አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የዶክትሬት ዲግሪዋን ጥናት ከምትሠራ አንዲት የውጭ ሀገር ተማሪ ጋር ተገናኘን፡፡ ጥናትዋን የምትሠራው በጎንደር ዘመን በተሳሉ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች ላይ ነበር፡፡ ለመገናኘታችን ምክንያት የሆነውም በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳንድ መረጃዎችን እንድሰጣት ፈልጋ ነው፡፡
ወደ እኔ የጠቆሟት ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን እንደምጽፍ ነግረዋት ነበር፡፡ ምን ያህል መጻሕፍት እና መጣጥፎች እንደ ጻፍኩ ጠይቃኝ ነገርኳት፡፡ ካዳመጠችኝ በኋላ ገርሟት የተናገረቸውን ግን እስከ መቼውም አልረሳውም፡፡ «እነዚህን ሁሉ ጽፈህ ግን የሚያነብብ ታገኛለህ?» አለችኝ፡፡ የግራም የቀኝም መመለስ ቸግሮኝ ዝም አልኩ፡፡ «ይቅርታ ወደዚህ ሀገር ስመጣ ጥሩ ያልሆነ ነገር ስለሰማሁ ነው» ብላ አስተያየቴን በሚጠብቅ መልኩ አየችኝ፡፡ «ምን ሰማሽ?» አልኩ ድክም ባለ ድምፅ፡፡ በውስጤ ግን «ምን ሰማሽ ደግሞ» ነበር ያልኳት፡፡