፣ነፍስ ዘርተው ተመላልሰዋል? የሚለው ጥያቄ ይነሣል፡፡ የዚህ ጥያቄ መነሻ ምክንያቱ ሁለት ይመስለኛል፡፡ አንዱ የታላላቅ ሰዎችን ሥራ በሚገባ መዝግቦ፣መታሰቢያቸውን አደራጅቶ፣ሥራቸው በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ልማዳችን እጅግም በመሆኑ አለቃ በቃል ብቻ በሚነገረው ሥራቸው እና ታሪካቸው የተነሣ ወደ ተረትነት በመቀየራቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዘመናችን ከኮምፒውተር፣ ከስልክ፣ ከመኪና እና ከአውሮፕላን ጋር የተያያዙ ቀልዶች ሁሉ በስማቸው ሲነገሩ ጊዜ አለቃ ገብረ ሐና እግዚአብሔር የፈጠራቸው ሰው ከመሆን ይልቅ በየዘመኑ የተነሣ ትውልድ ማለት የሚፈልገውን ሁሉ በስማቸው የሚልባቸው የተረት ገጸ ባሕርይ መስለው ታዩ፡፡

አለቃ ገብረ ሐና ግን በዚህች ምድር በኢትዮጵያ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ፎገራ ወረዳ ፣ናበጋ ጊዮርጊስ አጥቢያ ተወልደው ያደጉ የተፈጥሮ ሰው ናቸው፡፡ይህንን በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያገኛቸውን ያህል ማስረጃዎች ቀጥሎ ያቀርባል፡፡

Sunday, June 6, 2010

ተሳቢ

በቀደም ዕለት ነው፡፡ በአንድ ትልቅ አውራ ጎዳና ላይ አንድ የጭነት መኪና ከነ ተሳቢው ይጓዛል፡፡ እየሄደ ቆየና ድንገት ቆም አለ፡፡ ሾፌሩም ከጋቢናው ወረደና ወደ ተሳቢው አመራ፡፡ ሆድ ዕቃውን እና ዳሌውን ፈታተሸው፡፡ ከሳቢው ጋር የተያያዘበትን ገመድም አየው፡፡ ጎማዎቹን መታ መታ አደረጋቸው፡፡ እኔ የሚያደርገውን እንጂ የሚያስበውን ለማየት አልታደልኩም፡፡

ወደ ጋቢናው ተመለሰና መፍቻ ነገሮች ይዞ ወጣ፡፡ አንድ ሌላ ሰውም ዓይኖቹን እየደባበሰ አብሮት ወረደ፡፡ ምናልባት የደከመው ረዳት ይሆናል ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ ለሁለት ተጋግዘው ብረቱን ፈቱና ሳቢውን ከተሳቢው ለዩት፡፡ የመሳቢያውን ብረት መሬት አስነከሱና ተሳቢውን ወደፊት ሳብ አደረጉት፡፡ ከአካባቢው ብቅ ብቅ ያሉ ወጣቶች ልምድ ባለው አኳኋን ቀረቡና ለጥበቃ ሥራ በገንዘብ ተደራደሩ፡፡ ተስማሙ መሰለኝ፡፡ ሾፌሩ እና ረዳቱ ጋቢና ውስጥ ገብተው መኪናውን እያስጓሩ ወሰዱት፡፡ ምስኪኑ ተሳቢ ግን በቆመበት ቀረ፡፡

Friday, June 4, 2010

ሰበር ዜና


   አያሌ ኢትዮጵያውያንን የጨረሰው ነፍሰ ገዳይ እስካሁን አልተያዘም

አያሌ ኢትዮጵያውያንን ሳያውቁት በማታልለ፣ ዐውቀውትም ለመኖር ሲሉ በማስገደድ የገደለውና አሁንም ነፍስ እያጠፋ ያለውን ገዳይ እስካሁን ለመያዝ እንዳልቻለ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ይህ ነፍሰ ገዳይ ራሱን በተለያዩ ስሞች በየጊዜው የሚቀያይር ሲሆን በተለይም «አሉ» «ተባለ» «ይላሉ» «ይባላል» የሚሉትን ስሞች ይበልጥ እንደሚጠቀምባቸው ታውቋል፡፡

Thursday, June 3, 2010

ሰበር ዜና

አያሌ ኢትዮጵያውያንን የጨረሰው ነፍሰ ገዳይ እስካሁን አልተያዘም


ዝርዝሩን ነገ ዓርብ ይጠብቁ