Tuesday, May 18, 2010

ልዩ መርሐ ግብር ከግንቦት 10 እስከ 12ቅዱስ ያሬድ ማነው?


 የቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/  ይባላሉ /በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡/ የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/  ሚያዝያ 5 ቀን የሚል አለ/ ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡

ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ


ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኀ ፃማ ዘአልቦ ሐጻጼ
መልዕልተ ዕፅ /ኮሞ/ ነጸሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ

የሚል ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ ይህን አርኬ የድጓ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሷቸዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁናን ቀጥሎም ሢመተ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይን ከሦስት ወፎች/መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ በወፍ የተመሰሉ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ24ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ3 ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን «ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ» ብሎ አዜመ፡፡ ይህን ዜማ የደረሰበት ወሩ ታኅሳስ ቀኑም ዕለተ ሰኞ ነው ይባላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው «አርያም» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ የተሰጠው ስም ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ይህንን ዜማ በተመስጦ ሲያዜም ንጉሡ፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ መኳንንቱና ካህናቱ ወደ አኩስም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መጥተው በአድናቆት ያዳምጡት ነበር፡፡ ምክንያቱም ገደለ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገልጥልን ከዚያ በፊት በውርድ ንባብ ከሚደረግ ጸሎትና መንፈሳዊ አገልገሎት በቀር ይህን የመሰለ ዜማ አልነበረምና፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ፣የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ፣ እንዲሁም ለልዑል እግዚአብሔር፣ለእመቤታችን፣ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸውና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡ ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ፣ በእዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን ለነዚህም ስምንት የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ አንዴት ሁሉንም ይመስጥና ወደ አርያም በመንፈስ ይወስድ እንደ ነበር ለማስረዳት በገድሉም በሌሎችም መጻሕፍት የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ገብረ መስቀል፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በተሰባሰቡበት ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲያዜም ንጉሡ በመመሰጡ የተነሣ በመሰቀል ተሰላጢኑ ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው፡፡ ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ መዝሙሩን ሲፈጽም ንጉሡ መስቀል ተሰላጢኑን ቢያነሳው የቅዱስ ያሬድ ደሙ ፈሰሰ፡፡ ንጉሡ በዚህ ደንግጦ ለዚህ ካሣ ይሆን ዘንድ የፈለግከውን ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምናኔ መኖርና መዝሙሩንም በሚገባ ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ገለጠ፡፡ ምንም እንኳን አኩስምን ለቅቆ መውጣቱ ንጉሡን ቅር ቢያሰኘውም ቃሉን አንድ ጊዜ በመስጠቱ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከዚህ በኋላ አኩስምን ለቅቆ ወደ ስሜን ተራራ ጸለምት መጓዙ ይነገራል፡፡

በጐንደር ፎገራ በሚባል ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ ጣዕም ያለው ዜማውን ሲዘምር ተጠምደው የሚያርሱ በሬዎች ድምፁን እየሰሙ ገበሬውን ሥራ ስለ አስፈቱት በዚህ ተናዶ ቅዱስ ያሬድን በጅራፍ እንደ ገረፈው ይነገራል፡፡ ቦታውም «ወርቀ ደም´ እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል፡፡ ወርቃማና ንጹሕ ደሙ የፈሰሰበት ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ 11 ዓመት አስተምሯል፡፡ በእርሱ ዘመን ተሰዓቱ ቅዱሳን በሃይማኖት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መጥተው ስለ ነበር ቅዱስ ያሬድ ከአንዱ ከአባ ጰንጠሌዎን የውጭውን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቅ ነበር፡፡ በጆሮ የሰማውንም በዓይን ለማየት ሁለት ጊዜ ሮም የተባለችውን የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጐበኘሁ ይላል፡፡ «ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርዒክዋ» እንዲል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ለቁስጥንጥንያ ዜማ መነሻው ቅዱስ ያሬድ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚያደርጉት የቁስጥንጥንያን ዜማ የደረሰው ሊቅ ዜማውን አገኘው የሚባለው የቅድስት ሶፍያን ቤተ ክርስቲያን ሲዞር ከሰማው ዜማ ነው፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከተነሣበትና ወደ ሮሜ ሄድኩ ካለበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ምናልባት ያ ሰው ዜማውን የሰማው የቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያንን እየዞረ ሲዘምር ከነበረው ከቅዱስ ያሬድ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ Ancient and medival Ethiopian History/

ቅዱስ ያሬድ ማትያስና ዮሴፍ በተባሉ የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርት መሪነት ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ወጥቶ ከጻድቁ ጋር በመገናኘትና የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እያደነቀ ዙሪያውን ከዞረ በኋላ «ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፃሃ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን» ሲል ዘመረ፡፡ በዚያም ለአንድ ሳምንት ሰንብቶ ሄዷል፡፡

ቅዱስ ያሬደ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ጋር በመሆን በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና እስከ ጋሞጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ በመሄድ አስተምሯል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዐርባ ምንጭን ታሪክ ከቅዱስ ያሬድ፣ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ታሪክ ጋር ያያይዙታል፡፡ ሦስቱም ብርብር ማርያምን ለማየት ሄደው በነበረ ጊዜ በዛሬው ዐርባ ምንሥ አካባቢ ሠፍረው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ለወታደሩ የሚበቃ የሚጠጣ ውኃ በመጥፋቱ አቡነ አረጋዊ ጸልየው መሬቱን በመስቀል ቢመቱት ዐርባ ውኃዎች ፈለቁ ይባላል፡፡

ዐፄ ገብረ መስቀል የጣና ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያንን በሚያሠራ ጊዜ በዚያ ቦታ ለሁለት ዓመት ተቀምጦ ድጓውን በማስተማሩ ምልክት የሌለው ድጓው እስከ ዛሬ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ቀጥሎም የዙር አባን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ወደ ጋይንት በተጓዙ ጊዜም በዚያ ሁለት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለ ድርሰቱን አስተምሯል፡፡ ይህ ቦታ እስከ ዛሬ የዚህ ትምህርት ማስመስከሪያ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከዚያ በኋላ ወደ አከሱም ተመልሶ በመደባይ ታብር በተባለ ቦታ ቅዳሴያትን በዜማ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቦታ ከአከሱም 15 ኪ.ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አኩስምን ተሰናብቶ ለመሄድ ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገባና «ቅድስት ወብጽዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን ማዕርገ ሕይወት» እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን ድርሰቱን ሰተት አድርጎ አዘጋጀው፡፡ ይህንን ድርሰት ሲያዜም አንድ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ብሎ ይታይ ነበር ይባላል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በሰሜንና ወገራ፣ አገውና በጌምድር እየተዘዋወረ አስተምሮ ከሰሜን ተራራዎች ውስጥ እየጾመና እየ[ለየ በብሕትውና ለብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ባለው በጸለምት ዋሻ ውስጥ በ571 ዓ.ም ግንቦት 11 ቀን ተሠውሯል፡፡ ይህ ቦታ በተለምዶ የሰሜን ተራሮች በሚባለው ወስጥ የሚገኝ ከፍተኛና ብርዳማ ቦታ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ከማስተማሩም በላይ ለቅኔ ትምህርትም መሠረት ጥሏል፡፡

መቼም ለኢትዮጵያ ሊቃውንት ትልቁ ጥፋታቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ጊዜ አውሮፓዊ ወይንም አሜሪካዊ ቢሆን ኖሮ በስሙ የማይጠራ ነገር ባልነበረ ነበር፡፡ መንገዱ፣ትምህርት ቤቱ፣ ኮሌጁ፣ አደባባዩ፣ ምኑ ቅጡ፡፡ እኛም የፈረንጅ ነገር ስለምንወድ በየመማርያ መጽሐፋችን በተማርነው ነበር፡፡ ኢትዮያዊ ሆነና ተጎዳ፡፡ የመጀመርያዋን ዜማ የዘመረባት ቦታ እንኳን እንደ ዋዛ በድንጋይ ታጥራ ምልክት እንኳን የላትም፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በቀር ሀገሪቱ በስሙ ምንም አልሰየመችለትም፡፡ ያሬድ ግን በዓለም ላይ የመጀመርው የዜማ ኖታ/ ምልክት/ ባለቤት ነው፡፡ አሁን ለኛ ከፑኽኪን እና ከያሬድ የቱ ይቀርበናል፡፡ ከቸርችል እና ከያሬድ የቱ ይጠቅመናል፤ ከደጎል አደባባይ እና ከያሬድ አደባባይ የቱ ያኮራናል፤ ከቤኒን መንገድ እና ከቅዱስ ያሬድ መንገድ የቱ ይሻለናል፡፡

በርግጥ አሁን አሁን ጅምሮች ይታያሉ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ዩኒቨርሲቲ በአኩስም ከተማ ለመገንባት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ተጀምሯል፡፡ የከተማው ምክር ቤትም ቦታ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ ያድርሰን ብቻ፡፡

እስኪ አንድ ሃሳብ ላቅርብ፡፡ እናንተም ጨምሩበት፡፡ በ2005 ዓም የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ ዓመት ለማክበር በያላችሁበት በበጎ ፈቃደኛነት ኮሚቴ አቋቁሙ፡፡ ሌላ ሰው እንዲመጣ እባካችሁ አትጠብቁ፡፡ ዌብ ሳይት ሥሩ፤ ፌስ ቡክ ግሩፕ ክፈቱ፡፡ በየቦታው የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት በዓል ኮሚቴ የሚል አደራጁና በዐውደ ጥናት፣ በአውደ ርእይ፣ በዝማሬ፣ እናክብረው፡፡ የዜማ ሊቃውንት ዝማሬ አዘጋጁ፤ ሰዓሊዎች የሥዕል ዐውደ ርእይ አዘጋጁ፡፡ የዜማ ባለሞያዎች ስለ ቅዱስ ያሬድ ዜማ ለዓለም የሚያስተዋወቅ መርሐ ግብር ዘርጉ፡፡ ነገ አይደለም ዛሬ እንጀምር፡፡ ክብረ በዓሉ በ2004 ሚያዝያ  5 ቀን ይጀመርና በ2005 ግንቦት 11 ቀን ይፈጸም፡፡ እስኪ ሌላም ሃሳብ ጨምሩበትና አንዳች ታሪክ እንሥራ፡፡ እንዴው ግን ግንቦት 11 የዓመቱ የዜማ ቀን ቢሆን ምን ይመስላችኋል?32 comments:

 1. Betam yetekedese hasab newu bewuchim be wustim yalenewu lezeh sira enebeerta.

  Egziabher Agelgilotehen yebarkewu.

  ReplyDelete
 2. St Yared is one of the most famous in Ethopian Orthodox church and in Ethiopians even in the world who is very spiritual person,

  Daniel God bless you for you remember us it.

  We and my friend those live in my arround we will do that,

  God bless Ethiopia,

  ReplyDelete
 3. do not Forget This days,,, the so called Song or rap , Are We on the Right Line please We have To pray Cry Somethings Become Delted

  Dn

  ReplyDelete
 4. እውኑ ከወልድያ
  የቅዱስ ያሬድ በረከት ይደርብህ፣ ይደርብን፡፡

  ReplyDelete
 5. kalehiwet yesemaln, ende matusala edme yisitlin

  ReplyDelete
 6. Kale Hiwot Yasemalen
  Dani Kidus Yared Agelgilotihen Yibark

  ReplyDelete
 7. ቃለ ህይወት ያሰማልን! ዲን. ዳንኤል
  ውስጣችን ያለውን የሩቅ ናፋቂነታችንን አሳየኸን። በተለይ ለመንፈሳዊ ማንነታችን እና ለእኛነታችን በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘት ምክንያት የሆኑ ቅዱሳት አባቶቻችን ተረስተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፍጹም በሆነ ከመላዕክት በተገኘ ዜማ ፳፬ ሰዓት ስብሃተ እግዚአብሔርን የምታቀርብ በዓለም ብቸኛ የእምነት ተቋም ናት። እኛ በረከቱ ቀረብን እንጂ ዛሬም ድረስ የዚህ ፍሬ ተጠቃሚዎች ቤተ ክርስቲያን አሏት።
  በማህሌት ሰዓት ዕድሜያቸው ፸ እና ፹ የሚደርሱ አረጋውያን ካህናት ከቅዱስ ያሬድ የተረከቡትን ዜማ ያለ ዕረፍት በተመስጦ ሲያዜሙት ማየት እንዴት ልብን ይነካ! በዕንባ ጭምር የሚያዜሙ አባቶችን ለማየት በቅተናል። ድሮስ እግዚዘብሔር በመንበሩ በመላእክት የሚመሰገንበትን ዜማ ለኛ ለኢትዮጵያውያን “ብቻ!” መርጦ ሰጥቶ ቸርነቱን፤ ምርጫውን፡ አስቦ ልቡ የማይነካ ማን አለ።
  የቅዱስ ያሬድ ዜማ ምስጋና፤ ትምህርት፡ ምስራች፡ ምክር፤ ተግሳጽ፡ ንሰሃ፡ ሃዘን፡ መውደቅ፡ መነሳት፡ወዘተ… የሚገለጽበት ከመሆኑም በላይ ስለመልክዐ ምድር፡ ስለ መሬት እና አዝዕርት፡ ስለውሃ፡ ስለጠፈር፡ ስለነፋሳት፡ ስለዕጽዋት እና አዝዕርት፡ ስለግብርና እና ስለሌሎች ጠቅሰን ስለማንጨርሳቸው ጉዳዮች ሁሉ ዲን. ደንኤል እንዳለከው በወቅትና በዓላት ተቀምረው የተዘጋጁ መንፈሳዊ ሃብታት ገላጭ ነው።
  ያነሳኸው ቅዱስ ያሬድን እና ሥራዎቹን የመዘከር መርሃ ግብር በበኩሌ በጣም ተደስቸበታለሁ።
  እኔም ከዓመት በላይ ቅዱስ ያሬድን ለመዘከር የጀመርኳት ሥራ ነበረችኝ። ነገር ግን በስንፍና ምክንያት ከፍጻሜ አላደረስኳትም ነበር። ሃሳብህ ብዙ ምዕመናንን ያሰባስባል እኔም የጀመርኳትን እገፋባታለሁ።
  ቅዱሳንን በአገልግሎት ያጸና አምላክ እኛንም ያጽናን።
  ፍተ

  ReplyDelete
 8. ወለተብርሃንMay 19, 2010 at 10:19 AM

  ሰላም ዲ.ዳኒኤል እስከዛሬ ይቆጨኝ የነበረው በግጥሙም በታሪኩም ግሩም አድርገህ ገልጸኸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ የዜማ መናጋት፣ ቅዱስ ያሬድ ተዘንግቶ የሌለ ያሬድን ታሪክ ለማውራትና ለመተረክ የሚዳዳቸው ወይንም አዲስ ያሬዳውያን ነን ባዮች መነሳታቸውና የቀድሞው እውነተኛ ታሪክ በመዘንጋቱ ነው፡፡

  በእውነት ያነሳኻቸው ነጥቦች የተቀደሱ ናቸው፡፡ ከንባብ አልፎ ተግባራዊ ከሆነ ትልቅ ታሪክን ሰርቶ እንደሚያልፍ ተስፋ አለኝ፡፡ የቅዱሱ የያሬድ አምላክ የተግባር ሰዎች ያድርገን፡፡ በበረከቱ ይጎብኘን፡፡

  አንተንም ቃለ ሕይወት ያሰማልን ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን!

  ወለተብርሃን.

  ReplyDelete
 9. ቃለ ህይወት ያሰማልን :አንተንም በግልጋሎት ያበርታልን :ከቅ/ ያሬድ በረከት ያሳትፈን::

  ReplyDelete
 10. ቅዱስ፡ያሬድ፥በተመስጦ፡ወደ፡ሰማይ፡ተነጥቆ፥ከሱራፌልና፡ከኪሩቤል፡ማሕሌትን፡ተምሮ፡በሦስት፡ሰዓት፡እንደ፡ተመለሰ፥አኵስም፡ከተ ማ፡ወደምትገኘው፡ወደ፡ጽዮን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ገብቶ፥እታቦተ፡ጽዮን፡ፊት፡ቆሞ፥ድምፁ ን፡ከፍ፡አድርጎ፤«ሃሌ፡ሉያ፡ለአብ፤ሃሌ፡ሉያ፡ለወልድ፤ሃሌ፡ሉያ፡ለመንፈስ፡ቅዱስ፤ቀ ዳሜሃ፡ለጽዮን፡ሰማየ፡ሣረረ፤ወበዳግም፡አርኣዮ፡ለሙሴ፡ዘከመ፡ይገብር፡ግብራ፡ለደብተራ ።»፡(ለአብ፡ምስጋና፡ይገባል፤ለወልድም፡ምስጋና፡ይገባል፤ለመንፈስ፡ቅዱስም፡ምስጋና፡ይገባል ፤ከጽዮን፡አስቀድሞ፡ሰማይን፡ፈጠረ፤ዳግመኛም፡ለሙሴ፡የድንኳኑን፡ሥራ፡አሳየው።)፡ብሎ፡በልሳነ፡ግእዝ፡ዘመረ፡(ዘፀ.፡ም.፡፳፭፥ቍ.፡፰-፲)፡

  ReplyDelete
 11. እግዚአብሔር ይስጥልኝ አንደ ቅ ያሬድ አጥንት የሚያለመልመውን የመላእክት ዜማ ያሰማልኝ፡፡
  በማጠቃለያው የቀረበው ሀሳብ ድንቅ ነው፡፡
  አመቱን ሙሉ በዜማው የምንገለገለው እኛ ቅ. ያሬድን ግን አናውቀውም፡፡
  ማሳያ፡
  ዛሬ ንግሰ በዓሉ ላይ በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን የታደመው ምዕመን ብዛት ለቅ. ዑራኤል ወርሐዊ በዓል ከሚመጣ ሕዝብ ያንሳል፡፡
  ዓመታዊ በዓሉም እንደሆነ የሚያውቅ በጣም ጥቂት ሰው ነው፡፡
  ያሬድ ሆይ ባናስታውስህ...ብለን እንነሳ፡፡ያሬድ ክቡርና ንዑድ ነው ለኛ ግን ሞገስ ይጨምርልናል፡፡
  ዛሬ ዲ.ን ዳኒ ላዘከረው እኛ በረከቱ ይደርብህ እንለዋለን፡፡
  ይህን ቅዱስ አባት(በረከትህ ይደርብን ) ለማዘከር ያቀረብከው ሐሳብ ወድጄው ሳለ ጊዜው ራቀብኝ፡፡
  ለዝግጅት ከሆነ በጣም ረዝሟል፡፡1500 በመሆኑ ከሆነ ድንቅ ነው፡፡
  ግን ዋዜማዎቹን 1498-1499 ዓ.ም እንዴት ይከበሩ?
  ዋዜማምኮ ቁመት አለው፡፡
  የሆኖ ሆኖ እኔ በጎ ፈቃደኛ ነኝ ቢያን በደብሬ ቢበዛ...
  በድምቀት እንድታሰብ የድርሻዬን እንድወጣ ይርዳኝ፡፡
  ጀመርኩ
  "ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እም መላእክት ቅዱሳን
  እንዘይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሀቲከ፡፡"

  ያሬድ ካህን አንደበተ ማር
  እውነተኛ መምህር
  በጣፈጠ ዜማ በጠለቀ ምሥጢር
  ለአምላኩ ሲዘምር
  መላእክት በሰማይ ላይ
  ቅዱሳንም በምድር
  ይታዩት ነበር
  ሲዘምሩ በክብር
  (ዋይ በዜማ ቢሰማ)

  ያሬድ ማኅሌታይ ለእግዚአብሔር ካህኑ
  ስብሐተ ሥላሴ ዘይዜኑ
  ኦሪት ቶታኑ ወንጌል አሳዕኑ
  ትርድዐነ ነዓ በህየ መካኑ ከመ ጸበል ልቡሳን ጸርነ ይኩኑ

  ReplyDelete
 12. I like it is good idea I will try my best.

  ReplyDelete
 13. በአክሱም ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የቅዱስ ያሬድ የተሰየመ ዩኒቨርሲቲ ሊገነባ ነው
  አዲስ አበባ, ሚያዝያ 4 ቀን 2001 (አዲስ አበባ) - በአክሱም ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቅዱስ ያሬድ የተሰየመ መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጥበት ዩኒቨርሲቲ ሊገነባ ነው፡፡በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጀ ፕሮግራም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሆኗል።
  የዩኒቨርሲቲዉ አሰሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ኮሚቴው ዩኒቨርሲቲውን ለማስገንባት ከኅብረተሰቡI ጋር በመቀናጀት የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው።

  ዩኒቨርሲቲው ዜማ፣ዓለማዊና መንፈሳዊ ትምህርት እንደሚሰጥበትና ግንባታው የቅዱስ ያሬድ 1ሺህ 500ኛ የልደት በዓል በሚከበርበት በ2005 ለማጠናቀቅ ታቅዷል ብለዋል።

  ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሐብት ዩኒቨርሲቲው ለስሙ መሰየሙ ከዕውቀት መገብያነቱ ባሻገር፤ ታሪክን ጠብቆ ለማቆየት ያስችላል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ በተካሄደ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ዲያቆን ዳንኤል አስታውቀዋል።

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንደገጹት የሰው ኃይል ልማት አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት ከዘረጋችው መርሐ ግብር አንዱ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

  የትምህርት ተቋማትን መገንባት አገርን ማልማትና የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት በመሆኑ በቅዱስ ያሬድ የሚሰየመው ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

  http://www.ena.gov.et/AmharicNews/2009/Apr/12Apr09/85012.htm

  ReplyDelete
 14. እጅግ በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው ዳኒ፤ የቅዱስ ያሬድ አምላክ ይህን በጎ ሐሳብ ከፍጻሜ ያድርስልን.
  I will do what I can!

  ReplyDelete
 15. http://gzamargna.net/html/qelemqend_qnezema_ttumelsankas.html

  ReplyDelete
 16. የቅዱስ ያሬድ በረከት ይደርብን
  እግዚአብሔር ያበርታህ
  አበባየሁ(ዘሐመር)

  ReplyDelete
 17. thank you for posting to everyone about our spiritual father life story & remember his name all over. his prayer would be with u to the end. daniel God bless all of us!

  ReplyDelete
 18. continue be brave and may God blessing's is with you and your family.እግዚአብሔር ታሪካችን የሚነግሩን አባቶች፤ እናቶች፤ ወንድሞችና እህቶች አያሳጣን።

  ReplyDelete
 19. ሰናይ ውእቱ እሁየ፡፡

  ገ/ዮሐንስ

  ReplyDelete
 20. DN GEZAHAGN GETAHUN
  THIS IS AGREAT SUPPORIYIVE IDEA ALL TRUE ORTODOX TEWAHDO AND INCLUDING ME BESIDE YOU TO CELEBRATE THIS HOLY DAY.ST. YARED CONTRIBUTED ALOT OF THINGS FOR CHURCHS AS WELL AS THE WORLD.

  GOD BLESS US AND OUR COUNTRY ETHIOPIA.

  ReplyDelete
 21. thank you dn daniel,it is well organized and impresive article.as you told as if YARED was western ,there would be so many things in his name,including films.i think one of our problem is to appreciate and use what we have.we are rich in history and resource,but we are poor in unity and vision to our country.the cause of these are so many factor,what ever the factors and the problems, we have to restore our history and strngeth.we need a man like you. we are frasturated by our leader,i mean both religious and poltical,their concern is profit in the expnse of the people.realy it is a great shame ,we have to rverse this.whatever the past was already gone ,we start new way,change the way we act.i don't this is my random idea,what i have in my mind for a moment.
  God bless you your minstery.

  ReplyDelete
 22. GO ahead!it is good idea

  ReplyDelete
 23. እጅግ በጣም ጥሩ ሃሰብ ነው!

  ReplyDelete
 24. +++

  ይህን እንኩዋን ተወው ሙሉ ለሙሉ የወረብ ካሴት ነው። ሌላ የመዝሙር ካሴት አምጡና እርሱን አባዝተን ለቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ ጉባኤ እንሸጠዋለን አሉኝ አንዲት ትንሽዬ ግን ሀብታም የአውሮፓ ሀገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተዳድሩ «አባት» ። እኔም «ወይ አለመታደል! ብዬ ትዕዛዝ ተቀብዬ ወጣሁ።» ወረብ የተወረበ እንደሆነ ጊዜ የባከነ የሚመስላቸው ነገር ግን ጉንዳን እንደወረረው ሰው ከበሮውን ይዞ ብን ብን የሚል ዘፋፋኝ ዘማሪ ለጉባኤ ማድመቂያ ከባህር ማዶ ማስመጣትን እንደ ትልቅ ተግባር የሚያዩ ካህናት መድኃኔዓለም ልብ እንዲሰጣቸው ልንጸልይ ይገባል። ተወደደም ተጠላም የቤተ ክርስቲያንን ስርዓቱዋን የማስጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ እነርሱ ናቸውና። ምዕመንማ እንደ ስሙ ምዕመን ኢይደል!

  ReplyDelete
 25. It is better to do more in our home land than migrating to western contries and collecting money. It brings no change for our church and country. Let's try to transfer knoledge than money. Let's work in our gifts, cultures,and everyghing we have which are special and precious for us. Let's remember saint Yared the best. Let's please investigate our values.
  In my mind we are the best in the world. No one else has we have.Nobody is given what we have given. there is wisdom more than knowing God.
  May God bless Ethiopia.

  ReplyDelete
 26. አምላከ ቅዱስ ያሬድ በረከቱን ያድለን ያድልህ!
  አምላክ ቢፈቅድ እኔም በሙያዮ የሚጠበቅብኝኝ ለመወጣት ፈቃደኛ ነኝ(Structural engineer, Mekelle university instructor)

  ReplyDelete
 27. ማንም ሰው ስለ ቅዱስ ያሬድ ብጠየቅ የምሰጠው መልስ ኢትዩጵያ በቅንነት ያመለከቸው አምላክ ነቢያቶቹንና ሀዋርያቶቹን ሳትገድ እርሱን በአንድ ቀን ስብከት በማመኗ የሰጣት ልዩ ስጦታ ነው ብዩ የምናገረው፡፡ ቅ/ሬያድ ልዩ ገፀ በረከታችን ነው የኛ ሆነና ሳንስተዋውቀው ቀረን እንጂ፡፡ እኔ በራሳችን በኢትዩጵያውን ላይ አንድ ጥያቄ አለኝ ለምንድነው ለራሳችን ቅዱሳን ቦታ የማንሰጠው፡፡ በሕይወቴ አንድ በጣም የገረመኝ ነገር ልንገራችሁ ብዙ ጊዜ ዳንኤል ሲያስተምር የቅዱሳኖችን ስም በጣም ይጠራል ከእነዚ ውስጥ አንዱ አባ ጊዬርጊስ ዘጋስጫ ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ እርሱ የሳቸውን ስም ሲጠራ እኝህ አባት ማን ይሆኑ እል ነበር፡፡ መፀሀፈ ሚስጥር ተተርጐሞ እንደወጣ (ማጋነን ባይሆንብኝ ከመጀመሪያ ገዢዎቹ አንዷ ሳልሆን አልቀርም) ገዛሁት ወዲያውኑ ማንበብ ጀምሬ ለሊቱን ጨርሼው አደርኩኝ ልክ መፀሀፋን እንደጨረስኩ አንደበቴ ያወጣው ነገር በጣም ይገርመኛል ምነው ይሄ አባት ግብጻዊ በሆነ ኖሮ ነው ያልኩት ምክንያቱም መፀሀፈ ሚስጥር እነ ቂስሎስ፣ አትናቲዩስ ከጻፍት መፀሀፍ የሚስተካከል ነው ግን ያወቅነው ከስንት አመት በኋላ ነው……? የመጀመሪያው የኢትዩጵያ ጳጳስ አባ ሰላማ ቅ/ፍሬምናጦስ ስንቶቻችን እናውቀዋለን… ? ብዙ ብዙ ኢትዩጵያውን ቅዱሳንን ----? ስንቶቹን እናውቃለን…..?

  ቅ/ያሬድ ላይም ይሄን ነገር አያለሁ የማይጠገብ ሰማያዊ ዜማ የሰጠን፣ የኢ/ቤ/ክ በዝማሪ ስርአቷ ከአለም አቢያተ ክርስቲያናት ሁሉ በልጣና ደምቃ እንድትገኝ ያደረጋት ቅ/ያሬድ እርሱን መግለጽ በሚቻልበት መልኩ ብናከብረው ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ጊዜ ትዝ ይለኛል ቦሌ መዳህኒአለም ቅዱስ ፖትርያርኩ ስለ ቅ/ያሬድ ሲናገሩ ያሬድ እኮ ለኛ ትምክህታችን ነው ብለው ነበር በእርግጥም ትምክህታችን ነው፡፡ እኔም በሚደረገው ነገር ሁሉ በምችለው አቅም ለመተባበር ፈቃደኛ ነኝ፡፡

  ዳንኤል ይህንን ሀሳብ እንድታፈልቅ እውቀት የሰጠህ አምላክ ያሬድ ክብር ምስጋና ይድረሰው በሀሳብ ብቻ እንዳይቀር …እ.ን.ስ.ራ

  ReplyDelete
 28. YES the great idea dear D/n Daniel. really we all will do what you suggest. After writing this comment i will creat a group on facebook...God be with us to make our dream true

  ReplyDelete
 29. ያሬድ ያሬድ ያሬድ ቅዱሱ ያሬድ መቼም ከላይ ሆነህ ትመለከታለህ አይደል
  የዘመናችንን ‹‹ያሬዳውያን›› ምን አልካቸው

  ዳኒ ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 30. ጌታቸው ከአ.አ
  እጅግ በጠም ደስ ብሎኛል እና እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ይስጥልን

  ReplyDelete
 31. Really this is a blessed idea and hope be realized soon! Keep it up.

  ReplyDelete