Wednesday, April 7, 2010

አሜሪካን ያገኛት ማነው?
«በተለምዶ በሚታወቀው የዓለም ታሪክ «አዲሱ ዓለም» እየተባለ የሚጠራውን አሜሪካን ያገኘው ክርስቶፈር ኮሎምበስ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሁለት ነጥቦችን እንድናነሣ ያደርገናል DISCOVERY የሚለው ቃል ያልታወቀን ነገር ማሳወቅን፣ ያልተገኘን ነገር ማግኘትን የሚ ያመለክት ቃል ከሆነ፣ ኮሎምበስ አሜሪካን አገኘ ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ያች ቦታ ለአውሮፓውያን እንግዳ ትሁን እንጂ በውስጧ ግን ከጥንት ጀምረው ይኖሩባት የነበሩ ሕዝቦች ነበሩባትና፡፡ አውሮፓ ተገኘች እንደማትባለው ሁሉ አሜሪካም እንደ አዲስ ልትገኝ አትችልም፡፡

በሌላም በኩል ቃሉ «መጀመርያ በቦታው መድረስን የሚያመለክት ከሆነም ኮሎምበስ ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ ብዙ ሺ ዓመታት በፊት ወደ ቦታው ያቀኑ ሌሎች ሕዝቦች አሉና ኮሎምበስ አሜሪካን አገኛት ማለት አይቻልም» ይላሉ ሳፉ ኪቤራ የተሰኙ ጸሐፊ NEW AFRICA በተሰኘ መጽሔት yJANUARY 2001 እትም ላይ They came before Columbus በሚል ርእስ ባወጡት ጽሑፋቸው ፡፡

ኮሎምበስ ከመወለዱ ብዙ ሺ ዓመታት ቀድመው ወደ አሜሪካ የተጓዙት አፍሪካውያን ሲሆኑ፣ ባሕላቸውን በዚያው ይኖሩ ከነበሩት ቀያይ ሕንዶች ጋር አዋሕደውታል፡፡ የቀያይ ሕንዶችን አማልክት ተቀብለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኑቢያ - ኬምት ሕዝቦች የአሜ ሪካ ቀያይ ሕንዶችን አማልክት ወደ ሀገራቸው አምጥተው ሲያመልኳቸው ከመኖራቸውም በላይ እነዚህኑ ቀያይ ሕንዶች «የቤተ አማልክቱ ጠባቂዎች እና የዚያ ምድር መንፈሳውያን መዓርጋትን የያዙ ናቸው» ብለው ያምኑ ነበር፡፡

የአፍሪካውያን በአሜሪካ ምድር መገኘት ከአሜሪካውያን ቅድመ ታሪክ /pre-historic America/ የቀደመ ዘመንን /40¸000¬ – 6¸000 ቅልክ/ አስቆጥሯል፡፡

የኑቢያ– ኬሚት ሕዝቦች ወደ አሜሪካ ምድር የገቡት ከክርስቶስ ልደት በፊት 1200 ዓመት አስቀድመው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘግየት ብለውም ቢሆን፣ ከክርስቶፎር ኮሎም በስ በፊት በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙት የማንዲጋ ሕዝቦች ደግሞ በ1307 ዓም ወደዚ ያው ማምራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአፍሪካ አሜሪካውያን ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ባደረጉት በዶ/ር ኢቫን ቫን ሰርቲማ እና በመሳሰሉት ምሁራን እየተጠናከሩ የመጡት መረጃዎች የአፍሪካውያንን በአሜሪካ ምድር ከኮሎምበስ በፊት መገኘት እያመለከቱ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ኢቫን በ1977 ዓም ባሳተ ሙት They came before Columbus በተሰኘው መጽሐፋቸው ከኮሎምበስ በፊት አፍሪ ካውያን በአሜሪካ ምድር ይገኙ እንደነበሩ የአርኬዎሎጂ እና የሥነ ልሳን መረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡

በአፍሪካ ካሪቢያን ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በማበርከት የታወቀው ጸሐፊ ሪቻ ርድ ቢ ሙር The significance of African History በተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንደሚለው «የአፍሪካ ታሪክ /በዓለም ላይ/ያለው ተጽዕኖ አፍሪካ እና ሕዝቦቿ ያላቸውን ታሪክ ለመ ካድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ይታያል፡፡ ለረዥም ዓመታት ይህ ሁሉ የአፍሪካን ታሪክ ለማበላሸት ጥረት የተደረገው አፍሪካውያን ጥቂት ወይንም ምንም ዓይነት ዋጋ እንዳልነ በራቸው ለማሳየት መሆኑ ግልጽ ነው»፡፡

የማንዲጋ ጉዞ

የአርኬዎሎጂ ውጤቶች እና የታሪክ መዛግብት ከኮሎምበስ በፊት ከ1307- 1312 ዓም እኤአ ወደ አሜሪካን ምድር የተደረጉትን የአፍሪካውያንን ጉዞዎች በመግለጥ ላይ ናቸው፡፡ የ14ኛው መክዘ ሙስሊም የታሪክ ጸሐፊ የሆነው የአል ኡማርስ መረጃ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው፡፡ አል ኡማርስ የማንሳ ካንካን ሙሳ 1ኛን ትረካ መዝግቦ አቆይቶል ናል፡፡ ማንሳ ካንካን ሙሳ 1ኛ በወቅቱ የታወቀ የማንዲጋ /ማሊ/ ንጉሥ ሲሆን ወደ መካ ለመሳለም ሲጓዝ በ1324 እኤአ ግብጽ ካይሮ ውስጥ ነበር ከአል ኡማርስ ጋር የተገናኙት፡፡

ማንሳ ለአል ኡማርስ እንደ ተረከለት ማንዲጋውያን የአትላንቲክን ውቅያኖስን መጨረሻ ለማወቅ በነበራቸው ምኞት ወደ ምዕራብ ተደጋጋሚ ጉዞ አድርገው ነበር፡፡ ይህ ጉዞ ከማንሳ ቀደም ብሎ ማንዲጋን ያስተዳድር በነበረው ንጉሥ የተሰጠ ተልዕኮ ነበር፡፡ ከማንሳ የመካ ጉብኝት ጥቂት ዘግየት ብሎ የታሪክ መጽሐፉን ያዘጋጀው አል ኡማርስ እንደ ሚነግረን « (ማንሳን) የንጉሥነት ሥልጣኑ እንዴት ወደ እርሱ ዘንድ ሊደርስ እንደቻለ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም እኛ ሥልጣንን በትውፊት የሚያወርስ ቤተሰብ አባል ነን፡፡ ከእኔ በፊት የነበረው ንጉሥ የዚህን ውቅያኖስ ዳርቻ ማወቅ የማይቻል ነገር ነው የሚለውን ሃሳብ አይቀበልም ነበር፡፡ 200 መርከቦችን በወርቅ፣ በምግብ እና በውኃ እንዲሁም በሌሎች በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሞልቶ ከመርከበኞች ጋር መጀመርያ ላከ፡፡ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን መርከቦች እና መርከበኞችንም በሌላው ጊዜ እንዲሁ ላከ፡፡

«መርከበኞቹን ይመሩ ለነበሩት ካፒቴኖች ንጉሡ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡፡ «መመለስ ያለባችሁ የውቅያኖሱን ዳርቻ ካገኛችሁ ወይንም የጫናችሁት ምግብና ውኃ ካለቀባችሁ ብቻ ነው፡፡» እናም ለብዙ ጊዜ ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ በመጨረሻ አንድ መርከብ ብቅ አለ፡፡ የመርከቡን መሪም ምን እንዳጋጠማቸው ጠየቅነው፡፡ «ልዑል ሆይ» አለ ካፒቴኑ፡፡ «ለረዥም ጊዜ ያህል በውቅያኖሱ ላይ ከተጓዝን በኋላ በውቅያኖሱ መካከል አንዳች እንደ ወንዝ የሚፈስስ ውኃ አገኘን፡፡ መልኩም ሐምራዊ ይመስል ነበር፡፡ የኔ መርከብ ወደዚያ ለመድረስ የመጨረሻው ነበር፡፡ ከኔ በፊት የቀደሙት ሁሉም መርከቦች ወደዚህ ቦታ ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም አልተመለሱም፡፡ እኔ ግን ወደ ነበርኩበት ስለተ መለስኩ በዚያ ሐምራዊ ነገር ውስጥ ሰምጬ አልቀረሁም፡፡»

ነገር ግን ንጉሡ ሊያምነው አልቻለም፡፡ ስለዚህም 2000 ጀልባዎችን/Vessels / አዘጋጅቶ፣ መርከበኞችን እና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሞልቶ መልሶ ላካቸው፣ ያን ጊዜ ንጉሡ መንበሩን ለእኔ አስረክቦኝ ነበር፡፡ ያንን የመርከብ ካፒቴን እና ሌሎችን መርከበኞችም ከዚያ በኋላ ደግሜ አላየኋቸውም፡፡ እኔም የማይደፈረውን ሥልጣን እንደተረከብኩ ይሄው አለሁ፡፡»

ከማንሳ ሙሳ በፊት በማንዲጋ የነገሠው እና 2000 መርከቦችን ወደ ምዕራብ ለአሰሳ የላከው አቡበከሪ 2ኛ የተባለው የማንዲጋ ንጉሥ ነው፡፡ የአሰሳው ዳርቻ አቲሊስ ወይንም የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ወይንም የካሪቢያን መሬቶች ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡

እንደ አልጄርያው ምሁር እንደ ማሕሙድ ሐሚዱላህ አገላለጥ «የመርከቡ ካፒቴን ወደ ኋላ ለመመለስ በወሰነበት ጊዜ የአቡክሪ 2ኛ አሳሽ ኃይል የካሪቢያን ድንበር ላይ ደርሶ ነበር፡፡»

መርከቦችን የመሥራት ጥበብ በአፍሪካ ውስጥ ከኑቢያ እስከ ኬምት ድረስ የተስፋፋ እና የበለጸገ ነበር፡፡ አል ካቲ የተሰኘው የቲምቡክቱ የታሪክ ጸሐፊ የምዕራብ አፍሪካዋ የሶን ግሐይ የመጨረሻው ንጉሥ የሆነው አስክያ ኢሻቅ /1591 ዓም እኤአ/ ከሞሮኮ ጦር ወረራ ለመሸሽ 200 መርከቦችን በኒጀር ወንዝ ላይ ተጠቅሞ እንደነበር ይነግረናል፡፡ አል ካቲ እንደሚለው «የአስኪያ ንብረት የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ መርከቦች በዚያው መንገድ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ እንደ ምገምተው ቁጥራቸው ስድስት ወይንም ሰባት መቶ ሳይሆን አይቀርም፡፡»

ማንሳ ሙሳ መካን ከጎበኘ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ነበር ክሪስቶፈር ኮሎምበስ ወደ አሜሪካ ጉዞ የጀመረው፡፡ ኮሎምበስም ቢሆን ይህንን ለረዥም ዓመታት ሲካሄድ የኖረ ውን የማንዲጋዎች የምዕራብ አሰሳ አረጋግጧል፡፡ «ከምዕራብ አፍሪካ የሚነሡ የነጋዴ መርከቦች በየጊዜው ከጊኒ ወደብ እየተነሡ ወርቅ እና ሌሎች ሸቀጦችን ጭነው ወደ መካከለኛው አሜሪካ እየተጓዙ ይነግዱ ነበር፡፡ ወርቅን ከልዩ ልዩ ነገሮች ጋር በመቀ ላቀል የሚሠራ ልብስን ጥበብ ለመካከለኛው አሜሪካ ያስተማሩትም እነዚሁ አፍሪካ ውያን ናቸው፡፡

«የአሜሪካ ሕንዶች የጥጥ ፈትል ጥበብን በሽመና አሠራር ቀለም እያስገቡ ልክ ከጊኒ፣ ከሴራልዮን ወንዞች ዳርቻ እንደሚመጣው ምርት አድርገው ያዘጋጁ ነበር፡፡ በሁለቱ ምርቶች መካከልም አንዳችም ልዩነት አይታይም ነበር፡፡» በማለት ኮሎምበስ ጽፎ ነበር፡፡

ማንዲጋዎች ከአሜሪካ ሕንዶች ጋር ወርቅን እና «አልማይዛር» የተሰኘውን የጥጥ ልብስ ይነግዱ ነበር፡፡ ኮሎምበስ የእነዚህን ልብሶች መነሻ ቦታ ያወቅ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ስለ ጉዞው በጻፈው የጉዞ ማስታወሻ ላይ «የአሜሪካ ቀይ ሕንዶች /የሚጠቀሙበት/ አልማይዘር የተሰኘው ልብስ ከጊኒ እና ከሴራልዮን ወንዞች ዳርቻ የሚመጣውን ይመስላል» ያለው፡፡

ደቡብ አውሮፓን ይቆጣጠሩ የነበሩት ሙር የተባሉት የሰሜን አፍሪካ ሕዝቦች ከማን ዲጋ ግዛት ጋር በንግድ ይገናኙ ነበር፡፡ አልማይዘር የተሰኘውን ምርት ለስፔናውያን ያስተዋወቁትም እነርሱ ናቸው፡፡ ኮሎምበስ ልብሱን ሊያውቀው የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

African presence in Early America በተሰኘው መጽሐፉ ዶ/ር ቫን ሴርቲማ «ቀያይ ሕን ዶች፣ በዌስት ኢንዲስ የደረሱ ኮሎምበስን እና ሌሎች የአውሮፓ አሳሾችን ከ1492 እኤአ በኋላ ጥቂት ዘግየት ብሎ እነርሱ ጥቋቁር ጊኒያውያን ብለው የጠሯቸው ጥቁር ሕዝቦች ወርቅን ወደ ደሴቶቹ ማምጣታቸውን ነግረዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንቲ ሊያውያን ወርቅን የሚጠሩባቸው ቃላት ከማንዲጋ ቃላት ሊወረሱ ችለዋል» ብሏል፡፡ «ጉአና፣ ካኦና፣ጉአኒ፣ጉአኒን» የሚሉት የአንቲሊያ ቃላት «ጋና፣ካኔ፣ካኒ፣ካኒኔ፣ጋኒን» ከሚሉት የማንዲጋ ቃላት የተወረሱ ናቸው፡፡

አል ባክሪ የተባለው የሙስሊም የታሪክ ጸሐፊ በ1067 ዓም እኤአ «የንጉሡን እምነት የሚከተሉት የጥንቷ ጋና ሕዝቦች የጥጥ፣ የሐር እና በዝምዝም ወርቅ የተጠለፉ ልብ ሶችን ይለብሱ ነበር» ሲል ይገልጣቸዋል፡፡ ከአል ባክሪ አንድ መቶ ዓመታትን ዘግይቶ የጻፈው አል ኢድሪስ በምዕራብ አፍሪካ የነበሩት ሲላ፣ታኩር ፣ጋና እና ጋኦ የተባሉት ሕዝቦች አልማይዘር የተባለውን ልብስ ያዘወትሩ እንደነበር ጽፏል፡፡

ሙንጎ ፓርክ የተባለው የስኮትላንድ አሳሽ በ1795 እኤአ በኒጀር ወንዝ አጠገብ የነበረችውን «ሳንሳንዲንግ»ን ሲጎበኝ ያጋጠመውን እንዲህ ብሎ ዘግቧል «ይህ ቦታ በሙሮች የተሞላ ነው፡፡ እነርሱም ጨውን ከቤሮ /ዋላታ/፣ ዶቃ እና ዛጎል ከሜዲትራንያን እያስ መጡ በወርቅ እና በጥጥ ልብስ ይለውጡ ነበር፡፡ ይህ በውድ ዋጋ የሚሸጡት ልብስ በሙሮች እና በቤሮ ሕዝቦች ዘንድ እጅግ ተፈላጊነት ነበረው፡፡ እዚያ በዝናብ እጥረት ምክንያት ጥጥ አይመረትም ነበርና» ብሏል፡፡

የጥጥ ልብስ ጥበብ አውሮፓውያን ወደ ምዕራብ አፍሪካ ከመምጣታቻው እጅግ ቀደም ብሎ የተስፋፋ ጥበብ ነው፡፡ አካንስ የተባሉት የጋና ሕዝቦች እና የኮትዲቮራውያን ኬኔቴ /KENTE/ ከአውሮፓውያን ወይንም ከዐረቦች የተወረሰ አይደለም፡፡ ይህ አለባበስ የአካባቢውን ሕዝቦች ባሕል፣ እምነት እና ወግ የሚያንጸባርቅ፣ ከሃያ በላይ የተቀደሱ ምልክቶችን የያዘ፣ በአብዛኛውም ከጥንቶቹ የግብጽ ሕዝቦች ከኬምታውያን የተወረሰ ነው፡፡

በደቡብ አሜሪካ በሆንዱራስ የሚገኙት የማንዲጋ ጎሳዎች፣ ጃራዎች፣ እና ጉአባዎች ራሳቸውን «አልማሚዎች» ብለው ይጠራሉ፡፡ ይህም በዓረብኛ «አል ኢማሙ» የሚለው ቃል ውርስ ነው፡፡ ትርጉሙም «መሪ» ማለት ነው የሚል ግምት በአንዳንድ የታሪክ እና የሥነ ልሳን ሊቃውንት ዘንድ ተሰጥቷል፡፡ አውሮፓውያን ለመጀመርያ ጊዜ የቅዱስ ቬንሰንት ደሴትን ሲረግጡ በዚያች ምድር ሁለት ዓይነት ሕዝቦች ነበር ያገኙት፡፡ ጥቁር እና ቢጫ መልክ የነበራቸው፡፡ ጥቁሮቹ ሕዝቦች ራሳቸውን «ክላይፉርናምስ» ብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ ይህም «ካልፋቱ -ን-ናቢ» የሚለው የዓረብኛው ስያሜ ውርስ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመው እንግዲህ ከባርያ ንግድ መጀመር በፊት ነው፡፡

አስቀድመው በቅዱስ ቬንሰንት ደሴት የሠፈሩትና የደሴቲቱን መውጫ መግቢያ በሚ ገባ የሚያውቁት ማንዲጋዎች በ15ኛው መክዘ ከባርያ ንግድ እያመለጡ ለሚመጡት አፍሪካውያን ወገኖቻቸው በአካባቢያቸው የመደበቂያ ሥፍራ ይሰጡ የነበሩት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡

የኑቢያውያን - ኬምቶች ጉዞ፣ 1300 ቅልክ

ከአፍሪካውያን መካከል በአሜሪካ ምድር አስቀድመው የተገኙት የኑቢያ እና የኬምት ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይህ ቅድምናቸውም በ1858 ዓም እኤአ በተገኘው የአርኬዎሎጂ መረጃ ተረጋግጧል፡፡ ይህ ስምንት ጫማ ርዝመት እና 18 ጫማ ክበብ ያለው የኑቢያውያንን መልክ የያዘ የድንጋይ ላይ ቅርጽ፣ ከ800 እስከ 600 ቅልክ ባለው ዘመን የተሠራ መሆኑ ተመስክሮለታል፡፡ በሜክሲኮ፣ ትሬስ ዛፖቴስ በተሰኘች መንደር የተገኘው የሰው ራስ ቅል ቅርጽ ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ በመላዋ ደቡብ አሜሪካ 17 ተመሳሳይ ቅርጾች ተገኝተዋል፡፡

በ1869 ዓም እኤአ፣ ጆዜ ሜግላር የተባለው የሜክሲኮ ምሁር ስለዚሁ የሰው ራስ ቅል ቅርጽ «Mexican society of geography and statistic bulletin ´ በተሰኘው መጽሔት ላይ  ሲገልጥ «በ1862 እኤአ ሳን አንድሬ ቱክስትላ በተባለው ቦታ ነበርኩ፡፡ በሽርሽር ላይ እያለሁ የሰው ራስ ቅል መልክ ያለው የድንጋይ ቅርጽ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከመ ሬት ወጥቶ መታየት እንደ ጀመረ ሰማሁ»

«እኔም ወደ ቦታው እንዲወስዱኝ ጠየቅኩ፡፡ እዚያ ቦታ ስደርስም በአግራሞት ፈዘዝኩ፡፡ ያለምንም ማጋነን ይህ የኪነ ጥበብ ውጤት የሆነ ትልቅ የራስ ቅል ቅርጽ ነው፡፡ ያስደ ነቀኝ ነገር ቢኖር መልኩ ኢትዮጵያዊ መምሰሉ ነው፡፡ በዚህች ሀገር ውስጥ ጥንት ቀደም ብለው ጥቁር ሕዝቦች ይኖሩ እንደ ነበር ያመላክታል፡፡ ይህም በዓለም መጀመ ርያ አካባቢ መሆን አለበት» ብሎ ጽፎ ነበር፡፡

ይህንን እና ይህን የመሰለው የአፍሪካውያንን በአሜሪካ ምድር ቀድሞ መድረስ የሚያስረዱ ጽሑፎች እና መረጃዎች በአውሮ- አሜሪካውያን ምሁራን ዘንድ ሆን ተብለው እንዲዘነጉ እና እንዲድበሰበሱ ሳይደረጉ እንዳልቀሩ ይገመታል፡፡ ይህ የአፍሪካውያንን ታሪክ በአሜሪካ ምድር በደመቀ ሁኔታ የመግለጡ ነውር በ1939 ዓም ተገፈፈና አሜሪካዊው ሊቅ ማቲው ስቲርሊንግ፣ በስሚዞንያን ኢንስቲቲዩት እና በናሺናል ጂኦግራፊ ስፖንሰር የተደረገ አንድ የአርኬዎሎጂ ቡድን በመምራት ወደ አካባው ተጓዘ፡፡ ሜልጋር ከ 77 ዓመታት በፊት የገለጠውን የሰው ራስ ቅል ቅርጽ ለማጥናትም በሜክሲኮ ትሬስ ዛፖቴስ መንደር ተገኘ፡፡

በሚገባ ለስልሶ የተቀረጸው የራስ ቅል ቅርጽ ስተርሊንግን «አስደናቂ የሆነ ስሜትን ይፈጥራል፤ ምንም እንኳን ግዙፍ ቅርጽ ቢሆንም የኪነ ጥበብ ሥራው ያማረ እና ጥራት ያለው ነው፡፡ ምጣኔውም በሚገባ የተለካ፣የተመጣጠነ እና ፍጹም ነው፡፡ እውነታውን ለመግለጥ ከተፈለገ ይህ ቅርጽ የፈሰሰበትን ጥበብ ያሳያል፡፡ ገጽታዎቹ በሚገባ የሚለዩና መልኩም የጥቁር/ አፍሪካውያን/ መልክ ነው» እንዲል አድርጎት ነበር፡፡

ከዚህ ምስል በተጨማሪ የአፍሪካውያንን የብዙ አሥር ሺ ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ የሚያሳዩ እና ከ1500 ቅልክ እስከ 1500 ዓም የተሠሩ አያሌ ቅርጾችም ቴራ ኮስታ በተባለው የሜክሲኮ አካባቢ ተገኝተዋል፡፡ በመስከረም 1974 እኤአ፣ በአሜሪካ ጥናት 41ኛው የሜክሲኮ ጉባኤ ላይ፣ ዶ/ክ አንድርዜይ ዊርሲንስኪ የአፍሪካውያን የራስ ቅሎች ሜክሲኮ ውስጥ በቼሮ ዲ ላስ ሜሳ፣ በሞንቴ አልባና እና በታላቲልኮ መገኘታቸውን ገልጠው ነበር፡፡

የኪነ ጥበብን ታሪክ የሚያጠኑት ትውልደ ጀርመናዊ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ቮን ዉቴናው «Unexplained Faces In Ancient America» በተሰኘው መጽሐፋቸው ከአሜሪካ የተለመደው ታሪክ ቅድሚያ ያላቸውን የአፍሪካውያንን ገጽታዎች የሚያሳዩ የጎሳ መሪዎች፣ የካህናት፣ የዘፋኞች፣ እና የከበሮ መቺዎችን ምስሎች አሰባስበዋል፡፡

ሳፉ ኪቤራ በቁጭት እንደሚገልጡት «ይህ የአፍሪካውያን በአሜሪካ ምድር በቀደም ተነት የመገኘት ታሪክ ትኩረት አግኝቶ በሚገባ ያልተነገረለት በዘረኛነት እና የአፍሪካ ውያንን አስተዋጽዖ አኮስሶ የማየት ጠባይ በተላበሰው ምዕራብ ቀየድ አሠራር ምክንያት ነው፡፡ ሮም እና ስፔይንን በሚገባ ያስተዳደሩት የአምስቱ የኑቢያ /ኢትዮጵያ/ ነገሥታት ታሪክስ ቢሆን መች በሚገባ ይነገራል፡፡ ፍላቪየስ ሆኖርየስ /395 ዓም/፣ እንዲሁም የአኒባልን ምስል በሮም ከተማ ያሳነፀው እና በ200 ዓም ኬምትን የጎበኘው ንጉሥ ሴፕቲ ሚየስ ሴቨረስ /193 ዓም/ የኑቢያ/ ኢትዮጵያ/ ልጆች ነበሩኮ፡፡

የኦለሚ ሥልጣኔ /1200 ቅልክ- 400 ዓም/

ኦለሚ የሚለው ቃል ከአዝቴክ ቋንቋ የተገኘ ነው፡፡ አዝቴካውያን ከ15ኛው መክዘ በፊት በሜክሲኮ እጅግ ታላቅ የሆነ መንግሥት የነበራቸው እና በኋላ ወደ ደቡብ አሜሪካ የገቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዋና ከተማቸው ላ ቬንታ የተሰኘችው የሜክሲኮ ከተማ ነበረች፡፡ «ኦለሚ» የሚለው ቃል «ኦሊን» ከሚለው የእነርሱ ቃል የተወሰደ ሲሆን «ግንዲላ» ማለት ነው፡፡ ይህም «ግንዲላ ከሚመረትበት አካባቢ የመጡ ሕዝቦች» ለማለት ነው፡፡ በሀገራችን ቆለኛ ደገኛ እንደሚባለው ያለ ነው፡፡

«በደቡብ አሜሪካ አስቀድመው መኖር በጀመሩት በኦለማውያን የተዘጋጁ የጽሑፍ ማስረጃዎች አውሮፓውያን አካባቢውን ሲይዙ ወድመዋል፡፡ ስፔይን ውስጥ የነበረውን የአፍሪካውያን ሙሮችን ቤተ መጻሕፍት ያወደሙት አውሮፓውያን በደቡብ አሜሪካም ይህንን ጥፋት ደግመውታል፡፡» ይላሉ ሳፉ ኪቤራ፡፡

ዲጎ ዴ ላ አንዳ የተባሉት የስፔይን ጳጳስ «እነዚህ ሕዝቦች የተለዩ የፊደል መልኮችን በመጠቀም መጽሐፋቸውን፣ ጥንታዊ ወጋቸውን እና ሳይንሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ እኛም እጅግ ብዛት ያላቸውን መጽሐፎቻቸውን አግኝተን ነበር፡፡ የጥንቆላን ነገር የያዙ በመሆናቸው ሁሉንም አቃጠልናቸው፡፡ እነርሱ ግን እጅግ ተፀፀቱ፣ አብዝተውም አዘኑ» ብለዋል፡፡

አንቶኒዮ ዲ ኩይዳድ የተባለው የስፔይን የታሪክ ጸሐፊ በ1588 እኤአ «/ስፔይናውያን/ የጥንታውያን ዩካታውያንን ብዙ መጽሐፎች አቃጥለዋል፡፡ እነዚያ መጻሕፍት የዩካታው ያንን አመጣጥ እና ታሪክ የሚናገሩ ነበሩ» ሲል ጽፏል፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ቀድመው የሠፈሩት ሠፋሪዎች ከ3000 እስከ 2000 ቅልክ ባለው ጊዜ የገቡ ናቸው፡፡ የኦለማውያን ሥልጣኔ ግን ከሁሉም የላቀ ነበር፡፡ ይህ ሥልጣኔ በምዕራብ እስከ ጓቲማላ እና ሆንዱራስ፤ በመካከል እስከ ሜክሲኮ ጠረፎች፣ ኮስታሪካ እና ፓናማ ደርሶ ነበር፡፡

የኦሊማውያንን ሥልጣኔ ከፍ እንዲል ያደረጉት የኑቢያውያን ( ኬምት ሕዝቦች ወደ አካባቢው መምጣት ነው፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና አማልክቶቻቸውን ለአካባቢው ኦሊማውያን አውርሰዋል፤ እነርሱም ከኦሊማውያን ወርሰዋል፡፡ በ ላ ቬንታ የሚገኘው እና የግብፃውያንን የሚመስለው የኦሊማውያን ፒራሚድ እና የምስል ወካይ/ሄሮግላፊክስ/ ፊደላቸው ለዚህ የኑቢያውያን - ኬምቶች ተጽዕኖ አንዱ መገለጫ ነው፡፡

አሁን አሁን በአሜሪካውያን ምሁራን ዘንድ አፍሪካውያን ከአውሮፓውያን እጅግ እጅግ ቀድመው ወደ አሜሪካ ምደር መድረሳቸው የመከራከርያ ርእስ መሆኑ ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ዘመን ዋና አከራካሪው ነገር «የመጀመርያዎቹ አፍሪካውያን ከየትኛው የአፍሪካ ክፍል መጡ?» የሚለው ነው፡፡

ከኑቢያ- ኬምት ሥልጣኔ የቀደመ ታሪክ ባለው በ ታ - ሴቲ ሥልጣኔ /3800 ቅልክ/ በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፉ መርከቦች ሥዕል መገኘቱ የመርከብ ሥልጣኔ እና ውቅያኖስን የማቋረጥ ሃሳብ በአፍሪካውያን ዘንድ ያለውን ቀዳሚ ታሪክ ያሳየናል፡፡ ኒኮ 2ኛ የተባለው የኬምት ንጉሥ በ600 ቅልክ ባሕር ኃይሎቹን የአፍሪካን አህጉር በሙሉ ዞረው እንዲመጡ ማዘዙን እና ባሕር ኃይሉም ዞሮ መምጣቱን፤ ንጉሡም የሞቀ አቀባበል እንዳደረገላቸው መዛግብቱ ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሚገኙት መረጃዎች መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ምድር ያቀኑት አፍሪካውያን የኑቢያ-ኬምት ሕዝቦች መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ይህንን ቀደምትነታ ቸውን የሚያሳየው በአሜሪካ ምድር የተገነባው የመጀመረያው ፒራሚድ ነው፡፡ ይህ ፒራሚድ የቆመው እጅግ አስገራሚ በሆነ አቀማመጥ ነው፡፡ ዶ/ር ኢቫን ቫን ሰርቲማ African presence in Early America በሚለው መጽሐፋቸው ላይ «ፒራሚዱ የቆመው እንደ ሌሎቹ የግብጽ ፒራሚዶች ሁሉ በሰሜን ደቡብ አክሲስ ላይ ነው፤ ይህኛውም ፒራሚድ እንደ ግብጽ ፒራሚዶች ሁሉ ለቤተ መቅደስ እና ለመቃብርነት መንታ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በሜክሲኮ ቲዮቲዩካን በተባለው ቦታ የቆመው ባለ 225 ስኩዌር ሜትሩ ትልቁ ፒራሚድ መሠረቱ ልክ ከግብጽ ፒራሚድ ጋር ተመሳሳይ መጠን ያለው እና ትልቁን የግብጽ ፒራሚድን /226.5 ስኩዌር ሜትር/ የሚተካከል ነው» ብለዋል፡፡

በሁለቱ ፒራሚዶች መካከል ያለው ተመሳሳይነት በኬምት የነበሩት አስትሮሎጂስቶች እና የሂሳብ ሰዎች ናቸው ወደ አሜሪካ ተጉዘው ይህንን ፒራሚድ በተመጣጣኝ ስሌት እና መጠን የሠሩት የሚለውን ግምት እጅግ ያጠናክረዋል፡፡ ዶ/ር ኢቫን ከዚህም በተጨ ማሪ «የኦሊማውያን ሥልጣኔ በነበሩባቸው ቦታዎች በተደረጉ ጥናቶች የተገኙት የራስ ቁሮች ምስል የኑቢያ ( ኬምት ወታደሮች ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጨረሻው ሚሊኒየም የንጉሥ ራምሴ ወታደሮች ይለብሱት የነበረውን የሚመስል ነው፡፡ እነዚያ የራስ ቅላቸውን እና ማጅራታቸውን ይሸፍኑ ነበር፡፡ በራስ ቁራቸው ላይ የሚያደርጉት ጉትዬ ተንጠልጣይ ገመድ በሁለት ጆሮዎቻቸው ፊት እንዲወርዱ ያደርጉ ነበር፡፡» ብለዋል፡፡

የኬምታውያን እና የኦሊማውያን ሥልጣኔ በሌሎች ብዙ ገጽታዎችም ይመሳሰላል፡፡ በሜክሲኮ በ ቼሮ ዲ ላ ፔድሬ በሚገኘው የኦማውያን መቅደስ የቆመው የተከበረ ሰው ምስል ድርብ ዘውድ የደፋ፣ የኬምታውያንን ምልክቶች ያሉበት ነገር እንደሚሠዋ የሚ ያሳይ አፍሪካዊ መልክ ነው፡፡ የኬምታውያን የተቀደሰ ጀልባ በኦሊማውያን ሥዕሎች ላይ በተመሳሳይ መልክ እና ስያሜ ተሥሎ ተገኝቷል፡፡ የሥልጣን ምልክት የሆነው የኬምታውያን የልዑላውያን መውቂያም በሜክሲኮ በ ኦእቶቲትላ በተመሳሳይ መልኩ በተሳለው በኦሊማዊው ንጉሥ እጅ ይታያል፡፡

የግብፃውያን የሕይወት ምልክት የሆነው አንክህ በተመሳሳይ ስያሜ እና ምልክት በኦሊማውያን ዘንድ ተገኝቷል፡፡ ኦሊማውያን ይህንን ምልክት የሕይወት ዛፍ To-naca-qua-hui-tl ብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ የምልክቱ መጠን፣ ቅርጽ እና ቀለምም ከኬምታውያን ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

በኬምታውያን የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ የተጠቀሱት ዘጠኙ አማልክት በኦሊማውያን ዘንድ ነበሩ፡፡ በሜክሲኮ በሚገኘው ፒራሚድ ላይም «ዘጠኙ የጨለማ ልዑላን´ ተብለው ተጠርተዋል፡፡

እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ይዞ ተጨማሪ መረጃዎችን በወዲህም ሆነ በወዲያ ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡ ሁልጊዜ የምዕራባውያንን ድምፅ ብቻ እየሰሙ እና እርሱንም እንደ ዶግማ የማይቀየር እውነት አድርገው እየያዙ መጓዝ ሊያከትም ይገባዋል፡፡ አፍሪካውያን ምሁራን የትናንት ታሪካቸውን በመመርመር፤ ለዛሬውም ትውልድ የሥነ ልቡና ስንቅ በመሰነቅ በእልህ እና በቁጭት ለዕድገት እና ለልዕልና የሚነሣ ትውልድ መፍጠር አለባቸው፡፡ ለብዙ ዓመታት ሲከማች በነበረው የአፍሪካውያን የበታችነት ተረታ ተረት ምክ ንያት የወደቀውን የትውልድ ሞራል ከፍ አድርጎ በዚያው ላይ ወደ ላቀ ታሪክ የመሸጋገርያ ጊዜው አሁን ነው፡፡

ምዕራብ አፍሪካውያኑ አካኖች ሰንኮፋ ብለው የሚጠሩትን ፍልስፍና (ወደ ኋላ ተመልሶ ካለፉት ነገሮች ለአሁን ሥልጣኔ የሚጠቅሙትን ማምጣት) መጠቀም የሚያስፈልግበት ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ የጥቁር አፍሪካውያን ታሪክ ገና ብዙ ይቀረዋልና፡፡

14 comments:

 1. ዴርቶጋዳ
  ስላቀረብክልን ጽሁፍ እያመሰገንኩና ‹‹ በርታ ›› የሚለውን ምርቃቴን እያስቀደምኩ የሚከተሉተለውን እንደ አስተያየት ወይ ደግሞ እንደ ጥያቄ እንደምትቀበለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡-
  1. ‹‹አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ የሰሜኑን ህዝብ ወይም ደግሞ ከኦርቶዶክሳዊ ክርስትና መስፋፋት ጋር ተያይዞ ያለውን ብቻ ነው የሚጠቅሰው በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ታሪካቸው ያልተጣፈ እና ያለተነገረላቸው ህዝቦች አሉ ፡፡ በተለይ ደግሞ የደቡብ ህዝብ ›› የሚል አመለካከት በህዝቡ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ምሁራንም ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ኢሀዴግ ይህን አሳብ ለከፋፍለህ ግዛ መርሁ ጠምዝዞ ይጠቀምበታል በተለይ ይህ ነገር የጦዘው ብሔር ተኮር የሆነ እንቅስቃሴ በየክልሉ እየተስፋፋ ሰለሄደ ሊሆን ይችላል ፡፡አንዳንድ ምሁራንም የኢትዮፕያ ታሪክ የእነኝህን ህዝቦች ታሪክ አካቶ እንደገና መጻፍ አለበት የሚል ጽኑ አቋም አላቸው፡፡ /በእርግጥ እኔም የኢትዮጵያ ታሪክ በራሷ ልጆች እንደገና መጻፍ አለበት የሚል አስተያየት አለኝ/
  2. ሌላው ደግሞ ‹‹የእነኝህ ታሪካቸው ያልተጻፈላቸው ህዝቦች ሁነቶች ተጽፎ ቢገኝ እንኳን አግባብ ባለው መልኩ አልተጻፈም ብዙ ጊዜ ከባዕድ አምልኮ ጋር ተያይዞ ነው የሚጠቀሰው›› የሚል ትችት አለ፡፡
  3. አሁን አሁን ደግሞ ‹‹ የአንዳንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ‹‹የት መጣ›› አላግባብ ከስነ መንግስት ፈሊጥ /ፖለቲካ/ ጥቅም አኳያ ሊሆን ይችላል አከራካሪ እየሆነ መጥቷል፡፡እንደውም እነዚህ ህዝቡን እንወክላለን የሚሉ አፈ ቀላጤዎች የሆነ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ‹‹እኛ እኮ ሀገራችን እዚህ አልነበረም ዘራችን ይህ አይደለም›› የሚል ባዶ ፉከራ እያሰሙ ህዝቡን እየበከሉት ነው፡፡
  4. ደግሞ እኮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እራሱ ‹‹የጨለማ ዘመን ተብሎ›› የሚታወቅ የታሪክ ማስረጃ የለም እየተባለ የሚወራበት ሁኔታ አለ /በዘናዊ የታሪክ ትምህርት ውስጥ ማለት ነው/፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደግሞ ብዙ ገድሎች እና ሃይማኖታዊ ጽሁፎች አሏት ስለዚህ ስለ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተህ ብትጽፍልን በጣም ደስ ይለኛል፡፡
  ውድ ታላቅ ወንድሜ በዛሬው ጽሁፍህ ስለ አሜሪካ አገኛኘት ታሪክ አፍሪካውያን እና አንዳንድ ምሁራን ምን እንደሚሉ አስታውቀህናል ፡ እኛ ሀገር ደግሞ ብዙ ታሪካቸውን ያላውቅንላቸው ህዝቦች / ከሌላው እና ከተጻፈው ታሪካችን ሲነጻጸር/ አሉ፤በአንድ ዘመን እነ እከሌ ምን ነበር የሀገራዊ ተሳትፎአቸው የት ነበሩ የሚለውን ማወቅ እንፈልጋልን፡፡ እንደማውቀው ከሆነ አንተ ስለ ኦርቶዶክስ ‹‹የገድል መጻህፍት›› የተሻለ ዕውቀት አለህ ስለዚህ ከእዛ ውስጥ የተጻፈ ብዙ ጠቃሚ እና ያለንን የዕውቀት አድማስ የሚያሰፋ ነገር ሊኖር ስለሚችል እንደው ትዕዛዝ ካልሆነብኝ ‹‹ ቆፈር ቆፈር ›› አድረገህ ብታሳውቀን፡፡ልክ የአሜሪካ አገኛኘት አከራካሪ አንደሆነ ሁላ ኢትዮጵያ ውስጥም አመጣጣቸው አከራካሪ የሆነባቸው አካሎች አሉ አንደው ድፍረት ባይሆንብኝ ከላይ ስለጠቀስኩት ነገር አንድ ጽሁፍ ‹‹ ጀባ ብትለን››፡፡
  ለኔ ዴርቶጋዳ ማለት ቅድሚ የራስን ማወቅ ማሳወቅ እና ለሀገር ለወገን በሚጠቅም መልኩ የተደበቀን እውነት ፈልፍሎ አውጥቶ መገንዘብ ነው፡፡ይህ ሲሆን አለማቅማማቱ ለለውጥ ማቀንቀኑ ይጀመራል አሊያ ግን ግማሽ አካል ሆኖ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው፡፡
  ካጠፋሁ ‹‹አፉ በለኝ››

  ReplyDelete
 2. Hmmmmmm... interesting and confusing!!! But I second Dertogada's comment.

  ReplyDelete
 3. it so interesting but i have one comment:
  1. even though you have your ouw reason to present it at one time but as to me it is better to post it in part one and two unless it may take time to read, specially for those live in ethiopia with little internet acess. it is my comment for the future too.
  2. i have accepted DERTOGADA comment too

  ReplyDelete
 4. me.Daniel kibret, am realy glad to read this great history. this is valuable not only 4 ethiopians ( africans) but also 4 the "new world peoples" b/s their history have been neglected by most of western historians especiqally their pre- and ancient history.like wise, we our selves have still lots of assignments to be done.our early history is not yet studied very well. for that we need to work together.May God bless ur carrier

  ReplyDelete
 5. ዲ/ን ዳንኤል,

  የሃይማኖት መምህሮቸ ከአስር አመታት በፊት አንተ፣ ዲ/ን ኤፍሬምና ሌሎችም የማህበሩ ልጆች በመሆናችሁ በጣም ደስ ይለኛል። በቅርቡ ኢትዮጵያ መጥቸ ከማሕበሩ ሱቅ ሳይቀር ያንተን መጽሐፍ ለማግኘት ሞክሬ ሳይሳካልኝ በመመለሴ እያዘንኩ እያለሁ "ልብስና ምላስ"ን ከኢንተርኔት አገኘሁና አነበብኩ። መጽሐፉን ያላገኘሁበት ሃዘኔ ጠፋ። "ልብስና ምላስ"ን ስንት ሰው እንዲያነብ እንዳደረኩ ቁጥሩን በውል አላስታውስም። የእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳይለይህ የሁልጊዜም ጸሎቴ ነው። ይህ የጀመርከው የነኢቫን ሰርቲማ የሥራ ውጤት ደግሞ በጣም ብዙ ሊጻፍበት የሚችል ነው። ሌሎችም ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን የጻፉዋቸው በጣም የሚያስገርሙ እውነቶች አሉ። ሩኖኮ ራሺዲ (Runoko Rashidi)የሚባል ሰው በየሃገሩ እየዞረ ብዙ ሰርቷል። "Global African presence" የሚባል መድረክ/ፎረም አለው። ብዙ ሃሳብ ታገኝበታለህ። ወደጥቁር ዘረኝነት የሚያዘነብሉትን የአክራሪ አካሄድ ያላቸውን ትቶ አፍሪካውያንም ከአውሮጳውያኑ ባላነሰ በሁሉም መስክ ለዓለም ያበረከቱትን አስተዋጽዖ የሚያሳዩ መረጃ ያላቸው ብዙ ሥራዎች ታገኛለህ። ኢትዮጵያ ደግሞ በየመስኩ ቀዳሚ ቦታ እንደነበራት በነዚሁ ጥቁር አሜሪካውያን የተሰሩ አሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ የማናውቃቸው ስለሆነ እንዳንተ ባለ ማለፊያ ብዕረኛ ተሰርተው ቢቀርቡ ብዙ ሰው ሊጠቀምባቸው ይችላል። ከዚህ ቀደም ካላገኘኸው ይህ አድራሻ መነሻ ሊሆንህ ይችላል። http://www.cwo.com/~lucumi/runoko.html። በርታ። እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን። ባንተ ዕድሜ እስካሁንም የሰራኸው የሚገርም ነው። ገና ብዙ እንደምትሰራ አልጠራጠርም።

  ReplyDelete
 6. የአፍሪካውያን በአሜሪካ ምድር መገኘት ከአሜሪካውያን ቅድመ ታሪክ /pre-historic America/ የቀደመ ዘመንን /40¸000¬ – 6¸000 ቅልክ/ አስቆጥሯል፡፡
  Yih neger tikebelwaleh. Yegze aketater.
  dafiwe21@yahoo.com

  ReplyDelete
 7. dear dani,if i were u 'dertagadane' "afu alelewem".lafereteretewena any other part of Ethiopia does not need a history that is similar or equivalent to that of the north to stay united.what does it mean for the southern ethiopia if they were not able,in their history,to build obelisk like the axumites?it means nothing here is why:europe was not even close to axumite technology during that time but they made history after the axumites the idea of having no history does not stop them from making history does.so to may fellow ethiopians i would say u do not necessarily need history u can make history without any background.history is for those who believe in mental difference depending the color of their skin.so ur essay tells us that our fathers lived comfortably and exercised their knowledge in every thing that interests them and we can do them.

  ReplyDelete
 8. Dani. it is intersting so please countinue. because we are ethiopian have many history

  ReplyDelete
 9. ዳንኤል እግዚኣብሔር ይስጥልኝ!

  ጥቁር አሜሪካውያን ይህንን አካኼድ ተከትለው ሆን ተብሎ አፍሪካውያን ታሪክ እንደሌላቸው ሲደሰኮር፣ ሲነገረን፣ ስንሰማው፣ ስንማረውና ስንሸመድደው የኖርነውን እውነት የሚመስል ውሸት ጥሩ አድርገው እያፈረሱት ነው፡፡ ጥቁርነት ላይ የሚያጠነጥኑት ጽሑፎቻቸውን ስንመለከት ኢትዮጵያዊነት ሰፊ መሠረት ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክና ማንነት እንዳለው ይነግሩናል፤ ያስረዱናል፤ ያረጋግጡልናል፡፡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን መልካችን ጠየም ስላላለ ጥቁርነታችንን ሽምጥጥ አድርገው ሲክዱ ይታያል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ያለውን አፍሪካዊ ሙዚቃ የአፍሪካ ሙዚቃ ብለው በጥቅል ይጠሩታል- የኢትዮጵያ ሙዚቃ አፍሪካዊ አለመሆኑ ነው፡፡

  ብዙ የሀገር ታሪክ ፍቅር እንደሚያቃጥላቸው የሚነገርላቸው ሰዎች ራሳቸውን ሲገልጡ የሜሮዌ፣ የዳአማት ወይም የአኵስምን ሥልጣኔ መነሻ አድርገው ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን የኢትዮጵያዊነት መነሻው ከአኵስምም ይቀድማል፡፡ ሌላው ቀርቶ የግብጽን ፒራሚዶች የገነቡት ዛሬ ያሉት ከእስልምና መስፋፋት ጋር የገቡት ዐረቦች ሳይሆኑ ጥቁር ሕዝብ (ኢትዮጵያውያን) ለመሆናቸው በርካታ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ግብጽ የሚባለው ስም ራሱ በግሪካውያን የዛሬዋን ሰሜናዊ ግብጽ አካባቢ ያሉ ቦታዎችን ለመሰየም እስኪያውሉት ድረስ ከሜዲትራኒያን ባሕር ወዲህ ያሉ በናይል አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ተብለው ይጠሩ እንደነበር የሚያስተውለው ጥቂት ነው፡፡ ይህንን ጥንታዊ ታሪክ ስንመለከት የኢትዮጵያ ታሪክ የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ብለው ሲሟገቱ የታዘብናቸው ሰዎች ታሪክ ያልጠነቀቁና ኢትዮጵያዊነትን ከዛሬው የኢትዮጵያ ካርታ ጋር በጅማት ክር መስፋት የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ሆነው ይታያሉ፡፡ ይህም “አሜሪካን ከኮለምበስ በፊት አልነበረችም፡፡” የማለትን ያህል አለማወቅ ነው፡፡

  አውሮፓውያን ጽፈው ከሰጡን የዘለለ ታሪካችንን ስለማንማረው አናውቀውም፡፡ ትምህርት ቤቶቻችን የእንግሊዝ ፓርላማ መቼ እንደተመሠረተና ስለአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት የሚነግሩንን ያህል ትንሽ ይህንን እውነት ቢያካፍሉን እንዴት ድንቅ ነበር! በተማሪዎቻችሁ የምትወደዱ፣ የምትወደሱ የታሪክ መምህራን ወዴት ናችሁ?

  እያንዳንዳችን ያወቅነውን ነገር ለሰዎች የማካፈል ግዴታ አለብን፡፡ በተለይ ለታናናሾቻችን ኢትዮጵያዊነት ጨካኝ አውሮፓውያን ከነገሩንና እኛ ካዘጋጀንላቸው የመማሪያ መጻሕፍት በላይ ታሪክና ማንነት እንዳላት ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነት…

  ReplyDelete
 10. ደግ ብለሀል!! እራስህ በፍላጎት ይህን የመሰለውን የተደበቀን እውነታ ለማያውቁት ጊዜህን ሰውተህ ያወቅኸውን እውቀት ስላካፈልከን የተባረክ ሁን። ግን ልጠይቅህ የምፈልገው አንድ ነገር አለ ይኸውም ስለ ቃላት ውርስና ወይም ከየት እንደተገኘ ያስቀመጥከው ነው። ለምሳሌ "አልማሚ" የሚለው ቃል በዓረብኛ "አል ኢማሙ" ከሚለው ቃል ዝምድና ሲኖረው ነገር ግን እነዚያ አባቶቻችን ግዕዝን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ጥርጥር የለኝም። ምክንያቱም ኢትዬጵያውያን ነበሩ እንጂ ዐረቦች አልነበሩም። በመሠረቱ "ግዕዝ" የመጀመሪያ ማለት ሲሆን በቋንቋነቱም ሆነ በጽሁፍም ደረጃ ከሌሎች ቋንቋዎች የመጀመሪያነቱን ቦታ ይይዛል። መጽሐፉም እንደሚለው የሰው ሁሉ ቋንቋ አንድ ነበር። ስለዚህ እነዚያ አባቶቻችን እራሳቸውን ይሰይሙበት የነበረው ቋሎች ሁሉ ከግዕዝ የመጣ መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ ላሳስብ የምፈልገው ነገር መጀመሪያ ወደሌላ ቋንቋዋች ሄዶ ትርጓሜን ከመጎልጎል የለንን እንመርምር።

  አልማሚ፡ በግዕዝ አለማ፣ አልሚ
  ዓረብ እንኳን ቃሉ በግዕዝ ሲተረጎም አረበ፣ ወደ ምዕራብ ገባ/ተቀመጠ ማለት ነው።

  http://video.google.com/videoplay?docid=-3924842503305971166

  ReplyDelete
 11. Hello, Dn Daneil, how are you? Hope your are well with all your families.
  Dn. Daneil am masters student, in Population Studies; my stream is Population and Development.I want to do my Thesis around church ;especially on migration,displacement and the stand of the church on population issue.What will be your advice please?
  Thanking in advance, am
  ASNAKECH HABTAMU
  tamene.asnakech@gmail.com

  ReplyDelete
 12. God bless u D/n Daniel
  Am very proud to be an Ethiopian,am not saying Amhara,tigrie,oromo... cause I hate such name because am just more than such name called man(sew).Dear Dani I have same question with Dertogada so pls...pls...plz do that all question.Thank you our dear!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 13. የምእተ አመቱ ምርጥ ጸኀፊ ይወጣሀል፡፡እግዜአብሄር ይባርክህ ፡ጥበብን ጨምሮ ይግለጥልህ በርታ

  ReplyDelete
 14. Dear DK!! no need to go far to disprove their secret. i mean, not only the history of the "new world" is pejoratively given to their stupid human grace. please tell the history of the discovery of the origin of Nile river . Europeans associate its origin with the discovery of James Bruce. but, the fact is Ethiopian farmers, particularly the gojjam, sekela farmers live and use the river beginning from the spot for thousands of years. in the university, i my self teach my students as it was live with us and give credit for its origin to our hero farmers. thank you

  ReplyDelete