Thursday, May 20, 2010

ልዩ መርሐ ግብር ከግንቦት 10 እስከ 12

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ታላቅ ቦታ የያዘ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፡፡ ዐፄ ዳዊት ደግሞ «ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ» ብለውታል፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ አምኃ ጽዮን ይባላሉ፡፡ እንደ ድርሳነ ዑራኤል አባቱ በመጀመርያ የትግራይ በኋላ ደግሞ የሰግላ «ጋሥጫ» ገዥ ነበረ፡፡ እንደ ገድሉ ደግሞ ጠቢብና የመጻሕፍት ዐዋቂ፤ የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳን «ሥዕል ቤት» ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበር፡፡ የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ የመረመርን እንደሆነ ሁለቱም ምንጮች ስለ አንድ ጉዳይ የተለያዩ መረጃዎች የሚሰጡ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

ለምሳሌ በንጉሥ ላሊበላ ዘመን የአራቱ የኢትዮጵያ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች የታላላቅ አድባራት ገዥዎች ነበሩ፡፡ ከዚህም በላይ የአንዳንድ ገዳማት አበምኔቶችና በቤተ መንግሥት የሚያገለግሉ ካህናት አንድ አንድ አውራጃ ወይም ወረዳ ይሾሙ ነበር፡፡ በመሆኑም የአባ ጊዮርጊስ አባት ክህነትን ከገዥነት የደረበ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአባ ጊዮርጊስን እናት ገድሉ «ወእሙኒ እም ስዩማነ ወለቃ» ይላታል፡፡ ይህም በወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና / ከነበሩ መኳንንት ወገን መሆኗን ያመለክታል፡፡

አባ ጊዮርጊስ የተወለደው በ1357 ዓ.ም ነው፡፡ /ገድሉ ያረፈበትን ዘመንና ያረፈው በተወለደ በ60 ዓመቱ መሆኑን ስለሚገልጥ ከዚያ በመነሣት የሚገኝ ነው፡፡/ ወላጆቹ ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት መሆኑን ድርሳነ ዑራኤል ይተርክልናል፡፡

አባ ጊዮርጊስ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አባቱ የመጻሕፍት ሊቅ መሆኑን ስንመለከትና ገድሉም አባ ጊዮርጊስን በተመለከተ «ወሶበ ልሕቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆን» የሚለውን ስናጤነው አባቱ የመጀመርያውን ደረጃ ትምህርት ካስተማረው በኋላ ከጳጳሱ ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል ማለት ነው፡፡ ገድሉ ዲቁና የሰጡትን ጳጳስ ስም አይነግረንም፡፡ ነገር ግን በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጀመርያ የነበሩት አቡነ ሰላማ መተርጉም ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ተላከ፡፡ ወደ ሐይቅ የገባው በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት /1374-1306 ዓ.ም/ መሆኑን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያዩ ሊቃውንት የሚገኙባት፣በብዙ መጻሕፍት የተሞላችና ዙሪያዋን በሐይቅ በመከበቧ የተማሪን ሃሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነች ቦታ ናት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ? ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ «ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው» ብሎ መለሰው፡፡አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን «አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል » ብሎ እንደ ገና ላከው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁልጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር /በ1988 ዓ.ም የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን የጽሑፉ አዘጋጅ በጎበኘበት ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮ ገዳማውያኑ አሳይተውታል/፡፡ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና «አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ» አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዕ ልቦና አጠጣችው፡፡

ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡

አባ ጊዮርጊስ በዜማ /የያሬድን ዜማ ከአቡነ ሳሙኤል ዘጋርማ እንደተማረው ገድሉ ይነግረናል፡፡ /በዚያ ዘመን በዐፄ ዳዊት አማካይነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያሬድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድ ተሾሞ ሳያስተምር አልቀረም፡፡ምክንያቱም በኢትዮያ የድጓ ሊቃውንት ዝርዝር ውስጥ አባ ጊዮርጊስ ይጠቀሳልና/፣ በትርጓሜ መጻሕፍትና በቅኔ የጠለቀ ዕውቀት እንዳለው ድርሰቶቹ ይመሰክራሉ፡፡

የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል «ወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእም አሜሃ አሐዙ ይስአሉ እም ኀቤሁ ኩሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኩሉ ቃለ ማኅሌት፡፡»

ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ በዚያ ጊዜ የነገሥታቱ መቀመጫ በዚያ የነበረ ይመስላል፡፡ ለዚህ ሦስት ምልክቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው በነገሥታቱ መቀመጫ አካባቢ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚበዙት ሁሉ /አኩስምን፣ ላስታን፣ ጎንደርን፣ አንኮበርንና አዲስ አበባን በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል፡፡/ በጋሥጫም በዚያ ዘመን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በገድሉ ላይ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ በመጣ ጊዜ ወደ ቤተ መንግሥት እንዳስገቡት የሚገልጠው ነው፡፡ ሦስተኛው መረጃ ጋሥጫ የዐፄ ይስሐቅ የክረምት ጊዜ ማረፊያ እንደነበረች ገድሉ መግለጡ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ ሥላሴን አንድ ገጽ ብለው ያምናሉ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ውሸት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡

በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በድንግልና ጸንቶ ለመኖር እንደሚፈልግ ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው መነኮሰ፡፡ ገድሉ የት እንደ መነኮሰ አይገልጥልንም ነገር ግን አንድም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያለበለዚያም በደብረ ጎል ሊሆን እንደሚችል ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ከመነኮሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት «ወእምድኅረዝ ኮነ አቡነ ጊዮርጊስ መምህር ለነገሥት ወለካህናት ዘደብተራ ወለኩሉ ዐበይተ ቤተ መንግሥት፣ ለንቡራነ እድ ወለመኳንንት፣ ለመሳፍንት ወለኩሉ ተዐይነ ቤተ መንግሥት- ከዚህ በኋላ ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ታላላቆች፣ ለንቡራነ እድና ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡»

አባ ጊዮርጊስ በሸግላ በነበረ ጊዜ በወባ በሽታ ታምሞ ሊሞት ደርሶ እንደ ነበር ገድሉ ይናገራል፡፡ ታምሞ በነበረ ጊዜ አንድ ሌሊት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተገልጠውለት ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ልንወስድህ መጣን አሉት፡፡ እርሱም የድርሰት ሥራዬን ሳልሠራና እግዚአብሔርንም አብዝቼ ሳላመሰግነው አሁን አትውሰዱኝ ሲል ለመነ፡፡ እነርሱም ልመናውን ተቀብለውት ከሕመሙ ፈውሰውት ሄዱ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከበሽታው እንደ ተፈወሰ ወድያው የድርሰት ሥራውን የጀመረው፡፡

የመጀመርያ መጽሐፉን ጽፎ እንደ ጨረሰ ጠፍቶበት እንደ ነበር ገድሉ ይተርካል፡፡ በቤቱ ውስጥ የነበሩትን መጻሕፍት ሁሉ እያገላበጠ ቢፈልገውም ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ሌሊት በአገልግሎት ላይ እያለ እመቤታችን ተገልጣ «ለምን አስቀድመህ ሳትነግረኝ ጻፍክ?» ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም «አንቺን ደስ ያሰኘሁ መሰሎኝ ነውና ይቅር በይኝ» ሲል መለሰላት፡፡ ከዚህ በኋላ የድርሰት ሥራውን ፈቅዳለት ተሠወረችው፡፡ «ወሶቤሃ በርሃ ልቡ ከመ ፀሐይ ወሐተወ ውስተ ኅሊናሁ ባሕረየ መለኮት፤ ወነጸረ ኩሎ ኅቡአት - ከዚህ በኋላ ልቡ በራለት፣ ኅሊናውም ነገረ መለኮትን ዐወቀ፡፡ የተሠወረውንም ሁሉ ተመለከተ» ይላል ገደሉ፡፡

የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን  የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ ስለ አርጋኖን ድርሰቱ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጠዋል «ወሰመዮ በሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖነ ውዳሴ፣ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ ስብሐት - በሦስት ስሞችም ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖነ ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት  ይባላሉ፡፡» ይህ አገላለጥ አንድ ነገር እንድናስተውል ያደርገናል፡፡ ይሄውም ስለ አርጋኖን መጽሐፍ ይዘት ነው፡፡ በገድሉ ላይ አርጋኖን መጽሐፍ አንድ ሆኖ ሦስት ክፍሎች ያሉት ይመስላል፡፡ እስካሁን የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አርጋኖንንና እንዚራ ስብሐትን ለየብቻ አግኝቷቸዋል፡፡ አርጋኖን ከሰኞ እስከ ዓርብ ላሉት ዕለታት ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ እንዚራ ስብሐት ግን ከ«ሀ » እስከ «ፖ» ያሉትን ፊደላት በመክፈያነት በመጠቀም የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም አርጋኖንን አባ ጊዮርጊስ ሲያዘጋጀው አንድ ሆኖ በኋላ ግን በየክፍሉ እየተጻፈ የተባዛ ይመስላል፡፡

እመቤታችን አርጋኖንን ስለ ወደደችለት ዚማት /ምናልባት ዤማ ይሆን?/ በሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜ «ከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም»  ብላዋለች፡፡ ዐፄ ዳዊትም ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም እንዳጻፈው ገድሉ ይገልጣል፡፡

ከዚህ በኋላ የደረሰው ደርሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን /ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን/ መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ ይህን መጽሐፍ «መጽሐፈ ብርሃን» ብሎ የሰየመበትን ምክንያት ገድሉ ሲያበራራ «አስመ ውእቱ ያበርህ ወያስተርኢ ፍናወ ስብሐቲሁ ለእግዚአብሔር ወፍናወ ስብሐቲሆሙ ለትጉኃን ወለኩሎሙ ማኅበረ ቅዱሳን ልዑላነ ብርሃን ወዓዲ ይነግር እንዘ ያስተሐውዝ ውዳሴሃ ለድንግል ንጽሕት— የእግዚአብሔርን የምስጋናውን መንገድ ያበራል /አብርቶ ያመለክታልና፣ ልዑላነ ብርሃን የሆኑትን የማኅበረ ቅዱሳንንና የትጉኃንን የምስጋናቸውን መንገድ ያመለክታልና፣ የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና/ ይላል፡፡»

በዚያ ጊዜ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቁርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም » ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡

አባ ጊዮርጊስና አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተገናኙት አባ ጊዮርጊስ ወደ ዳሞት በሚጓዝ ጊዜ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ አለባበሱ እንደ ተርታ ሰው በመሆኑ አቡነ ሳሙኤል በመጀመርያ አላወቁትም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አባ ጊዮርጊስ ቅር ብሎት ወደ ዳሞት ተመለሰ፡፡ እንደ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ግምት ሁለቱን ያላግባባው ሥርዓተ ጸሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚያ ጊዜ በዋልድባ ሥርዓተ ጸሎቱ ሰባት ጊዜ በቀን መጸለይን የሚያዝ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በቀን ሰባት ጊዜ ብቻ መጸለዩ ለእግዚአብሔር ያንሰዋል ብሎ ያምን ነበር፡፡ ምናልባትም በዚያን ጊዜ 22 ሰዓት የሚፈጀውን ሰዓታት ሳያዘጋጅ አልቀረም፡፡

ከዚህ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ ሆነ፡፡ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ከጠየቀ በኋላ የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀቱን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቅዳሴያት ደራሲያቸው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍንጭ የሚሰጠን ይሆናል፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው አንዳንድ ካህናት የአባ ጊዮርጊስን ቅዳሴ ተቃውመው ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አርዮስን በቀጣበት መንገድ ቀጥቷቸዋል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ «ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ» ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀ መርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- «እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ? » ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል «እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?» በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ «በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም»  የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነœ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡

ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

አባ ጊዮርጊስ በወኅኒ ቤት እያለ ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ ውዳሴ ሐዋርያት  የተሰኘውንና የሐዋርያትን ምስጋና የያዘውን መጽሐፍ ያዘጋጀው በወኅኒ በነበረ ጊዜ ነው፡፡ አብዛኞቹን ድርሰቶቹን በዚህ ጊዜ ሳያዘጋጃቸው እንደማይቀር ይገመታል፡፡ ዐፄ ዳዊት በሞተ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች «በመሞቱ ደስ ልትሰኝ ይገባሃል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን «ጥቂት ቢኖር እወዳለሁ፤ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ነውና» ብሎ ነበር የመለሰው፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስ ከማ /ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ/ እንደ ነበሩ ገድሉ ይናገራል፡፡

ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡

የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ በ1399 ዓ.ም መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡

«ወበአሐቲ መዋዕል ተስዕሎ አሐዱ መስፍን ዘስሙ ቴዎድሮስ ዘይሰመይ ካዕበ ሊቀ ሐራ በእንተ ሃይማኖት ርትዕት ወደረሰ ሎቱ መጽሐፍ ዘይሰመይ ፍካሬ ሃይማኖት፡፡ ወሶበ ርእይዎ ወአንበብዎ ለውእቱ መጽሐፍ ንጉሥ ወኩሎሙ ካህናተ ምሥጢር ይቤሉ አማንኪ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ወቄርሎስ አፈ በረከት ተንሥኡ በመዋዕሊነ፡፡ ኢትዮጵያ ተመሰለት በቁስጥንጥንያ፣ ወተአረየታ ላዕለ እስክንድርያ - አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ ዳግመኛም የጦሩ አዛዥ የሚሆን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ፍካሬ ሃይማኖት  የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱ ና ባነበቡ ጊዜ በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች ብለው አደነቁ» ይላል ገድሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘውንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውንና የምታወግዘውን በግልጥና በዝርዝር የጻፈበትን መጽሐፍ እንዴት እንደ ደረሰው ሲገልጥ፡፡ ፍካሬ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እምነት በግልጥና በዝርዝር በማስቀመጥ ረገድ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመርያው ሥራ ነው የሚል እምነት የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አለው፡፡ የዘረዘራቸው የመናፍቃን ስሞችን እና ክህደታቸውን ስናይ በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንት ስለ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያላቸውን ዕውቀት ያሳየናል፡፡

አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት  የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡

ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዐለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው አባ ጊዮርጊስ ሞቷል ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ንፋስን ላከው፡፡ አውሎ ንፋሱ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሄድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለ መሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም አሳት አስነድዶ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውኃም ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡

ከግዞት ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን ተገልጣለት መከራው ሁሉ እንደ ሐዋርያት መሆኑን ገለጠችለት፡፡ አእምሮውን ብሩህ፣ ልቡናውን ትጉኅ የሚያደርግ እጅግ ብዙ ምሥጢር ነገረችው፡፡ ተሰናብታው ከሄደች በኋላ «እጅግ ብዙ መብራት አቅርቡ አምስት ፈጣን ጸሐፊዎችንም አምጡ » ብሎ አዘዘ፡፡ እርሱ እየነገራቸው እነርሱ እየጻፉ እረፍት ሳያደርጉ ሦስት ቀን ሙሉ አስጽፎ መጽሐፈ ምሥጢር የተሰኘውን መጽሐፍ ፈጸመ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይህንን ያደረገው ምናልባት በስደትና በመከራ ስለ ደከመ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አምስቱ ጸሐፍት የየድርሻቸውን አጠናቅቀው በአንድ አደረጉት፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህን ተመልክቶ በእጅጉ አደነቀ፡፡ «እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አፍ ተናገረ እንጂ » ሲል በወቅቱ መመስከሩን ገድሉ ይናገራል፡፡

ይህንም መጽሐፍ መጽሐፈ ምሥጢር  ሲል ሰየመው፡፡ የጻፈው በ1409 ዓ.ም እድሜው 52 በደረሰ ጊዜ ሲሆን የዚህ መጽሐፍ ቅጅ በነጋድያን እጅ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ በወቅቱ ሄዶ እንደ ነበር ገድሉ ያስረዳል፡፡

መጽሐፈ ምሥጢር የተጻፈበትን ዘመንና ምክንያት የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል ከዚህ በተለየ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ «በመዋዕሊሁ ለዝንቱ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ኮነ ተቃሕዎ በእንተ ሃይማኖት ወተዋሥአ አባ ጊዮርጊስ ምስለ አሐዱ አፍርንጅ ወሞዓ እስከ ከሠተ ወጸሐፈ መጽሐፈ ምሥጢር - በዚህ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ክርክር ሆነ፡፡ አባ ጊዮርጊስም ከአንድ ፈረንጅ ጋር ተከራክሮ ረታው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር የተባለውን መጽሐፍም ደረሰ፡፡»  ይላል፡፡ ይህ ግን የሚያስኬድ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ዐርፎ ነበርና፡፡

ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ ምድረ ሰዎን /ይህ ቦታና ጋሥጫ ቅርብ ይመስላሉ፡፡ እንደዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ግምት ከወለቃ ወንዝ ማዶ ያለው ሀገር ሰግላ፣ ወዲህ/ ወደ ሰሜን ሸዋ/ ያለው ሀገር ደግሞ ምድረ ሰዎን ተብሎ ሳይጠራ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ገድለ አባ ጊዮርጊስ ስለ ምድረ ሰዎን ሲናገር በዚያ የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እንዳለ ይተርካል፡፡ የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ያለው ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ገዳም ሥር ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በግዞት በነበረ ጊዜ በራእይ እመቤታችን ተገልጣ ዕረፍቱ በአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እንደሚሆን እንደ ነገረችው ገድሉ ይተርካል፡፡/

የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጥቶት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰወን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለ ነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡

ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ «ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ» ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1417 ዓ.ም በ60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡ ከመናገሻ ወደ ጋሥጫ የሚወስደው መንገድ በአዲስ አበባ በኩል አድርጎ፣ በደብረ ጽጌ በኩል ወጥቶ፣ በመርሐ ቤቴና በጉንደ መስቀል በኩል በማለፍ በሚዳና በወረሞ በኩል ወደ ቦረና የሚሻገር ይመስላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በ1986 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሚዳ ጉንደ መስቀል ቤተ ክርስቲያን በተገኘ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ በመንገድ ላይ በማረፉ ለጊዜው ዐጽሙ ያረፈበትን ቦታ ካህናቱ በክብር ጠብቀው አሳይተውታል፡፡ በገድሉም ላይ በዘመዶቹና በደቀ መዝሙሮቹ መካከል የት ይቀበር? በሚለው ጉዳይ ላይ ክርክር መነሣቱንና ንጉሡ በገዳሙ እንዲቀበር መወሰኑን ይገልጣል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ክርክሩ አልቆ ዐጽሙ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እስኪገባ ድረስ በሌላ ቦታ ዐጽሙ ዐርፎ መቆየቱን ገድሉ ጨምሮ ይገልጣል፡፡ በመሆኑን ያረፈበት ቦታ ጉንደ መስቀል ሳይሆን አይቀርም፡፡

እስካሁን ድረስ ያሉን ምንጮች የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ቁጥራቸው ከዐርባ በላይ እንደሆኑ ይገልጣሉ፡፡ በስም የምናውቃቸው ግን የሚከተሉትን ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡

1. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት

2. ኖኅተ ብርሃን /ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል/

3. ውዳሴ መስቀል

4. ቅዳሴ

5. ውዳሴ ሐዋርያት

6. አርጋኖነ ውዳሴ

7. ፍካሬ ሃይማኖት

8. መጽሐፈ ምሥጢር

9. ውዳሴ ስብሐት

10. እንዚራ ስብሐት

11. ሕይወተ ማርያም

12. ተአምኖ ቅዱሳን

13. መጽሐፈ ብርሃን

14. ጸሎት ዘቤት ቤት

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስሙ እና ክብሩ የተዘነጋ ሊቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ መጻሕፍቱም ለአንባብያን አልቀረቡም፡፡ በርግጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መጽሐፈ ምሥጢር የተሰኘው መጽሐፉ በአማርኛ ተተርጉሞ ቀርቧል፡፡ ይህ መጽሐፍ በማኅበረ ቅዱሳን፣ በገዳሙ እና በቅርቡ ደግሞ በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሦስት ጊዜ ለኅትመት ቀርቧል፡፡ ዘመኑ የአባ ጊዮርጊስ ነው ያሰኛል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ገዳሙን ለመርዳት ከፍተኛ ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

እኔ ገዳሙን ከአንድ ቀን የእግር ጉዞ በኋላ በቦታው አይቼዋለሁ፡፡ በደቡብ ወሎ ቦረና ውስጥ ይገኛል፡፡ ከደሴ እስከ ከላላ አንድ ቀን፤ ከከላላ እስከ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አንድ ቀን ይወስዳል፡፡ ገዳሙ ዙርያውን በሙስሊም የተከበበ፤ በተራራ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ አብዛኞቹ መነኮሳት ዐቅመ ደካማ ናቸው፡፡ ቦታው አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙ ወጣት መነኮሳት አይሄዱበትም፡፡ የሚገርመው ነገር የአካባቢው ሙስሊሞች ለገዳሙ ልዩ ከበሬታ አላቸው፡፡

እስኪ በተለይም በውጭ ሀገር የምትኖሩ እና ዐቅሙ ያላችሁ ምእመናን፣ ታሪክ ወዳጆች እና ሀገር ወዳዶች ይህ ታካዊ ቅርስ እንዳይጠፋ የምትችሉትን አድርጉ፡፡ ትልቁ ችግራቸው የዓመት ቀለብ ነው፡፡

በየአካባያችን ማኅበራትን እና ኮሚቴዎችን አቋቁመን መጻሕፍቱን ብናሰባስብ÷ በተለይ በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ ያሉትን፤ ስለ እርሱ ብንጽፍ፤ ገዳሙን ብንረዳ፤ ሰንበት ት/ቤቶቻችን በስሙ ቤተ መጻሕፍት እንዲያቋቁሙ ብናግዛቸው፡፡ በስሙ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ቤተ ክርስቲያን ብንተክል፡፡ በየዓመቱ ሐምሌ ሰባት ቀን የቅድስት ሥላሴ በዓልን የሚያነግሡ አድባራት የእርሱንም ታቦት አስገብተው በድርብ ቢያነግሡት፡፡ ቀኑ «የሊቃውንት ቀን» ተብሎ ቢከበርና እርሱንና ሌሎች ሊቃውንትን የምናስብበት ቀን ቢሆን፡፡ ዐውደ ጥናቶች፤ ሴሚናሮች፤ የቅኔ እና የዜማ ምሽቶችን በማዘጋጀት ብናስበው፡፡

18 comments:

 1. Danel,really i would like to thank you for your effert it is nice start.but i have one thing to ask you,why you prifer the blake bird for your bloge ?

  DD.
  seattle WA

  ReplyDelete
 2. Dear Ehuye Diakon,
  Kale Hiwotin yasemalin.Berekete abba Giorgis Zegasicha kante gar yihun.wagan yemayasker Egziabher yenefis waga yadirglih.Bezihu ketil.

  g/yohannes

  ReplyDelete
 3. በከመፈቀደ ይገብር ወበከመሃልዬ ይፌፀም
  እንዳለው አባታችን መልካም ሀሳብ ነው
  ገዳሙም በጥቅምት 23 ንግስ አለ
  ለበለጠ መረጃም ፳አመት ላይ የወጣውን ሲዲ መመልከት ይቻላል

  ReplyDelete
 4. ሲሎንዲስ ዘአውሮፓMay 20, 2010 at 3:22 PM

  እጅግ የሚወደድ ገድል ነው...የአባ ጊዮርጊስን የሚመስጥ ታሪክና አርአያነት ያለው ህይወት በዚህ መልኩ በማግኘቴ ደስ ብሎኛል።እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከነገስታቱ ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን ያከበረ፤ስለ እምነቱ አብዝቶ የመሰከረ፤የእግዚአብሔርና የእመቤታችን ፍቅር የበዛለት፤ለስጋዊ እረፍት ሳይሆን ለበረከት የኖረ...ይበል የሚያሰኝ ነው።
  አስተያየት
  1/የተጠቀሱት መጻህፍት ይህን ትውልድ ብዙ ሊያስተምሩ ሊመክሩ እንደሚችሉ አምናለሁ(ስለፍካሬ ሃይማኖት የተገለጸውን ልብ ይሉአል)።ስለመጻህፍቱ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ብንጥር(የት ይገኛሉ እንዴት ይታተሙ...)
  2/ቤተ ክርስቲያን በስማቸው ለማነጽ ለየሃገረ ስብከቱ(ለምሳሌ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት) ጥያቄ የምናቀርብበትን መንገድ ብንቀይስ
  3/የገዳሙን መነኮሳት ለማገዝ እየተደረገ ነው የተባለው ጥረት(ፕሮጀክት) ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ አድራሻው ግልጽ ቢደረግ
  *የዐፄ ዳዊት ልጆች ሲገለጹ ቴዎፍሎስ(ቴዎድሮስ?) የሚል አለ
  የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልን በአባቶቻችን የኅላ ገድል ወደፊት እንሄዳለን
  (We will look back to the future)
  በቅዱሳኑ የሚከብር እግዚአብሔር ይመስገን

  ReplyDelete
 5. Dear Dn. Daniel

  Thank you very much writing about Aba Geiorgis Zegasecha, I know a little about him but now thanks for u i can talk about him more.

  Thank you

  ReplyDelete
 6. We have been much benefited in this special event.I know that Aba Giorgis of Gasecha is the elite of Ethiopian church scholars.I remember in one of your research works about Ethiopian anaphoras/printed on Hamar magazine/ you mentioned that there are at least 20 anaphoras and the author of most of them was Aba Giorgis.Even if the research was to continue, I have one question in this regard.you have mentioned that only two of the 20 are translated from abroad and others are works of Aba Giorgis and if so does it mean that there were only two anaphoras before 13th century? How was the church celebrating the Mass before Aba Giorgis?
  I thank you Dani for your passion.

  ReplyDelete
 7. እስከ 13ኛው መክዘ ብዙዎቹ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የነበሯቸው ቅዳሴያት ከአራት አይበልጡም፡፡ ከሶርያ ቤተ ክርስቲያን በቀር፡፡ ግብፃውያንም ቅዳሴያትን ያደራጁት ከ13ኛው መክዘ በኋላ ነው፡፡ እስከዚህ ዘመን ድረስ በዓለም ቤተ ክርስቲያን ታዋቂ የሆኑ እንደ ቅዳሴ እግዚእ፣ቅዳሴ ሐዋርያት፣ባስልዮስ፣ ወዘተ ያሉት ነው ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡
  በሌላም በኩል ደግሞ ከ13ኛው መክዘ በፊት ገብተው ነገር ግን ያላገኘናቸው ቅዳሴያትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

  ReplyDelete
 8. Daniel Egziyabher yibarkeh...I am thankful to God to reveal about His Divine truth in the Holy land ethiopia, with the holy people like Aba Giorgis.....Bless Him!

  Daniel I have one suggestion...I am keen to know some Amharic words used in the article; for instance አበምኔቶችና, ዐቃቤ ሰዓት, ሥርግው....The words are not quite often used. I seldom face them in similar articles and always wish to know...but I can only guess from the context. Could you please put a footnote definitions when old(unusual) words are used in your articles.

  Bless you!

  ReplyDelete
 9. «አበ ምኔት» ማለት የገዳም አስተዳዳሪ ማለት ነው፡፡ «ዐቃቤ ሰዓት» በጥንት ዘመን ለሐይቅ እስጢፋኖስ አበ ምኔት የሚሰጥ መዓርግ ሲሆን የንጉሡን መርሐ ግብር የሚያወጣ የፕሮቶኮል ሹም እንደ ማለት ነበር፡፡ «ሥርግው» ማለት በግእዝ ያጌጠ ማለት ነው፡፡

  ReplyDelete
 10. Egziabher Yistelign!I have got the first part of `metsehafe mister`translated into Amharic.But I have questions
  1.How can we got the second part.
  2.Our recent translations are from Egypt.But equal emphaasis should be given for our own like that of aba Giyorgis`s Fikare Haymanot.
  3.Much is expected from the Minsstry of Culture and turism to assist the monastry
  Beterefe Berta

  ReplyDelete
 11. Thanks for your answer.Here is another question. I know you have translated the book " Fikare Haymanot" which is one of the most important books of Aba Giorgis in revealing Ethiopian Doctrine but not published. Could you say something about that?

  ReplyDelete
 12. Brother Daniel, I appreciate your works and dedication. But you haven't answered a question on why you chose the Eagle bird at the top of your article. I think we have the right to know every symbols that whoever used it, as it serves the whole Orthodox christian community. Kindly,

  ReplyDelete
 13. dani i have one quation is kidase mariam the work of aba Giorgis the gasicha ? i ask this becouse there are some poeple that says it is his work but he put aba Hiriakos to be the autor becouse he was very hamble{tihut}

  ReplyDelete
 14. Oh Dn.Daniel I thank u.really i pleased to know more about "Tsadiku" abatachin Aba Georgis.I have the book Metshafe Mstir,what surprised me is,it seems to be written for the existing christians(written before 700 yrs ago),it is the character of holly bible.
  And the 'tomar'initiated me to see the place.We should help the project held by Mahibere kidusan,we shouldn't expect others to do it.

  ReplyDelete
 15. በእውነት ወርቅ ነህ

  የኖረበትን ዘመን ወርቃማ ዘመን ያስባለ ወርቃማ ደራሲ አባ ጊዬርጊስ ራሴን አንተን አስተምራ ባሳደገች ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳገኘው ያረገኝ እ/ር የተመሰገነ ይሁን፡፡ አንተን እንድናውቅ የረዱንን ሁሉ አምላክህ ያስባቸው

  ማኪ
  አዲስ አበባ

  ReplyDelete
 16. Danie ye aba Georgious bereket yederebehe, yederebene.

  did he write all 14 kedasayate or one of them because i think aba Baselouse and some other kedusan wrote kedasae.

  ReplyDelete
 17. ብዕር ከመዘዙ እንዲህ ነው፡፡
  ለእዝራ ስቱኤል የታደለው የጥበብ ፅዋ ላንተም ይድረስህ!
  Yam

  ReplyDelete
 18. i liked abba giorgis very much.arganon ewnetim bewerq qelem metsaf yogebawal.

  ReplyDelete