ይህ ጽሑፍ በ2001 ዓም የኢትዮጵያ ፊሎሎጂ ማኅበር ባዘጋጀው 3ኛ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው፡፡
መግቢያ
በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ከ200 በላይ ገድላትን እስከ አሁን ለማየት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ የገድላቱ አጻጻፍ ተመሳሳይ የሆነ «ቅርጽ» /format/ እና ተመሳሳይ የሆነ «ፍሰት» /Flow/ የሚከተሉ ሆነው አግኝቻቸው ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ «ቅርጽ» የምለው የገድሉ ባለቤት ታሪክ፣ ገድል፣ ቃል ኪዳን፣ ተአምር እና መልክዕ የሚጻፍበት መንገድ ማለቴ ነው፡፡ በአብዛኞቹ ገድሎች መጀመሪያ የሃይማኖት መሠረት የሚሆነው ምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ሥጋዌ በመግቢያነት ይቀርባል፡፡ ከዚያም የቅዱሱ ትውልድ ይገለጣል፤ ቀጥሎም ገድሉ ይከተላል፤ ከዚያም የተሰጠው ቃል ኪዳን ይጻፋል፤ በመጨረሻም ተአምሩ እና መልክዑ ይቀርባል፡፡
«ፍሰት» የምለው ደግሞ የታሪኩ ቅደም ተከተል የቀረበበትን መንገድ ነው፡፡ ታሪኩ ከየት ተነሥቶ፣ በየት በኩል አልፎ፣ የት ይደርሳል የሚለው ነው፡፡ በብዙዎቹ ገድሎቻችን ከቅዱሱ ወላጆች ይጀምርና አወላለዱን ከገለጠልን በኋላ የአካባቢያዊ እና የትምህርታዊ ዕድገቱን፤ ገዳማዊ ሕይወቱን፣ የተቀበለውን መከራ፤ ዕለተ ዕረፍቱን ነው የሚተርክልን፡፡
የገድለ ዜና ማርቆስ አቀራረብ ግን ከዚህ ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ በመሆኑ ስለ ገድላት ያለንን ዕውቀት የሚያሳድግ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ መረጃም የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ገድሉን ለማንበብ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕድል ያገኘሁት የዛሬ ስድስት ዓመት በደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ ገዳም ከሚገኘው ዕቃ ቤት ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ ጊዜ ለረዥም ሰዓታት ማንበብ እና ከሌሎች ነገሮች ጋር ለማዛመድ የቦታው ሁኔታ አላመቸኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ማይክሮ ፊልም ማኑስክሪፕትስ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውን የማይክሮ ፊልም ቅጅ ለማንበብም በወቅቱ የማተሚያ መሣሪያው በመበላሸቱ በመብራት ረዥም ሰዓት ማጥናት አልተቻለም ፡፡ በዚህ መካከል ግን ገድለ ዜና ማርቆስን ገዳሙ አሳተመው፡፡ በመሆኑም ተረጋግቶ ለማጥናት ዕድል ተገኘ፡፡
ገድለ ዜና ማርቆስ ከብዙዎቹ ገድሎች የሚለይባቸው ነጥቦችን በዝርዝር ማየቱ ገድሉ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በመረጃ እና በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ያለውን ቦታ ያመለ ክታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን ገድላት ያለ ጥልቅ ጥናት ከመተቸትና ታሪክ የማይሽረው ስሕተት ከመሥራትም ያድናል በማለት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡