Thursday, April 29, 2010

ገንዳ

(በተለይ ሻማ ሆነው በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ)

አንድ መምህሬ ነበሩ፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ ጠይቀናቸው ያብራሩልንና ዘወትር የማት ለወጥ ምክር አለቻቸው፡፡ «ገንዳ እንዳትሆኑ» ይሉናል፡፡ ብዙ ጊዜ እሰማታለሁ እንጂ ለምን ብዬ ጠይቄ አላውቅም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ምን ማለታቸው እንደሆነ ለማወቅ ፈለግኩና ጠየቅኳቸው፡ «አያችሁ፣ ገንዳ ለከብቱ ሁሉ ያጠጣል እንጂ ለራሱ አይጠጣም፡፡ እንዲያውም ባጠጣ ቁጥር እየጎደለ ሄዶ ጭራሹኑ ይደርቃል፡፡ እናንተም እንደዚያ እንዳትሆኑ» አሉን፡፡ ለብዙዎች ምክር የሚሰጡ ለራሳቸው መካሪ ካጡ፤ ለብዙዎች የደስታ ምንጭ የሆኑ እነርሱ በኀዘን ከሰመጡ፤ ብዙዎችን የሚያዝናኑ እነርሱ ግን ከተደበሩ፤ ለብዙዎች የሀብት ምንጭ የሆኑ እነርሱ ግን በድኅነት ከተቆራመዱ፤ ብዙዎችን ያስተማሩ እነርሱ ዕውቀት ከጎደላቸው፣ብዙዎችን ያስታረቁ እነርሱ ዕርቅ ካጡ፣ ብዙዎችን የመሩ እነርሱ መንገድ ከጠፋባቸው፣ ብዙዎችን ያዳኑ እነርሱ መድኃኒት ካጡገንዳነት ማለት ይሄ አይደል እንዴ፡፡

በካባ ውስጥ ያለን ድንቁርና እና በቡቱቶ ውስጥ ያለን ዕውቀት ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ይባላል፡፡ መድረክ ላይ ወጥተው፣ ዓይን የሚስበውን እና ልብ የሚማርከውን ልብስ ለብሰው፣ ሕይወትን በቀልድ ቀምመው እኛን በሳቅ የሚያፈነዱን ሰዎች በእውነት የእነርሱ ሕይወት ትስቃለች? በኪናዊ ሥራዎቻቸው እኛ የገዛ ሕይወታችንን መለስ ብለን እንድናያት ያደረጉን እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን መለስ ብለው የሚያዩበት መነጽር አላቸው?

የትዳርን መልካምነት ፤የፍቅርን ጣፋጭነት ፣የቤተሰብን ደስታ፣ የማኅበራዊ ኑሮን ርካታ በዜማዎቻቸው ከሽነው ያቀነቀኑልን ወገኖች ትዳራቸውን እና የፍቅር ሕይወታቸውን፣ ቤተሰባቸውን እና ማኅበራዊ ኑሯቸውን ሲገመግሙት ያቀነቀኑለትን ያህል ሆኖ ያገኙታል? ወይስ ለዜማው ስኬት፣ ለገበያው ሥምረት፣ ለአድማጩ ሐሴት ሲሉ ብቻ ነው ያቀነቀኑት?

በፊልሞቻቸውም ይሁን በመድረክ ትወናቸው ኅብረተሰባችን ምቀኝነትን እና ክፋትን፣ ቅናትን እና ስግብግብነትን፣ ቂምን እና በቀልን፣ መሠሪነትን እና ተንኮለኛነትን እንዲያርቅ የሚያስተምሩን እና የሚያሳዩን ወገኖቻችን መልእክቱ ለተመልካቹ ብቻ ነው ወይንስ እነርሱንም ይመለ ከታል? መልእክቱ ለመድረክ ብቻ ነው ወይስ ወደ ቤታቸውም ይሄዳል? ጉዳዩ የኅብረተሰቡ ብቻ ነው ወይንስ እነርሱንም ይዳስሳል? ለመሆኑ እርስ በርሳቸው ደኅና ናቸው?

«ተማር ልጄ» ብለው እያዜሙ እነርሱ ግን «ትምህርት እስከ ስድስት፣ ዘመድ እስከ አክስት» የሚሉ ከሆነ፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ አንድነት እየሰበኩ እነርሱ ግን ግላዊነት የሚያጠቃቸው ከሆነ፤ ስለ ፍቅር እያቀነቀኑ እነርሱ ግን የትዳራቸውን ነገር ውኃ ውኃ የሚያደርጉት ከሆነ፤ አንድ ሰው ለአንድ ነው ካሉን በኋላ አንድ ለአሥር የሚመሩ ከሆነ፤ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ እያስተማሩ፣ በዚህ እና በዚያ መንገድ ትያዛላችሁ ብለው እየሰበኩ፣ እነርሱ ግን «አንቺው ታመጭው ፣አንቺው ትሮጭው» እንደ ሚባለው ምክሩን ለራሳቸው የማይጠቀሙበት ከሆነ ከዚህ በላይ ገንዳነት ምን አለ?

ሌሎች ሰዎች ሀብታቸውን ለሀገር ልማት እንዲያውሉት መንገር ብቻ ነው እንዴ፣ እኛስ ሀብታችንን የትም ከምንረጨው ለምን መሥመር አናስይዘውም፤ ሌሎች አንዳች ነገር ሲያስመርቁ ተገኝተን ምረቃውን እንደምናሞቀው ሁሉ የራሳችንን ነገርስ ለምን አናስመርቅም፤ ነው ወይስ ከምሽት ክበብ እና ከክትፎ ቤት በላይ ማቋቋም አንችልም? የሕግ አማካሪ፣ የቢዝነስ አማካሪ፣ የሂሳብ ባለሞያ፣ የሞያ አማካሪ እንዳይኖረን ያገደው የትኛው ሕግ ነው?

«አይሆንም እንጂ ቢሆንማ፣ ሽርሽር ወደ ጅማ» የሚል አንድ ሠርግ ላይ ሰምቻለሁ፡፡ አይሆንም እንጂ ቢሆንማ እኛም ሞያችንን በዕወቀት ብንደግፈው፣ ለሞያችን እና ለዕድገታችን የሚሆኑ ትምህርቶችን ከፍለን ተምረን ራሳችንም መሥመራችንን ብናው ቀው ጥሩ ነበር፡፡ ዲፕሎማ እና ዲግሪኮ ለመቀጠር ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የተማሩትን ቀጥረን በዘመናዊ መንገድ ሕይወታችንን ብንመራ መልካም ነበር፡፡ «አይሆ ንም እንጂ ቢሆንማ» አሉ፡፡ ከልጆቻችን ጋር ስለ ትምህርታቸው ለመወያየት፣ ትምህርት ቤትም ሄዶ የልጆችን ነገር ለመጠየቅ፣ ወደ ውጭ ወጣ ሲሉ በጣት ከማውራት ለመዳን፣ እኛም ዐውቀናል ጉድጓድ ምሰናልም ለማለት፤ መማርን የመሰለ ነገር የለም፡፡

ብዙ ሰዎች ሊያደንቁን ይችላሉ፣ ሊወደን የሚችል ግን አንድ ሰው ወይንም አንዲት ሴት ብቻ ናት፤ በብዙ ቦታዎች ልንጋበዝ እንችላለን፣ ሊኖረን የሚችለው ትዳር ግን አንድ ብቻ ነው፤ ፊርማችንን ብዙዎች ይፈልጉት ይሆናል፤ እውነተኛ ፍቅራችንን እና እኛነታችንን የሚፈልጉት ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ከኛ አንዳች ነገር መስማት የሚፈልጉ አያሌዎች ናቸው፤ ለኛ ጥቂት ነገር ሊነግሩን የሚችሉ ግን በጣት ይቆጠራሉ፤

ከኛ የሚፈልጉ አሉ፤ እኛን የሚፈልጉ መኖራቸው ግን ያጠራጥራል፤ በኛ የሚጠቀሙ ሞልተዋል፣ እነዚያ ሁሉ ግን እኛን ይጠቅማሉ ማለት አይደለም፤ ዝና ለተወሰነ ጊዜ ነው፣ ሕይወት ግን እስከ ሞት ድረስ ናት፤ መድረክ ላይ የሚያጨበጭቡልን እልፍ አእላፋት ናቸው፣ ከመድረክ ስንጠፋ የሚፈልጉን ግን እጅግ በጣም ጥቂት፤ ስንስቅ የሚስቁ አናጣም፤ ስናለቅስ ዕንባችንን የሚያብሱ ማግኘት ግን ይቸግራል? ሞያችንን የምናካፍለው ቁጥሩ ብዙ ነው፣ ችግራችንን የምናካፍለው ግን የት ይገኛል?

አውሮፕላን አገልግሎቱን በሚገባ ለመስጠት ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ ሊነሣበት እና ሊያርፍበት የሚችል አውሮፕላን ማረፊያ እና ሊበርበት የሚችል አየር፡፡ በቴክኖሎጂው ምጥቀት የተነሣ በሰዓት የፈለገውን ያህል ኪሎ ሜትር ቢበርም፤ ምቾቱ የተጠበቀ፣ ደረጃው የላቀ ቢሆንም፤ የቱንም ያህል ወደ ላይ እንደ ንሥር ቢነጠቅም፤ መነሻ እና ማረፊያ ከሌለው ግን ሄዶ፣ ሄዶ ነዳጁ ሲያልቅ መከስከሱ አይቀርም፡፡

በዜማቸው፣ በኪነ ጥበብ ውጤቶቻቸው፣ በትወናቸው፣ በሀብታቸው፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው፣ በሊቅነታቸው ወዘተ ታዋቂ የሆኑ እና አያሌዎችን ከኋላቸው ወይንም በዙሪያቸው ለማሰለፍ የበቁ ሰዎች፣ የቱንም ያህል ወደ ላይ እና ወደ ጎን በክብር እና በዝና፣ በአድናቆት እና በምስጋና፣ በሀብት እና በንብረት ቢመጥቁም፤ የቱንም ያህል በሕዝቡ ተወዳጅ እና ተፈቃጅ ቢሆኑም፤ እንደ አውሮፕላኑ ማረፊያ እና መነሻ ከሌላቸው ግን አንድ ቀን እነርሱም መከስከሳቸው የማይቀር ነው፡፡

ብዙ ሺዎች ሲያደንቁህ ከነበረበት መድረክ ወርደህ ቤትህ ስትገባ ምን ይጠብቅሃል፤ ቤትህ እንደ መድረኩ ይሞቃል? ብዙዎችን ካዝናናህበት የሳቅ ባሕር ወጥተህ ብቻህን ስትሆን ነፍስህ ምን ትልሃለች፤ አያሌዎች የተጠቀሙበትን ጉዳይ አቅርበህ ራስክን ስታየው ምንድን ነህ ይልሃል? ይህ ነው ከባዱ ጥያቄ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ለዚህች ሀገር ባለውለታ የሆኑ የሥነ ጥበብ እና የኪነ ጥበብ ሰዎች ታመው መታከሚያ፤ ተቸግረው መኖርያ፤ ዐርፈው መቀበርያ እያጡ ሲለመንላቸው ሳይ እኒያ መምህር የተናገሩት ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ አነሰም በዛም በወቅቱ ጥቂት ነገር አግኝተው ይሆናል፤ በወቅቱ መሬት ለማግኘት፣ ቤት ለመሥራት፣ ጥሪት ለመቋጠር ምቹ የነበሩ ሁኔታዎች እነርሱንም የሚመለከቱ ነበሩ፤ በወቅቱ አያሌ አድናቂዎች እና እነርሱ ካልመጡ ሞተን እንገኛለን የሚሉ ተመልካቾች ነበሯቸው፡፡ ታድያ ለምን እዚህ ደረጃ ላይ ወደቁ?

እኔ እንደሚመስለኝ የእኛ እንጂ የራሳቸው እንዲሆኑ ስላልረዳናቸው ነው፡፡ አጨበጨብንላቸው፣ አፏጨንላቸው፣ አቆላመጥናቸው፣ ጋበዝናቸው፣ እፍ እፍ አልንላቸው፣ አበድን ላቸው፤ ራሳቸውን ሆነው ማረፊያ ኖሯቸው እንዲኖሩ ግን አላደረግናቸውም፡፡

በየመንደራችን ጉልት ቸርችረው፣ ጠላ ጠምቀው፣ እንጨት ሰብረው፣ የዕለት ሥራ ተቀጥረው ሕይወትን ይገፉ የነበሩ ወገኖች፣ ቢያንስ የቀበሌ ቤት ለመከራየት፣ ዕድር እና ዕቁብ ለመግባት፣ ልጆቻቸውን አስተምረው የተሻለ ቦታ ለማድረስ፣ የሚያከራዩት ሰርቢስ ቤት ለመሥራት ሞክረዋል፤ «የሕዝብ ልጆች» እየተባሉ የኖሩ የኪነ ጥበብ እና የሥነ ጥበብ ሰዎች ግን፣ የሕዝብ ብቻ ሆነው የራሳቸው ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ «የሁሉም የሆነ የማንም አይሆንም» ይባል የለ፡፡

እንደ አውሮፕላኑ መነሻ እና ማረፊያ እንዲኖራቸው ማድረግ ነበረብን፡፡ መምከር ነበረብን፡፡ ማስጨነቅ ነበረብን፡፡ እነርሱም ማሰብ ነበረባቸው፡፡

አርቲስት ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ታዋቂ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ደራሲ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ጋዜጠኛ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ፖለቲከኛ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ነጋዴ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፡፡ ሰው ባትሆኑ ኖሮ እነዚህን ነገሮች ሁሉ መሆን አትችሉም ነበር፡፡ ሰው መሆናችሁ ሲያቆም ደግሞ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አብረው ያቆማሉ፡፡ ስለዚህም ዝናን እና ታዋቂነትን፣ ክብርን እና ሽልማትን፣ ገንዘብን እና ሀብትን፣አድናቆትን እና ተወዳጀነትን ስላገኛችሁበት ነገር ብቻ ሳይሆን ሰው ስለሆናችሁበትም ነገር ማሰብ አለባችሁ፡፡

አገር መውደድ ቤተሰብን እና ትዳርን ከመውደድ፣ ሕዝብን ማስተማር ራስን ከማስተማር፣ ሌላውን ማዝናናት የትዳር ጓደኛን ከማዝናናት፣ ተወዳጅነት በገዛ ልጆቻችን ከመወደድ፣ መደነቅ በትዳር አጋር ከመደነቅ፣ መከበር በመንደራችን ከመከበር፣ ደስተ ኛነት በግል ሕይወት ከሚገኝ ርካታ መጀመር አለበት፡፡ አውሮፕላን ማረፊያውን ለቅቀን አየር ላይ ብቻ የምንንሳፈፍ ከሆነ መከስከሳችን አይቀሬ ነው፡፡

ጊዜ ስለሌለን፤ ኪነ ጥበብ የሕዝብ ስለሆነች፣ ሕዝቡን በየአጋጣሚው ማገልገል ስላለብን፣ ሥራችን ሌሊትም ቀንም ስለሆነ፣ ሞያችን አንዳንድ ጊዜ ለብቻ መሆንን ስለሚፈልግ፣ ወደ ውጭ ሀገር በብዛት ስለምንወጣ፣ እዚህም እዚያም ስለምንፈለግ፣ እያልን የምንተወው ቤተሰብ፣ የምናሳዝናቸው የትዳር አጋሮቻችን እና ልጆቻችን በኋላ ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡ ጊዜ ላይኖረን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰው ነንና ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት የግድ ያስፈልገናል፡፡ ቤተሰብ የመነሻ እና የማረፊያ ሜዳችን ነው፡፡ አውሮፕላኑ ቢበላሽ ወርዶ የሚሠራው ማረፊያው ላይ ነው፡፡ ማረፊያው ከተበላሸ ምን መሆን ይችላል? «ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል» ይባል የለ!

ሕዝብ አይጨበጥም፡፡ ሕዝብ የሚባል መዋቅርም የለም፡፡ ሕዝብ ተቆጥሮ በትክክል አይታወቅም፡፡ ስለ ሕዝብም አፍን ሞልቶ ትክክለኛውን ስሜት መናገር አይቻልም፡፡ ሕዝብ የሚባል ተቋምም በሕግ ዘንድ የለም፡፡ ቤተሰብ ግን ይጨበጣል፡፡ ይቆጠራል፡፡ አፍን ሞልቶ ሊናገሩለትም ይቻላል፡፡ በሕግም የታወቀ ትርጉም እና ጥበቃ አለው፡፡ እናም የማይጨበጠው የሕዝብ ከመሆናችን በፊት፣ የሚጨበጠው የቤተሰባችን እንሁን፡፡

የጂኦግራፊ መምህራችን ምድር ሁለት ዓይነት ዙረት አላት ብለውናል፡፡ በፀሐይ ዙርያ እና በራስዋ ዛቢያ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተጠባብቀው ይኖራሉ፡፡ እኛም በፀሐይ ዙርያ ብቻ ሳይሆን እንደ ምድር በራሳችንም ዙርያ እንዙር፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተጠባብቀው ይኑሩ፡፡

ለምንድነው ቢሉ፤ ገንዳ እንዳንሆን፡፡

32 comments:

 1. DANIEL, BEAUTIFULLY WRITTEN AND WELL PUT TOGETHER. MAY GOD BLESS AND I EXPECT MORE WISDOM OF YOU ON THIS BLOG.

  ReplyDelete
 2. ወይ ነዶ!
  ‹‹ለብዙዎች ምክር የሚሰጡ ለራሳቸው መካሪ ካጡ፤ ለብዙዎች የደስታ ምንጭ የሆኑ እነርሱ በኀዘን ከሰመጡ፤ ብዙዎችን የሚያዝናኑ እነርሱ ግን ከተደበሩ፤ ለብዙዎች የሀብት ምንጭ የሆኑ እነርሱ ግን በድኅነት ከተቆራመዱ፤ ብዙዎችን ያስተማሩ እነርሱ ዕውቀት ከጎደላቸው፣ብዙዎችን ያስታረቁ እነርሱ ዕርቅ ካጡ፣ ብዙዎችን የመሩ እነርሱ መንገድ ከጠፋባቸው፣ ብዙዎችን ያዳኑ እነርሱ መድኃኒት ካጡ ገንዳነት ማለት ይሄ አይደል እንዴ፡፡›› እንዲህ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡ አሁን በጣም መሽቷል፤ እስኪ ትንሽ ጎኔን ላሳርፈው፡፡
  ዳዊት

  ReplyDelete
 3. Zare tegesastehe yalefegne meselogne nebere:: Lebe beye sayewe gene leka Atristm balehone sewe negne!! Se;ezihe eneme ende'akeme meneshana mederesheayene maweqe yitebeqebegnale. Thank You Deacon Daniel

  ReplyDelete
 4. yours piece are instructive and constructive. I hope you will do more than this.
  May God Bless Us All!!!
  Let's Have understanding capacity !!

  ReplyDelete
 5. What a good expression is it?
  "ዝና ለተወሰነ ጊዜ ነው፣ ሕይወት ግን እስከ ሞት ድረስ ናት፤ መድረክ ላይ የሚያጨበጭቡልን እልፍ አእላፋት ናቸው፣ ከመድረክ ስንጠፋ የሚፈልጉን ግን እጅግ በጣም ጥቂት፤ ስንስቅ የሚስቁ አናጣም፤ ስናለቅስ ዕንባችንን የሚያብሱ ማግኘት ግን ይቸግራል? ሞያችንን የምናካፍለው ቁጥሩ ብዙ ነው፣ ችግራችንን የምናካፍለው ግን የት ይገኛል?"
  God bless you,your family and your country

  ReplyDelete
 6. This Awsoem!!!I learnd and back to my heart!!! i don't realy give time for my Father, Sisers and Brother. I am just Lazy......But From now on i will!!! May God Help me!!!

  ReplyDelete
 7. አባግንባር (ከሮማ)April 29, 2010 at 11:07 AM

  ውድ ዲን. ዳንኤል፡

  ሰላምታዬ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ያቀረብከው ሃሳብ በጣም አስተማሪ ነውና እግዚአብሔር ይስጥልን እላለሁ፡፡

  አንድ ነገር ግን እጠብቃለሁ ካንተ ልክ አዲስ ነገር ላይ ያቀረብካቸውን ጽሁፎች ሰብስበህ እንደምትጠርዝ ሁሉ እዚሀ ድረ-ገጽ ላይ የሚሰጡህን አስተያየቶች ደግሞ ሰብስበህ ጥሩ አስተማሪ ነገር ታስነብበናለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎችህ ላንተ ካላቸው አድናቆት ባሻገር አስተማሪ የሆኑ እይታዎችን ያንፀባርቃሉና፤ እንዲያውም በእኔ እይታ ከአዲስ ነገር ይልቅ እዚህ ላይ በምታወጣቸው ጽሑፎች ተጠቃሚ የሆንክ ይመስለኛል፡፡

  እግዚአብሔር መጨረሻችንን ያሳምረው እያልኩ ለዛሬው በዚሁ እሰናበትሃለሁ፡፡ ገንዳ ከመሆን የጠብቀን አሜን!ወንድምህ አባግንባር፡፡

  ReplyDelete
 8. ሻማና እኔ

  ጭለማ አይቼ
  እንዳይውጠኝ ፈርቼ
  ሻማውን አብርቼ
  ብርሃኑ ተፈንጣጥቆ
  ዙሪያ ገባውን አድምቆ
  እኔን ከድቅድቅ አላቆ
  በነጸብራቁ ረክቼ
  ሳበቃ ተደስቼ
  ዞሬ ባየው እንባ ውጦት
  የራሱ 'ሳት ራሱን በልቶት
  እኔን ከድቅድቅ አላቆ
  እርሱ ደቆ አልቆ
  አስታወሰኝ እኔነቴን
  ለራሴ ያልሆንኩትን
  ለሰው ስኖር ያኖርኩትን።

  መክ.

  ReplyDelete
 9. ተስፋብርሃንApril 29, 2010 at 11:46 AM

  ውድ ወድንሜ ዲ/ን ዳንኤል ቃለ ሕይወት ያሰማልን በዕውቀት ላይ ዕውቀትን ይጨምርልን ከዚህ ሌላ ምንም ማለት አልችልም

  ጥሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነጥብ ነው በርታ ግፋበት ድንግል ማርያም ከነልጇ አትለይህ

  ተስፋብርሃን

  ReplyDelete
 10. ሚያዚያ 21 2002 Abj

  (ሻማ ሆነው በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ላልካቸው)

  ReplyDelete
 11. Dn Daniel, I found it is well organized , broad and helpful idea.
  Abetu Amlakachin Mekari atasatan.

  ReplyDelete
 12. «አያችሁ፣ ገንዳ ለከብቱ ሁሉ ያጠጣል እንጂ ለራሱ አይጠጣም፡፡ እንዲያውም ባጠጣ ቁጥር እየጎደለ ሄዶ ጭራሹኑ ይደርቃል፡፡ እናንተም እንደዚያ እንዳትሆኑ» አሉን፡፡

  Amen Kalehiwot yasemalen wondimachin Dn. Daniel

  ReplyDelete
 13. " 'እንዲህ ልክ ልካችንን ንገሩን እንጂ' አሉ ንጉሱ" አለ በውቀቱ፡፡

  እሴብሐከ አሁየ።

  ReplyDelete
 14. I have lack of words to explain such type of written. It is very interesting expression.
  በመጀመሪያ እንዲህ ለመፃፍ ያበቃህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን
  እግዚአብሔር ክክፉ ነገር ይጠብቅህ ብዙ ለማስተማር ዕድሜ ይስጥህ
  ከዚህ በላይ ዝም ነው እንጂ የምለው የለጝ

  ReplyDelete
 15. wechew gude leka endih nene??
  DM

  ReplyDelete
 16. ‹‹የማይነጋ ሕልም ሳልም
  የማይድን በሽታ ሳክም
  የማያድግ ችግኝ ሳርም
  የሰው ሕይወት ስከረክም
  እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም፡፡››
  ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን

  ReplyDelete
 17. አኬ SAID ዳኒ ቃል ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 18. Betleyem la zihe zamen tesemami yehone betam kumnegern yemyasetemer naw ka hulu belaye rsen felego mageneyt ka bezu cheger endemyaden temeherten yesete naw. Daneal kante bezu negerochen yeche agerena hezb yetebekal bechal beyeametu leke endante mahone enkawan bayechelum tenesh yemikerarebu 10 sawochen lameferat betemokere ena abatoch enatoch ehet wenedemochem beteslot betsab malkam naw elalahu
  rajem edemena tenenten yeseteh

  Elroe
  Za Gechi

  ReplyDelete
 19. you the jentle man I proud of you.

  ReplyDelete
 20. አርቲስት ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ታዋቂ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ደራሲ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ጋዜጠኛ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ፖለቲከኛ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፤ ነጋዴ ከመሆናችሁ በፊት ሰው ናችሁ፡፡ ሰው ባትሆኑ ኖሮ እነዚህን ነገሮች ሁሉ መሆን አትችሉም ነበር፡፡ ሰው መሆናችሁ ሲያቆም ደግሞ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አብረው ያቆማሉ፡፡ ስለዚህም ዝናን እና ታዋቂነትን፣ ክብርን እና ሽልማትን፣ ገንዘብን እና ሀብትን፣አድናቆትን እና ተወዳጀነትን ስላገኛችሁበት ነገር ብቻ ሳይሆን ሰው ስለሆናችሁበትም ነገር ማሰብ አለባችሁ፡፡

  ReplyDelete
 21. Danny
  I was waiting for your articles week by week when you were writting on Addis Neger. Now I can't wait to read what your next point of reflection.
  God bless you and your family
  Aklilu

  ReplyDelete
 22. Betam Ameseginalehu

  ReplyDelete
 23. እግዚአብሔር ጥበብን ያብዛልህ …..እግዚአብሔር ጥበብን ያብዛልህ …..

  ReplyDelete
 24. D.DANNY YOU ARE A MIRROR FOR US,OH! GOD BLESS YOU!! PLEASE KEEP IT UP OK!

  ReplyDelete
 25. I REALY WONDAR YOU!NOT ONLY THE WAY THAT YOUR EXPRESSION,BUTALSO THE FEATURE WHICH ARTICULAT RAW DATA AND IDEA TO MAKE THEM ALIVE AS THE COVANATE OF HUMAN BENIG AND PLANTS.THE NATURAL CONVATION OF PLANTS AND HUMANBENING WHICH MAKE THEM ALIVE EACH OTHER.NO ONE ALIVE INDEPENDENTLT WITH OUT EXCHANGE OFCARBODIOXID AND OXGEN RESPECTIVELY.YOUR WERITING ANDIDEA LIKE THIS.[Iam Baroke The salisaiShe]

  ReplyDelete
 26. You are right Dani!
  Your writings are Hopefully rewarding.You are being the mirror of these generation.What can I say more than....

  ReplyDelete
 27. ብዙዎቻችንን ያስተማረ ነው
  እኔ ግን ራሴንም ሌሎችንም ሰዎችን ሳስብ ድራማ እየሰራን የምምንኖር ነው የሚመስለኝ፡፡ እንደውም የውሸት ተዋናይ ጭምብል ያጠለቅን ራሳችንን መሆን የማንችል ሰዎች፡፡ በዚህ ጽሁፍ መሰታወትነት ራሴን አይቸበታለሁ፡፡

  እግዚአብሔር ረጅም ዕድሜና ጤንነትን ይስጥህ፡፡

  ኤልሮኢ
  ዘገቺ

  ReplyDelete
 28. beautiful...............beautiful....... no word!!!!!!!!!!
  don't forget to take care of you and protect urself from the socalled " bezu memesgen kemiametaw fetena" .
  coz we ( I) need ur everything.
  Selase yetebekuh,
  Yabatochachin tsnatachewuna bereketachew kant gar yehun.
  once again no word to say thanx and to express how much u r important to us

  ReplyDelete
 29. ''ሕዝብ አይጨበጥም፡፡ ሕዝብ የሚባል መዋቅርም የለም፡፡ ሕዝብ ተቆጥሮ በትክክል አይታወቅም፡፡ ስለ ሕዝብም አፍን ሞልቶ ትክክለኛውን ስሜት መናገር አይቻልም፡፡ ሕዝብ የሚባል ተቋምም በሕግ ዘንድ የለም፡፡ ቤተሰብ ግን ይጨበጣል፡፡ ይቆጠራል፡፡ አፍን ሞልቶ ሊናገሩለትም ይቻላል፡፡ በሕግም የታወቀ ትርጉም እና ጥበቃ አለው፡፡ እናም የማይጨበጠው የሕዝብ ከመሆናችን በፊት፣ የሚጨበጠው የቤተሰባችን እንሁን፡፡...''

  What a nice article !
  God bless you bro Daniel

  Beamlak !

  ReplyDelete
 30. አ/ሚካኤልMay 7, 2010 at 4:19 PM

  ዲያቆን ዳንኤል

  ሁለገብ የሆነ ፀሐፊ በዚህች ዘመን ያሰፈልጋል
  እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንህ ያብዛልን
  ዕድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን።እኛም አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን ተጠቃሚዎች ያድርገን።
  እንዲህ ያለውን ለማን ይቻለዋል?
  ሌላው ዳኒ ምናልባት አንተ ሳታስበው ቀረህ ብዬ ሳይሆን ስለ ኢትዮዽያውያን ፊደሎች አቀራረጽና አጻጻፍ
  አንድ ብትለን በእርግጥ ሊቃውንቱ ያሉት እንዳለ ሆኖ(በተለይም አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው) እንዳሰፈሩልን ይህ ልል የቻልኩት ለምሳሌ ንጉሥ ሲፃፍ
  ፩. ንጉስ
  ፪. ንጉሥ
  ትክክለኛው ፪ኛው እንደሆነ ። ልክ እንደዚሁ ሌሎችም
  በ “ ሀ” “ሐ” “ኀ” “ሠ” “ ሰ” “ አ” “ዐ” “ ፀ “ “ጸ” የሚፃፉ ስሞች የትኛው ፊደል መጠቀም እንዳለብን ያለህን ብትለን

  በርታ ቀጥል

  ReplyDelete
 31. ሚሊዮን ፍቃዱJuly 14, 2010 at 2:15 PM

  ዳኒ እግዚአብሄር ካንተ ጋር ይሁን
  ሚሊዮን ፍቃዱ

  ReplyDelete