Friday, April 24, 2015

እየተስተዋለ


እነዚህ ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸውን አንለውጥም ብለው የተሠዉ፡፡ ‹ስደተኛ ኢትዮጵያውያን› የሚለውን አገላለጽ ነፍሴ ትጸየፈዋለች፡፡ ከአኩሪው የሰማዕትነት ተግባራቸው በላይ ስደተኛነታቸው ለማጉላት ስለሚያኮበኩብ፡፡ ሰው በሀገሩ ቢኖር፣ ቢሠራና ቢከብር የመጀመሪያ ምርጫው ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን፡፡ ነገር ግን ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› ይባላልና የቸገረው ቢሰደድ ምን ይፈረድበታል? በርግጥ ስደቱ በሰላም፣ በሕግና በጤና ቢሆን የማይወድ የለም፡፡ ግን ሁል ጊዜ ይቻላል ወይ? ምቹ ሁኔታስ አለ ወይ? ዛሬ ከአውሮፓ፣ አሜሪካና አውስትራልያ፣ ከአፍሪካና እስያ ገንዘባቸውን እየላኩ አንዳንዴ ከቡና በላይ አንዳንዴም ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሬውን የሚያስገኙልን ወገኖች አብዛኞቹ ዛሬ ‹ሕገ ወጥ› በምንለው መልኩ የሄዱ አይደለም ወይ? እንዲያ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን መሠረታዊ ምክንያት መፍታት እንጂ የሆኑበትን መንገድ ማውገዝ ምን ይጠቅማል? 

የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን!
ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 10÷32
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ወጣቶች
ምእመናንና ምእመናት
ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡
በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኃይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳዶችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡
ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጉዘው በደማቸው ማሕተም ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡

Wednesday, April 22, 2015

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት የተሰጠ የሐዘን መግለጫ


ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ..

እስመ በእንቲኣሁ ይቀትሉነ ኲሎ አሚረ፡፡ ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ
ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን:: መዝ.4322

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ነው፡፡ ይህንንም ስንል ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ምንም በደል ሳይገኝበት በአይሁድ ተከስሶ በግፍ የሞት ፍርድም ተፈርዶበት በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ የሰው ልጆችን ዕዳ በደል ደምስሶ ነጻ እንዳወጣንና ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንዳደለን በማመን እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት በሰጠው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ትመራለች ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ይህንኑ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አምነው በሥራ ሲገልጡ ኑረዋል፤ ዛሬም በዚሁ እውነታ ይገኛሉ፡፡
ስለእውነት መሥዋዕትነት መክፈል ለቤተ ክርስቲያን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በየዘመናቱ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ያደላቸው ቅዱሳን ሰዎች የጌታን ፈለግ ተከትለው ስለክርስትናቸው ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በማመናቸውና ይህንንም በይፋ በመመስከራቸው ብቻ በክፉዎች ሰዎች እጅ በሥጋቸው መከራ እየደረሰባቸው ለሞት በመብቃታቸው ሰማዕት እየሆኑ አልፈዋል፡፡