Tuesday, May 4, 2010

ስለ ንባብ የአንባብያን አስተያየቶች

አንባቢ ትውልድ እንዲኖረን ኅጻናት ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል 

ዲ/ን ዳንኤል፣

እጅግ በጣም ጥሩ ጽሑፍ ነው። እግዚአብሔር ያቆይልን።

መፍትሔው ብዙ ሊሆን ቢችልም አንዱና ምናልባትም ከዋናዎቹ አንዱ የሚከተለው ይመስለኛል። የሚያነብ ትውልድ እንዲኖረን በመጀመሪያ የሚያነቡ ኅጻናት እንዲኖሩ ያስፈልጋል።

ማንኛውንም በጎ ልምድ ማንበብን ጨምሮ በአጭር ጊዜ የሚዳብር አይደለም። ይልቁንም በእድሜ ከጠነከሩ በኋላ ለመለወጥ ጥረት ቢደረግም በውስጥ ስላልዳበረ ለውጡ ዘላቂ አይሆንም። ፈደልንም ሆነ የማስተማር ስርዓቱን ወደሰጡን የሃገራችን ሊቃውንት ብንመለከት ከዚያ ትልቅ ቁምነገር እንማራለን። አንተ እንደጠቀስከው በተወሰኑ ዘመናት የማንበብንና የመጻፍን ነገር የሚያዳክሙ ክስተቶች ቢፈጠሩም ለመማር ከቻለው በጣም ጥቂት የማሕበረሰብ ክፍል ውስጥ የነበሩትን ብዙ የማይባሉ መጻሕፍት እያስደጎሰና እየጠረዘ ተንከባክቦ በመያዝ እያነበበ ለማወቅ ይጥር የነበረና አውቆም የተራቀቀ ትውልድ የነበረን መሆኑ አይካድም። ይልቁንም በቤተክርስቲያን። ያ የሆነው በሃገራችን ሊቃውንት በተሰራው ስርዓት መሠረት ትምሕርት የሚጀመረውና ልጆች ከማንበብ ጋራ የሚተዋወቁት (ዳዊት በመድገም ወዘተ) ገና በኅጻነነታቸው ወራት ስለነበረ ነው።

ያ አሁን በጣም የተዳከመ ይመስለኛል። ዳዊቱን አስተውናቸው ግን እሱን የሚተካም ባይሆን በመጠኑም የሚረዱ የንባብ መጻሕፍትን አላዘጋጀንላቸውም። የዛሬ 30 ዓመትም ሆነ ዛሬ በሳምንት አንዴ በሬድዮ "የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች" ከማለት ያለፈ - እሱንም ዕድሜ ለአባባ ተስፋዬ - የተደረገ ነገር የለም። ስንት ነገር ይሰራል። እውነተኛ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎች ግን አሁንም አይታዩም። የእነሱን ፍላጉት የሚያካትቱ የሕዝብ ላይበራሪዎች አሁንም ለኢትዮጵያ ኅጻናት የሰማይ ጥግ እንደሆኑባቸው ነው። የሌላውንም ላይበራሪ ቁጥርና ጥራት የምናውቀው ነው። እንደእውነቱ ከሆነ በአስተዳደሩም፣ በተቋማትም በሕብረተሰቡም ኅጻናት በሃገራችን ገና ከሰውነት ክብር አልደረሱም። ስለሌላው ብዙ ይባላል እንጂ የኅጻናት ነገር አሁንም እንደተዘነጋ ነው። የማንበብንና የመጻፍን ነገር አነሳን እንጂ ሌላ ሌላው ትውልዱን የምንወቅስበት ነገር ሁሉ የመፍትሔ ውሉ የጠፋብን በዚህ ምክንያት ነው። በወቅቱ ልጆች ላይ ያልዘራነውን ምርት በኋላ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው።

አሁን እጅግ ዘመናዊ ተቀባይነት ያለው የኅጻናት ማስተማሪያ ዘዴ የአባቶቻችንን የማስተማር ዘዴና ስርዓት የሚያረጋግጥ ሆኗል። ልጆች ድምጽ ለማውጣት ገና ከሚሞክሩብት የሁለትና ሦስት ወራቸው ጊዜ ጀምሮ ከንግግሩ ጋር አብረው ከማንበብና ትንሽ ቆይቶም ከመጻፍ ጋር መተዋወቅ አላባቸው የሚል ነው። በዚህም መሰረት መናገርን እየሰሙ ራሳቸው እንዲሚጀምሩት ማንበብንም እያዩና እየሰሙ ሊለማመዱት የሚያስችል ተፈጥሮ አላቸው የሚል ነው። ይህ እስከአምስት አመታቸው ያለው ወርቃማ ጊዜ በሙያው ጠበብት "window of opportunity/የመልካም እድል መስኮት" የሚባል ነው። ኅጻናት በዚህ ጊዜ ደጋግመህ ያስያዝካቸውን ነገር እስከሕይወታቸው ፍጻሜ አይተውትም። ቅዱስ መጽሐፍ ልጆችን በኅጻንነታቸው መንገድ ስለማሳየት የሚነግረን እምነታቸውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በጎ የተባለውን ነገር ሁሉ ይመስለኛል። ማንበብና መጻፍ ደግሞ ከዚህ የሚመደቡ ናቸው።

ስለአውሮፓውያን የማንበብ ልምድ አንስተሃል። በአውሮፓና አሜሪካ ገና የተወለዱ ኅጻናትን ጨምሮ ስንት አይነት መጻሕፍት በየዓመቱ እያታተሙ እንደሚቀርቡላቸው የምታውቀው ነው። ለቁጥር የሚያታክቱ የሕዝብ ላይበራሪዎቻቸው ሁሉም ከአዋቂዎች አኩል አንዳንዴም በበለጠ መደርደሪያዎቻቸው በኅጻናት መጻሕፍትና የድምጽና ምስል መረጃዎች የተሞሉ ናቸው። ወላጆች ለልጆች መጻሕፍትን ማንበብ የሚጀምሩት አንዳንዴም ገና በማኅጸን እያሉ ነው። እኔ በምኖርበት አገር ነፍሰጡር እናቶች በእርግዝናቸው ጊዜ ከሚደረግላቸው የማያቋርጥ ወርሃዊና በኋላም ጊዚው እየቀረበ ሲሄድ ሳምንታዊ የጤና ክትትል በተጨማሪ ይልቁንም ለበካሮች ስለልጅ አያያዝ፣ ስለአመጋገብ፣ ስለጡት ማጥባትና ስለመሳሰለው በነጻ ስልጠና ይሰጣቸዋል። በዚህ ስልጠና ከሚሸፈኑት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የኅጻናትን የአእምሮ ዕድገት የሚመለከት ነው። በዚህ ርዕስ ስር ከሚነገራቸው መካከል አንዱ ለልጆቻቸው ከእርግዝናቸው ወራት ጀምሮ በቀን የተወሰነ ሰዓት መጻሕፍትን አንብቡላቸው የሚል ነው። ከዚህ የተጀመረ ንባብ በኋላም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ውጤቱን ያው የጠቅስከው ነው። አንባቢ ትውልድ እንዲኖረን ኅጻናት ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ለማለት ነው። እግዚአብሔር ይስጥልኝ። የእኛንም ጥረት እግዚአብሔር ውጤት ወደምናመጣበት መንገድ ይምራልን።
     ሙሉጌታ

‹‹ጦማሪዎች ሆይ መጻህፍቱ ይገኙ እንጂ ለማንበብ ወደኋላ አንልም ለማስነበብም አናቅማም በሉ››

Derto Gada said...

በእውነቱ ይህ መሳጭ ርዕስ ነው፡፡ ለማንኛውም በበኩሌ ጓደኞቼን እና ቤተሰቦቼን የሚከተሉትን ሁለት ዘዴዎችን በመጠቀም ከኢ-አንባቢነት ወደ ‹‹ከፊል›› አንባቢነት ለውጯለሁ፡-

1. ስላነበብኩት መጸሀፍ በጣም አወራለሁ /እወያያለሁ/ ፡- አንድ መጸሀፍ ካነበብኩ በኋላ ባገኘሁት አጋጣሚ በዚያ መጸሃፍ ውስጥ ስለተጠቀሱት ነገሮች እያነሳሁ በጨዋታችን እና በውይይታችን መካከል ጣል አደርጋለሁ ፡፡ በተለይ ወቅቱን የጠበቀ መጸሀፍ ከሆነ ሰሚዬ ይበዛል፡፡ መጀመሪያ ግን እማወራው እነርሱ ስለሚወዱት ነገር ነው፡ ለምሳሌ አንድ ጓደኛዬ ኳስ በጣም ይወዳል እኔ ደግሞ ኳስ አልወድም ነገር ግን መረጃዎች አያመልጠኝም፡፡ስለዚህ መጀመሪያ ስለኳስ ‹‹ለኮስ›› አደርግና ቀጥዬ ደግሞ የኔን ጉዳይ እቀጥላለሁ፡፡ታዲያ በዚህ ዘዴ ሁለት ጓኞቼ ካለማንበብ ወደ መጸሀፍ ገዢነት እና አንባቢነት ተሸጋግረዋል፡፡ስለዚህ ውይይት ጠቃሚ ነገር ነው፡፡

2. የገዛሁትን /የማነበውን መጸሀፍ ሰው በሚመለከተው ቦታ ላይ አስቀምጣለሁ፤

ይህ ዘዴ ቤተሰባችን የማንበብ ባህል እንዲያዳብር እረድቶናል፡፡ ስገዛ ወይም ሳነብ መጀመሪያ ፊት ለፊት ይቀመጣል፡፡ከዚያ ይሄ ደግሞ ምን ያደርግልሀል ብለው ይቆጡኛል፤ይዘልፉኛል፡፡እኔም በተራዬ ስለመጸሀፉ እናገራለሁ ከዚያ በሚቀጥለው ቀን ከተቀመጠበት ከተነሳ ሊነበብ ሄዷል ማለት ነው፡፡ ጓደኞቼ መጸሀፍ ይዤ ሲያዩኝ ይጠይቁኛል ባይጠይቁኝም በሚወዱት ነገር ገብቼ ስለመጸሀፉ አወራለሁ ከዚያም ወደ ማንበብ ይጠጋሉ ወይም ያነባሉ ፡፡

3.አንዳንድ መጻህፍት፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያነበብኩት መጸሀፍ ከመሰጠኝ ጨዋታዬ ሁሉ ስለዚያ ይሆንና ሰዎችን ሁሉ ያን መጸሀፍ እንዲያነቡልኝ እለምናለሁ ብል ‹‹አልዋሸሁም›› ፡፡ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነኝ ‹‹ ዴርቶ ጋዳ ›› መጸኃፍ ነው ፡፡ይህን መጸሀፍ እኔ ቢያነስ 20 ሰው እንዲገዛው ያደረኩኝ ሲሆን ከአስራ አምስት ሰው በላይ ደግሞ መጸሀፉን እንዲያነቡት አድርጊያለሁ ከዚያም የውይይት ሰሜት ፈጥሬ ነበር፡፡ የሚገርመኝ እርሱን መጸሀፍ ያነበቡ ሰዎች ከማንበብ እርቀው የነበሩት ተመልሰዋል አንብበው የማያቁት ደግሞ ለማንበብ ጉጉት አድሮባቸዋል….ሌላም ሌላም፡፡

እኛ ሀገር በንባብ ባህላችን ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ነገሮችን በተመለከተ ከላይ ወንድማችን የገለጸው ነገር ትክክል ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች በኳስ እና በፊልም ፍቅር ተለክፈናል ከዚህ ካለፈ ደግሞ በማዳመጥ ሱስ ተለክፈናል፡፡ የማንበብን ባህል ለማዳበር እየሞከረ ያለው ደግሞ የኑሬ ውድነቱ፤የተፈላጊ /ተጠቃሽ/ መጸሀፍት አለመገኘቱ ……እያበሳጨው ይገኛል፡፡
‹‹ጦማሪዎች ሆይ መጻህፍቱ ይገኙ እንጂ ለማንበብ ወደኋላ አንልም ለማስነበብም አናቅማም በሉ››

ገዝቶ የሚያነብ ሰው ከመፍጠራችን በፊት
አውሰነው የሚያነብ ሰው መፍጠር መቻል አለብን
Getachew said...

የዘመነኛው ኅብረተሰብ ዓይናማው ሀያሲ (ይህን ስም ዳቦ ሳላስቆርስ ሰጥቼሃለሁ)- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ለመነሳታችንም ለመውደቃችንም ወሳኝ የሆነውን ነገር በሰላ ብዕርህ ስለበለትከው እግዚአብሔር ይስጥህ። አለማንበባችን ራሱ ጉዳት ቢሆንም በማንበብ ፈንታ የማናደርጋቸው ነገሮች ደግሞ እጅግ ጎጂዎች መሆናቸው ነው ጥፋታችንን እጅግ ከባድ የሚያደርገው። እስቲ ወደ ሌላ ሳልሄድ መፍትሔ ወዳልከው ልሂድና አንዲት ነጥብ ብቻ ላንስቀምጥ፡

ገዝቶ የሚያነብ ሰው ከመፍጠራችን በፊት አውሰነው የሚያነብ ሰው መፍጠር መቻል አለብን። ማንበብ የሚወድ ሰው ጥሩ መጽሐፍ እንደወጣ ሲሰማ ወይም እጁ ሲገባ “አፉ ምራቅ ይሞላል” - እኔ እንደዛ ይሰማኛል። ስለዚህ የንባብ ክበቦችን መቋቋም አለባቸው ። መጻህፍቶቹን በማዋጣት መግዛት ወይም ከቤተ መጻህፍት መዋስ፤ ከዛ በጋራ ማንበብ፤ የተነበበው መጽሐፍ ላይ በመወያየት መጽሀፉን መበለት እንዳዛ እያለ እያጣጣመው ሲመጣ መጨረሻ ላይ የራሴ ካልሆነ ወደሚለው መንፈስ ይሄዳል። የሚጣፍጥ ነገር መቼም እየተዋስኩ እበላለሁ እድሜ ልኬን የሚል የለም።

በድምጽ ቢሆን ኑሮ ብዙ የምለው ነገር ይኖር ነበር። ግን ታይፕ ማድረግ ደከመኝ።

የኔ ድካም አንድ ነገር አስታወሰኝ - ራስህ ታይፕ አድርገህ፡ በኢትዮጵያ ኢንተርኔት ፍጥነት ራስህ መጠሞሪያ ገበታው ላይ ጭነህ፤ በሳምንት ሁለትና ከዛም በላይ ለምታንበሸብሸን ላንተ የአድናቆትና የምሥጋና ፊደላት ተሰካክተው አድናቆቴንና ምሥጋናየን አድምቀው ያደርሱልኝ ዘንድ መመኘት እንዳለብኝ።

ጌታቸው

ብጽፍስ አንባቢ የታለ፣ ባነብስ የሚነበብ የታል ብሎ መስነፍ
Eccl. said...

ልጅ ሆኜ የመጽሐፍ ቀበኛ የምባል ዓይነት ነበርኩ።የቤተ መጻሕፍት ኃላፊው ለምሳ ሲወጡ እንኳን ቆልፈውብኝ ሂዱ እላቸው ስለነበር ማታ ሲዘጉት አንድ መጽሐፍ ይዤ እንድሔድ ይፈቅዱልኝ ነበር። ማትሪክ ልንፍተን አካባቢ በል አሁን ትምህርትህን አጥና ሌላውን ትደርስበታለህ አሉኝ። እስካሁን ባልደርስበትም። ዩኒቭርስቲ እያልሁ ከትምህርት ውጪ ባመት አንድ መጽሓፍ ማንበቤን አላስታውስም። ስመረቅ በወር ቢያንስ 2 መጻሕፍት እገዛና አነባለሁ ያልኩት ሰውዬ ቃሌን ሳልጠብቅ ዓመታት ተቆጠሩ። ለምንድነው የማላነበው/የማናነበው/ ወይም የማንጽፈው ብዬ ራሴን ስጠቅ እርግጠኛ ትክክለኛ መልሱን ላገኘው ባልችልም ሃሳቤን ላካፍል። እየበሉ እየጠጡ ዝም... እንዳይሆን

ምክንያቶቹ፥

1. የተረጋጋና የሰከነ ሕይወት ስለማንመራ - የቀን ተቀን ኑሮን ለማሸነፍ በምናደርገው እሩጫ ረጋ ብለን የምናነብበት ጊዜ ማጣት። 2. በማንበባችን የቀረብን ነገር ያለ ስለማይመስለን - ሁሉም ሰው ያው ነውና።

3. የመጻሕፍት ውድ መሆን - አንድ ጥሩ መጽሓፍ አማካኝ ዋጋ 50-100 ብር /የሃገር ውስጡ/ አካባቢ ነው በዚህ ዋጋ ገዝቶ ለማንበብ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚከብድ ይመስለኛል። በእርግጥ መግዛት እየቻልኩም የመጻሕፍት ፍቅሩ ኖሮም የድሮው የማንበብ ሙዴ አለምጣቱ ይገርመኛል። ተገዝተው የተቀመጡት ብዙ ናቸውና።

4. የሚያነቡትንና የሚጽፉትን እንደ ልዩ ፍጥረት እያዩ ማድነቅ እንጂ ፣ እኔም ጥሩ አንባቢ ልሆን እችላለሁ ልጽፍም እችላለሁ ብሎ ለመጻፍ የመነሳት ወኔ ማጣት

5. ብጽፍስ አንባቢ የታለ፣ ባነብስ የሚነበብ የታል ብሎ መስነፍ

ይገርምሃል ዳኒ ያንተ ብሎግ ትንሽ አነቃቅቶኛል። የመጀመሪያ ግጥሜን የጻፍኩት የዛሬ ሳምንት አካባቢ ነው።

ሌላዋ በ10ደቂቃ ውስጥ የተጻፈችው "እኔና ሻማ" የምትለዋ "ገንዳ" ብለህ የጻፍከው ላይ ያለችው ናት።ባታምርም በኩሬን ሰጠሁህ።

በርታ።2 comments:

  1. Betam yegermale leke lekachenen negeren!
    Gen ande neger lebel "nechchu yemebeltun yememeselgm quche belew selemeyanebu newe"
    Thankyou a lot

    ReplyDelete