Wednesday, March 31, 2010

ገድለ ዜና ማርቆስ የያዛቸው መረጃዎችና ሁነቶች


ይህ ጽሑፍ በ2001 ዓም የኢትዮጵያ ፊሎሎጂ ማኅበር ባዘጋጀው 3ኛ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው፡፡


መግቢያ

በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ከ200 በላይ ገድላትን እስከ አሁን ለማየት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ የገድላቱ አጻጻፍ ተመሳሳይ የሆነ «ቅርጽ» /format/ እና ተመሳሳይ የሆነ «ፍሰት» /Flow/ የሚከተሉ ሆነው አግኝቻቸው ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ «ቅርጽ» የምለው የገድሉ ባለቤት ታሪክ፣ ገድል፣ ቃል ኪዳን፣ ተአምር እና መልክዕ የሚጻፍበት መንገድ ማለቴ ነው፡፡ በአብዛኞቹ ገድሎች መጀመሪያ የሃይማኖት መሠረት የሚሆነው ምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ሥጋዌ በመግቢያነት ይቀርባል፡፡ ከዚያም የቅዱሱ ትውልድ ይገለጣል፤ ቀጥሎም ገድሉ ይከተላል፤ ከዚያም የተሰጠው ቃል ኪዳን ይጻፋል፤ በመጨረሻም ተአምሩ እና መልክዑ ይቀርባል፡፡

«ፍሰት» የምለው ደግሞ የታሪኩ ቅደም ተከተል የቀረበበትን መንገድ ነው፡፡ ታሪኩ ከየት ተነሥቶ፣ በየት በኩል አልፎ፣ የት ይደርሳል የሚለው ነው፡፡ በብዙዎቹ ገድሎቻችን ከቅዱሱ ወላጆች ይጀምርና አወላለዱን ከገለጠልን በኋላ የአካባቢያዊ እና የትምህርታዊ ዕድገቱን፤ ገዳማዊ ሕይወቱን፣ የተቀበለውን መከራ፤ ዕለተ ዕረፍቱን ነው የሚተርክልን፡፡

የገድለ ዜና ማርቆስ አቀራረብ ግን ከዚህ ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ በመሆኑ ስለ ገድላት ያለንን ዕውቀት የሚያሳድግ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ መረጃም የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ገድሉን ለማንበብ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕድል ያገኘሁት የዛሬ ስድስት ዓመት በደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ገዳም ከሚገኘው ዕቃ ቤት ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ ጊዜ ለረዥም ሰዓታት ማንበብ እና ከሌሎች ነገሮች ጋር ለማዛመድ የቦታው ሁኔታ አላመቸኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ማይክሮ ፊልም ማኑስክሪፕትስ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውን የማይክሮ ፊልም ቅጅ ለማንበብም በወቅቱ የማተሚያ መሣሪያው በመበላሸቱ በመብራት ረዥም ሰዓት ማጥናት አልተቻለም ፡፡ በዚህ መካከል ግን ገድለ ዜና ማርቆስን ገዳሙ አሳተመው፡፡ በመሆኑም ተረጋግቶ ለማጥናት ዕድል ተገኘ፡፡

ገድለ ዜና ማርቆስ ከብዙዎቹ ገድሎች የሚለይባቸው ነጥቦችን በዝርዝር ማየቱ ገድሉ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በመረጃ እና በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ያለውን ቦታ ያመለ ክታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ገድላት ያለ ጥልቅ ጥናት ከመተቸትና ታሪክ የማይሽረው ስሕተት ከመሥራትም ያድናል በማለት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የመጽሐፉ ጸሐፍት

ገድለ ዜና ማርቆስ ስለገድሉ ጸሐፍት ከሌሎቹ ገድሎች በተሻለ ዝርዝር መረጃ ይለግሠናል፡፡ በብዙዎቹ ገድሎች ጸሐፊው አንድ ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ በገድለ ክርስቶስ ሠምራ «ለዛቲ መጽሐፍ ጸሐፍክዋ አነ ፊልጶስ ወልዱ ለተክለ ሃይማኖት ዘብሔረ ሸዋ በመዋዕለ ንጉሥነ ዳዊት ዳግማዊ፡፡ ጸሐፍክዋ አነ እንዘ ትነግረኒ ለልይ ከመ ይትናገሩ ቅዱሳን ሶበ በጽሐ ጊዜ ዕረፍቶሙ» ይላል፡፡ በዚህም እጨጌ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ጊዜ ዕረፍቷ በደረሰ ጊዜ እየነገረችኝ ጻፍኩት ይለናል፡፡ በገድለ አባ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን ደግሞ «አነሂ ጸሐፍኩ ለክሙ ዘሰማዕኩ በእዝንየ እምነ ደቂቁ ምእመናን ወቦ ዘርኢኩ በአዕይንትየ መንክራት ዘገብረ እስመ አነ ልህቁ ታኅተ እገሪሁ»፤ ሃይማኖተኛ የሆኑ ልጆቹ ሲናገሩ በጆሮዬ የሰማሁትን፤ እኔም ከእግሩ ሥር የያደግኩ ነኝና በዐይኔ ያየሁትን ድንቅ ሥራውን ጻፍኩላችሁ» ይላል፡፡ በገድለ ዜና ማርቆስ ግን የገድሉ ጸሐፍት ብዙ ናቸው፡፡

ሀ. የመጀመሪያዎቹ ጸሐፍት

በመቅድሙ አንቀጽ 1 ላይ እንደ ተገለጠው ገድሉን መጀመሪያ የጻፉት አባ አካለ ክርስቶስ፣ አባ ዮሴፍ እና አባ ገብረ መስቀል የተባሉ የአቡነ ዜና ማርቆስ ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡ ገድሉ የሚገልጥልን የጸሐፍቱን ስም ብቻ አይደለም፡፡ ከየት ከየት እንደ መጡም ይገልጥልናል፡፡ አባ ዮሴፍ ከየሐ ላሊበላ፣ አባ አካለ ክርስቶስ ከተከዜ በረሃ፣ አባ ገብረ መስቀል ደግሞ ከገዳመ ዘጌ /ገጽ 78/ የመጡ አበው ናቸው፡፡ እነዚህ አበው የአቡነ ዜና ማርቆስን ዝና ሰምተው በትሩፋታቸው ተማርከው የተከተሏቸው ደቀ መዛሙርት ናቸው፡፡

ለ. ሁለተኛው ጸሐፊ

የደብረ ብሥራት አበምኔት በነበረው በአባ ገብረ ክርስቶስ ዘመን ገድሉ እንደ ገና ተጽፏል፡፡ ያም የሆነው በገዳሙ ከሚገኘው የአቡነ ዜና ማርቆስ መቃብር አፈር ተቀብቶ የታወረ ዓይኑን ባዳነውና በኋላም ፈጣን ጸሐፊ በሆነው በጸሐፌ መንክራት ዮሐንስ አማካኝነት ነው፡፡ /ገጽ. 192/፡፡

ሐ. ሦስተኛው ጸሐፊ

ከአባ ገብረ ክርስቶስ ጋር በመሆን አባ ገብረ መርዓዊ የተባሉት አባት ከዕረፍቱ በኋላ በመቃብሩ ላይ የተደረገውን ጽፈዋል፡፡

መ. አራተኛው ጸሐፊ

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት /1391-1460 ዓ.ም/ የአቡነ ዜና ማርቆስ ዐጽም ሲፈልስ የሆነውን ታሪክ ደግሞ አባ ዮሐንስ የተባለው አባት ጽፎ አስቀድሞ ከተጻፈው ከገድሉ መጽሐፍ እንዲካተት አድርጓል፡፡ /ገጽ. 144/፡፡

ሠ. አምስተኛው ጸሐፊ

በተለይ አቡነ ዜና ማርቆስ በሕይወት እያሉ ያደረጓቸውን ተአምራት አሰባስበው የጻፏቸው አባ ገብረ መስቀል፣ አባ እንድርያስ፣ አባ ገብረ ሚካኤል የተባሉ አበው መሆናቸውን ገድሉ ይተርክልናል /ገጽ. 272-273/፡፡

ረ. ስድስተኛው ጸሐፊ

በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ የገዳሙ አበምኔት የነበረው አባ ቃለ ዐዋዲ ገድሉን ለመጨረሻ ጊዜ ጽፎ አጠናቅቆታል፡፡ ይህም ከርሱ በፊት የነበሩትን ምንጮች በመጠቀምና እስከ እርሱ ዘመን የተፈጸሙትን ተአምራት በማጠቃለል ገድሉን እና ተአምራቱን ያጠናቀቀው ይመስላል፡፡ «ይህንን የድርሳንና የተአምር መጽሐፍ የጻፈው የደብረ ብሥራት አበ ምኔት አባ ቃለ ዐዋዲ ነው» ይላል ገድሉ /ገጽ. 377/፡፡ ይህም ገድሉ ከተጀመረበት እስከ ተጠናቀቀበት ድረስ 200 ዓመታት ጊዜ የወሰደ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህንን ሁኔታ ስንመለከተው ገድለ ዜና ማርቆስ የተጻፈው ታሪኩ ሲፈጸም በአካል በነበሩ፤ የዓይን ምስክር በሆኑ አበው እና እማት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለዚህም ነው ገድሉ ይህንን ያህል ዘመን የፈጀው፡፡

የታሪኩ መገኛ

ገድለ ዜና ማርቆስ የአቡነ ዜና ማርቆስ ታሪክ እና ተአምር ከየት ሊገኝ እንደቻለ ይነግረናል፡፡ ታሪካቸውን በተመለከተ «ያን ጊዜ ወደ በረሐ ገብቶ ሱባኤ ይዞ በጽሙና ሰባት ዓመት በኖረበት ጊዜ ልጆቹ ያዩትን ተአምራቱን ጻፉ፤ ያላዩትንም እኅቱ ማርያም ክብራ ከልደቱ ጀምራ የሆነውን ሁሉ እየነገረቻቸው ጻፉ፡፡ /ገጽ.144/፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ምንጮችን እናገኛለን፡፡ የአቡነ ዜና ማርቆስ እኅት ማርያም ክብራ ከልጅነት ጀምሮ ያለውን ታሪክ የዓይን ምስክር ሆና ታውቃለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ በገዳ ማዊ ሕይወት የሆነውን ሁሉ ያዩትን ጽፈዋል፡፡

ሌላው የታሪክ ምንጭ ደግሞ «ከዕረፍቱ ጊዜ እና ከዕረፍቱ በኋላ የተደረገውን» የጻፉት አባ ገብረ ክርስቶስ /የገዳሙ አበምኔት የነበሩ/ እና አባ ገብረ መርዓዊ ናቸው፡፡ /ገጽ.144/ ዐጽሙ በሚፈልስ ጊዜ በአካል ተገኝቶ የነበረው አባ ዮሐንስም ያየውን ጽፎ በገድሉ ውስጥ አካትቷል /ገጽ.144/፡፡ አባ ቃለ ዐዋዲም በግራኝ ጊዜ ራሱ በአካል ተገኝቶ የተፈጸመውን ለማየት የበቃ ሰው ነው፡፡ /ገጽ. 146/፡፡ በመሆኑም ያየውን ጽፎ በገድሉ አካትቶታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ለተልእኮ ወጥተው ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ የተልእኮዋቸውን ዜና ለደቀመዛሙርቶቻቸው ይተርኩላቸው እንደነበረ ገድሉ ይነግረናል፡፡ /ገጽ.101/፡፡

ከታሪኩ በተጨማሪም የተአምራቱን ምንጮች ጸሐፊዎቹ በሚገባ አስቀምጠውልናል፡፡ ለምሳሌ በገጽ 150 ሊቀ ጳጳሳቱ የነገራቸው መሆኑን፣ በገጽ 151 «ከእስክንድርያ የመጡ ሰዎች ነገሩን» ይላል፤ በገጽ 170 ዓይንዋ የተፈወሰላት ሴት የሰጠችው ምስክርነት፤ ልጇ የሞተባት ሴት የሰጠችው ምስክርነት /ገጽ. 27/ ያመነችው አረማዊት ሴት የሰጠችው ምስክርነት /ገጽ. 244/፣ የአክሱም መነኮሳት የሰጡት ምስክርነት /ገጽ. 310/ ለዚህ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከትግራይ የመጣው መኮንን የሰጠው ምስክርነት/ገጽ 312/፤ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው የነበሩ ወንድሞች የሰጡት ምስክርነት /ገጽ. 313/ የአቡነ አረጋዊ ገዳም መነኮሳት የሰጡት ምስክርነት /ገጽ. 318/፣ የግብጽ ሰዎች እና የሊቀ ጳጳሱ ረድእ የሰጡት ምሥክርነት /ገጽ. 327/፤ በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት ከአይሁድ እና ከተንባላት የመጡ 60 መልእክተኞች በሀገራቸው የተፈጸሙትን ተአምራት ወደ ገዳሙ ከስጦታ ጋር ይዘው መጥተው አስረክበው ነበር፡፡ «እኛም ጽፈን ከአባታችን ዜና ማርቆስ የገድሉ መጸሐፍ ጋር አኖርነው» ይላል ጸሐፊው /ገጽ. 369-370/፡፡

ተአምሩን የጻፉት አበው በመጽሐፈ ገድሉ ውስጥ ተአምሩን ከማካተታቸው በፊት የማረጋገጥ ሥራ ይሠሩ እንደነበረ መረጃ እናገኛለን፡፡ «እኛም ነገርዋን ሰምተን ከሀገርዋ ሰዎችም ጠይቀን፤ አረማዊ ንጉሥም እንዳመነና ወደ ንጉሣችን ወደ ዘርዐ ያዕቆብ መልእክተኞች እንደላከ ነገርዋ እውነት ሆነ» /ገጽ. 294/ ይሉናል ጸሐፊዎቹ፡፡

ይህ ሁኔታ ተአምራት የተፈጸመላቸው ሰዎች ስእለታቸውን ለመፈጸም ወይንም ደግሞ ተአምር የሠራላቸውን ቅዱስ ገዳም ለማየት ወደ ገዳሙ ሲመጡ አባቶች ታሪኩን አረጋግጠው በገድሉ ይመዘግቡት እንደነበር ያስረዳናል፡፡

የተአምራቱ አጻጻፍ እና ቁጥር

ገድለ ዜና ማርቆስን በመጨረሻ ያጠቃለለው አባ ቃለ ዐዋዲ ተአምራቱን በሁለት ከፍሏ ቸዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ከማረፋቸው በፊት የተፈጸሙ እና ካረፉ በኋላ የተፈጸሙ፡፡

አቡነ ዜና ማርቆስ ከተወለዱበት እስከ ዐረፉበት ጊዜ የተደረጉ 22 ተአምራት በገድሉ ተመዝግበዋል /ገጽ. 384/፡፡ ይህም ጽሑፍ የተጻፈው አቡነ ዜና ማርቆስ ባረፉ በ3ኛ ዓመት መሆኑን ገድሉ ይናገራል፡፡ /ገጽ 385/ ያረፉት በ1433 ዓ.ም በመሆኑ /እንደ ገድሉ ከሆነ፤ ሌሎች መረጃዎች ግን በ1402 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡/ የመጀመሪያዎቹ ተአምራት የተጻፉት በ1436 ወይም በ1405 ዓ..ም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁለተኛዎቹ ተአምራት ቁጥራቸው 44 ሲሆን የተጻፉት በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት /1391- 1460 ዓ.ም/ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በዐፄ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት አንድ ተአምር በአባ ቃለ ዐዋዲ አማካኝነት ተጨምሮአል፡፡ ይህ ሁኔታ የተአምራቱ ቁጥር 67 መሆኑን ያመለክታል፡፡ እንደ እኔ እምነት ቅዱሳት መጻሕፍትን ሠፍሮ እና ቆጥሮ መመዝገብ እና በቀኖና መወሰን /በተለይ ተአምራትን/ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከ600 ዓመታት በላይ የቆየ ታሪክ ያለው መሆኑን ከሚያሳዩት ማሳያዎች አንዱ ይህ ይመስለኛል፡፡

በታተመው ገድል 'ሁለተኛ ክፍል' በሚል ርዕስ ከተቀመጡት ተአምራት መካከል ከ17ኛው ተአምር በቀር /በመጋቢት ወር ስለተፈጸመ በወቅቱ ለማንበብ እንዲመች ወደዚህ ክፍል የገባ ይመስላል/ የቀሩት 21 ተአምራት አቡነ ዜና ማርቆስ ባረፉበት ዓመት እና በቀጣዩ ዓመት የተፈጸሙ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም በተአምራቱ መካከል የምናገኛቸው መረጃዎች ስለዚያ ዘመን የሚተርኩ ናቸውና፡፡

'ካልእ ተአምር' ተብለው ከተመዘገቡት 17 ተአምራት መካከል ሁሉም አቡነ ዜና ማርቆስ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ያደረጓቸውን ተአምራት የሚነግሩን ናቸው፡፡ 'ሦስተኛው ተአምር' ተደርገው የተቀመጡት 22 ተአምራት ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እስከ ዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግ ሥት ባለው ዘመን ውስጥ ጻድቁ ካረፉ በኋላ ያደረጉትን ተአምራት የሚገልጡ ናቸው፡፡

በጠቅላላው በሁለተኛ ክፍል መጀመሪያ የተጻፉት 25፣ በሁለተኛ ክፍል የተቀመጡት 17፤ በሦስተኛ ክፍል ያሉት 22 ተአምራት ሲደመሩ 64 ተአምራት ይሆናሉ፡፡ ይህም በገድሉ ገጽ. 384 ከተጠቀሰው ድምር ቁጥር ከ67 በሦስት ያንሳል፡፡ በመሆኑም አንድም ከታሪክ ጋር ተቀላቅሏል፡፡ ያለበለዚያም ከዋናው ገድል ተገልብጦ ሳይደርሰን ቀርቷል ማለት ነው፡፡

የገድሉ ጸሐፊዎች ታሪኩን በታሪክ፣ ተአምሩን በተአምር መድበው በየፈርጁ ለማስቀመጥ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ሥራቸው ይመሠክራል፡፡ በታሪኩ ላይ የማይገኝና በተአምሩ የሚገኝ ነገር ሲኖር «በኋላ በአባታችን የተአምር መጽሐፍ እንነግራችኋለን፤ በተአምር መጸሐፉ ተጽፏልና» ይሉናል /ገጽ.89/፤ በሌላ ቦታም ታሪኩን ከዘረዘሩ በኋላ «የቀረውን ግን በተአምሩ መጽሐፍ እንነግራችኋለን፣ በተአምሩ ለኃጥአን የሚጠቅም ታላቅ ነገር የንስሐ ዜና አድርጎ የሠራላቸው አለና፡፡ አሁን ግን ወደ መጀመሪያው የገድሉን ነገር ወደ መናገር በእግዚአብሔር ሰላም እንመለስ» ይሉናል /ገጽ.97-98/፡፡ በገጽ. 99 ላይ ደግሞ «ግራኝ ለማጥፋት በተነሣ ጊዜ የዚህች የደብረ ብሥራት ገዳም አበምኔት የነበረ አባ ቃለ ዐዋዲ የጻፈውን፣ አባታችን ዜና ማርቆስ ስለ ልጆቹ ያደረገውን ተአምራቱን በተአምር መጽሐፉ ኋላ እንነግራችኋለን» ይላል፡፡ ይህም ነገሮችን በየመልካቸው ለመመዝገብ ያደረጉትን ጥረት ያሳያል፡፡

ጊዜን ለማመልከት ያደረጉት ጥረት

የገድሉ ጸሐፊዎች ነገሮቹ የተፈጸሙበትን ጊዜ በትክክል ለመግለጥ ልዩ ልዩ መንገ ዶችን ተጠቅመዋል፡፡ በዚህም አብዛኞቹ ገድሎች ከሚጠቀሙበትና ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተወረሰ ከሚታመነው ድርጊቱን ብቻ ከመግለጥ ነባር ባህል ወጣ ብለዋል፡፡

ለምሳሌ ግርማ አስፈሪ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት አቡነ ዜና ማርቆስ 40 ዓመታቸው ነበረ ይሉናል፡፡ /ገጽ.88/ የግርማ አስፈሪ ጠቅላላ የንግሥና ዘመኑ 25 ዐመት መሆኑንም ገድሉ ያሳያል /ገጽ. 88/፡፡

እንደ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከሆነ ግርማ አስፈሪ የንዋየ ማርያም ስመ መንግሥት ሲሆን በሌላ ስሙ ውድም አስፈሪ ይባላል፡፡ የነገሠውም ከሰይፈ አርዕድ ቀጥሎ ከዐፄ ዳዊት 1ኛ በፊት ከ1371-1380 ዓ.ም ድረስ ነው፡፡ በመሆኑም ግርማ አስፈሪ የነገሠው በ1374 ዓ.ም ከሆነ እና በዚያ ጊዜ አቡነ ዜና ማርቆስ  ዕድሜያቸው 40 ዓመት ከሆነ የተወለዱት /ከ3372 ሲቀነስ 40/ በ1331 ዓ.ም አካባቢ ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ የንግሥና ዘመኑን 9 ዓመት ብቻ ነው የሚያደርጉት፡፡ የአቡነ ዜና ማርቆስ ዕድሜ በጠቅላላው 140 ዓመት ነው፡፡ በመሆኑም ያረፉት በ1471 ዓ.ም አካባቢ ነው ማለት ነው፡፡ ገድሉ ያረፉበትን ዓመት በዐፄ እንድርያስ ዘመን መሆኑን ያመለክታል ንጉሥ እንድርያስ በ1429 ዓ.ም አካባቢ ነው የነገሠው፡፡ በመሆኑም ዘመኑ ተቀራራቢ ነው፡፡

ሊቃነ ጳጳሳት

ገደለ ዜና ማርቆስ ስለ ልዩ ልዩ ሊቃነ ጳጳሳት መረጃዎች ይሰጣል፡፡ ከግብጽ ተሹመው የመጡ አባ ጌርሎስ፣ አባ በርተሎሜዎስ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ ማቴዎስ ስለሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት በመጠኑም ቢሆን ይነግረናል፡፡ ከአራቱ መካከል አቡነ ጌርሎስ እና አቡነ በርተሎ ሜዎስ ሰፋ ያለ ቦታ ይዘዋል፡፡ አባ ጌርሎስ ያረፉት አቡነ ዜና ማርቆስ በዐጸደ ሥጋ እያሉ በምሁር ገዳም ሲሆን በንጉሥ ከተማ በደብረ የረር ሊቀብሯቸው ሳለ አባታችን አገኟቸው፡፡ /ገጽ. 66/ /ምናልባት ከአዲስ አበባ ምሥራቅ በሚገኘው የረር ተራራ ይሆን/
ከዚያም ደመና ነጥቆ ሥጋቸውን ወደ ደብረ ደይ የአርባዕቱ እንስሳ ቤተክርስቲያን ወሰደው በዚያም ተቀበሩ፡፡ ደይ ከዜና ማርቆስ ገዳም አጠገብ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ በተራራው ላይ ሕዝብ ናኝ /እንድርያስ/ ያሠራው ቤተ ክርስቲያን ፍራሽ ይገኛል፡፡

በገድለ ዜና ማርቆስ የእስክንድርያ ሊቃn ጳጳሳትን በተመለከተም መረጃ እናገኛለን፡፡

ፓትርያርክ ዮሐንስ

ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ባረፉ ጊዜ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ በዚያ ወቅት አንድ የሚያስገርም ነገር በገድሉ ላይ ተጽፏል፡፡ ሌሎች በዕለተ ቀብሩ የተገኙት ሁሉ እንጀራ ሲመገቡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ በድንገት በመገኘታቸው የሚመገቡት ነገር አልተዘጋጀም ነበር፡፡ የሚመገቡት የስንዴ እንጀራ መሆኑን ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህም ከግብጻውያን ባህል ጋር የተስማማ ነው፡፡ በኋላም የስንዴ እንጀራ ተፈልጎ እንደቀረበላቸው ይገልጥልናል /ገጽ. 152/፡፡

በግብጻውያን የሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር መሠረት በዚህ ወቅት የነበሩት አቡነ ዮሐንስ 12ኛ /1480-83 እ.ኤ.አ/ ወይም ደግሞ አቡነ ዮሐንስ 13ኛ /1484- 1524 እ.ኤ.አ/ ናቸው፡፡ በአቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍት ጊዜ የተገኙት ከሁለቱ አንዱ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ፓትርያርክ አባ ማቴዎስ

ከደብረ ብሥራት የተነሡ 12 ደቀ መዛሙርት በግብጽ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ ያገኟቸው ሊቀጳጳስ የእስክንድርያው 88ኛ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ መሆናቸውን ገድሉ ይገልጥልናል /ገጽ. 324/ ፡፡እርሳቸው በመንበረ ማርቆስ በነበሩ ጊዜ በኢትዮጵያ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ 92ኛው ጳጳስ አቡነ ማርቆስ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚያስገርመው ነገር የመረጃ አሰጣጡ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሊቃነ ጳጳሳቱን ስም ከነ ተራቸው /ስንተኛ እንደሆኑ መግለጡ፤/ በሌላ በኩል ደግሞ ለበለጠ ማስረጃ በእስክን ድርያ የነበሩትን ፓትርያርክ ከኢትዮጵያው ጰጳስ ጋር አጣምሮ መጥራቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡

ሜንያድረስ የተባለው የታሪክ ምሁር በጻፈው /The two thousand years Coptic Christianity/ በተባለው መጽሐፍ እንደ ምናገኘው አባ ማቴዎስ ሰማንያ ስምንተኛ ሳይሆን 87ኛ ፓትርያርክ ናቸው /1378-1408/፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያውያን አበው የሚቆጥሩበትና ግብጻውያን የሚቆጥሩበት ተለያይቶ ይሆናል፤ ያለበለዚያም ደግሞ በኋላ ዘመን የተፈጠረ የገልባጭ ስሕተት ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ የጳጳሳት ዝርዝር መሠረት አቡነ ማርቆስ በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግ ሥት የነበሩትና በ1513 ወሎ የነበረው መካነ ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር የባረኩት አባት ናቸው፡፡ አቡነ ማርቆስ ቤተክርስቲያኑን ሲባርኩ ዕድሜያቸው ከመቶ ዓመት በላይ ሆኖ ነበር፡፡

በዘመኑ የነበሩ አበው

ገደለ ዜና ማርቆስ ስለ አቡነ ዜና ማርቆስ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎች በዘመኑ የተነሡ አበውም መረጃዎችን ይለግሠናል፡፡ ስለ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ፣ አባ ሕፃን ሞዓ፣ አባ አኖርዮስ ታላቁ፣ አባ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አባ ቀውስጦስ ዘመሐ ግል፣ በመጽሐፉ ውስጥ ታሪካቸው ይገኛል፡፡ በተለይም በገጽ.4 ላይ ከተጉለት የተነሡ ቅዱሳንን የዘር ሐረግ በዝርዝር ነው የሚያሳየን፡፡

በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት

በዚያ ዘመን አካባቢ የተነሡ ነገሥታት ታሪክም በገድለ ዜና ማርቆስ ተመዝግቧል፡፡ የዐፄ ይኩኖ አምላክ /ገጽ. 7፣ 51-52/፡፡ ዐፄ ዓምደ ጽዮን በዘመኑ ከነበሩት አበው ጋር ከተጣሉ በኋላ እንዴት ወደ ሰላም መንገድ እንደተመለሱ /ገጽ. 248- 254/፤ ስለ ዐፄ ሰይፈ አርዕድ /ገጽ. 275-279/፤ በገድሉ ውስጥ እናገኛለን፡፡

ሌሎች ታሪካዊ መረጃዎች

ገድለ ዜና ማርቆስ ለቤተክርስቲያን ታሪክ ጥናት እጅግ የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ታሪካዊ መረጃዎችን ይዞልናል፡፡ ስለ ጥንቱ የጉራጌ ሀገረ ስብከት /ገጽ. 31/፤ መጀመሪያ ሸዋ ውስጥ ስለተተከሉት አብያተ ክርስቲያናት /ገጽ. 65/፤ የመስቀል በዓል አከባበር በዚያ ዘመን ምን ይመስል እንደነበር /ገጽ. 67/፤ በዘመኑ የነበረው የክርስቲያን - እስላም ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር /ገጽ.54፣ 118፣173፣183፣234፣285/፤ በዚያ ዘመን ስለነበረው የአርጎባ ሕዝቦች ሁኔታ /ገጽ. 290/፤ በሸዋ አካባቢ ስለነበሩ ቤተ እስራኤል /ገጽ. 67/ ስለማኅሌተ ጽጌ አጀማመር /ገጽ. 67-75/ ፤በዐፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት የሰንበት ክርክር እንዴት እንደተጀመረ /ገጽ.89፣275-279/፤ በእናርያ ይገኝ ስለ ነበረው ቀይ ወርቅ፣ /ገጽ.183/፤ ስለ በልበሊት ገዳም እና ስለ አባ ፊቅጦር /ገጽ.186 -187/፤ ጸሐፌ መንክራት ዮሐንስ ተአምረ ማርያምን በጻፈ ጊዜ እመቤታችን ያደረገችለትን ነገር /ገጽ.192/፡፡ ተአምረ ማርያም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በፊት እንደ ነበረ መረጃ ይሰጣል፡፡ የግራኝ ሠራዊት የሸዋን አካባቢ አብያተ ክርስቲያናት እንዴት አድርጎ እንዳቃጠላቸው /ገጽ.378/፤ ስለ እጨጌ ዕንባቆም /ገጽ.333/፤ ስለ ደቅ ደሴት /ገጽ.114 -117/ በዚያ ዘመን ስለ ነበረው ቅዳሴ ሁኔታ /ገጽ.129-133/፡፡

የአቡነ ዜና ማርቆስ ትምህርት

ገድለ ዜና ማርቆስን ከሌሎች ገድሎች ከሚለዩት ነገሮች ሌላው ደግሞ የአቡነ ዜና ማርቆስን ትምህርት ብቻ ሳይሆን የትምህርታቸውን ቢጋር ጭምር መያዙ ነው፡፡

የአቡነ ዜና ማርቆስ የትምህርታቸው ቢጋር /ገጽ. 94-95/ በዚያ ዘመን የነበሩ አበው ምንን እንዴት ያስተምሩ እንደ ነበር የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚህም በላይ አባታችን ለእስላሞች ትምህርት የሰጡት መልስ /ገጽ.180/፤ ስለ ሰንበት ያስተማሩት ትምህርት /ገጽ. 256 - 267/ በገድሉ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህም በላይ አባታችን ከማረፋቸው በፊት ያደረጉት የመሰናበቻ ንግግር /ገጽ. 134-139/ በዝርዝር በገድሉ ላይ ይገኛል፡፡

በዚያ ዘመን የነበረው የተሳላሚዎች ጉዞ

በዚያ ዘመን የሸዋ ገዳማውያን ከትግራይ፣ ኤርትራ እና ግብጽ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እና የመንገዳቸውን አቅጣጫ በገድሉ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ዐሥራ ሁለት የሚሆኑ የገዳመ ዜና ማርቆስ መነኮሳት ከሸዋ እስከ ኢየሩ ሳሌም ያደረጉት ጉዞ፣ የጉዞው አቅጣጫ፣ ያረፉበት ቦታ እና ያጋጠማቸው ነገር በዘመኑ ይደረግ የነበረው ሃይማኖታዊ ጉዞ እንዴት እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ከዜና ማርቆስ ገዳም ተነሥተው በወርዕ ወንዝ በኩል ወደ ደብረ አቁያጽ፤ ከዚያም ወደ አባ አሌፍ - ደብረ ሃሌ ሉያ /ደብረዳሞ/- በሱዳን በኩል በዓባይ ወንዝ በጀልባ አድርገው ወደ ግብጽ ነበር የገቡት፡፡ በእያንዳንዱ ገዳም ይደረግላቸው የነበረውን አቀባበል ስናይ በሰሜን እና በደቡብ ገዳማት መካከል ከዘረኝነት የጸዳ ፍቅር እና መከባበር እንደነበር እናያለን፡፡

ተጓዦቹ ገዳማቱን እየተሳለሙ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ሁለት ዓመት ያህል ፈጅቶባቸዋል/ገጽ. 370/፡፡

አስደናቂው የኢየሩሳሌም ክርክር

ከገዳመ ዜና ማርቆስ የተነሡት ዐሥራ ሁለቱ መነኮሳት በግብጽ በኩል ኢየሩሳሌም ገብተው አርባውን ጾም ጾመው የትንሣኤን በዓል አከበሩ፡፡ አብሮአቸው ወደ ኢየሩሳሌም የገባው የግብጹ ሊቀ ጳጳስ በምእመናን ተጋብዞ ወደ ግብዣ ሲገባ እነዚያ መነኮሳት የሚጋብዛቸው አጥተው በውጭ ቀሩ፡፡

አንድ ዮሐንስ የሚባል ሮማዊ መምህር /ምናልባት ካቶሊክ ሳይሆን አይቀርም/ በውጭ በበዓል ቀን መቀመጣቸው አሳዝኖት ወደ ቤቱ ወሰዳቸው፡፡ ለእነርሱ ምግብ ካቀረበ በኋላ ሌሎች መነኮሳት አምጥቶ አብረዋችሁ ይብሉ ብሎ ቀላቀላቸው፡፡ እኒያ የገዳመ ዜና ማርቆስ መነኮሳት በሃይማኖት ስለምንለያይ አብረን አንበላም አሉ፡፡ በዚህ የተናደደው ዮሐንስ ደብድቦ በጨለማ ቤት አሠራቸው፡፡ በኋላም በሰው ጥቆማ ዮሐንስ ተይዞ መነኮሳቱ ከገቡበት የጨለማ ቤት እንዲወጡ ተደረገ፡፡

የሀገሩ ገዥ በዮሐንስ ግፍ ተናድዶ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡ ከመነኮሳቱ መካከል አባ በኃይለ ማርያም የሚባል መምህር እኛ ነፍስ አንገድልም፤ ነገር ግን ስለሃይማኖቱ እንከራከርዋለን ብሎ ጠየቀ፡፡ ከዚያም ዕብራይስጥ እና የዐረብ ቋንቋ መቻሉን ሀገረ ገዥው ጠየቀው፡፡ አባ በኃይለ ማርያም የዕብራይስጥ እና የዐረብ ቋንቋን ከደብረ ሊባኖሱ መምህር ከእጨጌ ዕንባቆም መማሩን ተናገረ፡፡ ዕንባቆም በ15ኛው መክዘ መጨረሻ ወደ ክርስትና የገባ እና ከዚያም የደብረ ሊባኖስ እጨጌ እስከ መሆን የደረሰ፣ አንቀጸ አሚን የተሰኙ ሁለት መጻሕፍትንም የጻፈ የመናዊ ሰው ነው፡፡

ጉባኤው ተዘጋጀ፡፡ አባ ዳንኤል ዘገዳመ እንጦንስ፤ አባ ማርቆስ ዘገዳመ ቁስቋም፤ አባ ዮሐንስ የአትሪብ ሊቀጳጳስ፤ አባ ኤፍሬም የሀገረ መሊጣ ሊቀጳጳስ፤ አባ ሚካኤል የመርያ ኤጲስ ቆጶስ፤ አባ ሚካኤል እና አባ ማርቆስ የሚባሉ መምህራን ከግብጽ፣ ከሶርያና ዮርዳኖስ አብያተ ክርስቲያናት ተገኝተዋል፡፡ አባ ስምዖን የተባለ የመዓልቃ ገዳም አባትም በጉባኤው ተካፍሏል፡፡ የግብጹ ሊቀ ጳጳስ አባ ማቴዎስ ዳኛ ሆኖ ተገኘ፡፡ የአይሁድ እና የዐረብ አለቆች ተጋበዙ፡፡

የአርማንያ ኤጲስ ቆጶስ- አባ ባስልዮስ፤ የቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ አባ ቴዎድሮስ፤ የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ፤ የሶርያ ኤጲስ ቆጶስ አባ ዘካርያስ በጉባኤው ተሰየሙ፡፡ አባ ዮሴፍ የተባለ ሰውም የአባ በኃይለ ማርያምን እና የሮማዊው ዮሐንስን ቃል ወደ ሶርያ ቋንቋ እንዲተረጉም ተመደበ፡፡

በዚህ ሁሉ ጉባኤ ፊት ነው ክርክሩ የተካኼደው፡፡ ይህ ክርክር በጠቅላላው የገድሉን 33 ገጾች የሸፈነ ነው፡፡ አባ በኃይለ ማርያም የሚያነሣው ሐሳብ፣ የሚጠቅሰው ጥቅስ፣ የሚያቀርበው ማስረጃ በዚያ ዘመን የነበሩ ሊቃውንትን የዕውቀት አድማስ የሚያሳይ፣ ዕውቀታቸው እንደ ማር ከየአቅጣጫው የተቀመመ መሆኑን የሚመሰክር ነው፡፡ በዐረብኛ፣ በዕብራይስጥ እና በግእዝ መናገር እና ማሳመን የሚችል በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ዕውቀቱን ያስመሰከረ ሊቅ ነው አባ በኃይለ ማርያም፡፡

አባ ቃለ ዐዋዲ

የገድለ ዜና ማርቆስ ጸሐፊ አባ ቃለ ዐዋዲ ኢብን ኢብራሂም አሕመድ አልጋዚ ከምሥራቅ ወደ መካከለኛው ሸዋ እየገፋ ሲመጣ የደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ገዳም አበ ምኔት ነበር፡፡ አባ ቃለ ዐዋዲ ገድሉን እንዴት እንደ ጻፈው፤ በገዳሙ የነበሩ መጻሕፍትን እንዴት ከጥፋት እንዳዳነ ይተርክልናል፡፡ 200 መጻሕፍትን እና 16 ታቦታትን በደብረ ብሥራት ደበቃቸው፡፡ 200 መጻሕፍትን እና 7 ታቦታትን በሸር ካቢ ዋሻ /የት እንደሆነ አላወቅኩም/ ደበቀ፡፡ ካዘጋጃቸው የአባ ዜና ማርቆስ ገድል ቅጂዎች አምስቱን በጉራጌ ይገኝ በነበረው በምሁር ገዳም፤ ሁለት የገድለ ዜና ማርቆስ ቅጂዎችን እና 300 መጻሕፍትን በጋይ ዋሻ /ከዜና ማርቆስ ገዳም አጠገብ የሚገኝ/፤ 400 መጻሕፍትን ወተጌ በምትባል ሀገር ባለች ዋሻ፤ አንድ ገድለ ዜና ማርቆስ እና 100 መጻሕፍትን በእንቡ ልቡልና ዞረት ገደል በሚገኝ ዋሻ /ቀወት ውስጥ/ አስቀመጠ፡፡

ከዚህ በኋላ 400 መጻሕፍትን እና 2 ታቦታትን ይዞ፤ 1200 ደቀ መዛሙርት አስከትሎ፤ 14  ታቦታት የያዙ 547 መነኮሳት አጅበውት ወደ በጌምድር ተጓዘ፡፡ /ገጽ. 379/ ከላይ የተጠቀሱ መጻሕፍትን ስንደምራቸው 1608 መጻሕፍት በገዳሙ ውስጥ እንደነበሩ ያስረዳናል፡፡ ለእኔ እጀግ በጣም የሚደንቅ መረጃ ነው፡፡ አባ በኃይለ ማርያም ያለ ምክንያት በሙሉ ልብ በኢየሩሳሌም አደባባይ ስለ ሃይማኖቴ ልከራከር አላለም፡፡ በእነዚህ ሁሉ መጻሕፍት የተከበበ ሊቅ ራሱ መጽሐፍ ማለት ነውና፡፡

በገዳሙ ውስጥ ከ1200 በላይ ደቀ መዛሙርት /ተማሪዎች/ እና ከ547 በላይ መነኮሳት እንደ ነበሩ ስናነብ ደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ በዚያ ጊዜ የሊቃውንት መፍለቂያ የገዳማውያን መናኸርያ እንደ ነበር ያሳየናል፡፡ አባ ቃለ ዐዋዲ የደበቃቸው እነዚያ መጻሕፍት ከጦርነቱ በኋላ ይውጡ፣ ይቅሩ መረጃው የለኝም፡፡

በዚያ ጊዜ ገዳሙ ለሌሎች የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መጋቢ አስተዳዳሪ ሆኖ ስለሚያገለግል፤ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እና መናኝ ካህናት ታቦታትን ከገዳም ስለሚያገኙ በገዳማት ውስጥ ብዙ ታቦታት ይገኙ ነበር፡፡ በገድለ ዜና ማርቆስ ተመዝግቦ እንዳገኘነው በገዳሙ ውስጥ 57 ታቦታት ነበሩ፡፡

ገድለ ዜና ማርቆስ በተደጋጋሚ ሊነበብ፤ ከልዩ ልዩ ነገሮች አንፃር ሊተነተን የሚገባው ገድል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገድላት እንዴት ተጻፉ፣ ምንጫቸው ምን ነበር? ማን ጻፋቸው? እንዴት ሊጠበቁ ቻሉ? ከታሪክ ጋር ያላቸው ተዛምዶ? ወዘተን ለመሳሰሉ የዘመኑ ጥያቄዎች መልስ ከሚሰጡት ገድላት አንዱ ነው፡፡

ገድለ ዜና ማርቆስ አንዳንድ ወገኖች ገድልን በተመለከተ ያላቸውን ደከም ያለ አስተሳሰብ ሊያርምላቸው የሚችልና ጥናታቸውን ከንቀት ሳይሆን ከአክብሮት እንዲጀምሩ የሚያደርግ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የጻድቁ በረከት ይደርብን፡፡15 comments:

 1. Amen Kale Hiwotne Yasemalen!Mengeste Semayaten Yawarselen! Yebetekerstiyan merejawoch kefel 2ten Begugut Entebabekalen. Yabertalen!

  ReplyDelete
 2. +++
  አሜን ይደርብን - አንተንም ቃለ ህይወት ያሰማልን!
  ይህን የፃፉ እጆችህም ይባረኩ ።
  ሀብተ-ስላሴ

  ReplyDelete
 3. Thank you for ur wonderful analysis of the book.I am also amazed zat The Book of The Miracles of Marry was there before the times of king Zerayakob.

  Many historians wrote that it was King Zerayakob who introduced the book during the times of Aba Michael and Aba Gabriel.

  Good to know zat the book was there before them
  Thank you

  ReplyDelete
 4. Thank you Dn Daniel
  Kale heyote yasemalen.
  I think the is a typo.errore
  Abun Zena Markose edmeyachew 40 amete kehone yeteweldote 1372-40 = 1331 or 1332 yehonal in the articl it says 3372-40 = 1331 I think it is a tyop errore. you can corecte it.
  My God be with you and our tewhedo church keep up the v.goooooooooooooooooooood job.
  Thank you
  From USA,Alexandria, VA

  ReplyDelete
 5. Amen!!! Kale Hiwot Yasemah.
  Next time can you write some thing about Abune Betre Mariam ( If I am not mistaken He is a founder for Mehal Zegie Giorgis) please.

  ReplyDelete
 6. Amen!!!!!
  kalehiwot yasemalen

  ReplyDelete
 7. Dn Dani,Selam leke .....

  Medhanealem Kante gar yihun kemalet besteqer Minis malet yichalal.Dingil Wondimen tebikiwu.

  Kaleb,Canada

  ReplyDelete
 8. i don't know how i would get the gedl in the US, i would do anything to read the book. Thank you very much for presenting this research on your blog. It was wonderful reading it. Hope you will keep me reading your blog.

  ReplyDelete
 9. Kale Hiwot Yasemah Eriste Mengiste Semayatin Yawarsih. Yesadiku bereket, amalaginet ayileyen. yesewu mechereshawu siyamir newuna mecheresahin yasamirlih. TEBAREK!!!!!!!!!!!

  Lozamariam

  ReplyDelete
 10. I knew a little about Gedle-zena Markos through when I read some writtings on Ethiopian History (When it is being cited as a source of information).
  But nothing has shown me the importance of this Gedel like reading this piece.
  This Gedel made one of the writtings that I want to read.
  Thank you very much for bringing this Dn. Daniel.
  I will be very happy to hear many more about such thing. For example,if you know some ancient writtings about aratu kidusan negesitat, Abreha-weatsibeha, king Kaleb and His Son.
  Thank you a lot.

  ReplyDelete
 11. I knew a little about Gedle Zena Markos through some writtings on Ethiopian History (When it is being cited as a source of information).
  But nothing has shown me the importance of this Gedel like reading this piece.
  This Gedel made one of the writings that I want to read,just because of this piece.
  Thank you very much for bringing this Dn. Daniel.
  I will be very happy to hear many more about such thing. For example,if you know some ancient writtings about aratu kidusan negesitat, Abreha-weatsibeha, king Kaleb and His Son.
  Thank you a lot.

  ReplyDelete
 12. አ/ሚካኤልMay 7, 2010 at 3:48 PM

  ዲያቆን ዳንኤል
  እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንህ ያብዛልን
  ዕድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን።እኛም አድናቂዎች ብቻ ሳንሆን ተጠቃሚዎች ያድርገን።
  እንዲህ ያለውን ለማን ይቻለዋል?
  በርታ ቀጥል

  ReplyDelete
 13. First and for most thank you very much for your information sharing. I have a question.
  Where is the location of Zena Markos Gedam?

  ReplyDelete
 14. በግራ በኩል አሉት ሜኑዎች ላይ click here for pdf የሚሉት hyper link አልሆኑም ስለዚህ በትትክክል ቢደረጉ. ሌላው አማርኛው ገጽ ላይ እንግሊዝኛ መጠቀሙ ምን ይጠቅማል

  ReplyDelete