Thursday, April 22, 2010

ባልን ማን ፈጠረው?


«ባል ሚስቱን በሥራ ቢረዳት ፣በቤት ውስጥ ቢተጋገዙ፣ የባል ትምክህት ቀርቶ የሚስት ተጨቋኝነት ተወግዶ በእኩልነት ቢኖሩ፣ ባሎች በልጆች አስተዳደግ፣ በማዕድ ቤት አስተዳደር፣ የቤት ቀለብ በመግዛት ቢሳተፉ» እየተባለ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሃሳቦች ይሰነዘራሉ፣ ትምህርቶች ይሰጣሉ፣ ቅስቀሳዎች ይደረጋሉ፡፡ ሃሳቦቹ መልካሞች ቢሆኑም እጅግ ግን የዘገዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሃሳቦች የሚነሡትና እንዲተገበሩም የሚፈለጉት አብዛኞቹን ሊለወጡበት በማይችሉበት፣ ያለበለዚያም ጥቂት ለውጦችን ብቻ በሚያመጡበት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ነውና፡፡

ባልነት ማኅበረሰቡ ሲሠራው የሦስት ነገሮች ድምር ውጤት አድርጎ ነው፡፡ የወንዴነት፣ የወንድነት እና የአባ ወራነት፡፡ «ወንዴነት» በተፈጥሮ የሚገኝ ጾታ ነው፡፡ ወንድነት እና አባ ወራነት ግን ማኅበረሰቡ የሚፈጥራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው «ወንዴን ፈጣሪ ባልን ግን ማኅበረሰቡ ይፈጥረዋል» የሚባለው፡፡

በኛ ማኅበረሰብ ዘንድ «ወንድነት» የተፈጥሮ ጾታን ብቻ አያመለክትም፡፡ ወንድነት ጀግንነትን፣ አሸናፊነትን እና ታላቅነትን የሚያመለክትም ነገር ነው፡፡

ወግድልኝ ድጓ ወግድልኝ ቅኔ
ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ

በሚለው የአርበኛነት ግጥምም «ወንዶች» ብሎ የጠራቸው «ጀግኖች»ን ነው፡፡

«ወንድ» የሚለው ስያሜ ለሴቶችም ሊሰጥ የሚችል ቅጽል ነው «እርሷ እኮ ወንድ ናት» እንዲሉ፡፡ እንዲያም ቢሆን እንኳን ማኅበረሰባችን ይህንን ስያሜ ለሁለቱ ጾታዎች የሚሰጥበት መንገድ ይለያያል፡፡ ማኅበረሰባችን «ወንድነት» ከወንዴነት ጋር የተያያዘ እንዲሆን ይፈልጋል፣ ይጠብቃል፡፡ ወንድነትን ከሴቴነት ጋር አብሮ እንዲኖር ግን አይጠብቅም፡፡ ለዚህ ነው «ወንዱ ልጅ እንደ ሴት አለቀሰ» በማለት ማልቀስ ከወንድ የማይጠበቅ፣ ሴት ብታደርገው ግን የማያስገርም ነገር አድርጎ የሚገልጠው፡፡ በሌላም በኩል በሴቷ ዘንድ የጀግንነት ሥራ የታየባት እንደሆነ በዚያው በሴትነትዋ እንደማድነቅ

ጉድ በል ጃን አሞራ ተደነቅ ስሜን
ሴቷ ልጅ እንደ ወንድ ነዳችው ነጩን

በማለት በጣልያን ጦርነት ጊዜ የገጠመው ለዚህ ነው፡፡ ይህም ከወንዶቹ የሚጠበቀውን ሴቷ ልጅ መሥራቷን ለማመልከት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ «ሴቴነት» እና «ሴትነትም» እንዲሁ ይለያያሉ፡፡ «ሴቴነት» ጾታ ነው፡፡ «ሴትነት» ግን ማኅበረሰቡ የሚፈጥረው ገጸ ባሕርይ ነው፡፡ ሴትነትን ከሴቴ ጾታ ጋር ብቻ ሳይሆን «ከመሸነፍ፣ ከማልቀስ፣ ከመፍራት እና ጠባየ ስስ ከመሆን» ጋር ማኅበረሰቡ አያይ ዞታል፡፡ ይህንኑ በባሰ ሁኔታ ለመግለጥም «ሴታ ሴት» የሚል ቃል ጨምሮለታል፡፡ ሴቶቹ እንኳን ራሳቸው ከወንዶቹ ጋር ሲጣሉ ድፍረት በተሞላው ልብ «ቀሚስ ብለብስ ሴት እንዳል መስልህ» እያሉ ይናገራሉ፡፡ «ፈሪ እንዳልመስልህ» ማለታቸው ነው፡፡ ችግሩ ግን «ሴትነት» ከሴቴዎች የሚጠበቅ፣ቢከሰት የማይገርም ነገር ተደርጎ ሲወሰድ፣ በተቃራኒው ከወንዴዎች የማይጠበቅ እና የሚያሳፍር ነገር ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡

ሴትነት እና ወንድነት ማኅበረሰባችን ለሁለቱ ጾታዎች ያለውን አመለካከት፣ ደረጃ እና ከሁለቱ ጾታዎች የሚጠብቀውን ነገር የሚያመለክቱ ራሱ ማኅበረሰባችን የፈጠራቸው ነገሮች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሣ አብዛኛውን ጊዜ «ባልነት» የሦስት ነገሮች ድምር ውጤት እንዲሆን አድርጎ ማኅበረሰቡ ቀምሮ ሠርቶታል፡፡ ወንዴነት፣ወንድነት እና አባ ወራነት፡፡

ማኅበረሰቡ «ወንድ» የተባለውን ገጸ ባሕርይ ሲቀርጸው አደባባይ ከመዋል ጋር፣ ገድሎ ከመፎከር ጋር፣ ኃይልን ከመጠቀም ጋር፣ ከአሸናፊነት ጋር ነው፡፡ «ሴትነት»ን ደግሞ ቤት ውስጥ ከመዋል፣ ከተሸናፊነት፣ ከማጀት እና ከጭምትነት ጋር አያይዞታል፡፡ በዚህም ምክንያት ማኅበረሰባችን ለወንዶች ይሰጠው የነበረውን ቦታ ያህል ለሴቶች ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ሴት ስትወለድ አንድ ጊዜ ወንድ ሲወለድ ሦስት ጊዜ እልል የሚለው ወንዴነትን ከጀግንነት ጋር ስለሚያያይዘው ነው፡፡

ለብዙ ዘመናት ወንድ ነገሥታት ከሚስቶቻቸው ጋር ሲነግሡ እንዳልኖሩ ሁሉ እቴጌ ዘውዲቱ በነገሡ ጊዜ ባላቸው አብረው እንዳይነግሡ የተደረገው ከዚሁ የማኅበረሰቡ አመለካከት የተነሣ ነው፡፡ ባላቸው ከነገሡ መንግሥቱን ይቀናቀናሉ፣ በኋላም የፈለግነውን ለማስደረግ እምቢ ብለው ክንዳቸውን ያሳያሉ ተብሎ ተፈርቶ፡፡

ማኅበረሰቡ እንዲህ አድርጎ የቀረጻቸውን «ወንድ» እና «ሴት» የሚባሉ ሁለት ገጸ ባሕርያትን ማኅበረሰባዊ ሚና በተመለከተ በተረቶቹ፣ በግጥሞቹ፣ በአባባሎቹ፣ በስያሜዎቹ፣ በንግግሮቹ ሁሉ ይበልጥ ያጠነክራቸዋል፡፡ አሁን እንኳን ሠለጠነ በሚባለው ዘመን ትንንሽ ዕቃዎችን «አንቺ» ብለን ስንጠራ ትልልቅ ዕቃዎችን ግን «አንተ» ብለን የምንጠራቸው ይሄው በየተረቱ እና በየአፈ ታሪኩ፣ በየሠርጉ እና ልቅሶው እየሰማን ስንቀረጸው የኖርነው ነገር አልለቀን ብሎ ነው፡፡ ስለ ሴቶች መብት የተቋቋሙ ብዙዎቹ ማኅበራት እና ድርጅቶች እንኳን ድርጅታቸውን «አንተ» ብለው እንጂ «አንቺ» ብለው የማይጠሯት ይሄው የማኅበረሰቡ ትርጓሜ ውስጣቸው በማያነቃንቁት መሠረት ላይ ስለተገነባ ነው፡፡

ባልን መጀመርያ የሚፈጥሩት ራሳቸው እናቶች ናቸው፡፡ «ወንድ ነህ» እያሉ ከሚሰጡት ማሞካሻ ጀምሮ ወደ ማጀታቸው የተጠጋውን ልጅ «ሴታ ሴት፣ እዚህ ጓዳ ውስጥ ምን ያርመጠምጥሃል» እያሉ እስከማባረር ድረስ የባልነቱን ተግባር ከልጅነቱ ያስለምዱታል፡፡ ሴቶች ልጆቻቸውን የቤት ሞያ ለማስተማር የሚያደርጉትን ጥረት ያህል ለወንዶች ልጆቻቸው ያንን ለማድረግ አያስቡም፡፡ ሲያስቡ እንኳን «አንተ ወጡን ሠርተህ ሚስትህ ምን ልትሠራ ነው?» እያሉ ከመገረም ጋር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ማኅበረሰቡም ቢሆን የአንዳንድ እናቶችን ተግባር ይቃወመዋል፡፡ «ልጁን የቤት ሠራተኛ አድርጋ አስቀረችው፤ እንግዲህ ይሄ ልጅ ሚስት ነው ባል የሚያገባው» ይላቸዋል፡፡

ብዙዎቻችን የምናውቀው

ይወለድ እና እነከፍ እንከፉ
ጋን ይሸከማል ከነድፍድፉ

የሚለው ሥነ ቃል እኮ ጀግንነትን የሚያበረታታ ይመስላል እንጂ መልእክቱ ሌላ ነው፡፡ እንከፍ እንከፉ ከተወለደ ጋንን ከነድፍድፉ ይሸከማል ነው የሚለው፡፡ ጋንን ከነ ድፍድፉ የሚሸከም «እንከፍ» ለምን ይሆናል፡፡ ጀግናውስ ለምን አይሸከምም? ይህንን ነገር ሴቶቹ ሲያደርጉት የሚተች የለም፡፡ ወንዶቹ ሲያደርጉት ግን እንደ እንከፍነት ይወሰዳል፡፡ ይህንን እየሰማ ያደገ ልጅ ታድያ «እህትህን ውኃ አሸክማት» ቢባል እንዴት እሺ ይላል፡፡

በአንድ ወቅት ሁለት ባል እና ሚስቶች ተጣሉና ሽምግልና ተቀመጥን፡፡ ከኔ ጋር ሽማግሌ ሆነው የተቀመጡት ሰዎች በእድሜ የእኔን እጥፍ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ነበሩ፡፡ እኔ ወደ ሽምግልናው የገባሁት ቤተሰቡን በሌላ ሁኔታ ስለማውቅ ነበር፡፡ የጠቡ መነሻ ባልየው ከሚስታቸው ውጭ ሌሎች ልጆች እንዳሏቸው መታወቁ ነበር፡፡ ሚስት በዚህ ዓይነት ልንተማ መን አንችልም፡፡ መጀመርያ ነገር ትዳሬን አፍርሷል፣ ሁለተኛም ዋሽቶኛል ብለው ለሽማግ ሌዎቹ አቀረቡ፡፡ ወደ ሰባ ዓመት የተጠጉት አንደኛው ሽማግሌ የተናገሩት ነገር ምንጊዜም አይረሳኝም፡፡ «ወንድ ልጅ ሌላ ቦታ አይሂድ ማለት'ኮ ወንድ ልጅ አይሽና ማለት ነው» የሚል ምሳሌ አመጡ፡፡ ከሁለት ሰዎች በቀር ሌሎቹ አምስት ሽማግሌዎች ይህንኑ ሃሳብ አጠናከሩት፡፡ ማኅበረሰቡ ለወንዶች እዚህ ድረስ መብት ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ይህንን እየሰማ ያደገ ልጅ ነገ ምን ዓይነት ባል ሊሆን ይችላል?

ጥሩ ወንድ በሌለበት ጥሩ ባል፣ጥሩ ሴት በሌለበትም ጥሩ ሚስት መመኘት የዋሕነት ነው፡፡ ጥሩ ሴት ማለትኮ መልካም ሥነ ምግባር ያላት፣ ክብሯን የጠበቀች፣ሞያ የምትችል እና መልከ ቀና የሆነች ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የሴትነት ሚናን በሚገባ የምታወቅ መሆንም አለባት፡፡ እርሷ ራስዋ ማኅበረሰቡ የቀረጸውን የተሳሳተ ገጸ ባሕርይ የተሸከመች እና ችግሩም የማይገባት ከሆነች «ጥሩ ሴት» አፈራን ማለት አንችልም፡፡

ጥሩ ወንድም እንዲሁ፡፡ መልክና ቁመና፣ጠባይ እና አመል ብቻ ጥሩ አያሰኝም፡፡ ወንድነትን ማኅበረሰቡ ስለ ወንዶች ከፈጠራቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች ጋር ደባልቆ የሚቀበል፣የችግሩ ፈጣሪ ባይሆን እንኳን የችግሩ ሰለባ ከሆነ «መልካም ወንድ» ፈጠርን ማለት አይቻልም

ባልነት በወንድነት ውስጥ ያድግና በጋብቻ ጊዜ ይገለጣል እንጂ ባልነት በጋብቻ ቀን አይጀ መርም፡፡ ከተበላሸ ወተት የተስተካከለ እርጎ አይገኝም፡፡ እርጎውኮ በወተቱ ውስጥ ነበረ፡፡ እርጎው እርጎ ተብሎ ከመጠራቱ በፊት ወተት ነበር፡፡ እርጎነት የሚጀመረው ወተትነት ሲጀመር ነው፡፡ እርጎው ጥሩ እንዲሆን የፈለገ ሰው መጀመሪያ መከባከብ ያለበት ወተቱን ነው፡፡ በእኩልነት የሚያምኑ፣ የሥራ ልዩነት የማይፈጥሩ፣ ሳሎኑንም ጓዳውንም የሚያውቁ፣ ሚስቶቻ ቸውን በሁለመናቸው የሚራዱ ባሎችን ከጎረምሶች መካከል መፈለጉ እምብዛም የሚያዋጣ አይመስልም፡፡

ምዕራባውያን ባሎች ከኢትዮጵያውያን በተሻለ የጓዳውን ሥራ ይሠሩታል፡፡ ጓደኞቻቸው ይህንን ቢያውቁ ምንም አይመስላቸውም፡፡ እነርሱም ያንኑ ያደርጉታልና፡፡ ቤት በመዋላቸው ወይንም ጓዳ ጓዳውን በመዋላቸው «ሴታ ሴት» ብሎ የሚሰድባቸው የለም፡፡ ለምን? እነርሱም በጾታ ወንዴዎች ናቸው፡፡ በእኛ ሀገር ካሉት ወንዴዎች ጋር የጾታ ልዩነት የለባቸውም፡፡ ልዩነቱ ማኅበረሰቡ አንድ ዓይነት ሆነው የተፈጠሩትን ወንዴዎች ሁለት ዓይነት አድርጎ እንደገና መፍጠሩ ነው፡፡ ያኛው ማኅበረሰብ «ወንድ» ለሚለው ገጸ ባሕርይ የሰጠው ትርጓሜ ጓዳውንም እንዲጨምር መሆኑ፣ እና የኛ ማኅበረሰብ ጓዳ ጓዳውን መከልከሉ ነው ልዩነቱ፡፡ ለዚህም ነው ባልን ማኅበረሰቡ ይፈጥረዋል የሚባለው፡፡

እዚህም በየጎረቤቶቻችን ቀድሞ የነቃ ቤተሰብ አግኝተው እና የማኅበረሰቡንም ትችት ችለው ባልነትን ለወንድነት ከተሰጠው ትርጉም በተጨማሪ አስፍተው የተቀረጹ ወንዴዎች አሉ፡፡ የሴቶችን ማኅበረሰባዊ ሚና መጋራት የባልነት አንዱ ተግባር አድርገው እንዲወስዱት ሆነው በመቀረጻቸው በጾታ ከሌሎቹ ወንዴዎች አንዱ ቢሆኑም እንኳን ባልነቱ ላይ ግን ሌላ ሆነው መልሰው ተወልደዋል፡፡ ባልን ማኅበረሰብ ይፈጥረዋል ማለት ይህ ነው፡፡

እነዚህን ባሎች ማግኘት የሚቻለው ከዛሬ ሕፃናት ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን ባሎች የመፍጠር ሥልጣንም በዛሬው ማኅበረሰብ ጫንቃ ላይ ነው፡፡ ልጆቻችን በሕፃንነታቸው ያልተማሩትን ሥራ በኋላ ከየት ያመጡታል? በልጅነታቸው ያላወቁትን ጓዳ በኋላ የት ያውቁታል? በልጅነታቸው ያልተረከቡትን ኃላፊነት በኋላ ከማን ይቀበሉታል?

44 comments:

 1. Gude eko new.Balen man feterw alki I was not sure of the answer till i read it."ባልነት በወንድነት ውስጥ ያድግና በጋብቻ ጊዜ ይገለጣል እንጂ ባልነት በጋብቻ ቀን አይጀ መርም፡፡ ከተበላሸ ወተት የተስተካከለ እርጎ አይገኝም"፡፡ We have to change our way of rasing our childre.'እነዚህን ባሎች ማግኘት የሚቻለው ከዛሬ ሕፃናት ውስጥ ነው'. Egziabher tsegawen yabizaleh lela min elalhu.

  ReplyDelete
 2. በጣም ጥሩ ጎሽ በርታ ይህ ነው ያንተ ስጦታ በዚህ ዙሪያ እኔም መረጃ ልሰጥህ እችላለሁ
  ግን ለምን በአካል ተገናኝተን አንወያይም?
  tesfa

  ReplyDelete
 3. God Bless D/n Danny

  It really astonishes me how you analysis the subject of matter from an angle that is hidden from most of us. You get to the source of the matter with clear evidence and finish on how to resolve the problem.

  Why are so many of us incapable of observing with your level of vision ?

  I can’t wait to read your next article.

  You are gifted by the Grace of God to make us see what is in front of us.

  ReplyDelete
 4. ዲ .ዳንኤል እጅግ ደስ የሚል አሰተውሎት የያዘ በማኅበረሰባችን
  ውስጥ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት እንድናስተውል ያደርጋል እና ቢቻልህ የወንዶች እና የሴቶች እኩልነት እውነተኛ አንድምታ ይዘህ በትቀርብ የብዙኃንን የልብ ትርታ ይደመጣልጣና ለመዳሰስ ብትሞክር ጥሩ ይመስለኛል።

  ReplyDelete
 5. Well Said Deacon. I really enjoyed reading today's blog and wish it is possible to borrow your eyes for one week (ezine lebuna). I totally agree with your solution but the problem I had is we are becoming such a short sighted community and our effort is concentrated on blaming today's husbands instead of working on tomorrows husbands'. May God give us the wisdom to shape our tomorrow today.

  ReplyDelete
 6. Hi Dn. Daneil, it is a good saying. "mintadergewaleh yeh hulu astedadeg yametabin tata new" especally, men lets start to change it together.


  DM

  ReplyDelete
 7. yam

  hi dani thank u for urs articles which u have raised in the community.

  keep it up .....

  i thank u

  ReplyDelete
 8. wow this amezing View!!! Weye Yehechi "Neser" Yematayew Yele..........Thanks for creating a good attitued for us and the next generation!!! Tsegawen Yabzaneh!

  ReplyDelete
 9. Dn.Daniel melkame eyeta new yabertaline...

  ReplyDelete
 10. "tikile" alu yetikikle abate.
  really u r correct for all Ethiopians(the d/ce is only degree). but u know what my families are like the above but i thought that i don't repeat the same mistake in the future when i become husband(if God wills). what i learn from u is it is possible but difficult b/cs i am an Ethiopian. please all of us try to Exercise from the Existing family.
  thank u dani Temechetognale
  Keep it up

  ReplyDelete
 11. "tikile" alu yetikikle abate

  ReplyDelete
 12. በነገራችን ላይ ዳኒ ይህ ነገር ሚስት ሆነው እንደ ባል ለሚየደርጋቸውም ይሆን ይሆን ከሆነ እሰየው ነው ካልሆነ ግን ባሎች እራሳቸው ሚስት ለመሆን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል አለበለዚያ ሆለቱም ሚሰት ወይም ሁለቱም ባል ከሆኑ ችግር ነው

  ReplyDelete
 13. መልካም ጽፈኃል፡፡እግዚአብሄር ያበርታልን፡፡

  ገ/ዮሐነንሰስ

  ReplyDelete
 14. አባግንባር (ከሮማ)April 23, 2010 at 11:18 AM

  ውድ ዲን. ዳንኤል
  የተለመደው ሰላምታዬ ይድረስህ፡፡

  አንድ ነገር ትዝ አለኝ የሽምግልናውን ገጠመኝህን ስትነግረን፡፡ ሁለት በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ወግ ይዘው ሲጨዋወቱ “….ኤድያ! ወንድ ድሮ ቀረ…ድሮ እኮ ቅጥኝ ያልተያዘ ወንድ ወንድ አይባልም አሁን ምን ወንድ አለና ነው …፡፡” ይሄንን አባባል እየሰማ ያደገውስ ወንድ እንዴት ባል ይሁን?

  በሴቶች በኩልም ቢሆን ወንድ ሲወለድ እልልታው ከፍ ተደርጎ ለሴት ግን ቁጥሩ ማነሱ ሁሌም የሚያስገርመኝ ነገር ነው፤ ለምን መሰለህ እልል የሚሉትም ሴቶቹ ሆነው ሳለ ማዳላቱ ለምን አስፈለገ? እንደገና የሴቶች ጉዳይ ተብሎ ደግሞ ድርጅት ማቋቋምን ምን አመጣው? ለሁሉም ግን አቀራረብህን ስለተማርኩበት እግዚአብሄር ይስጥልኝ ብያለሁ፡፡

  ReplyDelete
 15. THANKS DANI EGZIABHIRE YEBARKHE .............

  ReplyDelete
 16. Dear Dn.Daniel I suggest you to listen the sermon,"real dating",of Fr.Anthony(Coptic priest)
  to see the view of Coptic church on this issue.

  ReplyDelete
 17. ዳኒ እግዚአብሔር ይርዳህ
  በርታ ቀጥል ከዲያቢሎስ ፈተና እግዚአብሔር ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 18. Thank God who gives you such a brilliant mind Di.Daniel. It is also my wish to see a change from our men.

  ReplyDelete
 19. በቅርቡ የኢትዮጵያ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር በበሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲቆም ጠየቀች ሲባል ብትሰሙስ?

  ReplyDelete
 20. Dear Dn Dani, that is a reality. Thank you very much. But, we should know that some wives in the Western (Europe) are also still under the influence of Husbands! A white freind of mine has told me that there are many cases of divorces because the husband doesn't like the way his wife dresses or perfumes, or... Don't you think that some of the Ethiopian cultures helped husbands and wives to tie together (with real love), compared to the lack of "SineMigbar" and the rate of divorces we obsrve in the Western? I hope, one day, you will say something about the core (nice) cultures of Ethiopians that lacks from the others (even other African countries).
  May God bless you!

  ReplyDelete
 21. TANKS DANI GOOD JOB!!

  ReplyDelete
 22. ዉድ ዳኒ ቃለ ሕይወት ያሰማልን። በመጀሪያው አንቀጽ ላይ "...ሃሳቦቹ መልካሞች ቢሆኑም እጅግ ግን የዘገዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሃሳቦች የሚነሡትና እንዲተገበሩም የሚፈለጉት አብዛኞቹን ሊለወጡበት በማይችሉበት፣ ያለበለዚያም ጥቂት ለውጦችን ብቻ በሚያመጡበት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ነውና፡፡" የሚለውን ተመልክቼ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ነበር ቀሪውን ክፍል ሳነብ የቆየሁት። የጽሑፉን ዓቢይ መልዕክት የያዘውን የመጨረሻው አንቀጽ ላይ "እነዚህን ባሎች ማግኘት የሚቻለው ከዛሬ ሕፃናት ውስጥ ነው፡፡" የሚለውን ሳነብ ተጽናናሁ። ምክንያቱም በነገይቱ ኢትዮጵያ እህቶቻችን ትዳራቸውን የሚያከብሩ ሚስቶቻቸውን እንደራሳቸው የሚወዱ ባሎችን ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ዛሬ በነማሙሽዬ ላይ መስራት እንደሚቻል ይገልጻልና። ሰሚ አጣች እንጂ ቅድስት ቤተክርስቲያን እኮ ልጆቿ ሲጋቡ ጋብቻቸውን የአብርሐምና የሳራ እንዲሆን ታስተምራለች። ምክንያቱም በአብርሐምና በሣራ ቤት መከባበር መደማመጥ ነበረ። ባል ሚስቱን ይሰማል ሚስት ባሏን ትሰማ ነበር።ሁለቱም ትላልቅ ጉዳዮች ላይ መወሰን ይችሉ ነበር። እናታችን ሣራ ይስሐቅ ከእስማኤል ጋር ሊያድግ አይገባውም ብላ አጋርን እንዲያሰናብታት በነገረችው ጊዜ አብርሐም የሚስቱን ሀሳብ ሳይንቅ ፈቃዷን ፈጽሟል። እንዲህ መከባበር ከሰፈነበት ትዳር ይስሐቅን የመሰለ ቅንና ታዛዥ ልጅ ተገኝቷል። እኔ ግን በጣም የሚያስፈራኝ የነገዎቹን ባሎች የዛሬዎችን ማሙሾች ማን ሊያስተምራቸው ነው? በቃል ብቻ ሊማሩ ይችላሉ። በተግባር ማስተማር የሚችሉ በቂ ባሎች ይኖሩ ይሆን? አላውቅም።

  ReplyDelete
 23. +++
  በርታ ግን መ/ቅ ላይ ወንድ የሴት ራስ ነዉ ይላል:: እንዴት ነዉ ???????????
  ማብራሪያ ያስፈልገዋል እላለሁ::

  አድናቂ እህትህ

  ReplyDelete
 24. +++
  Selam Dn. Daniel,
  I always was looking something like this to tell other who is our brother. When I was back home, by the time you taught us at St. Markos church at 6 killo... I was dreaming : if he got a chance, he will write something different that teach us every one...
  Now that dream comes true.

  Write more... more and more. I love to read your articles, books, and love to listen your preaching... like "Yahiyoch Kis.” So unique from other preaching

  Bertalign Eski.

  ReplyDelete
 25. Just to give a response to one of the replies posted, yes it is true that the Bible says... "wenede yeset eras new"; however, it doesn't mean guys or husbands should not participate in housekeeping stuff such as cooking, shopping, or sharing the load of taking care of kids. One time I read an article “I’m a wife but I need a wife” I think it is one of the articles written by Dn. Danie…correct me if I’m wrong. I’m not one of the female’s right activists; however, I’m not up for the big name that our society gave for guys.
  I remember back in time when my sister and I were kids, my aunt and her husband (I guess I could say my uncle) came from abroad after they got their doctorate in medicine. My father had never and ever participated in household activities which by then I thought it was normal. So what happened was,… my uncle took the broom and started sweeping the balcony (veranda) floor. For me and my sister, it was the first time to see a man holding a broom and sweeping the floor. I remember how we laughed. We embarrassed him; and he dropped the broom and went to the bedroom. I had never seen him involved in such kind of household activities since that day. For him it was normal because he came from abroad and he has been doing it for years but for us…hmmm …O! NO…NO… NO…!!!We told the story to my mother and my father and a few other people as if he had done something wrong … very bad thing. But …I mean what is wrong with it …absolutely nothing. I do respect my husband and I believe it brings more love and respect if I get help in household stuff from him.
  MB from MN

  ReplyDelete
 26. እኛ የሀበሻ ወንዶች ስደት ካልወጣን መች የማጀት ስራ እናውቅና::የማህበረሰቡ ተጽኖ ሊሆን ይችላል አጥብቆ ማጀት መውደድም አልወድም::

  ReplyDelete
 27. Thanks Dani. When you want to write on the issue of sex discrimination you have to broaden your view to the time of creation till the present and through the whole generation of the world. You know at present time concerning the gender issue there two outlooks: just like what we observe in the Ethiopian politics and the real equality of sexes as revealed in holy scriptures. For me all the problems you have mentioned will be solved first through understanding the church teaching about the issue. In fact this also needs a critical observation. As you know the church servants, most of us, haven't a clear understanding of it. Some of us have influenced by the surrounding socio politics waves, some of also interpret the scriptures according to our feeling. As the holy Bible narrates the story of creation Adam and Eve were created from the same material. Most of us focused on Gen.2:18-25, but neglecting Gen.1:26-28. Both of them.Adam and Eve were created in God's image and likeness, from the dust of the land and their soul have the same nature. Their difference is only in gender. People of the same nature but different gender and has different given task: Example motherhood and fatherhood. Adam never becomes mother and Eve never becomes father. This is the grace that God gave them. And also there is also an other difference: difference in physical strength. Please refer the EOTC commentary on the 1Pet. 1:7. Through all these we can observe one amazing thing: the wisdom of God. Though He is only one but He made all these similarity and difference. Out of these, who has an enlighten soul praises the Lord in the high. Dear Dani, let me ask you to turn your view to the surrounding animals. The chicken, the lion, the monkey.... Could you observe among them the issue of gender? How these beings those haven't a rational soul deal with?
  The second advisable means to solve the gender issue is developing a true love among the husband and wife. For many of us living together or engaging to a marriage with somebody seems a true love. According to the scripture love goes beyond that. Love is, in a simple way,giving but not taking. Giving self, giving glory,....What do you think about the kids who were upbrought in a family based on this type of Love. Let me conclude: All of us let us stop criticizing our forefathers and fathers. Let us have a clear teaching of our beloved church and love our spouce as we love ourself. Then there never be anybody who look his spouce who is his organ as inferior to him and start to act against her or him.
  Blessings.
  Kesis, Cairo.

  ReplyDelete
 28. ወንድም ዲ ዳኒ. ጽሁፍህን ወደድኩት!! ቢቻልህ ስለወንድ እና ስለሴት እኩልነት የበለጠ ብትጽም መልካም ነው በአሁኑ ዘመን ሴቶች ወንድ የሆኑበት ዘመን ነው ምክንያቱም የሚቀጥለው
  1. ወልደው ለባል አሳልፈው ይጠፋሉ
  2. ግብረግንኙነት እኛ ካላደረግን ይላሉ
  3. ገብተን ካልቀደስን ካላገለገልን ይላሉ
  ስንቱ ተነግሮ

  ReplyDelete
 29. continue with this

  ReplyDelete
 30. በእውነቱ ጥሩ ሃሳብ ነው ያነሳህው መልካም ባልነትም ሆነ ሚስትነትን ማህበረሰቡ የሚፍጥርው መሆኑ እንዳለ ሆኖ 'ዘግዪቷል' በሚል ሰበብ ላለመለወጥ ምክናየት መፍጠር ግን የለብንም። ስለዚህ ባሎች ለመለውጥ ሚስቶች ደግሞ ይሄ ጸባይ የመጣው ከጋብቻ በኋላ አለመሆኑን በመረዳት ሊማማሩ ይገባል። ሌላው መልካም ባልነት ከጋብቻ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከጋብቻ በፊትም ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው። በትምህርት በስራ አጋጣሚ ከቤተሰብ የምንርቅበት ግዜ ብዙ በመሆኑ።
  ለመልካም እይታህ ምስጋናዬ የላቀ ነው፣
  ቸር ያቆየን።

  ReplyDelete
 31. Thanks Dani for sharing you did what must be done and you really fill the gap !!! Thanks, ...yes indeed...and very true...But still we can make a change in the young folks as well...not noly on the kids..even if it is teh must to work on Kids as well...But still with our young and younng adults as well... So pls you guys, try to be changed and think civilized to work and start to be changed from the bottom.....

  ReplyDelete
 32. May the Almighty Lord Jesus Christ always be with you brother!
  It is the kind of thing that we should help and cooperate since the purpose of marriage( unity)is to be safe labour of each other in every respect of life! I really lack words to express my feelings! thank you so much......
  your brother in Christ!

  ReplyDelete
 33. when i read the article my mind ask me how it is dismissed from our country? & i'm try to suggest the truth that occur in our village. one day there was conflict b/n bal @ mist what i saw there, mist kicked her bal, & somebody said 'endet yasedbenal'enam lerasie endih alkut setua temtita bihon endih yle nebern! hod yfgew.

  ReplyDelete
 34. This article touches my inner part of my life . Up to recent days , I hate to go to kitchen but one day the house maid has lost her father and left my house with out preparing my dinner . to make the long history short .I passed the night empty stomach.
  Had I learn t how to cook before , I would not have starved for a single day .

  ReplyDelete
 35. እኔ ማህበረሰቡ የሰጠውን የወንድነት ትርጉም ወደ ጎን ትቼ ባል ብሆንም ሚስቴ ግን የተቀበለችኝ አይመስለኝም ፡፡ በዚህም ሁል ጊዜ በድርጊቱዋ አዝናለሁ፡፡

  ReplyDelete
 36. Egziabher Yisitilign,

  Yihe malet yene bal new. Esu rasu new.

  ReplyDelete
 37. Selam Dn. Kebret,
  I really like your post. I believe gender inequality is a global issue so I will be happy if you say more in the future. What I don't understand is that (1) most females like masculinity in their partners;(2)most people don't differentiate sex and gender; (3) and most women believe marriage should be patriarchal. I believe women are victims in most marriages this days. And I don't understand why women still want to get married/ keep their marriage. I don't see how women are benefiting from marriage. Can you explain some of these?
  Thanks,
  God be with u!

  ReplyDelete
 38. God bless you. its very good

  ReplyDelete
 39. I can’t wait to read your next article.

  ReplyDelete
 40. ፍሬሕይወት

  እግዚአብሔር ረዳን ለሰዎችም ማስተዋልን ሰጣቸው፡፡
  መምሬ፤የዘመን ባለቤት ዘመንህን አበርክቶ ይስጥልን፤ በዘመንህ ፍጻሜም በመንግሰቱ ያሰብልን
  አሜን!

  ReplyDelete
 41. ye agelegelote zemeniehen yibarkewe rejem edemiee!!

  ReplyDelete
 42. besega kamikenu ena kamitenakolu yitebikihi

  ReplyDelete