Sunday, April 4, 2010

የኔ ጀግናይድረስ ለ CNN ቴሌቭዥን ጣቢያ

በቀደም ዕለት ፕሮግራማችሁን ስከታተል የዓመቱን የCNN ጀግኖች ምረጡ የሚል ማስታወቂያ በተደጋጋሚ አየሁ፡፡ ነገር ግን ምርጫው ካቀረባችኋቸው ዕጩዎች መካከል ሆነብኝና ተቸገርኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ልመርጣት የምችላት የኔዋ ጀግና አልተካተተችምና፡፡ እናንተ ካቀረባችኋቸው ዕጩዎች የተለየች፣ ምናልባትም ሥራዋን ባለማወቅ የተነሣ ማንም በዕጩነት ሊያቀርባት የማይችል አንዲት ጀግና አለች፡፡ የእኔ ጀግና እርሷ ነች፡፡

በ1960ዎቹ መጨረሻ የዚህች ሀገር ልጆች ጎራ ለይተው ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ብለው ተጨፋጨፉ፡፡ ከሁለቱም ወገን እልፍ አእላፋት ልጆች ደማቸው እንደ ጨው ተዘርቶ ቀረ፡፡ አባታችን ከቤት እንደወጣ የቀረው ያኔ ነበር፡፡

በኋላ በኋላ እንዳወቅኩት አባቴ ቀይ ሽብር ተፋፍሞበት መንገድ ላይ ተጥሎ ኖሯል፡፡ ለእናቴ ከኀዘኑ በላይ የጎዳት አስከሬኑን ለማንሣት በየቢሮው ደጃፍ፣ በየባለሥልጣናቱ ግቢ ያየችው መከራ፣ የከፈለችው ጉቦ ነው፡፡ እንዲህ ላለው ነገር እንግዳ በመሆኗ ሰዎች ይሆናል ያሏትን ሁሉ ታደርግ ነበር እንጂ ለውጤቱ ርግጠኛ አልነበረችም፡፡

ቀብሩ በዘመድ አዝማድም፣በጉቦም ተፈጸመ፡፡ ቀጣዩ ኑሮ ግን በዘመድ እና በጉቦ የሚዘለቅ አልሆነም፡፡ የቤት እመቤቷ እናታችን እናትም አባትም ሆነች፡፡ ቤቱ የሚተዳደረው በአባታችን ደመወዝ እና በእናታችን ጉልበት ነበር፡፡ አሁን የመተዳደርያውን ገንዘብ ማምጣቱም ሆነ የቤቱን ሥራ መሥራቱም የርሷ ኃላፊነት ነበር፡፡ እኛ ልጆቿ ደግሞ እንዳናግዛት ለሥራ ያልደረስን ለመብል ያላነስን ሕፃናት ነበርን፡፡ ለእናታችን የአባትነት ኃላፊነቱ እንጂ ወጉ እና መዓርጉ አልተረፋትም፡፡

እናታችን የመጀመርያውን ብርቱ ትግል ያደረገችው ሕልውናዋን ለማስጠበቅ ነው፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም ያሰቡ ሰዎች የተከራየነውን ቤት መውሰድ ፈለጉና ቀበሌ ተጠራች፡፡ «አሁን ባለቤትሽ ስላረፈና አንቺም ገቢሽ አነስተኛ ስለሆነ ይህንን ሰፊ የቀበሌ ቤት ለቅቀሽ በዐቅምሽ ሌላ አነስ ያለ ቤት ውሰጅ» ተባለች፡፡ መክፈል እንደምትችል፤ ስትቸገር ያን ጊዜ ጉዳዩን እንደምታመለክት ለማን ታስረዳው፡፡ ለመናገር እንጂ ለመስማት ዝግጁ የሆነ ባለሥልጣን ማግኘቱ ነበር ከባዱ፡፡ ያውምኮ የቤቱ ኪራይ ሃያ አምስት ብር ነበር፡፡ መቼም አንዳንድ ደግ ሰው በየዘመኑ አይጠፋም፡፡ ከአመራሮቹ መካከል በደረሰባት ነገር ያዘኑ ሰዎች ረድተዋት በስንት መከራ ቤታችንን ከመልቀቅ ተረፍን፡፡

በርግጥ ለእናታችን ያችን ሃያ አምስት ብር ማግኘቱም ቢሆን ከባድ ነበር፡፡ ሥራ ለመቀጠር ስትሄድ ያ የቀይ ሽብር ታሪክ ቀድሟት ይደርስና ምክንያቱንም ውጤቱንም በማታውቀው ነገር፣ የርሷ ፍላጎት እና ተሳትፎ ይኑርበት አይኑርበት ባልተጣራ ነገር አዝና ትመለሳለች፡፡ ከሁሉም የሚከብዳት ግን ባሏ የሞተባት ሴት ሁሉ ለሥጋዊ ነገር ትንበረከካለች ብለው በሚያስቡ ወንዶች የሚመጣባት ፈተና ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሥራ ፈተናው ቤታቸው ይሰጥ ይመስል ቤታቸው ይቀጥሯታል፡፡ ሌሎቹ የመሥሪያ ቤቱ ቢሮ ጠቧቸው ሆቴል የተከራዩ ይመስል ሆቴል ይቀጥሯታል፡፡

እንጀራ ነውና መቅረት እየከበዳት፣ ችግሩን ታውቃለችና መሄዱም እየዘገነናት ለኛ ስትል አንድ ሁለት ጊዜ ሞከረችው፡፡ ነገር ግን የተፈለገው ዕውቀቷ እና ጉልበቷ ሳይ ሆን ሴትነቷ መሆኑን ስታውቅ እንደ አራስ ነበር ተቆጥታባቸው፣ እንደ አንበሳ አግሥ ታባቸው ትመጣና ቤት ገብታ ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡ ጸጋዬ ገብረ መድኅን «ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው» ብሎ ነበር፡፡ ወንድ ልጅ ብቻ አይደለም ብቻውን የሚያለቅሰው፡፡ አባትም እናትም ሆና ልጆቿን የምታሳድግ ጀግና እናትም ብቻዋን ነው የምታለቅሰው፡፡ ልጆቿ እንዳይረበሹባት ልጆቿ ፊት አታለቅስም፡፡ መጠቃቷ እንዳይታ ወቅበት በአደባባይ አታለቅስም፡፡ ብቻዋን ነው የምታለቅሰው፡፡

ወርቆቿን ሸጠች፣ጥሩ ጥሩ ልብሶቿን ሸጠች፣ የቤት ዕቃዎቿን ሸጠች፣ በደኅና ጊዜ የገዛ ቻቸውን ጫማዎቿን ሳይቀር መሸጧን ከቤታችን ሲጠፉ ነበር የምናውቀው፡፡ በኋላም እኛን ሁሉ ያሳደገችውን አንዲት አነስተኛ ሱቅ ከፈተች፡፡ እኛ ትምህርታችን እና ኑሯ ችን አልተቋረጠም፡፡ የእርሷ ሰውነት ግን እየተለወጠ ሲሄድ ይታወቀናል፡፡ እርሷ ከኑሮ ጋር ብቻ አይደለም የታገለችው ከበሽታ ጋር ጭምር ነው፡፡ ሕመሟ እንዳይታወቅባት በውስጧ ትቋቋመው ነበር፡፡ ብተተኛ ብትተኛ እንኳን ከሁለት ቀን በላይ አትተኛም፡፡ በኋላ በኋላ ግን በሽታውንም አሸነፈችው መሰል አያማትም ነበር፡፡

ዛሬ ዛሬ ሳስበው የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ግዥልን ያልናትን ሁሉ ትገዛለች፡፡ አድርጊልን ያልናትን ሁሉ ታደርጋለች፡፡ አንድም ቀን አትማረርም፡፡ ከየት እንደምታመጣው አላውቅም፡፡ እኛ ፊት እንደ ድሮው ትጫወታለች፡፡ ለትምህርታችን የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አልተጓደለም፡፡ ከየት ነበር የምታመጣው? የሚለውን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ እንደ ጧፍ አብርታ፣ እንደ ሻማ ቀልጣ ድህነትን አሸንፋ ልጆቿን አስተምራ ለሀገር ያበረከተች ይህች የጀግኖች ጀግና አይደለችም?

ዛሬ ዛሬ «ሃርድ ቶክ» ላይ ቀርበው ከባድ ከባድ ጥያቄዎችን በድፍረት የሚመልሱ ተጠያቂዎች ሲያደነቁ እሰማለሁ፡፡ ባታውቋት ነው እንጂ የኔ እናት ስንት «የሃርድ ቶክ» ጥያቄ በድፍረት መልሳለች መሰላችሁ፡፡ ያውም በቴሌቭዥን ሳይሆን በሕይወት፡፡ አባታ ችን የት ሄደ? ለሚለው የኛ የልጆቿ ጥያቄ ሁልጊዜ መልስ መስጠት አለባት፤ ለምን ሌላ ባል አታገቢም ? ለሚለው የዘመዶቿ ጥያቄ መልስ መስጠት አለባት፤ እንዴት እርሱ የለም ብለሽ እንዲህ እና እንዲያ ታደርጊያለሽ? ለሚለው የአባታችን ዘመዶች ጥያቄ መልስ መስጠት አለባት፤ በብቸኝነቷ ሊጠቀሙ ለሚፈልጉ ዘለሌዎች መልስ መስጠት አለባት፤ እንዲህ ለምን አታደርጊም እንዲያ ለምን አታደርጊም እያሉ ያለ ፍላጎቷ ሊያስኬዷት ለሚፈልጉ ጎረቤቶቿ እና ወዳጆቿ መልስ መስጠት አለባት፡፡ እና ይህች ጀግና አይደለችም ትላላችሁ፡፡ «ሀርድ ቶክ»ን ሳይሆን «ሀርድ ላይፍ»ን የተቋቋመች፡

እንዲያ ብቻዋን እየታገለች፡፡ አገር በሙሉ ድንኳን ተክሎ ለአባቴ ልቅሶ መቀመጡን እያወቀው፣ ጀግንነቷን ግን የሚያደንቅላት አልነበረም፡፡ ከፍ እያልኩ ስሄድ የሚያናድደኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ ሠርግ እና ተዝካር ስትጠራ በመጥሪያ ወረቀቱ ወይንም ካርዱ ላይ የአባቴ ስም ይጻፋል እንጂ የርሷ ስም አይጻፍም፡፡ እድር የምንከፍለው፣ የቤት ኪራይ የምንከፍለው፣ መብራት እና ውኃ የምንከፍለው በአባቴ ስም ነው፡፡ ለምን? እርሷኮ አባትም እናትም ሆና እየኖረች ነው፡፡

በሠፈራችን የአባቴ እና የእናቴ እድር የተለያየ ነው፡፡ የወንድ እድር እና የሴት እድር፡፡ አባቴ በሕይወት እያለ እርሷ ወደ ሴት እድር እርሱ ደግሞ ወደ ወንድ እድር ነበር የሚሄዱት፡፡ አሁን ግን አባትም እናትም ሆናለችና በሁለቱም እድር መገኘት ያለባት፤ መክፈል ያለባት እርሷው ናት፡፡ የሴት እድር በጓዳ ሥራ መጠመዱ የተለመደ ስለሆነ እዚያ ስትሄድ እርሷም ጓዳ ገብታ ትሠራለች፡፡ የሚገርመኝ ግን የወንድ እድርተኞች የመጀመርያ ቀን ድንኳን ተክለው ድንኳን ውስጥ ከብበው ካርታ ከመጫወት ውጭ አንዳችም ሥራ የላቸውም፡፡ እርሷ የወንድ እድር ክፍያዋን ብትከፍልም እንደ ወንድ እድርተኞች ድንኳን ውስጥ እንድትቀመጥ የሚፈቅድላት ግን የለም፡፡ ለክፍያው እና ለጥሪው ወንድ፣ ለሥራው ግን ሴት ናት፡፡

ማኅበረሰቡ ለጀግንነቷ ዕውቅና ላለመስጠት ያላደረገው ጥረት አልነበረም፡፡ በሴትነቷ የሚደርስባትን ጥቃት ሁሉ ችላ፤ አባትም እናትም ሆና ባሳደገች ልጆቿን «የሴት ልጅ» እያለ ይሳደባል፡፡ ለመሆኑ ግን የሴት ልጅ ያልሆነ ማን አለ፡፡ «የሴት ልጅ» ማለት ስድብ ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስስ ቢሆን፣ መጽሐፍ ቅዱሱም ቁርአኑም እንደሚሉት ያለ አባት ከእናት አይደለም እንዴ የተወለደው? «የሴት ልጅ» ማለት እንዴት ስድብ ይሆናል፡፡ ለመሆኑ የፈጣሪን ሥራ ተካፍላ የምትሠራ ሴት አይደለችም ወይ? ልጅን አርሞ እና ቀጥቶ ማሳደግ የሚችለው ወንድ ብቻ ነው ያለው ማነው?

እንዲያውም አንድ ጊዜ ታናሽ ወንድሜ ነገሩ ሁሉ አበሳጨውና «ያለ አባት ይህንን ሁሉ ለፍተሽ አሳድገሽ ለምንድን ነው በአንቺ ስም የማልጠራው? ይሄው ሰው ሁሉ የሠራውን ሕንፃ በስሙ እየሰየመ አይደለም? ታድያ አንቺ በአካልም፣ በዕውቀትም፣ በምግ ባርም አንፀሽ ያሳደግሺውን ልጅ በስምሽ ብትጠሪ ምን ነውር አለው? እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ የአባቴን ስም አስቀይራለሁ» ብሎ አስደንግጧት ነበር፡፡ የርሱን ሃሳብ ለማስ ቀየር በትኁት ሰብእና እንዴት እንደ ደከመች ትዝ ይለኛል፡፡ እርሷ ልፋቱን እና ውጤቱን እንጂ ስሙን እና ሽልማቱን መች ትፈልገዋለች፡፡

እኛን ለማሳደግ ለፋች፡፡ ቆይቶ ደግሞ ማደጋችንም ፈተና ሆነባት፡፡ ከሦስቱ ልጆቿ ሁለታችን ወንዶች ስለነበርን ብሔራዊ ውትድርናውን ትፈራው ነበር፡፡ «ምነው ሴት ብቻ በወለድኩ» ትላለች፡፡ በሴት ልጆች ላይ እንዲህ እና እንዲያ ዓይነት ጥቃት ደረሰ ስትባል ደግሞ፣ «እንኳንም ወንዶች ወለድኩ» ትላለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ አምጣ እንደ ወለደችን አምጣ መልሳ ብትውጠን ትወድድ ነበር፡፡ «ምናለ አምጬ እንደ ወለድኳችሁ አምጬ መዋጥ ብችል፤ ደኅና ዘመን ሲመጣ መልሼ እወልዳችሁ ነበር» ትለናለች፡፡

እኅቴ ሁልጊዜ አንድ ነገር ይቆጫታል፡፡ ሰው በእናቱ ማኅፀን የኖረበት ጊዜ ለምን ከእድ ሜው ጋር እንደማይቆጠር፡፡ እንደ እናት ማኅፀን ምቹ እና ሰላማዊ፣ ያለ ሃሳብ እና ያለ ሰቀቀን የተኖረበት የት አለ? ምርጫ፣ ቅርጫ፣ ክፍያ፣መዋጮ፣ተቆራጭ፣ ፖለቲካ፣ ፓርቲ፣ ፍርድ ቤት፣ፖሊስ ጣቢያ፣የሌለበት ልዩ ዓለም የታለ? ታድያ እንዲህ ያለው ሕይወት ከእድሜ ካልተቆጠረ ምኑ ሊቆጠር ነው ትል ነበር፡፡

ወርቋን ሽጣ ለልጆቿ ወርቅ የሆነ ሕይወት ከለገሰች እናት በተሻለ ጀግና ሆኖ ማን ወርቅ ይሸለማል? ወርቅንማ እንደ ወርቅ በእሳት ለተፈተነ ነው መስጠት፤ ምሳሌው ከአማናዊው ጋር ሲሠምር ደስ ያሰኛልኮ፡፡

ስለዚህም እርሷን ሸልሙልኝ፤ የእኔ ጀግና እርሷ ናት፡፡ ያለምንም በጀት፣ያለ ማንም አጋር ፣ ያለማንም አማካሪ፣ ያለ ምክር ቤት እና ካቢኔ፣ያለ ውጭ ርዳታ፣ ግብር ሳትሰበስብ ለሠለሳ ዓመታት ያህል ቤተሰቦቿን አባትም እናትም ሆና የመራች፤ ችግርን ተቋ ቁማ ታሪክ ያደረገች እናት፣ ፓርላማ ባለበት፣ካቢኔ በሚመክርበት፣ግብር ተሰብስቦ በጀት በሚመደብበት፣የውጭ ርዳታ በሚጨመርበት፣ አማካሪ በበዛበት ሥፍራ መምራት አትችልም የሚላት ማነው‼ የኔ ጀግና እርሷ ናት እርሷን ሸልሙልኝ፡፡

ባሎቻቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት አጥተው በብቸኛነት እና በጀግንነት ችግርን አሸንፈው፣ ልጆቻቸውን በማሳደግ ለወግ ለመዓርግ ላደረሱ እናቶች መታሰቢያ፡፡

77 comments:

 1. Wow nice one thanks.

  ReplyDelete
  Replies
  1. መቼም ዳንኤል ሳነበው ከእንባ ጋር ነው።
   ፈጣሪ ይሸልማት እንጂ፣ የደረሳችሁላት እናንተ ደግሞ ሸልሟት በተራችሁ አንቀባሯት በህይወት ካለችላችሁ
   ግዜ እንዳይቀድማችሁ ቅደሙት አስደስቷት በተራችሁ
   የእናትማ ዋጋዋ ብዙ ነው፣ ተመን የላትም
   ወልጄ አይቼዋለሁ ጭንቀቷን፣ እሷን ሆኜ አይቸዋለሁ

   Delete
 2. Happy Easter.
  This is not fictitious,I believe.The writing absolutely depicts a true story of Ethiopian mothers now and then.Yes, everyday heroines too deseve a hero's prize.I now see why your emblem is eagle.Thank you and keep it up!

  ReplyDelete
 3. ende werk besat tefetinew yewetu tenkara enat. ye Tsinat, ye tigist ena ye alama koratinet misale.
  wengelin benibab sayihon betegbar yeteregomu yehaymanot arbegna!!!!

  Fetari be mengistu abizito yishelimachew

  ReplyDelete
 4. I vote for her You are right

  ReplyDelete
 5. ይገርማል .........እኔ ኮ .....ዳ/ን ዳንኤል የኔን እናት ታውቃት ነበር እንዴ ...በጣም ይገርማል ልቤን ስልነካኝ ነው ...እንድህ ሁና ነበር ያሳደገችን የእኔ ጀግና እናት...ጣላ ....አረቄ .......ሺልጣ......ሸጧ......ያሳደገችን እግዚአር እድሜዋን ያርዝምልኝ .....ብላችሁ አስቡልኝ...የኔ ጀግና እርሷ ናት እርሷን ሸልሙልኝ .....ዲ.ዳንኤል ክብረትን ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን እያቀረብሁ አሁንም እግዚአብሔር ዕውቀቱን ያብዛልህ እላለሁ

  ሶል

  ReplyDelete
 6. ሠላም ለሁላችሁ ይሁን

  መናገር የምችለው ከተጠቀሰው ውጭ ያለ አይመስለኝ ለመሪነትም ሆነ ለማንኛውም ነገር ከቤት ነው የሚጀምረው ይህንን የቤት ሀላፊነት ደግሞ ከወንዶች ይልቅ እናቶቻችን እንደሚወጡ እናውቃለን ደግነትም ሲገለፅ በእናት መልክ ነው "እናት የሆነ ሰው እኮ ነው እየተባለ ነገር ግን ከተገለፀው ሀሳብ ውስጥ ብዙን ግዜ ሴት በወንድ ትጠራለች ይህ ደግሞ ከባህል፣ከሃይማኖት ጋር ባለ ነገር የተያያዘ ነው፡፡ አበው እንዳለሁት /እመት እንዳሉት/ ስለማይባል

  ለምሳሌ አበበች ጎበና፣ሜሪ ጆይ፣ቻቺ ታደሰ፣እማሆይ ሂሩተ፣........................................................................................................የዳንኤል ክብረት እናት፣የኔ እናት....................................................................................................................

  ReplyDelete
 7. ዳኒ አንተ 1000 መን ነበረብህ .... ገግነ ምንታረዋለህ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ቀድህ መጣህና ትወውልዱ ላዉህ አለ ደገመ ይህ ፅኁፍ የኔ እናት ታሪክ ነው አመሰግሁ።

  ReplyDelete
 8. Tesfa


  That is exactly my story,the difference is we lost our dad in natural death.just like you we were three, two boys and and sister.yes ethiopian mothers suffer a lot for their kids.

  ReplyDelete
 9. አምደ ማርያምApril 6, 2010 at 1:14 AM

  ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
  Dear Dn denial
  It is really teaching .it remind me my own family.
  Good job keep up.

  Happy eastern መልካም በአል ይሁንልህ.

  ReplyDelete
 10. ኪዳነማርያም
  ዳኒ
  ዛሬ በአንተ ጽሁፍ እናቴን አየሁዋት በእውነት ለካ ጀግና ናች።ታድያ ዛሬ ደርሼ ምን ላድርግልሽ ስላት ምን እንደምትል ታውቃለህ? ”ያ ምስኪን ይህንን አለምና ደስታችሁን ቀና ብሎ ማየት ቢችል” ትላለች ዛሬም ስለአባታችን ይቆጫታል።ታድያ ከእርሱዋ ሌላ ማን ጀግና ይኑር በእውነት? በፍቅር ጀግና በእምነት ጀግና በመከራ ጀግና ……..በምን አልጀገነችም ልበል? ሁሌ በውስጤ ይብሰለሰል ነበር ዛሬ በአንተ ብዕር አደባባይ ወጣ ዛሬም የእርስዋ ጀግንንት ጉልበት ሆኖኝ አጦራት ዘንድ እተጋለሁ።
  እግዚአብሄር ይስጥህ፤ጸጋውን ያብዛልህ!

  ReplyDelete
 11. ኪዳነማርያም
  ዳኒ
  ዛሬ በአንተ ጽሁፍ እናቴን አየሁዋት በእውነት ለካ ጀግና ናች።ታድያ ዛሬ ደርሼ ምን ላድርግልሽ ስላት ምን እንደምትል ታውቃለህ? ”ያ ምስኪን ይህንን አለምና ደስታችሁን ቀና ብሎ ማየት ቢችል” ትላለች ዛሬም ስለአባታችን ይቆጫታል።ታድያ ከእርሱዋ ሌላ ማን ጀግና ይኑር በእውነት? በፍቅር ጀግና በእምነት ጀግና በመከራ ጀግና ……..በምን አልጀገነችም ልበል? ሁሌ በውስጤ ይብሰለሰል ነበር ዛሬ በአንተ ብዕር አደባባይ ወጣ ዛሬም የእርስዋ ጀግንንት ጉልበት ሆኖኝ አጦራት ዘንድ እተጋለሁ።
  እግዚአብሄር ይስጥህ፤ጸጋውን ያብዛልህ!

  ReplyDelete
 12. Dertogadawa enate
  ገና ምን ተነግሮ የእናት ውለታ የብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶች ታሪክ ነው ያጤንክልን፡፡ የእኔ እናት ዘመዶች ሁሉ ይመሰክሩላታል የሴት ወንድ ሆና ነው ያሳደገችኝ ምክንያቱም ታዋቂው የቲያትር ባለሙያ አባቴ ኢሃዲግ ሲገባ በተኛበት ምን እንደነካው ሳይታወቅ ተኝቶ ቀረ፡፡ከዚያም ወደ አዲስ ሰፈር ወደ አዲስ ቦታ ገባን እናቴ ታዲያ የቤት እመቤት ነበረች የማታውቀውን አለም ከእግዚአብሔር ጋር ተመካክራ ተደባለቀችው፡፡እንጀራ ሸጠች ፤ጎመን ሸጠች፤የጽዳት ሰራተኛ ሆነች፤ትምህርቷን እንደምንም ጨረሰች፤ያልተሞከረ ነገር የለም ነገር ግን ያምሆኖ ሁለት ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆቿን ማሳደግ ከባድ ነበር፡፡ጾም ማደር የተለመደ ነበር ፡፡ አሁን ሳስበው ከሁሉ በላይ የሚያበሳጨኝ ለራሱም ይሻሻላል እኔንም ይረዳኛል ብላ ያገባችው ሰው ከእርሷ አልፎ ቤቱን በጠበጠው እኛ እምንበላው እያጣን እርሱ መጠጥ ጠግቦ መጥቶ ቤት ይደበድባል እግዚአብሔር ከሰጠን መልካም እንቅልፍ ይነሳናል፡፡ብቻ ሁሉም አለፈ እና ዛሬ በመልካም ሁኔታ ላይ እኩዮቿ የሆኑ ልጆቿን ለማድረስ በቃች ባል ተብዬው ግን እስከ አሁን የቤቱ ፈተና ሆኖ ቀረ፡፡የማይረሳኝ ነገር ታዲያ ስናጠፋ ትገርፈንና አስቀምጣ እንዴት ሆና እንደምታሳድገን እያለቀሰች ትነገረን ነበር ከዚያ አብሮ መላቀስ ነበር፡፡ አሁን እኔ እያደኩኝ ስመጣ የእናት ፍቅር እየጨመረ መጣብኝ እምመኘው ነገር ቢኖር በቻልኩት ነገር እናቴን ማስደሰት ነው ይህን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር አደርገዋለሁ ምክንያቱም አላቅማም አላፈገፍግም ለእናቴ ለውጥ፡፡
  ያሁን ዘምን እናቶች ያስቸገራቸው ድሎት ነው አጉል መብት ተብዬውም ሳይበዛ አልቀረም ሌላው ቀርቶ ልጅ እንዴት እንደሚያዝ እንኳን አታውቅም መንገድ ላይ እንደ አመት በአል በግ እየጎተተችው መሄድ ነው፡፡ሲያለቅስ ደግሞ መቀጥቀጥ ነው፡፡ስነምግባር ማስተማር ለአሁን እናት ልጅን ማጨናነቅ ሆኗል ፡መንከባከብ ማለት ደግሞ ብር መስጠት ሞባይል መስጠት በቃ ማምነሽነሽ ሆኗል እንደው ምኑ ቅጡ ልብ ይስጥልን ነው የሚባለው፡፡የትክክለኛ እናቶች በረከት ይድረሳቸው ለሴቶቻቸን፡፡

  ታዲያ ዲ/ን ዳንኤል የጻፋት እናት እና የእኔናት ዴርቶጋዳ አይደሉም ወይ ? የትኛውም መከራ ሳይሰቃት ልጆቿን ለመመገብ ወደኋላ ሳትል ሳታቅማማ ልጆቿን ለመለወጥ መከራን የዘመረች እናት ናት ፡፡ይሄ ነው ለእኔ ዴርቶጋዳ ማለት፡፡
  እናመሰግንሃልን ወንድማችን we never hesitate

  ReplyDelete
 13. i am really impressed,cried ,since it reminds me my mom. she is strong more the the expressed one and it was for my self and for my brother.
  she suffered , but she got what she want thanks to God .

  thanks Dani, nice View .

  ReplyDelete
 14. Dear Dani, Yes you provoked all of our life background and those hidden stories behind our appearance today. Who is not sensitively touched by such life experience. Realy you scanned all of our livelihood virtually and found the real image of us.

  What can I say; May God exeedingly bless you with His abundat wisdom again and again. Yes let me vote for my mother although I am not yet blessed to help her even at my old age.

  ReplyDelete
 15. በመጀምሪያ ዳኒ እንክዋን ለብርሀነ ትንሳኤው ብሰላም አደረሰህ::
  ያንተ ጀግና ከ እኔዋ ጀግና ጋር አንድ አይነት ናት ግን አንተ በሚያምር መልኩ ግልጽ አድርገህ አስቀምጥከው እግዚአብሄር ይባርክህ::ደሞ እኮ የ ሴት ልጅ በመሆኔ በጣሙን ነው የምኮራው::

  ReplyDelete
 16. The selection need not only to depend on sex. There are also fathers who experience such ups and down

  ReplyDelete
 17. Dear Daniel:

  Min libelih bicha enatochachinin endemestewat silasayehen egzier yistih elalehu. Hud yifjew biye kuchi sil, ante be bi'er ametahewu. Ahunim le Enatochachin rejim edimen tena yistilin amen!

  ReplyDelete
 18. Egziabher Tsegawun Yabezaleh Dani!

  Yes, that is what an Ethiopian mother is. By the way, there are few fathers who play the role of mother as well.

  I think the reason we don't count our womb life is not to mix with the 'peace-less' life we are living in this world. Thank you again! Berta yeGna neser!

  ReplyDelete
 19. ታሪካቸው ያልተነገረ እጅግ ብዙ ጀግና ሴቶችን ሁሉ የሚወክል ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ እናቴን ነው በልጅነቴ ያጣሁት፡፡ አባቴ የእናት ልብ ነበረው፡፡ እንደ እናትም ሆኖ አሳደገን፡፡ የኔ ስጋት እኔ የአባቴን ያህል ፍቅር ለሚስቴና ለልጆቼ ይኖረኝ ይሆን የሚል ነው፡፡ ሁላችንም በህይወታችን የምናወቃቸው ጀግኖች አሉ አልዘከርናቸው ሆኖ ነው እንጂ

  ReplyDelete
 20. Dear Danie

  Your story describes the lives of 75% of Ethiopian mothers. Even in the presence of the father figure this is how they live their lives.

  ReplyDelete
 21. ዳኒ
  ስለ እናትነት ጀግና የጻፍከው ጽሁፍ እጅጉን በጣም ጥሩ ነገር ነው!!! ይሁንና ሰዎች እራሳቸው ባመጡት ጣጣ ወደቁና እንደገናም እግዚ. ከወደቁበት አስነሳቸው ይህ ሁሉ ግን ስጋዊ (ምድራዊ) ነገር ነው። መንፈሳዊ አባት ስለሆንክ ስጋዊውን አውርተህ ማቆም የለብህም!! እኔም እስቲ ስለዚያች ምስጊን በግብጽ በረሃ ስለተንከራተተችው እናቴ ትንሽ ልበል። ገና በህጻንነቷ መድሃኒቴ የሆነውን ህጻን(ኢየሱስን) ተሸክማ በበረሃ የተንከራተተችው ብርዱና ቁሩእየተፈራረቀባት የተሰቃየችው፡ ያም ሁሉ አልበቃ ብሎ ልጇ ኢየሱስ የእኔን በደል ተሸክሞ እንደዚያ በመስቀል ላይ ሲንገላታ፣ ተጠማሁ ሲል እንኳ አጥብታ ያሳደገችው እናቱ ውሃ እንዳትሰጠው በጦርና በሰይፍ እያስፈራሩዋት ስንቱን ችግር አለፈችው። ክብር ለጌታ ይሁንና እነሆ ስቃይዋን ተመለከተና የክብር ባለቤት አደረጋት። ታዲያ ሰዎች ይህ ሁሉ ፍቅር አልገባቸው አለና አሁንም ሊያንገላቱዋት ይሞክራሉ። ይገርማል!!!! የ እርሷን ፍቅር ቢረሱ እንኳ የልጁዋን ፍቅር እንዴት ሊረሱ ይችላሉ? ስለሃጢያታቸው በተገረፈ፣ በተሰቀለና በሞተ! በማያዳግም ሁኔታ የሃጢያትን ደሞዝ ሙሉዉን ክፍያ በከፈለ! ምን አጠፋና? ለመሆኑ ይህን ላደረገ ብቻውን ቢመለክና ቢዘመርለት የት ላይ ነው ጥፋቱ? እናቴ ያን ሁሉ ዘመን ( 33 ዓመት) አብራው ስትኖር ያሳለፈችው ዘመን የሃዘን ዘመን ነበር አንድ ቀን ሰለቸኝ ደከመኝ ሳትል አንድ ቀን መንገድ ላይ ቢቀርባት እንኳ እንዴት እየተንቦጀቦጀች እንደፈለገችው የሚያውቅ ያውቀዋል። ስለዚህ ከዚች እናት ብዙ መማር እንችላለን ለማለት ያህል ነው። በተረፈ ዲ. ዳኒ እንደመንፈሳዊ አባትነትህ ምሳሌዎችህን ለወንጌል ብታዉላቸው የበለጠ መልካም የሚሆን ይመስለኛል!!!!
  ewnet

  ReplyDelete
 22. Dani,

  Touching story. I felt that you wrote my story. Moms deserve the best. Every one of us has a lot to say about our moms. They went through trials and tribulations to raise us.

  ReplyDelete
 23. Dn.Daniel you know what i think?
  we dont need to have one daniel we need millions like u........Tsegawun yabzalih

  ReplyDelete
 24. 10Q dani!! I need alot of daniels for our country and the world.Are u preparing some one who will replace u? Tsihufun befit addis neger lay anbibewalew.Gazetawim alegn.Gin degime ahun sayew betam wiste teneka.Sile inate endasib aderekegn.Ay yante neger bekininet silemitisera yisakalihal. EGZIABHER kante gar yihun!! KANTE BEHUWALA YEMINES DANIEL GIN LEZIHICH ALEM AZEGAJILIN YEMILEW TILIKU MASASEBIYAYE NEW!!!

  ReplyDelete
 25. My brother @ Dertogada, I doubt if this is Yismaeke- the author of the famous book. Your comment about the mothers of this generation is not really fair. Hulum beyezemenu endeye chilotaw yifetenal. The challenge of this generation especially those educated women is not money, but time and people. We still suffer to take care of our children though we are educated and working. Dn Daniel's Aricle in AN " Mist negn mist efeligalehu" could explain the challenge of this Generation.

  I support this topic that those widowers during the fashist Dergue are really Heroes. But at least those husbands are killed so they expect no support. But in this generation, the problems are not the same- the husbands are alive but are not lucky enough to take care of the kids. Those poor mothers didn't teach them to support their wives, as they used to take all the burdens. So they expect their wives to suffer as their mothers did. But for me "ye enatin wileta mekfel yemichalew, balefechiw enat sayhon, be addisua enat be hiywot balechiw ena bemitmetawa enat new". Yageba bemistu, yalageba be guadegnochu ena be ehitochu mekfel yichilal. Because enat min gizem enat nat- zetegn wer sataregiz yemitiweld enat yelechim, bemitim hone be CS satisekay lij ye mitagegn enat yelechim, be lijua edget yematichenek enat yelechim. As you said in your comment lij endet endemiyaz yematawik enat yelechim. lijiwan meketat yemitiwed enat yelechim- yishashalilign yihonal bila kemaseb wichi . I would like to tell you my own experience here. once I bit my son for his repeated mistakes. But while he was crying, I went into my bed room and cried.

  Sorry, to be long but to summarize, we shouldn't necessarily blame the the current generation to emphasize the past. Zemenun wajut yilal metsihafu. kefetena yawitan.

  T/D Mother of three age 33 (MA)

  ReplyDelete
 26. አባግንባርApril 7, 2010 at 3:27 PM

  ቅኔ አልቀኝላት አልታደልኩምና
  መወድስም የለኝ እሷን የሚያጽናና
  ምህሌትም አልቆም እኩለ ቀን ነዉና
  እናንተው መርቁልኝ ዘላለም ያኑርሽ በሉና
  እናቴን መርቁልኝ ዕድሜ ይስጥሽ በሉና፡፡

  ReplyDelete
 27. she is ma mom too thank u d/n daniel. great view ; the apostel st. paulos says " be menfese yemezera be huletume yachedal ; be segam be nefsem" LONG LIVE TO MAM!!!!!

  ReplyDelete
 28. እጅግ በጣም ጥሩ ትውስታ ማንነትን ያስታወሰ የእናት ወለታዋን ለማዘከር የረዳኝ ቆም ብዬ የትላንቱን ማንነቴን ያስቃኝኝ በመሆኑ
  እጅጉን የአሰደስተኝ የአሰለቅሰኝ እና የአሳዘነኝ ውሳጣዊ እኔነቴን የበረበረኝ የብዙኃንን ኢትዮዽያውያን እናቶች ታሪክን የሚያወሳ
  በመሆኑ በርካታ ጀግናዎች ያሉባት ግን ውለታቸው የተረሳባቸውን
  የህይወትን አርድ ቶክ አሸንፈው እንደሰም ቀልጠው እንደ ሻማ ነድደው ያለፉ የታሪክ ጀግኖች መኖራቸውን ወለል አድርጌ እንዳያቸው
  አደርጎኛል ።
  ዲ.ዳንኤል እግዚአብሔር ይጠብቅህ

  ReplyDelete
 29. dani these great thank you

  ReplyDelete
 30. yes dani that is my mom,i was tearing while i was reading the article,thank you again and yes we should aknowledge them all ethiopian mothers as a hero and may GOD bless them again and again.

  ReplyDelete
 31. 10Q Dani...good view.its not only you but many of us have almost similar background.the bad thing is, we couldn't stop it and it is still expanding day to day.lets we stand to make it history....

  ReplyDelete
 32. That mom has already received the Prize. The genuine apprecuation of her son. And by telling her story, you have brought her to immortality.

  ReplyDelete
 33. deep view dani keep it up

  ReplyDelete
 34. Ye-ahune zemene Enatoche, we have to learn a lot from our mothers.

  ReplyDelete
 35. I dont have words but u touch my heart God bless u.

  ReplyDelete
 36. Thank you Dn. Daniel. You told everybody about my mom.

  ReplyDelete
 37. Dani, u only post what u like? I said this is where u belong. Not church ...

  ReplyDelete
 38. After that reading, I do not know what I am thinking and even what to think!!! One thing I know for sure is that they remain our hero's forever!!! For me they are too big for CNN hero!!! Most CNN winners so far gave up their money or their passion or pleasure for something they believed in, which is still excellent. But our mothers, they gave up their life for their kids!!! May be we should organize another big event to honor them!!!!

  ReplyDelete
 39. dani.......no words to say....just God be with u and ur family!!!

  ReplyDelete
 40. D/n Daniel,
  Endemin aleh?
  Bizu wedimochena ehitoche kelay endebarekuh...egziyabher tsegawin yabzalih...
  I have read this same article on Addis Neger during their good old days and surprisingly I read it today with the same passion.
  Thank you!

  ReplyDelete
 41. @ewnet,
  Your perspective of looking the article is very genius and you related it to our Holly mother St.Mary. Hmmmm...

  ReplyDelete
 42. I couldn't say more... It is all said...
  Truelly it is the story of my Mom... And it is well presented YENE JEGENAWA ESUA NAT.
  Dn. Daniel I can't say thank You enough!!!!

  Thank U very much.

  ReplyDelete
 43. O dani I read this more than 10 times from Addis Neger I apprciat it . this is almost all Ethiopians Mather Life . I like it very well 10Q God Help you !! I expect more from you

  ReplyDelete
 44. It is interesting really i don't know how can i tell my felling to.....wow!keep it up! no word may God bless and save you.

  ReplyDelete
 45. be sewech zend yematitaseb negergin beEgziabihere bicha yemtitawek yejegnoch jegna-- ur mothers!!!!  Desta

  ReplyDelete
 46. awo yene jegenawa Esu nech, Emeyeee Enate, Many thanks dani for posting this touching story.

  May God Bless u and your family.

  ReplyDelete
 47. dn daniel,
  i'm so impressed by the story, its a real life among many mothers of ours they deserve great award, but above all to give them credit for what they did. and i'm happy to get your articles on the internet we missed you so much after what happened to addis neger, but i suggest you to collect and publish them all in book.
  God be with you!!!

  ReplyDelete
 48. Really it is very nice,you raised the forgotten issue.
  Thanks Dani!!
  God bless you!

  ReplyDelete
 49. Even if they leave together , even if she don't go out to sale enjera, ..., even if her houe covered everything......, even if her cloth covered all her inside, ...,even if her hasband is a doctor(rich)...I can say all enat passed this way...bse she is the carrier of the house , bse she is responisble for all the hard jobs and responsiblities..., bse she take care of 5+ kids,.... I cry cry cry when I read this article, i was working but can't stop my self...that is the life of Ethiopian mother.

  When i use to go to entoto to relax myself.... i always sob for the ladies who carry very long wood( & cheraro) and go dowen to shero meda.. ዳገት ወታ እንጨት ለቅማ ተሸክማ ቍልቁለት ወርዳ ቤት ስትደርስ እንጀራ ጋግራ እርሱን ሸጣ ባገኘችው ብር ዘይት ሽንኩርት ገዝታ ወጥ ሰርታ አብልታ u can guess how the day pass and next day will be the same.....My God ...Can say nothing more.

  ReplyDelete
 50. aslekeskegn D/n Daniel

  ReplyDelete
 51. Awwwww no words to express luv it.....great keep on God bless u

  ReplyDelete
 52. Eh ... .. . your message touched me since i am a mother i am satisfied. This is the only answer for those they thought they are 'nigus' in the home (some husbands and fathers).

  ReplyDelete
 53. wow!!! keep it up Dani!

  ReplyDelete
 54. I lack words to appreciate this article. what i can only say is God bless U.

  ReplyDelete
 55. entune la emiwd sayhone ya emital enkan yahne banib yrasun ent ygagtal.
  ka balu ga abra ya mitnor enat gagina endamithn aycalew

  ReplyDelete
 56. Dani, do you know my mother relly? While reading this, I was drawing mental images about my Mother and our past life. Please Dani, post here also your writings that are printed in "Addis Neger" News Paper. You are relly true and sensible men.
  Let the Love of our Lord Jesus christ be with you!

  ReplyDelete
 57. Dn. Daniel
  What you said happened

  http://abcnews.go.com/GMA/Recipes/inspiring-housekeeper-wins-emerils-mothers-day-breakfast-bed/story?id=10579164

  ReplyDelete
 58. medi said
  Thanks Dani your message touched me since i am a mother i am satisfied because i was suffering a lot yes i am jegna with the help of God.
  let Saint Mary & her son Jesus Christs with you

  ReplyDelete
 59. The structure of the history resembles with my mother's. It is true; no one can be brave as a mother who struggled and won life for her children.

  ReplyDelete
 60. amazing looking Dani.

  ReplyDelete
 61. ዳኒ አመሰግናለሁ!!!! ድንቅ እይታ!
  ‹‹ለእናቶቻችን ፍጣሪ እድሜ ይስጣቸው››
  እናቴ ስለሁሉም ነገረ አመሰግንሻለሁ
  ‹‹ፈጣሪ ብድር መላሽ ያርገኝ››
  መላኩ ከአዲስ አበባ
  ለእናቴ ወርቅነሽ ገመቹ
  አዲስ አበባ

  ReplyDelete
 62. No words! I better keep silent!! but one thing ur mom already got her prize " u are better than a Gold" i am not comparing a man with matrial..but i am pretty sure ur mom already achived!!
  Shimels E.

  ReplyDelete
 63. እኔ ደግሞ ያነበብኩት ከተጻፈ ከአንድ አመት በኋላ ቢሆንም እንኳን አሁን ሳነበው በጣም ስለዎደድኩት ከአባትም በላይ ሆና እነ ስርጉተ ስላሴን እነ አማኑኤልን…በስነ ስረአት ማሳደግ ለቻለችው ሶስና (የኔ ጀግና) ማስታወሻ ትኁንልኝ እላለሁ፡፡ ስለጻፍከው አመሰግንሃለሁ ዳኒየ፡፡

  ReplyDelete
 64. yeni jegena ABATE new.enatem abatem hono yasdegegne.Dn Danie eni gen lezih jegena yekfelkut neger yelem.lelaw biqer eni sew hogne enkuwa berase qomi alsayehutem.zarem yeni neger yaslqesewal.enim libe dem eyneba enoralehu.min laderg????

  ReplyDelete
 65. Awesome Dany. You really reflected the true life of most mothers in Ethiopia. For me, the prize for these women is not from CNN but when their children start to recognize and feel their scarification as you write it. You know - you are more than gold medal for your mom.

  ReplyDelete
 66. This is my own story. It is touching. I felt like there is nothing which i can do to pay back my mom. she is the best gift for me from God. I was crying a lot and was so nervous about her deeds on my graduation day you know what she said "That is my duty". She thinks it is her duty to live for me. She thinks it is her duty to do beyond her capacity for me.

  ReplyDelete
 67. በጣም የሚገርም ነው። ለኔ አባቴ ሁሉም ነገሬ ነው ለኑሮው ለልጆቹ ያልከፈለው ነገር የለም። ሁሉም በዚች ምድር ማድረግ የሚገባውን ሁሉ ከፍሎ ነው የእኔ አባት 9 ልጆችን አሳድጎ ዛሬ ሁላችንም በመልካም ስራ ላይ እነገኛለን። እግዚአብር ይመስገን እሱም እድሜ ሰጥቶት በ80ዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኛል። በዚህ ወስጥ ግን ያላትን ገቢ አስቤዛ አቻችላ ሳትሰለች የምትኖር እኔ ከምለው በላይ አንተ የገለፅከውን መከራ ችላ ሴት በመሆኗ እናት በመሆኗ ትልቅ ዋጋ ሰጥታ ከፍተኛውን ጫና ችላ ያሰደገችኝ እኔቴ ደግሞ የእውነት ጀግና መሆኗን ያአንተን ጽሁም ሳነብ ማመሳሰል ወደድኩ። የእወነት ጀግና ናት በተለይ በሽታን ተቋቁማ ስላልከው የእኔዋ ጀግና እናት ደግሞ ለአመታት አብሮአት የኖረውን የአስም በሽታ ለምዳው እንደበሽታ አትቆጥረውመ ቸሩ መደሃኒአለም ያውቃል እያለች እያሳለች ትሰራለች ታማ ተኝታም አምጡት እዚህ ሁኜ ልስራው ትላለች እንዳልከው። ".. ለሥራ ያልደረስን ለመብል ያላነስን ሕፃናት " ሆነንባት። ዛሬ ደግሞ ወጉ ደርሶኝ የራሴን ስራ እንኳን ይዜ ገቢ ፈጥሬ እንዳለክውም የውጭ አርዳታም ጨ-ምሬ ጫናው ዞሮ ዞሮ ሴት ላይ ነው የእውነት የሴት ልጅን ጫና የእናትን መከራና ስቃይ ነው የገለፅከውና በጣም አመስግናለሁ።

  እንኳንስ የገቢ ምንጭ የሆነው አባት ሞቶ አሟሟቱ አላምር ብሎ ሌላ ስቃይ ተጨሮበት ልጅን ያለመንም ገቢ ሳትሰለች ሳትጨነቅ ማሳደግ ጀግና የሚለው ቃል የሚያንሳት ይመስለኛል። ይህን መከራ ችለው ላሳደጉን እናቶች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።
  እግዜር ይስጥልን ላንተም እራሳችን እናቶቻችን አባቶቻችን ቤታችን አካባቢያችን እንድናይ ስላደረግከን።

  ReplyDelete
 68. የኔ ጀግና ደግሞ ካንተ እናት የተለየች ናት። የኔጀግና እህቴ ፣ናት ዕናትም ኣባትም ወንድምምዕህትም ናት።

  ReplyDelete
 69. ዳኒ ቆይ ግን ምን አይነት እይታ ነው ያለህ በጣም ይገርማል

  ReplyDelete
 70. well done dani. The article is matched with my mom story

  ReplyDelete