Monday, May 10, 2010

ኦርቶዶክሳዊ መምህር፣ ዕውቀቱ እና ክሂሎቱ ክፍል 2

ባለፈው ጊዜ አንድ መምህር ከየት ከየት ትምህርት ሊያገኝ እንደሚችል መመልከት ጀምረን ነበር፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት ስለሚገኝ ዕውቀት በመጠኑ አይተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሌሎችን እናያለን፡፡                                                                           

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት፡
ሁሉም ነገር በመጽሐፍ አልተጻፈም፤ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በጸሎቱ፣ በማኅሌቱ፣ በቅዳሴው፣ወዘተ የምናገኛቸው ትምህርቶች እና ሥርዓቶች ለቤተ ክርስቲያን ርቱዐዊ ጉዞ አስፈላጊ ናቸው፡፡


የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ውሳኔዎች
በየዘመናቱ የተነሡ መናፍቃንን፣ በየጊዜው የተፈጠሩ ችግሮችን፣ በየሁኔታው የገጠሙ ፈተናዎችን ለመፍታት በጉባኤያት ተሰብስበው አበው የደነገጓቸው ድንጋጌዎች ቤተ ክርስቲያን ከማዕበል ወጥታ ወደ ጸጥታ ወደብ እንድታመራ ያደረጉ፤ የቤተ ክርስቲያንንም አንድነት ያጸኑ ዋልታዎች ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁለት ዓይነት ጉባኤያት ተደርገዋል፡፡                           

ዓለም ዐቀፍ ጉባኤያት፡ እነዚህ ጉባኤያት በወቅቱ የነበሩ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የተሳተፉባቸው፣ የቤተ ክርስቲያንንም ጉዞ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ጉባኤያት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በ325 ዓም የተደረገውን ጉባኤ ኒቂያ፣ በ381 ዓም የተደረገውን ጉባኤ ቁስጥንጥንያ እና በ431 የተደረገውን ጉባኤ ኤፌሶን ትቀበላለች፡፡ ለሌሎቹ ግን ርቱዓን ናቸው ብላ ዕውቅና አትሰጥም፡፡

አካባቢያዊ ጉባኤያት እነዚህ ጉባኤያት በአንድ አካባቢ የተነሡ ችግሮችን ለመፍታት በአካባቢው የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት የሠሯቸው ጉባኤያት ናቸው፡፡ የእስክንድርያ፣ የጋንግራ፣ የዕንቆራ፣ የካርታጎ ወዘተ እየተባሉ የሚጠሩ ጉባኤያት ናቸው፡፡ በሀገራችንም በ14ኛው መክዘ የተደረገውን የደብረ ምጥማቅ ጉባኤ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድ የቤተ ክርስቲያን መምህር በእነዚህ በሁለቱ ዓይነት ጉባኤያት የተወሰኑ ውሳኔዎችን ማወቅ አለበት፡፡

ተጨማሪ ዕውቀቶች

አንድ አስተማሪ ቅዱሳት መጻሕፍትን ስላወቀ ብቻ ሊያስተምር አይችልም፡፡ ዘመኑንም ማወቅ አለበት፡፡ ዘመኑን ማወቅ ማለት ደግሞ፡

• የዘመኑን አስተሳሰብ ማወቅ

• የዘመኑን ችግሮች ማወቅ

• የዘመኑን ጥያቄዎች ማወቅ

• የዘመኑን የአኗኗር ሁኔታ ማወቅ

• የዘመኑን ሥርዓተ ማኅበር ማወቅ ማለት ነው፡፡

እነዚሀን ነገሮች ለማወቅ ደግሞ ሚዲያዎችን መከታተል፣ የዘመኑን ወሳኝ መጻሕፍት ማንበብ እና አካባቢን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ሃብታም እና ድኻ፣ ጋብቻ፣ ወዘተ መጻሕፍቱን ስናነብ ሊቁ ዘመኑን እንዴት እንደተረዳው እናውቃለን፡፡ የግሪክን ፈላስፎች፣ የዘመኑን ዜናዎች፣ የወቅቱን የአኗኗር ባህል በውስጡ ይተነትናቸዋል፡፡ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የጻፈውን የሙሴ ሕይወት ስናነብ የግሪክ ፈላስፎችን አመለካከት እንዴት እንዳፈረሰ እናያለን፡፡

አንድ አስተማሪ ከላይ ያሉትን ምንጮች መጠቀም የሚያስችሉት ሦስት መሣርያዎች አሉ፡፡ እነርሱም

• የማንበብ ልምድ

• መረጃ የማሰባሰብ ልምድ እና

• የቋንቋ ችሎታ ናቸው፡፡

የማንበብ ልምድ፡­ የማያነብ ሰባኪ ባያስተምር ይመረጣል፡፡ ከሚደርቅ ምንጭ የሚያረካ ውኃ አይገኝምና፡፡ ማንበብ ደግሞ ከመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ተንቀሳቃሽ መጻሕፍት ከሆኑት ሊቃውንት መማርም ነው፡፡ ከቀደሙት አበውም ሆነ ከማንደርስበት የዕውቀት ምንጭ መማር የምንችለው በማንበብ ነው፡፡ ስለዚህም ሰባኪው የማነበብ እና የማጣጣም ልምድ ሊያዳብር ይገባዋል፡፡ ወስኖ፣ ጊዜ እና ገንዘብ መድቦ ማንበብ ልምድ መሆን አለበት፡፡ የምናነባቸው መጻሕፍት እንደ በያይነቱ ምግብ ከሁሉም አቅጣጫ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ የሕክምና ሰዎች ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ የሚመገብ ሰው የተለያዩ ቫይታሚኖች፣ ማዐድኖች እና ገንቢ ነገሮች የማግኘት ዕድሉ ይሰፋል እንደሚሉት ሁሉ ልዩ ልዩ ዓይነት መጻሕፍትን ማንበብም እንደዚሁ ነው፡፡

የማሰባሰብ ልምድ፡­ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በቀላሉ አይገኙም፡፡ በየገዳማቱ እና በየሊቃውንቱ፤ በየቤተ መጻሕፍቱ እና በየሙዝየሙ ተበትነዋል፡፡ እነዚሀን ለማገኘት ትእግሥት እና ጥረት ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎችን በኮፒ፣ በድምጽ፣ በማስታወሻ፣ በኣካል እና በአእምሮ የማሰባሰብ ልምድ ያስፈልጋል፡፡

የቋንቋ ችሎታ፡­ ግእዝን፣ ዐረብኛን፣ ዕብራይስጥን እና ግሪክን የመሳሰሉ ቋንቋዎች የጥንት ጽሑፎችን ለመመርመር፤ እንግሊዝኛ ደግሞ በዘመኑ የተጻፉትንም ሆነ የተተረጎሙትን ለማግኘት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ዐቅማችን የፈቀደውን ያህል ብናውቃቸው በሩ ወለል ብሎ ይከፈትልናል፡፡

የማስተማር ዓላማ

ኦርቶዶክሳዊ የማስተማር ዐላማው ማስደነቅ፣ ማስደመም፣ ማዝናናት፣ ማሳወቅ፣ ማስጨብጨብ፣ ወዘተ አይደለም፡፡ ማዳን ነው፡፡ (Tadros The Syrian, Orthodox Teaching. P 35) ሰዎች እግዚአብሔርን ዐውቀው፣ በክርስትና ሕይወት ኖረው፣ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያዊው ሄሬኔዎስ በጻፈው «መድፍነ መናፍቃን» በተሰኘው መጽሐፉ መግቢያ ላይ ማርቅያኖስ የተባለውን ልጁን ሲመክረው «ይህንን የምጽፍልህ ከጥቂቱ ነገር ብዙ ዐውቀህ፣ የእውነትንም ልዩ ልዩ ክፍሎች ተረድተህ፣ የእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮችም ተገንዝበህ፣ የመዳንን ፍሬ እንድታፈራ ነው» ብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሳመን፣ ማሳተፍ እና ማስቀጠል ወሳኞቹ ናቸው፡፡ (Irnaeus, On The apostolic preaching. P 29)

ማሳመን፡ ማለት አንድን ሰው በበቂ ኦርቶዶክሳዊ ዕውቀት ማስታጠቅ ነው፡፡ እንዳይናወጽ እና እንዳይወድቅ አድርጎ መትከል ነው፡፡ ነገ መምህሩ እንኳን ባይኖር ተማሪው በራሱ ሊኖር እንዲችል አድርጎ መገንባት ነው፡፡

ማሳተፍ ደግሞ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

ማስቀጠል ደግሞ እየጾመ፣ እየጸለየ፣ አሥራት እያወጣ፣ ሰንበቴ እየጠጣ፣ እየተማረ፣ እያስተማረ፣ እየጻፈ፣ እየቀደሰ፣ እያስቀደሰ፣ ወዘተ በአገልግሎት እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡

በዚህ ጉዞ ውስጥ ሰባኪው ምእመናን በሦስት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጽናት መለካት አለበት

በዕውቀት የታነጹ እንዲሆኑ፡­ ኦርቶዶክሳዊውን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ሕግ፣ የአበው ታሪክ፣ ወዘተ በሚገባ ማወቃቸውንና ለመመስከር በሚያበቃ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ማረጋጥ

በክርስቲያናዊ ኑሮ የታነጹ እንዲሆኑ፡­ ክርስቲያኖች በሦስቱ መሠረታውያን እሴቶች ማለትም በጾም ፣ጸሎት እና ምጽዋት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚሳተፉ እንዲሆኑ፤ በጎ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እና ከነቀፋ የጸዱ እንዲሆኑ መከታተል

በልዩ ልዩ ግንኙነቶች ርቱዓን እንዲሆኑ፡­ ከማኅበረሰቡ፣ ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቤተሰባቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከንግድ አጋሮቻቸው ወዘተ ጋር በእምነት የተቃኘ፣ በሥነ ምግባር የተጎበኘ አቀራረብ እና አኗኗር እንዲኖራቸው፡፡

በአሁን ዘመን ያሉ ሰባክያን የሚያስፈልጓቸው አምስት ነገሮች

1/ የውይይት እና የዕውቀት መገበያያ መርሐ ግብሮች

ሰባክያን ያገኟቸውን ዕውቀቶች፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና ያቀዷቸውን ሃሳቦች የሚመካከሩባቸው የዕውቀት ጉባኤያት ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ጉባኤያት ጥናቶችን፣ ትምህርቶችን፣ ውይይቶችን እና የልምድ ልውውጦችን ማካተት አለባቸው፡፡ ይህን የመሰሉ መድረኮች በሀገር አቀፍም ሆነ በአካባቢ ደረጃ ሊመሠረቱ ይችላሉ፡፡

2/ ተተኪዎችን ማፍራት

ፍላጎት እና ተነሣሽነት ያላቸውን ማሳወቅ እንጂ የሚያውቁትን ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረግ ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ጥረት፣ ትጋት እና ፍላጎት ያላቸውን መርጦ በግል፣ በቡድን እና በማኅበር በማሠልጠን ማሠማራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እንደምናደርገው ሲንቀሳቀሱ የማይታዩትን ለማንቀሳቀስ ከመሞከር፤ የሚንቀሳቀሱትን የሰሉ የበቁ እንዲሆኑ ማድረግ ይሻላል፡፡

3/ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም

ቪዲዮ፣ መቅረጸ ድምፅ፣ ኮምፒውተር ወዘተ የመሳሰሉትን መሣርያዎችን በበቂ ሁኔታ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለየም ሰባክያን የኢንተርኔትን አጠቃቀም አውቀው ብሎ ጎችን በመክፈት፣ ዌብሳይቶችን በማዘጋጀት፣ የኢሜይል ትምህርቶችን በመላክ ወዘተ እንዲሳተፉ መደረግ አለበት፡፡

4/ መንፈሳዊ ድፍረት እና ንቃት

ዛሬ ዛሬ መድረኮቻችን ዕውቀት እና ሕይወት በሌላቸው ሰባክያን እየተሞሉ ይመስላል፡፡ እነዚህ ሰባክያን ያላቸው አንድ ነገር ቢኖር ድቅድቅ ድፍረት ነው፡፡ ሌሎች በትኅትና ዝም ሲሉ እነርሱ በድፍረት ያልሆኑትን ነን ብለው ወጡ፡፡ ስለዚህም ያልተማሩትንም፣ የማያምኑበትንም ያስተምራሉ፡፡ አሁን ከእውነተኞቹ መምህራን መንፈሳዊ ድፍረት እና አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ ንቃት ያስፈልጋል፡፡ ራሳችሁን በዕውቀት እና በአተያይ አዘምኑ፡፡ የምታውቁትን ሁሉ «እናውቃለን፤ ግን አይጠቅምም ብለን ተውነው» ለማለት ማቻል አለባችሁ፡፡

የትምህርት ደረጃዎቻችንንም እናሻሽል፡፡ ወደፊት ከአብነት ትምህርት ቤት የሚመጡት እያነሡ፤ ከዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የሚመጡት እየበዙ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለሆነም አብረናቸው ማደግ ይኖርብናል፡፡ ካልሆነም በማንበብ እና በመከታተል ራሳችንን ማብቃት አለብን፡፡

5/ በመዋቅር መሥራት ነገር ግን ያለ መዋቅር ማሰብ

ሥራን በአደረጃጀት፣ በመዋቅር እና በተቋማዊ መንገድ መሥራት መልካም ነው፡፡ ሃሳብን ግን በመዋቅር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ መዋቅሮች ይረዱናል፤ ያግዙናል እንጂ አይተኩንም፡፡ ስለሆነም ለማንበብም፣ ለመጻፍም፣ ለማስተማርም፣ ለመማርም፣ ለማደግም፣ ለመሻሻልም፣ ወንጌልን ለማስፋፋትም፣ ለማሠልጠንም መዋቅርን እና መዋቅርን ብቻ መጠበቅ የለብንም፡፡ አንዳንዶቻችን በኮሚቴ፣ በማኅበር፣ በቡድን፣ በጽዋ ካልተሰበሰብን ሥራ መሥራት የምንችል አይመስለንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ለሥራ መልካም ሊሆኑ ይችላሉ ለማሰብ ግን መሰብሰብ አያስፈልግም፤ መጸለይ እና መጨነቅ እንጂ፡፡ ከመዋቀራችን በፊት ሰው ነበርን፡፡ ስለሆነም መጀመርያ የሰውነታችንን ሥራ እንሥራ፡፡ በጀት ፈልገን፣ ሰው አስተባብረን ለመሥራት እንሞክር እንጂ ሁሉን በዕቅድ እና በበጀት፣ በመመርያ እና በስብሰባ አናድርገው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር12 comments:

 1. Thanks as always.

  I do hope that those who consecrate themselves as preachers will learn a number of wisdom from this article. nowadays our laity are just following particular preachers looking only the beauty of their words and expressions. That is why we don't have fruitful results in our church.

  We need more Clerical training centers that could harvest a number of two side bladed swords.

  We need our Archbishops and bishops to write more on our church and the clerical missionary.

  we need our church to work more on spiritual and social activities for the laity.

  We need to strengthen our efforts to keep our church's heritage and pass the next generation.

  We need have strong and well organized church administration so as to control and protect illegal activities of preaching.

  we need our fathers pray so that we can be able to walk stand on this chaotic world.


  Let God give you long life Dani.

  ReplyDelete
 2. kale eywete yasemaline
  please all of us(both "MIMANANE" and "MEMIRANE") don't measure other peoples by this criteria but for ourself only(discussion is possible on the issue only).

  ReplyDelete
 3. ኦርቶዶክሳዊ መምህር፣ ዕውቀቱ እና ክሂሎቱ
  በሚል ርዕስ ያስነበብከን ሁለት ተከታታይ ክፍል ብዙውን የሚያስተምር ነው፡፡ ለመረዳት እንደቻልኩት የመምህራን መስፈርትን ሳስበው በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ፕሮግራም ለመምራት እንኳን ምን ያህል አሰቸጋሪ ሞሆኑን አውቄያለሁ፡፡
  ሁሉንም አሟልቶ የሚሰጥ አምላክ ስለሆነ በቀናነት ጎዳናውን የያዙ ክርስትና እድገቱ በአንድ ቀን ስላልሆነ መበርታትና መጠንከርን ያስተማረን ጽሁፍ ነው፡፡
  ዲ.ዳንኤል እነዚህን ጽሁፎች ሁሉም አግኝቶ ስለማያነባቸው ማለትም ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ በመጽሃፍ መልክ ብታሳትመውና ሁሉም አግኝቶት ቢያነብ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

  ለማንኛውም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

  ReplyDelete
 4. እግዚአብሄር ይባርክህ! ‘’ኦርቶዶክሳዊ የማስተማር ዓላማው ማስደነቅ፣ ማስደመም፣ ማዝናናት፣ማሳወቅ፣ማስጨብጨብ፣ ወዘተ አይደለም ማዳን ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን አውቀው በክርስትና ሕይወት ኖረው ምንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ማድረግ ነው’’፡፡ እንዴት ያለ ግሩም አገላለጽ ነው ግን ምን ያህሎቹ ሰባኪዎቻችን ይህንን እንደሚረዱት እግዚአብሄር ይወቀው ላልተረዱትም ከዚህ በኃላ እንዲገነዘቡት ጥሩ የማንቂያ ደውል ይመስለኛል፡፡ ፍላጎትና ተነሳሽነት ያላቸውን እንዲያውቁ ማድረግም ሆነ የሚያውቁትን ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረግ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ስራ አይደለም በመሆኑም በተለይም ፍላጎትና ተነሳሽነት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን ሰዎች ወደ ሚፈለገው መስመር ለማስገባት መጽሐፍ ቅዱሱን ብቻ መሰረት ያደረገ ሳይሆን የተለያዩ ሌሎች ሊቃውንት የጻፎአቸውን መጽሐፍት፣የነሱን ህይወት፣መንፈሳዊ ያልሆኑ ሌሎች ምንጮችን፣ (ዳኒ እዚህ ጋር ‘’ከእግዚአብሔር አንቅደም’’ በሚለው ስብከትህ ላይ የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤልን የልጆች መጽሐፍት ያጣቀስክበት መንገድ ሁልጊዜም ይገርመኛል) እና የመሳሰሉትን እንደየሁኔታው መጠቀሙ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ከራሴና ከአካባቢዬ ካገኘሁት ልምድ ተነስቼ መመስከር እችላለሁ፡፡ አሁንም ይህንን እጅግ ጠቃሚና ጣፋጭ ሀሳብህን እንድታጋራን እግዚአብሄር ጸጋውን ያብዛልህ!!

  ReplyDelete
 5. Wow!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!Dani Thank you so much for your very intersting view,advice and sharing of knowledge because it is very important for our EOTC preacher if thye are accepted positively with full of commitement.Dani please keep in touch your devotion i have learned a lot of things which are important in my life.God be with you.

  GLORY OF OUR GOD AND HIS MOTHER ST.MERRY.

  Andinet.
  Dire Dawa, Ethiopia

  ReplyDelete
 6. GOD BLESS YOU AND YOUR FAMILY

  ReplyDelete
 7. thank you very much Dani, GOD BLESS YOU

  ReplyDelete
 8. It is great Opurtunity for all in posative view of the world to maximize the use of technology. It helps to address the whole world.D/n Daniel really would like to thank Alimght God for all social critiques and theologic view you reflect on different media. God Bless Us all.
  Keep doing current demand!

  ReplyDelete
 9. that was great you can do more

  ReplyDelete
 10. p/se post such kind of historys more ,it is interesting!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 11. BETAM LIYU TIMIHERET NEW...EWINETEGNA MEMHIRANIN EGZIABHER AMILAK YABIZALIN.....KHY DANI

  ReplyDelete